ማዕዶት የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ በሃይማኖት እንዲጸኑ ወደ ጽድቅ እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3
ሰኞ 23 ሜይ 2016
ቅዳሜ 21 ሜይ 2016
ስብከት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
«ለጊዜው
ብቻ ያምናሉ» ሉቃ.8፥13
በክረምት
ወቅት ተነበው ስብከት ከሚሰበክባቸው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ መካከል አንዱ የዘሪው ምሳሌ ተብሎ የሚጠራው የምንባብ ክፍል
ነው፡፡ ይህን በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ማርቆስ፣ ቅዱስ ሉቃስ
ጽፈውታል፡፡
የምሳሌያዊ
ትምህርቱ ዋና መልዕክት አንድ ገበሬ በሚዘራበት ወቅት ዘሩ በተለያየ የማሳው ቦታ ላይ እንደሚወድቅ የወደቀበትም መሬት ሁኔታ
ለዘሩ መብቀል መጠውለግ ብሎም ፍሬማ መሆን ምክንያት መሆኑ ማስረዳት ነው፡፡ ከዚህም ምንባባት መካከል ቅዱስ ሉቃስ ከጻፈው ምንባብ
ወስጥ ገበሬው ከዘራው ዘር መካከል በዓለት ላይ እንደሌሎቹ ወንጌላውያን አባባል በጭንጫ መሬት ላይ የወደቀውን ዘር አበቃቀል
ከዚያም ፍሬ ሳይሰጥ መድረቁን እንመለከታልን፡፡
ይህን
በምሳሌ የተነገረው ቅዱሳን ሐዋርያት ትርጉሙን መረዳት ባለመቻላቸው ጌታቸውን መምህራቸውን ጠይቀውት ነበር፤ እርሱም ዘሩ
የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በዓለት ላይም የወደቀው ዘር ሥር ሳይሰድ ለጊዜው ብቻ ማደጉ እርጥበት ስላልነበረው ፥ፀሐይ በወጣ
ጊዜ ግን መጠውለጉን፥ በፍጥነትም መድረቁን ነግሯቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚዘራበት ልቦናቸው ዓለት ጭንጫ መሬት የሆነቦቸው
ሰዎች ቃሉን ሰምተው ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበሉ ለጊዜው ብቻ የሚያምኑ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው
የሚሰናከሉ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። ማቴ.13 ፥1 ማር 4፥1 ሉቃ.8 ፥13
«…እናንተ
ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን?» በማለት ነቢዩ አሞጽ የጭንጫ መሬት ለፈረስ
ግልቢያም ለእርሻም እንደማይሆን ይናገራል፡፡ አሞጽ 6፥12-13 የመሬቱም
ጠባይ ለፍሬው ዕድገት የሚረዳውን ውሃ የማይቋጥር ፣ሥሩ ቆንጥጦ የሚይዝበት አፈር የሌለው፤ በእርሱ ላይ የበቀለውም ለጊዜውም
ብቻ በቅሎ ነገርግን አቅም ስሌለው ፀሐይ መቋቋም ባለመቻሉ የሚደርቅ ነው፡፡ በጪንጫ መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በመብቀሉ
እና ቅጠል በማሳየቱ ብቻ በስተመጨረሻ ግን አብቦ አያፈራም፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትም የእግዚአብሔርን ቃል ለአንድ ሰሞን ይሁን
ለረጅም ዘመን የሰማ ብቻ መንፈሳዊ ፍሬ አያፈራም፡፡ በምግባር በሃይማኖት በመጽናት የፀሐዩን ሀሩር ለመቋቋም በጥልቅ መሠረት
ላይ መተከል አለበት አንጂ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም « ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን
እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን
ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ
ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።» ሉቃ.6 ፥ 47-49 ማቴ 7፥25
ጐርፍም
በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም የተባለው በትክክለኛ መንፈሳዊ መሠረት ላይ
የተመሰረተ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትም በምግባር በሃይማኖት ጥልቅ መሠረት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ሊያጠፋው
የሚመጣበተን ፈተና በሙሉ የመቋቋም ኃይል አለው፡፡ በጭንጫ መሬት ላይ እንደበቀለችው ቅጠል ለጊዜው አምሮ ተውቦ የፀሐዩን ንዳድ
ትኩሳት ማለትም ፈተናንን ማለፍ ሳይችል ቀርቶ አይወድቅም፡፡ ሐዋርያው ጳዉሎስም በመልእክቱ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ
ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 ያለው መልዕክት ይህን ይበልጥ
ያስረዳልናል፡፡
የነቢያት
መሠረት እና የሐዋርያት መሠረት የእውነት እና የጽድቅ ነበር፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ብዙ መከራን በአሕዛብ ፊት
ከምስክርነታቸው የተነሳ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እና ነቢያት በመልካም መሬት ላይ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት
መሥርተው ነበር፡፡ በዘመኑ የገነነው ንጉሥ ነቢያትን እንደሰም ሳያቀልጣቸው፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን የሮም ፀሐይ ሳያጠወልጋቸው፤
ቤታቸውን ሊያፈርስ የመጣው ጎርፍ ከሃይማኖት ሳያናውጣቸው ቀርቷል፤ አንገታቸው እኪቀላ ድረስ፣ ቆዳቸው እኪገፈፍ ሰማዕትነትን
ተቀብለው በሃይማኖት ቆሙ፡፡ ደስ እያላቸውም በብዙ ድካም እና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ልንገባ ይገባናል በማለት በምግባር
ፀኑ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ
ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ” ኤፌሶን 3፥16-17 እንዳለ
የቤታቸው የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማድረግ በልባቸው አኖሩት ሥር መሠረታቸውም
ለዓለም ሁሉ ቤዛ ለመሆን በቀራንዮ አደባባይ በተሰቀለው በመድኃኒታችን ፍቅር ሆነ ፡፡
በጪንጫ
መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በቅሎ ነበር ሥሩን ወደ ወንዝ ዳር ሳይሰድ በመቅረቱ በድርቅ ዘመን ፀሐዩ ሲበረታ ፍሬውን
አቋረጠ ደረቀ፡፡ ነቢዩ ኤርምያስንም ይህን በማስመልከት የጻፋ ምንኛ ድንቅ ይሆን እንዲህም ይለናል “በእግዚአብሔር የታመነ
እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ
እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።” ኤርም 17፥8
ፍሬው
የማያቋርጠው ዛፍ ዕምነቱ በእግዚአብሔር ላይ ነው፤የሚመጣውንም ፈተና እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ድል ያደርጋል፡፡ ሥሮቹን
ዘርግቶ ሕይወት የሆነውን ውኃ እንደሚጠጣ ተክል ከሕይወት ውኃ ከእግዚአብሔር ቃል ይጠጣል እና በድርቅ ዓመት በክፉ ዘመን
አይሰጋም አይደናገጥም ለጌዜው ሳይሆን እስከመጨረሻው ያምናል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ሳያቋርጡ የምግባር የሃይማኖት ፍሬ መስጠት የሚቻለው
በውኃ ዳር በተመሰለች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተተክሎ ሥርን ዘረግቶ ከትምህርቷ ሲቀዱ ብቻ ነው፡፡ የነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት
መዝሙር ይህን ያስታውሰናል “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር
ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ
ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” መዝሙረ ዳዊት
1
በጪንጫ
መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በጣም በፍጥነት ነበር የበቀለው፡፡ ይህም ገበሬው የድካሙን ፍሬ እንዲያይ በቅጠሉ ማማር እና
መስፋትት እዲደሰት ለፍሬውም ተስፋ አንዲያደርግ አድረጎት ነበር፡፡ ይህም ፈጥና ጥላ ሆና ከአፍታ ቆይታ በኋላ የረገፈችውን የነቢዩን
ዮናስ የቅል ዛፍ ታስታውሰናለች፡፡ “ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ ከተማይቱንም
የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥ ከጭንቀቱም
ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።በነጋው ግን
ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት። ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር
ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ።
እግዚአብሔርም ዮናስን፦ በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም፦ እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል
አለ።እግዚአብሔርም፦ አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው
ቅል አዝነሃል።እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ
ለነነዌ አላዝንምን? አለው።” ትንቢተ ዮናስ 4፥3-11
በአንድ
ለሌት የበቀለች በአንድ ለሌት የደረቀችው የቅል ቅጠል ነቢዩ ዩናስ ለረጅም ጊዜ ጥላ ትሆነኛል ብሎ ተስፋ አድረጎ
ነበር፡፡ይልቁኑ ትበቅል ዘንድ ላልደከመባት እና ላላሳደጋት ቅል እንዲ ማዘኑ ያስገርማል፡፡ እግዚአብሔር ለተከላቸው እና
ላበቀላቸው በሕይወት እንዲኖሩም ተስፋ ያደረገበቸው መቶ ሃያ ሺህ የነነዌ ሰዎች በፍጥነት ወደ ጥፋት መግባት ምንኛ ያሳዝን፡፡ በስተመጨረሻም
ነቢዩ ዮናስ የሰዎቹ መጥፋት ገዶት በከተማዋ ተዘዋውሮ የአዋጅ ነጋሪ ሆኖ ጾም ጸሎትን ሰበካቸው፡፡ ግራና ቀኝ የማታውቀው ከተማ
በነቢዩ ዮናስ አዋጅ ከመጣባት እሳት በንስሐ እና በዕንባ መለምለም ችላ ፍሬዋን አፍራች፡፡
ዛሬም
በአንድ ለሌት መንፈሳዊያን በአንድ ለሌት ደግሞ ጭልጥ ያለ አረመኔ የሚሆኑ ሰዎቸን እግዚአብሔር ከሚመጣው ቁጣ ይድኑ ዘንድ ምን
ያህል ያዝንላቸው ይሆን? ግራና ቀኙን የማያውቀው የእግዚአብሔር ተክል የሆነው ምዕመን በታላላቆቹ ከተሞች ተሰግስጎ ተቀምጧል፤ እንደ
ነቢዩ ዮናስ ስለራሱ መጠለያ፣ ጥላ፣ ፈረጅያ ሳይጨነቅ በየገጠሩ በየስርጡ እየዞረ የንሥሐን ፍሬ ያፈሩ ዘንድ የአዋጅ ነጋሪ ቃል
የሚነግራቸው ማን ይሆን? ራሱ ከሚያገኘው ድቃቂ ሳንቲም አስበልጦ በነፍሳቸው ስለሚጠፉ ምእመናን የሚጨነቅ አገልጋይ ማን ይሆን?
እሳት የተቃጣበት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር በታላላቅ ከተሞች ያለ የማያፈራ ምዕመን ፉቱን ወደ ንሥሐ ይመልስ ዘንድ የማንቂያውን
ደውን የሚያስጮህ ፍሬአማ ጽኑ አገልጋይ ለ ቤተ ክርስቲያን ይፈልጋታል፡፡
የፀሐይ
ከትኵሳት ቅጠልን ሣርንም እንዲያጠወልግ፥ አበባውንም እንደሚያረግፍና፥ የመልኩም ውበት እንደሚያጠፋ ፤በጪንጫ መሬት ላይ የተዘራ
ዘር ከበቀለ አና ቅጠል ካወጣ በኋላ ከሌሎች ተክሎች ተለይቶ ፀሐዩን መቋቋም ያቅተዋል፡፡ ፀሐይ ለሁሉም ሳታዳላ እንደምትወጣ
ማንኛውም ክርስቲያናዊ ሕይወት ፀሐይ የተባለ ፈተና ያጋጥመዋል፡፡ ይህንንም በጽናት ተቋቁሞ ማሳለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም
ሲመክር ፈተና ለክርስቲያኖች የማይቀር ነውና በመጣባችሁ ጊዜ ጠውልጋችሁ አትዘኑ በደስታ ተቀብላችሁ ተቋቁማችሁት እለፉት ይለናል
“ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ
ቍጠሩት ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ
ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን
የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ
ማንንም አይፈትንም።ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤
ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” ያዕቆ 1፥1- 14፣ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፥6-7
ክርስቲያናዊ
ሕይወት እንደወርቅ በእሳት ተፈትኖ ማለፍ መሆኑ ያልተረዱ ሰዎች ይክዳሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው ሥር ሰደው ያልታነጹ
ሃይማኖታቸውን በሚገባ ያልተረዱ መሆናቸው ነው፡፡ ሐዋርያው
ጳውሎስም ቆላስይስ ሰዎች የመከራቸው እንዲህ በማለት ነበር “ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥
ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ
በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” ብሎአል፡፡ ቆላ 2፥7፣ ሮሜ ሰዎች 11፥15-17 ሮሜ 15፥14
ብዙ ተደክሞበት ሳለ ነገርግን መሠረቱን ጥልቅ ያላደረገ በሃይማኖት
ያልታነጸ ምዕመን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም ይታለላል እንደዚ ያሉትን ሰዎች ነቢዩ በግሩም
ቃል እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል “ተክለሃቸዋል ሥር ሰድደዋል፤አድገዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው
ግን ሩቅ ነህ።» ትንቢተ ኤርም 12፥1-2 ነቢዩ ኤርምያስ እንዳለው የማያቋርጥ ፍሬ የሌላቸው ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት
በጽኑ መሠረት የታነጸ ሳይሆን በአንደበታቸው ብቻ ቃሉን የሚናገሩ ቅንጣት ታክል እንኳን መልካም ሥራ የሌላቸው የአምልኮ መልክ
ብቻ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን የመጨረሻው ዘመን ሰዎቸን ምን አይነት ጠባይ እንዳላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ
በላከው መልእክቱ ላይ ይገልጸዋል “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ
ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥
ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥
በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ
ደግሞ ራቅ።” 2ኛ
ወደ ጢሞቴዎስ
3፥1-3
ከእግዚአብሔር
ይልቅ ተድላን የሚወዱ ሰዎች ችኩሎች ስሆኑ ለጊዜው ብቻ ያምናሉ መልካም የሆነውንም የማይወዱ ጨካኞችም በመሆናቸው አያመሰግኑም
ቅድስናም የላቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል ስለሚክዱ በሃይማኖት በምግባር አይጸኑም፡፡ ሃይማኖተኝነት በጊዜ ገደብ የሚወሰን
ሲያመቸን የምናጠብቀው ሌላ ጊዜ ደግሞ የምንተወው አይደለም ዋጋ መንግሥተ ሰማያት የሚሰጠው ጀምረን ባቋረጥነው ሳይሆን
እስከመጨረሻው ህቅታ ድረስ በፈጸም ነው ፡፡ ይህን በማስመልከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈው መልእክት
ምንኛ አስተማሪ ነው «የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤» ዕብ.3፥14 የክርስቶስ መንግስት ተካፋይ
ለመሆን መጽናት ያሻል ቅዱስ ጳውሎስ ተማሪውን ጢሞቴዎስን በማስተማሩ ተግባሩ እንዲጸና ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥
ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፥2 ብሎታል፡፡
ጊዚያዊ ክርስትና ጊዜያዊ ዕምነት የለም “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” ማቴ 10፥22
ናዝሬት ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተሰበከ
አንድ ፍቅር አንድ ልብ
ሰዎች እግዚአብሔርን የሚያመልኩት የሚወዱት ባልተከፋፈለ በአንድ ልብ ነው፡፡ እስራኤላውያን
የጸና እና የተረጋጋ ልብ ስላልነበራቸው ወላዋዮች በአምልኮተ እግዚአብሔር የማይጸኑ ነበሩ ፡፡ ይህን የተረዳው እግዚአብሔር በመሪያቸው በሙሴ አማካኝነት አምላካቸውን በአንደበታቸው ሳይሆን በአንድ ልብ፤ በአንድ ሀሳብ እንዲወዱ እና እንዲያመልኩት አዘዛቸው፡፡ “እስራኤል ሆይ፥ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው ፡፡ አንተም አምላክህን
እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ።” ዘዳ 6፥5
“በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ
እግዚአብሔርን ውደድ ” የሚለው ቃል፤ እግዚአብሔርን ለመውደድ ፍፁም ልብ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡ ሀሳብ
እና ፍቅር መኖሪያቸው ልብ ነው፡፡ ፍጹም ልብ ወደ አንድ ሀሳብ ሲመራ፤ አንድ ሀሳብ ደግሞ ወደ ፍጹም ነፍስ እና ኃይል ያደርሳል፡፡ ስሊህም በልባችን እግዚአብሐርን እንወዳለን፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ በልባችን በአንድ ሀሳብ እግዚአብሔርን በምንወድበት ጊዜ ባልንጀራችንንም እንደምንወድ አስተምሮናል፤
እንዲህ በማለት “ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም
ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ
የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”
እነዚህ ሁለት ትእዛዛት ማለትም እግዚአብሔርን መውድ እና ባልንጀራን መውደድ በአንዱ ልባችን
ውስጥ በአንድ ሀሳብ በፍቅር ይጠቃለላሉ፡፡ ሁለተኛይቱ ትእዛዝ የታላቁ ትእዛዝ አካል በመሆኗ የማይነጣጠሉ ፍቅርን መሰረት ያደረጉ
አንድ ሀሳብ ናቸው፡፡ ፊተኛይቱ ታላቁ ትእዛዝ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መውደድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ፍቅር የለም ቢኖር
እንኳን ኃጢአት ነው፡፡ ስለዚህም ታላቂቱ እና ፈተኛይቱ የተባለችው ከእርሷ የሚያንሱ እንጂ የሚበልጡ ስለሌሉ ነው፡፡ እንዲሁም ከእርሷ
የሚከተሉ እንጂ የሚቀድሙ ባለመኖራቸው እግዚአብሔርን ከመውደድ የሚበልጥ የሚቀድም ነገር ምንም አይኖርም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ሁለት አይነት ሰዎች እውነተኛውን ምላሽ እንዲሰጡ በጥብቅ
አሳስበን የሚከተለውን ጥያቄ እናቅረብላቸው፡፡ በስዕለት ወንድ ልጅ ለወለደችው እናት እንዲህ እንበላት “እውነቱን ተናገሪ ከልጅሽ
እና ከእግዚአብሔር ማንን ትወጃለሽ?” ብለን ብንጠይቃት፡፡ እንደዚሁም ለማግባት ጥቂት ቀናት የቀረውን ሙሽራ “በጣም ከምትወዳት
ከእጮኛህ እና ከእግዚአብሔር ማንን ትወዳለህ ? ” ተብሎ ጥያቄ ቢቀርብለት ምን አይነት ፈታኝ እና ከባድ ጥያቄ ቀረበልን ካሉ በኋላ
መልሳቸው እንደዚህ ይሆናል፡፡ ወንድ ልጅ በስዕለት ያገኘችው እናት መልሷ “ ልጄን ነው የምወደው ” ከሆነ፡፡ እንደዚሁም “ጎልማሳ
በሚስቱ እንዲሉ” የሙሽራውም መልስ “እጮኛዬን” ከሆነ ፤ ከሰጪው ከእግዚአብሔር ይልቅ ስጦታውን አብልጠው ወደዋል እና ኃጢአት ይሆንባቸዋል፤
ምክንያቱም የፊተኛይቱን ትእዛዝ የሆነችው እግዚአብሔርን መውደድ ከማንኛውም እና ከምንም አስቀድሞ ፣ አስበልጦም ጭምር በፍጹም ልብ
እግዚአብሔርን መውድ ስለሆነ ፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ከእግዚአብሔር አስበልጠን የምንወደው
እንደሌለን ሲያስተምረን “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ
ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤” ብሎአል፡፡ማርቆስ 10፥37
ነገር ግን እግዚአብሔር ለእርሱ ካለን ፍቅር ይልቅ ሌሎችን ካስበለጥን
ልባችን ወደ እርሱ እስኪመለስ ድረስ ይተወናል እንጂ ፈጽሞ አይጠላንም፡፡ ይህንንም አስደናቂ የእግዚአብሔር ፍቅር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ
ዘጋሥጫ እንዲህ በማለት ገልጾታል “እግዚአብሔር ከሚወደው ሰው ይልቅ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ያስደንቀኛል” ብሎአል፡፡ ምክንያቱም
የእግዚአብሔር ፍቅር ከባሕሪው የሚገኝ ነውና፡፡
ፈተኛይቱ ትእዛዝ በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን መውድ ነው፡፡ ሀሳባችንን ለማንም ሳናስቀድም
ለእግዚአብሔር ብቻ መስጠት ነው፡፡ ራስ ካሳ ፍኖተ አእምሮ በተሰኘው መጽሐፋቸው “እግዚአብሔርን መውደድ ማለት የምትወደውን ነገር
ማናቸውንም ነገር ቢሆን ለእኔ ይቅርብኝ፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሁንልኝ ብለህ፤ ቢቻልህ ጨርሰህ፤ ባይቻልህ ከፍለህ የምትወደውን
መስጠት ነው” ብለዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን መውደዳችን የሚታወቀው በአንደበታችን በምናደርገው ንግግር ሳይሆን በሙሉ ልብ ለእግዚአብሔር
በመታዘዛችን እና ስለእርሱ ፍቅርም በምንከፍለው መሥዋዕትነት ነው፡፡
“ አንድ ሀሳብ ይሁንላችሁ፤”
የሚለው ቃል እግዚአብሔር በአንድ ሀሳብ በፍጹም ኃይል ልንወደው እንደሚገባ
ያስረዳል፡፡ በተረት “አንዱን ይዞ ፤አዱን አንጠልጥሎ” እንዲሉ በአንድ ልብ ሁለት ሀሳብ፤ ሁለት ፍቅር አይቻልም፡፡
አባቶቻችንም “ሁለት ልብ ያለው ሁሌም የታወከ ነው ” እንደ ሚሉት በሁለት ሀሳብ ሲዋልል ይኖራል፡፡ ቅዱስ ወንጌልም ይህንን
ሲያረጋግጥልን “ለሁለት
ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም
ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ” ማቴ 6•24 የሚለን፡፡ ስለዚህ
ዓለምንም እግዚአብሔርንም እንደ አስፈላጊነቱ እየለዋወጡ መውደድ አይቻልም፤ ምክንያቱም ፍቅር በአንድ ልብ
ነውና፡፡
የተከፋፈለ ልብ ፈጽሞ አንድ ፍቅር የለውም፡፡እንዲህ አይነት ልብም ይዘን እግዚአብሔርን
እንወዳለን እናመልካለን ብለን መናገራችን እንኳን ድፍረት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የሚወደው እና የሚፈልገው በአንዳች ነገር
ያልተከፋፈለ አንድ የፍቅር ልብ ነው፡፡ ሰውም ቢሆን ፣ ገንዘቡም ቢሆን በዓለሙ ውስጥ ያለው ወርቁም ብሩም ቢሆን በፍጹም ፍቅር
ልንወደው አይገባንም፡፡ እግዚአብሔርን የምናመልክበትን እና የምንወድበትን ልባችንን ሊቆጣጠረውም ወይም አብላጫውን ቦታ ከፍለን ልንሰጠው
አይገባም፡፡ ይህን ያደረግን እንደሆነ ለእግዚአብሔር መገዛት አንችልም ፡፡ በዚህም የተነሳ የፊተኛይቱን ትዕዛዝ እንሽራለን፡፡ የመጀመሪያይቱን ትእዛዝ በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን መውደድ ዘላለማዊ ሲሆን የተቀረው ፍቅር ግን ጊዜያዊ ነው፡፡ዛሬ
በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ትልቁ ደዌያችን የተከፋፈለ ፍቅር ነው፡፡ ለእግዚአብሔር በልባችን ያለው ሥፍራ እጅግ ጠቦ በጊዜያዊው
ዓለም ሀሳብ ተጣቧል፡፡እግዚአብሔርንም ዓለምንም መውደድ እንፈልጋለን፤ ስለ እግዚአብሔርም ስለ ዓለምም እናስባለን፡፡
በፍጹም ልባችን እግዚአብሔርን ያመለክን እንደሆነ ሌሌች ሰዎችን እንዴት መውደድ እንችላለን
ለሚለው ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፡፡ ሌሎቹን ሁሉ የምንወደው በእግዚአብሔር ፍቅር መሰረትነት ነው፡፡ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።
በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” እንደተባለ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል “ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ
እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”
1ኛ ዮሐ 4፥8 እንደዚሁም በሌላ መልእክቱ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ
ይኖራል።”1ኛ ዮሐ 4፥16 በማለት ያስተምራል፡፡
ፍቅር ሁለት ልቦችን አንድ ሀሳብ ማድረግ ነው፡፡ ወይም ሁለት ልቦችን በተመሳሳይ ስሜት እና
ፍላጎት ሀሳብ ማስተሳሰር ነው፡፡ ይህም የተቀደሰ ፍቅር ይሆናል፡፡ ስሜቱም በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የተመሰረተ ከሆነ ከእርሱ
ጋር የማይጋጭ የማይበልጥ መንፈሳዊ ፍቅር ነው፡፡ባልንጀራችንንም ስንወድ በዚህ መርህ መሰረት ነው፡፡
ፍቅር ሳይኖረን ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ብንፈጽም ከንቱ ድካም ይሆንብናል ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም “ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ
ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም”። 1ኛ ቆሮ
13፥ በማለት ተናግሮአል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ፣ ኑሮአችንን አገልግሎታችንን ሁሉ በአንድ ፍቅር ፣ በአንድም ልብ፣ በአንድም አሳብ እናድርግ፡፡ በዚህ እግዚአብሔርን መውደዳችን ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔርም
ከእኛጋር ይሆናል፡፡
ይቆየን
ያዕቆብ ሰንደቁ
ግንቦት 13 2008
አዲስ አበባ
ቅዳሜ 7 ሜይ 2016
ስብከት
በመጣህበት መንገድ አትመለስ
1ኛ ነገሥት. 13፥1
በንጉሥ ኢዮርብዓምም ዘመን
እንዲህ ሆነ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ
ቤቴል መጣ፡፡ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገረ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ
የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት
ያቃጥልብሃል” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። በዚያም ቀን፦ እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው እነሆ፥ መሠዊያው
ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
ንጉሡም ኢዮርብዓም
የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ“ያዙት” አለ። በእርሱም
ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው
ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው።“
አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው
እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች። ንጉሡም “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም
ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ አለ “የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር
አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፡፡ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ
በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና ” አለው። ከዚያም ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ ሳይመለስ በሌላም መንገድ ሄደ።
በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፡፡
ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ እና የንጉሡ እጅ ደርቃ ጸልዮ እንደፈወሰው
ነገሩት፡፡ ሽማግሌው ነቢይ የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ ጠይቆ አህያውን ጭኖ ተጎዘ፡፡ ባየውም ጊዜ “ከይሁዳ የመጣኸው
የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህ ? ”ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም “አዋ እኔ ነኝ” አለው፡፡ ሽማግሌው ነቢይ “ከእኔ ጋር ሄደህ
እንጀራ እንብላ ”አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም “በመጣህበት መንገድ አትመለስ፤ ከማንም ጋር እንጀራ አትብላ፣ ውኃ አትጠጣ
ተብዬ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዝዤአለሁ” አለው፡፡
ሽማግሌው ነቢይ የሐሰት ቃል
ፈጥሮ “እኔም እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ የእግዚአብሔር መልአክ
ተገልጦ እንጀራ እንዲበላ ወደ ቤትህ ጋብዘው ብሎኛል” አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም የሽማግሌውን ነቢይ የሐሰት ቃል አምኖ በመጣበት
መንገድ ተመልሶ ወደ ቤተልሔምም መጣ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በላ ውኃ ጠጣ፡፡ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ በሽማግሌው ነቢይ
የእግዚአብሔር መልእክት ተገለጠለት፡፡ ከይሁዳም ለመጣም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው ተባለ፡፡
እንዲህም አለው “በእግዚአብሔር አፍ ላይ አምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ተመልሰህም እንጀራ
አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም” ተብለሀል
አለው፡፡
የእግዚአብሔር ሰውም አህያውን ጭኖ ከሽማግሌው ነቢይ ቤት ወጥቶ በመጣበት
መንገድ ተመለሰ፡፡ በመንገድም አንበሳ አግኝቶት ሰብሮ ገደለው፡፡ ሬሳውም መንገድ ላይ ተጋድሞ ነበረ፡፡ አንበሳውም አህያውንም ሳይነካው በአጠገቡ ዝም ብሎ ቆመ፡፡ ነገሩን የተመለከቱ ሰዎች ሽማግሌው ነቢይ
ባለበት ከተማ ሲያወሩ ተሰማ፡፡ ያም ከመንገድ የመለሰው ሽማግሌ ነቢይ ወሬውን በሰማ ጊዜ “በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመጸ የእግዚአብሔር
ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደተናገረው ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰቡሮም ገድሎታል”አለ፡፡ ልጆቹንም አህያ ጫኑልኝ ብሎ ወደ
ስፍራው ሄደ፡፡
በደረሰም ጊዜ ሬሳው ወድቆ አንበሳው አጠገቡ ቆሞ አህያውንም ሳይሰብረው
ተመለከተ፡፡ ሬሳውንም በአህያ ጭኖ ያለቅስለት እና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞ መጣ፡፡ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው
ዋይ ዋይ ወንድሜ ብሎ አለቀሰለት፡፡ ለልጆቹም እንዲህ አላቸው በሞትኩኝ ጊዜ እርሱ መቃብር አጠገብ ቅበሩኝ፤ አጥንቶቹም ከእርሱ
አጥንቶች ጋር አንድ ይሁኑ፡፡ በሰማርያ ከተሞች ውስጥ በቤተልሄም መሰዊያ ላይ የተናገረው ነገር በእዉነት ተፈጽሞአልና፡፡
ንጉሥ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ ሳይመለስ ቀረ በኮረብታዎቹ ላይ መስገጆዎችን
ሠራ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ለእርሱ ቤት ኃጢአት ሆነ፡፡
የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሥ ፊት ባደረገው ተአምራት የተነሳ
ልሸልምህ፣ በቤተ መንግስት ልጋብዝህ ብሎ ንጉሡ ሲጠይቀው፤ በመጣህበት መንገድ አትመለስ፣ አትብላ፣ አትጠጣ ተብያለሁ ብሎ እጅ
መንሻውን ባለመቀበል የመጀመሪያው ፈተና ድል አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ፈተና ደግሞ በዕድሜ አረጋዊ ከሆነ ከእውነተኛ ነቢይ ቀረበለት፡፡
በውሸት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦልኛል በመጣህበት መንገድ ተመለስ እንጀራ ብላ ውኃ ጠጣ ተብለሀል በማለት፤ እግዚአብሔር ካዘዘው
ትእዛዝ ጋር የሚቃረን ትእዛዝ አስተላለፈለት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሰው ነቢይ መሆኑን እና ሽምግልናውን ከግምት በማስገባት ነገሩን
በደንብ ሳይመረምር፤ ቀድሞ ለምን ታዘዝኩኝ ? አሁን ደግሞ ለምን? እንዴት ተቀየረ ? ብሎ ሳያስተውል፤ የሐሰት ቃል በመስማት የእግዚአብሔርን
ቃል ተላለፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ሰው መሳሳት ዋና
ምክንያት እግዚአብሔር ካዘዘው ትእዛዝ የበለጠ ሽማግሌዉ ነቢይ የነገረውን ቃል ሳይመረምር አምኖ መቀበሉ ነው፡፡ የማንኛውንም መንፈሳዊ
ሕይወት ጉዞ መመዘኛችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል፣ያዘዘው ትእዛዝ አይለውጥም ማሻሻያም አያደርግለትም፡፡ በኦሪትም ለቤተ እስራኤል እንዲህ ብሎአቸው ነበር
“ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም።” ኦሪት
ዘኍ.23፥19 በነቢዩም በእንባቆም ትንቢት “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም
በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱ አይዘገይም። ዕንባ. 2፥3 ብሎአል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ”ብሎአል፡፡ ማቴ 24፥ 35፣ ማር ፥31፣ ሉቃ 21፥ 33፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከሚሻር
የሰማይ እና ምድር ማለፍ እንደሚቀል ተናግሮአል፡፡
ይህ የእግዚአብሔር ሰው በመጣበት መንገድ ወደ ኋላ የተመለሰው፤ ከእውነተኛው
ነቢይ የሐሰት ቃል በመስማቱ እና ሳያስተውል ፣ ሳይመረምር አሜን ብሎ በመቀበሉ ነው፡፡ ሐሰተኞች ነቢያት እና መምህራን እውነተኞች
ነን ብለው የሚመጡበት ጊዜ አለ፡፡ይህ የተለመደ እና በስፋት የትንቢት ማስጠንቀቂያ የተነገረለት ነው፡፡ የረቀቀ እና የሚከፋው ግን
ቀድሞ በእውነተኛነታቸው በጣም ታዋቂ በሆኑት ነቢያት፣ መምህራን የሐሰት የትንቢት ቃል በሚናገሩበት ወቅት ነው ፡፡ እንዲህ አይነቱን
ከባድ ፈተና ማለፍ የሚቻለው የተነገረው ቃል፤ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና አለመሆኑን በመመርመር፤ እንዲሁም የነገሩን ትክክለኛነት
በቅዱሳት መጻሕፍት ጋር መስማማቱን በመመዘን ነው፡፡
ዲያብሎስ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ትእዛዝ እና መንገድ ለማሳሳት፤ ልዩ
ልዩ አይነት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡በዚህም የረጅም ጊዜ ልምድ እና ክህሎት አለው፡፡ ዲያብሎስ መንፈሳዊያን እና ዓለማውያን ሰዎችን
ለማሳት የሚጠቀምበት ስልት የተለያየ ነው፡፡የመንፈሳዊያን መንገድ ለማስቀየር እና ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጭ ለማድረግ ሲፈልግ በመንፈሳዊያን
ሰዎች አድሮ፤ መንፈሳዊ የሚመስል ሐሰት ይዞ ይቀርባል፡፡ ይህን የዲያብሎስ ውጊያ ድል ለማድረግ ጥልቅ ማስተዋልን ይፈልጋል፡፡ ለዚህም
ነው መጽሐፍ ቅዱስ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም
ይጋርድሃል፥”ምሳ.2፥11 የሚለን ፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት
ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ምሳ. 9፥6 የሚለን፡፡ ማስተዋልን የምናገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን
“በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።” ኢዮብ. 12፥13
ይለናል፡፡ እንዲሁም “በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን
የሰጠ ማን ነው?”ይላል፡፡ ኢዮብ. 38፥36
፡፡ በቅዱስ ወንጌልም “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል
የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥” በማለት ተጽፎአል ፡፡ ማቴ 24፥15 ፡፡ስለዚህ
ከእግዚአብሔር ዘንድ በምናገኘው ማስተዋል ተመርተን በሃይማኖት መንገድ በምግባር፣ በቱሩፋት መጽናት እንችላለን፡፡
በሃይማኖት መንገድ ለመጽናት ወደ
ኋላ ላለመመለስ፤ ከማስተዋል በተጨማሪ መንፈስን ሁሉ በጥርጣሬ መመርመር አለብን፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት
ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ብዙዎች
ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” በማለት ይመክረናል፡፡ 1ኛ ዮሐ. 4፥1 ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ስለመጡ
ነቢይ ነኝ፣ ራይዕ ተገልጦልኛል፣ የፈውስ ሀብት ተሰጥቶኛል፣ አጠምቃለሁ፣ለማናቸውም ችግር በፍትሄ እሰጣለሁ፣ድንቅ ተአምራት
አደርጋለሁ ወዘተ … ያለውን ሁሉ በስሜት ማመን እና መከተል
የለብንም፡፡ በበቂ ሁኔታ ሳንመረምር ስለ እውነተኛነታቸው ለሌሎች ልንመሰክርም አይገባም፡፡ መገኛቸው መንደር ቢሆንም ፤ በተቀደሰው
ስፍራ ቢቆሙም፤ ቀደም ብለው እውነተኛ አገልጋዮች ቢሆኑም እንኳን፤ ሳንመረምር ልናምንባቸው አይገባንም፡፡ ጊዜ የሚገልጠው
የተደበቀ የጥፋት የእርኩሰትን፣ ገንዘብ መውደድን እና ዝሙትን ፤ ቀድሞ ወደ መጣንበት ኃጢአት መንገድ የሚመልሱ ተግባሮችን ሁሉ
ሊፈጽሙ እና ሊያስፈጽሙን ይችላሉና፤ ከሐሰተኛ ትምህርታቸው ልንጠበቅ ይገባል፡፡
በቅዱስ ወንጌል “ብዙ ሐሰተኞች
ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤” ማቴ.24፥11 እንደተባለ በሐሰተኞች ተአምራት ምልክት ተሳስተን የያዝነውን የሃይማኖት
መንገድ እንዳንቀይር፡፡በመጨረሻው ዘመን መዳረሻም ከሚመጡት ፈተናዎች መካከል በእውነተኛ ቦታ እና ከእውነተኛ ሰዎችን የዲያብሎስ
መጠቀሚያ በማድረግ የጥንቆላ ትንቢትን ማናገር ነው፡፡ በዚህም የብዙዎችን ተቀባይነት አግኝተው፤ ብዙዎችን ከያዙት የጽድቅ
መንገድ አስተው ወደ ሌላ የስህተት መንገድ ይመራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ
የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” 1ኛ ቆሮ.11፥14 በማለት ሰይጣን በለወጣቸው ሰዎች ስብከት፣ ተአምራት፣
ልዩ ልዩ ምልክት እንዳንስት የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እንዳንጥስ ያስጠነቅቀናል፡፡
በእግዚአብሔር
ትዕዛዝ ላይ አምፆ ወደ ኋላ በመመለሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ሰው በአንበሳ ተሰብሮ ሞተ፡፡ በሃይማኖት ጉዞ ጀምሮ ማቋረጥም
ሆነ ወደ ኋላ መመልከት አይቻልም፡፡ በቅዱስ ወንጌልም “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ
አይደለም… ።” ተብሎአል፡፡ ሉቃ.9፥62 መንገዱን ጀምረው ጉዞቸውን ያቋረጡት ሳይሆኑ እስከ መጨረሻው የሚጸኑት ናቸው
ለሰማያዊው መንግስት የሚገቡት ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ጀምረው የሚያቋርጡትን ሰዎች ሲገልጣቸው “አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት
ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ
ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል። ” 2ኛ የጴጥ.2፥21 ብሎአል፡፡
የጽድቅን መንገድ ጀምረው የሚያቋርጡ ሰዎች የሚውጠውን ፈልጎ አድብቶ ለሚጠባበቃቸው ዲያብሎስ ትልቅ ደስታ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት
ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” 1ኛ የጴጥ. 5፥8 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከተሰጠን የቅድስና መንገድ
ጀምረን ከማቋረጥ የጽድቅን መንገድ አለማወቅ ይቀላል፡፡ ዛሬ በዚህ የስልጣኔ ማማ ላይ በደረሰው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች፤ የጽድቅን
መንገድ ጀምሮ ማቋረጥን ሰማያዊ ፍርድ የሚያሰጥ ሳይመስላቸው እንደ ዋዛ ቀለል አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ብዙዎች የጽድቅን መንገድ
ጀመሩ አንበሳ በተባለው ዲያብሎስ ተሰብረው ከመሀል አቋረጡ፤ የተክሊል ጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ሽረው ተፋቱ ፣ ቆርበው አፈረሱ፤ ንሥሐ
ገብተው ረከሱ፣ ዘምረው ዘፈኑ፣ ቀስሰው አፈረሱ፣ መንኩሰው ቆብ ጣሉ፡፡
በጀመርነው የጽድቅ መንገድ እስከ መጨረሻው እንድንጓዝ የዲያብሎስን ፈተና በእምነት ጸንተን
እንድንቃወም
የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጀነት አይለየን አሜን፡፡
ያዕቆብ ሰንደቁ
ቅዳሜ ሚያዚያ 29 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
ልጥፎች (Atom)