ቅዳሜ 7 ሜይ 2016

ስብከት

በመጣህበት መንገድ አትመለስ    1ኛ ነገሥት. 13፥1
በንጉሥ ኢዮርብዓምም ዘመን እንዲህ ሆነ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፡፡ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገረ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። በዚያም ቀን፦ እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
ንጉሡም ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ“ያዙት” አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው።“ አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች። ንጉሡም “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ አለ “የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፡፡ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና ” አለው። ከዚያም ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ ሳይመለስ በሌላም መንገድ ሄደ።
በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፡፡ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ እና የንጉሡ እጅ ደርቃ ጸልዮ እንደፈወሰው ነገሩት፡፡ ሽማግሌው ነቢይ የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ ጠይቆ አህያውን ጭኖ ተጎዘ፡፡ ባየውም ጊዜ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህ ? ”ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም “አዋ እኔ ነኝ” አለው፡፡ ሽማግሌው ነቢይ “ከእኔ ጋር ሄደህ እንጀራ እንብላ ”አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም “በመጣህበት መንገድ አትመለስ፤ ከማንም ጋር እንጀራ አትብላ፣ ውኃ አትጠጣ ተብዬ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዝዤአለሁ” አለው፡፡
ሽማግሌው ነቢይ የሐሰት ቃል ፈጥሮ “እኔም እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤  የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንጀራ እንዲበላ ወደ ቤትህ ጋብዘው ብሎኛል” አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም የሽማግሌውን ነቢይ የሐሰት ቃል አምኖ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ወደ ቤተልሔምም መጣ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በላ ውኃ ጠጣ፡፡ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ በሽማግሌው ነቢይ የእግዚአብሔር መልእክት ተገለጠለት፡፡ ከይሁዳም ለመጣም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው ተባለ፡፡ እንዲህም አለው “በእግዚአብሔር አፍ ላይ አምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ተመልሰህም እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም” ተብለሀል አለው፡፡
የእግዚአብሔር ሰውም አህያውን ጭኖ ከሽማግሌው ነቢይ ቤት ወጥቶ በመጣበት መንገድ ተመለሰ፡፡ በመንገድም አንበሳ አግኝቶት ሰብሮ ገደለው፡፡ ሬሳውም መንገድ ላይ ተጋድሞ ነበረ፡፡ አንበሳውም አህያውንም  ሳይነካው በአጠገቡ ዝም ብሎ ቆመ፡፡ ነገሩን የተመለከቱ ሰዎች ሽማግሌው ነቢይ ባለበት ከተማ ሲያወሩ ተሰማ፡፡ ያም ከመንገድ የመለሰው ሽማግሌ ነቢይ ወሬውን በሰማ ጊዜ “በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመጸ የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደተናገረው ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰቡሮም ገድሎታል”አለ፡፡ ልጆቹንም አህያ ጫኑልኝ ብሎ ወደ ስፍራው ሄደ፡፡
በደረሰም ጊዜ ሬሳው ወድቆ አንበሳው አጠገቡ ቆሞ አህያውንም ሳይሰብረው ተመለከተ፡፡ ሬሳውንም በአህያ ጭኖ ያለቅስለት እና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞ መጣ፡፡ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው ዋይ ዋይ ወንድሜ ብሎ አለቀሰለት፡፡ ለልጆቹም እንዲህ አላቸው በሞትኩኝ ጊዜ እርሱ መቃብር አጠገብ ቅበሩኝ፤ አጥንቶቹም ከእርሱ አጥንቶች ጋር አንድ ይሁኑ፡፡ በሰማርያ ከተሞች ውስጥ በቤተልሄም መሰዊያ ላይ የተናገረው ነገር በእዉነት ተፈጽሞአልና፡፡ 
ንጉሥ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ ሳይመለስ ቀረ በኮረብታዎቹ ላይ መስገጆዎችን ሠራ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ለእርሱ ቤት ኃጢአት ሆነ፡፡
           የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሥ ፊት ባደረገው ተአምራት የተነሳ ልሸልምህ፣ በቤተ መንግስት ልጋብዝህ ብሎ ንጉሡ ሲጠይቀው፤ በመጣህበት መንገድ አትመለስ፣ አትብላ፣ አትጠጣ ተብያለሁ ብሎ እጅ መንሻውን ባለመቀበል የመጀመሪያው ፈተና ድል አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ፈተና ደግሞ በዕድሜ አረጋዊ ከሆነ ከእውነተኛ ነቢይ ቀረበለት፡፡ በውሸት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦልኛል በመጣህበት መንገድ ተመለስ እንጀራ ብላ ውኃ ጠጣ ተብለሀል በማለት፤ እግዚአብሔር ካዘዘው ትእዛዝ ጋር የሚቃረን ትእዛዝ አስተላለፈለት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሰው ነቢይ መሆኑን እና ሽምግልናውን ከግምት በማስገባት ነገሩን በደንብ ሳይመረምር፤ ቀድሞ ለምን ታዘዝኩኝ ? አሁን ደግሞ ለምን? እንዴት ተቀየረ ? ብሎ ሳያስተውል፤ የሐሰት ቃል በመስማት የእግዚአብሔርን ቃል ተላለፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ሰው መሳሳት ዋና ምክንያት እግዚአብሔር ካዘዘው ትእዛዝ የበለጠ ሽማግሌዉ ነቢይ የነገረውን ቃል ሳይመረምር አምኖ መቀበሉ ነው፡፡ የማንኛውንም መንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ መመዘኛችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል፣ያዘዘው ትእዛዝ አይለውጥም ማሻሻያም አያደርግለትም፡፡ በኦሪትም ለቤተ እስራኤል እንዲህ ብሎአቸው ነበር  “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም።” ኦሪት ዘኍ.23፥19 በነቢዩም በእንባቆም ትንቢት “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱ አይዘገይም። ዕንባ. 2፥3 ብሎአል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ”ብሎአል፡፡ ማቴ 24፥ 35፣ ማር ፥31፣ ሉቃ 21፥ 33፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከሚሻር የሰማይ እና ምድር ማለፍ እንደሚቀል ተናግሮአል፡፡
ይህ የእግዚአብሔር ሰው በመጣበት መንገድ ወደ ኋላ የተመለሰው፤ ከእውነተኛው ነቢይ የሐሰት ቃል በመስማቱ እና ሳያስተውል ፣ ሳይመረምር አሜን ብሎ በመቀበሉ ነው፡፡ ሐሰተኞች ነቢያት እና መምህራን እውነተኞች ነን ብለው የሚመጡበት ጊዜ አለ፡፡ይህ የተለመደ እና በስፋት የትንቢት ማስጠንቀቂያ የተነገረለት ነው፡፡ የረቀቀ እና የሚከፋው ግን ቀድሞ በእውነተኛነታቸው በጣም ታዋቂ በሆኑት ነቢያት፣ መምህራን የሐሰት የትንቢት ቃል በሚናገሩበት ወቅት ነው ፡፡ እንዲህ አይነቱን ከባድ ፈተና ማለፍ የሚቻለው የተነገረው ቃል፤ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና አለመሆኑን በመመርመር፤ እንዲሁም የነገሩን ትክክለኛነት በቅዱሳት መጻሕፍት ጋር መስማማቱን በመመዘን ነው፡፡
ዲያብሎስ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ትእዛዝ እና መንገድ ለማሳሳት፤ ልዩ ልዩ አይነት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡በዚህም የረጅም ጊዜ ልምድ እና ክህሎት አለው፡፡ ዲያብሎስ መንፈሳዊያን እና ዓለማውያን ሰዎችን ለማሳት የሚጠቀምበት ስልት የተለያየ ነው፡፡የመንፈሳዊያን መንገድ ለማስቀየር እና ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጭ ለማድረግ ሲፈልግ በመንፈሳዊያን ሰዎች አድሮ፤ መንፈሳዊ የሚመስል ሐሰት ይዞ ይቀርባል፡፡ ይህን የዲያብሎስ ውጊያ ድል ለማድረግ ጥልቅ ማስተዋልን ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ  “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥”ምሳ.2፥11 የሚለን ፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ምሳ. 9፥6 የሚለን፡፡ ማስተዋልን የምናገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።” ኢዮብ. 1213 ይለናል፡፡ እንዲሁም  “በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?”ይላል፡፡ ኢዮብ. 3836 ፡፡ በቅዱስ ወንጌልም እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥” በማለት ተጽፎአል ፡፡ ማቴ 24፥15 ፡፡ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምናገኘው ማስተዋል ተመርተን በሃይማኖት መንገድ በምግባር፣ በቱሩፋት መጽናት እንችላለን፡፡
 በሃይማኖት መንገድ ለመጽናት ወደ ኋላ ላለመመለስ፤ ከማስተዋል በተጨማሪ መንፈስን ሁሉ በጥርጣሬ መመርመር አለብን፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” በማለት ይመክረናል፡፡ 1ኛ ዮሐ. 4፥1 ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ስለመጡ ነቢይ ነኝ፣ ራይዕ ተገልጦልኛል፣ የፈውስ ሀብት ተሰጥቶኛል፣ አጠምቃለሁ፣ለማናቸውም ችግር በፍትሄ እሰጣለሁ፣ድንቅ ተአምራት አደርጋለሁ ወዘተ …  ያለውን ሁሉ በስሜት ማመን እና መከተል የለብንም፡፡ በበቂ ሁኔታ ሳንመረምር ስለ እውነተኛነታቸው ለሌሎች ልንመሰክርም አይገባም፡፡ መገኛቸው መንደር ቢሆንም ፤ በተቀደሰው ስፍራ ቢቆሙም፤ ቀደም ብለው እውነተኛ አገልጋዮች ቢሆኑም እንኳን፤ ሳንመረምር ልናምንባቸው አይገባንም፡፡ ጊዜ የሚገልጠው የተደበቀ የጥፋት የእርኩሰትን፣ ገንዘብ መውደድን እና ዝሙትን ፤ ቀድሞ ወደ መጣንበት ኃጢአት መንገድ የሚመልሱ ተግባሮችን ሁሉ ሊፈጽሙ እና ሊያስፈጽሙን ይችላሉና፤ ከሐሰተኛ ትምህርታቸው ልንጠበቅ ይገባል፡፡  
በቅዱስ ወንጌል “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤” ማቴ.24፥11 እንደተባለ በሐሰተኞች ተአምራት ምልክት ተሳስተን የያዝነውን የሃይማኖት መንገድ እንዳንቀይር፡፡በመጨረሻው ዘመን መዳረሻም ከሚመጡት ፈተናዎች መካከል በእውነተኛ ቦታ እና ከእውነተኛ ሰዎችን የዲያብሎስ መጠቀሚያ በማድረግ የጥንቆላ ትንቢትን ማናገር ነው፡፡ በዚህም የብዙዎችን ተቀባይነት አግኝተው፤ ብዙዎችን ከያዙት የጽድቅ መንገድ አስተው ወደ ሌላ የስህተት መንገድ ይመራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” 1ኛ ቆሮ.11፥14 በማለት ሰይጣን በለወጣቸው ሰዎች ስብከት፣ ተአምራት፣ ልዩ ልዩ ምልክት እንዳንስት የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እንዳንጥስ ያስጠነቅቀናል፡፡
            በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አምፆ ወደ ኋላ በመመለሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ሰው በአንበሳ ተሰብሮ ሞተ፡፡ በሃይማኖት ጉዞ ጀምሮ ማቋረጥም ሆነ ወደ ኋላ መመልከት አይቻልም፡፡ በቅዱስ ወንጌልም “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም… ።” ተብሎአል፡፡ ሉቃ.9፥62 መንገዱን ጀምረው ጉዞቸውን ያቋረጡት ሳይሆኑ እስከ መጨረሻው የሚጸኑት ናቸው ለሰማያዊው መንግስት የሚገቡት ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ጀምረው የሚያቋርጡትን ሰዎች ሲገልጣቸው “አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል። ” 2ኛ የጴጥ.2፥21 ብሎአል፡፡
የጽድቅን መንገድ ጀምረው የሚያቋርጡ ሰዎች የሚውጠውን ፈልጎ አድብቶ ለሚጠባበቃቸው ዲያብሎስ ትልቅ ደስታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።”  1ኛ የጴጥ. 5፥8 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከተሰጠን የቅድስና መንገድ ጀምረን ከማቋረጥ የጽድቅን መንገድ አለማወቅ ይቀላል፡፡ ዛሬ በዚህ የስልጣኔ ማማ ላይ በደረሰው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች፤ የጽድቅን መንገድ ጀምሮ ማቋረጥን ሰማያዊ ፍርድ የሚያሰጥ ሳይመስላቸው እንደ ዋዛ ቀለል አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ብዙዎች የጽድቅን መንገድ ጀመሩ አንበሳ በተባለው ዲያብሎስ ተሰብረው ከመሀል አቋረጡ፤ የተክሊል ጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ሽረው ተፋቱ ፣ ቆርበው አፈረሱ፤ ንሥሐ ገብተው ረከሱ፣ ዘምረው ዘፈኑ፣ ቀስሰው አፈረሱ፣ መንኩሰው ቆብ ጣሉ፡፡
በጀመርነው የጽድቅ መንገድ እስከ መጨረሻው እንድንጓዝ የዲያብሎስን ፈተና በእምነት ጸንተን እንድንቃወም
 የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጀነት አይለየን አሜን፡፡
ያዕቆብ ሰንደቁ
ቅዳሜ ሚያዚያ 29 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ