በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን
ክፍል ሁለት
እቤት ስገባ አመሻሽ ላይ ስለነበር ዘመዶቼ እስኪሰበባሰቡ ድረስ ጠበኩኝ፡፡ ውጭ ሀገር መሄድ እንደማልፈልግ ነገ ወደ ሐረር ለዛውም ወደ ገዳም እንደምሄድ ተናገርኩኝ፡፡ አነጋገሬ ቁጣ ቁጣ የሚል ስለነበር ዘመዶቼ ግራ ተጋብተዋል “ምነው? ምነካሽ? ለምን መጣሽ ለምንስ ተመልሰሽ ትሄጃለሽ?”ሲሉኝ ቡሶቴ ሁሉ ተጠራቅሞ እንባዬ በቁሜ ተዘረገፈ፤መናገር አቅቶኝ በተንተባተበ አንደበት“በጠዋት መኪና አሳፍሩኝ ”ብዬ ወደ መኛታ ክፈሌ ገባሁ፡፡
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ በ13ኛው ክፍለዘመን የተነሱ ከቡልጋ አውራጃ በኢቲሳ አካባቢ ከታወቁ ደጋግ ሰዎች ከአባታቸው ከእንድርያስ እና ከእናታቸው ከአርሶንያ የተወለዱ ጻድቅ ናቸው፡፡ ከአሥራ ሁለቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት ደቀመዛሙርት መካከለ አንዱ ናቸው፡፡ በዚህ ታላቅ ገዳም አጽማቸው አርፎ የቃልኪዳናቸውን በረከት ምእመናን ድኅነት ያገኙበታል፡፡
ከመናሐሪያ የተነሳው አውቶብስ ሐረር ደርሰን ወደ አሰበ ተፈሪ ከተማ እስክንደርስ ድረስ ሹፌሩ መዝሙር ያዘምር ነበር፡፡ በተለይ የዘማሪ እንግዳወርቅ ለአባ ሳሙኤል መዝሙር ማን እንዳዘዘው ባለውቅም ደግሞ ደግሞ ያሰማዋል፡፡ በጣም ተመስጬ እንባዬ እየወረደ አብሬ እዘምራለሁ ፦ …
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ መነኮስ ኃያል ቤቴ ግባ
ታስባርካለህ ሰውን ምድር ቅርብነህ አንተ ለእግዚአብሔር
የበረሀው መናኝ ግሩምነው ገድልህ
ምድርህን አስባርከሀል ከፍ አድርገህ በእጅህ
ታምርነው ገዳምን ላየ
ረድኤት በረከት ገበየ
ልጆችህ በገዳም ውስጥ ያሉት
ሳሙኤል ሳሙኤል ይላሉ
አዝማች
አይሻገርብሽ እህልም ኃጢአት
ጌታችን ብሎታል ዋልድባን መሬት
ህርመት ይዘው ልጆቹ በሙሉ
ቋርፍ ነው ዘውትር የሚበሉ
አዝማች
የጣመ ያለመ አጥተን
ዮርዳኖስ ጠበል ምግብ ሆነልን
አዝማች
አስኬማውን ለብሶ በገዳም ሲኖር
የትህትና አባት ነው የሕግ መምህር
ሃሌሉያን ሄደን
አይተን አብረን ካንተ እንኑር አልን
…እያለ ይቀጥላል ፡፡
አሰበ ተፈሪ ስደርስ በስተግራ የሚወስደውን መንገድ ይዥ 12 ኪሎሜትር ተጉዥ ከአውቶቡሱ ወረድኩኝ፡፡የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም በየት አቅጣጫ እንደሆነ እየጠየኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ከፊት ለፊቴ የሚታየውን ተራራ ጢሻውን መንገድ ሁሉ በሕልሜ ስላየሁት የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡
አውቶብስ ውሰጥ የሰማሁት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የሚለው መዝሙር ያቃጭልብኛል፡፡ ፍርሀት የተቀላቀለበት ደስታ እየተሰማኝ ነጠላዩን ሰብሰብ አድርጌ ዳገቱን መውጣት ጀመርኩኝ፡፡ በዚያ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ብቻዬን ዳገቱን መውጣት ተያያዝኩት፡፡ ዛፉን ንፋስ ባወዛወዘው ቁጥር ድምፅ ስሰማ እደነግጥ እና አማትባለሁ፡፡ ትንሽ አለፍ እንዳልኩኝ ደስ የሚል ወረብ ይሰማል፤ እጣን ይሸታል፣ ጸናፅል ይንሿሿል፣ ከበሮ ይመታል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኑ የቀረብኩኝ መስሎኝ “እንዴ እንዲህ ቅርብ ነው እንዴ?” እላለሁ ነገርግን የሚታየኝ ጫካ ብቻ ነበር፡፡ የወረቡ ድምፅ ግን ወደ እኔ እየቀረበ መጣ የሚመስጥ ልብ የሚማርክ ነበር እስከ አሁን አልረሳሁትም በልቤ ሰሌዳ ተጸፏል እንዲህ የሚል የግዕዝ ወረብ
ደምፀ ወተሰብከ ውስተ ዓለም
ዓለም ውስተ ዓለም፣
ለሳሙኤል ኮከበ ገዳም ትሩፍ ዜና ምግባር፡፡
ተመስጬ ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ዳገት እየወጣሁ ከኋላዬ ኮቴ ተሰማኝ ደንግጬ መዞር አቃተኝ፡፡“አይዞሽ በርቼ አትፍሪ”የሚል ድምፅ ስሰማ ልቤ ተሰነጠቀ፡፡ እንደምንም ብዬ ወደ ኋላ ዞር ስል አንድ ሰውዬ “ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ነው የምትሄጂው”ቡሎ በትህትና ጠየቀኝ፡፡ ድንጋጤ ይሁን አላውቅም መልኩን አላየሁትም ነበር፡፡ ዝግ ባለ ድምፅ አዋ አልኩት፡፡ ላግዝሽ አለና በጀርባዮ ያያዝኩትን አነስተኛ ሻንጣ ከላዩ ላይ አወረደና ያዘው፡፡
በሁኔታው ግራ ገባኝ የምናገረው ጠፋኝ አሁን ሰውዩውን አስተዋልኩት ቀጭን አረንጎዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ያላት ነጭ ነጠላ ካለይ አድርጎል፡፡ ከውስጥ ያረጀ እና የነተበ በእሳት የተበላ ልብስ ለብሷል፡፡ ፊቱን ትኩር ብዬ ለማየት ፈራሁ፡፡ በጨረፍታ ሳየው ያ በሕልሜ ወደ አባ ሳሙል ዘንድ ይዞሽ ይሄዳል የተባለው ሰውዬ መሆኑን አወኩኝ፡፡ በነጠላው ውስጥ ያየሁት የአባ ሳሙኤል ስዕል ያለበት መስቀል ያንጸባርቃል፡፡
የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ከትናንት በስትያ መሀል መርካቶ ሳየው ባማረ የከተማ ልብስ፣በጥሩ ዘመናዊ መኪና፤ዛሬ ደግሞ በገዳም አሮጌ እራፊ ጨርቅ በባዶ እግር ብዬ ተገረምኩ፡፡ ለ አፍታ ዝም ካልኩ በኋላ መጠየቅ እንኳ አለብኝ ብዬ በፍርሀት “ወንድሜ አንተ ማነህ?በህልሜስ ያየሁ… ትናንት መርካቶ ያየሁ አንተነህ?” አልኩት፡፡ አንገቱን ወደመሬት አቀርቅሮ “እኔ ረድ እባላለሁ የአባ ሳሙኤል ገዳም አገልጋይ ነኝ”አለኝ፡፡
ዳገቱን እየወጣን በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ እያለፍን ስለገዳሙ አመሰራረት ስለ አባ ሳሙኤል ገድል እና በረከት ይተርክልኝ ጀመር፡፡ ታሪኩን ሲተርክልኝ የተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ ደስ እያለኝ እሰማ ጀመር፡፡ ትረካውን ቀጠለ “በዚህ ገዳም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቸሩ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ስውር ቤተመቅደሶች አሉ፤ይህ ብቻም አይደለም በገዳሙ የከበሮ፣ የጸናጽል፣ የቅዳሴ ድምጽ ይሰማል፤ የተለየ የእጣን መዓዛም ይሸታል፡፡በጽሞና ለሰማው ልብን ወደሰማየ ሰማያት ይዞ የሚሄድ ሕብረ ዝማሬ ይደመጣል፡፡ በአባታችን በአቡነ ሳሙኤል ገድልም እንደተጻፋ እንደ ሔኖክና ኤልያስ ሞትን ሳይቀምሱ የተሰወሩ በርካታ ቅዱሳን መኖሪያ ታላቅና ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡በቦታው ላይ የተሰወሩ ቅዱሳን ለገዳማውያኑም ሆነ በዓለም ለሚኖሩ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው ለያዙ ሰዎች እየተገለጡ ይታዮቸዋል፤ መልእክት ይነግሯቸዋል” አለኝ፡፡
ትረካውን ቀጠለ በዚህ በአሰቦት ገዳም የተሰወሩ ቅዱሳን አባቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ1934 ዓ.ም ከዋልድባ ወደዚህ መጥተው የተሰወሩ 500 ቅዱሳንከማኅበረ ሥላሴ ገዳም 1000 መናንያን መጥተው በዚህ ቦታ ተሰውረዋል፡፡አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ባሕታዊ ለ10 ዓመት ያህል በዋሻ ዘግተው ከኖሩ በኋላ በ1945 ዓ.ም ከሰው በመሠወር ከቅዱሳን ሕብረት ተቀላቅለዋል ፡፡የገዳሙ ላሞችን ለብዙ ዘመናት ሲጠብቁ የኖሩ ባሕታዊ ክፍሌ የተባሉ በ1964 ዓ.ም ተሰውረዋል፡፡ ባሕታዊ አባ በላይ ወ/ሚካኤል የተባሉ መነኩሴ ሐምሌ ሰባት ቀን 1972 ዓ.ም ከቅዳሴ በኋላ በመነኮሳት ፊት በይፋ በቅዱሳን ተጠርተው እንደተሰወሩ በወቅቱ በቦታው የነበሩ አበው ምስክር ናቸው፡፡ አለኝ እና ለአፍታ ዝም አለ፡፡
ይገርምሻል ብሎ ትረካውን ቀጠለ “ይህ ቦታ መካነ ስዋሬ የዕርገት የርቀት ቦታ ነው እያለ እየነገረኝ በተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ፡፡በፊቴ ደመና ግጥም አለ የብርሃን ምንጣፍ ተነጥፎ ይታየኛል፤ ሰማያዊ ጸናጽል ድምጽ ሰምቼው የማላውቀውን ዜማ ሰማሁ፡፡ ከፊት ለፊታችን ወደ እኛ የሚመጡ አንድ ታላቅ አባት ታዩኝ ገና ወደ እኛ እየቀረቡ ሲመጡ መቆም አቅቶኝ ወደ ምንጣፉ ተደፋው፤ ማየትም ሆነ ቀና ማለት አልቻልኩም፡፡ ድምጽ ይሰማኛል የሚያረጋጋ የታላቅ ቅዱስ አባት ብራኬ “አቤቱ ሕዝብሕን አድን ርስትህን ባርክ ”የሚል፡፡ ወዲያው የኪዳን ጸሎት ደረሰ፤ ቀጠለና ቅዳሴ ይቀደስ ጀመረ ፤ልዩ የእጣን መአዛ ልብን የሚያስደስት ሽቱ ይሸታል፡፡
አብሮኝ የመጣው ሰው “እሺ ጻድቁ አባታችን ”እያለ ሲናገር አባ ሳሙኤል እንደተገለጹ ገባኝ፡፡ ለእኔ አይታዬኝም ድምፃቸው ነው የሚሰማኝ እንዲህ አሉ “ በዛሬው ዕለት ይህን ቅዱስ ገዳም በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ ለዘመናት ሲያገለግለኝ የኖረውን ወዳጄን ወደ ቅዱሳን ስፍራ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ልጄ “በስውር የሠራውን መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ከሥላሴ ዘንድ በይፋ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀበልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሰው ያላወቀውን የጽቅ ሥራህን፣ በሥውር ያደረከውን ተጋድሎህን ሁሉ ሥላሴ አይተውቷል፤ሰማያዊ ዋጋም ተሰጥቶሀል” እያሉ ይመርቁታል፡፡ እርሱም በትህትን “ይህ ለእኔ አይገባም ቅዱስ አባታች ገና መቼ አገለገልኩ ምኞት ፍላጎት ፍቅር ነው እንጂ ብዙ ሥራ ይቀረኛል ”እያለ በፍርሀት በትህትና ሲናገር ሰማሁ፡፡
እኔ በሰመመን ውስጥ ሆኜ መስማቴን ቀጠልኩ እንዲህ አሉት “ይህችን አጠገብህ ያለችውን ትንሽ ልጄን እንኳን ይዘሀት መጣህ፡፡ ዲያብሎስ ሊያጠፋት ይፈታተናታል፤ ነገርግን በጸሎቷ ታሸንፈዋለች ዋጋዋ ትልቅ ስለሆነ በዚሁ በአባ ሳሙኤል ገዳም ጸንተሽ ተቀመጪ ከቅዱሳን ጋር አብረሽ ዲያብሎስን ተዋጊው፤ በገዳም ጸንተሽ ደጅ ጥኚ፤ ጊዜው ሲደርስና ጠላት ሲወገድልሽ ብዙ በረከት ታገኚያለሽ” በላት አሉት፡፡ በመስቀላቸው ሲባርኩኝ አይኔ በርቶ ማየት ጀመርኩኝ ይሕን የዛሬውን ሰማያዊ ምሥጢር ማየትሽን ለማንም ሰው እንዳትናገሪ አደራ የረድን ነጠላ እንቺ በቦርሳ ይዘሽ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ሂጂ ነጠላው የእኔ በረከት ነው ወገብሽን ታጠቂበት” ብለው ባረኩኝ፡፡
የቅድሙ ደመና ወደ አጠገቤ መጣና በድጋሚ ከበበኝ በድጋሚ ዐይኔ ተከፈተና ማየት ጀመርኩ፡፡ ሁሉት ቅዱሳን መላእክት አብሮኝ ከመጣው ከረድ አጠገብ በቀኝ እና በግራ ቆመው ታዩኝ፡፡ ልክ መላእክቱ አጠገቡ ሲቆሙ ነጠላውን ወደኔ ወርውሮ ወደ ሰማይ ከፍ ሲል ታየኝ በግዘፈ ሥጋ ከፍ ከፍ እያለ ሲወጣ ተመለከትኩኝ ዐይኔን ተክዬ እየተመለከትኩኝ ደመናው ጭኖ ቀጥ አርጎ ወደ ሰማይ ወሰደው፡፡ ከነበርኩበት መንፈሳዊ ተመስጦ ነቃሁ የረድን ነጭ ነጠላ በእጄ ይዤለሁ፡፡ በሥርዓቱ እጥፍጥፍ አድርጌ ሻጣዬ ውስጥ ከትቼ ዳገቱን ጫካውን አቋርጬ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ጉዞዩን ቀጠልኩ፡፡
የታሪኩ መጨረሻ እና ክፍል ሦስት ይቀጥላል
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ