በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን
የታሪኩ መጨረሻ እና ክፍል ሦስት
ገዳም ስደርስ አስቀድሜ በሕልሜ ያየሁት ቤተክርስቲያን ሕንፃ አገኘሁት፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ ሥራህ ድንቅ ነው” በዬ አመስግኜ ዘወር እንዳልኩ “የገዳሙ መናንያን እግሬን ለማጠብ፣ እቃዬን ለመቀበል የሚበላ ዳቤ ለማዘጋጀት ተሯሯጡ፡፡ ጸሎት አድርሼ ቤተ ክርስቲያኑን ዞሬ ተሳልሜ ስጨርስ ተቀብለው የማርፍበት ቦታ ሰጡኝ፡፡
የገዳሙ መናንያን ትናንት ቀን ብዙ እንጀራ ሲጋግር እና ወጥ ሲሠራ የነበረው ረድ የጀመረውን ሥራ አቋርጦ መጥፋቱ አሳስቧቸው ለገዳሙ አበምኔት ተነገሯቸው፡፡ አበምኔቱ ደንግጠው ትልቁን የገዳሙን ደወል አስደወሉ፡፡ መናንያኑን ሲሰበሰቡ “ ወንድማችን ረድ የጀመረው ሥራ አቋርጦ ስለጠፋ የተጀመረው የገዳሙ ሥራ እንዳይቋረጥ ተባብራችሁ በረድ ፋንታ ሆናችሁ ሥሩ፡፡ የተፈጨው እህል ትንሽ ስለሆነ ቡዙ ኩንታል መፈጨት አለበትና አደራ በየተራ ፍጩ፡፡ የተቀራችሁ ደግሞ ረድ ጾም እና ተጋድሎ አብዝቶ በገድል ብዛት አሞት አንድ ቦታ ወድቆ እንዳይሆን በየቦታው በየሥርቻው ፈልጉት ” ብለው አዘዙ፡፡
የገዳሙ አበምኔት የረድ መጥፈት በጣም አስጨነቃቸው፡፡ በሰርክ ጉባኤ ላይ ከጸሎት በኋላ “ልጄን የበላ አውሬ አልጮህ አለ፣ ገዳማችን ተጎዳ ረድኤቱን በረከቱን አጣ ” እያሉ ያዝናሉ ፡፡ ሀዘናቸውን ሳይ ይህንን ጭንቀት ስሰማ በጣም አዝኜ “በቃ ለምን እውነታውን አልነግራቸውም” ብዬ አሰቡኩኝ፡፡ ግን ደግሞ መልሼ አሰብ ሳደርግ “ለማንም እንዳትናገሪ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ ሳስታውስ ፈራሁ፡፡ ደግሞስ “የወደፊቱም ኑሮዩ በዚሁ ገዳም አይደል እንዴ የሚቀጥለው እንዴት ብዬ ይህን መናገር እችላለሁ? ”ብዩ በትምህርተ መስቀል አማትቤ ዝም አለኩኝ፡፡
በአባ ሳሙኤል ገዳም ሰባተኛ ቀን ሞላኝ፡፡ ከሌሎች ገዳም የበለጠ መንፈሳዊ በረከት ያገኘሁበት ስለሆነ መንፈሳዊ ደስታ ተሰሞቶኛል፡፡ ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል አጽማቸው ያረፈበት ቦታ ማታ ማታ ሄጄ እጸልያለሁ፡፡ “ አባቴ በበረኮቶት ይባርኩኝ ወደ ፈተና እንዳልገባ ጠብቁኝ፣ ዲያብሎስን ድል የማደርግበትን ኃይል ስጡኝ ” እያልኩኝ እማፀናለሁ፡፡ የረድ መጥፋት የገዳሙ መናንያን መነጋረሪያ ነቱን ቀጥሏል፡፡ ከማንም ሰው ጋር በዚህ ጉዳይ ፈጽሞ አላወራም ሁሉንም ነገር በልቤ ይዥዋለው፡፡
የገዳሙ አበምኔት ብራኬ ለመቀበል መስቀል ለመሳለም ሲሄድ እንግዳ በመሆኔ ይሁን በሌላ ምክንያት በትኩረት ያዩኛል፡፡ እኔም “ያየሁትን ምስጢር ያውቁ ይሆን?” እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ እስከመቼ ይሆን ? ይህ ምሥጢራዊ መንፈሳዊ ትዕይንት ለማንም ሳልናገር የምኖረው ”እያልኩኝ ከራሴ ጋር አወራለሁ፡፡ ለካ ምሥጢር መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡
በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ሱባኤ (ሰባት ቀን) ማለቴ ነው በሰላም በማጠናቀቄ መንፈሳዊ ደስታ ተሰማኝ፡፡ የዲያቢሎስ ውጊያ እንደማያቋርጥ ባውቅም ለዛሬ የተለመደውን ያህል ጸሎት ለማድረግ ድካም ተሰማኝ፡፡ ሰው ደካማ ፍጥረት ነው ለዛሬ የተለመደው ጸሎቴ ስግደቴን ልተወው ብዬ ተኛሁ፡፡ ጠዋት ስነሳ ሰውነቴ ተሳሰረ አእምሮዬ ደነዘዘ፡፡ ቀኑን ሙሉ እንዲሁ በራስምታት፣ በቁርጥማት አሳልፌ ማታ የሰርክ ጸሎት ለማድረግ ወደ ቤተክርስቲያን ገባሁ፡፡ ገዳማውያኑ በተመስጦ ደስ በሚል ዜማ ጸሎት እያደረሱ እያለ ጸሎቱን የሚያውክ ነጎድጎዳዊ ድምጽ ተሰማ፡፡ ገዳሙን ማወክ የፈለገው ዲያብሎስ እያጎራ በጠበጠው፡፡ ደግነቱ የገዳሙ አበምኔት ስለገዘቱት ሌላ ምስጢር ሳይቀባጥር ዝም እንዲል ተደረገ ፡፡ ስነቃ ጸሎቱ አልቆ ስለነበር ሰዎች ደግፈውኝ ወደ ማደሪያዬ ሄድኩኝ፡፡
የገዳሙ አበምኔት እላዬ ላይ ያደረውን ጸላየ ሰናይ ኃይል ተመለክተው “በምን ቻለችው ይህን ክፉ ጠላት” ብለው አዘኑ፡፡ ማምሻውን “ዮርዳኖስ በሚባለው ጸበል ጠዋት እንዳጠምቅሽ ነይ ”ብለው መልእክተኛ ላኩብኝ፡፡ የመጀመሪያው ቀን በሰላም ተጠመኩ፡፡ በሁለተኛው ቀን በጣም አመመኝ፡፡ ለሥስተኛ ቀን እንዳልጠመቅ ብዙ ጥረት ቢያደርግም በግድ በትግል ተጠመቅሁ፡፡ መቼም የሀሰት አባት ነው ተሰናብቻለሁ እለቃለው ብሎ ማለ ተገዘተ፡፡ ወደ ህሊናዬ ስመለስ ጠበል ጠጥቼ ገብቼ ተኛሁ፡፡
ከምሽት ጸሎት ሰዓት ጀምሮ ዲያብሎስ ገዳሙን እጀግ በሚያሳዝን ሁኔታ አወከው፡፡ መናንያኑን መደብደብ ጸሎታቸውን ማቋረጥ መዝለፍ ለሊቱን ሁሉ ሲረብሽ አድሮ በነጋታው ጸበል እንዳልጠመቅ የሴቶች ልማድ (የወር አበባ) መጣብኝ እናም ጸበሉን መጠመቅ አቋረጥኩኝ፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ አእምሮዩን አሳተኝ መናንያኑን መረበሽ፣ በመሳደብ፣ በመደብደብ ብዙ በጠበጥኩኝ፡፡ የሚመለከተኝ ሁሉ “ለገዳሙ ፈተና ሆኜ እንደመጣሁ ቆጠረኝ፡፡”ጥቂት ወደ ራሴ ስመለስ ወደ ገዳሙ አበምኔት ቀርቤ “መዳኛዬ ይህ ገዳም እንደሆነ እና ከዚህ መውጣት እንደማልፈልግ ” ነገርኳቸው፡፡ “የሴቶች ልማዱ ከቆመ እኔ ራሴ አጠምቅሻለሁ አይዞሽ በፍቅር እና በትህት ተስፋ ሰጡኝ!” ከቀን ወደ ቀን አይምሮዬን እያሳተኝ እየባሰቡኝ ገዳሙን በሙሉ አወኩኝ፡፡ የገዳሙን አንድነት እና ጸሎት የሚፈትን ችግር በመግጠሙ ምክንያት ገዳሙን የሚያስተዳድሩ አባቶች በጉዳዩ ላይ ሰፉ ውይይት አደረጉ፡፡ በጉባኤው ቡዙ ክርክር ከተደረገ በኋላ “ለገዳሙ ሰላም እና አንድነት ሲባል ከገዳሙ ውጭ ባለ ሌላ ጸበል ቦታ ተጠምቃ ሲሻላት ትምጣ” የሚል ውሳኔ ተወሰነ፡፡
የመጨረሻውን ውሳኔ የነገሩኝ የገዳሙ አበምኔት ነበሩ “ልጄ የገዳሙ አስተዳደር ከገዳሙ ለቀሽ እንድትወጪ ስለወሰነ ሌላ ቦታ ሄደሽ ጸበል ተጠመቂ” አሉኝ፡፡ እንባዬ ዱቡ፣ ዱብ እያለ ሲቃ ያዘኝ፡፡ እዚህ ለመቆየት “ በቃ አትናገሪ የተባልኩትን ነገር መናገር አለብኝ በዬ አሰብኩ” ነገርግን አፌ ላይ አድርሼ እንደገና ይህ ታላቅ ምስጢር ነው ቡዬ ዋጥኩት፡፡ እየተንተባተብኩኝ “እኔ መሆን የምፈልገው እዚሁ ገዳም ነው ”አልኩኝ፡፡ አበምኔቱም“ አይሆንም የሚሸኙሽ መናንያን መጥተዋል እኔም በር ድረስ እሸኝሻለሁ” አሉ፡፡
ጎዜን ሰብስቤ “በውስጤ የያዝኩትን ምስጢር ልናገር ወይስ ይዤው ሊሂድ ” እያልኩ እያመነታው ወደ ገዳሙ በር ተጠቃው እኔን ከገዳም ማስወጣት አላማው የነበረው ዲያብሎስ መውጣቴን ለማፋጠን ብሎ እኔን ቀየረኝ እና የተለመደውን ስድቡን ረብሻውን ቀጠለ፡፡ የሚሸኙን መናንያን በመማታት፣ በመገፈታተር በመሳደቡ ጉልበቱን አሰባስቦ ይወራጭ ጀመረ፡፡ የለበስኩት ልብስ ከላዬ ላይ ተበጫጨቀ ሻንጣዬ ልብሴ ሁሉ ተበታተነ፤ በአካባቢው ግርግር በመፈጠሩ ለመተጋገዝ ብዙ መናንያን ተሰበሰቡ፡፡ አንድ አባት “እቃዋን ሰብስቡላት ተሸክማችሁ ከገዳሙ ውጭ ወዳለው ዋርካ ሥር አድርጎት” አሉ፡፡ ወዲያው በፍጥነት ተሸክመው ከገዳሙ አስወጡኝ፡፡
የገዳሙ አበምኔት ግን በድንጋጤ ዐይናቸውን በተበታተነው ልብስ ላይ አሳረፉ፤የሚያዩትን ነገር ማመን አቃታቸው፡፡ ነጭ ነጠላ ቀጨን አረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ጥለት ያለው በላዩ ላይ አባ ሳሙኤል ዘወገግ ተብሎ ሥዕል የተጠለፈበት ነጠላ አዩ፡፡
ይህ ነጠላ ለምወደው ልጄ ለረድ የሰጠሁት ነበር፤ እንዴት እርሷ ዘንድ መጣ? ምሥጢሩ ምንድ ነው፡፡ መናንያኑ ነጠላውን አንስተው ለገዳሙ አበምኔት ሰጧቸው፡፡ ነጠላው በክብር አጣጥፈው ምሥጢሩ ምንድነው? የሚለውን ለመጠየቅ ከገዳሙ ግቢ ውጭ ወዳለሁት ወደ እኔ ዘንድ መጡ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከገዳሙ ሳልወጣ በፊት ቢሆን ምንኛ ድንቅ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ታሪክ ከሆነ እነሆ ሰባት ዓመት ሆነው፡፡ ከዲያቢሎስ ውጊያ ነፃ ባልወጣም፤ በእግዚአብሔር ቸርነት በመላኩ በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት በመንፈሳዊ ሕይወት እየተጋሁኝ ነው፡፡ ይህን የተረዳው ዲያቢሎስ እኔን ከሃይማኖት ለማሳት በምግባር ለማቆሸሽ አሕዛብ ለማድረግ ብዙ ሮጧል፡፡ ወደ ገዳሙ መንገድ ስጀምር፣ የአባ ሳሙኤል ስም ስጠራ በሕመም ይመታኛል፤ ወደ ቦታውም እንዳልደርስ ይፈትነኛል፡፡
ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ተመልሼ ለመግባት እና እግዚአብሔር በፈቀደልኝ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ገና ደጅ እየጠናሁ ነው፡፡ በዚህ በብሥራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ዕምነቱን ተቀብቼ፣ መስቀሉን ተሳልሜ ሕመሜ ሲቀልልኝ ፊቴን ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት አዞራለሁ፡፡ በምሄድበት ቦታ ሁሉ በምስጢር በጥንቃቄ “ስለ አሰቦት ገዳም ስለ ጻድቁ አባታችን አቡነ ሳሙኤል” ብዬ ስለምን እጁን የማይዘረጋልኝ፤ ምን ላድርግ የማይለኝ ሰው የለም፡፡ እንደዋዛ ከየሰዉ የሰበሰቡኩትን ገንዘብም ሆነ ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ በማጠራቀም ከረድ እንደተማርኩትም በማይታወቅ ሰው ለገዳሙ በሥውር እልካለሁ፡፡
በዐይኔ የተመለከትኩት በብርሃን የተከበበ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል አስደናቂ ክብር ተፈታታኜን ዲያብሎስን እንደ ጉም ተኖ እንዲጠፋ ማድረግ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ያገለግል የነበረውን ረድን ተክቼ በስውር ገዳሙን አገልግዬ በረከት እንዳገኝ በሥጋዬ ላይ የመጣብኝ ሕመም፣ መከራ ሁሉ ለበጎ ሆነ፡፡ በህመሜ ምክንያት ገዳም ተመልሼ መግባት ስለማልችል፤ ሁሉም ለበጎ ሆኖ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ የኃጢአት መደምሰሻ ሥራ እንድሠራ ሌሎችም ምዕመናንን ከበረከቱ እንዳሳትፍ አደረገኝ፡፡
ከገዳም ከወጣሁበት ከዚያች ቀን በኋላ ከገዳሙ መናንያን አንድም ሰው አግኝቼ አላውቅም፡፡ የበለጠውን ክብር ለማግኘት ጊዜያዊውን ፈተና መከራ ሁሉ ለመቋቋም ጠዋት ማታ በጸሎት እማጸናለሁ፡፡ ምኞቴ በአባ ሳሙኤል ገዳም በድንግልና ሕይወት ተወስኖ እያገለገሉ መኖር ነው፡፡ በእውነት አምናለው ይህ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ ውብ ሆኖ ይከናወናል፡፡ አሁን ረድን ተክቼ የገዳሙ አገልጋይ ሆኜ ወደ ቅዱሳን ስፍራ እኔም እንዲሄድ ከ ተሰወሩት ቅዱሳን ጋር በቅዱሳን ሀገር አብሬ መኖር እየናፈኩኝ በዚህ ከንቱ ዓለም እየኖርኩኝ ነው፡፡
ተፈጸመ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ