ዓርብ 10 ማርች 2023

ስብከት

 

ዲያብሎስን ተዋግቼ አሸንፈው ይሆን ?

በዓለም ላይ ከሚደረጉ ጦርነቶች ሁሉ የከፋው ጦርነት ረቂቅ ከሆኑት ርኩሳን መፋፍስት ጋር መዋጋት ነው፡፡ ዲያብሎስ በውጊያ ስልቱ የረቀቀ፤ ብዙ ሠራዊት ያለው፤ የረጅም ጊዜ መንፈሳዊ ጣርነት ልምድ ያካበተ ተዋጊው፡፡ ከቅዱስ ሚካኤል እና ከሠራዊቱ ጋር ሲዎጋ እንኳን አላፈረም፡፡ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከ ዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገር አልደፈረም፡፡ ” ይሀዳ መልዕክት 1

 የእግዚአብሔር ወዳጅን ኢዮብን በሐሰት ከሶ ልጆቹን ገድሎ ሰውነቱን በቁስል መቶ ሲዎጋው ጨካኝ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ “ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ወጡ፣ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ፡፡ መጽሐፈ ኢዮብ.2÷1

ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር ፊት ይከሰው ዘንድ እድፋም ልብሱን እና ያረጀ ጥምጣሙን እየጠቆመ አበሳውን ገለጠበት፡፡ ዲያብሎስ የታላቁን ካሕን ከእሳት የወጣውን ትታግ ኢያሱን በደልን አንድ በአንድ እየቆጠረ ሳይፈራ በድፍረት ከሰሰው፡፡ እግዚአብሔር ግን በምህረት ወደ ኢያሱ ተመለከተ፡፡ ይህንንም ሁኔታ ነቢዩ ዘካሪያስ ገልፆታል “እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፤ ሰይጣንም ይከሰው ዘንድ በስተቀኝ ቆሞ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሰይጣንን ሰይጣን ሆይ፦ እግዚአብሔር ይገሥጽህ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽሕ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን? አለው፡፡” ትንቢተ ዘካርያስ 3÷1-2

በሐዋርያት ጉባኤ መካከልም ሾልኮ በመግባት ይሁዳን ከወንድሞቹ ማኅበር ለየው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ያልታጠቀውን ወታደር ይሁዳ፤ ለሠላሳ ቡር ብሎ መምህሩን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ በክፉ ሀሳብ ማረከው፡፡ “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደደረሰ አውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው፡፡ እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ አሳብ ካገባ በኋላ …፡፡ ዮሐ.13÷1-2

ዲያብሎስ የአዳምን ዘር በሙሉ ይዋጋል ፤ማንንም አይንቅም አያፍርም፡፡ ቦታ አይመርጥም በከተማ ይሁን በገዳም፤በመኖሪያ-ቤት ይሁን በመሥሪያ-ቤት ሰዎችን ከእግዚአብሔር እና ራሳቸውን ከሚጠቅም መልካም ነገር ለማሳት አይደክምም፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ ላይ ነው ብሎ ጉዞውን ከማቋረጥ ከማሰነካከል ቸል አይልም፡፡ በጾም ተጠምዶል ብሎ ጾሙን እና ጸሎቱን ከማርከስ ወደ ኋላው አይመለስም፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ሆኖ በገዳመ ቆሮንጦስ ሲጾም መራብን አይቶ በሦስት ታላላቅ ኃጢአት ማለትም በስስት፣ በትዕቢት እና በገንዘብ መውደድ ለመፈተን ሲመጣ ሳይፈራ ሳይፈራ በጭካኔ ነበር፡፡

ዲያብሎስ ፍጹም ሰው የሆነውን የባሕሪ አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ፈተና በገዳመ ቆሮንጦስ በጾም መራቡን አይቶ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ይህን ድንጋይ እንጀራ ይሁን ብለህ እዘዝ በማለት ነበር፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስም ክርስቶስ የሳፈረው ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስ “ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ” ተብሎ ተጽፎአል በማለት ነው፡፡

 የመጀመሪያው የውጊያ ስልቴም ሆነ የማሰናከያ ጥያቄዬ አልተሳካልኝም ሳይል ዲያብሎስ ሁለተኛ ፈተናውን ለማቅረብ ምንም ሐፍረት አልተሰማውም ነበር፡፡ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ የዓለምን መንግስታት በሙሉ በቅጽበት አሳየው፤ይህ ስልጣን ክብራቸውም ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷልም ” አለው፡፡ እናም “ይህን ሁሉ ለምወደው ለማንም እሰጠዋለውና ለአንተ እሰጥሀለው፤ ስለዚህም አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ ሁሉ ለአንተ ይሆናል ” አለው፡፡ ኢየሱስም “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል ” በማለት አሳፍሮታል፡፡

የዓለም መንግስታት ስልጣን እና ክብራቸው የተሰጠው ዲያብሎስ ለሚሰግዱለት እና ለሚወዱት በዓለም ያለውን ወርቅ ገንዘብ እና ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይው ላይ እንዲህ ይላል “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድርም ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡” ራዕይ 12÷9  ስለዚህም ባለሙሉ ክብር እና ባለስልጣን ሆኖ ክፍውን እና ጨለማውን ዓለም ያስተዳድራል፡፡ ከ ዓለም አናት ላይ ቆሞ ሠራዊቱን በመላክ ዓለም በኃጢአት እና በክፋት ስትተራመስ በማየት ይደሰታል፡፡ ሰውና እግዚአብሔርን ለማጣላት ተግቶ ሴራ ይሸርባል፡፡ ኃጢአት በሰዎች ላይ ሰፍኖ ሰውነታቸው እንዲረክስ በትጋት ይሠራል፡፡



የመጨረሻው ለጌታችን እና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበለት ፈተና ወደ ኢየሩሳሌም መቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከዚህ ወደታች ራስህን ወርውር፤ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በድናጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል፤ ተብሎ ተጽፎአልና በማለት ነበር፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስም መልሶ “ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል” በማለት ከፊቱ ገስጾ አባሮታል፡፡ ዲያብሎስም ፈተናውን ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ እስከ ቀራንዮ መስቀል ላይ ድረስ ፍጹም ሰው የሆነውን አምላክ ጊዜ እየጠበቀ ከመፈታተን ቦዝኖ ግን አያውቅም ነበር፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም የሰውልጆች ጠላት ባለጋራ የሆነው ዲያብሎስ፤ የዓለም መንግስታት ስልጣን እና ክብራቸው ስለሚያስተዳድር ፤ዘወትር በዓለም የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ ከመንፈሳዊ መንገድ ከእግዚአብሔር መንግስት ለማስወጣት እንደሚያገሳ አንበሳ ሊውጠን እንደሚዋጋን ጽፏል፡፡ “በመጠን ኑሩ ንቁም ባለጋራችሁ ዲያብሎስም የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና ” 1ኛ ጴጥሮ. 5÷8

እግዚአብሔር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ፍጹም ሰው የሆነው የጠፉትን በጎቹን ለመፈለግ እና ያጣነውን ልጅነትን እንድናገኝ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መልእክቱ “ስለዚህ የዲያብሎስ ሥራ እንዲፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና ከእግዚአብሔርም ተወልዶልና ሊያደርግም አይችልም፡፡” ይላል፡፡ 1ኛ ዮሐንስ መልእክት 3÷9፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልጀነት ጸጋ ዲያብሎስን ድል የምናደርግበትን መንፈሳዊ ኃይል ሰጠን፡፡ ዐቢይ ፆምን ቀድሶልን ታላላቅ ኃጢአትን ድል በማድረግ እናንተም እንዲሁ አድርጉ በማለት አርዓያውን ተወልን፡፡ ተዋግተን ለማሸነፍ እንድንችልም ሐዋርያው ጳውሎስም “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡” ኤፌ 6÷11 ይላል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ በበኩሉ “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል” በሏል፡፡ ያዕቆብ 4÷7

የእግዚአብሔር ልጆች ዲያብሎስን ይቃወሙታል ይዋጉታል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስም በመልእክቱ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው ይላል፡፡ የዲያብሎስ ልጆች ጽድቅን አይወዱም ወንድማቸውን አይወዱም በማለት ያስረዳል፡፡ 1ኛ ዮሐንስ መልእክት 3÷10፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን በመርከብ ተጉዘው ወደ ቆጵሮስ ሄዱ ጵፋ በሚባል ስፍራ በሚገኝ ሙኩራብ ተገኝተው አስተዋይ ለሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ለተባለው አገረ ገዥ ወንጌል ሲሰብኩ በርያሱስ የሚሉት ጠንቋይ አገረ ገዥውን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ሐዋርያትን ተቃወማቸው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “አንተ ተንኰል ሁሉ የሞላብሕ፤ የዲያብሎስ ልጀ፤ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፤ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን ? እውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም ” ብሎታል፡፡ እንደ በርያሱስ የዲያብሎስ ልጆች እንደ አባታቸው ዲያብሎስም የጽድቅ መንገድ ሁሉ ጠላቶ ናቸው፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፈሪሳዊያንን “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነበረ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፤ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና፡፡” ዮሐ.8÷44   በማለት የዲያብሎስ ልጆች ምን አይነት ሥነ-ምግባር እንዳላቸው አስረድቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋል፡፡” 1ኛ ዮሐን. 3÷8፡፡ እንደለ፡፡ በዓለም ላይ የሰፈነውን ኃጢአት፣ርኩሰት፣ተንኮል አቀነባብሮ የሚያመርተው ዲያብሎስ ሲሆን አስፈጻሚዎቹ ደግሞ በዓለም የሚኖሩ የዲያብሎስ ልጆች ናቸው፡፡



ወዳጄ እንግዲህ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ ዲያብሎትን ተዋጋው ድል ታደርገዋለህ፡፡ ከክፍ ምኞት ሽሽ መልካም በማድረግም ፅና፤ ዘወትር በጸሎትህም በሥራህም ሁሉ ዲያብሎስን ካደው፣ ተቃወመው ከአንተ ይሸሻል፡፡ በቁጣህ ላይ ፀሀይ አይግባ ለዲያብሎስም ፋንታ አትስጠው፡፡

ዐቢይ ጾም ዲያብሎስን ድል ማድረጊያ ዋናው መሳሪያችን ነው፡፡ በየዓመቱ ትጾማለህ በጾሙ መካከል ይሁን በስተመጨረሻ በዲያብሎስ የቀረበልህን ፈተና ምን ያህል ድል አድርገኸው ይሆን? የጾሙ ስኬት መለኪያ ዲያብሎሱን እና ሥራውን ተቃውመህ ድል ማድረግህ ነው፡፡ ኃጢአተኛ ነኝ ንቆ ይተወኛል ብለህ እንዳትዘናጋ፤ በየዓመቱ በሚመጣው አብይ ጾምን በዘልማድ መፆም የለብህም፡፡ መንፈሳዊ ደረጃህን ከፍ ለማድረግ ጹም፡፡ በመንፈሳ ኃይል የሚመጣብህን ፈተና ድል ማድረግን በመለማመድ ይሁን፡፡

እንግዲህ በፍርሀት ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዛ፤ ዲያብሎስን ተቃወመው ከአንተም ይሸሻል፡፡ ዲያብሎስ ለሚወደው ለማንም የዚህን ዓለም ኃላፊ ጠፊ ጊዚያዊ ነገር ካለምንም መስፈርት እሰጥሀለው ብቻ የእግዚአብሔር ልጅ አትሁን እያለ ማባበያ፣ ማማለያውንም በብዛት ይዞ ሊፈትንህ ይመጣልና ተጠንቀቅ፡፡ በውጊያው ዛሬ አሸንፌዋለው ብለህ አትዘናጋ ፀሐይ ሲጠልቅ አድብቶ ደግሞ ደጋግሞ ይመጣል፡፡ወዳጄ  ፈተናውን ስለጨረሰ እስከ ጊዜው ከአንተ ዞር አለ እንጂ አላበቃም ፡፡ እንግዲያውስ እስከ መጨረሻው ህቅታ ድረስ በሃይማኖት በምግባር ጸንተህ አሸንፋው፡፡ ዲያብሎስን ተዋግቼ አሸንፈው ይሆን? አዎ በእግዚአብሔር ኃይል ተዋግተህ ታሸንፈዋለህ፡፡

ያዕቆብ ሰንደቁ

የካቲት 30 ቀን 2015ዓ/ም

አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ  https://yakobsendeku.blogspot.com/

ቴሌግራም https://t.me/MaedotYakobSendekupage

የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርስ  ፔጁን Like Share Comment ያድርጉ::





 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ