ዓርብ 10 ማርች 2023

ስብከት

 

“አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ፡፡”መዝሙር 141÷3

ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ እና በጸሎቱ ይህን ኃይለ-ቃል የተናገረው በልብ የታሰበው ሁሉ ስለማይነገር ያሰብኩትን ሁሉ ልናገር ብዬ ጥፋት ውስጥ እንዳልገባ ለአፌ ጠባቂ ለከንፈሮቼም መዝጊያ አብጅለት ለማለት ነው፡፡

ሰዎች ልንጸልይባቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል አንዱ አንደበት ነው፡፡ አንደበታችን መዚጊያ ካለምክንያት  እንዳይከፈት ቁጥብ ሥርዓት ያለው አንዲሆን! የታረመ ቃልን የሚያፈልቅ እንዲሆን! በጸሎት መጠየቅ ይገባናል፡፡

በሰው ፊት የሚነገሩ ንግግር ጠባቂ ካለው አንደበት የወጣ የታረመ ካልሆነ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡ ካልተዘጋ አንደበት የሚወጣ ቃል ጥፋቱ ብዙ ነው፡፡ በተረትም “ከአፍ የወጣ አፋፍ ” እንዲሉ ከአንደበት ለሚወጣ ንግግር ከመናገር በፊት መጠንቀቅ ይገባል እንጂ አንዴ ከተናገሩት በኋላ የፈሰሰ ውኃ ነው መመለስ አይቻልም፡፡ በልባችን ያሰብነውን ደግም ይሁን ክፉ ጊዜው እና ቦታው ሳይፈቅድልን እንዳመጣልን ከተናገርን ከአንደበታችን ቃል ሳይሆን እሳት ወጥቶ ጥፋት ያጠፋል፡፡

በሀገራችን ባሕል ለአነጋገር ሥርዓት ትኩረት ይሰጣል፤ ለከንፈሮችም መዝጊያ ይበጃል፡፡ በአዋቂዎች፣ በሕፃናት ፣በታመመ ሰው፣ በነፍሰ ጡር ሴት ፊት የሚነገሩ ቃላት ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ በማይገባ ጊዜ እና ቦታ ከማይጠበቅ ሰው የማይጠበቅ ንግግር የተሰማ እንደሆነ ተናጋሪው እንደ “ነውረኛ” ይቆጠራል  “አፈ ቀላል” ተደርጎም ይወቀሳል፡፡ ይህን ማኅበረሰባችን ስለሚጠየፈው ብዙ ጊዜ በልባችን ያሰቡነውን ሁሉ ብንናገር “ሰው ምን ይለኛል” በማለት ብቻ ለአንደታችን መዝጊያ እናበጃለን፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን ሰዎች ያለገደብ ነውረኛ የስድብ ቃላትን ከአንደበታቸው ሲያዘንቡ እንያለን፡፡ ዘመኑ ተለውጦ ከሕጻናት ከአዋቂዎች ሳይቀር ነውር የሆነ ንግግር በተለያየ መንገድ በቀላሉ ይሰማል፡፡ የማኅበራዊ ትሥስር ገጾች የሚለጠፉ መልእክቶች በአንዴ ለብዙ ሰው ይዳረሳሉ፡፡ ልጥፎቹን ያየው ሰው ሁሉ የራሱን አስተያየት እንዲሰጥ እድል በመስጠቱ በአንደበታችን ድምጹ አውጥተን ለመናገር የምናፍርባቸውን ቃላት ሁሉ በማኅበራዊ ገጽ ላይ በነፃነት ይዘዋወራል፡፡ በዚሕም ያልተገባ ቃላትን ማውጣትን እንለማመዳለን፡፡ 

ከአንደበታቸው በወጣ ንግግር የተነሳ በዓለም ላይ ብዙ ኪሳራ ደርሶል፡፡ ከ አንደበት የወጡ ቃላት ጣርነትን አምጥተዋል፡፡ እንዲያውም የቃላት ጣርነት የዋናው ጣርነት መግቢያ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ዝናቸውን ያጡ ታዋቂዎች፤ ዘመድ ወዳጅ የተቀየማቸው ፣ የንግድ ሥራቸው የተበላሸባቸው ታላላቅ ኩባንያዎችን ፤ኑሯቸው ሁሉ የተመሰቃቀለባቸው ብዎች ናቸው እንዲያው ቤት ይቁጠራቸው ማለት ይሻላል፡፡  ሁሉም ታዲያ ነገሩ ካለፈ በኋላ ሲጠየቁ በመናገራቸው ይጸጸታሉ፡፡ በአንድ ነገርም ይስማማሉ “ምነው ያንጊዜ ለአፌ መዝጊያን ባበጀው ኖሮ፤ ባልናገር ቢቀርብኝስ” የሚል ያለፈ ጸጸት፡፡ እናማ ለሁሉም ነገር ለምናውቀውም ፣ለማናውቀውም ፣ለሚመለከተን ለማይመለከተን ፣ቸኩለን ከአንደበታችን ቃል ከማውጣት መቆጠብ ጥሩ ልምምድ ነው፡፡ አስቦ አስልቶ መናገር ለአንደበታችን ጠባቂ ማበጀት ደግሞ ለሁሉም የሰውልጅ ይበጃል ፡፡

ወዳጄ! በተለይ በዚህ በዐቢይ ጾም ከ እህል ከውሃ እንደተከለከልክ ሁሉ አንደበትህን ከውሸት እና ጸያፍ ንግግር ከመናገር ከልክለው፡፡ ጾም ሰውነትን ማሰልጠን ነውና አንደበትህን የታረመ ነገር በመናገርን አሰልጠነው፡፡

 ያኔ የተሞላ ጾም የሚሆን አይመስልህም ?

የካቲት 13 2015 አዲስ አበባ

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ