ዓርብ 10 ማርች 2023

ወግ

 

 “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ”

በቅርቡ ናጄሪያ ውስጥ አንድ የሃይማኖት ተቋም ለአምልኮ ሥፍራ ግንባታ እያካሄደ እያለ የተሾመው አገልጋይ ሲሚንቶውን፣ ብረቱን እየወሰደ ገንዘቡን እመዘበረ የራሱን ቤት ይሠራል፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች አዝነው ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ያደርጉታል፡፡

 ይህን መጥፎ ምግባር አምርሮ ይጠላ የነበረ ሌላ አገልጋይ ይሾማል፡፡ የተሾመው አዲስ አገልጋይ የአምልኮ ቦታውን ግንባታ መጎተቱን አይቶ ሥራውን ያፋጥናል፤ ሙስናንም ይጠየፋል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ አገልጋዩም ሥራውን ከተቀበለ ወራት አለፈ፡፡ የአምልኮ ቦታው ግንባታ ግን ጭራሹኑ ቆመ፡፡

አዲሱ ተሾሚ አገልጋይ ለግንባታ በተመደበው በጀት በውድ ዋጋ መሀል ከተማ መሬት ገዝቶ ባለ አራት ፎቅ ቤት ለራሱ መሥራት ጀመረ፡፡ በፍጥነት ብቅል ያለው ሕንጻ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ አገልጋዩም ሲሚንቶውን፣ ብረቱንም ቁሳቁሱንም እየወሰደ የራሱን ቤት መገንባቱን አፋጠነው፡፡

ሁኔታውን ያዩት አማኞች “ገንዘባችን ተዘረፈ የባሰው መጣብን” ብለው ጮሁ፡፡ ከዚያም ስብሰባ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ አገልጋዩንም ጠርተው “የአምልኮ ቤታችንን ግንባታ አቁመህ የራስህን ቤት ሠራህ ኃላፊነትህ አስረክቡ” ብለው ጮሁበት፡፡ አገልጋዩም ሰውን ሳያፍር ፈጣሪን ሳይፈራ በኩራት “የመጣው ይመጣል እንጂ በፍጹም አገልግሎቴን አልተውም ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ሕዝቡም አጥብቆ “ገንዘባችን ዘርፈሀል በፍጥነት ልቀቅ ” ብለ ተቆጡ፡፡

አገልጋዩም የነገሩን መጋጋል አይቶ “እባካችሁ በፈጣሪ ስም እለምናችኋለው የጀመርኩትን ፎቅ ቤት እስክጨርስ ድረስ ታገሱኝ፤ ከዚያ አገልግሎቴን አቆማለው” ብሎ አረፈው፡፡ ሕዝቡም “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ሠራህ” ብለው ጉዳዩን ወደ ሕግ ወሰዱት፡፡

“ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት”

በአንድ አፍሪካ ሀገር የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት የሚሠራ የእቃ ግዥ ባለሙያ ነበር፡፡ ግብረሰናይ ድርጅቱ ዋና መሥሪያቤቱን ሲገነባ፤ የግንባታ ቁሳቁስ እንዲገዛ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ግንባታው ቶሎ እንዲጠናቀቅ በጀት ተመደበለት፡፡ ነገርግን ሥራው ሊፋጠን አልቻለም፡፡

የግዥ ባለሙያ የሚከፈለው መጠነኛ ደመወዝ ቢሆንም በሥራው ግን ትጉህ ነው፡፡ መቼም ወሬ አይደበቅም አይደል “ቤት እየሰራ ነው” ተብሎ ይወራል፤ እናም አጅሬው ከመሥሪያቤቱ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የጀመረውን የራሱን ቤት ግንባታ፤ አጣድፎ ይሠራ ጀመር፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በሙሉ መብራት፣ ሶኬት፣ መዝጊያ፣የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች፣ታይልስ፣ ሴራሚክ፣ የግድግዳ ቀለም፣ ምንጣፍ ፣ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ጌጣጌጥ ብቻ የቀረ ነገር የለም “ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት” በሚል መርህ ቤቱን በአጭር ጊዜ አሳምሮ ሠራው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ሰውዬው ይግረማችሁ ብሎ አዲሱን ቤት ለማስመረቅ ተዘጋጀ፡፡

የቤቱን ምርቃት አስመልክቶ ድግስ ደግሶ ሰው አላበዛም በማለት የመሥሪያቤቱ ባልደረቦቹን እና የሥራ ኃላፊዎችን ብቻ የድግሱ ታዳሚ አደረጋቸው፡፡ እንግዶቹን ጠርቶ ሳይፈራ ሳያፍር በሙሉ ልብ የሠራውን አዲስ ቤት እየዞረ አስጎኛቸው፡፡ ሠራተኞቹ እና የሥራ ኃላፊዎቹ በነገሩ ተገርመው ፊታቸው ቀላ፣ናላቸው ተበጠበጠ፡፡

 ከመካከላቸው አንዱ የሥራ ኃላፊ በቁጣ “ለካ የዋናው መሥሪያቤት ግንባታ የዘገየው ቅርንጫፉ እየተሠራ ነው” አለ፡፡ ቀጠለ በቁጣ ንግግር “የተጠራነው ለቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን ምርቃት ነው ማለት ነው ብሎ ጠየቀ ? የግዥ ባለሙያ ትንሽ እፍረት እንኳን ሳይሰማው ፈገግ እያለ ማስጎብኘቱን ቀጠለ፡፡ ሌላው ሠራተኛ ደግሞ “ይህ እኮ የአንተ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ሁሉ ነገሩ የግብረሰናይ ድርጅቱ ነው፤ የግድግዳው ቀለም እንኳን የመስሪያቤታችን ጋር ተመሳሳይ ነው ”አለ በንዴት፡፡ ሌሎቹም ሰዎች “በፍጥነት እና በጥራት ተገንብቶ ያለቀውን ቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን በመመረቃችን ተደስተናል ብለው በምጸት ቀልደው እርፍ አሉ፡፡

የግዥ ባለሙያው በማግስቱ ጠዋት ሥራ ሲገባ የስንብት ደብዳቤ እና የፖሊስ ምርመራ መጥሪያ ተሰጠው፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት የተቀበለውን ደብዳቤ ይዞ ራሱ ወደ ገነባው ቅርንጫፍ መሥሪያቤት  ወደ ሆነው አዲሱ መኖሪያ ቤቱ ሄደ፡፡

ወዳጄ ! እንዚህን ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ቦታቸው የተለያየ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ፤ ሥራቸው ደግሞ አገልጋይ እና ደሞዝተኛ፤ ምን ትላቸዋለህ ?

 

 

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ