በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
«ለጊዜው
ብቻ ያምናሉ» ሉቃ.8፥13
በክረምት
ወቅት ተነበው ስብከት ከሚሰበክባቸው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ መካከል አንዱ የዘሪው ምሳሌ ተብሎ የሚጠራው የምንባብ ክፍል
ነው፡፡ ይህን በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ማርቆስ፣ ቅዱስ ሉቃስ
ጽፈውታል፡፡
የምሳሌያዊ
ትምህርቱ ዋና መልዕክት አንድ ገበሬ በሚዘራበት ወቅት ዘሩ በተለያየ የማሳው ቦታ ላይ እንደሚወድቅ የወደቀበትም መሬት ሁኔታ
ለዘሩ መብቀል መጠውለግ ብሎም ፍሬማ መሆን ምክንያት መሆኑ ማስረዳት ነው፡፡ ከዚህም ምንባባት መካከል ቅዱስ ሉቃስ ከጻፈው ምንባብ
ወስጥ ገበሬው ከዘራው ዘር መካከል በዓለት ላይ እንደሌሎቹ ወንጌላውያን አባባል በጭንጫ መሬት ላይ የወደቀውን ዘር አበቃቀል
ከዚያም ፍሬ ሳይሰጥ መድረቁን እንመለከታልን፡፡
ይህን
በምሳሌ የተነገረው ቅዱሳን ሐዋርያት ትርጉሙን መረዳት ባለመቻላቸው ጌታቸውን መምህራቸውን ጠይቀውት ነበር፤ እርሱም ዘሩ
የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በዓለት ላይም የወደቀው ዘር ሥር ሳይሰድ ለጊዜው ብቻ ማደጉ እርጥበት ስላልነበረው ፥ፀሐይ በወጣ
ጊዜ ግን መጠውለጉን፥ በፍጥነትም መድረቁን ነግሯቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚዘራበት ልቦናቸው ዓለት ጭንጫ መሬት የሆነቦቸው
ሰዎች ቃሉን ሰምተው ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበሉ ለጊዜው ብቻ የሚያምኑ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው
የሚሰናከሉ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። ማቴ.13 ፥1 ማር 4፥1 ሉቃ.8 ፥13
«…እናንተ
ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን?» በማለት ነቢዩ አሞጽ የጭንጫ መሬት ለፈረስ
ግልቢያም ለእርሻም እንደማይሆን ይናገራል፡፡ አሞጽ 6፥12-13 የመሬቱም
ጠባይ ለፍሬው ዕድገት የሚረዳውን ውሃ የማይቋጥር ፣ሥሩ ቆንጥጦ የሚይዝበት አፈር የሌለው፤ በእርሱ ላይ የበቀለውም ለጊዜውም
ብቻ በቅሎ ነገርግን አቅም ስሌለው ፀሐይ መቋቋም ባለመቻሉ የሚደርቅ ነው፡፡ በጪንጫ መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በመብቀሉ
እና ቅጠል በማሳየቱ ብቻ በስተመጨረሻ ግን አብቦ አያፈራም፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትም የእግዚአብሔርን ቃል ለአንድ ሰሞን ይሁን
ለረጅም ዘመን የሰማ ብቻ መንፈሳዊ ፍሬ አያፈራም፡፡ በምግባር በሃይማኖት በመጽናት የፀሐዩን ሀሩር ለመቋቋም በጥልቅ መሠረት
ላይ መተከል አለበት አንጂ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም « ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን
እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን
ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ
ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።» ሉቃ.6 ፥ 47-49 ማቴ 7፥25
ጐርፍም
በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም የተባለው በትክክለኛ መንፈሳዊ መሠረት ላይ
የተመሰረተ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትም በምግባር በሃይማኖት ጥልቅ መሠረት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ሊያጠፋው
የሚመጣበተን ፈተና በሙሉ የመቋቋም ኃይል አለው፡፡ በጭንጫ መሬት ላይ እንደበቀለችው ቅጠል ለጊዜው አምሮ ተውቦ የፀሐዩን ንዳድ
ትኩሳት ማለትም ፈተናንን ማለፍ ሳይችል ቀርቶ አይወድቅም፡፡ ሐዋርያው ጳዉሎስም በመልእክቱ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ
ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 ያለው መልዕክት ይህን ይበልጥ
ያስረዳልናል፡፡
የነቢያት
መሠረት እና የሐዋርያት መሠረት የእውነት እና የጽድቅ ነበር፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ብዙ መከራን በአሕዛብ ፊት
ከምስክርነታቸው የተነሳ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እና ነቢያት በመልካም መሬት ላይ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት
መሥርተው ነበር፡፡ በዘመኑ የገነነው ንጉሥ ነቢያትን እንደሰም ሳያቀልጣቸው፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን የሮም ፀሐይ ሳያጠወልጋቸው፤
ቤታቸውን ሊያፈርስ የመጣው ጎርፍ ከሃይማኖት ሳያናውጣቸው ቀርቷል፤ አንገታቸው እኪቀላ ድረስ፣ ቆዳቸው እኪገፈፍ ሰማዕትነትን
ተቀብለው በሃይማኖት ቆሙ፡፡ ደስ እያላቸውም በብዙ ድካም እና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ልንገባ ይገባናል በማለት በምግባር
ፀኑ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ
ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ” ኤፌሶን 3፥16-17 እንዳለ
የቤታቸው የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማድረግ በልባቸው አኖሩት ሥር መሠረታቸውም
ለዓለም ሁሉ ቤዛ ለመሆን በቀራንዮ አደባባይ በተሰቀለው በመድኃኒታችን ፍቅር ሆነ ፡፡
በጪንጫ
መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በቅሎ ነበር ሥሩን ወደ ወንዝ ዳር ሳይሰድ በመቅረቱ በድርቅ ዘመን ፀሐዩ ሲበረታ ፍሬውን
አቋረጠ ደረቀ፡፡ ነቢዩ ኤርምያስንም ይህን በማስመልከት የጻፋ ምንኛ ድንቅ ይሆን እንዲህም ይለናል “በእግዚአብሔር የታመነ
እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ
እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።” ኤርም 17፥8
ፍሬው
የማያቋርጠው ዛፍ ዕምነቱ በእግዚአብሔር ላይ ነው፤የሚመጣውንም ፈተና እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ድል ያደርጋል፡፡ ሥሮቹን
ዘርግቶ ሕይወት የሆነውን ውኃ እንደሚጠጣ ተክል ከሕይወት ውኃ ከእግዚአብሔር ቃል ይጠጣል እና በድርቅ ዓመት በክፉ ዘመን
አይሰጋም አይደናገጥም ለጌዜው ሳይሆን እስከመጨረሻው ያምናል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ሳያቋርጡ የምግባር የሃይማኖት ፍሬ መስጠት የሚቻለው
በውኃ ዳር በተመሰለች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተተክሎ ሥርን ዘረግቶ ከትምህርቷ ሲቀዱ ብቻ ነው፡፡ የነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት
መዝሙር ይህን ያስታውሰናል “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር
ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ
ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” መዝሙረ ዳዊት
1
በጪንጫ
መሬት ላይ የተዘራ ዘር ለጊዜው በጣም በፍጥነት ነበር የበቀለው፡፡ ይህም ገበሬው የድካሙን ፍሬ እንዲያይ በቅጠሉ ማማር እና
መስፋትት እዲደሰት ለፍሬውም ተስፋ አንዲያደርግ አድረጎት ነበር፡፡ ይህም ፈጥና ጥላ ሆና ከአፍታ ቆይታ በኋላ የረገፈችውን የነቢዩን
ዮናስ የቅል ዛፍ ታስታውሰናለች፡፡ “ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ ከተማይቱንም
የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥ ከጭንቀቱም
ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።በነጋው ግን
ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት። ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር
ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ።
እግዚአብሔርም ዮናስን፦ በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም፦ እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል
አለ።እግዚአብሔርም፦ አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው
ቅል አዝነሃል።እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ
ለነነዌ አላዝንምን? አለው።” ትንቢተ ዮናስ 4፥3-11
በአንድ
ለሌት የበቀለች በአንድ ለሌት የደረቀችው የቅል ቅጠል ነቢዩ ዩናስ ለረጅም ጊዜ ጥላ ትሆነኛል ብሎ ተስፋ አድረጎ
ነበር፡፡ይልቁኑ ትበቅል ዘንድ ላልደከመባት እና ላላሳደጋት ቅል እንዲ ማዘኑ ያስገርማል፡፡ እግዚአብሔር ለተከላቸው እና
ላበቀላቸው በሕይወት እንዲኖሩም ተስፋ ያደረገበቸው መቶ ሃያ ሺህ የነነዌ ሰዎች በፍጥነት ወደ ጥፋት መግባት ምንኛ ያሳዝን፡፡ በስተመጨረሻም
ነቢዩ ዮናስ የሰዎቹ መጥፋት ገዶት በከተማዋ ተዘዋውሮ የአዋጅ ነጋሪ ሆኖ ጾም ጸሎትን ሰበካቸው፡፡ ግራና ቀኝ የማታውቀው ከተማ
በነቢዩ ዮናስ አዋጅ ከመጣባት እሳት በንስሐ እና በዕንባ መለምለም ችላ ፍሬዋን አፍራች፡፡
ዛሬም
በአንድ ለሌት መንፈሳዊያን በአንድ ለሌት ደግሞ ጭልጥ ያለ አረመኔ የሚሆኑ ሰዎቸን እግዚአብሔር ከሚመጣው ቁጣ ይድኑ ዘንድ ምን
ያህል ያዝንላቸው ይሆን? ግራና ቀኙን የማያውቀው የእግዚአብሔር ተክል የሆነው ምዕመን በታላላቆቹ ከተሞች ተሰግስጎ ተቀምጧል፤ እንደ
ነቢዩ ዮናስ ስለራሱ መጠለያ፣ ጥላ፣ ፈረጅያ ሳይጨነቅ በየገጠሩ በየስርጡ እየዞረ የንሥሐን ፍሬ ያፈሩ ዘንድ የአዋጅ ነጋሪ ቃል
የሚነግራቸው ማን ይሆን? ራሱ ከሚያገኘው ድቃቂ ሳንቲም አስበልጦ በነፍሳቸው ስለሚጠፉ ምእመናን የሚጨነቅ አገልጋይ ማን ይሆን?
እሳት የተቃጣበት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር በታላላቅ ከተሞች ያለ የማያፈራ ምዕመን ፉቱን ወደ ንሥሐ ይመልስ ዘንድ የማንቂያውን
ደውን የሚያስጮህ ፍሬአማ ጽኑ አገልጋይ ለ ቤተ ክርስቲያን ይፈልጋታል፡፡
የፀሐይ
ከትኵሳት ቅጠልን ሣርንም እንዲያጠወልግ፥ አበባውንም እንደሚያረግፍና፥ የመልኩም ውበት እንደሚያጠፋ ፤በጪንጫ መሬት ላይ የተዘራ
ዘር ከበቀለ አና ቅጠል ካወጣ በኋላ ከሌሎች ተክሎች ተለይቶ ፀሐዩን መቋቋም ያቅተዋል፡፡ ፀሐይ ለሁሉም ሳታዳላ እንደምትወጣ
ማንኛውም ክርስቲያናዊ ሕይወት ፀሐይ የተባለ ፈተና ያጋጥመዋል፡፡ ይህንንም በጽናት ተቋቁሞ ማሳለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም
ሲመክር ፈተና ለክርስቲያኖች የማይቀር ነውና በመጣባችሁ ጊዜ ጠውልጋችሁ አትዘኑ በደስታ ተቀብላችሁ ተቋቁማችሁት እለፉት ይለናል
“ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ
ቍጠሩት ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ
ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን
የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ
ማንንም አይፈትንም።ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤
ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” ያዕቆ 1፥1- 14፣ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፥6-7
ክርስቲያናዊ
ሕይወት እንደወርቅ በእሳት ተፈትኖ ማለፍ መሆኑ ያልተረዱ ሰዎች ይክዳሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው ሥር ሰደው ያልታነጹ
ሃይማኖታቸውን በሚገባ ያልተረዱ መሆናቸው ነው፡፡ ሐዋርያው
ጳውሎስም ቆላስይስ ሰዎች የመከራቸው እንዲህ በማለት ነበር “ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥
ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ
በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” ብሎአል፡፡ ቆላ 2፥7፣ ሮሜ ሰዎች 11፥15-17 ሮሜ 15፥14
ብዙ ተደክሞበት ሳለ ነገርግን መሠረቱን ጥልቅ ያላደረገ በሃይማኖት
ያልታነጸ ምዕመን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም ይታለላል እንደዚ ያሉትን ሰዎች ነቢዩ በግሩም
ቃል እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል “ተክለሃቸዋል ሥር ሰድደዋል፤አድገዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው
ግን ሩቅ ነህ።» ትንቢተ ኤርም 12፥1-2 ነቢዩ ኤርምያስ እንዳለው የማያቋርጥ ፍሬ የሌላቸው ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት
በጽኑ መሠረት የታነጸ ሳይሆን በአንደበታቸው ብቻ ቃሉን የሚናገሩ ቅንጣት ታክል እንኳን መልካም ሥራ የሌላቸው የአምልኮ መልክ
ብቻ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን የመጨረሻው ዘመን ሰዎቸን ምን አይነት ጠባይ እንዳላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ
በላከው መልእክቱ ላይ ይገልጸዋል “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ
ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥
ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥
በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ
ደግሞ ራቅ።” 2ኛ
ወደ ጢሞቴዎስ
3፥1-3
ከእግዚአብሔር
ይልቅ ተድላን የሚወዱ ሰዎች ችኩሎች ስሆኑ ለጊዜው ብቻ ያምናሉ መልካም የሆነውንም የማይወዱ ጨካኞችም በመሆናቸው አያመሰግኑም
ቅድስናም የላቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል ስለሚክዱ በሃይማኖት በምግባር አይጸኑም፡፡ ሃይማኖተኝነት በጊዜ ገደብ የሚወሰን
ሲያመቸን የምናጠብቀው ሌላ ጊዜ ደግሞ የምንተወው አይደለም ዋጋ መንግሥተ ሰማያት የሚሰጠው ጀምረን ባቋረጥነው ሳይሆን
እስከመጨረሻው ህቅታ ድረስ በፈጸም ነው ፡፡ ይህን በማስመልከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈው መልእክት
ምንኛ አስተማሪ ነው «የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤» ዕብ.3፥14 የክርስቶስ መንግስት ተካፋይ
ለመሆን መጽናት ያሻል ቅዱስ ጳውሎስ ተማሪውን ጢሞቴዎስን በማስተማሩ ተግባሩ እንዲጸና ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥
ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፥2 ብሎታል፡፡
ጊዚያዊ ክርስትና ጊዜያዊ ዕምነት የለም “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” ማቴ 10፥22
ናዝሬት ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተሰበከ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ