ረቡዕ 15 ማርች 2023

ወግ “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.19፥12

 

 “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.1912

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ትምህርት በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለማየት ገና ልዑል አልጋወራሽ ሆነው እያለ በገንዘባቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን አሠርተው ሚያዚያ 17 ቀን 1917 ዓ/ም አስመርቀዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን ይኖሩበት የነበረውን ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስትን ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን በመስጠት እና  የግል ገንዘባቸውን ማቋቋሚያ እንዲሆን በማርክት ሚያዚያ 27 ቀን 1952 ዓ/ም ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት፤ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን ፤ከቤተ መንግስት ቀለብ እየተሰፈረ በልዩ እንክብካቤ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ጎበዝ ተማሪዎች ይማሩበታል፡፡ ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ከአውሮፓ እና አሜሪካን የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ፡፡ አስተማሪዎቹ የቀለም ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ የካቶሊክ ዕምነትን ለማስፋፋት የሚሲኦናዊ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተማሪዎች ባደረጉት ክትትል ደረሱባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ይህ መረጃ ሲደረሳቸው የኢየሱሳዊያኑን እንቅስቃሴ የሚያጠና ሕቡ ማኅበር በማቋቋም ክትትል ጀመሩ፡፡ ማኅበሩ ጉዳዩን በማጥናት ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ፤ ለጠቅላይ ቤተ-ክህነት አሳውቀው፤ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ሊቃውንትን ሰብስበው ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተጋረጠውን ፈተና በማስረዳት ጉባኤውን በዕንባ አራጩት፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት ተመሳሳይ ውይይት እንዲደረግ ጉባኤው ወስኖ ተበተነ፡፡

ከጉባኤው በኋላ ወዲያውኑ የማኅበሩ ምሥጢር እየሾለከ በመውጣቱ ዋና ዋናዎቹ የማኅበሩ መሪዎች ታሰሩ፡፡ ተማሪዎች ከተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ታገዱ፤ ገሚሶቹም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ፡፡ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ማስፈራሪያና ቅጣት ለሃይማኖታቸው ጠበቃ ከመሆን ሳያግዳቸው፤ በተዘዋወሩበት ትምህርት ቤትም ቅርንጫፍ ማኅበር በማቋቋም ማህበሩን ከበፊቱ የበለጠ አጠናከሩ፡፡

በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የቀሩት ተማሪዎች ግን ስለብዙ ምክንያት የተማሪዎች አድማ እንዲቀሰቀስ አደረጉ፡፡ በተማሪዎቹም አመጽ ትምህርት ተቋረጠ ንብረት ወደመ፡፡ ብጥብጡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ከቤተ መንግስት አባ ሐና ጂማና ተልከው ተማሪዎቹን አነጋገሩ፤አድማው ግን ሊበርድ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም አድማው ሊረግብ የቻለው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በመገኘት ተግሳጽ እና ምክር በመስጠታቸው ነበር፡፡

ንጉሡ በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ራሳቸውን የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ከራሳቸው ገንዘብ እና ንብረት ወጪ በማውጣት ለሌት ተቀን ይጥሩ ነበር፡፡ ይህን ምኞታቸውን እና ተስፋቸውን የሚያሰናክል ተግባር ተማሪዎች በመፈጸማቸው አዘኑ እጅግም ተቆጡ፡፡ ተማሪዎቹም በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው የአድማቸውን ምክንያት ማስረዳት ጀመሩ፡፡ የተማሪዎቹ የተወረጠ ተወካይ በንጉሡ ፊት የአድማውን ምክንያት በዝርዝር ያስረዳ ጀመር፡፡ ንጉሡ በሆነው ነገር ተበሳጭተው የሚናገረውን ተማሪ በጥፊ መቱት፡፡ የንጉሡን ጥፊ የቀመሰው ተማሪ ሌላውን ያልተመታው ሁለተኛ ጉንጩን አመቻችቶ ሰጣቸው፡፡ ንጉሡም በሁኔታው ተደናግጠው በድጋሚ ለመማታት የሰነዘሩት እጃቸውን ለመሰብሰብ ተገደዱ፡፡

ተማሪው ከሁሉም ነገር በላይ ሃይማኖቴ ይበልጣል በማለቱ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ “እኔ ግን እላችኋለው ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩግን ቀኝ ጉጭህን በጥፊ ለሚመታ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙሩለት፡፡”ማቴ.5፥39 “ጉንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ሥጠው፤መጎናጸፊያውንም ለሚወስድብህ እጀጠባብህን ደግሞ አትከልክለው” ሉቃ.6፥29 የሚለውን የወንጌል ቃል በንጉሡ ፊት ፈጸመው፡፡

በዚያን ወቅት የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ለማንቃት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች መፈጠር እና መስፋፋት፣ ምስካዬ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር እንዲመሰረቱ ምክንያት መሆኑን ጀጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ ሕይወቴ በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈውልናል፡፡

ወዳጄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተማሪው በፈጸመው መንፈሳዊ ተግባር ደንግጠው ትምህርት ወስደው እጃቸውን በድጋሚ ሊፈጽሙት ከነበረው የኃይል ተግባር እንዲቆጠብ አድርገዋል፡፡ ሁለተኛውን ጉንጩን ሰጥቶኛል ምን ያመጣል ብለው ጥፊያቸውን ሳይደግሙት ፤ በዙሪያቸው ባሉት  የሃይማኖት አባቶች መኮንንቱ እና መሳፍንቱ ፊት የንጉሡን ክብር የሚቀንስ ስህት ከመሥራት ተቆጥበዋል፡፡ የዚያን ሰሞን ይህ ክስተት በተማሪዎቹ እና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ሲወራ ሰነበተ፤ ንጉሡም በጥቁር መዝገብ ጥቁር ታሪክ ሳይጽፍ በጣም ካበሳጫቸው ተማሪ ትምህርት ወሰዱ፡፡

በየትኛውም ከፍታ ቦታ ብንሆን፣ ሥልጣን እና ጉልበት ቢኖረንም ፣በአጠገባችን በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ትምህርት የምንወስድ ከሆነ ፤ ከዳግማዊ ስህተት እንጠበቃለን፡፡ ከ እኛ ዙፋን በታች የሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ እኛን ከስህተት የመጠበቅ አቅም የማስተማርም ዕድል አላቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሜት በስህተት እጃችንን ሰንዝረን ከሆነ ጥፋታችንን እንዳንደግመው አስተማሪ ካገኘን ፣ካደመጥንም ከ ከባዱ ሁለተኛው ሥህተት እንተርፋለን፡፡ ታስቦሙ ይሁን በድንገት ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ቶሎ ትምህርት መውሰድ እና ራስን ማስተካከል ብልህነት ነው፡፡

በዓለማችን ላይ እንደምንመለከተው ብዙ ነገሥታት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ ብዙ አስተማሪ ክስተቶች በተደጋጋሚ ቢፈጠሩም፤ልባቸው ደንድኖ ትምህርት መውሰድ ሲያቅታቸው እንመለከታለን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ የጻፈው ቃልም ይህን ያሳያል “ ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፍ ነገር አለ፤ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፡፡” መክብብ.10፥5  ወዳጄ ስህተቱን አውቆ የሚያርም ሰው አስተዋይ ነው!

ያዕቆብ ሰንደቁ  

መጋቢት 2 ቀን  2015ዓ/ም

አዲስ አበባ

ቴሌግራም https://t.me/MaedotYakobSendekupage

የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርስ  ፔጁን Like Share Comment ያድርጉ::

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ