ዓርብ 10 ማርች 2023

ወግ

 

የትኛው ይሻልሀል ?

ሰሞኑን ከሜክሲኮ ወደ አራትኪሎ ታክሲ ተሳፍሬ ልክ አራትኪሎ ታክሲ መውረጃው ጋር ስደርስ እንዲህ ሆነ፡፡ ገና ታክሲውን ሲያየው ሰውነቱ በስፖርት የዳበረ ወጠምሻ የታክሲ ተራ አስከባሪ፤ በመስኮት አንገቱን ብቅ ያደረገውን የታክሲ ረዳት “አንተ እንኳንም አገኘሁ” እያለ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ወደ ተሳፈርንበት ታክሲ እየሮጠ መጣ፡፡

የታክሲ ረዳቱን ከተራ አስከባሪው የሰውነት ግዝፈት ጋር ሲነፃፀር በዝሆን እግር ስር እንደወደቀች አነስተኛ ነገር ያህል ነበር፡፡ የታክሲው በር ተከፍቶ ተሳፋሪዎች ሲወርዱ ተራ አስከባሪው እጁን ለቡጢ ጨብጦ ፊቱን አኮሳትሮ በፍጥነት ሲመጣ አይ በቃ አይለቀውም አያስተርፈውም ብዬ ሽምቅቅ አልኩኝ፡፡

ረዳቱ የመጣው ይምጣ እንጂ ማን ይፈራል ያለ ይመስላል፡፡ ማስፈራሪያውንም ዛቻውንም ከምንም ሳይቆጥር በእጁ ያያዘውን ገንዘብ ወደ ኪሱ በፍጥነት ከተተው፡፡ ሳይፈራ ኮስተር ብሎ “ና ማን የሚፈራህ መሰለህ” ብሎ የሸሚዙን  እጅ ወደ ላይ ሰቡስቦ በቁመትም በግዝፈት ወደሚበልጠው ተራ አስከባሪ ስር በፍጥነት ሄዶ ተወሽቆ ወደ ላይ ቀና እያለ ያየው ጀመረ፡፡

እኔም በልቤ ሲጣሉ ልገላግል ነው ወይስ ቆሜ ላይ ነው እያልኩኝ ፈዝዤ ቀረሁ፡፡ ተሳፊው እና በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሁኔታውን ለማየት አፍጥጠን ቆምን፡፡

ተራ አስከባሪው እስሩ የተወሸቀውን የታክሲ ረዳት አንገቱን እንቅ አድርጎ ወደ ላይ አንጠለጠለው፡፡ እንደገናም መልሶ ወደ መሬት አወረደው እና ደግሞ ደጋግሞ “ተው ብዬህ አልነበረም እንዴ? ዛሬ የመጨረሻ ነው ትመርጣለህ” እያለ ጮኸበት፡፡ ረዳቱም ግራ በመጋባት “ልቀቀኝ እንጂ ምኑን ነው የምመርጠው” እያለ ተወራጨ፡፡

ተራ አስከባሪው በግዙፍ ሰውነቱ ቁልቁል የሚያየውን የታክሲ ረዳት አንገቱን እንዳነቀው “በል ምረጥ እኮ ምረጥ ስድብ ይሻልሀል ወይስ ምክር፤ አሁን እስኪበቃኝ ድረስ ልስደብህ አለበለዛ ደግሞ ልምከርህ ቶሎበል ምረጥ ብሎ ጮሆበት፡፡ ረዳቱ በሁኔታው ተገርሞ “ከሆነማ ብትመክረኝ ይሻለኛል ”ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡

 ለአጭር ደቂቃ የሆነ ክስተት አስገራሚ ነበር፡፡ ይሄ የታክሲ ረዳት “ደግ ጉልበተኛ ላይ ይጣልህ” የሚል ምርቃት ደርሶለታል መሰለኝ ያሁሉ ድንፋታ በምክር ተቀየረለት፡፡ እኛም እንገላግላለን ብለን ቡጡ ሳንቀምስ ስድቡንም ሳንሰማ ወደ ጉዳያችን ሄድን፡፡

ወዳጄ ከጉልበተኛ መካከል ለካ የሚራራ አስተዋይም ይገኛል፡፡ በዓለም ስንት ጉልበተኛ አለ መሳለህ እንደፈለገ የሚያንጠለጥልህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ የሚወዘውዝህ፡፡ እናም እንደዚህ የታክሲ ረዳት ደገኛውን ይስጥህ እንጂ አስመርጦ የሚቀጣህ፡፡ ለአንተ ግን የትኛው ይሻልሀል ? ከቁጣ፣ ከስድብ፣ ከዱላ ምክር አይሻልም !

  “በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው፡፡” መጽሐፈ ምሳሌ 24÷6

ያዕቆብ ሰንደቁ

መጋቢት 1 ቀን 2015

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ