ሰኞ 28 ማርች 2022

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

 

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

በ ያዕቆብ ስንደቁ

ከዓመታት በፊት በዕለተ ስቅለት አዲስ አበባ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታሪኳን የነገረችኝ አንድ ምዕመን የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ከሚነበበው የወንጌል ንባቡ ክፍል ጋር የሚገጥም ነበር ፡፡ ታሪኩን ከመተረኬ በፊት የማቴዎስ ወንጌል 6÷1-7 የተጻፋን ኃይለቃል ላንብብላችሁ  

 “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። …”

ይህ ምንባብ የተራራው ስብከት ከሚባለው መካከልሆኖወርቃማውቃልበመባል ይታወቃል፡፡ የሚያስተላልፈው ትምህርትም መንፈሳዊ ተግባር ለሰው ታይታ ተብሎ የሚከናወን አለመሆኑን ነው፡፡ ብዙ ሰዎችጸሎታቸውን፣በጎሥራቸውን ሁሉ በአደባባይ በሰውፊት ማድረግይፈልጋሉ፡፡ምዕመናንም ለቤተክርስቲያን መባ በአይነትም ሆነ በገንዘብም በምንሰጥበት ወቅት እዩልኝ ፣አሳውቁልኝ ፣አስነግሩልኝ ሳንል በስውር ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ሰዎች እንዲያውቁልን ብለን ማንኛውንም መንፈሳዊ ተግባር የምንሠራ ከሆነግብዞችእንባላለን ዋጋችንንም ከሰማይ ሳይሆን ከሰው ዘንድ እንቀበላለን፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክስቶስም “ይህንን እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ” ነው ያለው ፡፡

v v v

ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ብዙ ስውራን አባቶች ወዳሉበት ጥንታዊ ቦታ ይህች ሴት ልታጋራኝ ወደ ወደደችው ታሪክ እንሂድ

ሐረር እስላም ክርስቲያኑ በአንድ ላይ ተቀላቅሎ የሚኖርበት ከተማ ነው፡፡ ተወልጄ ያደኩት እዚያው ቢሆንም እናቴ ክርስቲያን ነበረች በልጅነቴ ሞታለች፡፡ በቡቸኝነት በማደጌም ይሁን በጤና እክል ብቻ በማላውቀው ምክንያት ሁሌ ሕመምተኛ ነኝ፡፡ ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲመጣ ግን መንፈሳዊ ዝንባሌ ውስጤ አደረና በገዳም በምንኩስና ሕይወት ጸንቼ መኖር ተመኘው ፡፡

ወንድም እና እህቴም የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ብዙ አብረን ባለመኖራችንም ያንያህል ቀረቤታም ፍቅርም የለንም፡፡ በአጠገቤ ምስጢሬን የማካፍለው ሰው የለም፤ ሁሌም ብቸኛ ና ጭምት ነኝ፡፡ ከገዳም ስመለስ ወይም ከሆነ የጸበል ቦታ ስመጣ አንዳንዴ ደግሞ የምበላው ሳጣ ፤የተወሰኑ ቀናት ከአባቴ እና ከወንድም እህቴ ጋር እቆያለሁ፡፡ የተቀረውን ጊዜ በገዳማት፣በጸበል ቦታ ፣የንግስ በዓል ባለበት ቦታ ሁሉ በመዞር ጤና ስፈልግ ከራረምኩኝ፡፡

ቤተሰቦቼ የሕልም እናት እያሉ ይጠሩኛል፡፡ እንቅልፍ ከወሰደኝ በአብዛኛው ሕልም አያለሁ፡፡ እኔ ደግሞ “ክፉው ሕልሜ ነው የምለው፡፡ አንዳንዴ አስጨናቂ እና ከባድ ሕልም ስለማይ እፈራዋለው፡፡ በሕልሜ ከማየው ደስ ከሚለኝ ነገር አንዱ የማላውቀው ገዳም ስሄድ አስቀድሜ ግቢውን፣ አጸዱን፣ የቤተክርስቲያኑን ሁኔታ የማገኛቸውን አባቶች ማየቴ ነው፡፡ በተቀረው እንኳን ብዙ አስፈሪና ክፉ ሀገራዊም ፣ግለሰባዊም ሕልም ስለማይ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ሕልም እንደማይ ከቤተሰቦቼ በቀር ሌላ ሰው አያውቅም እኔም አላወራም ፡፡ ምናልባት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ካላገኘሁት በስተቀር በፍጹም ሕልሜን ለማንም ሰው አልናገርም፡፡ ሕልሜን መናገሬ ያመጣብኝ ጣጣ ብዙ ስለሆነ ትምህርት ወስጃለሁ፡፡

የሕመሜ ምክንያት ቤተሰቦቼ የሚያመልኩት ከ ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዛር መንፈስ ነው፡፡  በአንድ ታላቅ ገዳም በድንገት አንዴ ብቻ ያየዋቸው ታላቅ አባት “የዛር መንፈስ እንዳለብኝ ቅዱስ ገብርኤል እንደሚራዳኝ ተግቼም እንድጸልይ ነግረውኛል፡፡ አንድ ቀን ደግሞ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አሞኝ ወድቄ ጸበል ስጠመቅ መንፈሱ ለፍልፎ ራሱን አጋለጠ፡፡

ከጀመርኩት የክርስትና መንገድ ለማሰናከል የሚፈታተነኝ ዲያብሎስ የሚያደርገውን ጥረትቆጥሬ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ በአንድ ገዳም የማውቃቸው አባት ያለብኝን ፈተና አይተው “የዲያብሎስ ውጊያዎችየግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ኛ የጻፉትን አያሌው ዘኢየሱስ የተረጎመውን መጽሐፍ አንብቢው ብለው በመከሩኝ ጊዜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ማንበብ የጀመርኩ ሰሞን እንቅልፍ እያዳፋኝ ቢያስቸግረኝም ሳላርጥ ጭራሽ ማስታወሻ እየያዝኩ አጠናሁት፡፡

 ተፈታታኜ ዲያብሎስ “የካበተ የሥራ ልምድ ያለው መንቻካ ፣ማንንም የማይንቅ ፣ሴሬኛ መሆኑን ከመጽሐፉተረዳሁ ፡፡ ዲያብሎስን ድል የምነሳበትን መሳሪያ ጸሎት፣ ስግደት፣ ጾም መሆኑን በመማሬ ውጊያውን አፋፍሜ በሰውነቴ ውስጥ እንዳይቀመጥ አስጨነኩት፡፡ አንዳንዴ ውጊያው በጣም ሲበረታብኝ “ቆይ ግን ለምንድን ነው? እኔን የሚፈታተነኝ ? አንዲት ትንሽ ሴት ለመጉዳት ይህ ሁሉ ድካሙ ለምን ይሆን?እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ “ብዙ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት የሚችሉ ቅድስና ያላቸው አባቶች እያሉ! እኔ ላይ ለምን ጌዜውን እና ጉልበቱን ይጨርሳል እላለሁ በግርምት ፡፡

ለጥያቄዬ መልስ ለማግኘት “የዲያብሎስ ውጊያዎች መጽሐፍን ሳገላብጥ ከዚህ በፊት ያላስተዋልኩትን ቃል አነበብኩኝ “ውጊያውን አርጦ ደክሞት እረፍት ወደስዶ አያውቅም ፣ማንንም ሰው አይንቅም” የሚለውን፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን በሙሉ ከእግዚአብሔር መንግስት ለማስወጣት ካለድካም የሚሠራ ጠላት መሆኑን ተረዳው፡፡ ከዚያም “ጠላትን ማወቅ የማሸነፊያ ቁልፍ ነው” ብዮ በየገዳሙ በጸሎት፣ በስግደት በየፀበሉ በመጠመቅ ውጊያውን ድል ለማድረግ ተጋሁ ፡፡

 በምሔድበት ገዳም ሁሉ ከአበው የማገኘው እንክብካቤ እና ፍቅር ተስፋ እንዳልቆርጥ አድርጎኛል፡፡ ጸበል ተጠምቄ፣ ሰግጄ ፣መስቀል ተሳልሜ ከላዬ አልላቀቅ ያለ ክፉ መንፈስ፤እንዴት እና መቼ ከእኔ እንደሚለይ ለማወቅ ብዙ እጸልያለሁ፡፡ አባቶችን በጸሎት ጠይቁልኝ “እስከመቼ እንዲህ በሰይጣን ታውኬ እኖራለሁ? እያልኩኝ እጠይቃለሁ፡፡ መልሱ ግን “ቆይ ገናነው ጌዜው አልደረሰም ጠብቂ ሕመም ብቻ ሳይሆን በረከትም አለበትና ደጅ ጥኝ የሚል ብቻ ነበር፡፡

ሐረር ብኖርም ስለ ደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ብዙም ሰምቼ አላውቅም፡፡ ምሥጢሩ ባይገባኝም የጻድቁ አባ ሳሙኤል ስም ሲጠራ፣አሰቦት ገዳም ሲነሳ ሰውነቴ ይግላል፣ ልቤ ይረበሻል፡፡ ብዙ ኪሎሜትር አርጬ በሰሜን፣ በደቡብም ወዳሉ ገዳማት ስሄድ ከርሜ ሐረር ስመጣ ፤በቅርብ እዚሁ በአሰበተፈሪ በኩል ወዳለው ገዳም መርቶኝ አያውቅም፡፡

አስታውሳለሁ ቀኑ የ ህዳር የቅዱስ ገብርኤል ዋዜማ ነው፡፡ ተኝቼ በሕልሜ የማየው ጠይም ሰው “እኔ ቅዱስ ገብርኤል ነኝ ብሎ አነጋገረኝ፡፡ የተላኩበትን መልእክት በጥንቃቄ አድምጪ “ሥሉስ ቅዱስን በአሰቦት ገዳም ተገኝተሽ አመስግኝ፤ በዚያም ጸንተሽ ተቀመጪ፤በቅርቡ የሥላሴ አገልጋይ ወደ አንቺ ይመጣሉ ብዙ በረከት ያላቸው አባት ምልክታቸውም በአንበሳ ላይ ተቀምጠው የሚሄዱ ናቸው ከእግራቸው ሥር ወድቀሽ በረከታቸውን ውሰጂ ብሎ አዘዘኝ፡፡ ጠዋት ከ መኝታዮ ሥነሳ ሰውነቴ ዝሎ መቆም አቅቶች ተዝለፈለፈ፡፡ እንደምንም የተለመደውን ጸሎቴን አድርሼ ሥጋዬን ለማበርታት ምግብ ፍለጋ ከመኝታ ቤቴ ወጣሁ፡፡

v v v

 በታህሳስ 1 ሌሊት የለመደው ሕልሜ ከአሰበተፈሪ መገንጠያ ጀምሮ ወደ የአሰቦት ገዳም የሚወስደውን ዳገት ከዚያ አልፎም የአባ ሳሙኤልን ገዳም የሴቶች ገዳም መሆኑን ጭምር ነግሮ አሳየኝ፡፡ ጻድቁ አባ ሳሙኤልን ፊታቸው እንደ ፀሐይ እያበራ፤በአንበሳ ላይ ተቀምጠው ረጅም የብረት መሚያ መስቀል በዕጃቸው ይዘው አየሁ፡፡ ከእሳቸው በስተኋላ ሆኖ ራቅ ብሎ የሚከተላቸው ደግሞ አለባበሱ የከተማ ሰው አይነት የሆነ አንድ ሰው ይታየኛል፡፡ በአንገቱ ላይ የአባ ሳሙኤል ምስል ያለበት የነሀስ መስቀል አድርጎል፡፡ በአነስተኛ ሻንጣ ከያዘው ገንዘብ እያወጣ “ይሄ ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ይሆናል፣ይሄ ደግሞ ለገዳሙ መናንያን ቀለብ መግዥያ ነው፣ ይህ ደግሞ ለእርሶ የእረፍት በዓል ዝክር ይሆናልእያለ ላጻድቁ ያስረዳል፡፡

አባታችን አባ ሳሙኤል ፍታቸውን ወደ እኔ አዙረው ለዚያ ሰው “ይህችን ልጄን ለበዓለ ዕረፍቴ ይዘሀት እንድትመጣ ብለው አዘዙት፡፡ ሰውዬውን ትኩር ብዬ አየሁት ፊቱ በብርሀን ተሞልል ትህትና የተመላ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሌላ ዳገት ወጥተን ምዕራፈ ቅዱሳን በሚባል ቦታ ደርሰን ከሰውዬው ጋር አረፍ አልን ምንም ንግግር የለም፡፡ ከተቀመጥንበት ተነስተን ረጅሙን ተራራ ወጥተን ወደ ሜዳው ስንደርስ ዙሪያውን በብርሃን የተከበበ ቤተክርስቲያን ከውሥጡ ብዙ ነጫጭ የለበሱ ሰዎች የሚያስቀድሱበት ልዩ የእጣን መዓዛ ያለው አየሁ፡፡ እየፈራሁ “ይህ የማን ቤተ ክርስቲያን ነው? በዬ ጠየኩ፡፡ የገዳሙ አበምኔት መሆናቸውን በኋለ ያወኳቸው ሰው “የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነው ሲሉኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡

የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ስውራን በሞት ሳይነጠቁ የሚኖሩበት ነው፡፡ ብዙ ቅዱሳንም በሕይወተ ሥጋቸው ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉበት ቦታ ነው፡፡ ስውራን አበው ባሉበት ቦታ የከበሮ ድምጽ ይሰማል፣የዕጣኑ መአዛ ያውዳል፡፡ በገዳሙ ውስጥ መናንያን በጾም፣ በጸሎት፣ በገድል፣ በቱርፉት ተወስነው ይኖራሉ፡፡

ታህሳስ 12 ቀን በሚከበረው የአባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል እና በቅድስት ሥላሴ በዓል ከሩቅም ከቅርብም አበው መነኮሳት ምእመናን ከየቦታው ተሰቡስበው ይመጣሉ፡፡ የእንግዶችን እግር አጥቦ የሚበሉትን ዳቤ ፣ንፍሮ የሚጠጡት ጠላ አዘጋጅቶ መቀበል የገዳሙ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የገዳሙ የተግባር ቤት ለብዙ ሰዎች ምግብ በማሰናዳት በከባድ አገልግሎት ውስጥ ያልፋል፡፡የሚጠጣ ጠላ መጥመቅ ፣ዳቤ መጋገር፣ ንፍሮ መቀቀል፣ ወጥ መሥራት፣እንጨት መልቀም ፣ዳገቱን ወጥቶ ወርዶ ውሀ መቅዳት የመናንያኑ የአገልግሎት ድርሻ ነው፡፡

ገዳሙን በሚያስፈልገው ሁሉ የሚረዱ ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም፤ የሚያስፈልገው ነገር ሲሟላ ነው እንጂ እገሌ እንዲህ አደረገ ተብሎ አይነገርም፡፡ በዐቢይ ጻም፣ በፍልሰታ ገዳምያኑ በጸሎት ብዙ ስለሚጠመዱ የእነርሱን ፈንታ ድርጎውን የሚያሰናዳ ፣እንጨት የሚሰብር፣ ዱቄት የሚፈጭ ፣ጭስቤት ገብቶ ወጥ በትልቅ ጎላ የሚያበስል አንድ አገልጋይ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለታላላቅ መናንያንም ሆነ ለወጣኒ (ለጀማሪ) መነኮሳት የፈለጉበት ቦታ የሚላክ ማገልገል ብቻ ሥራው የሆነ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ታዲያ ሲመጣ እንጂ ሲሄድ አይታወቅም፡፡ ሰው እንዲያውቀው አይፈልግም፤ ብዙ አያወራም ብቻ “ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት ነው የሚለው፡፡

አሮጌ ያደፈ ልብስ የሚለብስ ሥራውን እንጂ እርሱነቱ የማይታወቅ ሰው ነበር፡፡ አንዳንዴ በዓመት ሦስት አራቴ መጥቶ ለወራት የሚሆን እህል ፈጭቶ ፣ማገዶ ለቅሞ ሌላም ሥራ ሰርቶ ሰው ሳያየው ሹልክ ብሎ ይሄዳል፡፡ “ስምህ ማነው? ከየትነው የመጣህው?ብሎ የሚጠይቀውን ሰው አይወድም፡፡ እንደዚህ ሲጠይቁኝ“ ሕመሜ ይነሳብኛል ፣ግዝት አለብኝ ብሎ ይቆጣል፡፡ “እሺ ማን ብለን ስምህን እንጥራው ሲሉት “ረድ ብላችሁ ጥሩኝ የአባ ሳሙኤል አገልጋይ እያለ ይናገራል፡፡

የገዳሙ አበምኔት የማኅበር ጸሎት ላይ በገዳሙ ሥራዎች ቃለምዕዳን ሲሰጡ ለገዳሙ የሚያስፈልገወን ነገር ይናገራሉ፡፡ ከከተማ መምጣት ያለበት ነገር ካለ በቅጽል ስሙ “ ረድ ተብሎ ለሚጠራው ለአባ ሳሙኤል አገልጋይ “ ከተማ ስትሄድ ለጻድቁ ወዳጆች ንገርልን ይሉታል፡፡ እርሱም “አደርሳለሁ ብሎ እጅ ነስቶ ይቀመጣል፡፡ እናም የገዳሙ መናንያን የአባ ሳሙኤል አገልጋይ የሆነው ይህ ሰው ለመናንያኑ ከባድ የሆነውን የገዳሙን ማብሰያቤት ሥራ ጨፈቃ እንጨት ጨምሮ እሳቱን አንድዶ፣ውሀ ቀድቶ፣ ሊጥ አቡኩቶ ፣እንጀራ ሲጋግር ያድራልወጥ በትልቅ በርሜል ሲያበስል ወላፈኑ አይፈጀውም፣እንቅልፍ አያሸንፈውም ድካም አይሰማውም ፡፡ አምስት መናኝ የሚሠራውን ሥራ ብቻውን ስለሚያከናውን መናንያኑ በሙሉ በመገረም “የጻድቁ ረድኤት እየጠበቀው ነው እንጂ እንዴት እሳቱን ቻለው ይላሉ፡፡

 የገዳሙ አበምኔትም አገልግሎቱን በማየት አረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ቀጭን ጥለት ያለው በአራቱም አቅጣጫ የአቡነ ሳሙኤል ሥዕል የተጠለፈበት ነጭ ነጠላ ሸልመውታል፡፡ ረድ በከተማ የሚያውቃቸው ብዙ ባለጠጎችን ለምኖ ለገዳሙ የሚያስፈልገውን እጣን፣ ጧፍ፣ መገበሪያ ስንዴ፣ የመናንያን ልብስ አቡጀዴ፣ ጨው፣ ዘይት ሌሎቸንም ነገር በአይሱዙ መኪና አስጭኖ ሰዎች ይዘው እንዲመጡ ይደረጋል፡፡

ገዳሙን ለረጅም ዘመን የሚረዱ አንድ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰው እየሰጡት ነው ረድ ይዞ የሚመጣው ይባላል፡፡ይህ በየጊዜው ለገዳሙ የሚደረገው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ “ነገር ምንድ ነው? እያሉ መናንያኑ መወያያ በማድረጋቸው የተለያዩ ወሬዎች ተወሩ፡፡ የገዳሙ አበምኔት በሰርክ ጉባኤ መናንያኑ ሁሉ በተሰበሰቡበት ተቆጥተው “ከእንግዲህ ወዲህ በገዳም እንዲህ አይነት ወሬ ማውራት አይቻልም፤ የገደማችን በረከት ያስቀርብናልብለው ነገሩን አዳፍነው በማውገዛቸው ስዚህ ነገር ማውራት ውግዝ ሆኖ ወሬው ቆመ፡፡

v v v

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዘመዶቼ የጤናዮን ችግር ተመልክተው እነርሱ በሚኖሩበት ሀገር ሕክምና እንዳገኝ አመቻቹልኝ፡፡ ይህን ጉዳይ ለመከታተል ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ የማርፍባቸው ዘመዶቼ ብዙ ለሃይማኖት ግድ ስለሌላቸው መንፈሳዊ ደስታ አይሰማኝም፡፡ አንድ ቅዳሜ ቀን ወደ ሐረር እቃ እንድልክ ተልኬ አይሱዙ መኪና እቃ የሚጭንበት መርካቶ ሄድኩኝ፡፡

በአነስተኛ ካርቶን የታሰረውን መልእክት ለማድረስ አይሱዙ መኪኖቹ የሚጭኑበት ቦታ ደርሼ “ሐረር የሚጭነው የትነው ስል አንድ ትንሽልጅ ጠየኩኝ  “ እዛጋር ነው ብሎ ወደ ማዶ አሳየኝ፡፡ መኪኖቹ ወደ ቆሙበት መጠጋት ጀመርኩኝ፡፡ ገና በደንብ ሳልጠጋ አንድ ሰው በርካታ ቁሳቁ በጆንያ እና በማዳበሪያ ወደ መኪና ያስጭናል፡፡ የማውቀው መስሎኝ ትኩር ብዬ አየሁት፡፡ እርሱ ግን አላየኝም፡፡

ሰውዮው መልከ መልካም ሙሉ ልብስ የለበሰ ባለጸጋ ኑሮ የተመቸው ሰው ይመስላል፡፡ ይህም ይጫንላቸው እያለ ካለስስት ከማከፋፈያው ብዙ ገንዘብ የሚያወጡ እቃዎችን ያስጭናል፡፡ እንዴ “ይሄ ሰው በህልሜ ያየሁትን ሰው ይመስላል ብዮ ሳልጨርስ ሰውዬው እቃ ወደቀበት እና ወደ መሬት ጎንበስ አለ ፡፡ ከሸሚዙ ውስጥ ብቅ ያለው ማህተም ላይ ያንጠለጠለውን ሳይ ደነገጥኩኝ በሕልሜ ያየሁትን የአባ ሳሙኤል ምስል ያለበት መስቀል ነው ያንጠለጠለው ፡፡

እኔ በቆሙኩበት ቀረሁ እርሱ በፍጥነት ገንዘቡን ከፋፍሎ “ አደራ አሰቦት ስትደርሱ ታጥፋችሁ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም አድርሱ ብሎ ሲናገር ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ከቆምኩበት ሳልንቀሳቀስ ሰማያዊ ዘመናዊ መኪናውን አስነስቶ ከአካባቢው ተሰወረ፡፡ በዐይኔ ብከተለው ተሰውሮ ቀረ ፡፡ወዲያው ወደ አይሱዙ ሹፌር ሄድኩና “ይህ እቃ ሐረር ታደርስልኝ ብዬ ጠየኩትብዙ ሳያቅማማ “እሺ ብሎተቀበለኝ፡፡ ቀጠልኩና “ይህን እቃ ለማነው የጫናችሁት? አልኩት፡፡ በጥያቄዬ ግራ የተጋባው ሹፌር “ለገዳም ነዋ! ለአባ ሳሙኤል ሲለኝ ልቤ ማረጋገጫ እንዳገኘ ቆጥሮ እርፍ አለ! በድንጋጤ አንደበቴ ተሳሰረና ወደ ኋላ ዞሬ…ጉዞ ወደ ቤት ሆነ፡፡

ክፍል ሁለት ይቀጥላል