ኑሮ ለማሸነፍ
አጭር ልብወለድ
በንግድ ሥራ መተዳደር ከጀመርኩኝ እነሆ አሥር ዓመት አለፈኝ ፤ ኑሮ ለማሸነፍ ጥሬ ግሬ ለመኖር ታትሬ እሠራለሁ፡፡ ነግጄ ለማትረፍ ከትንሽ እስከ ቀላል የተባሉትን ሥራዎች ሁሉ ሠርቻለሁ፡፡ ከመንግስት፣ ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ ልዩ ልዩ ብድሮችን በመውሰድ የንግድ ሥራዬን ለማፋጠን ያደረኩት ሙከራም መክኗል፡፡ ጉዳዩ “የችሎታ ማነስ ነው” እንዳልል፤ እኔ ሀሳብ የለገስኳቸው ሰዎች ከእኔ በተሻለ ሠርተው ተለውጠዋል፤ ዕጣ ፋንታ እንዳልል የሚገርሙ መልካም የሥራ አጋጣሚዎችን በማግኘት የተነሳ ዕድለኛ እንደሆንኩኝ ሰዎች ይነግሩኛል፡፡ ሠራቼ የማገኘውን ገንዘብ መቅኖ አጥቶ ባክኖ ይቀራል፡፡ ተጠራቅሞ ቅርስ ሊሆነኝ ሲገባው እጄ ሳይገባ ሳልቆጥረው በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ተሰናብቶኝ ሄዳል፡፡ ያገኘኋቸው ብዙ ጥሩ እና አጎጊ ሥራዎች ሠርቼ ውጤት ላይ ሳይደርስ መሀል ላይ ተሰናክለው ይቀራሉ፡፡ ገንዘብን አላባክንም ሱስ የለብኝም፤ ተግቼ እሠራለሁ ግን ሥራዬ መቅኖ የሌለው እርባናቢስ ነው፡፡
ቤተሰቦቼ፣ ባልንጀሮቼ በሁኔታው በመገረም ደግሞም መቸገሬ እና መጎዳቴ ቢያሳስባቸው የየራሳቸውን ምክር ይሰጡኛል፡፡ በተደጋጋሚ ሥራ አልሳካ ማለቱን የተመለከቱት “ለምን ለባለስልጣናት መማለጃ (ጉቦ) በመስጠት አትሠራም” ሲሉ፤የመኪና መለዋወጫ ሱቅ ገበያ መቀዝቀዙን የተመለከቱት ደግሞ “አዋቂ (ጠንቋይ) ዘንድ ሄደህ መፍትሄ ፈልግ ” ብለው ይጠቁመኛል፡፡ እኔ ግን የእነርሱን ምክር ለመቀበል ልቦናዬ ሃይማኖቴም አልፈቀደም፡፡ ምርጫዬ እግዚአብሔር ሆነ ዘወት ተስፋ አደርገዋለው፤ እመካበታለሁም፡፡
በክርስትና ሕይወቴ ትጉህ አይደለሁም፤ብቻ በሥጋዊ ኑሮዬ ሥኬትን አለማግኘት እና መቸገር ስለሚያበሳጨኝ እግዚአብሔርን አማርረዋለሁ፤ ደግሜ ደጋግሜ አማርራለሁ እነጫነጫለሁ እበሳጫለሁ በጥቅሉ ደስተኛ አይደለሁም ፡፡ ከመኖሪያ ቤቴ አጠገብ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስያን አለ፡፡ ጠዋት ወደ ሥራ ስሄድ ቤተ ክርስቲያን ገብቼ በአጭሩ “በሰላም ያሳደርከኝ በሰላም አውለኝ ብዬ” ሦስቴ ከአንገቴ ጎንበስ ጎንበስ ብዬ በሩን ተሳልሜ ያባረሩኝ ይመስል በፍጥነት እሄዳለሁ፡፡ የሚገርመኝ ደግሞ ምንም የምቸኩሉበት የሚያጣድፍ ጉዳይ አለመኖሩ ነው፡፡ ውስጤን የሚያብከነክነኝን የኑሮዬን ጉዳይ አንስቼ ጸልዬ አላውቅም፡፡ ነገርግን ከቅዱስ ሚካኤል ጋር የተለየ ቁርኝት አለኝ ልደቴ፣ ታምሜ የዳንኩበት፣ መጀመሪያ ሥራ የያዝኩበት ቀን የሚካኤል ቀን ነው፡፡ በዕለቱ ቤተክርስቲያን ደርሼ ጸሎት አድርጌ ወደ ጉዳዮ ካልሄድኩ ባጣ ባጣ ቃሪያ ጥፊዮን ቀምሼ እውላለሁ፡፡ ስለዚህ የተለየ አክብሮት እና ፍቅር አለኝ ፡፡ በአብዛኛውን የቅዱስ ሚካኤል ቀን በእለተ ቀኑ ሥራ ሳልሰራ አከብረዋለሁ፡፡
ቅዳሜ ኪሴ ባዶ ሆኖ ቡዙ ባለእዳዎቼ አይናቸውን አፍጥጠው መጥተውብኝ የምከፍለው አጥቼ ተጨንቄአለሁ ይባስ ብሎ ደግሞ ለሠራተኞች የምከፍለው ብር በማጣቴ በጣም ተበሳጭቼ ግራገብቶኛል፡፡ ቅዳሜ አመሻሽ ድረስ ስልኬን አጥፍቼ ከሥራ ቦታዬ ተደብቄ ቆየሁ፡፡ በማግስቱ እሁድ የቅዱስ ሚካኤል ቀን መሆኑን ሳውቅ መረጋጋት እና ደስታ ተሰማኝ፡፡ ሌሊቱን ሁሉ በሀሳቡ ማዕበል ስናወጽ እንቅልፍ አጥቼ አደርኩ፡፡ እሁድ ዕለት ሲነጋጋ ከመኝታዬ ተነስቼ ነጠላዬን አጣፍቼ ኪዳን ለማድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገባሁ ፤ሥርዓተ ቅዳሴውን በተመሰጦ አስቀደስኩ፡፡ ከወተሮው የበለጠ መንፈሳዊ ደስታ እና ብርታት ውስጤ ዘልቆ ሲገባ ይሰማኛል፡፡ ሌሊቱን ሁሉ በጣም ተከፍቼ በማደሬ የሆዴን ብሶት ሁሉ ለቅዱስ ሚካኤል በጸሎት መንገር ጀመርኩኝ፡፡ እንባዬ ምንጣፍን እያራሰው ሰውነቴ እስኪዝል ድረስ የልቤን ሀዘን የሆነውን የዕለት እንጀራዬን ኑሮዬን ስለማስተካከል ልመናዬን በጽኑ ዕምነት አቀረብኩኝ፡፡
ቅዳሴ ሥርዓቱ አልቆ ውስጥ ያላችሁ እና በዙሪያው የምትገኙ ሁሉ በዓውደ ምህረቱ ላይ ትምህርት ስለሚሰጥ ፊት ለፊት ወንበር ላይ ተቀመጡ ሲባል እየሰማሁ ብቻ ራሴን ወንበር ላይ ተመቻችቼ ተቀምጬ አገኘሁት፡፡ መምህሩ እንዲህ ብሎ ማስተማር ጀመረ “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ” ኢሳ.1፥19 እግዚአብሔርን እሺ በማለት መታዘዛችን የሚገለጠው ሕጉን እና ትዕዛዙን አክብረን በመፈጸም ነው፡፡ ኑሮአችን እንዲባረክ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሆነውን አሥራቱን፣ በኩራቱን፣ ቀዳሚቱን ማውጣት አለብን እያለ ማስተማሩን ቀጠለ ውኃ እንደጠማው ሰው ቃሉ ወደ ውስጤ ጅው ብሎ ቁርቁር እያለ ሲገባ ይታየኛል፡፡
መምህሩ ማስተማሩን እንዲህ እያለ ማስተማሩን ቀጠለ በቡሉይ ኪዳን ነቢዩ ለእግዚአብሔር ቤት በሚሠጠው በኩራት በረከት እንደሚያሰጥ እንዲህ እያለ ያስረዳል “የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኵራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ።” ቡሏል፡፡/ትን. ሕዝ. 44፥30/ ብዙዎቻችን የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ሳንሰጥ በረከት ማግኘት እንፈልጋለን ነገርግን መጀመሪያ መቅደም ያለበት እሺ ብሎ መታዘዝ ነው ብሎ አስተማረ መምህሩ የሚናገረው የእግዚአብሔር ቃል እኔን እያፈራረሰ የሚጠግነኝ አዲስ ቅርጽ የሚሰጠኝ እየመሰለኝ መላ ሰውነቴን ወረረው ፡፡
በዓውደ ምህረቱ ላይ የሚሰጠው ትምህርት በጣም ውሳጣዊ ሰውነቴን እየሠረሰረ ገብቷል ከመመሰጤ የተነሳም ከሌላው ሰው የበለጠ ጮክ እያልኩኝ አሜን አሜን እል ነበር፡፡ መምህሩም ትምህርቱን ቀጥሎ እንዲህ አለ “አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ።” ትንቢተ. ሐጌ.1፥5-6 በማለት በሰፊው ትምህርቱን ሰጠ፡፡
መምህሩ ሲያስተምር ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ እያለ ሲናገር መንገዴና ልቤ የተዘበራረቀብኝ መሆኑን ተረዳሁ እንዲያውም እኔን የሚያውቀኝ ይመስል ሁሉም የሚናገረው ቃል በሙሉ የእኔን ሕይወት የሚመለከት የሚወቅስ ነበር፡፡ በተለይ ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ይመስላል የሚለው ቃል ልቤን ሰበረው፡፡ ትምህርቱ ተጠናቀቀ እኔ ግን ፈዝዤ ቀረሁ ምን ላድርግ ? ምን ልሁን አልኩኘ ?
ከትምህርቱ በኋላ ስረጋጋ ቆም ብዬ እኔ ማነኝ ቤቴስ ምንድን ነው ? ቡዬ ራሴን ጠየኩኝ ራሴን መረመርኩት መንፈሳዊ ሂወቴን ፈተሽኩኝ፡፡ ከቀናት ጽሞና በኋላ አንድ ነገር ተረዳሁ መንፈሳዊ ሕይወቴ ሲስተካከል እና ለእግዚአብሔር ስታዘዝ የዚህን ዓለም በረከት እንደማገኘ በእርግጠኝነት ተረዳሁ ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በትክከለኛው የክርስትና መስመር መጎዝ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
የመጀመሪያው እርምጃዬ የእግዚአበሔርን ቃል በሚገባ መማር የተማሩትንም በተግባር ለማዋል መጣር ነበር፡፡ ቀጥሎ የንሥሓ አባት መያዝ፣ በንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታቅ በጾም እና ጸሎት መትጋት ሆነ፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ሕይወቴ የኃላፊውን ዓለም ሀብት እና ንብረት ለመሰብሰብ የነበረኝ ጉጉት ሁሉ ቀረ፡፡ ዓለምን ናቁት መንገዴም አስተሳሰቤም ሁሉ በመንፈሳዊ ሆነ፡፡ አድራሻዬ ተለወጠ ቤተክርስቲያን መሄድ መጸለይ ማስቀደስ ትምህርት መማር መልካም ሥነ-ምግባርን ለመተግበር መጣጣር ለድሆች እና ለችግረኞች ማዘን፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያዘው ከንግድ ሥራዬ ከማገኘው ገቢ ላይ አሥራቱን በዕለቱ በመቀነስ ለብቻው በማስቀመጥ አጠራቅሜ ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ጀመርኩኝ፡፡ ትኩረቴ ሁሉ መንፈሳዊ ነገር ላይ ቢሆንም ለረጅም ዘመን የገነባሁት የሥራ ባሕል ሥላለኝ ተግቼ ሥራዬን እሠራለሁ፡፡ ቀስ በቀስ የሥራዬ በረከት እጅግ ብዙ ሆነ፡፡ ለብዙ ዘመናት በሥራዬ ላይ የነበረው እንቅፋት በቅዱስ ሚካኤል ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ተወገደልኝ፡፡
የእለት እንጀራ ለማግኘት እንዳልተቸገርኩኝ አሁን ግን የእግዚአብሔር በረከት ኑሮዮን መላ ተትረፈረፈ፡፡ በንግድ ሥራዬ የማገኘው ገቢ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከማገኘው ገቢ አሥራት ማውጣት ጀመርኩኝ፡፡ ገቢዬ እያደገ እኔም የማወጣው አሥራት ጨመረ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ቢሆንም አሥቴን አጠራቅሜ ሂሳብን ሠርቼ ለቤተ ክርስቲያን እሰጣለሁ፡፡ የድርጅቴ ሂሳብ ሠራተኞች በየዕለቱ ሂሳብ አንድ አሥረኛው ለይተው ከሌላ ገንዘብ ጋር ሳይቀላቅሉ በጥንቃቄ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ሲሆን እነሆ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመት ሞላው፡፡
ገቢዬ እያደገ አሥራቱም እየጨመረ በጥቷል፡፡ የተጠራቀመውን ገንዘብ ከንግሥ በዓላቱ ጋር በማስታከክ ለህዳር ሚካኤል በዓል ሰሞን እና ለሰኔ ሚካኤል በዓል ግድሞ ወደ ቤተክርስቲያኑ አስተዳደር በመሄድ ደረሰኝ እያስቆረጥኩ እሰጣለሁ፡፡ በዚያን ሰሞን ብዙ መንፈሳዊ በረከት አገኛለሁ መንፈሳዊ ግዴታዩንም በመወጣቴ እግዚአብሔር እንደተደሰተ በልዩ ልዩ መንገድ አውቃለሁ ፡፡ የተለየ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በንግስ በዓሉ ዕለትም ነዳያንን ጦም አዳሪዎችን፣ ጸበል ጸዲቅ በማዘጋጀት ቡሉ ጠጡ በማለት መንፈሳዊ ግዴታዬን እወጣለሁ ፡፡
የህዳር ሚካኤል በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ሲቀረው የግል ሥራዬን ትቼ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅት ላይ ነበርኩ፡፡ በየዓመቱ የተለመደውን የአሥራት ገንዘቤን ሂሳብ ለማድረግ ከሂሳብ ባለሙያዎቼ ጋር ስቡሰባ ተቀምጨ የአደራ ገንዘቡ የሆነውን አሥራቴን ቤተክርስቲያን ወስጄ ገቢ እስካደርግ በጣም ተቻኮልኩኝ መክንያቱም ደብራችን ለጀመረው የቤተክርስቲያን እድሳት ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሂሳቡ ሲሠራ ገንዘቡ በጣም ብዙ ሆነ፡፡ በሁለት ኩርቱ ፌስታል ሙሉ ገንዘቡን ቋጥሬ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የለመዱኩትን ተግባር በመፈጸም መንፈሳዊ በረከት እና ደስታ ለማግኘት ተዘጋጀሁ፡፡
በሥራ ቦታ ካለወትሮው ባለጉዳዩች በዙብኝ፤ ከውጭ ሀገር ለሥራ ጉዳይ ስልክ ተደውሎ ረጅም ሰዓት አወራሁ፡፡ የእጅ ስልኬ ረጅም ሰዓት በመያዜ ባለቤቴ ስትደውል ስላላገኘችኝ ተከፋች፤ መልሼ ብደውልላትም ስልኩን አታነሳውም፡፡ ወደ ቤት መሄድ አለብኘ ቡዬ ተጣድፌ መኪናዬ ውስጥ ብገባ የመኪናዬ ሞተር እንቢ ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ከሰዓታት በኋላ በግፊ መኪናዬ ሲንቀሳቀስ ቅድሚያ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድ ይገባኛ ብዬ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሜ ጸሎቴን ስጨርስ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በመሄድ በፈስታል የሞላውን የአስራት ገንዘብ ለአዲሷ ገንዘብ ያዥ ሳላስቆጥር ስልክ እያወራሁ ተቻኩዬ ከቤተክርስቲያን ወጣሁ፡፡
ወዲውኑ የሰውነት አካሌን ሁሉ የሚቆረጣጥም ልቤን ፍርሃት ፍርሐት የሚል ስሜት ይሰማኝ ጀመር፡፡ ጉንፋን ወይም ብርድ ሊሆን ይችላል እቤት ሄጄ አረፍ ብዬ ሌሊት ቤተክርስቲያን እመጣለሁ በዬ አሰብኩኝ፡፡ ነገርግን ሕመሙ እየበረታብኝ ልቤን እየጨነቀኝ ሲመጣ ለምን ይሆን ? ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩኝ ፡፡ ላለፉት ዓመታት ሳደርገው ከነበረው መንፈሳዊ ተግባር ያጎደልኩት ነገር የለም እንዲያው የዘንድሮው ከሌላ ጊዜ የተሻለ ነበረ፡፡
እቤት ገብቼ ትንሽ ስላመመኝ ልተኛ ብዩ ወደ መኝታ ክፍል ገባሁ፡፡ የመኝታ ሰዓቴ በቅዠት እና በጭንቀት አለፈ፡፡ አሥራ አንድ ሰዓት ሲሆን በግድ ሰውነቴን ጎትቼ ወደ ቤተ ክርስቲን ሄዱኩኝ፡፡ ጸሎተ ኪዳን አደረስኩ ቅዳሴም አስቀደስኩ፡፡ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ ዑደት ሲያደርግ እንደሌላው ጊዜ በእልልታ መዘመር አቃተኝ ሰውነቴ መቆም አቅቶት ራደ፡፡ ከዚህ በፊት በነበረኝ ተሞክሮ የአስራት ገንዘብ በሆነ መንገድ የጎደለ ወይም የዘገየ ከሆነ ሥራዬ ኑሮዬ ሁሉ መበታወክ ምልክት ይሰጠኝ ነበር፡፡ ዛሬም የሆነ የተፈጠረ ሥህተት ቢኖር ነው እንጂ በጤናዬ እንዳልሆነ ጠረጠርኩኝ፡፡ የዚህን ጊዜ እግዚአብሔርን ያስቀየምኩበት መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን ያስከፋሁበት ተግባር መኖር አምኜ ተቀበልኩኝ፡፡
የአሥራት ገንዘቤን አጠራቅሜ በዓመት ሁለቴ በሰኔ ሚካኤል እና በህዳር ሚክኤል የንግስ በዓል ዕለት የመስጠት ልምድ አለኝ፡፡ ትዝ ሲለኝ ቢሮ ገንዘብ ማስቀመጫ ካዝና ውስጥ ስለነበር በሆነ መንገድ ከታሰበው ሂሳብ ላይ ቀንሰውለት ይሆናል ብዩ ገመትኩኝ፡፡ ወዲውኑ የእጅ ሥልኬን አውጥቼ ወደ ጸሐፊዬ ደወልኩኝ፡፡ የመዝሙር እና የእልልታ ድምፅ አሰምታኝ ስልኩን ዘጋችው፡፡ ጭንቅ እንደያዘኝ ታቦቱ ዑደት አድረጎ ሲቆም ወደ ቤቴ አቀናው፡፡ እቤት ስሄድ ማንም ሰው የለም የቤተሰቡ አባላት በሙሉ በዓል ለማክበር ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሄደዋል፡፡ ሶፋ ወንበር ላይ ጋደም እንዳልኩ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡
ከእንቅልፌ የነቃሁት ቡና ፈልቷል ጸበል ጸሲቅ ቅመስ ብለው ሲቀሰቅሱኝ ነው፡፡ ወዲያው “ገብረ ሚካኤል” የሚል ድምፅ ሰማሁ የንስሐ አባቴ ናቸው፡፡ “በል ንቃ እንጂ ምነው? አመመህ እንዴ ? አሉ” ተነስ በል ያዝ “እንካ በረከቱን ውሰድ ” ብለው የተቆራረሰ ዳቦ ያለበት ሳህን የያዘ እጃቸውን ዘረጉልኝ፡፡ ዳቦውን ለማንሳት ተንገዳግጄ ቆምኩኝ፡፡ የእንቅልፍ ድብርት እንዲለቀኝ መታጠቢያ ቤት ገብቼ ታጠብኩኝ፡፡ አሁን በመጠኑ ነቃሁ፡፡
የንስሐ አባቴን በቅጡ ሰላምታ እኳን ሳልሰጣቸው “ዛሬ የሆነ ጥፋት ያጠፋሁ ይመስለኝል ለወትሮው የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በማከብርበት ወቅት ይሰማኝ የነበረው መንፈሳዊ ደስታ ሁሉ ርቆኝ በዓሉን በህመም አከበረኩት” አልኳቸው፡፡ የንስሐ አባቴም “አታስለምድ አትከልክል” ይላሉ አባቶች “ካስለመድከው መንፈሳዊ ተግባር ያስቀረህው አለ እንዴ?” አሉኝ፡፡ አረ በፍጹም ጸበል ጸዲቁም ከተለመደው የበለጠ ሆኗል አስራቴንም ትናንትና ከፍያለሁ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኑ ሊያሰራው ላቀደው መጠለያ የተወሰነ ወጪ ይሸፍናል ብዬ እያሰብኩኝ ነበረ አልኩአቸው፡፡ በመሀል አቋረጡኝ እና “ለመሆኑ ስንት ብር ነው?” አሉ “ሦስት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ብር ነዋ ” አልኩ፡፡
እግዚአብሔር ይመስገን በርትተህልኝል ሥራህ ሁሉ ተባርኮልሀል አሉ፡፡ ለመሆኑ ደረሰኝ አስቆረጥክ? ሲሊ ጠየቁኝ፡፡ እንዴታ አባ “ለአዲሷ ገንዘብ ያዥ ወዲያው ነው ያስቆጠርኩት” አልኮቸው፡፡ “እስቲ የታለ” አሉ ከሱሪዬ ኪስ ውስጥ ደረሰኝ አውጥቼ ሰጠዋቸው፡፡ ደረሰኙን ገና ሲመለከቱት በድንጋጤ “እንዴ እንዴ ሦስትመቶ ሺህ ሰማንያ አምስት ሺህ አይደለ እንዴ ከፈልኩ የምትለኝ ደረሰኙን አይተህዋል ልጄ በቁጥርም በፊደልም የተጻፈው ሰማንያ አምስት ሺህ ነው፤ እንዴ ስሙም እኳ ገብረሚካኤል ሳይሆን ኃይለሚካኤል ተብሎ ነው የተጻፈው”ብለው መስቀላችው ከፍ አድርገው አማተቡ፡፡
በህመሜ ላይ ይህ አስደንጋጭ ዜና ጭው የሚል ስሜት ተሰማኝ መረጋጋት አቃተኝ በድንጋጤ ባለሁበት ፈፍዤ ቀረሁ፡፡ “ምንው ልጄ ደረሰኙን አይተህ አትቀበልም ነበር አሉ?” በመገረም፡፡ አይ “አባ በጣም ቸኩዬ ስለነበር ብሩንም ሳላስቆጥር ነው፤ በዛላይ ሰዓቱ ሲመሽ የባንክ ገልግሎት ዝግ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን ይዥ መጣሁ” አልኳቸው፡፡ አይ ልጄ “ጊዜው እኳ ከባድ ነው ቅዱስ ሚካኤል ቤቱን እየጠበቀ ነው እንጂ ቡዙ ቀማኛ፣ ወንበዴ አለ ” ብለው ቁና ተነፈሱ፡፡ ኮስተር ብለው “በል ልጅ የሆነ ነገር የተሠራ ኃጢአት አለ ለማንኛውም ቤተ ክርስቲያን ሄደን እናጣራ”ብለው ተያይዘን ተጎዝን፡፡
አሁን ውስጤን ይሰማኝ የነበረው ድካም ፍርሀት በሙሉ ከእኔ እርቋል ተሳስሮ የነበረው ሰውነቴ ተፍታቷል፡፡ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተጠጋን ቁጥር ዛሬ ከእኔ እርቆ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግን አብሮኝ የነበረ መንፈሳዊ ሀሴት ይሰማኝ ጀመር፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ቢሮ ከንሥሐ አባቴ ጋር ገባን፡፡ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ጋር ቀረቤታ ነበረን አንዳንዴም ለቤተክርስቲያኑ በአስቸኳይ የሚያስፈልግ ነገር ሲኖር ደውለው ያዙኛል፡፡ ቡራኬ ተቀብለን ተቀመጥን የሆነውንም ነገር ሁሉ ነገር ናቸው፡፡ በጥሞና አዳመጡኝ እና ደረሰኙን ትክ ብለው ተመለከቱት፡፡ ደግመው ደጋግመው አዩትን “ይሄነገር ሞዴል ሰላሳ ነው እንዴ አሉ? ምነው ቁጥሩ ፈዘዘብኝ ” ብለው ስልኩን አንስተው የቁጥጥር ክፍል ባለሙያውን ጠሩት፡፡ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ከመቀመጫቸው ተነሱ አንገታቸው ላይ የደረቡትን ጥቁር ልብስ አውልቀው ጠረጴዛ ላይ አስቀመጡ የቅዱስ ሚካኤል ያለህ ምንዐይነት ጉድነው በማለት አዘኑ ፊታቸው ቀላ ተኮሰታተረ፡፡
የቤተክርስቲያኑ የቁጥጥር ባለሙያ መጣና በፊታቸው ቆመ “ከሂሳብ ሹሙ ጋር ሆናችሁ ከትናንት ጀምሮ በደረሰኝ የገባውን ገቢ አሁኑኑ አሳውቁኝ ደረሰኛችሁን ይዛችሁ ኑና እዚህ እኔ ፉት ሥሩ” አሉ፡፡ ቁጥሩ አባታችን “ግማሹ ደረሰኝ የዕለት ገንዘብ ሰበሰሳቢዋ ጋር ነው” አለ፡፡ አሰተዳዳሪውም ቆጣ ብለው “እሷንም ፈልጋችሁ አንድ ላይ ኑ ”ብለው ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ እነርሱ ወጣ እንዳሉ ስልካቸውን አነሱና የጥበቃ ኃላፊውን ጠሩት ወዲያውኑ መጣ፡፡ የጥበቃ ኃላፊውን መስቀል አሳልመውት ወደ ጆሮው ጠጋ ብለው የሆነ ነገር በሹክሹታ ነገሩት እሺ ብሎ ወጣ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ “ለመሆኑ ገንዘብን የተቀበሎት ማነው”? ብለው ጠየቁኝ፤ አባታችን አዲሷ ሴቷ ገንዘብ ያዠ ናት” አልኩኝ ፡፡ በምን ሰዓት ነው አሉ ? ወደ ማታ ላይ አሉና መለስኩኝ ፡፡ ጥያቄያቸውን ቀጠሉ “ገንዘቡን ስታስረክብ አብሮዎት ማን ነበር?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ “አረማንም አልነበረም ብቻዬን ነበረኩኝ” አልኩኝ፡፡ ቆይ እሺ “ደረሰኙ በሌላ ሰው ስም ሲፃፍ ለምን ዝም ብለው ተቀበሉ?” አሉኝ፡፡ ወዲያው አስተውዬ አላየሁትም አልኳቸው ፡፡ ሌላ ጥያቄ ሳይጠይቁኝ ቁጥጥሩ እና ሂሳብ ሹሙ መጡ፡፡
ሂሳብ ሹሙ “እስከ አሁኑ ሰዓት በደረሰኝ የገባዉ ገንዘብ ከመቶ ሃያ ሺህ ብር በላይ ነው” አለ፡፡ አስተዳዳሪው ተቆጥተው “እርሱን አይደለም የጠየኩህ ከትናንት ጀምሮ በተቆረጠውን ደረሰኝ፣የገባውን የገንዘብ መጠን፣ ያስገባውን ሰው ስም ፣የደረሰኝ ቁጥር በቅደም ተከተል በነጭ ወረቀት ላይ ጻፉልኝ ” አሉ፡፡
በሩ ተንኳኳ የቤተከርስቲያኑ ጸሐፊ እና የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር ነበር የመጡት፡፡ አስተዳዳሪው መጣችሁ ለአስቸኳይ ጉዳይ ፈልጋችሁ ነበር አዳራሽ ሆነን እናውራ ብለው ተነስተው ወጡ፡፡
ሂሳብ ሹሙ እና ቁጥጥሩ መረበሽ ይታይባቸዋል፡፡ ሂሳብ ሹሙ በጎሪጥ ተመለከተኝ፡፡ እኔም ፍጥጥ ብዬ አየሁት እና “ለመሆኑ የእለት ገንዘብ የምትሰበስበዋ ወዴት ሄደች አልኩት” ቆጣ በዬ፡፡ እርሱም በተራው “እኔ እንጃ አላውቅም” አለ በአጭሩ፡፡ የንስሐ አባቴ ብዙ የሚያውቁት ነገር ያለ ይመስለኝል መስቀላቸውን በእጃቸው እየመቱ ዝም ብለው ቁጭ ብለዋል፡፡ ሂሳብ ሹሙ ከደረሰኙ ላይ የገለበጠውን የገቢ መጠን በዝርዝር አስቀምጦል አንደኛ ሁለተኛ እያለ እስከ ሃያ መድረሱን ለቁጥጥሩ ይነግረዋል፡፡
በሩ ተከፈተ የቤተ ክርስቲያኑ አሥተዳዳሪ የሰበካ ጉባኤው አባላት ጸሐፊው ሆነው መጡ አስተዳዳሪው የተመዘገበውን የደረሰኝ ውጤት ለማየት ጎጉተዋል፡፡ ገና ሳይቀመጡ የመዘገብከው የታለ ብለው ተቀብለው ማንበብ ጀመሩ አንደኛ የገቢ መጠን አምስት ሺህ ብር ሁለተኛ ሦስተኛ እያሉ እስከ ሃያ ድረስ አነበቡ፡፡ ሦስት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ብር የሚል ገንዘብ ደረሰኙ ላይ አልተመዘገበም፡፡ ይህን ስሰማ ደነገጥኩኝ እና ላብ አሰመጠኝ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ከጠረጴዛቸው ስር ያስቀመጡትን ደረሰኝ ብድግ አድርገው እያሳዩ ይህን ደረሰኝ ማነው የቆረጠው ቁጥሩ 0012 ይላል ብሩስ የት ደረሰ አሉ፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር በተቃጠለ ስሜት ቁጣ ቁጣ እያላቸው “የምትጠቀሙበት የደረሰኝ ቁጥር ከስንት ነው የሚጀምረው” ቡለው ቁጥጥር ክፍሉን ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ “አሁን እየተጠቀምንበት ያለው ከ 0705 ጀምሮ ነው” ብሎ መለሰ፡፡
አስተዳዳሪው “ከያዛችሁት ዝርዝር ውስጥ ስምንት መቶ ሃምሳ ብር የሚል የሰማው መሰለኝ እርገጠኛ ለመሆን እስቲ ዝርዝሩን እዩት” አሉ፡፡ ሂሳብ ሹሙ ወረቀቱን ተመልክቶ አዎ አለ፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበሩም እሺ በማን ስም ነው የተቆረጠው ?አሉት ሂሳብ ሹም መለሰ በገብረ ሚካኤል ነው አለ ፡፡ በሆነው ነገር ሁሉም ተገርመው አዘኑ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪው በቁጣ “እዚህ ቤት በሁለት ደረሰኝ በመጠቀም ወንጀል እየተሰራ ነው፡፡ የሚካኤልን መገበሪያ ሰርቆ የበላ ሳይለፈልፍ አይቀርም እንዲሉ አበው ቅዱስ ሚካኤል ደግሞ በዕለተ ቀኑ በዓመተ ክብሩ ሌባዉን እያጋለጠ ተአምራቱን አየሠራ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ገንዘብ የሚሰርቅ የይሁዳ ቢጤ የምዕመናንን ገንዘብ የሚዘርፍ ሌባ ማነው”በማለት በቁጣ ተናገሩ፡፡ አስተዳዳሪው “ለዕለት ገንዘብ ሰብሳቢዋን ስልክ ደወላችሁ” ብለው ጠየቁ ፡፡ “ተደውሎላት ቶሎ እመጣለሁ ብላለች” አለ ጸሐፊው፡፡
በሩ ተንኳኳ የጥበቃ ኃላፊው ነው የተጠሩት መጥተዋል አለ ለአስተዳዳሪ መልካም መጣሁ አንዴ ጠብቁኝ በላቸው አሉት፡፡ የጥበቃ ኃላፊ በሩን ሊዘጋ ሲል የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢዋ መጣች መስቀል ተሳልማ ቁጭ አለች፡፡
የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበር እኔ ልቅደም በሚል ፈጠን ብለው “እንዴት ዋልሽ ለአንድ ጉዳይ ፈልገንሽ ነበር ” አሏት፡፡ ገንዘብ ተቀባይዋ ሴት ኳስተር ብላ “ ለምን ነበር” አለች፡፡ ሊቀመንበሩ ቀጥለው “እኝህ ወንድ ማችን እዚህ ደብር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናች በገንዘባቸው በጉልበታቸው አገልጋይ ናቸው፡፡ ትናንት አንቺ ዘንድ መጥተው ገንዘብ ሲያስገቡ በስም ተሳሳተና ኃይለሚካኤል ተብሎ ደረሰኝ ተቆረጠላቸው በዚህ ቅር ተሰኝተው ነው፡፡ ስለዚህ ተስተካክሎ ደረሰኝን እንዲቆረጥላቸው ደረሰኙን አምጨውና እዚሁ ሁላችንም ባለንበት ተሰርዞ ሌላ ደረሰኝ ይቆረጥላቸው” አሉ፡፡ በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር የንግግር ብልሀት ሁላችንም ተገረምን አዋ ብለን ደገፍ ናቸው፡፡
እኔም ቀጠል አድርጌ “በእውነቱ ከሆነ እኔም የክርስትና ስሜ ተቀይሮ ደረሰኝ በመቆረጡ በጣም አዝኛለሁ አልኩ፡፡ የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢዋ አንደበቷ ተሳስሮ ግራ በመጋባት ስሜት ተቁነጠነጠች እና “የካዝና ቁልፍ አልያዝኩም ” ብላ መልስ ሰጠች፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር “እንዴ ደረሰኙም እንደ ብሩ በካዝና ነው እንዴ የሚቀመጠው” ሲሏት “የኮመዲኖ ቁልፍ ” ማለቴ ነው አለች፡፡ ኮሞዲኖው ተሰብሮም ቢሆን ደረሰኙ መውጣት ስላለበት ከጥበቃ ኃላፊው ጋር አብረሽ ሂጂ ተባለች፡፡
ከቢሮው ስትወጣ ሁለት ዩኒፎርም የለበሱ ፖሊሶች ጠበቋት፡፡ ፖሊሶቹን ስታይ “ለምንድ ነው የመጡት ስትል በፍርሀት ሆና ጠየቀች፡፡” ፖሊሶቹም የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በመጠርጠሩ ነው ብለው ወደ ቢሮዋ አብረው ሄዱ፡፡ ቢሮዋ ሲከፈት የደረሰኝ ጥራዝ እና ጥሬ ገንዘብ ሃምሳ ሺህ ብር ተገኘ፡፡ ከፖሊሶቹ ጋር ተመልሳ ወደ ስብሰባው ቦታ መጣች፡፡ የሰበኮ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር ጥያቄአቸውን ቀጠሉ ከገብረ ሚካኤል ገንዘብ ተቀብለሻል? አሉአት አዎ ብላ መለሰች፡፡ ምን ያህል? አሉዋት ሰማንያ አምስት ሺህ ብር ብቻ ለእርሱም ደረኝ ተቆርጦላቸዋል አለች፡፡ ገንዘቡ የት አለ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢ ተደርጎል ለማን ሰጠሽ “ለሂሳብ ሹም” አለች፡፡ የቆረጥሽው ደረሰኝ የቤተክርስቲያኑን ነው ማለት ሞዴል ሰላሣን ነው ተባለች መልስ ሳትሰጥ አቀረቀረች ፡፡
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እስቲ ገብረሚካኤል ስንት ብር ነው ይዘህ የመጣህው ዝም አትበል ተናገር እንጂ አሉኝ፡፡ የሆነውን ነገር ማመን አቅቶኝ ግራ ገባኝ እኔ የብዙ ጊዜ የተጠራቀመ ስለነበር ብሮዬ ከሂሳብ ሠራተኛዬ ጋር ሆኜ ገቢዬን አስልቼ አንድ አስረኛውን ሥስት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ብር በሁለት ፌስታል ነው እንደተለመደው ያመጣሁት እንዲያውም ቸኩያለሁ አልቆጠርኩትም ብዮ ተናግራለሁ በወቅቱ ስልክ እያወራሁ ደረሰኙን ተቀብዬ ኪሴ ውስጥ ከትቼ ብቻ ሳላየው ሄድኩኝ ብዬ በከፍተኛ ቁጣ መናገር ጀመርኩኝ፡፡
የሰባካ ጉባኤ ሊቀመንበሩ በመካከላችን ፖሊሶችም ስላሉ የዕለት ገንዘብ ያዥ እና ሂሳብ ሹም ለፖሊስ ቃላቸውን ይስጡ፡፡ ፖሊሶች የሚፈልጉትን ማስረጃ በሙሉ ወስደው ምርመራ ያድርጉ፡፡ ለቤተክርስቲያን ለሚመለከታቸው አካላት ቃለጉባኤ ተፈራርመን ሁኔታውን በደብዳቤ እናሳውቅ አሉ፡፡ በዚህ ሀሳብ ሁሉም ተስማሙ፡፡ የእለት ገንዘብ ያዥዋ የነገሩን ቁርጥ መሆኑን ስታውቅ እያለቀሰች ተሳስቼ ነው የልጆች እናትነኝ እባካችሁ ኑሮን ለማሸነፍ ነው እያለች ተርበተበተች ማልቀስም ጀመረች ሁሉንም አላጠፋሁትም ግማሹ አለ የሂሳብ ሹሙ ነው ይህን ዘዴ የነገረኝ እያለች ቡዙ መለፍለፍ ጀመረች ፖሊሶቹ አይዞሽ ቃልስን ብቻ ነው የምትሰጪው እያሉ ይዘዋት ሄዱ፡፡
በሆነው ነገር በጣም አዘንኩ ሌብነትን ወንጀልን ተጠይፌ አይሆንም በንፁህ እጄ ሠርቼ ማግኘት አለብኝ በማለት ያሳለፍኳቸው የድህነት ጊዜያት አስታወስኩ፡፡ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት በእግዚአብሔር ቸርነት የዚህን ዓለም ኑሮን ለማሸነፍ የማደርገው ፍልሚያ ትቼ ለሚበልጠው ዘላለማዊ ተስፋ የእግዚአብሔር መንግስት የምሮጥ ሆንኩኝ፡፡ የዚህ ዓለም ሀብት ከንቱ እንደሆ እግዚአብሔርን ከቀረብኩት ጊዜ ጀምሮ ተረድቻለሁ ፡፡ ገንዘብ ዘላለማዊ ሕይወት መዘጋጃ መሳሪያ መሆኑን ስለተረዳሁ ሳገኝ ለችግረኞች ስሰጥ አስራቴን ሳወጣ የቅዱሳን መታሰቢያ ሳከብር የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ስረዳ የተቸገረን ስጠይቅበት የቀደመውን ያህል ብዙ ሳልደክም ሕገ እግዚአብሔርንም ሳልጥስ በቀላል ድካም ብዙ በረከት አገኘው፡፡
ኑሮን ለማሸነፍ በምሮጥበት ጊዜ የስኬት መንገድ በጠፋኝ ሰሞን ምክርን ይለግሱኝ የነበሩ ወዳጆቼን ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ኑሮን አሸንፌ በብዙ መልኩ ውጤታማ የሆነ የበረከት ኑሮ ስኖር እኔም በተራዮ የስኬቴ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር መተዋወቅ እንደሆነ እንግራቸዋለሁ፡፡ ሥራ ቦታዬ በመጡ ቁጥር በየግድግዳው ላይ በፍሬም የለጠፍኮቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያሳየሁ ማብራሪያ እሰጣለሁ፡፡ በተለይም አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግስት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል ማቴ 6፥33 የሚለው የወንጌል ቃል እንዲሁም አንተ የመረጥከው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልከው ምስጉን ነው ከቤትህ በረከት እንጠግባለን፡፡ የሚለው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር 65፥4 በመጥቀስ እመሰክርላቸዋለሁ፡፡
ዛሬ በቅዱስ ሚካኤል በዓል ከዋዜማው ጀምሮ በሆነው ተአምራት ይበልጥ ወደራሴ ተመለከትኩኝ፤ ራሴን ወቀስኩበት ትምህርት አገኘሁበት፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ባደረኩት ትንንቅ እግዚአብርሔርን ቀረብኩት አወቅኩት፡፡ ይበልጥ ስቀርበው የዚህ ዓለም ገንዘብ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ብቸኛው የኑሮ ስኬት የተቃና ሕይወት መንገድ እግዚአብሔርን መቅረብ ማወቅ፤ ሕጉን እና ትእዛዙን አክብሮ መስራት መሆኑን ተረዳሁ ሰዎች ይህን ባለመረዳት ከእግዚአብሔር በልዩ መንገድ በተለያየ ስፍራ ይሰርቃሉ በረከታቸውንም ያጣሉ፡፡
በ ያዕቆብ ሰንደቁ
የካቲት 29 /2014
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ