ቅዳሜ 2 ኤፕሪል 2022

ወግ በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን የታሪኩ መጨረሻ እና ክፍል ሦስት

 

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

የታሪኩ መጨረሻ እና ክፍል ሦስት

 ገዳም ስደርስ አስቀድሜ በሕልሜ ያየሁት ቤተክርስቲያን ሕንፃ አገኘሁት፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ ሥራህ ድንቅ ነው በዬ አመስግኜ ዘወር እንዳልኩ “የገዳሙ መናንያን እግሬን ለማጠብ፣ እቃዬን ለመቀበል  የሚበላ ዳቤ ለማዘጋጀት ተሯሯጡ፡፡ ጸሎት አድርሼ ቤተ ክርስቲያኑን ዞሬ ተሳልሜ ስጨርስ ተቀብለው የማርፍበት ቦታ ሰጡኝ፡፡

የገዳሙ መናንያን ትናንት ቀን ብዙ እንጀራ ሲጋግር እና ወጥ ሲሠራ የነበረው ረድ የጀመረውን ሥራ አርጦ መጥፋቱ አሳስቧቸው ለገዳሙ አበምኔት ተነገሯቸው፡፡ አበምኔቱ ደንግጠው ትልቁን የገዳሙን ደወል አስደወሉ፡፡ መናንያኑን ሲሰበሰቡ “ ወንድማችን ረድ የጀመረው ሥራ አርጦ ስለጠፋ የተጀመረው የገዳሙ ሥራ እንዳይረጥ ተባብራችሁ በረድ ፋንታ ሆናችሁ ሥሩ፡፡ የተፈጨው እህል ትንሽ ስለሆነ ቡዙ ኩንታል መፈጨት አለበትና አደራ በየተራ ፍጩ፡፡ የተቀራችሁ ደግሞ ረድ ጾም እና ተጋድሎ አብዝቶ በገድል ብዛት አሞት አንድ ቦታ ወድቆ እንዳይሆን በየቦታው በየሥርቻው ፈልጉት ብለው አዘዙ፡፡

የገዳሙ አበምኔት የረድ መጥፈት በጣም አስጨነቃቸው፡፡ በሰርክ ጉባኤ ላይ ከጸሎት በኋላ “ልጄን የበላ አውሬ አልጮህ አለ፣ ገዳማችን ተጎዳ ረድኤቱን በረከቱን አጣ እያሉ ያዝናሉ ፡፡ ሀዘናቸውን ሳይ ይህንን ጭንቀት ስሰማ በጣም አዝኜ “በቃ ለምን እውነታውን አልነግራቸውም ብዬ አሰቡኩኝ፡፡ ግን ደግሞ መልሼ አሰብ ሳደርግ “ለማንም እንዳትናገሪየሚለውን ማስጠንቀቂያ ሳስታውስ ፈራሁ፡፡ ደግሞስ “የወደፊቱም ኑሮዩ በዚሁ ገዳም አይደል እንዴ የሚቀጥለው እንዴት ብዬ ይህን መናገር እችላለሁ? ብዩ በትምህርተ መስቀል አማትቤ ዝም አለኩኝ፡፡

በአባ ሳሙኤል ገዳም ሰባተኛ ቀን ሞላኝ፡፡ ከሌሎች ገዳም የበለጠ መንፈሳዊ በረከት ያገኘሁበት ስለሆነ መንፈሳዊ ደስታ ተሰሞቶኛል፡፡ ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል አጽማቸው ያረፈበት ቦታ ማታ ማታ ሄጄ እጸልያለሁ፡፡ “ አባቴ በበረኮቶት ይባርኩኝ ወደ ፈተና እንዳልገባ ጠብቁኝ፣ ዲያብሎስን ድል የማደርግበትን ኃይል ስጡኝ እያልኩኝ እማፀናለሁ፡፡ የረድ መጥፋት የገዳሙ መናንያን መነጋረሪያ ነቱን ቀጥል፡፡ ከማንም ሰው ጋር በዚህ ጉዳይ ፈጽሞ አላወራም ሁሉንም ነገር በልቤ ይዥዋለው፡፡

የገዳሙ አበምኔት ብራኬ ለመቀበል መስቀል ለመሳለም ሲሄድ እንግዳ በመሆኔ ይሁን በሌላ ምክንያት በትኩረት ያዩኛል፡፡ እኔም “ያየሁትን ምስጢር ያውቁ ይሆን? እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ እስከመቼ ይሆን ? ይህ ምሥጢራዊ መንፈሳዊ ትዕይንት ለማንም ሳልናገር የምኖረው እያልኩኝ ከራሴ ጋር አወራለሁ፡፡ ለካ ምሥጢር መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ሱባኤ (ሰባት ቀን) ማለቴ ነው በሰላም በማጠናቀቄ መንፈሳዊ ደስታ ተሰማኝ፡፡ የዲያቢሎስ ውጊያ እንደማያርጥ ባውቅም ለዛሬ የተለመደውን ያህል ጸሎት ለማድረግ ድካም ተሰማኝ፡፡ ሰው ደካማ ፍጥረት ነው ለዛሬ የተለመደው ጸሎቴ ስግደቴን ልተወው ብዬ ተኛሁ፡፡ ጠዋት ስነሳ ሰውነቴ ተሳሰረ አእምሮዬ ደነዘዘ፡፡ ቀኑን ሙሉ እንዲሁ በራስምታት፣ በቁርጥማት አሳልፌ ማታ የሰርክ ጸሎት ለማድረግ ወደ ቤተክርስቲያን ገባሁ፡፡ ገዳማውያኑ በተመስጦ ደስ በሚል ዜማ ጸሎት እያደረሱ እያለ ጸሎቱን የሚያውክ ነጎድጎዳዊ ድምጽ ተሰማ፡፡ ገዳሙን ማወክ የፈለገው ዲያብሎስ እያጎራ በጠበጠው፡፡ ደግነቱ የገዳሙ አበምኔት ስለገዘቱት ሌላ ምስጢር ሳይቀባጥር ዝም እንዲል ተደረገ ፡፡ ስነቃ ጸሎቱ አልቆ ስለነበር ሰዎች ደግፈውኝ ወደ ማደሪያዬ ሄድኩኝ፡፡

የገዳሙ አበምኔት እላዬ ላይ ያደረውን ጸላየ ሰናይ ኃይል ተመለክተው “በምን ቻለችው ይህን ክፉ ጠላት ብለው አዘኑ፡፡ ማምሻውን “ዮርዳኖስ በሚባለው ጸበል ጠዋት እንዳጠምቅሽ ነይ ብለው መልእክተኛ ላኩብኝ፡፡ የመጀመሪያው ቀን በሰላም ተጠመኩ፡፡ በሁለተኛው ቀን በጣም አመመኝ፡፡ ለሥስተኛ ቀን እንዳልጠመቅ ብዙ ጥረት ቢያደርግም በግድ በትግል ተጠመቅሁ፡፡ መቼም የሀሰት አባት ነው ተሰናብቻለሁ እለቃለው ብሎ ማለ ተገዘተ፡፡ ወደ ህሊናዬ ስመለስ ጠበል ጠጥቼ ገብቼ ተኛሁ፡፡

 ከምሽት ጸሎት ሰዓት ጀምሮ ዲያብሎስ ገዳሙን እጀግ በሚያሳዝን ሁኔታ አወከው፡፡ መናንያኑን መደብደብ ጸሎታቸውን ማረጥ መዝለፍ ለሊቱን ሁሉ ሲረብሽ አድሮ በነጋታው ጸበል እንዳልጠመቅ የሴቶች ልማድ (የወር አበባ) መጣብኝ እናም ጸበሉን መጠመቅ አቋረጥኩኝ፡፡

ከዚያች ቀን ጀምሮ አእምሮዩን አሳተኝ መናንያኑን መረበሽ፣ በመሳደብ፣ በመደብደብ ብዙ በጠበጥኩኝ፡፡ የሚመለከተኝ ሁሉ “ለገዳሙ ፈተና ሆኜ እንደመጣሁ ቆጠረኝ፡፡ጥቂት ወደ ራሴ ስመለስ ወደ ገዳሙ አበምኔት ቀርቤ “መዳኛዬ ይህ ገዳም እንደሆነ እና ከዚህ መውጣት እንደማልፈልግ ነገርኳቸው፡፡ “የሴቶች ልማዱ ከቆመ እኔ ራሴ አጠምቅሻለሁ አይዞሽ በፍቅር እና በትህት ተስፋ ሰጡኝ!” ከቀን ወደ ቀን አይምሮዬን እያሳተኝ እየባሰቡኝ ገዳሙን በሙሉ አወኩኝ፡፡ የገዳሙን አንድነት እና ጸሎት የሚፈትን ችግር በመግጠሙ ምክንያት ገዳሙን የሚያስተዳድሩ አባቶች በጉዳዩ ላይ ሰፉ ውይይት አደረጉ፡፡ በጉባኤው ቡዙ ክርክር ከተደረገ በኋላ “ለገዳሙ ሰላም እና አንድነት ሲባል ከገዳሙ ውጭ ባለ ሌላ ጸበል ቦታ ተጠምቃ ሲሻላት ትምጣ የሚል ውሳኔ ተወሰነ፡፡

የመጨረሻውን ውሳኔ የነገሩኝ የገዳሙ አበምኔት ነበሩ “ልጄ የገዳሙ አስተዳደር ከገዳሙ ለቀሽ እንድትወጪ ስለወሰነ ሌላ ቦታ ሄደሽ ጸበል ተጠመቂ አሉኝ፡፡ እንባዬ ዱቡ፣ ዱብ እያለ ሲቃ ያዘኝ፡፡ እዚህ ለመቆየት “ በቃ አትናገሪ የተባልኩትን ነገር መናገር አለብኝ በዬ አሰብኩ ነገርግን አፌ ላይ አድርሼ እንደገና ይህ ታላቅ ምስጢር ነው ቡዬ ዋጥኩት፡፡ እየተንተባተብኩኝ “እኔ መሆን የምፈልገው እዚሁ ገዳም ነው አልኩኝ፡፡ አበምኔቱም“ አይሆንም የሚሸኙሽ መናንያን መጥተዋል እኔም በር ድረስ እሸኝሻለሁ አሉ፡፡

ጎዜን ሰብስቤ “በውስጤ የያዝኩትን ምስጢር ልናገር ወይስ ይዤው ሊሂድ እያልኩ እያመነታው ወደ ገዳሙ በር ተጠቃው እኔን ከገዳም ማስወጣት አላማው የነበረው ዲያብሎስ መውጣቴን ለማፋጠን ብሎ እኔን ቀየረኝ እና የተለመደውን ስድቡን ረብሻውን ቀጠለ፡፡ የሚሸኙን መናንያን በመማታት፣ በመገፈታተር በመሳደቡ ጉልበቱን አሰባስቦ ይወራጭ ጀመረ፡፡ የለበስኩት ልብስ ከላዬ ላይ ተበጫጨቀ ሻንጣዬ ልብሴ ሁሉ ተበታተነ፤ በአካባቢው ግርግር በመፈጠሩ ለመተጋገዝ ብዙ መናንያን ተሰበሰቡ፡፡ አንድ አባት “እቃዋን ሰብስቡላት ተሸክማችሁ ከገዳሙ ውጭ ወዳለው ዋርካ ሥር አድርጎት አሉ፡፡ ወዲያው በፍጥነት ተሸክመው ከገዳሙ አስወጡኝ፡፡

የገዳሙ አበምኔት ግን በድንጋጤ ዐይናቸውን በተበታተነው ልብስ ላይ አሳረፉ፤የሚያዩትን ነገር ማመን አቃታቸው፡፡ ነጭ ነጠላ ቀጨን አረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ጥለት ያለው በላዩ ላይ አባ ሳሙኤል ዘወገግ ተብሎ ሥዕል የተጠለፈበት ነጠላ አዩ፡፡

 ይህ ነጠላ ለምወደው ልጄ ለረድ የሰጠሁት ነበር፤ እንዴት እርሷ ዘንድ መጣ? ምሥጢሩ ምንድ ነው፡፡ መናንያኑ ነጠላውን አንስተው ለገዳሙ አበምኔት ሰጧቸው፡፡ ነጠላው በክብር አጣጥፈው ምሥጢሩ ምንድነው? የሚለውን ለመጠየቅ ከገዳሙ ግቢ ውጭ ወዳለሁት ወደ እኔ ዘንድ መጡ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከገዳሙ ሳልወጣ በፊት ቢሆን ምንኛ ድንቅ ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ታሪክ ከሆነ እነሆ ሰባት ዓመት ሆነው፡፡ ከዲያቢሎስ ውጊያ ነፃ ባልወጣም፤ በእግዚአብሔር ቸርነት በመላኩ በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት በመንፈሳዊ ሕይወት እየተጋሁኝ ነው፡፡ ይህን የተረዳው ዲያቢሎስ እኔን ከሃይማኖት ለማሳት በምግባር ለማቆሸሽ አሕዛብ ለማድረግ ብዙ ሮጧል፡፡ ወደ ገዳሙ መንገድ ስጀምር፣ የአባ ሳሙኤል ስም ስጠራ በሕመም ይመታኛል፤ ወደ ቦታውም እንዳልደርስ ይፈትነኛል፡፡

ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ተመልሼ ለመግባት እና እግዚአብሔር በፈቀደልኝ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ገና ደጅ እየጠናሁ ነው፡፡ በዚህ በብሥራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ዕምነቱን ተቀብቼ፣ መስቀሉን ተሳልሜ ሕመሜ ሲቀልልኝ ፊቴን ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት አዞራለሁ፡፡ በምሄድበት ቦታ ሁሉ በምስጢር በጥንቃቄ “ስለ አሰቦት ገዳም ስለ ጻድቁ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ብዬ ስለምን እጁን የማይዘረጋልኝ፤ ምን ላድርግ የማይለኝ ሰው የለም፡፡ እንደዋዛ ከየሰዉ የሰበሰቡኩትን ገንዘብም ሆነ ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ በማጠራቀም ከረድ እንደተማርኩትም በማይታወቅ ሰው ለገዳሙ በሥውር እልካለሁ፡፡  

በዐይኔ የተመለከትኩት በብርሃን የተከበበ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል አስደናቂ ክብር ተፈታታኜን ዲያብሎስን እንደ ጉም ተኖ እንዲጠፋ ማድረግ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ያገለግል የነበረውን ረድን ተክቼ በስውር ገዳሙን አገልግዬ በረከት እንዳገኝ በሥጋዬ ላይ የመጣብኝ ሕመም፣ መከራ ሁሉ ለበጎ ሆነ፡፡ በህመሜ ምክንያት ገዳም ተመልሼ መግባት ስለማልችል፤ ሁሉም ለበጎ ሆኖ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ የኃጢአት መደምሰሻ ሥራ እንድሠራ ሌሎችም ምዕመናንን ከበረከቱ እንዳሳትፍ አደረገኝ፡፡  

ከገዳም ከወጣሁበት ከዚያች ቀን በኋላ ከገዳሙ መናንያን አንድም ሰው አግኝቼ አላውቅም፡፡ የበለጠውን ክብር ለማግኘት ጊዜያዊውን ፈተና መከራ ሁሉ ለመቋቋም ጠዋት ማታ በጸሎት እማጸናለሁ፡፡ ምኞቴ በአባ ሳሙኤል ገዳም በድንግልና ሕይወት ተወስኖ እያገለገሉ መኖር ነው፡፡ በእውነት አምናለው ይህ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ ውብ ሆኖ ይከናወናል፡፡ አሁን ረድን ተክቼ የገዳሙ አገልጋይ ሆኜ ወደ ቅዱሳን ስፍራ እኔም እንዲሄድ ከ ተሰወሩት ቅዱሳን ጋር በቅዱሳን ሀገር አብሬ መኖር እየናፈኩኝ በዚህ ከንቱ ዓለም እየኖርኩኝ ነው፡፡  

ተፈጸመ

 

 

ዓርብ 1 ኤፕሪል 2022

ወግ በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

 

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

ክፍል ሁለት

      እቤት ስገባ አመሻሽ ላይ ስለነበር ዘመዶቼ እስኪሰበባሰቡ ድረስ ጠበኩኝ፡፡ ውጭ ሀገር መሄድ እንደማልፈልግ ነገ ወደ ሐረር ለዛውም ወደ ገዳም እንደምሄድ ተናገርኩኝ፡፡ አነጋገሬ ቁጣ ቁጣ የሚል ስለነበር ዘመዶቼ ግራ ተጋብተዋል “ምነው? ምነካሽ? ለምን መጣሽ ለምንስ ተመልሰሽ ትሄጃለሽ?ሲሉኝ ቡሶቴ ሁሉ ተጠራቅሞ እንባዬ በቁሜ ተዘረገፈ፤መናገር አቅቶኝ በተንተባተበ አንደበት“በጠዋት መኪና አሳፍሩኝ ብዬ ወደ መኛታ ክፈሌ ገባሁ፡፡

አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ በ13ኛው ክፍለዘመን የተነሱ ከቡልጋ አውራጃ በኢቲሳ አካባቢ ከታወቁ ደጋግ ሰዎች ከአባታቸው ከእንድርያስ እና ከእናታቸው ከአርሶንያ የተወለዱ ጻድቅ ናቸው፡፡ ከአሥራ ሁለቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት ደቀመዛሙርት መካከለ አንዱ ናቸው፡፡ በዚህ ታላቅ ገዳም አጽማቸው አርፎ የቃልኪዳናቸውን በረከት ምእመናን ድኅነት ያገኙበታል፡፡

ከመናሐሪያ የተነሳው አውቶብስ ሐረር ደርሰን ወደ አሰበ ተፈሪ ከተማ እስክንደርስ ድረስ ሹፌሩ መዝሙር ያዘምር ነበር፡፡ በተለይ የዘማሪ እንግዳወርቅ ለአባ ሳሙኤል መዝሙር ማን እንዳዘዘው ባለውቅም ደግሞ ደግሞ ያሰማዋል፡፡ በጣም ተመስጬ እንባዬ እየወረደ አብሬ እዘምራለሁ ፦ …

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ መነኮስ ኃያል ቤቴ ግባ

ታስባርካለህ ሰውን ምድር ቅርብነህ አንተ ለእግዚአብሔር

 

የበረሀው መናኝ ግሩምነው ገድልህ

ምድርህን አስባርከሀል ከፍ አድርገህ በእጅህ

 

ታምርነው ገዳምን ላየ

ረድኤት በረከት ገበየ

 

ልጆችህ በገዳም ውስጥ ያሉት

ሳሙኤል ሳሙኤል ይላሉ

 

አዝማች

አይሻገርብሽ  እህልም ኃጢአት

ጌታችን ብሎታል ዋልድባን መሬት

 

ህርመት ይዘው ልጆቹ በሙሉ

ቋርፍ ነው ዘውትር የሚበሉ

 

አዝማች

የጣመ ያለመ አጥተን

ዮርዳኖስ ጠበል ምግብ ሆነልን

አዝማች 

አስኬማውን ለብሶ በገዳም ሲኖር

የትህትና አባት ነው የሕግ መምህር

 

ሃሌሉያን ሄደን

አይተን አብረን ካንተ እንኑር አልን

 እያለ ይቀጥላል ፡፡

አሰበ ተፈሪ ስደርስ በስተግራ የሚወስደውን መንገድ ይዥ 12 ኪሎሜትር ተጉዥ ከአውቶቡሱ ወረድኩኝ፡፡የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም በየት አቅጣጫ እንደሆነ እየጠየኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ከፊት ለፊቴ የሚታየውን ተራራ ጢሻውን መንገድ ሁሉ በሕልሜ ስላየሁት የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

አውቶብስ ውሰጥ የሰማሁት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የሚለው መዝሙር ያቃጭልብኛል፡፡ ፍርሀት የተቀላቀለበት ደስታ እየተሰማኝ ነጠላዩን ሰብሰብ አድርጌ ዳገቱን መውጣት ጀመርኩኝ፡፡ በዚያ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ብቻዬን ዳገቱን መውጣት ተያያዝኩት፡፡ ዛፉን ንፋስ ባወዛወዘው ቁጥር ድምፅ ስሰማ እደነግጥ እና አማትባለሁ፡፡ ትንሽ አለፍ እንዳልኩኝ ደስ የሚል ወረብ ይሰማል፤ እጣን ይሸታል፣ ጸናፅል ይንሿሿል፣ ከበሮ ይመታል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኑ የቀረብኩኝ መስሎኝ “እንዴ እንዲህ ቅርብ ነው እንዴ? እላለሁ ነገርግን የሚታየኝ ጫካ ብቻ ነበር፡፡ የወረቡ ድምፅ ግን ወደ እኔ እየቀረበ መጣ የሚመስጥ ልብ የሚማርክ ነበር እስከ አሁን አልረሳሁትም በልቤ ሰሌዳ ተጸፏል እንዲህ የሚል የግዕዝ ወረብ  

ደምፀ ወተሰብከ ውስተ ዓለም

ዓለም ውስተ ዓለም፣

ለሳሙኤል ኮከበ ገዳም ትሩፍ ዜና ምግባር፡፡

ተመስጬ ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ዳገት እየወጣሁ ከኋላዬ ኮቴ ተሰማኝ ደንግጬ መዞር አቃተኝ፡፡“አይዞሽ በርቼ አትፍሪየሚል ድምፅ ስሰማ ልቤ ተሰነጠቀ፡፡ እንደምንም ብዬ ወደ ኋላ ዞር ስል አንድ ሰውዬ “ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ነው የምትሄጂውቡሎ በትህትና ጠየቀኝ፡፡ ድንጋጤ ይሁን አላውቅም መልኩን አላየሁትም ነበር፡፡ ዝግ ባለ ድምፅ አዋ አልኩት፡፡ ላግዝሽ አለና በጀርባዮ ያያዝኩትን አነስተኛ ሻንጣ ከላዩ ላይ አወረደና ያዘው፡፡

በሁኔታው ግራ ገባኝ የምናገረው ጠፋኝ አሁን ሰውዩውን አስተዋልኩት ቀጭን አረንጎዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ያላት ነጭ ነጠላ ካለይ አድርጎል፡፡ ከውስጥ ያረጀ እና የነተበ በእሳት የተበላ ልብስ ለብሷል፡፡ ፊቱን ትኩር ብዬ ለማየት ፈራሁ፡፡ በጨረፍታ ሳየው ያ በሕልሜ ወደ አባ ሳሙል ዘንድ ይዞሽ ይሄዳል የተባለው ሰውዬ መሆኑን አወኩኝ፡፡ በነጠላው ውስጥ ያየሁት የአባ ሳሙኤል ስዕል ያለበት መስቀል ያንጸባርቃል፡፡

የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ከትናንት በስትያ መሀል መርካቶ ሳየው ባማረ የከተማ ልብስ፣በጥሩ ዘመናዊ መኪና፤ዛሬ ደግሞ በገዳም አሮጌ እራፊ ጨርቅ በባዶ እግር ብዬ ተገረምኩ፡፡ ለ አፍታ ዝም ካልኩ በኋላ መጠየቅ እንኳ አለብኝ ብዬ በፍርሀት “ወንድሜ አንተ ማነህ?በህልሜስ ያየሁ… ትናንት መርካቶ ያየሁ አንተነህ?አልኩት፡፡ አንገቱን ወደመሬት አቀርቅሮ “እኔ ረድ እባላለሁ የአባ ሳሙኤል ገዳም አገልጋይ ነኝአለኝ፡፡

ዳገቱን እየወጣን በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ እያለፍን ስለገዳሙ አመሰራረት ስለ አባ ሳሙኤል ገድል እና በረከት ይተርክልኝ ጀመር፡፡ ታሪኩን ሲተርክልኝ የተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ ደስ እያለኝ እሰማ ጀመር፡፡ ትረካውን ቀጠለ “በዚህ ገዳም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቸሩ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ስውር ቤተመቅደሶች አሉ፤ይህ ብቻም አይደለም በገዳሙ የከበሮ፣ የጸናጽል፣ የቅዳሴ ድምጽ ይሰማል፤ የተለየ የእጣን መዓዛም ይሸታል፡፡በጽሞና ለሰማው ልብን ወደሰማየ ሰማያት ይዞ የሚሄድ ሕብረ ዝማሬ ይደመጣል፡፡ በአባታችን በአቡነ ሳሙኤል ገድልም እንደተጻፋ እንደ ሔኖክና ኤልያስ ሞትን ሳይቀምሱ የተሰወሩ በርካታ ቅዱሳን መኖሪያ ታላቅና ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡በቦታው ላይ የተሰወሩ ቅዱሳን ለገዳማውያኑም ሆነ በዓለም ለሚኖሩ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው ለያዙ ሰዎች እየተገለጡ ይታቸዋል፤ መልእክት ይነግሯቸዋል አለኝ፡፡

ትረካውን ቀጠለ በዚህ በአሰቦት ገዳም የተሰወሩ ቅዱሳን አባቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ1934 ዓ.ም ከዋልድባ ወደዚህ መጥተው የተሰወሩ 500 ቅዱሳንከማኅበረ ሥላሴ ገዳም 1000 መናንያን መጥተው በዚህ ቦታ ተሰውረዋል፡፡አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ባሕታዊ ለ10 ዓመት ያህል በዋሻ ዘግተው ከኖሩ በኋላ በ1945 ዓ.ም ከሰው በመሠወር ከቅዱሳን ሕብረት ተቀላቅለዋል ፡፡የገዳሙ ላሞችን ለብዙ ዘመናት ሲጠብቁ የኖሩ ባሕታዊ ክፍሌ የተባሉ በ1964 ዓ.ም ተሰውረዋል፡፡ ባሕታዊ አባ በላይ ወ/ሚካኤል የተባሉ መነኩሴ ሐምሌ ሰባት ቀን 1972 ዓ.ም ከቅዳሴ በኋላ በመነኮሳት ፊት በይፋ በቅዱሳን ተጠርተው እንደተሰወሩ በወቅቱ በቦታው የነበሩ አበው ምስክር ናቸው፡፡ አለኝ እና ለአፍታ ዝም አለ፡፡

ይገርምሻል ብሎ ትረካውን ቀጠለ “ይህ ቦታ መካነ ስዋሬ የዕርገት የርቀት ቦታ ነው እያለ እየነገረኝ በተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ፡፡በፊቴ ደመና ግጥም አለ የብርሃን ምንጣፍ ተነጥፎ ይታየኛል፤ ሰማያዊ ጸናጽል ድምጽ ሰምቼው የማላውቀውን ዜማ ሰማሁ፡፡ ከፊት ለፊታችን ወደ እኛ የሚመጡ አንድ ታላቅ አባት ታዩኝ ገና ወደ እኛ እየቀረቡ ሲመጡ መቆም አቅቶኝ ወደ ምንጣፉ ተደፋው፤ ማየትም ሆነ ቀና ማለት አልቻልኩም፡፡ ድምጽ ይሰማኛል የሚያረጋጋ የታላቅ ቅዱስ አባት ብራኬ “አቤቱ ሕዝብሕን አድን ርስትህን ባርክ የሚል፡፡ ወዲያው የኪዳን ጸሎት ደረሰ፤ ቀጠለና ቅዳሴ ይቀደስ ጀመረ ፤ልዩ የእጣን መአዛ ልብን የሚያስደስት ሽቱ ይሸታል፡፡

አብሮኝ የመጣው ሰው “እሺ ጻድቁ አባታችን እያለ ሲናገር አባ ሳሙኤል እንደተገለጹ ገባኝ፡፡ ለእኔ አይታዬኝም ድምፃቸው ነው የሚሰማኝ እንዲህ አሉ “ በዛሬው ዕለት ይህን ቅዱስ ገዳም በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ ለዘመናት ሲያገለግለኝ የኖረውን ወዳጄን ወደ ቅዱሳን ስፍራ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ልጄ “በስውር የሠራውን መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ከሥላሴ ዘንድ በይፋ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀበልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሰው ያላወቀውን የጽቅ ሥራህን፣ በሥውር ያደረከውን ተጋድሎህን ሁሉ ሥላሴ አይተውል፤ሰማያዊ ዋጋም ተሰጥቶሀል እያሉ ይመርቁታል፡፡ እርሱም በትህትን “ይህ ለእኔ አይገባም ቅዱስ አባታች ገና መቼ አገለገልኩ ምኞት ፍላጎት ፍቅር ነው እንጂ ብዙ ሥራ ይቀረኛል እያለ በፍርሀት በትህትና ሲናገር ሰማሁ፡፡

እኔ በሰመመን ውስጥ ሆኜ መስማቴን ቀጠልኩ እንዲህ አሉት “ይህችን አጠገብህ ያለችውን ትንሽ ልጄን እንኳን ይዘሀት መጣህ፡፡ ዲያብሎስ ሊያጠፋት ይፈታተናታል፤ ነገርግን በጸሎ ታሸንፈዋለች ዋጋዋ ትልቅ ስለሆነ በዚሁ በአባ ሳሙኤል ገዳም ጸንተሽ ተቀመጪ ከቅዱሳን ጋር አብረሽ ዲያብሎስን ተዋጊው፤ በገዳም ጸንተሽ ደጅ ጥኚ፤ ጊዜው ሲደርስና ጠላት ሲወገድልሽ ብዙ በረከት ታገኚያለሽ በላት አሉት፡፡ በመስቀላቸው ሲባርኩኝ አይኔ በርቶ ማየት ጀመርኩኝ  ይሕን የዛሬውን ሰማያዊ ምሥጢር ማየትሽን ለማንም ሰው እንዳትናገሪ አደራ የረድን ነጠላ እንቺ በቦርሳ ይዘሽ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ሂጂ ነጠላው የእኔ በረከት ነው ወገብሽን ታጠቂበትብለው ባረኩኝ፡፡

የቅድሙ ደመና ወደ አጠገቤ መጣና በድጋሚ ከበበኝ በድጋሚ ዐይኔ ተከፈተና ማየት ጀመርኩ፡፡ ሁሉት ቅዱሳን መላእክት አብሮኝ ከመጣው ከረድ አጠገብ በቀኝ እና በግራ ቆመው ታዩኝ፡፡ ልክ መላእክቱ አጠገቡ ሲቆሙ ነጠላውን ወደኔ ወርውሮ ወደ ሰማይ ከፍ ሲል ታየኝ በግዘፈ ሥጋ ከፍ ከፍ እያለ ሲወጣ ተመለከትኩኝ ዐይኔን ተክዬ እየተመለከትኩኝ ደመናው ጭኖ ቀጥ አርጎ ወደ ሰማይ ወሰደው፡፡ ከነበርኩበት መንፈሳዊ ተመስጦ ነቃሁ የረድን ነጭ ነጠላ በእጄ ይዤለሁ፡፡ በሥርዓቱ እጥፍጥፍ አድርጌ ሻጣዬ ውስጥ ከትቼ ዳገቱን ጫካውን አርጬ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ጉዞዩን ቀጠልኩ፡፡

                  የታሪኩ መጨረሻ እና ክፍል ሦስት ይቀጥላል