ዓርብ 22 ጁላይ 2022

 



  በጥንት ሮማውያን ዘመን መልከ መልካም በውጊያ ስልቱ የታወቀ የጦር መኰንን ነበር፡፡ ገና በወጣትነቱ ጀምሮ የጦር ትምህርት ቤት ገብቶ በመማር ብዙ የጦር ሥልት ተምሯል፡፡ በእውቀቱ ከተማሪዎች በላይ የሆነ በደፋርነቱና በቆራጥነቱ የታወቀ በኢላማ ተኩስ ፣በውኃ ዋና ፣በጂዶ ፣በፈረስ ግልቢያ የተዋጣለት ስፖርተኛ በመሆኑ ዝናው የናኘ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አንድ እጩ የጦር መኰንን መማር የሚገባውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተምሮ በመተግበር ክብረወሰን ሰበረ፡፡

በወታደራዊ ትምህርት ቤት ሆኖ ስልጠናውን ሲወስድ ከአሰልጣኞቹ እና ሰልጣኞቹ ጋር ተግባብቶ ሥራውን ማከናወን ይቸገራል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ታዲያ ያልሰከነው አመሉ ነው ፡፡ የጀግንነቱን እና የዓላማ ጽናቱን ያህል አለመረጋጋቱ እና ወጣ ያለ ጠባዩ ደግሞ አስገራሚ ነው፡፡ ማናቸውንም ውሳኔ ስሜታዊ ሆኖ መወሰኑ ሀሳቡንም  በየጊዜው መቀያየሩ አይ አመል ያሰኛል፡፡ በነገሮች ላይ ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ በቆራጥነት መጽናት ወታደራዊ ችሎታ መሆኑን ቢማርም ቢያስተምርም እርሱ ግን ጽናት የሌለው አመለቢስ ነው፡፡ በንድፈ ሀሳብና በተግባራዊ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ቢኖረውም ወታደራዊ ሥነ-ምግባር ግን እጅግ ዝቅተኛ ነጥብ አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ምክንያት ከተማረበት ትምህርት ቤት ሳይወጣ ለረጀም ጊዜ በዚያው ሆኖ አዲስ ምልምል ወታደሮቸን ሲያለማምድ በተራ ሥራ ላይ ከረመ ፡፡

ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ጥብቅ በሆነበት ትምህርት ቤት አዲስ ተማሪዎችን ሲቀበል ሲያለማምድ ቢቆይም በስሜት ሆኖ የሚፈጽማቸው ጥፋቶች ለወቀሳ እና ለከሰሳ ብሎም ለቅጣት ይዳርጉታል፡፡ ባካበተው የወታደርነት ሙያ እጩ መኮንኖችን ቢያሰለጥንም እውቀት እንጂ ሥነ-ምግባርን አያስተምራቸውም፡፡ ያሰለጠናቸው ብዙ ሺህ ወታደሮች ተመርቀው ለወታደራዊ ማዕረግ በቅተው በጦርሰራዊቱ ልዩ ክፍል በሥራ ላይ ሲሠማሩ ስልጣን ማማ ላይ ሲቀመጡ እሱ ግንስሜታዊው አሰልጣኝ ” የሚል ስም ተቀጽሎለት ወዳጅ ሳያፈራ በአመለቢስነቱ ታዋቂ ሆኖ  አሠልጣኝ መኰንን ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡

በተለይ ለወታደር ወሳኝ የሆነውን ከስሜት ነፃ የሆነ ውሳኔ መወሰን እና በአቋም መጽናት ባለመቻሉ ሁሉም የሠራዊቱ አባላት ግራ ይገባቸው ነበር፡፡ ተማሪዎቹን በወታደራዊ ሰዓት ከሌሊቱ 8 0 0 (ሰአት) ይህን ተራራ ወጥታችሁ በዚህኛው ሸለቆ ወርዳችሁ ይህን ገዥ መሬት ተቆጣጠሩ ብሎ የወታደራዊ ልምምድ ትእዛዝ ያስተላልፋል ፡፡ አዳዲሶች ምልምል ወታደሮች በተባለው ሰዓት ለመድረስ ከእንቅልፍ ነቅተው፣ ጎዛቸውን ሰብስበውየክረምቱን ውሽንፍር ተቋቁመው፣ ዳገት ቁልቁለቱን ወርደው በዝናብ ታጥበው ገዥ መሬቱን ለመቆጣጠር ጥቂት ሲቀራቸው በሬዲዮ መልእክት ልኮ “ሰልጣኞቹን መልሷቸው” ብሎ ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ ወዲያው ፊሽካ ይነፋናወደኋላ ተመለስ ስልጠናው ቀርቷል” የሚል አስደንጋጭ መልእክት ይነገራል፤ የሠልጣኞቹ ሀሞት ፈሶ ጉልበታቸው ርዶ ድካማቸው ሁሉ ግቡን ሳይመታ ውሃ በልቶት ይቀራል፡፡

“ስሜታዊው አሰልጣኝ ” ከበላይ አለቆቹ ከበታች ሰልጣኞቹ ጋር ተስማምቶ ለመሥራት እንቅፋት የሆበትን ክፍ ዓመሉን እንዲተው ብዙ ተመክሯል፡፡ ወዳጆቹ ሁሉ በተደጋጋሚ አእምሮውን እንዲጠቀምበት ስሜታዊነቱን እንዲተው ምክንያታዊ ሆኖ ሥራውን እንዲሠራ፣ ሚዛናዊ ሆኖ እንዲያስብ፣ አንደበቱን እንዲቆጥብ ብቻ አመዛዝኖ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መክረውታል፡፡ እርሱ ግን የማይጨበጥ አቋሙንያልተረጋጋ ሰብእናውን ለማስተካከል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡

 “ስሜታዊው አሰልጣኝ ” ስሜቱንም፡- እንደ ፈረስ በፍጥነት በመጋለቡ መድረሻውን የማያውቅ የማይጨበጥ የማይታወቅ ሰብና ኖረው፡፡ ጠዋት እንደ ማር እንደ ወተት የጣፍጠ ንግግር ተናግሮ ያመሰገነውን ሰልጣኝ ወታደር ከሰዓት የጠዋቱን ሦስት እጥፍ አምርሮ ኮሦ ሆኖ ተሳድቦ ዘልፎ አሳዝኖት ይገኛል፡፡ በቀን ውስጥ ጠባዩ እንደ አየሩ ሁኔታ ይለዋወጣል፡፡ ስሜቱም በየሰዓቱ ይቀያየራል፤ አንዴ ደመናማ ፣አንዳንዴ ጭጋጋማ ሲነሳበት ደግሞ ዝናባማ ሆኖ ውሽንፍሩን ሲጥል፣ በረዶውን ሲያራግፍ ይውላል፡፡ የሮማ መንግስት ይህን  “ስሜታዊው አሰልጣኝ ” በወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ እስከመቼ ነው አስቀምጦ የሚያቆየው ብለው የጦር ሠራዊቱ ሁሉ ይማረሩበት ነበር፡፡

* * *

የሮማ ንጉሣዊ አገዛዝ ከብዙ ኃያላን ጣርነት ተከፈተበት፡፡  “ስሜታዊው አሰልጣኝ ”  እንዴት እኔ እያለሁ ሀገሬ ትደፈራለት ብሎ ከጦር ትምህርት ቤት ወጥቶ ወደ ጦር ግምባር ዘመተ፡፡ በጦርነት ዓውድ ውስጥ ሆኖ ለማመን የሚቸግሩ የጦር ፍልሚያዎችን በማድረግ ለሕይወቱ ሳይሰስት በእሳት ተፈትኖ ጀግንነቱን አሳየ፡፡ የሀገሩን ክብር ለማስከበር ጠላቶቹን ለማሳፈር በፈጸመው ጀግንነት ስሜታዊነቱ አመለቢስነቱ እስኪረሳ ድረስ የተከበረ የተደነቀ ሆነ፡፡ በፈጸመው ጀብዱ በአንዴ የኮለሌል መአረግ ተሰጠው፡፡

ጦርነቱ ተጠናቆ የሮማ መንግስት ወታደራዊ ጀብዱ ለፈጸሙት ወታደሮች የዕውቅና እና የሽልማት መርሐግብር አከናወነ፡፡ ለዚህ ጀግና ከኮለሌል ማዕረግ ወደ ብርጋዲየር ጄነራል ማዕረግ እድገትና ዋጋቸው ውድ የሆኑ በአልማዝ እና በወርቅ የተንቆጠቆጡ የጀግና ሊሻኖች የሀገሪቱ የክብር ሜዳሊያ ከንጉሡ እንዲቀበል ተደረገ፡፡

እድሜው እየጨመረ ልምዱ እየዳበረ ሲመጣ ነውጠኛ ዓመሉ እየሰከነ ደፍራሽ ስሜቱ እየጠራ መጣ፡፡ ንጉሡም ይህን አመሉን ቢያውቅም ረጅም ዘመን በታማኝነት ሀገሩን አገልግሏል በማለት ደረጃ በደረጃ ብርጋዲየር ጄነራል ወደ ሜጀር ጄነራል ከዚያም ሌፍተናንት ጄነራል በመጨረሻም ሙሉ ጀኔራል ማዕረግ ካገኘ በኋላ በክብር በጡረታ ከሠራዊቱ እንዲሸኝ አደረገው፡፡ 

 

* * *

በየዓመቱ ንጉሡ በዓለ ሲመት (የተሾመበትን በዓል) ከተለያዩ የዓለም ሀገራት እንግዶች ጠርቶ በድግስ በፌሽታ ያከብራል፡፡ በንጉሡ 60ኛው የንግስና በዓል ላይ መገኘት ክብርም ግዴታም ነው፡፡ በንጉሡ በዓለ ሲመት ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ ብዙ የጦር መኰንኖች ተጋብዘው ነበር፡፡ የንጉሡ ቤተሰቦች እና ወዳጆች በተሰበሰቡበት በዚህ ግብዣ  “ስሜታዊው አሰልጣኝ ” ጡረታ ላይ ቢሆንም ለሀገሩ በዋለው ውለታ እና በንጉሡ ዘንድ ባለው እውቅና በጄኔራል ማዕረጉም ጭምር የንጉሡን ግብዣ እንዲታደም በክብር ተጠራ፡፡  

ንጉሡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ንግግር ካደረገ በኋላ በይፋ የግብዥው ሥነ-ሥርዓት ተጀመረ፡፡ የንጉሥ ማዕድ ሰፊ ሆኖ ጠጁ ሲቆሮቆር፣ ወይኑ በዋንጫ ሲጠጣ፣ ጮማው ሲቆረጥ አመሸ፤ ሰፊው የየንጉሥ ግብር ቤት በደስታ ተናወጸ፡፡ ከቆይታ በኋላ የተፈቀደላቸው እንግዶች ንግግር የሚያደርጉበት ሰዓት ሲደርስ የተንጣለለው የንጉሡ አዳራሽ በሺህ የሚቆጠሩ እንግዶችን ቢይዝም በጸጥታ ተዋጠ ፀጥ ርጭ አለ፡፡ የመርሐግብሩ አጋፋሪ ከሌላ ሀገር የመጡ ልዑላን ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዞ ከሩቅ ሀገር የመጡ እንግዶች ደስታቸውን በየተራ መግለጸ ጀመሩ፡፡

በየተራ የሚደረገው ንግግር እንዳለቀ በጸጥታው መሀል “ስሜታዊው አሰልጣኝ ጀነራልከተቀመጠበት ተንደርድሮ ተነስቶ በፍጥነት መድረኩ ላይ ተገኝ፡፡ በዚህ ትልቅ ሥርዓት ባለው የንጉሥ ግብዣ እንዲህ አይነት ድፍረት በአንገትን ለመቀላት ሰይፍ እንደማስቀመጥ መሆኑን ያወቁት የጦር መኰንኖች በሙሉ በፍርሃት እና በሀፍረት ተሸማቀቁ፡፡ ንጉሡ በትዝብት አይን እያየ አጋፊሪውን በዐይኑ ጠቅሶ እንዲናገርፈቀድለት አለ፡፡ ጡረተኛው ስሜታዊው ጄኔራል በስሜት ሆኖ በሥካር መንፈስ በተኮላተፈ አንደበት “ከነገሥታት ሁሉ ከፍ ያለ የሮማ ንጉሡ ዓመት ይንገሥ ብሎ ማወደስ ጀመረ፤ ከዚያም በመድረኩ ላይ ወታደራዊ ሠልፍ እያሳየ ጎንበስ ቀና ቡሎ ወታደራዊ ሠላምታመስጠት ንጉሡን በማወደስ በምሥጋና ጎርፍ አደራሹን ሞላው” ታዳሚውም እየሣቀ በጭብጨባና በፉጨት አዳራሹን አደመቀው፡፡ ጄኔራሉ በዚህ ሳያበቃ ስሜቱ ያዘዘውን ሁሉ በመናገር ስሜት እና ሲቃ ተሞልቶ ከዓመታት በፊት በጦር ሜዳ የፈጸመውን ጀብዱ ያገኘውን ሽልማት በኩራት ዘርዝሮ አወራ፡፡ በአሰልቺ ንግግሩ ብዙዎች ቢታዘቡትም ቶሎ ሊያበቃ ግን አልቻለም፡፡ ከዚያም በአጋፋሪው ወደ መድረክ ወጥቶ አጠገቡ በመቆም አስወረደው፡፡

 ለወትሮው እንኳን ንጉሳዊ ሥርዓቱን በአደባባይ ማዋረድ ይቅር እና በትንሽ ጥፈትም የሚቆጣው ንጉሥ ሥሜታዊው ጄኔራል ዝም ብሎ መስማቱ ሁሉን አስደንቆ ነበር፡፡ የዚያን ቀን የእራት ምሽት እና የስሜታዊው ጄኔራል መዘላበድ የተመለከቱት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች “የእኛን ክብር ነው ያዋረደው” ብለው ተበሳጩ፡፡ የጄኔራሉ ስሜታዊነት በከተማው ሁሉ መነጋገሪያ ሆኖ ከረመ፡፡ ጄኔራሉ በንጉሥ ግብዣ ላይ ስሜታዊ ሆኖ ሲቀባጥር ንጉሡ ሳይቆጣ በዝምታ ማለፉ የጦር ሠራዊቱ በሙሉ “ጄኔራሉ የንጉሡ የቀኝ እጅ ቢሆን ነው እንጂ እንዴት በዝምታ ታለፈ ” ብለው አጉረመረሙ፡፡ ይህን የሠራዊቱን ሀሜት የሠማው ንጉሥ “ንጉሠ ነገሥቱን አወደሰ እንጂ ምንም አላጠፋም እንዲያውም ታማኝ ጄኔራል እርሱ ብቻ ነው ” ብሎ ከጡረታው ተመልሶ የቤተ መንግሥቱ የጥበቃ የበላይ ኃላፊ እንዲሆን ሾመው፡፡

* * *

በሮማውያን የዘመን አቆጣጠር ዓዲስ ዓመት በሚገባበት ሰሞን በአንድ ምሽት ንጉሡ ከወደዳቸው ጋር ጽዋውን የሚያነሳበት ቀን ነው ብሎ በአይነቱ ለየት ያል ትልቅ የእራት ግብዣ አሠናዳ፡፡ በግብዥው ላይ የሚታደሙት ሰዎች እነማን እንደሆኑ አልታወቀም፡፡ በሮማ ከተማ ከቤተመንግስት ሾልኮ የወጣ ወሬ ተብሎ ስለንጉሡ ግብዣ የተለያየ ግምት ተሰጠ፡፡ በሮማ ከተማ በስፋት የተናፈሰው ወሬ ንጉሡ ስልጣኑን ለአልጋ ወራሹ ከማውረሱ በፊት ሹመት ሊሰጥ ተብሎ ነበር፡፡ ገሚሱ ደግሞ ንጉሡ ሹም ሽረት በማድረግ አዳዲስ ባለሟል እና የጦር መኮንንችን ለመሾምስቧል ብሎ ደመደመ፡፡ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባል ስለ ንጉሡ ድግስ በሮማ ከተማ የሚወራው ወሬ የሁሉንም ትኩረት ሳበ፤ የሰሞኑ ወሬ ሆኖ መነጋገሪያ ሆነ፡፡

በሮማ ከተማ ወታደራዊ መኮንኖችም ሆኑ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች በጭንቀት ተዋጡ፡፡ ከሥልጣኔ እሻር ይሆን? የት ይሆን መውደቂያዬ ወይስ ለየትኛው ቦታ እሾም ይሆን? ብለው እንቅልፍ አጡ፡፡ ሹማምንቱ እና መሳፍንቱ ከሹመታቸው ሲሻሩ የሚያጡትን ጥቅማጥቅምና ክብር እያሰሉ ፊታቸው እየቀላ፣ ልባቸው እየራደ፣ ጨጎራቸው እያረረደምግፊታቸው እየጨመረ መጣ፡፡ እንሾማለን ብለው ያሰቡት ደግሞ በደስታ እየፈነደቁ የሹመታቸውን ምክንያት አድርገው በሚያዘጋጁት ግብዥ ላይ ማንን እንደሚጠሩሰዎች የስም ዝርዝር ይመዘግቡ ጀመር፡፡ ለደስታ መግለጫ ዝግጅቱም የሚያወጡትን ወጪ በማስላትም ተጨነቁ፡፡

የሮማ ከተማ ሥራዋን ፈታ ጠዋትም ማታም የምታናፍሰው ወሬ የንጉሥ ሹም ሽረት እና በዚህም ምክንያት ስለሚዘጋጀው የንጉሡ ግብዥ ሆነ ፡፡ የንጉሡ ግብዥ ቀኑና ሰዓቱ ታውቆ በየደረጃው በተለያየ ማዕረግ ጥሪው ወረቀት ተበተነ፡፡ መጥሪያ ወረቀቱ የደረሳቸው መጠራታቸውን በኩራት ሲያወሩ፤ ያልተጠሩት ደግሞ በሀዘን ተቆራመቱ፡፡ የሮማ ከተማ ወሬ ሁሉ እገሌ ወደ ንጉሥ ራት ግብዥ ተጠርቷል ወይስ አልተጠርራም ሆነ፡፡

ለወታደራዊ መኰንኖች የተዘጋጃ መጥሪያም ሆነ የድግሥ ቦታ የተለየ ነበር፡፡ ጥሪውም የማዕረግ እድገት እና ንጉሣዊ ሽልማት እንዳለበት ያሚያስረዳም ነው ተብሎ ተወራ፡፡ የንጉሥ መልዕክተኞችም ከተራ ወታደር አንስቶ እስከ ከፍተኛ የጦር አዛዥች ድረስ የተመረጡ ጥቂት ሰዎችን በየቤታቸው እየሄዱ የጥሪ ወረቀት ሰጡ፡፡

የግብዣው ሰዓት መድረሱ አይቀር የተመረጡት የጦር መኰንኖች የማዕረግ ልብሳቸውን ለብሰው ቤተመንግሥቱ በር ላይ ሲደርሱ አስተናባሪዎቹ በመጥሪያ ወረቀቱ መሰረት በየደረጃቸው እርሶ በዚሂኛው በር ይግቡ እርሶ ደግሞ በዛኛው እያሉ በክብር አስተናገዶቸው፡፡ ንጉሡን እንወደዋለን እሱም ይወደናል ብለው የሚያስቡት ሁሉ በተለያየ ደረጃ በንጉሡ ግብዣ ላይ ታደሙ፡፡

በመጠራቱ እርግጠኛ የሆነው ስሜታዊው ጄነራል የጥሪው ወረቀት ይደርሰኛል ብሎ ቀኑን ሙሉ ሲጠባበቅ ቢውልም ጥሪው ሳይደርሰው በመቅረቱ ተበሳጨ፡፡ ንጉሡ የማይወዳቸው የተጠሉ የበታች ወታደራዊ መኰንኖች በመጠራታቸውን ሲያይ ደግሞ ንዴቱ አይሎ ለምን አልተጠራሁም ብሎ ተቆጨ፡፡ የእራቱ ሥነ-ሥርዓት ሊጀመር ሰዓታት ሲቀሩት የጄነራሉ ስሜት እየጋለ መጣ፤ ራሱን መቆጣጠር ስላቃተውም በፍጥነት ወደ ቤተመንግስት ተጎዘ፡፡

ቤተ መንግስቱን የሚጠብቁት ወታደርች የጄነራሉ መቻኮል አይተው ረፍዶባቸው ነው እንጂ ዋና የንጉሡ ወዳጅ ስለሆነ የግብዣው ተሳታፊ ይሆናሉ ብለው ወታደራዊ ሰላምታ ሰጥተዋቸው አሳለፉቸው፡፡ በዋናው ቤተመንግስት በር ጠባቂ ወታደሮች የጥሪ ወረቀት እየተቀበሉ እንግዶችን ሲያስገቡ ጄኔራሉ ለመግባት ወደ ደጃፍ ተጠጉ  ወታደሮቹም እባኮን የጥሪ ወረቀት አሳዩን ብለው ጠየቁ ፡፡ መጥሪያ ወረቀት እንደሌላቸው ሲያስረዱትጌታዬ የጥሪ ወረቀት ከሌሎት በግብዣው ቦታው የሚቀመጡበት ወንበር ስለማይታወቅ መግባት አይችሉም” ብሎ ወታደሩ በትህትና አስረዳቸው፡፡  

ስሜታዊው ጄነራል ራሳቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ወታደሩን በቁጣማንን እንደምታናግር አታውቅም ማለት ነው ባቀናነው ቤተመንግስት በንጉሣችን ግብዥ አንተ ማን ሆነህ ነው እኔን የምትከለክለኝ እንዴትስ ግባ አትግባ ልትለኝ ትችላለህ” ብለው በቁጣ ደነፋበት፡፡ ወታደሩ የጄነራሉን ስሜታዊነት እና ቁጡነት ስለሚያውቅ ረጋ ብሎ     ጌታዬ ወደ እራቱ ግብዣ የተጠሩትን የስም ዝርዝር ላሳዮት ይህው ይመልከቱ፤ የእርሶ ስም ግን የለም ምንም ማድረግ አልችልም” አላቸው፡፡ ጄነራሉ የስማቸውን አለመኖር ሲያውቁ ጭራሽ ብስጭታቸው ባሰ፡፡ በቁጣማነው ይህንን አይነት አጸያፊ ተግባር ያደረገው? ምክንያቱስ ምንድነው? ብለው ተቆጡ ፡፡ ትሰማለህ ወታደር “ይህ ነገር በፍጥነት ይጣራልኝ አዝዥሀለሁ እኔ የንጉሡ ታማኝ ጄኔራል በመሆኔ ስሜ ከተራው ሰው ጋር መመዝገብ ላያስፈልግ ይችላል፤ ስለዚህም ለአለቆችህ በፍጥነት ሬድዮ አድርገህ አሳውቀኝ ”ብለው አንቧረቁበት፡፡

ጠባቂ ወታደሩ በሬዲዮ መገናኛ የጄኔራሉን መጠራት ጠየቀ የተሰጠው ምላሽቆይ ጠብቅ መልስ እንሰጥሀለንየሚል ነበር፡፡ በቤተመንግስቱ ጀጃፍ ጄኔራሉ ቆመው እያለ ብዙ ወታደራዊ መኰንኖች የጥሪ ወረቀታቸውን እያሳዩ ገቡ፡፡ የዚህን ጊዜ የጀኔራሉ ስሜት መስመር እየለቀቀ መጣ፤ ፊታቸው ፍም መሰለ ደማቸው ፈላ ፡፡ ወታደሩም የሬዲዮን መልዕክት መጥቷልጌታዬ እባኳትን ጥሪው እርሶን አይመለከትም ወደ ቤቶ ይመለሱአላቸው፡፡ ጄነራሉ ግን ነገሩን መቀበል አቃታቸው፡፡

ጄኔራሉ ፊታቸውን አኮሳትረው ከንፈራቸውን ነክሰው “ይሄ የአንድ ራት መብላት ወይም አለመብላት ጉዳይ አይደለም፤ ዘመኔን በሙሉ ለሮማ መንግስት ሳገለግልቆየሁበት የሀገር የክብር ይዞኝ ነው የእኔ በዚህ ግብዣ አለመጠራት ተራ ስህተት አይደለም፡፡” ንግግራቸውን በቁጣ ከፍ ባለ ድምፅ ቀጥለው “ከዚህ በፉት በጦር ማሰልጠኛ  ተቋም ስሜታዊው አሰልጣኝ የሚል ስም ተሰጥቶኝ ለዘመናት ተረስቼ ነበር፡፡ ነገርግን ለሀገሬ እና ለንጉሱ ክብር በጦር ሜዳ በፈጸምኩት ጀግንነት ለንጉሥ ሽልማት በቃሁኝ፡፡ ወደ ግብዣው እንዳልጠራ ያደረጉኝ ንጉሣችን አይደሉም እርግጠኛ ነኝ ጠላቶች እኔን ለመጉዳት ያደረጉት ሴራ ነው፡፡” እያሉ በምሬት ቁጣቸውን ገለጹ፡፡

ወታደሮቹም በልመና እባኳን ጄኔራልከዚህ አካባቢ ዞር ይበሉ ጥሪው እርሶን አይመለከትም” አሎአቸው፡፡ የዚህን ጊዜ ጄኔራል ስሜታዊ ሆነው ሽጉጣቸውን ላጥ አድርገው በወታደሩ ግንባር ላይ ደቀኑበት፡፡ ሌሎች ወታደሮችም ደግሞ በፍጠነት ወደ ጄነራሉ መሳሪያቸውን አቀባብለው ደቀኑ፡፡ የነገሩ መካረር የተመለከተው የጠባቂ ወታደሮች አለቃወታደሮቹ በሙሉ መሳሪያችሁን በሙሉ ወደ ታች አድርጉ” ብሎ አዘዘ፡፡ ከዚያም ወደ ጄኔራሉ ቀርቦ በቀስታ “እባኳን ጌታዬ አይቆጡ ነገሩ ቀላል ነው በሰላም ይፈታል” ብሎ ሲያረጋጋቸው፤ ከወታደሩ ግንባር ላይ ሽጉጣቸውን አውርደው ያላበውን ፊታቸውን በመሀረባቸው ማበስ ጀመሩ፡፡

* * *

 በቤተመንግስቱ በራፍ ላይ የሆነው ትዕይንት ቆይቶ ከንጉሡ ባለሞሎች ዘንድ ተሰማ፡፡ ከቆይታ በኋላ የመጣው የሬድዬ መልእክት ወደ ንጉሡ የእራት ግብዣ ጀኔራሉን እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል የሚል ሆነ፡፡ የጠባቂዎቹም አዛዥ ጀኔራል ይቅርታ ያድርጉልን ይህን ነገር ንጉሣችን ሰምተው እንዴት ወዳጄ ሳይጋበዝ ይቀራል ብለው “እነሆ በእኔ ቀኝ ተቀምጦ ጽዋውን እንዲጠጣ ፈቅጃለው” ብለዋል አሉት፡፡

ጄኔራሉ ከዚያቁጣ ስሜት ረግበው በክብር ወደ ንጉሡ የእራት ግብዥ ለመግባት ወታደሩን ተከትለው በኩራት ወደፊት ሄዱ፡፡ መግቢያው በር ላይ ሲደርሱ መሳሪያቸውን አስቀምጠው ተፈትሸው ወደ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፡፡ አስተናባሪውም በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት ጀኔራሉን በክብር ተቀብሎበስተግራው በኩል ገብተው ከፍተኛ መኳንኖች ባሉበት ቦታ ላይ ጽዋውን ይጠጡ፣ የንጉሡን ድግስ ይጋበዙ” ብሎ ቦታውን አመላከታቸውና ከአጠገባቸው ተሰወረ፡፡

* * *

በዚያን ቀን ምሽቱ አልፎ ጎህ ቀዶ ፀሐይ ስትወጣ በሮማ ከተማ የተሰማው ዜና የመስራች ሳይሆን አሳዛኝ መርዶ ነበር፡፡ ነጋሪት ተጎስሞ፣ መለከት ተነፍቶ በየገበያው የታወጀው አዋጅ “የንጉሥ ወዳጅ መስለውንጉሡን ሥርዓትን ለመገርሰሥ ሲያሴሩ የነበሩ እና ታላቁን የሮማ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለማፍረስ የሞከሩ ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች እና የበታች መኳንኖች እርምጃ ተወስዶባቸዋል በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉም ተደርጎል” የሚል ነበር፡፡ ስሜታዊው ጄሬራል የንጉሱ ወዳጅ ሆኖ ሳለ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር የሞት ጽዋው ጠጣ ፡፡ ባልተጠራበት ግብዣ በስሜት ካልተጋበዝኩ ብሎ ያልተደገሠለትን የሞት ድገስ በስሜት ተቋደሰ፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ማሰብ፣ ማመዛዘንማስታወስ እንዲችል ሆኖ የተፈጠረ ነው፡፡ በደስታ ጊዜ የሚደሰት በሀዘን ጊዜ የሚያዝንም ተፈጥሮአዊ የሆነ ስሜት አለው፡፡ የምናየውን፣ የምንሰማውንም ለመውደድም ሆነ ለመጥላትም ይህንኑ ስሜታችንን እንጠቀማለን፡፡ በዚሁ ስሜታችን ደስ ያለንን ለማድረግ፤ የምንጠላውን ደግሞ ለመተው እንችላለን፡፡ አስተዋይ ሰዎችሜታቸውን እንዲመራቸው እንደልብ የፈቀደው ቦታ እንዲያደርሳቸው አይፈቅዱለትም፡፡ ሚዛኑን ጠብቀው በሰከነ መንገድ ይጠቀሙበታል፡፡ እንዲያውም ስሜታቸው ርቆ ሄዶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ይገድቡታል፡፡

ሁሉም ሰው ስሜት በተለያየ መጠንም ለስሜቱ ተገዤ ይሆናል፡፡ ሰዎች ከእንስሳት የምንለየው በሰከነው እና ምክንያታዊ በሆነው አስተሳሰባችን እና ስሜታችንን በመቆጣጠር በመቻላችን ነው፡፡ ከአንደኛው ሰው ስሜታዊነት ሌላው ሰው የሚለየው ደግሞ ለሥሜታችን በምንሰጠው መብት እና ለስሜታችን ተገዠ በምንሆንበት መጠን ነው፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ትንሽ የምትመስል የስሜታችን ነፃነት ሰጥተን የተደራረበ ስህተት እንፈጽማለን፡፡ ታዲያ በታሪካችን ላይ እንዳየነው ስሜታዊው ጄኔራል ስሜታችንን እንድንቆጣጠር ስንመከር ካልሰማን እና በላያችን ላይ እንዲሰለጥን ካደረግነው ወደ ጥፋት ይወስደናል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ትልቁ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት ነው፡፡

እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም፦ ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም፦ አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት።

በሁኔታው የተደናገጠው ንጉሥ ዳዊት ሥህተቱን ለመሸፈን በስሜት ተጎዘ፡፡ ወደ ጦርሜዳ መልክተኛ ልኮ የቤርሳቤህን ባለቤት ኦርዮን ከጦር ሜዳ አስመጣው፡፡ ከሚስቱ ጋር ገብቶ እንዲተኛ በወይን ጠጅ በማለፊያ ምግብም አጠገበው፡፡ ኦርዮን ግን ታቦተ ጸዮን በጎጆ ሆና ጎደኞቼ ጦርነት ላይ እያሉ እኔ እንዴት ከሚስቴ ጋር እደሰታለሁ ብሎ ቤቱ ሳይገባ በሜዳላይ አደረ፡፡

ንጉሥ ዳዊት በአእምሮው አስተውሎ ቆም ብሎ ሳያስብ ንጉሥነኝ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ ብሎ ለሁለተኛ ጊዜ ኦርዮን የሚያሰክር መጠጥ እና ማለፊያ ምግብ ሰጠው፡፡ ከሚስቱ ጋር ይተኛል ብሎ ቢጠብቅም ሳይሆን ቀረ፡፡ የመጨረሻው የንጉሥ ዳዊት ስሜታዊ ውሳኔ ከቀደመው ስህተት የበለጠ ነበር፡፡

በነጋም ጊዜ ዳዊት ኢዮአብ ለሚባለው የጦር አዛዥ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው። በደብዳቤውም፦ ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ። ስሜቱን ለማስደሰት ንጉሥ ዳዊት በፈጸመው ስህተት የሰው ነፍስ አጠፋ ከእግዚአብሔር ተጣላ እጁ በደም ታጠበ፡፡

ስሜታዊነት በግለሰብ ሕይወት በዓለማችን የዕለት ተዕለት ሁኔታ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በስሜት ፍቅር ይመሠረታል፣ በስሜት ጦር ይሰበቃል፣ በስሜት ሰላም ይሰፍናል፣ በስሜት ሰላም ይደፈርሳል፡፡ በስሜት ሰዎችን ከፍ ያለ ማማ ላይ አውጥተን እናከብራለን፡፡ በስሜት የሰቀልነውን አሽቀንጥረን ወደዚያ ለመወርወር ደግሞ እንጣደፋለን፡፡ በጠዋቱ ስሜታችን ወደን በከተሰዓቱ ስሜታችን ደግሞ አምርረን ጠልተን እንታያለን፡፡ ስሜታዊነት ዓለምን እየመራ ዝቅ ያሉትን ከፍ ሲያደርግ ከፍ ያሉትን ደግሞ ሲያወርድ ይታያል፡፡

 ሰዎች ለስሜታቸው ምን ያህል ተገዤ እንደሚሆኑ በታሪክ በጠቀስነው ስሜታዊ ጀኔራል ብቻ ሳይሆን በየግል ህይወታችን በዕለት ተዕለት ኑሮችን የሚገጥሙን ክስተቶች አመላከች ናቸው፡፡ ስለዚህ ስሜት ኃይለኛ ገዥ ነው ልንል እንችላለን፡፡ በስፖርት ጨዋታ የሚመለከቱ ሰዎችን ምን ያህል የስሜት ተገዤ እንደሆኑ እንመልከት፡፡ የቦክስ ጨዋታ በስሜት የሚመለከት አንድ ደጋፊ በጣም ሲጮህ በስሜት መላ ሰውነቱን ሲያንቀሳቅስ ጮክ ብሎ “በለው ድገመው” ሲል እጆቹን ጨብጦ ሳያስበው አጠገቡ ያለውን ሰው በቦክስ ግጥም አድርጎ ሲመታው ልንመለከት እንችላለን፡፡

 የእግርኳስ ጨዋታ የሚመለከቱ ደጋፊዎች ለሚደግፉት የእግርኳስ ቡድን የሚኖራቸው ስሜት አስደናቂ ነው፡፡ ሲያሸንፍ አቅላቸውን ስተው ልብሳቸውን አውልቀው በመኪና ላይ ተንጠልጥለው በደስታ ሲፈነጥዙ የታያሉ፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሚደግፉት ቡድን በራሱ ስህተት ሲሸነፍ ሽንፈቱን በጸጋ መቀበል አቅቷቸው ለብዙ ቀናት ስሜታቸው ተቀያይሮ ምግብ አልበላ፣ ውኃ አልጠጣ ይላቸዋል፡፡ ለ ቀናት አኩርፈው ጨጎራቸው ታሞ የሚከርሙትን ደጋፊዎች ስንመለከት “ያልተቆጣጠሩት ስሜት ምን ያህል ኃይለኛ ነው” ያስብላል፡፡

ከዚሁ እግርኳስ ጨዋታ ሳንወጣ የጦርነት ያህል ፍጥጫ ባለባቸው የዋንጫ ጨዋታ ላይ ስሜታዊ የሆነ የእግርኳስ ተጫዋች ከባለጋራ ቡድን ጋር በሚያደርገው ፍልሚ በስሜት ተነሳስቶ ተሳድቦ ወይም በቴስታ ተማቶ ፍጹም ቅጣት ምት ቢያሰጥ ወይም ደግሞ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታው ቢወጣ ያንን የእግርኳስ ፍልሚያ ባዶ አድርጎ ደጋፊዎችን በስሜት ያስቆጣል፡፡ በዚህ ስሜቱ ምክንያት ቡድኑ ቢሸነፍ ደግሞ የዚያን ጊዜ የደጋፊዎች ስሜት ገንፍሎ ብዙ ጥፋት ያመጣል፡፡ ብቻ ለተጨዋቹም ለቡድኑም ለደጋፊውም ስሜት ዋጋ አስከፍሎ ሁል ጊዜ  በታሪክ ጥቁር ነጥብ ጥሎ በቁጭት ሲታወስ ይኖራል፡፡

* * *

በዓለማዊ ሥፍራ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ቦታም ቢሆን ስሜታዊነት ብዙ ተጽዕኖ ሲፈጥር ይችላል፡፡ጀማሪ ምዕመን ከጳጳሱ ይበልጣል” የሚባለውም ስሜታዊነት በጀማሪ ክርስቲያን ዘንድ ጎልቶ እንደሚታይ ያሳያል፡፡ በተለይ የእግዚአብሔርን ቃል በምንማርበት ወቅት ስሜታዊ ሆነን በአንዴ ሁሉንም ሕግጋት መፈጸም የምንችል ይመስለናል፡፡

በአንድ ወቅት ለጀማሪ መንፈሳዊ ትምህርት ተማሪዎች ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ትምህርት ሲሰጥ በትምህርቱ ልባቸው የተነካ ወጣት ሴት ተማሪዎች “ከእንግዲህ ወዲህ የዚህ ዓለም ጌጥ ምን ይጠቅመናል” ብለው በስሜት ውሳኔዎችን ወሰኑ፡፡ እንዲሂም አሉ “ሱሪ አንለብስም፣ የጥፍር ቀለም አንቀባም፣ አርቴፍሻል ጸጉር አናደርግም ” ወዘተ … ብለው ወሰኑ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ጌጣቸውን አርቀው ጣሉ ልብሳቸውን በእቃ ለወጡ፡፡

 ነገሩ በስሜት የሆነ በጥልቅ ክርስቲያናዊ መሰረት ላይ የታነፀ ባለመሆኑ ፤ የወጣት ሴቶች ውሳኔ ለረዥም ጌዜ አልዘለቀም፡፡ ጊዜው ሄደ ያ የጋለው ስሜታዊነት መብረድ ጀመረ እናም ሁሉም ወደ ቀደመ አለባበሱ እና ጌጡ ተመለሰ በፊት ይጠቀሙበት ከነበረው አዘውትረው እና አብዝተው ያጌጡበት ጀመር፡፡ ሌሎቹም በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ጌታችን በትህትና የደቀመዛሙርቱን እግር እንዳጠበ ሲማሩ “ትህትናን በተግባር እንፈጽመው” ብለው በስሜታዊነት ተነሳስተው ከቤተሰባቸው ጀምረው ወደ ጎረቤት ሄደው የሰፈሩን ሰው በሙሉ እግር አጠቡ፡፡ ነገርግን ስሜቱ ሲሰክን እንኳን በትህትና እግር ማጠብ ይቅር እና እጅ ለማስታጠቡም ፍቃደኛ ያሌሆኑ ትህትና የሌላቸው ሥነ-ምግባር የለሽ ሆነው “አይ ስሜታዊነት የማያስኮነው የለም ”አስብለዋል፡፡   

በመንፈሳዊ ቦታዎች ላይ የሚመጣው ስሜታዊነት መልካም ነገሮችን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድንፈጽም እና ራሳችንን ለዲያቢሎስ ውጊያ በማመቻቸት ከመንፈሳዊ ሕይወት እንድንሰናከል ያደርገናል፡፡ እዚህ ላይ ከዓመታት በፊት ገና ጀማሪ ምእመናን እያለን የገጠመኝን ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ትምህርት በስፋት ይሰጥ ነበር፡፡ ቅዱስ ወንጌልን ከማቴዎስ ወንጌል አንስቶ እስከ ዮሐንስ በተከታታይ ይሰበካል፡፡ ትምህርቱን ለመማር ሠራተኛው ከሥራው ወጥቶ ተማሪውም ከ 11፡30 በኋላ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ ይሰበካል፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ሲሰሙት ማንነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት በመሆኑ ተሰባኪያኑ በሙሉ ራሳቸውን መርምረው ዓለምን እንዲጠሉ ልባቸውም እንዲሰበር አድርጎል፡፡ ብዙዎች በቀደመው ሕይወታቸው ተጸጽተው በንስሓ ተመለሱ፡፡ የወንጌልን ትምህርት እየተማረ የሚመጣው ሰው ሁሉ “ቤተክርስቲያንን አወኳት ወደድኳት” በማለት በመንፈሳዊ ደስታ ተመሰጠ፡፡

በዚያን ጊዜ የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩት የዛኔው አባ ኃለኢየሱስ ክንፈ ሚካኤል (የበኋላው አቡነ መልኬጼዴቅ) ወጣቶችን የሚያበረታቱበት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲቀርቡ የሚያደርጉበት መንገድ ልዩ ነበር፡፡ ወጣቶች መርሐግብር እንዲመሩ ፣መዝሙር እንዲዘምሩ፣ ጥቅስ እንዲያነቡ ያበረታታሉ፤ ብቻ የእግዚአብሔር ጸጋ ስለተሰጣቸው በሚያስተምሩት ትምህርት ሴት፣ ወንዱ፣ ወጣት ፣አዛውንቱ ሁሉም ሰው ሰምቶ ምን ላድርግ ይላል፡፡ የሰማውንም የእግዚአብሔር ቃል ፍሬ እንዲያፈራ የበኩሉን ይጣጣራል፡፡

“ቤተክርስቲያን ሰው የላትም ሰው እንሁንላት” የሚለውን የአባ ኃለኢየሱስን ትምህርት እየሠሙ በመንፈሳዊ ሕይወት ልምምድ ውስጥ ያለፉ የተወሰኑ ወጣቶች ገዳም ገብተን ተምረን ቤተ-ክርስቲያንን አናገልግል የሚል መንፈሳዊ ሀሳቡ ግን በስሜት የታጀበ ቅንአት አደረባቸው፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ጉዳይ ላይ ውይይት መደረግ ተጀምሮ ውይይቱ ከዳር ሳይደርስ ከመካከላቸው አምስት ወንድሞች ዓለምን ንቀን መንነን በገዳም ተወስነን በምንኩስና ሕይወት እንኖራለን ከዚያም ቤተክርስቲያን ሰው እንሆናለን ብለው ቁርጥ ያለ ወሳኔያቸውን አሳወቁ፡፡

አምስቱ ወጣቶች የተንቦገበገውን መንፈሳዊ ስሜታዊነት ይዘው ሀሳባቸውን ዳር ለማድረስ ወደ አባ ኃይለኢየሱስ ዘንድ ሄደው በዝዝርዝር መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ቁርጠኛ ውሳኔያቸውን አስረዱ፡፡ አባ ወጣቶቹ የመጡበትን ጉዳይ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ ለመሆኑ ዓለማዊ ትምህርት ትማራላችሁ ብለው ጠየቁ? ጥያቄያቸውን ቀጥለው ደግሞስ ስነተኛ ክፍል ናችሁ? ብለው ጠየቁ፡፡ ወጣቶቹም ቀልጠፍ ብለውገና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችን እየተከታተልን ነው የመንገኘው” ብለው መለሱ፡፡ አባታችን ሰውን የመረዳት ትልቅ ችሎታ ስለነበራቸው የአምስቱን ወጣቶች ስሜት በሚገባ መረዳት ችለዋል፡፡ የጋለውን የወጣቶች ስሜታዊነት ሳያጣጥሉ በጥንቃቄ ባለበት እንዲቀጥል አድርገው ረጋ ብለው ፍላጎታቸውን አዳመጡ፡፡

ትንሽ ደቂቃ ዝም ብለው ካሰቡ በኋላ “ለመሆኑ ገዳም ስትገቡ ትምህርታችሁን ምን ልታደርጉት አስባችኋልአሉ  ወጣቶቹም መለሱ “አባታቸን ትምህርቱንማ እንተወዋለን አሉ፡፡ አባታችን የፈካው ፊታቸውን ኩስትር አድርገው መልሰውእንዴ እንዴት ሊሆን ይችላል፤ እስከዛሬ ድረስ ለፍታችሁ ተምራችሁ ወላጆቻችሁም ብዙ ደክመው አስተምረው፤ እንደቀልድ ነው የምታቋርጡት፤ ይሄ እንኳን ተገቢ አይደለም ” ብለው ዝም አሉ፡፡ በእጃቸው የያዙትን ነጭ ጭራ ግራና ቀኝ እያወዛወዙ ቆይ ደግሞስ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ልጆቼ “ቤተክርስቲያን የሚያገለግለግ ሰው ትምህርቱን ጀምሮ ያቋረጠ፤ በኋላ ደግሞ ገዳም ከገባ በኋላ ያቋረጥኩትን ትምህርቴን ልጨርስ ብሎ የጀመረውንም ምናኔ ( የመንኩሥና ሕይወት ) አቋርጦ ወደ ከተማ የሚወጣ፤ ብቻ አንዱን ጀምሮ አቋርጦ ሌላውንም ጀምሮ የሚያቋርጥ ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ ሰው መሆን አለበት እንዴ?” አሉ ትንሽ ቆጣ ባለ ድምፅ፡፡

ጭራቸውን አስቀምጠው መስቀላቸውን መዳፋቸው ላይ መታ መታ እያደረጉ “ልጆቼ እግዚአብሔርን መፈለጋችሁ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል መወሰናችሁ በጣም ደስ ይላል፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! ነገር ግን ገዳም ለመግባት እና በምንኩሥና ሕይወት ለመወሰን ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ደጅ መጥናት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ገዳም ሲገባ ገዳም ያሉ ታላላቅ አባቶችን ጠይቆ እንጂ በስሜት ዘው ተብሎ አይደለም፡፡ ቅድመ ዝግጅቱ ብዙ ነው ፡፡ በተጨማሪም መንፈሳዊ ልምምድ ይፈልጋል፤ ደግሞም በስሜት መንኩሰው በስሜት ምንኩስናቸውን እንደዋዛ የተው ብዙዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ አይነቱን ሰው አይደለም የምትፈልገው ለዓላማ የሚመነኩስን  ጽኑ መንፈሳዊ ሕይወት ያለው፤ በአንድ ቦታ ረግቶ የሚቀመጥ ፤ረጀም ዘመን ለመማር የተዘጋጀ ነው ” አሉ፡፡

መስቀላቸውን መዳፋቸው ላይ አሳርፈው በፈገግታ “ወደ ገዳም ለመግባት በማሰባችሁ ልጆቼ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ እኔ እንደ አባትነቴ የማዛችሁ ነገር ቢኖር፡- የከተማ ኑችሁን እንደገዳም ቆጥራችሁ ሰውነታችሁን መንፈሳዊ ሕይወትና መንፈሳዊ ተጋድሎ አለማምዱት፤ አብዝታችሁ ፁሙ፣ ጸልዩ ፣በጎ ነገር ሥሩ፡፡ የጀመራችሁትንም ዓለማዊ ትምህርት እስከ ከፍተኛው ማዕረግ አድርሱት፡፡ ዋናው ልጆቼ ልባችሁ ይመንኩስ የልብ ሰው ሁኑ ስሜታዊ አትሁኑ፤ እድሜ እኳ ረጅም ነው አያልቅም፡፡ ልጆቼ “ነገ ሌላ ስሜት ተሰምቷችሁ እንዳትቆጩ ዓለማዊ ትምህርታችሁን አጠናቃችሁ ጨርሱ፡፡ ኪዚያ ደግሞ በሙሉ ልብ የቤተክርስቲያንን ትምህርት ትማራላችሁ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆናችሁ ቤተክርስቲያን ታገለግላላችሁ እንደዚህ ነው ማድረግ የሚገባችሁ ብለው ምክራቸውን ሰጡ፡፡ በስሜታዊነት ተንደርድረው ገዳም ለመግባት የመጡትን አምስት ወጣቶች አረጋግተው መለሷቸው፡፡

አባታችን እንዳሉት ጊዜው ሄዶ ያ ትኩስ ስሜት እየቀዘቀዘ ማስተዋል ሲመጣ እነዚህ ወጣቶች በመንፈሳዊ ሕይወት ሲበስሉ ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ማወቅ እንደሚገባ ተረዱ ራሳቸውንም ወቀሱ፡፡ በስሜት ገዳም እንገባለን ብለው የነበሩት ወጣቶች በዚያ ባሰቡት ገዳማዊ ሕይወት መጎዝ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በስሜት ጦርነት ተሸንፈው እንዳይወድቁ የደብሩ አስተዳዳሪ የአባ ኃለኢየሱስ ምክር መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በማስተዋል እና በምክንያታዊነት እንዲመሩ አገዛቸው፡፡

ደብራችን ደብረ ብስራት ለቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ “ቤተ ክርስቲያን ሰው የላትም ሰው ሁኑላት ” የሚለው የአባታችን ትምህርትም እንዲሁ አልቀረም ፍሬ አፍርቷል፡፡ ስብከተ ወንጌል ከሚማሩት ሰንበት ትምህርትቤት ከሚያገለግሉ ወጣቶች መካከል ዲያቆናት ቀሳውሰት ሆነው በሀገር ውስጥ በመላው ዓለም ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ነው፡፡ በገዳማዊ ሕይወት ተወስነው እየኖሩ ያሉት ወንዶችም ሴቶችም መነኮሳት በቡዛት  አፍርቷል፡፡ ምንኩሥናው የሰመረላችው ሁሉ ግን በስሜት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በችኮላ ሳይሆን በደጅ ጥናት በመንፈሳዊ ብስለት ያደረጉት ብቻ ናቸው፡፡

* * *

ስሜታዊነት በተለያ የእድሜ፣ የስልጣን፣ የሀብት ክልል የሚከሰት ጊዜያዊ ክስተት ሲሆን በኋላ ግን መለስ ብለን ስንመለከተው የሚጸጽት ጠባይ ነው፡፡ ስሜታዊነት በሕይወታችን ጉዞ ላይ ለሚያጋጥመን ድንገተኛ ክስተቶች ምክንያታዊ ሳንሆን ሚዛኑን ሳንጠብቅ በዘፈቀደ የምንሰጠው አጸፋዊ ምላሽ ነው ፡፡ የብዙዎቻችን ግለሰባዊም ይሁን ማኅበራዊ ሕይወት በሥሜታዊነት የተነሳ ታሞ ያወቃል፡፡ በስሜታዊነት ወስነው ተጋብተው በስሜታዊነት ጨዋታ ፈረሰ ዶቦ ተቆረሰ ብለው እንደ ሕፃናት የትዳርን ማኅበራ ኃላፊነት ያልተወጡ አሉ፡፡ በስሜታዊነት የመናፍቃን መዝሙር ዘምረው መጽሐፍ አንብበው ከሃይማኖት መንገድ መጥተው ራሳቸውን በክህደት የወጉ ብዙዎች ናቸው፡፡  ሊያሳልፉት የሚችሉትን ጊዜያዊ ችግር ጎንበስ ብለው ማለፍ አቅቷቸው በስሜታዊነታቸው የተነሳ ጥሩ የሥራ፣ የትምህርት፣ የኑሮ ዕድል ያበላሹ፤ ብዙ የስሜት ተጎጂዎች አሉ፡፡

ሰዎች ባሉበት ሁሉ ስሜታዊነት አለ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የሚቀዘቅዘውን የስሜታችንን ንዝረት ታግሰን ማሳለፍ ስንችል የሀገራችንን የማኅበረሰባችን የራሳችንን ታሪክ እናበላሻለን፡፡ የነገሮችን መጨረሻ አርቀን ማየት ባለመቻል ምክንያታዊ ሳንሆን የረጅሙን ጉዞ መዳረሻ ለማበላሻት ተባባሪዎች የሆንም አንጠፋም፡፡ በምክንያት መናገር፣ በምክንያት መሥራት፣ ማስተዋል ሲገባን በስሜታዊነት ሆ ብለን ጮኸን የመረጥነው ምርጫ፣ የሄድንበት መንገድ ትልቅ ጠባሳ ጥሎብን መልሰን አዝነናል፡፡

ሰዎች የራሳቸውን ስሜት መቆጣጠር ባለመቻላቸው ምክንያት የሌሎች ስሜታዊያን ሰዎች መጠቀሚያ ይሆናሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችንም የሌሎች ስሜት ተጋብቶባቸው በማያውቁት ጉዳይ ገብተው ለምን እና እንዴት እንደሆነ ሳይጠይቁ ተባባሪ ሆነው ንብረት ያወደሙ፣ የንጹሀንን ቤት ያቃጠሉ፣ ወንድማቸውን በጭካኔ ያቃጠሉ፣ የተቀደሱ የሃይማኖት ቦታዎች ላይ እሳት የለኮሱ ስሜታዊያን፤ ማመዛዘን ትተው ምክንያታዊነትን አጉድለው ብቻ ሌሎች ሰዎችን ተከትለው የመጨረሻውን የሰዎችን የጭካኔ ጠባይ አሳይተዋል፡፡

በመንፈሳዊውም በዓለማዊ ሕይወታችን የስሜታችን ባርያ ላለመሆን እንወስን፡፡ የግል ሕይወታችን፣ ማኅበራዊ ኑሮአችን ሁሉ ከስሜት የጸዳ በማስተዋል የተደገፈ ይሁን፡፡ የሰፈነብንን ስሜታዊነት ቀስ በቀስ በመቀነስ ነገሮችን ተገቢነት በብዙ አቅጣጫ ወደፊትም ጭምር እንመልከት፡፡ ከስሜታዊነት ሰብእና ልንላቀቅ የምንችለው ነገሮችን በሚዛናዊነት እና በምክንያታዊነት ቆም ብለን በመመዘን ነው፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠን የሰውነት ፀጋ አእምችን በመጠቀም ለማናቸውም ጉዳይ አውጥቶ እና አውርዶ አሰላስሎ ስሜታዊ ሳይሆኑ መወሰን ይበጃል፡፡ አንደ ስሜታዊው ጄኔራል የስሜታችን ተገዥ ሆነን ስሜታችን እንዳያጠፋን እንጠንቀቅ፡፡

ሐምሌ 15 2014

አዲስ አበባ