ሐሙስ 25 ዲሴምበር 2025

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ

 

ናቡከደነጾር (Nebuchadnezzar II) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ

ናቡከደነጾር (Nebuchadnezzar II) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የባቢሎን ንጉሥ ሲሆን፣ ታሪኩ በሰፊው የሚገኘው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነው። በተለይም በትንቢተ ዳንኤል እና በሁለተኛ ነገሥት ላይ በዝርዝር ተጽፏል። ናቡከደነጾር  ዋናው የታሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚገኙባቸው ምዕራፎችና ቁጥሮች የሚከተሉት ናቸው፦

 በትንቢተ ዳንኤል

ናቡከደነጾር ከነቢዩ ዳንኤል ጋር የነበረው ግንኙነትና ያያቸው ሕልሞች እዚህ ይገኛሉ፦

 

·         ዳንኤል ምዕራፍ 1 ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ማርኮ ወደ ባቢሎን እንደወሰዳቸው ይናገራል።

 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ወደ ሰናዖር ምድር ወደ አምላኩ ቤት ወሰደው፥ ዕቃውንም ወደ አምላኩ ግምጃ ቤት አገባው።

ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም  ሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ለጃንደረቦች አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ።


 

·      ዳንኤል ምዕራፍ 2 ንጉሡ ያየው የታላቁ ምስል ሕልም እና ዳንኤል ሕልሙን የፈታበት ክፍል

 ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።  ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።

ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፤ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ።  ስለዚህም ንጉሡ ተበሳጨ እጅግም ተቈጣ፥ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ።  ትእዛዝም ወጣ፥ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፤ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉ ዘንድ ፈለጉአቸው።

 የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘበኞቹ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረው፤  ለንጉሡም አለቃ ለአርዮክ መልሶ፦ የንጉሡ ትእዛዝ ስለ ምን ቸኰለ? አለው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል አስታወቀው።

 ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ።  የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው።  የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ።

 ·         ዳንኤል ምዕራፍ 3 ንጉሡ የወርቅ ምስል አቁሞ እንዲሰገድ ማዘዙ፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን ወደ እቶን እሳት ማስጣሉና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸው።

 ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ።

 አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥  የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

 ·         ዳንኤል ምዕራፍ 4 ንጉሡ በትዕቢቱ ምክንያት አእምሮውን ስቶ እንደ አራዊት ለሰባት ዓመታት በጫካ መኖሩና በኋላም ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገኑ።

  ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር።  ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ።

 ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና፦ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፦ መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው።

በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።  ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና።  

በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ።  አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።

 #ናቡከደነጾር #Nebuchadnezzar #ዳንኤል #ባቢሎን #ወርቅ

  ንጉሥ ናቡከደነጾርን በጣም ያስጨነቁት ሕልሞች  ይቀጥላል

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ