ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤
የሉቃስ ወንጌል 9፥32
ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም። ሉቃ 9÷28-37
የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበ ዕለት ነው፡፡
ለደብረ ታቦር ኩነት እንደ ዐበይት ምክንያት አድርገን የምንወስደው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከተሉትን ደቀመዛሙርቱን በቄሳርያ አካባቢ ሲደርሱ የጠየቃቸው ጥያቄ ነው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ እንዲህ ጽፎታል፡፡
ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። ብሎታል፡፡ (ማቴ 16፡13-20)
ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የመሰከረውን ምስክርነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ይሰሙ ዘንድ፣ ከነቢያት (ሙሴና ኤልያስ) አንደበት ይረዱ ዘንድ፣ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ይዞቸው ወጣ፡፡ (ማቴ 17፡1-10)
ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ማርቆስ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር ቅዱስ ጰጥሮስ የተናገረበትን ቀን እና የደብረ ታቦር ተራራ ድርጊት የተፈጸመበትን ቀን ቆጥረው ስድስት ቀን በኃላ ብለው ሲጽፉ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ በፊልጶስ ቂሣርያ ድርጊቱ ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ደብረ ታቦር መገለጥ ያሉትን ቀኖች በሙሉ በመቁጠር ስምንት እንዳደረሰው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙን ሐዋርያት በተራራው ሥር ትቶ ለምን ቅዱስ ጴጥሮስን ቅዱስ ያዕቆብን እና ቅዱስ ዮሐንስን ለምን መርጦ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ላይ አውጥቶ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይመልስልናል፡፡
‹‹ቅዱስ ጴጥሮስ ፍቅሩን በተደጋጋሚ በመናገር ገልጿል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ለመድኃኒታችን የተለየ ፍቅር እንዳለው በወንጌል ሳይቀር ‹ጌታን የሚወደው› ተብሎ ተነግሮለታል ፡፡ቅዱስ ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር በመሆን በለመነው ልመና አንተ የምትጠጣውን ጽዋ እንጠጣለን እስከማለት የጠየቀ በመሆኑ በማቴ 20፡22 በዚህ ምክንያት መርጦቸዋል ›› በሏል፡፡
በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር አብ ለመጀመሪያ ጊዜ መድኃኒታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ "እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ። " ማቴ 3፥17 በደብረታቦር ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ "ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።"ሉቃ 9፥35
የደብረ ታቦር ተራራን ወጥተው የተገኙት ሦስቱ ደቀመዛሙርት ምስጢረ መለኮት ተካፋይ ሲሆኑ ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።
ታላቁን ምሥጢረ ሥጋዌ እግዚአብሔር ዓለምን የሚያድንበትን ጥበብ በሚነገርበት በብርሃን በተከበበ ተራራ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው በተለይም ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎቹን ሐዋርያት ዘንግቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በደብረታቦር ተራራ ላይ ዳስ ሠርቶ /ድንኳን ጥሎ / መኖር ይሻለናል ብሎ ጠየቀው ፡፡
ወንጌላዊያኑ ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ደካማ ጎን ገልጸውታል ቅዱስ ማርቆስ "እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር።" ሲል (ማርቆስ 9፥6 ) ቅዱስ ሉቃሰ ደግሞ "የሚለውንም አያውቅም ነበር።" ሉቃ 9፥33 በማለት ነቅፈውታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ስለ ከበደባቸው ድምጹን መስማት አልቻሉም። ጌታችን የከበደባቸውን እንቅልፍ በችርነቱ አርቆላቸው ሙሴን እና ኤልያስን እንዲሁ መለኮታዊ ክብሩን ተመለከቱ።
ከከበደበት እንቅልፍ በደንብ ያልነቃው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች ከእርሱም ሲለዩ ምድራዊ ጥያቄ አቀረበ። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ።
ቅዱስ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ የከበደባቸው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ብቻ አልነበር። ቅዱስ ማቴዎስ በ ወንጌሉ ፤ በጌቴ ሴኒ የሆነውን እንዲህ ጽፎታል በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፦ እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና፦ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ቅዱስ ማርቆስም ደግሞም "መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።" በማለት ይህንኑ ታሪክ ነግሮናል ። ማር 14፥40
በጌቴ ሴማኒም ሆነ ደብረ ታቦር ምስጢረ መለኮት የተገለጠባቸው የብርሃን ድንኳን የሚተከልበት ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝባቸው ድምፁን የምንሰማበት የክብር ቦታ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች ናቸው።
በዚህ ስፍራ ተገኝተው ከመንፈሳዊ ይልቅ ሥጋዊ ከሰማያዊ ይልቅ ምድራዊ ሀሳብ የሚቀባጥሩ ሰዎች እንቅልፍ የከበደባቸው ሰነፎች ናቸው።በሠርግ ቤት ተገኝተው ሙሽራው አይመጣም ብለው እንደተኙት ሰነፍችን ይመስላል "ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። " የማቴዎስ ወንጌል 25፥5 እንቅልፍ የከብድባቸው ሰዎች ሰነፎች ናቸው ጠቢብ ሰሎሞንም "አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ይላል ። ምሳ 6፥9 ቅዱስ ጳውሎስም "ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና።"ወደ ሮሜ ሰዎች 13፥11 ይለናል።
በቅዱሱ ተራራ ከፍ ብለን ከተገኘን ከእንቅልፍ ነቅተን ለጽድቅ ለመንግስተ ሰማያት ለሚያበቃ ሥራ እንትጋ።
ይቆየን
ያዕቆብ ሰንደቁ
ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ/ም
አዲስ አበባ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ