ዓርብ 16 ጃንዋሪ 2026

ወግ

 ዮርዳኖስ ወደ ኋላ ሲመለስ

በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ሲከበር የኢትዮጵያ ጎዳናዎች ነጭ የለበሱ ምዕመናን ታቦት አጅበው ሲዘምሩ  በደመቀ ዝማሬ ሰፈሩ ሁሉ ሲደምቅ በሩቅ ምስራቅ በምትገኘው ኢየሩሳሌም ደግሞ ተፈጥሮ ለፈጣሪዋ የምትገዛበት አንድ ድንቅ ክስተት ይከናወናል። የዮርዳኖስ ወንዝ። ይህ ወንዝ ተራ የውኃ ፍሰት አይደለም፤ የሰው ልጅ ታሪክ የተቀየረበት፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ የሰረጸበትና በየዓመቱ ዓለምን በግርምት የሚያስቆም የታሪክ ክስተት ነው።



የ ቅዱስ ያሬድ ዜማና የባሕር መሸሽ

1,500 ዓመታት በፊት፣ በደብረ ዳሞ ተራራ ሥር የቆመው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በትዝታና በዓይን ዕይታ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ስለ ጌታ ጥምቀት እንዲህ ሲል ዘመረ፦ "ባሕር አየችና ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።" ይህ ዜማ በኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት ሲስተጋባ፣ ብዙዎች እንደ ምስጢራዊ ግጥም ይቆጥሩት ይሆናል። ነገር ግን ጉዳዩ ከግጥም በላይ ነው።

ቅዱስ ያሬድ "ጾመ ድጓ" ድርሰቱ ላይ እንዳብራራው፣ ጌታ ወደ ዮርዳኖስ የሄደው ሊቀደስ ሳይሆን ሊቀድስ ነው።

ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ ድርሰቱ ላይ (በተለይም በዘመነ አስተርእዮ እና በጥምቀት ወቅት በሚዘመሩ ክፍሎች) የጌታን ወደ ዮርዳኖስ መሄድ "ሊቀደስ ሳይሆን ሊቀድስ" መሆኑን በጥልቀት ገልጾታል። እንዲህ ይላል፦ "ኢመጽአ ኢየሱስ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይትቀደስ እምዮሐንስ፣ አላ ከመ ይቅድሶ ለዮርዳኖስ ወከመ ይባርክ አጥቢያተ ማይ።" ትርጉም፦ ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ የመጣው ከዮሐንስ ዘንድ ሊቀደስ (ሊነጻ) አይደለም የሄደው፤ ይልቁንም ዮርዳኖስን ሊቀድሰው የአዳም ልጆች ያጡትን የፀጋ ልጅነት ሊመልስልን የውኃ ምንጮችን ሊባርክ ነው እንጂ ብሏል፡፡

 ቅዱስ ያሬድ  መዝሙረ ዳዊት መዝሙር 113 (114) ÷ 3 ላይ ካለው "ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ" ሚለው ኃይለ ቃል መነሻ በበዓለ ጥምቀት ድጓው ላይ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፦  "ርእየተከ ባሕር ወጎየየት፣ ወዮርዳኖስ ገብአ ድኅሬሁ..." (ባሕር አየችህና ሸሸች፣ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ) በማለት ወንዙ ፈጣሪውን አውቆ በመሸሽ የሰጠው የክብር ሰላምታ ነው ቡሏል።

የዐይን እማኞች ምስክርነት፡ ከሩሲያ እስከ ግሪክ

ዛሬ 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ይህ የ ቅዱስ ያሬድ ምስክርነት በቪዲዮ ካሜራዎችና በሺዎች በሚቆጠሩ እማኞች እየተረጋገጠ ነው። በየዓመቱ በጃንዋሪ 19 (በኢየሩሳሌም ጥምቀት ዕለት) የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ጸሎት አድርገው መስቀሉን ወደ ወንዙ ሲጥሉ፣ ዓለምን የሚያስደንቅ ነገር ይከሰታል።



ከሩሲያ የመጣችው ማሪና ፔትሮቫ የተባለች እማኝ 2018 (እ.ኤ.አ) ባየችው ነገር ተገርማ እንዲህ ትላለች፦ "መስቀሉ ውሃውን ሲነካው ወንዙ ልክ እንደ ሰው ተባብሮ ቆመ። ከዚያም ፍሰቱ ወደ ኋላ መመለስ ጀመረ። በዚያ የነበርን ሁሉ በግርምት ጮኽን።" ትላለች፡፡ ሌላኛው እማኝ አንድሬስ ኒኮላስ ደግሞ በሙያው መሐንዲስ ቢሆንም፣ "ተፈጥሮ ለፈጣሪዋ ስትገዛ አየሁ፤ ይህ ሳይንሳዊ ማብራሪያ የሌለው ድንቅ ነው" ሲል ይመሰክራል።


የሚዲያ ዘገባዎችና የተአምሩ ማስረጃዎች

ይህ ክስተት በምስጢር የሚደረግ ሳይሆን እንደ RT Sputnik እና Greek Reporter ባሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ነው።

በየዓመቱ በኤጲፋንያ (ጥምቀት) በዓል ወቅት የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ወይም ጳጳሳት መስቀሉን ወደ ባሕር ወይም ወደ ወንዝ የሚጥሉበት ሥነ-ሥርዓት እጅግ አስደናቂ ነው። ይህ ድርጊት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁንና ውኃውን መባረኩን የሚያመለክት ነው።

መስቀሉ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሲጣል ወጣቶች መስቀሉን ለማግኘት ወደ ቀዝቃዛው ውኃ ዘልለው ይገባሉ። መስቀሉን መጀመሪያ አግኝቶ ለፓትርያርኩ የሚያስረክበው ሰው ዓመቱን ሙሉ ልዩ በረከት እንደሚያገኝ ይታመናል። ይህ ሥነ-ሥርዓት በግሪክ ምዕመናን ዘንድ እጅግ መንፈሳዊና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን የሚያስደንቅ ትዕይንት ነው።

·         ፓትርያርኩ መስቀሉን ሲጥሉ የወንዙ ሞገድ በድንገት አቅጣጫውን ይለውጣል።

·         ምእመናን በወንዙ ላይ የጣሏቸው አበቦችና ቅርንጫፎች ወደ ታች ከመፍሰስ ይልቅ ወደ ኋላ ተመልሰው ወደ ፓትርያርኩ ይጠጋሉ።

·         ወንዙ እጅግ ረጋ ብሎ በሚፈስበት ሰዓት እንኳ፣ መስቀሉ ሲያርፍበት ውሃው በኃይል ይናወጣል።



የታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ ዋቢ

ይህ ተአምር ድንገት የመጣ ሳይሆን "ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።" ተብሎ አስቀድሞ   በመዝሙር 114፥3 በትንቢት የተነገረ ነው እንደ ጀሮም መርፊ (Jerome Murphy-O'Connor) ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች "The Holy Land" በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለ ዮርዳኖስ ወንዝ መንፈሳዊ ኃይልና ስለ በዓለ ጥምቀት ድምቀት በሰፊው ጽፈዋል። የቤተክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘቂሣርያም ከመጀመሪያዎቹ መቶ ክፍለ ዘመናት ጀምሮ የነበሩ ክርስቲያን ተጓዦች ይህንኑ ተአምር ይመሰክሩ እንደነበር አስፍሯል።

ለምን ወደ ኋላ?

የዮርዳኖስ ወደ ኋላ መመለስ ተራ የተፈጥሮ ክስተት አይደለም። ለቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይህ የሰው ልጅ ከኃጢአት ፍሰት ተመልሶ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱ ምልክት ነው በማለት ያስተምራሉ። ሳይንስ "ተፈጥሯዊ አይደለም" ቢለውም፣ በየዓመቱ በዚያው ዕለትና በዚያው የጸሎት ሰዓት መደጋገሙ ግን ነገሩ መለኮታዊ መሆኑን ያረጋግጣል።

ቅዱስ ያሬድ በጥንት ዘመን በዜማ የገለጠው ምስጢር፣ ዛሬ በዮርዳኖስ ዳርቻ በዓይን እየታየ ነው። ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ጌታ መሆኑን ተፈጥሮ ራሷ የምትሰጠው ዘላለማዊ ምስክርነት ነው።

ከወዲሁ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፡፡

ያዕቆብ ሰንደቁ

ጥር 2018 አዲስ አበባ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ