ቅዳሜ 7 ሜይ 2016

ስብከት

በመጣህበት መንገድ አትመለስ    1ኛ ነገሥት. 13፥1
በንጉሥ ኢዮርብዓምም ዘመን እንዲህ ሆነ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፡፡ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገረ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። በዚያም ቀን፦ እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
ንጉሡም ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ“ያዙት” አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው።“ አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች። ንጉሡም “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ አለ “የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፡፡ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና ” አለው። ከዚያም ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ ሳይመለስ በሌላም መንገድ ሄደ።
በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፡፡ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ እና የንጉሡ እጅ ደርቃ ጸልዮ እንደፈወሰው ነገሩት፡፡ ሽማግሌው ነቢይ የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ ጠይቆ አህያውን ጭኖ ተጎዘ፡፡ ባየውም ጊዜ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህ ? ”ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም “አዋ እኔ ነኝ” አለው፡፡ ሽማግሌው ነቢይ “ከእኔ ጋር ሄደህ እንጀራ እንብላ ”አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም “በመጣህበት መንገድ አትመለስ፤ ከማንም ጋር እንጀራ አትብላ፣ ውኃ አትጠጣ ተብዬ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዝዤአለሁ” አለው፡፡
ሽማግሌው ነቢይ የሐሰት ቃል ፈጥሮ “እኔም እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤  የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንጀራ እንዲበላ ወደ ቤትህ ጋብዘው ብሎኛል” አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም የሽማግሌውን ነቢይ የሐሰት ቃል አምኖ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ወደ ቤተልሔምም መጣ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በላ ውኃ ጠጣ፡፡ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ በሽማግሌው ነቢይ የእግዚአብሔር መልእክት ተገለጠለት፡፡ ከይሁዳም ለመጣም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው ተባለ፡፡ እንዲህም አለው “በእግዚአብሔር አፍ ላይ አምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ተመልሰህም እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም” ተብለሀል አለው፡፡
የእግዚአብሔር ሰውም አህያውን ጭኖ ከሽማግሌው ነቢይ ቤት ወጥቶ በመጣበት መንገድ ተመለሰ፡፡ በመንገድም አንበሳ አግኝቶት ሰብሮ ገደለው፡፡ ሬሳውም መንገድ ላይ ተጋድሞ ነበረ፡፡ አንበሳውም አህያውንም  ሳይነካው በአጠገቡ ዝም ብሎ ቆመ፡፡ ነገሩን የተመለከቱ ሰዎች ሽማግሌው ነቢይ ባለበት ከተማ ሲያወሩ ተሰማ፡፡ ያም ከመንገድ የመለሰው ሽማግሌ ነቢይ ወሬውን በሰማ ጊዜ “በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመጸ የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደተናገረው ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰቡሮም ገድሎታል”አለ፡፡ ልጆቹንም አህያ ጫኑልኝ ብሎ ወደ ስፍራው ሄደ፡፡
በደረሰም ጊዜ ሬሳው ወድቆ አንበሳው አጠገቡ ቆሞ አህያውንም ሳይሰብረው ተመለከተ፡፡ ሬሳውንም በአህያ ጭኖ ያለቅስለት እና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞ መጣ፡፡ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው ዋይ ዋይ ወንድሜ ብሎ አለቀሰለት፡፡ ለልጆቹም እንዲህ አላቸው በሞትኩኝ ጊዜ እርሱ መቃብር አጠገብ ቅበሩኝ፤ አጥንቶቹም ከእርሱ አጥንቶች ጋር አንድ ይሁኑ፡፡ በሰማርያ ከተሞች ውስጥ በቤተልሄም መሰዊያ ላይ የተናገረው ነገር በእዉነት ተፈጽሞአልና፡፡ 
ንጉሥ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ ሳይመለስ ቀረ በኮረብታዎቹ ላይ መስገጆዎችን ሠራ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ለእርሱ ቤት ኃጢአት ሆነ፡፡
           የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሥ ፊት ባደረገው ተአምራት የተነሳ ልሸልምህ፣ በቤተ መንግስት ልጋብዝህ ብሎ ንጉሡ ሲጠይቀው፤ በመጣህበት መንገድ አትመለስ፣ አትብላ፣ አትጠጣ ተብያለሁ ብሎ እጅ መንሻውን ባለመቀበል የመጀመሪያው ፈተና ድል አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ፈተና ደግሞ በዕድሜ አረጋዊ ከሆነ ከእውነተኛ ነቢይ ቀረበለት፡፡ በውሸት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦልኛል በመጣህበት መንገድ ተመለስ እንጀራ ብላ ውኃ ጠጣ ተብለሀል በማለት፤ እግዚአብሔር ካዘዘው ትእዛዝ ጋር የሚቃረን ትእዛዝ አስተላለፈለት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሰው ነቢይ መሆኑን እና ሽምግልናውን ከግምት በማስገባት ነገሩን በደንብ ሳይመረምር፤ ቀድሞ ለምን ታዘዝኩኝ ? አሁን ደግሞ ለምን? እንዴት ተቀየረ ? ብሎ ሳያስተውል፤ የሐሰት ቃል በመስማት የእግዚአብሔርን ቃል ተላለፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ሰው መሳሳት ዋና ምክንያት እግዚአብሔር ካዘዘው ትእዛዝ የበለጠ ሽማግሌዉ ነቢይ የነገረውን ቃል ሳይመረምር አምኖ መቀበሉ ነው፡፡ የማንኛውንም መንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ መመዘኛችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል፣ያዘዘው ትእዛዝ አይለውጥም ማሻሻያም አያደርግለትም፡፡ በኦሪትም ለቤተ እስራኤል እንዲህ ብሎአቸው ነበር  “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም።” ኦሪት ዘኍ.23፥19 በነቢዩም በእንባቆም ትንቢት “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱ አይዘገይም። ዕንባ. 2፥3 ብሎአል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ”ብሎአል፡፡ ማቴ 24፥ 35፣ ማር ፥31፣ ሉቃ 21፥ 33፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከሚሻር የሰማይ እና ምድር ማለፍ እንደሚቀል ተናግሮአል፡፡
ይህ የእግዚአብሔር ሰው በመጣበት መንገድ ወደ ኋላ የተመለሰው፤ ከእውነተኛው ነቢይ የሐሰት ቃል በመስማቱ እና ሳያስተውል ፣ ሳይመረምር አሜን ብሎ በመቀበሉ ነው፡፡ ሐሰተኞች ነቢያት እና መምህራን እውነተኞች ነን ብለው የሚመጡበት ጊዜ አለ፡፡ይህ የተለመደ እና በስፋት የትንቢት ማስጠንቀቂያ የተነገረለት ነው፡፡ የረቀቀ እና የሚከፋው ግን ቀድሞ በእውነተኛነታቸው በጣም ታዋቂ በሆኑት ነቢያት፣ መምህራን የሐሰት የትንቢት ቃል በሚናገሩበት ወቅት ነው ፡፡ እንዲህ አይነቱን ከባድ ፈተና ማለፍ የሚቻለው የተነገረው ቃል፤ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና አለመሆኑን በመመርመር፤ እንዲሁም የነገሩን ትክክለኛነት በቅዱሳት መጻሕፍት ጋር መስማማቱን በመመዘን ነው፡፡
ዲያብሎስ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ትእዛዝ እና መንገድ ለማሳሳት፤ ልዩ ልዩ አይነት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡በዚህም የረጅም ጊዜ ልምድ እና ክህሎት አለው፡፡ ዲያብሎስ መንፈሳዊያን እና ዓለማውያን ሰዎችን ለማሳት የሚጠቀምበት ስልት የተለያየ ነው፡፡የመንፈሳዊያን መንገድ ለማስቀየር እና ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጭ ለማድረግ ሲፈልግ በመንፈሳዊያን ሰዎች አድሮ፤ መንፈሳዊ የሚመስል ሐሰት ይዞ ይቀርባል፡፡ ይህን የዲያብሎስ ውጊያ ድል ለማድረግ ጥልቅ ማስተዋልን ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ  “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥”ምሳ.2፥11 የሚለን ፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ምሳ. 9፥6 የሚለን፡፡ ማስተዋልን የምናገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።” ኢዮብ. 1213 ይለናል፡፡ እንዲሁም  “በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?”ይላል፡፡ ኢዮብ. 3836 ፡፡ በቅዱስ ወንጌልም እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥” በማለት ተጽፎአል ፡፡ ማቴ 24፥15 ፡፡ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምናገኘው ማስተዋል ተመርተን በሃይማኖት መንገድ በምግባር፣ በቱሩፋት መጽናት እንችላለን፡፡
 በሃይማኖት መንገድ ለመጽናት ወደ ኋላ ላለመመለስ፤ ከማስተዋል በተጨማሪ መንፈስን ሁሉ በጥርጣሬ መመርመር አለብን፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” በማለት ይመክረናል፡፡ 1ኛ ዮሐ. 4፥1 ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ስለመጡ ነቢይ ነኝ፣ ራይዕ ተገልጦልኛል፣ የፈውስ ሀብት ተሰጥቶኛል፣ አጠምቃለሁ፣ለማናቸውም ችግር በፍትሄ እሰጣለሁ፣ድንቅ ተአምራት አደርጋለሁ ወዘተ …  ያለውን ሁሉ በስሜት ማመን እና መከተል የለብንም፡፡ በበቂ ሁኔታ ሳንመረምር ስለ እውነተኛነታቸው ለሌሎች ልንመሰክርም አይገባም፡፡ መገኛቸው መንደር ቢሆንም ፤ በተቀደሰው ስፍራ ቢቆሙም፤ ቀደም ብለው እውነተኛ አገልጋዮች ቢሆኑም እንኳን፤ ሳንመረምር ልናምንባቸው አይገባንም፡፡ ጊዜ የሚገልጠው የተደበቀ የጥፋት የእርኩሰትን፣ ገንዘብ መውደድን እና ዝሙትን ፤ ቀድሞ ወደ መጣንበት ኃጢአት መንገድ የሚመልሱ ተግባሮችን ሁሉ ሊፈጽሙ እና ሊያስፈጽሙን ይችላሉና፤ ከሐሰተኛ ትምህርታቸው ልንጠበቅ ይገባል፡፡  
በቅዱስ ወንጌል “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤” ማቴ.24፥11 እንደተባለ በሐሰተኞች ተአምራት ምልክት ተሳስተን የያዝነውን የሃይማኖት መንገድ እንዳንቀይር፡፡በመጨረሻው ዘመን መዳረሻም ከሚመጡት ፈተናዎች መካከል በእውነተኛ ቦታ እና ከእውነተኛ ሰዎችን የዲያብሎስ መጠቀሚያ በማድረግ የጥንቆላ ትንቢትን ማናገር ነው፡፡ በዚህም የብዙዎችን ተቀባይነት አግኝተው፤ ብዙዎችን ከያዙት የጽድቅ መንገድ አስተው ወደ ሌላ የስህተት መንገድ ይመራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” 1ኛ ቆሮ.11፥14 በማለት ሰይጣን በለወጣቸው ሰዎች ስብከት፣ ተአምራት፣ ልዩ ልዩ ምልክት እንዳንስት የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እንዳንጥስ ያስጠነቅቀናል፡፡
            በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አምፆ ወደ ኋላ በመመለሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ሰው በአንበሳ ተሰብሮ ሞተ፡፡ በሃይማኖት ጉዞ ጀምሮ ማቋረጥም ሆነ ወደ ኋላ መመልከት አይቻልም፡፡ በቅዱስ ወንጌልም “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም… ።” ተብሎአል፡፡ ሉቃ.9፥62 መንገዱን ጀምረው ጉዞቸውን ያቋረጡት ሳይሆኑ እስከ መጨረሻው የሚጸኑት ናቸው ለሰማያዊው መንግስት የሚገቡት ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ጀምረው የሚያቋርጡትን ሰዎች ሲገልጣቸው “አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል። ” 2ኛ የጴጥ.2፥21 ብሎአል፡፡
የጽድቅን መንገድ ጀምረው የሚያቋርጡ ሰዎች የሚውጠውን ፈልጎ አድብቶ ለሚጠባበቃቸው ዲያብሎስ ትልቅ ደስታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።”  1ኛ የጴጥ. 5፥8 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከተሰጠን የቅድስና መንገድ ጀምረን ከማቋረጥ የጽድቅን መንገድ አለማወቅ ይቀላል፡፡ ዛሬ በዚህ የስልጣኔ ማማ ላይ በደረሰው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች፤ የጽድቅን መንገድ ጀምሮ ማቋረጥን ሰማያዊ ፍርድ የሚያሰጥ ሳይመስላቸው እንደ ዋዛ ቀለል አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ብዙዎች የጽድቅን መንገድ ጀመሩ አንበሳ በተባለው ዲያብሎስ ተሰብረው ከመሀል አቋረጡ፤ የተክሊል ጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ሽረው ተፋቱ ፣ ቆርበው አፈረሱ፤ ንሥሐ ገብተው ረከሱ፣ ዘምረው ዘፈኑ፣ ቀስሰው አፈረሱ፣ መንኩሰው ቆብ ጣሉ፡፡
በጀመርነው የጽድቅ መንገድ እስከ መጨረሻው እንድንጓዝ የዲያብሎስን ፈተና በእምነት ጸንተን እንድንቃወም
 የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጀነት አይለየን አሜን፡፡
ያዕቆብ ሰንደቁ
ቅዳሜ ሚያዚያ 29 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ

ቅዳሜ 30 ኤፕሪል 2016




በዓላት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ትንሣኤ ልቡና

“በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ። በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ጲላጦስም ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።” የማቴዎስ ወንጌል 27፥57-66

“ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን፦ አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው። መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ” የማርቆስ ወንጌል 16፥1-8

“ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።” የሉቃስ ወንጌል 24፥1-12

“ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ። ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።”  የዮሐንስ ወንጌል 20፥1-18
ጌታችን አስቀድሞ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አስነሳዋለው፤ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ ብሎ በተናገረው መሰረት መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ውለታቸውን አስበው በማለዳም ሽቶ ለመቀባት የመጡት ሴቶች፤  ጲላጦስም እንዲጠብቁት ዘዛቸው ወታደሮች የዘጉትን የመቃብሩን ድንጋይ ማን ያነሳልናል? ብለው አዝነው ነበር፡፡ ነገርግን በመቃብሩ ራስጌና ግርጌ የነበሩት ቅዱሳን መላእክት ታላቁን ድንጋይ አንከባለው እንደተናገረው ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሳቱን አበሰሩአቸው፡፡ የሚያስፈራው እና ሀዘን የተሞላው የመቃብር ስፍራ በብርሃን ጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ የመቃብሩ ድንጋይ ተንከባሎ በውስጡም ጌታ የለበሰው ልብስ ብቻ ታየ፡፡ የትንሣኤውንም ምስራች ለወንድሞች ሐዋርያት ሊናገሩ ሴቶቹ ፈጥነው ሄዱ፡፡
ትንሣኤ የበዓላት ሁሉ በኵር ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሥጋቸው በመቃብር በስብሶ ነፍሳቸው በሲኦል ወይህኒ የነበሩት አዳም እና ልጆቹ ነፃ የወጡበት ዕለት ነው፡፡ ሞት፣ መቃብር፣ የሲኦል ጨለማ ድል ተነሳ ፡፡ ዲያብሎስ ተንሰራፍቶ ከያዘው ሥልጣን በውርደት ተሻረ፡፡ ከመቃብር በኋላ መነሳት፤ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ተረጋገጠ፡፡ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ”ዮሐ.5፥28 እንደተባለ ሙታንም ሁሉ በአዋጅ በአንድ እንደሚነሱ ታወቀ፡፡ በሕጉ እና በትእዛዙ የተጎዙት ጌታችን የሰጠን የሕይወት ትንሣኤ ይካፈላሉ፡፡ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” እንዳለ ሐዋርያው ፡፡ ሮሜ. 6፥5
የመድኃኒታችን ትንሣኤ ከባርነት ወደ ነፃነት፤ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ 16፥33 እንዳለን በእርሱ ትንሣኤው የእኛ ትንሣኤ፤ በእርሱ ድል አድራጊነት እኛም ዓለምን እንደምናሸንፍ አረጋገጠልን፡፡ በሞት ማሰሪያ የተተበተበው ደካማው የአዳም ሕይወት የማሸነፍ ኃይል አገኝ፡፡ የተጫነበት እጅግ ትልቁ የመቃብር ድንጋይ ከፊቱ ገለል እንዲደረግለት ሆነ፡፡ መንገዱም በትንሣኤው ብርሃን ተቅናናለት፡፡
የትንሣኤ በዓል ስናከብር እግዚአብሔር የሰጠንን አንጸባራቂ የማሸነፍ ኃይል በማሰብ፤ ብርሃንኸን ላክልን፣በልቦናችን አብራልን እያልን እንዘምራለን፡፡ የክርስትና ሕይወት ኃጢአትን እና ዓለምን አሸንፎ በትንሣኤው ብርሃን የደመቀ ልቦና ይዞ ለእግዚአብሔር መንግስት መዘጋጀት ነው፡፡በዓሉ የሚከበርበት ዐብይ ምክንያትም እንደ መቃብር ድንጋይ የተዘጋብን የዚህ ዓለም ኃጢአት አንከባለን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ነው፡፡ሐዋርያው “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤” ፊል. 3፥10-11 እንዳለ እግዚአብሔር ያማናውቅ እንድናወቅ፤ ያልቀረብን እንድንቀርብትንሣኤ መሰናክሉ ሁሉ ተወገደልን፡፡እግዚአብሔር በሰጠን ዘመን የትንሣኤን በዓል ስናከብር በልባችን ደንዳናነት ጠንቅ የጨለመውን ሕይወታችንን በማስተካክል ትንሣኤ ልቡና በማምጣት ይሁን፡፡
ክርስቶስ ተነስቷአል በመቃብር ውስጥም የለም!
መልካም ፋሲካ ለሁላችንም ይሁንልን!
ያዕቆብ ሰንደቁ
ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ፡፡
 

ዓርብ 22 ኤፕሪል 2016

ወግ እልል በሉ

እልል በሉ
 በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለንግስ በዓል በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መዳረሻ በሰው ተሞልቷል፤ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ሴቱ ፣ወንዱ ተሰብስቧል፡፡ የተጋበዘውም መምህር ከአሥራ አምስት ቀን አስቀድሞ ባስተማረባቸው መድረኮች ሁሉ በእዚህ ቦታ ተገኝቶ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር፡፡ በየታከሲው ፣ በየመንገዱም የስብከቱን ርዕስ `ጠቅሶ የወረቀት ማስታወቂያዎችን ለጥፎ ይህንንም ብዙ ሰው ሰምቶ እና ተጠራርቶ እንዲመጣ ረድቷል፡፡ በዓውደ ምህረቱ በግራ እና ቀኝ በኩል ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች ተተክለዋል፡፡ ከድምፅ ማጉያው የሚወጣው ድምፅ ምድርን ያንቀጠቅጣል፡፡ በየሠርግ ቤት እንደምናየው የዓውደ ምህረቱም ዓዕማድ/ምሰሶዎች/ ዙሪያውን በነጭ ሻማ ጨርቅ ጥቅልል ተደርገዋል፣ በክብ ቅርጽ በአንድ ላይ የታጨቁ ልዩ ልዩ ቀለም ያላቸው ፊኛዎች ተሰድረዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪም በጸሎት መርሐግብሩን ከፈቱ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል ቀጠል አደረጉና “አሁን በቀጥታ ሁላችሁም በጉጉት ወደምጠብቀው  መምህር እወስዳችኋለሁ” አሉ፡፡ እኔም በልቤ “ጎሽ ወደ ትምህርቱ ልንተላለፍ ነው” ብዬ የልቦናዬን ሰሌዳ አዘጋጀሁ፡፡ ሰባኬ ወንጌሉ “ከዚያ በፊት ግን ምዕመናን”  አሉ “የዕለቱን መምህር ላስተዋውቃችሁ” በማለት እንደገና ንግግር ሲጀምሩ፤ ከበስጭቴ የተነሳ ሀሞቴ ፈሰሰ፡፡  ንግግራቸውን ቀጠሉ “መምህራችንን ዛሬ ወደዚህ ዓውደ ምህረት ለማምጣት በጣም ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለን፤ ከብዙ ቦታ ተሻምተን ነው ፡፡ ስለዚህ ደስ ይበላችሁ ምዕመናን እስቲ እልል ብላችሁ አመስግኑ” አሉ፡፡ ምዕመኑም ወዲያውኑ በእልልታ ጸፈውን መለሰ፡፡ ቀጠሉም እንዲህ አሉ “እውነት ነው የምላችሁ! መምህራችን እውቀታቸው የመጠቀና የረቀቀ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ተዘዋውረው ያስተምራሉ፤ እነሆ ዛሬ እኛን ለማስተማር ውድ ጊዜአቸውን ሰውተው ስለመጡ ወንዶች በጭብጨባ ሴቶች በእልልታ እንኳን ደህና መጡልን አንድትሉ እጠይቃለሁ” አሉ፡፡ ለእልልታና ለጭብጨባ በቋፍ ላይ የሚገኘው ምእመን መታዘዙ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት ድምቅ አድርጎ እልልታውን እና ጭብጨባውን አሰማ፡፡ “ያንሳል እስቲ ድገሙት” ተባለ ምዕመኑ እንደገና “እልል እልል አለ ”መምህራችን ወደ መድረረኩ እየመጡ ስለሆነ እስቲ በጭብጨባ “ሾዋ፣ ሾዋ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው” ተባለ፡፡ ምዕመኑም እያጨበጨበ ጌጠኛ ጥቁር ቀሚስ የለበሰ አጠር ደልደል ያለ መምህር ወደ መድረኩ መጣ፡፡
ሁሉም ዐይኖቹን ወደ ዓውደ ምህረቱ ተክሎ በትኩረት ያያል፡፡ ከመምህሩ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ አጠር አና ደልደል ያለ ወጣት መምህር ወደ መድረኩ ወጥቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ቆመ፤ የምዕመኑ ጭብጨባው ያባራው መምህሩ ተረጋግቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ከቆመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው፡፡ በሁኔታው በጣም ግራ ገባኝ፤ በአውደ ምህረቱ ላይ የተቀመጡት ታላላቅ አባቶች ሁኔታውን ሳይቃወሙ በዝምታ ይመለከታሉ፡፡ እንደገናም መለስ ብዬ “መቼም መምህሩ በታላቁ ዐቢይ ጾም የማህሌቱ ከበሮ ተሰቅሎ ሳለ ፤ ለእርሱ የተጎሰመውን የምስጋና ነጋሪት እና እልልታ ውጦ ዝም አይልም፡፡ እንዲያውም ተቋውሞውን በመግለጽ የደብሩን ሰባኬ ወንጌል ይወቅሳል፤የተፈጸመውም ድርጊት ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ውጭ መሆኑን ጠቅሶ ማስተካከያ ይሰጣል ብዬ ተጽናናሁ ፡፡
 ወጣቱ መምህር ሰላምታውን ጨርሶ ካበቃ በኋላ “በዙሪያው ያላችሁ ምእመናን በሙሉ ሁለት እጃችሁን ወደ ላይ ወደ ሰማይ ዘርጉ” አለ፡፡ እኔም በሁኔታው ተገርሜ “ወይ ጉድ ይባስ አታምጣ! ደግሞ ጭብጨባው እልልታው ሳያንስ እጃችሁን ኪሳችሁ ውስጥ ከታችሁ ገንዘብ አምጡ ሊል ነው” ብዬ ኪሴን አሰቡኩት፡፡ ሁሉም እጁን አወጣ ከዚያም “ሦስቴ እልል ብላችሁ አጨብጭቡበት” አላቸው፡፡ ምዕመኑም እልታውን አደመቀው፡፡ መምህሩም ያንሳል፣ ያንሳል ምዕመናን ድገሙት ብሎ በድጋሚ አስደገማቸው፡፡ ከዚያም ቀጠለና ከሀገረ ስብከት የመጡትን እንግዶች፣ የደብሩን አስተዳዳሪን፣ የቤተ ክርስቲያኑን ፀሐፊ፣ የሰባኬ ወንጌሉንም ስም እየጠራ ተራ በተራም እያስጨበጨ እልል አስባለላቸው፡፡
ምዕመናን  “ለዛሬ ወደተዘጋጀው ትምህርት ከማለፌ በፊት አንድ ማሳሰቢያ አለኝ” አለ መምህሩ ፡፡ ቆጣ ባለ ድምፅ “ምእመናን ቁጥራችሁ ብዙ ቢሆንም  የእልልታ ድምፃችሁ ግን አነስተኛ ነው፤ስታጨበጭቡም አይሰማም፤ ስለዚህ ጉባኤው አልደመቀም፤”አለ፡፡ ቀጠል አድርጎም መዝሙረኛው ዳዊት እንኳ በመዝ 47÷1 “አሕዛብ ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ፡፡” ይላል በማለት እርሱ ከፈጸመው ድርጊት ጋር ባይስማማም በስፋት የእልልታን ጠቀሜታ አስተማረ፡፡  እኔም ከአሁን አሁን በማስታወቂያ ላይ የተለጠፈውን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን ርዕስ ትምህርት ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ነገር ግን ማስታወቂያ የተነገረለት ወቅታዊው የትምህርት ርዕስ ተዘንግቶ ካለጊዜው እና ሰዓቱ እልልታን በመጻፍም፣ በተግባርም መማር ጀመርን፡፡
በመሀል በሀሳብ ተጠልፌ ያለሁበትን እስክረሳ ድረስ ከውስጤ ጋር ሙግት ጀመርኩ ፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የመደንገግ፣ የማሻሻል ሥልጣን ያለው ማነው ? ቅዱስ ሲኖዶስ ወይስ? መምህራን፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ የአካባቢ ወጣቶች ፤ ቆይ ከመቼ ጀምሮ ነው በታላቁ ዐብይ ጾም ማጠናቀቂያ ሳምንት ውስጥ እልታ እና ጭብጨባ ፤ በመጽሐፉ እንደ ተጻፈ እልልታ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት እንጂ የግለሰቦችን በውዳሴ ከንቱ የምንጠልፍበት ገመድ ነው እንዴ ? እያልኩ ከራሴ ጋር እሞገታለሁ ፡፡  በግምት ሰላለሳ ደቂቃ ያህል በሀሳብ ማዕበል ስንገላታ ቆየሁ፡፡ልክ መምህሩ ወደ ዕለቱ ትምህርት መሸጋገሩን ሲናገር ከያዘኝ ተመስጦ ነቃሁ፡፡
 መምህሩ በየታክሲው እና በየመንገዱ ላይ ከራሳቸው ስም ቀጥሎ በጉልህ የለጠፉትን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን የትምህርት ርዕስ ያስተምራሉ ብዬ ብጠብቅም ባልታወቀ ምክንያት ርዕሱን ቀይረው “ሉሲፈር እና ሥራው” ብለው ትምህርት መስጠት ጀመሩ፡፡ ለአርባ ደቂቃም ካስተማሩ በኋላ ሰዓት አልቋል ተብለው በወንዶች ጭብጨባ በሴቶች እልልታ ታጅበው ከአውደ ምህረቱ ወረዱ፡፡
እልልታ ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ የምስጋና መሥዋዕት ነው፡፡ ይህም በጥንቃቄ ይፈጸማል እንጂ በልማድ እና በዘፈቀደ አይከናወንም፡፡ እልልታን ተቀባብሎ ለማለት የምእመናን ፍጥነት ይገርማል ፡፡ ከሌላው ሰው ስለሰሙ ብቻ እልልታቸውን የሚያሰሙ አሉ፡፡ በአንድ ወቅት የደብራችን ሰበካ ጉባኤ ሊመንበር የነበሩት ሰው በተመሳሳይ ርዕስ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ስንለዋወጥ ያጫወቱኝን አስታውሳለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡ በወቅቱ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር መንፈሳዊ አገልገሎት እያስታጎሉ ያስቸገሩ ዲቆናትን እና ቀሳውስትን ጠርቶ ምክርም ይሰጣል፡፡ ምክርሩን ሰምተው ጥፋታቸውን ያላረሙትን አገልጋዮች ቀጣቸው፡፡ በዕለተ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ከተቀጡት መካከል አንዱ ካህን በድምፅ ማጉያ ማስታወቂ ተናገሩ “ሰበካ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኑን በሚገባ ማስተዳደር ስላልቻለ፤ የበላይ አካላት በወሰኑት መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ከኃላፊነቱ ተሸሮል፡፡ በቅርብ ቀን አዲስ ሰበካ ጉባኤ ይመረጣል፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ሁላችሁ ደስ ይበላችሁ እል በሉ አጨብጭቡ ” ብለው ሲናገሩ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያለው ምዕመን በሙሉ እልልታውን እና ጭብጨባውን አስተጋባ፡፡ ከመካከላቸውም አንድም ሰው ለምን? እና እንዴት? ብሎ የጠየቀ ምዕመን አልነበረም ፡፡ በሁኔታው በጣም የተበሳጩት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊመንበር በፍጥነት ወደ መድረኩ መጥተው ቀደም ተብሎ የተነገረው ሁሉ ስህተት መሆኑን እያስረዱ እያለ ተናግረው ሳይጨርሱ እልታው እና ጭብጨባው ከበፊቱ በበለጠ አስተጋባ ፡፡  ለትክለኛውም ለተሳሳተውም መረጃ ሳይመረምር በፍጥነት እልልታውን ያሰማው በአንድ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበ አንድ መንጋ ነው፡፡በማለት የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡፡
በንግስ በዓላት፣ስዕለት የሰመረለት በማህሌት ምስጋና ማቅረብ የሚሻ ሁሉ በእልልታ እና በጭብጨባ ምሰስጋና ያቀርባል፡፡ በታላላቅ አጽዋማት እና በሱባኤ ወቅት ሀዘን ተመስጦ እና ንሥሐ እንጂ እልልታ ጊዜው አይደለም፡፡ እልልታ መቼ እና እንዴት መባል እንዳለበት እልል አስባዩም እልል ባዩም ሊያውቅ ይገባል፡፡ አነስ ያለች የእልታ ድምፅ ስለተሰማ ብቻ ያን ተቀብሎ አድምቆ እልል ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ አንዲት ዘወትር ከእግዚአብሔር ቤት የማይለዩ እናት ያጋጠማቸውን እንዲህ አጫውተውኝል፡፡ በሰንበት ቅዳሴ ለማስቀደስ ቤተ ክርስቲያን ሄደን አንድ በሩቁ ከማውቃቸው ባልቴት ጎን ለጎን ተቀምጠናል፡፡ ከቅዳሴ በኋላ መብራት በመጥፋቱ የተነሳ ድምፅ ማጉያው ስለማይሠራ ከቤተምቀደሱ የሚተላለፈው መልእክት በደንብ ባይሰማም አንድ ካህን ስለ አንድ የደብሩ አገልጋይ በሞት መለየት ተናገሩ፡፡ ከወደ ኋላችን ግን የአንድ ሴት የእልልታ ድምፀ ተሰማ፡፡ አጠገቤ ያሉት ባልቴት ወዲያውኑ እልልታውን ተቀብለው አድምቀው እልታ አሰሙ፡፡ ከወደፊት ያለው ሰው በሙሉ ፊቱን ወደ እኛ ሲያዞር በጣም ተሸማቀኩ፡፡በሁኔታው በጣም አዝኜ አጠገቤ ያሉትን ሴት “እሜቴ ለመሆኑ ምን እንደተባለ ሰምተው ነው እልልታውን ያቀለጡት ብላቸው ? ሴትዬዋ ፈጠን ብለው አዬ ልጄ  የተባለውን እንኳን ምንም አልሰማሁም! ዳሩ ግን መምሬ እገሌ እኮ ምንጊዜም ቢሆን መልካም እንጂ ክፉ ነገር አይናገሩም ብዩ ነው” ቡለውኝ አረፉት፡፡በማለት ነግረውኛል፡፡ 
ስብከተ ወንጌል አገልግሎት እየተሰጠ መምህራን እያቋረጡ እልልታን የሚያሰሙ አሉ፡፡ አንዳንድ መምህራን እንዲያውም ትምህርታቸውን አቋርጠው እባካችሁ እኔ እልል በሉ ስላችሁ ትላላችሁ ብለው ማሳሰቢ እስከመስጠት ይደርሳሉ፡፡ መምህራን  አስተምረው ከመድረክ ሲወርዱ እንደቀደሙት አባቶቻችን ሥርዓት “ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ፤ የኃጢአት መደምሰሻ ያድርግልህ” የሚለው ምርቃት ቀርቶ አዲስ ሥርዓት በሆነው በደመቀ እልልታ እና ጭብጨባ መታጀብ ሆኖአል፡፡ ይህን ስህተት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው ብሎ በይፋ ማስተካከያ የሰጠ ሰባኬ ወንጌሌም ይሁን ሰባኪ አላጋጠመኝም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የደመቀ እልልታ እና የማያቋርጠው ጭብጨባ ከሌለ በድጋሚ እዚያ ቦታ መጥቶ ማስተር የማይፈልግ መምህርም አይጠፋም፡፡ በአሥራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት ዓመተ ምህረት ገደማ  በወቅቱ የስብከት አገልግሎት በመስጠት የታወቁ አንደበተ ርዕቱዕ መነኩሴ ነበሩ ፡፡ ታዲያ ቅዱስ ወንጌልን እየሰበኩ በየትመህርቱ መሀል ያቋርጡና “እዚህ ጋር ሦስት ጊዜ አጨብጭቡ ፤ እልልም በሉ”ይሉ ነበር፡፡ ይህን የተመለከቱ ሌሎች መምህራንም እንደሳቸው ማስጨብጨብን ጀመሩ፡፡ ነገሩ እንግዳ ልማድ ቢሆንም እንኳን ምዕመኑ በደስታ ተቀብሎት ያጨበጭብ ጀመር ፡፡ በኋላም ታላላቅ  የቤተ ክርስቲያን አባቶች መነኩሴውን ጠርተው አዲስ ሥርዓት አታምጡ፤ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት እንጂ፤  በጭብጨባ የሚታጀበው ዓለማዊ ስብሰባ አይደለም በማለት ገስጸው ሥህተታቸውን እንዲያርሙ አድርገዎቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ለረጅም ዘመን ተቋርጦ የነበረው በስብከት መሀል እና አስተማሪ አስተምሮ ሲጨርስ ማጨብጨብ እልልታን አስከትሎ እንደ አዲስ መጥቷል፡፡ ይህ አዲስ ነገር የተጀመረው በዚህ ጊዜ እና በእገሌ አማካኝነት ነው ማለት ባይቻልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡በሚገርም ፍጥነትም አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ መስፋፋት ችሎአል፡፡
ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ፣ መምህራን ፣ሰባኬያነ ወንጌል በትህትና እና በሥርዓት የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቀኖናዋ ውጭ የሆነ ተግባር ሲፈጸም ለማረም ለምን ቸል ይላሉ የሚለው ያልተለመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ያልተገባውን እልልታ ከንቱንም ውዳሴ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ፣ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉት ለምን  ይሆን ? ተስማምተውበት ወይስ ይሉኝታ ይዟቸው፡፡  በቀደመ  ዘመን የነበሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቅእነታቸው በአደባባይ ተመስክሮላቸው ንግግራቸው በትህትና ነበር፡፡እውነት የሆነው ትምህርታቸው እና እውቀታቸው በአደባባይ እንዲነገር ሰዎች እንዲያውቁላቸው እንዲያወድሷቸው ፈቃደኛ አልነበሩም ፈጽሞ ይቃወሙት ነበር፡፡ የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበሩት አንድ መምህር በአንድ ዓውደምህረት ላይ ሲያስተምሩ መርሐግብር መሪው ሰፋ አድርጎ አሞግሶ የሊቃውንት ጉባኤ አባል መሆናቸውን እና ሊቅ መሆናቸውን ተናግሮ እንዲያስተምሩ ጋበዛቸው፡፡ መምህሩ ለመስተማር ወደ አውደ ምህረቱ ሲወጡ በመጀመሪያ የተናገሩት እርሳቸው ሊቅ መባል እንደማይገባቸው ሊቃውንትስ ሰው የማያውቃቸው እንደኔ በመድረክ ያልታዩ ታላላቅ አባቶች በቤተ ክርስቲያን እንዳሉ ገሚሶቹም እንዳለፉ እርሳቸው ከሁሉ ያነሱ ታናሽ መሆናቸውን እና የሊቃውንት ጉባኤም አባል የሆኑት እንዲያው ቁጥር ለማሞላት እንደሆነ ከልብ በሆነ ሰሜት ለተሰባኪው ምእመናን በአጽንኦት እንዲገነዘቡ አድርገው እርማት ሰጥተዋል፡፡ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ሰምተው ዝም ብለው የሚሄዱት ቢበዙም፤ አልፎ አልፎ ግን ማስተካከያ የሚሰጡ አሉ ፡፡ በቅርቡ በአንድ ቤተ ክርስቲያን በወርሃዊ በዓል ላይ ያጋጠመኝን አስታወሳለሁ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል እንደለመደው በዕለቱ ለማስተማር ለተጋበዙት መምህር ብዙ ውዳሴ አቀረበ፤ እል አስባለላቸው፡፡ ትምህርቱን እንዲያስተምሩ መምህሩን ጋብዞ ከመድረክ ወረደ፡፡ ወጣቱ ሰባኬ ወንጌልም መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ይሉይኝታ ሳይዘው እና ሳያፍር “ቀደም ሲል ሰባኬ ወንጌሉ ስለ እኔ የተናገሩት በሙሉ ስህተት ነው” ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ “የተወደዳችሁ ምዕመናን እዚህ የመጣችሁት የእግዚአብሔርን ቃል ልትሰሙ እንጂ ገና መጨረሻችን እንኳን ያልታወቀውን የእኔ አይነቱን ደካማ ዝና ለመስማት አይደለም፤ ስለዚህ ምዕመናን ይህን የማይጠቅም ነገር ከአይምሮአችሁ ሰሌዳ ውስጥ ሰርዙት፣ ደምስሱት፣ እባካችሁ ፈጽማችሁ አጥፉት” በማለት በማስተካከያ ሰጥቶ፤ ሰባኬ ወንጌሉን በአውደ ምህረቱ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ሲያስተምር ተመልክቻለሁ፡፡
 ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት እመቤት ናት፤ በምን አይነት ሁኔታ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባት የሚመራት ሕግ እና ቀኖና አላት፡፡ በዘፈቀደ የሚሆን ነገር የለም፤ ለ ዕልልታው፣ ለጭብጨባው፣ ለምስጋናውም ሥርዓት አለው፡፡ ከዓለማዊ  ጉባኤ፣ ስብስብ የምንለይበትም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተዘጋጀው ሥርዓታችን ነው፡፡ ለዓውደ ምህረት አዳዲስ ልማዶችን ማስተናገጃ መሆን ተጠያቂው ማነው? የሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘም ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በገዛ የራሷ ልጆች ሥርዓቷን ስትጥስ የሚያርም አካል የላትም፡፡ የስበከተ ወንጌል ኃላፊዎችም ሌላው ጋር የተመለከቱትን ስህተት ጨማምረው እና አሻሽለው ወፍራም ስህተት ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ በአንዱን ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት የሰራውን ስህተት በሌላኛው ሲደገም ማየታችን፤ ከከተማ እስከ ገጠር በተመሳሳይ ጊዜ መዳረሱ ስጋት ላይ ይጠለናል፡፡  ሕገ ቤተ ክርሰቲያን ይጣሳል፤ ለወደፊትም መጥፎ ልማድ ያመጣል በማለት አርቀን አስበን በማስተዋል ስንሠራ አንታይም፡፡ ምዕመኑም ቢሆን እል በሉ ሲባል እልል ከማለት ውጪ፤ አጨብጭቡ ሲባል ከማጨብጨብ ውጪ፤ ለምን እና በምን ሁኔታ ማለት እንዳለበት ሊያውቅ ፤ ለስብከተ ወንጌል መሥፋፋት ገንዘቡን ሳይሰስት ፣ጉልበቱን ሳይቆጥብ እንደሚሰጥ ሁሉ የእኔስ ተሳትፎዬ ምንድነው ብሎ ሊጠይቅ ይገባው ነበር፡፡ ከዚህ የከፋ ሥርዓት ቢመጣ እልል እልል ብለን እንቀበለዋለን ወይ? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ምዕመናን “ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።”ዕብ 13፥9 እንዳለ በነፈሰው ነፋስ ሁኑ እናዳይወስደን እሰጋለሁ!

ያዕቆብ ሰንደቁ
ሚያዚያ 15 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ