በዓላት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ትንሣኤ ልቡና
“በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ
መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲሰጡት
አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ
አንከባሎ ሄደ። መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ። በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ
በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን
በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥
የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ጲላጦስም ጠባቆች
አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።”
የማቴዎስ ወንጌል 27፥57-66
“ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም
እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ።
እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም
አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ
አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን፦ አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ
እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ
ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው። መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም
አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ” የማርቆስ ወንጌል 16፥1-8
“ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።” የሉቃስ ወንጌል 24፥1-12
“ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ
ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ
ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና
ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና
አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም
ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ
ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም
ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም
ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ። ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ
መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም
በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም
እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥
አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር
ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤
ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው
አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።” የዮሐንስ ወንጌል 20፥1-18
ጌታችን አስቀድሞ ይህን ቤተ
መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አስነሳዋለው፤ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ ብሎ በተናገረው መሰረት መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ
ፍቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ውለታቸውን አስበው በማለዳም ሽቶ ለመቀባት የመጡት ሴቶች፤ ጲላጦስም እንዲጠብቁት ያዘዛቸው ወታደሮች የዘጉትን የመቃብሩን ድንጋይ ማን ያነሳልናል? ብለው አዝነው ነበር፡፡ ነገርግን
በመቃብሩ ራስጌና ግርጌ የነበሩት ቅዱሳን መላእክት ታላቁን ድንጋይ አንከባለው እንደተናገረው ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሳቱን
አበሰሩአቸው፡፡ የሚያስፈራው እና ሀዘን የተሞላው የመቃብር ስፍራ በብርሃን ጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ የመቃብሩ ድንጋይ ተንከባሎ
በውስጡም ጌታ የለበሰው ልብስ ብቻ ታየ፡፡ የትንሣኤውንም ምስራች ለወንድሞች ሐዋርያት ሊናገሩ ሴቶቹ ፈጥነው ሄዱ፡፡
ትንሣኤ የበዓላት ሁሉ በኵር
ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሥጋቸው በመቃብር በስብሶ ነፍሳቸው በሲኦል ወይህኒ የነበሩት አዳም እና ልጆቹ ነፃ
የወጡበት ዕለት ነው፡፡ ሞት፣ መቃብር፣ የሲኦል ጨለማ ድል ተነሳ ፡፡ ዲያብሎስ ተንሰራፍቶ ከያዘው ሥልጣን በውርደት ተሻረ፡፡
ከመቃብር በኋላ መነሳት፤ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ተረጋገጠ፡፡ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤
መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ
ክፉም ያደረጉ ለፍርድ
ትንሣኤ ይወጣሉ”ዮሐ.5፥28 እንደተባለ ሙታንም ሁሉ በአዋጅ በአንድ እንደሚነሱ ታወቀ፡፡ በሕጉ እና በትእዛዙ የተጎዙት
ጌታችን የሰጠን የሕይወት ትንሣኤ ይካፈላሉ፡፡ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ
ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” እንዳለ ሐዋርያው ፡፡ ሮሜ. 6፥5
የመድኃኒታችን ትንሣኤ ከባርነት ወደ ነፃነት፤ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት
ነው፡፡ ጌታችን
በመዋዕለ ትምህርቱ “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ 16፥33 እንዳለን በእርሱ ትንሣኤው የእኛ ትንሣኤ፤ በእርሱ ድል አድራጊነት
እኛም ዓለምን እንደምናሸንፍ አረጋገጠልን፡፡ በሞት ማሰሪያ የተተበተበው ደካማው የአዳም ሕይወት የማሸነፍ ኃይል አገኝ፡፡ የተጫነበት
እጅግ ትልቁ የመቃብር ድንጋይ ከፊቱ ገለል እንዲደረግለት ሆነ፡፡ መንገዱም በትንሣኤው ብርሃን ተቅናናለት፡፡
የትንሣኤ በዓል ስናከብር
እግዚአብሔር የሰጠንን አንጸባራቂ የማሸነፍ ኃይል በማሰብ፤ ብርሃንኸን ላክልን፣በልቦናችን አብራልን እያልን እንዘምራለን፡፡ የክርስትና ሕይወት ኃጢአትን እና ዓለምን
አሸንፎ በትንሣኤው ብርሃን የደመቀ ልቦና ይዞ ለእግዚአብሔር መንግስት መዘጋጀት ነው፡፡በዓሉ የሚከበርበት ዐብይ ምክንያትም እንደ
መቃብር ድንጋይ የተዘጋብን የዚህ ዓለም ኃጢአት አንከባለን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ነው፡፡ሐዋርያው “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ
በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው
ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤”
ፊል. 3፥10-11 እንዳለ እግዚአብሔር ያማናውቅ እንድናወቅ፤ ያልቀረብን እንድንቀርብ በትንሣኤ መሰናክሉ ሁሉ ተወገደልን፡፡እግዚአብሔር በሰጠን ዘመን የትንሣኤን
በዓል ስናከብር በልባችን ደንዳናነት ጠንቅ የጨለመውን ሕይወታችንን በማስተካክል ትንሣኤ ልቡና በማምጣት ይሁን፡፡
ክርስቶስ ተነስቷአል በመቃብር ውስጥም የለም!
መልካም ፋሲካ ለሁላችንም ይሁንልን!
ያዕቆብ
ሰንደቁ
ቅዳሜ
ሚያዚያ 22 ቀን 2008ዓ.ም
አዲስ
አበባ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ