ዓርብ 22 ኤፕሪል 2016

ወግ እልል በሉ

እልል በሉ
 በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለንግስ በዓል በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መዳረሻ በሰው ተሞልቷል፤ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ሴቱ ፣ወንዱ ተሰብስቧል፡፡ የተጋበዘውም መምህር ከአሥራ አምስት ቀን አስቀድሞ ባስተማረባቸው መድረኮች ሁሉ በእዚህ ቦታ ተገኝቶ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር፡፡ በየታከሲው ፣ በየመንገዱም የስብከቱን ርዕስ `ጠቅሶ የወረቀት ማስታወቂያዎችን ለጥፎ ይህንንም ብዙ ሰው ሰምቶ እና ተጠራርቶ እንዲመጣ ረድቷል፡፡ በዓውደ ምህረቱ በግራ እና ቀኝ በኩል ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች ተተክለዋል፡፡ ከድምፅ ማጉያው የሚወጣው ድምፅ ምድርን ያንቀጠቅጣል፡፡ በየሠርግ ቤት እንደምናየው የዓውደ ምህረቱም ዓዕማድ/ምሰሶዎች/ ዙሪያውን በነጭ ሻማ ጨርቅ ጥቅልል ተደርገዋል፣ በክብ ቅርጽ በአንድ ላይ የታጨቁ ልዩ ልዩ ቀለም ያላቸው ፊኛዎች ተሰድረዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪም በጸሎት መርሐግብሩን ከፈቱ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል ቀጠል አደረጉና “አሁን በቀጥታ ሁላችሁም በጉጉት ወደምጠብቀው  መምህር እወስዳችኋለሁ” አሉ፡፡ እኔም በልቤ “ጎሽ ወደ ትምህርቱ ልንተላለፍ ነው” ብዬ የልቦናዬን ሰሌዳ አዘጋጀሁ፡፡ ሰባኬ ወንጌሉ “ከዚያ በፊት ግን ምዕመናን”  አሉ “የዕለቱን መምህር ላስተዋውቃችሁ” በማለት እንደገና ንግግር ሲጀምሩ፤ ከበስጭቴ የተነሳ ሀሞቴ ፈሰሰ፡፡  ንግግራቸውን ቀጠሉ “መምህራችንን ዛሬ ወደዚህ ዓውደ ምህረት ለማምጣት በጣም ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለን፤ ከብዙ ቦታ ተሻምተን ነው ፡፡ ስለዚህ ደስ ይበላችሁ ምዕመናን እስቲ እልል ብላችሁ አመስግኑ” አሉ፡፡ ምዕመኑም ወዲያውኑ በእልልታ ጸፈውን መለሰ፡፡ ቀጠሉም እንዲህ አሉ “እውነት ነው የምላችሁ! መምህራችን እውቀታቸው የመጠቀና የረቀቀ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ተዘዋውረው ያስተምራሉ፤ እነሆ ዛሬ እኛን ለማስተማር ውድ ጊዜአቸውን ሰውተው ስለመጡ ወንዶች በጭብጨባ ሴቶች በእልልታ እንኳን ደህና መጡልን አንድትሉ እጠይቃለሁ” አሉ፡፡ ለእልልታና ለጭብጨባ በቋፍ ላይ የሚገኘው ምእመን መታዘዙ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት ድምቅ አድርጎ እልልታውን እና ጭብጨባውን አሰማ፡፡ “ያንሳል እስቲ ድገሙት” ተባለ ምዕመኑ እንደገና “እልል እልል አለ ”መምህራችን ወደ መድረረኩ እየመጡ ስለሆነ እስቲ በጭብጨባ “ሾዋ፣ ሾዋ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው” ተባለ፡፡ ምዕመኑም እያጨበጨበ ጌጠኛ ጥቁር ቀሚስ የለበሰ አጠር ደልደል ያለ መምህር ወደ መድረኩ መጣ፡፡
ሁሉም ዐይኖቹን ወደ ዓውደ ምህረቱ ተክሎ በትኩረት ያያል፡፡ ከመምህሩ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ አጠር አና ደልደል ያለ ወጣት መምህር ወደ መድረኩ ወጥቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ቆመ፤ የምዕመኑ ጭብጨባው ያባራው መምህሩ ተረጋግቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ከቆመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው፡፡ በሁኔታው በጣም ግራ ገባኝ፤ በአውደ ምህረቱ ላይ የተቀመጡት ታላላቅ አባቶች ሁኔታውን ሳይቃወሙ በዝምታ ይመለከታሉ፡፡ እንደገናም መለስ ብዬ “መቼም መምህሩ በታላቁ ዐቢይ ጾም የማህሌቱ ከበሮ ተሰቅሎ ሳለ ፤ ለእርሱ የተጎሰመውን የምስጋና ነጋሪት እና እልልታ ውጦ ዝም አይልም፡፡ እንዲያውም ተቋውሞውን በመግለጽ የደብሩን ሰባኬ ወንጌል ይወቅሳል፤የተፈጸመውም ድርጊት ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ውጭ መሆኑን ጠቅሶ ማስተካከያ ይሰጣል ብዬ ተጽናናሁ ፡፡
 ወጣቱ መምህር ሰላምታውን ጨርሶ ካበቃ በኋላ “በዙሪያው ያላችሁ ምእመናን በሙሉ ሁለት እጃችሁን ወደ ላይ ወደ ሰማይ ዘርጉ” አለ፡፡ እኔም በሁኔታው ተገርሜ “ወይ ጉድ ይባስ አታምጣ! ደግሞ ጭብጨባው እልልታው ሳያንስ እጃችሁን ኪሳችሁ ውስጥ ከታችሁ ገንዘብ አምጡ ሊል ነው” ብዬ ኪሴን አሰቡኩት፡፡ ሁሉም እጁን አወጣ ከዚያም “ሦስቴ እልል ብላችሁ አጨብጭቡበት” አላቸው፡፡ ምዕመኑም እልታውን አደመቀው፡፡ መምህሩም ያንሳል፣ ያንሳል ምዕመናን ድገሙት ብሎ በድጋሚ አስደገማቸው፡፡ ከዚያም ቀጠለና ከሀገረ ስብከት የመጡትን እንግዶች፣ የደብሩን አስተዳዳሪን፣ የቤተ ክርስቲያኑን ፀሐፊ፣ የሰባኬ ወንጌሉንም ስም እየጠራ ተራ በተራም እያስጨበጨ እልል አስባለላቸው፡፡
ምዕመናን  “ለዛሬ ወደተዘጋጀው ትምህርት ከማለፌ በፊት አንድ ማሳሰቢያ አለኝ” አለ መምህሩ ፡፡ ቆጣ ባለ ድምፅ “ምእመናን ቁጥራችሁ ብዙ ቢሆንም  የእልልታ ድምፃችሁ ግን አነስተኛ ነው፤ስታጨበጭቡም አይሰማም፤ ስለዚህ ጉባኤው አልደመቀም፤”አለ፡፡ ቀጠል አድርጎም መዝሙረኛው ዳዊት እንኳ በመዝ 47÷1 “አሕዛብ ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ፡፡” ይላል በማለት እርሱ ከፈጸመው ድርጊት ጋር ባይስማማም በስፋት የእልልታን ጠቀሜታ አስተማረ፡፡  እኔም ከአሁን አሁን በማስታወቂያ ላይ የተለጠፈውን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን ርዕስ ትምህርት ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ነገር ግን ማስታወቂያ የተነገረለት ወቅታዊው የትምህርት ርዕስ ተዘንግቶ ካለጊዜው እና ሰዓቱ እልልታን በመጻፍም፣ በተግባርም መማር ጀመርን፡፡
በመሀል በሀሳብ ተጠልፌ ያለሁበትን እስክረሳ ድረስ ከውስጤ ጋር ሙግት ጀመርኩ ፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የመደንገግ፣ የማሻሻል ሥልጣን ያለው ማነው ? ቅዱስ ሲኖዶስ ወይስ? መምህራን፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ የአካባቢ ወጣቶች ፤ ቆይ ከመቼ ጀምሮ ነው በታላቁ ዐብይ ጾም ማጠናቀቂያ ሳምንት ውስጥ እልታ እና ጭብጨባ ፤ በመጽሐፉ እንደ ተጻፈ እልልታ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት እንጂ የግለሰቦችን በውዳሴ ከንቱ የምንጠልፍበት ገመድ ነው እንዴ ? እያልኩ ከራሴ ጋር እሞገታለሁ ፡፡  በግምት ሰላለሳ ደቂቃ ያህል በሀሳብ ማዕበል ስንገላታ ቆየሁ፡፡ልክ መምህሩ ወደ ዕለቱ ትምህርት መሸጋገሩን ሲናገር ከያዘኝ ተመስጦ ነቃሁ፡፡
 መምህሩ በየታክሲው እና በየመንገዱ ላይ ከራሳቸው ስም ቀጥሎ በጉልህ የለጠፉትን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን የትምህርት ርዕስ ያስተምራሉ ብዬ ብጠብቅም ባልታወቀ ምክንያት ርዕሱን ቀይረው “ሉሲፈር እና ሥራው” ብለው ትምህርት መስጠት ጀመሩ፡፡ ለአርባ ደቂቃም ካስተማሩ በኋላ ሰዓት አልቋል ተብለው በወንዶች ጭብጨባ በሴቶች እልልታ ታጅበው ከአውደ ምህረቱ ወረዱ፡፡
እልልታ ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ የምስጋና መሥዋዕት ነው፡፡ ይህም በጥንቃቄ ይፈጸማል እንጂ በልማድ እና በዘፈቀደ አይከናወንም፡፡ እልልታን ተቀባብሎ ለማለት የምእመናን ፍጥነት ይገርማል ፡፡ ከሌላው ሰው ስለሰሙ ብቻ እልልታቸውን የሚያሰሙ አሉ፡፡ በአንድ ወቅት የደብራችን ሰበካ ጉባኤ ሊመንበር የነበሩት ሰው በተመሳሳይ ርዕስ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ስንለዋወጥ ያጫወቱኝን አስታውሳለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡ በወቅቱ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር መንፈሳዊ አገልገሎት እያስታጎሉ ያስቸገሩ ዲቆናትን እና ቀሳውስትን ጠርቶ ምክርም ይሰጣል፡፡ ምክርሩን ሰምተው ጥፋታቸውን ያላረሙትን አገልጋዮች ቀጣቸው፡፡ በዕለተ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ከተቀጡት መካከል አንዱ ካህን በድምፅ ማጉያ ማስታወቂ ተናገሩ “ሰበካ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኑን በሚገባ ማስተዳደር ስላልቻለ፤ የበላይ አካላት በወሰኑት መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ከኃላፊነቱ ተሸሮል፡፡ በቅርብ ቀን አዲስ ሰበካ ጉባኤ ይመረጣል፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ሁላችሁ ደስ ይበላችሁ እል በሉ አጨብጭቡ ” ብለው ሲናገሩ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያለው ምዕመን በሙሉ እልልታውን እና ጭብጨባውን አስተጋባ፡፡ ከመካከላቸውም አንድም ሰው ለምን? እና እንዴት? ብሎ የጠየቀ ምዕመን አልነበረም ፡፡ በሁኔታው በጣም የተበሳጩት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊመንበር በፍጥነት ወደ መድረኩ መጥተው ቀደም ተብሎ የተነገረው ሁሉ ስህተት መሆኑን እያስረዱ እያለ ተናግረው ሳይጨርሱ እልታው እና ጭብጨባው ከበፊቱ በበለጠ አስተጋባ ፡፡  ለትክለኛውም ለተሳሳተውም መረጃ ሳይመረምር በፍጥነት እልልታውን ያሰማው በአንድ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበ አንድ መንጋ ነው፡፡በማለት የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡፡
በንግስ በዓላት፣ስዕለት የሰመረለት በማህሌት ምስጋና ማቅረብ የሚሻ ሁሉ በእልልታ እና በጭብጨባ ምሰስጋና ያቀርባል፡፡ በታላላቅ አጽዋማት እና በሱባኤ ወቅት ሀዘን ተመስጦ እና ንሥሐ እንጂ እልልታ ጊዜው አይደለም፡፡ እልልታ መቼ እና እንዴት መባል እንዳለበት እልል አስባዩም እልል ባዩም ሊያውቅ ይገባል፡፡ አነስ ያለች የእልታ ድምፅ ስለተሰማ ብቻ ያን ተቀብሎ አድምቆ እልል ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ አንዲት ዘወትር ከእግዚአብሔር ቤት የማይለዩ እናት ያጋጠማቸውን እንዲህ አጫውተውኝል፡፡ በሰንበት ቅዳሴ ለማስቀደስ ቤተ ክርስቲያን ሄደን አንድ በሩቁ ከማውቃቸው ባልቴት ጎን ለጎን ተቀምጠናል፡፡ ከቅዳሴ በኋላ መብራት በመጥፋቱ የተነሳ ድምፅ ማጉያው ስለማይሠራ ከቤተምቀደሱ የሚተላለፈው መልእክት በደንብ ባይሰማም አንድ ካህን ስለ አንድ የደብሩ አገልጋይ በሞት መለየት ተናገሩ፡፡ ከወደ ኋላችን ግን የአንድ ሴት የእልልታ ድምፀ ተሰማ፡፡ አጠገቤ ያሉት ባልቴት ወዲያውኑ እልልታውን ተቀብለው አድምቀው እልታ አሰሙ፡፡ ከወደፊት ያለው ሰው በሙሉ ፊቱን ወደ እኛ ሲያዞር በጣም ተሸማቀኩ፡፡በሁኔታው በጣም አዝኜ አጠገቤ ያሉትን ሴት “እሜቴ ለመሆኑ ምን እንደተባለ ሰምተው ነው እልልታውን ያቀለጡት ብላቸው ? ሴትዬዋ ፈጠን ብለው አዬ ልጄ  የተባለውን እንኳን ምንም አልሰማሁም! ዳሩ ግን መምሬ እገሌ እኮ ምንጊዜም ቢሆን መልካም እንጂ ክፉ ነገር አይናገሩም ብዩ ነው” ቡለውኝ አረፉት፡፡በማለት ነግረውኛል፡፡ 
ስብከተ ወንጌል አገልግሎት እየተሰጠ መምህራን እያቋረጡ እልልታን የሚያሰሙ አሉ፡፡ አንዳንድ መምህራን እንዲያውም ትምህርታቸውን አቋርጠው እባካችሁ እኔ እልል በሉ ስላችሁ ትላላችሁ ብለው ማሳሰቢ እስከመስጠት ይደርሳሉ፡፡ መምህራን  አስተምረው ከመድረክ ሲወርዱ እንደቀደሙት አባቶቻችን ሥርዓት “ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ፤ የኃጢአት መደምሰሻ ያድርግልህ” የሚለው ምርቃት ቀርቶ አዲስ ሥርዓት በሆነው በደመቀ እልልታ እና ጭብጨባ መታጀብ ሆኖአል፡፡ ይህን ስህተት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው ብሎ በይፋ ማስተካከያ የሰጠ ሰባኬ ወንጌሌም ይሁን ሰባኪ አላጋጠመኝም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የደመቀ እልልታ እና የማያቋርጠው ጭብጨባ ከሌለ በድጋሚ እዚያ ቦታ መጥቶ ማስተር የማይፈልግ መምህርም አይጠፋም፡፡ በአሥራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት ዓመተ ምህረት ገደማ  በወቅቱ የስብከት አገልግሎት በመስጠት የታወቁ አንደበተ ርዕቱዕ መነኩሴ ነበሩ ፡፡ ታዲያ ቅዱስ ወንጌልን እየሰበኩ በየትመህርቱ መሀል ያቋርጡና “እዚህ ጋር ሦስት ጊዜ አጨብጭቡ ፤ እልልም በሉ”ይሉ ነበር፡፡ ይህን የተመለከቱ ሌሎች መምህራንም እንደሳቸው ማስጨብጨብን ጀመሩ፡፡ ነገሩ እንግዳ ልማድ ቢሆንም እንኳን ምዕመኑ በደስታ ተቀብሎት ያጨበጭብ ጀመር ፡፡ በኋላም ታላላቅ  የቤተ ክርስቲያን አባቶች መነኩሴውን ጠርተው አዲስ ሥርዓት አታምጡ፤ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት እንጂ፤  በጭብጨባ የሚታጀበው ዓለማዊ ስብሰባ አይደለም በማለት ገስጸው ሥህተታቸውን እንዲያርሙ አድርገዎቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ለረጅም ዘመን ተቋርጦ የነበረው በስብከት መሀል እና አስተማሪ አስተምሮ ሲጨርስ ማጨብጨብ እልልታን አስከትሎ እንደ አዲስ መጥቷል፡፡ ይህ አዲስ ነገር የተጀመረው በዚህ ጊዜ እና በእገሌ አማካኝነት ነው ማለት ባይቻልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡በሚገርም ፍጥነትም አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ መስፋፋት ችሎአል፡፡
ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ፣ መምህራን ፣ሰባኬያነ ወንጌል በትህትና እና በሥርዓት የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቀኖናዋ ውጭ የሆነ ተግባር ሲፈጸም ለማረም ለምን ቸል ይላሉ የሚለው ያልተለመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ያልተገባውን እልልታ ከንቱንም ውዳሴ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ፣ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉት ለምን  ይሆን ? ተስማምተውበት ወይስ ይሉኝታ ይዟቸው፡፡  በቀደመ  ዘመን የነበሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቅእነታቸው በአደባባይ ተመስክሮላቸው ንግግራቸው በትህትና ነበር፡፡እውነት የሆነው ትምህርታቸው እና እውቀታቸው በአደባባይ እንዲነገር ሰዎች እንዲያውቁላቸው እንዲያወድሷቸው ፈቃደኛ አልነበሩም ፈጽሞ ይቃወሙት ነበር፡፡ የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበሩት አንድ መምህር በአንድ ዓውደምህረት ላይ ሲያስተምሩ መርሐግብር መሪው ሰፋ አድርጎ አሞግሶ የሊቃውንት ጉባኤ አባል መሆናቸውን እና ሊቅ መሆናቸውን ተናግሮ እንዲያስተምሩ ጋበዛቸው፡፡ መምህሩ ለመስተማር ወደ አውደ ምህረቱ ሲወጡ በመጀመሪያ የተናገሩት እርሳቸው ሊቅ መባል እንደማይገባቸው ሊቃውንትስ ሰው የማያውቃቸው እንደኔ በመድረክ ያልታዩ ታላላቅ አባቶች በቤተ ክርስቲያን እንዳሉ ገሚሶቹም እንዳለፉ እርሳቸው ከሁሉ ያነሱ ታናሽ መሆናቸውን እና የሊቃውንት ጉባኤም አባል የሆኑት እንዲያው ቁጥር ለማሞላት እንደሆነ ከልብ በሆነ ሰሜት ለተሰባኪው ምእመናን በአጽንኦት እንዲገነዘቡ አድርገው እርማት ሰጥተዋል፡፡ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ሰምተው ዝም ብለው የሚሄዱት ቢበዙም፤ አልፎ አልፎ ግን ማስተካከያ የሚሰጡ አሉ ፡፡ በቅርቡ በአንድ ቤተ ክርስቲያን በወርሃዊ በዓል ላይ ያጋጠመኝን አስታወሳለሁ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል እንደለመደው በዕለቱ ለማስተማር ለተጋበዙት መምህር ብዙ ውዳሴ አቀረበ፤ እል አስባለላቸው፡፡ ትምህርቱን እንዲያስተምሩ መምህሩን ጋብዞ ከመድረክ ወረደ፡፡ ወጣቱ ሰባኬ ወንጌልም መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ይሉይኝታ ሳይዘው እና ሳያፍር “ቀደም ሲል ሰባኬ ወንጌሉ ስለ እኔ የተናገሩት በሙሉ ስህተት ነው” ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ “የተወደዳችሁ ምዕመናን እዚህ የመጣችሁት የእግዚአብሔርን ቃል ልትሰሙ እንጂ ገና መጨረሻችን እንኳን ያልታወቀውን የእኔ አይነቱን ደካማ ዝና ለመስማት አይደለም፤ ስለዚህ ምዕመናን ይህን የማይጠቅም ነገር ከአይምሮአችሁ ሰሌዳ ውስጥ ሰርዙት፣ ደምስሱት፣ እባካችሁ ፈጽማችሁ አጥፉት” በማለት በማስተካከያ ሰጥቶ፤ ሰባኬ ወንጌሉን በአውደ ምህረቱ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ሲያስተምር ተመልክቻለሁ፡፡
 ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት እመቤት ናት፤ በምን አይነት ሁኔታ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባት የሚመራት ሕግ እና ቀኖና አላት፡፡ በዘፈቀደ የሚሆን ነገር የለም፤ ለ ዕልልታው፣ ለጭብጨባው፣ ለምስጋናውም ሥርዓት አለው፡፡ ከዓለማዊ  ጉባኤ፣ ስብስብ የምንለይበትም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተዘጋጀው ሥርዓታችን ነው፡፡ ለዓውደ ምህረት አዳዲስ ልማዶችን ማስተናገጃ መሆን ተጠያቂው ማነው? የሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘም ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በገዛ የራሷ ልጆች ሥርዓቷን ስትጥስ የሚያርም አካል የላትም፡፡ የስበከተ ወንጌል ኃላፊዎችም ሌላው ጋር የተመለከቱትን ስህተት ጨማምረው እና አሻሽለው ወፍራም ስህተት ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ በአንዱን ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት የሰራውን ስህተት በሌላኛው ሲደገም ማየታችን፤ ከከተማ እስከ ገጠር በተመሳሳይ ጊዜ መዳረሱ ስጋት ላይ ይጠለናል፡፡  ሕገ ቤተ ክርሰቲያን ይጣሳል፤ ለወደፊትም መጥፎ ልማድ ያመጣል በማለት አርቀን አስበን በማስተዋል ስንሠራ አንታይም፡፡ ምዕመኑም ቢሆን እል በሉ ሲባል እልል ከማለት ውጪ፤ አጨብጭቡ ሲባል ከማጨብጨብ ውጪ፤ ለምን እና በምን ሁኔታ ማለት እንዳለበት ሊያውቅ ፤ ለስብከተ ወንጌል መሥፋፋት ገንዘቡን ሳይሰስት ፣ጉልበቱን ሳይቆጥብ እንደሚሰጥ ሁሉ የእኔስ ተሳትፎዬ ምንድነው ብሎ ሊጠይቅ ይገባው ነበር፡፡ ከዚህ የከፋ ሥርዓት ቢመጣ እልል እልል ብለን እንቀበለዋለን ወይ? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ምዕመናን “ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።”ዕብ 13፥9 እንዳለ በነፈሰው ነፋስ ሁኑ እናዳይወስደን እሰጋለሁ!

ያዕቆብ ሰንደቁ
ሚያዚያ 15 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ


 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ