ቅዳሜ 30 ኤፕሪል 2016




በዓላት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ትንሣኤ ልቡና

“በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ። በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ጲላጦስም ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።” የማቴዎስ ወንጌል 27፥57-66

“ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን፦ አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው። መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ” የማርቆስ ወንጌል 16፥1-8

“ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።” የሉቃስ ወንጌል 24፥1-12

“ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ። ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።”  የዮሐንስ ወንጌል 20፥1-18
ጌታችን አስቀድሞ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አስነሳዋለው፤ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ ብሎ በተናገረው መሰረት መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ውለታቸውን አስበው በማለዳም ሽቶ ለመቀባት የመጡት ሴቶች፤  ጲላጦስም እንዲጠብቁት ዘዛቸው ወታደሮች የዘጉትን የመቃብሩን ድንጋይ ማን ያነሳልናል? ብለው አዝነው ነበር፡፡ ነገርግን በመቃብሩ ራስጌና ግርጌ የነበሩት ቅዱሳን መላእክት ታላቁን ድንጋይ አንከባለው እንደተናገረው ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሳቱን አበሰሩአቸው፡፡ የሚያስፈራው እና ሀዘን የተሞላው የመቃብር ስፍራ በብርሃን ጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ የመቃብሩ ድንጋይ ተንከባሎ በውስጡም ጌታ የለበሰው ልብስ ብቻ ታየ፡፡ የትንሣኤውንም ምስራች ለወንድሞች ሐዋርያት ሊናገሩ ሴቶቹ ፈጥነው ሄዱ፡፡
ትንሣኤ የበዓላት ሁሉ በኵር ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሥጋቸው በመቃብር በስብሶ ነፍሳቸው በሲኦል ወይህኒ የነበሩት አዳም እና ልጆቹ ነፃ የወጡበት ዕለት ነው፡፡ ሞት፣ መቃብር፣ የሲኦል ጨለማ ድል ተነሳ ፡፡ ዲያብሎስ ተንሰራፍቶ ከያዘው ሥልጣን በውርደት ተሻረ፡፡ ከመቃብር በኋላ መነሳት፤ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ተረጋገጠ፡፡ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ”ዮሐ.5፥28 እንደተባለ ሙታንም ሁሉ በአዋጅ በአንድ እንደሚነሱ ታወቀ፡፡ በሕጉ እና በትእዛዙ የተጎዙት ጌታችን የሰጠን የሕይወት ትንሣኤ ይካፈላሉ፡፡ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” እንዳለ ሐዋርያው ፡፡ ሮሜ. 6፥5
የመድኃኒታችን ትንሣኤ ከባርነት ወደ ነፃነት፤ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ 16፥33 እንዳለን በእርሱ ትንሣኤው የእኛ ትንሣኤ፤ በእርሱ ድል አድራጊነት እኛም ዓለምን እንደምናሸንፍ አረጋገጠልን፡፡ በሞት ማሰሪያ የተተበተበው ደካማው የአዳም ሕይወት የማሸነፍ ኃይል አገኝ፡፡ የተጫነበት እጅግ ትልቁ የመቃብር ድንጋይ ከፊቱ ገለል እንዲደረግለት ሆነ፡፡ መንገዱም በትንሣኤው ብርሃን ተቅናናለት፡፡
የትንሣኤ በዓል ስናከብር እግዚአብሔር የሰጠንን አንጸባራቂ የማሸነፍ ኃይል በማሰብ፤ ብርሃንኸን ላክልን፣በልቦናችን አብራልን እያልን እንዘምራለን፡፡ የክርስትና ሕይወት ኃጢአትን እና ዓለምን አሸንፎ በትንሣኤው ብርሃን የደመቀ ልቦና ይዞ ለእግዚአብሔር መንግስት መዘጋጀት ነው፡፡በዓሉ የሚከበርበት ዐብይ ምክንያትም እንደ መቃብር ድንጋይ የተዘጋብን የዚህ ዓለም ኃጢአት አንከባለን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ነው፡፡ሐዋርያው “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤” ፊል. 3፥10-11 እንዳለ እግዚአብሔር ያማናውቅ እንድናወቅ፤ ያልቀረብን እንድንቀርብትንሣኤ መሰናክሉ ሁሉ ተወገደልን፡፡እግዚአብሔር በሰጠን ዘመን የትንሣኤን በዓል ስናከብር በልባችን ደንዳናነት ጠንቅ የጨለመውን ሕይወታችንን በማስተካክል ትንሣኤ ልቡና በማምጣት ይሁን፡፡
ክርስቶስ ተነስቷአል በመቃብር ውስጥም የለም!
መልካም ፋሲካ ለሁላችንም ይሁንልን!
ያዕቆብ ሰንደቁ
ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ፡፡
 

ዓርብ 22 ኤፕሪል 2016

ወግ እልል በሉ

እልል በሉ
 በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለንግስ በዓል በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መዳረሻ በሰው ተሞልቷል፤ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ሴቱ ፣ወንዱ ተሰብስቧል፡፡ የተጋበዘውም መምህር ከአሥራ አምስት ቀን አስቀድሞ ባስተማረባቸው መድረኮች ሁሉ በእዚህ ቦታ ተገኝቶ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር፡፡ በየታከሲው ፣ በየመንገዱም የስብከቱን ርዕስ `ጠቅሶ የወረቀት ማስታወቂያዎችን ለጥፎ ይህንንም ብዙ ሰው ሰምቶ እና ተጠራርቶ እንዲመጣ ረድቷል፡፡ በዓውደ ምህረቱ በግራ እና ቀኝ በኩል ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች ተተክለዋል፡፡ ከድምፅ ማጉያው የሚወጣው ድምፅ ምድርን ያንቀጠቅጣል፡፡ በየሠርግ ቤት እንደምናየው የዓውደ ምህረቱም ዓዕማድ/ምሰሶዎች/ ዙሪያውን በነጭ ሻማ ጨርቅ ጥቅልል ተደርገዋል፣ በክብ ቅርጽ በአንድ ላይ የታጨቁ ልዩ ልዩ ቀለም ያላቸው ፊኛዎች ተሰድረዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪም በጸሎት መርሐግብሩን ከፈቱ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል ቀጠል አደረጉና “አሁን በቀጥታ ሁላችሁም በጉጉት ወደምጠብቀው  መምህር እወስዳችኋለሁ” አሉ፡፡ እኔም በልቤ “ጎሽ ወደ ትምህርቱ ልንተላለፍ ነው” ብዬ የልቦናዬን ሰሌዳ አዘጋጀሁ፡፡ ሰባኬ ወንጌሉ “ከዚያ በፊት ግን ምዕመናን”  አሉ “የዕለቱን መምህር ላስተዋውቃችሁ” በማለት እንደገና ንግግር ሲጀምሩ፤ ከበስጭቴ የተነሳ ሀሞቴ ፈሰሰ፡፡  ንግግራቸውን ቀጠሉ “መምህራችንን ዛሬ ወደዚህ ዓውደ ምህረት ለማምጣት በጣም ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለን፤ ከብዙ ቦታ ተሻምተን ነው ፡፡ ስለዚህ ደስ ይበላችሁ ምዕመናን እስቲ እልል ብላችሁ አመስግኑ” አሉ፡፡ ምዕመኑም ወዲያውኑ በእልልታ ጸፈውን መለሰ፡፡ ቀጠሉም እንዲህ አሉ “እውነት ነው የምላችሁ! መምህራችን እውቀታቸው የመጠቀና የረቀቀ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ተዘዋውረው ያስተምራሉ፤ እነሆ ዛሬ እኛን ለማስተማር ውድ ጊዜአቸውን ሰውተው ስለመጡ ወንዶች በጭብጨባ ሴቶች በእልልታ እንኳን ደህና መጡልን አንድትሉ እጠይቃለሁ” አሉ፡፡ ለእልልታና ለጭብጨባ በቋፍ ላይ የሚገኘው ምእመን መታዘዙ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት ድምቅ አድርጎ እልልታውን እና ጭብጨባውን አሰማ፡፡ “ያንሳል እስቲ ድገሙት” ተባለ ምዕመኑ እንደገና “እልል እልል አለ ”መምህራችን ወደ መድረረኩ እየመጡ ስለሆነ እስቲ በጭብጨባ “ሾዋ፣ ሾዋ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው” ተባለ፡፡ ምዕመኑም እያጨበጨበ ጌጠኛ ጥቁር ቀሚስ የለበሰ አጠር ደልደል ያለ መምህር ወደ መድረኩ መጣ፡፡
ሁሉም ዐይኖቹን ወደ ዓውደ ምህረቱ ተክሎ በትኩረት ያያል፡፡ ከመምህሩ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ አጠር አና ደልደል ያለ ወጣት መምህር ወደ መድረኩ ወጥቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ቆመ፤ የምዕመኑ ጭብጨባው ያባራው መምህሩ ተረጋግቶ አትሮኖሱን ተደግፎ ከቆመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው፡፡ በሁኔታው በጣም ግራ ገባኝ፤ በአውደ ምህረቱ ላይ የተቀመጡት ታላላቅ አባቶች ሁኔታውን ሳይቃወሙ በዝምታ ይመለከታሉ፡፡ እንደገናም መለስ ብዬ “መቼም መምህሩ በታላቁ ዐቢይ ጾም የማህሌቱ ከበሮ ተሰቅሎ ሳለ ፤ ለእርሱ የተጎሰመውን የምስጋና ነጋሪት እና እልልታ ውጦ ዝም አይልም፡፡ እንዲያውም ተቋውሞውን በመግለጽ የደብሩን ሰባኬ ወንጌል ይወቅሳል፤የተፈጸመውም ድርጊት ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ውጭ መሆኑን ጠቅሶ ማስተካከያ ይሰጣል ብዬ ተጽናናሁ ፡፡
 ወጣቱ መምህር ሰላምታውን ጨርሶ ካበቃ በኋላ “በዙሪያው ያላችሁ ምእመናን በሙሉ ሁለት እጃችሁን ወደ ላይ ወደ ሰማይ ዘርጉ” አለ፡፡ እኔም በሁኔታው ተገርሜ “ወይ ጉድ ይባስ አታምጣ! ደግሞ ጭብጨባው እልልታው ሳያንስ እጃችሁን ኪሳችሁ ውስጥ ከታችሁ ገንዘብ አምጡ ሊል ነው” ብዬ ኪሴን አሰቡኩት፡፡ ሁሉም እጁን አወጣ ከዚያም “ሦስቴ እልል ብላችሁ አጨብጭቡበት” አላቸው፡፡ ምዕመኑም እልታውን አደመቀው፡፡ መምህሩም ያንሳል፣ ያንሳል ምዕመናን ድገሙት ብሎ በድጋሚ አስደገማቸው፡፡ ከዚያም ቀጠለና ከሀገረ ስብከት የመጡትን እንግዶች፣ የደብሩን አስተዳዳሪን፣ የቤተ ክርስቲያኑን ፀሐፊ፣ የሰባኬ ወንጌሉንም ስም እየጠራ ተራ በተራም እያስጨበጨ እልል አስባለላቸው፡፡
ምዕመናን  “ለዛሬ ወደተዘጋጀው ትምህርት ከማለፌ በፊት አንድ ማሳሰቢያ አለኝ” አለ መምህሩ ፡፡ ቆጣ ባለ ድምፅ “ምእመናን ቁጥራችሁ ብዙ ቢሆንም  የእልልታ ድምፃችሁ ግን አነስተኛ ነው፤ስታጨበጭቡም አይሰማም፤ ስለዚህ ጉባኤው አልደመቀም፤”አለ፡፡ ቀጠል አድርጎም መዝሙረኛው ዳዊት እንኳ በመዝ 47÷1 “አሕዛብ ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ፡፡” ይላል በማለት እርሱ ከፈጸመው ድርጊት ጋር ባይስማማም በስፋት የእልልታን ጠቀሜታ አስተማረ፡፡  እኔም ከአሁን አሁን በማስታወቂያ ላይ የተለጠፈውን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን ርዕስ ትምህርት ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ነገር ግን ማስታወቂያ የተነገረለት ወቅታዊው የትምህርት ርዕስ ተዘንግቶ ካለጊዜው እና ሰዓቱ እልልታን በመጻፍም፣ በተግባርም መማር ጀመርን፡፡
በመሀል በሀሳብ ተጠልፌ ያለሁበትን እስክረሳ ድረስ ከውስጤ ጋር ሙግት ጀመርኩ ፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የመደንገግ፣ የማሻሻል ሥልጣን ያለው ማነው ? ቅዱስ ሲኖዶስ ወይስ? መምህራን፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ የአካባቢ ወጣቶች ፤ ቆይ ከመቼ ጀምሮ ነው በታላቁ ዐብይ ጾም ማጠናቀቂያ ሳምንት ውስጥ እልታ እና ጭብጨባ ፤ በመጽሐፉ እንደ ተጻፈ እልልታ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት እንጂ የግለሰቦችን በውዳሴ ከንቱ የምንጠልፍበት ገመድ ነው እንዴ ? እያልኩ ከራሴ ጋር እሞገታለሁ ፡፡  በግምት ሰላለሳ ደቂቃ ያህል በሀሳብ ማዕበል ስንገላታ ቆየሁ፡፡ልክ መምህሩ ወደ ዕለቱ ትምህርት መሸጋገሩን ሲናገር ከያዘኝ ተመስጦ ነቃሁ፡፡
 መምህሩ በየታክሲው እና በየመንገዱ ላይ ከራሳቸው ስም ቀጥሎ በጉልህ የለጠፉትን “በጾም እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚለውን የትምህርት ርዕስ ያስተምራሉ ብዬ ብጠብቅም ባልታወቀ ምክንያት ርዕሱን ቀይረው “ሉሲፈር እና ሥራው” ብለው ትምህርት መስጠት ጀመሩ፡፡ ለአርባ ደቂቃም ካስተማሩ በኋላ ሰዓት አልቋል ተብለው በወንዶች ጭብጨባ በሴቶች እልልታ ታጅበው ከአውደ ምህረቱ ወረዱ፡፡
እልልታ ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ የምስጋና መሥዋዕት ነው፡፡ ይህም በጥንቃቄ ይፈጸማል እንጂ በልማድ እና በዘፈቀደ አይከናወንም፡፡ እልልታን ተቀባብሎ ለማለት የምእመናን ፍጥነት ይገርማል ፡፡ ከሌላው ሰው ስለሰሙ ብቻ እልልታቸውን የሚያሰሙ አሉ፡፡ በአንድ ወቅት የደብራችን ሰበካ ጉባኤ ሊመንበር የነበሩት ሰው በተመሳሳይ ርዕስ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ስንለዋወጥ ያጫወቱኝን አስታውሳለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡ በወቅቱ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር መንፈሳዊ አገልገሎት እያስታጎሉ ያስቸገሩ ዲቆናትን እና ቀሳውስትን ጠርቶ ምክርም ይሰጣል፡፡ ምክርሩን ሰምተው ጥፋታቸውን ያላረሙትን አገልጋዮች ቀጣቸው፡፡ በዕለተ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ከተቀጡት መካከል አንዱ ካህን በድምፅ ማጉያ ማስታወቂ ተናገሩ “ሰበካ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኑን በሚገባ ማስተዳደር ስላልቻለ፤ የበላይ አካላት በወሰኑት መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ከኃላፊነቱ ተሸሮል፡፡ በቅርብ ቀን አዲስ ሰበካ ጉባኤ ይመረጣል፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ሁላችሁ ደስ ይበላችሁ እል በሉ አጨብጭቡ ” ብለው ሲናገሩ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያለው ምዕመን በሙሉ እልልታውን እና ጭብጨባውን አስተጋባ፡፡ ከመካከላቸውም አንድም ሰው ለምን? እና እንዴት? ብሎ የጠየቀ ምዕመን አልነበረም ፡፡ በሁኔታው በጣም የተበሳጩት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊመንበር በፍጥነት ወደ መድረኩ መጥተው ቀደም ተብሎ የተነገረው ሁሉ ስህተት መሆኑን እያስረዱ እያለ ተናግረው ሳይጨርሱ እልታው እና ጭብጨባው ከበፊቱ በበለጠ አስተጋባ ፡፡  ለትክለኛውም ለተሳሳተውም መረጃ ሳይመረምር በፍጥነት እልልታውን ያሰማው በአንድ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበ አንድ መንጋ ነው፡፡በማለት የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡፡
በንግስ በዓላት፣ስዕለት የሰመረለት በማህሌት ምስጋና ማቅረብ የሚሻ ሁሉ በእልልታ እና በጭብጨባ ምሰስጋና ያቀርባል፡፡ በታላላቅ አጽዋማት እና በሱባኤ ወቅት ሀዘን ተመስጦ እና ንሥሐ እንጂ እልልታ ጊዜው አይደለም፡፡ እልልታ መቼ እና እንዴት መባል እንዳለበት እልል አስባዩም እልል ባዩም ሊያውቅ ይገባል፡፡ አነስ ያለች የእልታ ድምፅ ስለተሰማ ብቻ ያን ተቀብሎ አድምቆ እልል ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ አንዲት ዘወትር ከእግዚአብሔር ቤት የማይለዩ እናት ያጋጠማቸውን እንዲህ አጫውተውኝል፡፡ በሰንበት ቅዳሴ ለማስቀደስ ቤተ ክርስቲያን ሄደን አንድ በሩቁ ከማውቃቸው ባልቴት ጎን ለጎን ተቀምጠናል፡፡ ከቅዳሴ በኋላ መብራት በመጥፋቱ የተነሳ ድምፅ ማጉያው ስለማይሠራ ከቤተምቀደሱ የሚተላለፈው መልእክት በደንብ ባይሰማም አንድ ካህን ስለ አንድ የደብሩ አገልጋይ በሞት መለየት ተናገሩ፡፡ ከወደ ኋላችን ግን የአንድ ሴት የእልልታ ድምፀ ተሰማ፡፡ አጠገቤ ያሉት ባልቴት ወዲያውኑ እልልታውን ተቀብለው አድምቀው እልታ አሰሙ፡፡ ከወደፊት ያለው ሰው በሙሉ ፊቱን ወደ እኛ ሲያዞር በጣም ተሸማቀኩ፡፡በሁኔታው በጣም አዝኜ አጠገቤ ያሉትን ሴት “እሜቴ ለመሆኑ ምን እንደተባለ ሰምተው ነው እልልታውን ያቀለጡት ብላቸው ? ሴትዬዋ ፈጠን ብለው አዬ ልጄ  የተባለውን እንኳን ምንም አልሰማሁም! ዳሩ ግን መምሬ እገሌ እኮ ምንጊዜም ቢሆን መልካም እንጂ ክፉ ነገር አይናገሩም ብዩ ነው” ቡለውኝ አረፉት፡፡በማለት ነግረውኛል፡፡ 
ስብከተ ወንጌል አገልግሎት እየተሰጠ መምህራን እያቋረጡ እልልታን የሚያሰሙ አሉ፡፡ አንዳንድ መምህራን እንዲያውም ትምህርታቸውን አቋርጠው እባካችሁ እኔ እልል በሉ ስላችሁ ትላላችሁ ብለው ማሳሰቢ እስከመስጠት ይደርሳሉ፡፡ መምህራን  አስተምረው ከመድረክ ሲወርዱ እንደቀደሙት አባቶቻችን ሥርዓት “ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ፤ የኃጢአት መደምሰሻ ያድርግልህ” የሚለው ምርቃት ቀርቶ አዲስ ሥርዓት በሆነው በደመቀ እልልታ እና ጭብጨባ መታጀብ ሆኖአል፡፡ ይህን ስህተት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው ብሎ በይፋ ማስተካከያ የሰጠ ሰባኬ ወንጌሌም ይሁን ሰባኪ አላጋጠመኝም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የደመቀ እልልታ እና የማያቋርጠው ጭብጨባ ከሌለ በድጋሚ እዚያ ቦታ መጥቶ ማስተር የማይፈልግ መምህርም አይጠፋም፡፡ በአሥራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት ዓመተ ምህረት ገደማ  በወቅቱ የስብከት አገልግሎት በመስጠት የታወቁ አንደበተ ርዕቱዕ መነኩሴ ነበሩ ፡፡ ታዲያ ቅዱስ ወንጌልን እየሰበኩ በየትመህርቱ መሀል ያቋርጡና “እዚህ ጋር ሦስት ጊዜ አጨብጭቡ ፤ እልልም በሉ”ይሉ ነበር፡፡ ይህን የተመለከቱ ሌሎች መምህራንም እንደሳቸው ማስጨብጨብን ጀመሩ፡፡ ነገሩ እንግዳ ልማድ ቢሆንም እንኳን ምዕመኑ በደስታ ተቀብሎት ያጨበጭብ ጀመር ፡፡ በኋላም ታላላቅ  የቤተ ክርስቲያን አባቶች መነኩሴውን ጠርተው አዲስ ሥርዓት አታምጡ፤ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት እንጂ፤  በጭብጨባ የሚታጀበው ዓለማዊ ስብሰባ አይደለም በማለት ገስጸው ሥህተታቸውን እንዲያርሙ አድርገዎቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ለረጅም ዘመን ተቋርጦ የነበረው በስብከት መሀል እና አስተማሪ አስተምሮ ሲጨርስ ማጨብጨብ እልልታን አስከትሎ እንደ አዲስ መጥቷል፡፡ ይህ አዲስ ነገር የተጀመረው በዚህ ጊዜ እና በእገሌ አማካኝነት ነው ማለት ባይቻልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡በሚገርም ፍጥነትም አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ መስፋፋት ችሎአል፡፡
ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ፣ መምህራን ፣ሰባኬያነ ወንጌል በትህትና እና በሥርዓት የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቀኖናዋ ውጭ የሆነ ተግባር ሲፈጸም ለማረም ለምን ቸል ይላሉ የሚለው ያልተለመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ያልተገባውን እልልታ ከንቱንም ውዳሴ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ፣ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉት ለምን  ይሆን ? ተስማምተውበት ወይስ ይሉኝታ ይዟቸው፡፡  በቀደመ  ዘመን የነበሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቅእነታቸው በአደባባይ ተመስክሮላቸው ንግግራቸው በትህትና ነበር፡፡እውነት የሆነው ትምህርታቸው እና እውቀታቸው በአደባባይ እንዲነገር ሰዎች እንዲያውቁላቸው እንዲያወድሷቸው ፈቃደኛ አልነበሩም ፈጽሞ ይቃወሙት ነበር፡፡ የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበሩት አንድ መምህር በአንድ ዓውደምህረት ላይ ሲያስተምሩ መርሐግብር መሪው ሰፋ አድርጎ አሞግሶ የሊቃውንት ጉባኤ አባል መሆናቸውን እና ሊቅ መሆናቸውን ተናግሮ እንዲያስተምሩ ጋበዛቸው፡፡ መምህሩ ለመስተማር ወደ አውደ ምህረቱ ሲወጡ በመጀመሪያ የተናገሩት እርሳቸው ሊቅ መባል እንደማይገባቸው ሊቃውንትስ ሰው የማያውቃቸው እንደኔ በመድረክ ያልታዩ ታላላቅ አባቶች በቤተ ክርስቲያን እንዳሉ ገሚሶቹም እንዳለፉ እርሳቸው ከሁሉ ያነሱ ታናሽ መሆናቸውን እና የሊቃውንት ጉባኤም አባል የሆኑት እንዲያው ቁጥር ለማሞላት እንደሆነ ከልብ በሆነ ሰሜት ለተሰባኪው ምእመናን በአጽንኦት እንዲገነዘቡ አድርገው እርማት ሰጥተዋል፡፡ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ሰምተው ዝም ብለው የሚሄዱት ቢበዙም፤ አልፎ አልፎ ግን ማስተካከያ የሚሰጡ አሉ ፡፡ በቅርቡ በአንድ ቤተ ክርስቲያን በወርሃዊ በዓል ላይ ያጋጠመኝን አስታወሳለሁ፡፡ የደብሩ ሰባኬ ወንጌል እንደለመደው በዕለቱ ለማስተማር ለተጋበዙት መምህር ብዙ ውዳሴ አቀረበ፤ እል አስባለላቸው፡፡ ትምህርቱን እንዲያስተምሩ መምህሩን ጋብዞ ከመድረክ ወረደ፡፡ ወጣቱ ሰባኬ ወንጌልም መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ይሉይኝታ ሳይዘው እና ሳያፍር “ቀደም ሲል ሰባኬ ወንጌሉ ስለ እኔ የተናገሩት በሙሉ ስህተት ነው” ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ “የተወደዳችሁ ምዕመናን እዚህ የመጣችሁት የእግዚአብሔርን ቃል ልትሰሙ እንጂ ገና መጨረሻችን እንኳን ያልታወቀውን የእኔ አይነቱን ደካማ ዝና ለመስማት አይደለም፤ ስለዚህ ምዕመናን ይህን የማይጠቅም ነገር ከአይምሮአችሁ ሰሌዳ ውስጥ ሰርዙት፣ ደምስሱት፣ እባካችሁ ፈጽማችሁ አጥፉት” በማለት በማስተካከያ ሰጥቶ፤ ሰባኬ ወንጌሉን በአውደ ምህረቱ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ሲያስተምር ተመልክቻለሁ፡፡
 ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት እመቤት ናት፤ በምን አይነት ሁኔታ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባት የሚመራት ሕግ እና ቀኖና አላት፡፡ በዘፈቀደ የሚሆን ነገር የለም፤ ለ ዕልልታው፣ ለጭብጨባው፣ ለምስጋናውም ሥርዓት አለው፡፡ ከዓለማዊ  ጉባኤ፣ ስብስብ የምንለይበትም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተዘጋጀው ሥርዓታችን ነው፡፡ ለዓውደ ምህረት አዳዲስ ልማዶችን ማስተናገጃ መሆን ተጠያቂው ማነው? የሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘም ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በገዛ የራሷ ልጆች ሥርዓቷን ስትጥስ የሚያርም አካል የላትም፡፡ የስበከተ ወንጌል ኃላፊዎችም ሌላው ጋር የተመለከቱትን ስህተት ጨማምረው እና አሻሽለው ወፍራም ስህተት ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ በአንዱን ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት የሰራውን ስህተት በሌላኛው ሲደገም ማየታችን፤ ከከተማ እስከ ገጠር በተመሳሳይ ጊዜ መዳረሱ ስጋት ላይ ይጠለናል፡፡  ሕገ ቤተ ክርሰቲያን ይጣሳል፤ ለወደፊትም መጥፎ ልማድ ያመጣል በማለት አርቀን አስበን በማስተዋል ስንሠራ አንታይም፡፡ ምዕመኑም ቢሆን እል በሉ ሲባል እልል ከማለት ውጪ፤ አጨብጭቡ ሲባል ከማጨብጨብ ውጪ፤ ለምን እና በምን ሁኔታ ማለት እንዳለበት ሊያውቅ ፤ ለስብከተ ወንጌል መሥፋፋት ገንዘቡን ሳይሰስት ፣ጉልበቱን ሳይቆጥብ እንደሚሰጥ ሁሉ የእኔስ ተሳትፎዬ ምንድነው ብሎ ሊጠይቅ ይገባው ነበር፡፡ ከዚህ የከፋ ሥርዓት ቢመጣ እልል እልል ብለን እንቀበለዋለን ወይ? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ምዕመናን “ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።”ዕብ 13፥9 እንዳለ በነፈሰው ነፋስ ሁኑ እናዳይወስደን እሰጋለሁ!

ያዕቆብ ሰንደቁ
ሚያዚያ 15 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ


 


ቅዳሜ 16 ኤፕሪል 2016

ወግ በስም ስህተት ነው



ወግ በስም ስህተት ነው


ከፍል ሦስት
ወዳጅ ዘመድ እርምህን
ልጅ በጠና የታመመባቸው ሁለት ሰዎች ከሩቅ ሀገር ድረስ የባሕል መድኃኒት አዋቂዋን እመት አይጠግቤን ቤት አጠያይቀው መጡ፡፡ የመንደሩ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ደፍሮ የሚገባ ሰው ስለሌለ እኛም ካየናቸው ቆየን አሉ ለሰዎቹ፡፡ ለዕድሩ ዳኛ ለቀጠናው ፖሊስ ሁኔታውን እናሳውቅ ብለው ወደ ጣቢያ ወረዱ፡፡
     የዕድሩ ዳኛ የአካባቢው ሽማግሌዎች እና የታጠቁ ፖሊሶች ግቢውን ከፍተው ገብ፡፡ ውሻው ሻንቆ ወፍራም ሰውነቱ መራመድ አቅቶታል፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ ጸጥታ ሰፍኖአል፡፡ ሞተዋል እንዳይሉ የግቢው ጠረን በመጥፎ ሽታ አልታወደም፡፡ ወደ መኝታ ክፍላቸው ዘልቀው ሲገቡ መደ ላይ እመት አይጠግቤ ራቁታቸውን ተዘርረዋል፡፡ ተጠግተው ሲያዳምቸው ትንፋሻቸው ል፤ ውነታቸውን ሲዳብሱት ቀዝቅዞአል፡፡ አይ ይህች ጉድ ሞታለች ሲል አንዱ በዝ ተናገረ፡፡ ሌላኛው በዝ ቀበል አድር እደጅ ለተሰበሰበው ሰው ወዳጅ ዘመድ እርምህን ብሎ ሲናገር የሰፈነው ጸጥታ በአንዴ በለቅሶ ደበላለቀ፡፡
      የአካባቢው ሽማግሌዎች የመግነዝ ጨርቅ አምጥተው አጥበው ገነዙአቸው፡፡ አስከሬኑን በሰሌን ውስጥ ጠቅልለው ለመክተት ሲዘጋጁ ትንሽ ትንፋሽ ሲጥ፣ ሲር፣ሲጢጥ ሲል ሰሙ፡፡ ሁሉም ተደናገጡ ገሚሶቹ አረ ጉድ! ነፍሳቸው አልወጣችም፤ አየር ያግኙ ፊታቸውን ፍቱላቸው አሉ፡፡ ሁሉም ተረባርበው በፍጥነት የመግነዙን ጨርቅ ፈቱላቸው፤ አየር እንዲገባም መስኮቱ ተከፈተ፡፡ ከቆይታ ላም ሰውነታቸው በዝግታ ተንቀሳቀሰ ተወራጨ፡፡ ምን እንደሆነ የማይገባ መናገር ጀመሩ፡፡ ነገሩን ያስተዋሉ ሽማግሌዎች እደጅ የሚለቀሰውን ለቅሶ እና ሙሾ አስቁመው “ጸልዩ እግዚኦ መሐረነ” በሉ ብለው ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ካህናት ይጠሩ ዘንድ መልእክተኞች በፍጥነት ተላኩ ፡፡
      ሱባኤውን ጨርሼ ከገዳም የማዕዶት ማግስት ማክሰኞ ወደ ሰፈር ደረስኩ፡፡ መንገድ ላይ ሁለት ሰዎች ወደ እኔ እየሮጡ መጡና ተደናግጠው እመት አይጠግቤ ሞተው ተገንዘው ሊቀበሩ ሲሉ እንደገና ከሞት ተነስተዋል፤ ሽማግሌዎቹ ካህናት ጠርታችሁ ብለውን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄድን ሳለ እነሆ እርሶን አገኘኖት ብለው አረዱ፡፡ ከዚያም አብረን ወደ እመት አይጠግቤ ቤት ጉዞአች ቀጠልን፡፡
    እመት አይጠግቤ ቤት ስንደርስ ግቢው በሰው ተሞልል፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ አሮጊመደቡ ላይ ተዘርረዋል፡፡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች አስወጥተን ውዳሴ ማርያም ፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ፍት ዘወል ፣ ደግመን ጸሎቱን ጨረስን፡፡ ከዚያም በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ብለን መስቀል ስናሳልማቸው ከእንቅልፍ እንደተቀሰቀሰ ሰው አፈፍ ብለው ብድግ አሉ፡፡
         እመት አይጠግቤ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ይንዘፈዘፋል ያለቅሳሉ፡፡ “ወይኔ ! ወይኔ ጉዴ ! ወየው ጉድ! ጉድ ! ጉድ ” ይላሉ ደጋግመው፡፡ ከእራስ ጸጉራቸው አንስቶ እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ይርገበገባል፡፡ ከንፈራቸው እየተንቀጠቀጠ “አየሁ በዐይኔ፣ በዐይኔ አየሁ ” እያሉ ይዘፈዘፋሉ፡፡ በፍርሀት ተውጠው በጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ ልብስ ደራርበው ወንበር ላይ አስቀመጧቸው ፡፡ ከዚያም እንደምንም እህል ቀምሰው ትንሽ በረቱ፡፡ እህል ውሃ ለማለት፤ እንዲሁም ለሌላም ሥራ መኝታ ቤት የነበረውን ሰው ወደ ውጭ እንዲወጡ አዘዝኩኝ፡፡ እመት አይጠግቤን ስላዩት ነገር እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው፡፡ ያዩትንም ነገር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ በሚገርም ሁኔታ ተረኩልኝ፡፡
        በደከመ ድም እንዲህ ሲሉ “መልአከ ሞት መጣና አን ኃጢአትሽ ከሰው ሁሉ የከፋ ነፍስ ፈጣሪሽ ይፈልግሻል” በማለት ጠራኝ፡፡ ወዲያው ነፍስ እና ሥጋዬ ተለያዩ፡፡ ነፍሴን በጥቁር ጨርቅ ሸፍኖ በመዳፉ ጭብጥ ውስጥ አስገባት፡፡ በሚያስፈራ ፍጥነትም በጨለማ መንገድ ወደ ሰማይ ወሰደኝ፡፡ በመንገዳችን ላይ በግምት ብዛታቸውም አምስት መቶ ሕፃናት ተሰልፈው ጠበቁኝ፡፡ ዐይናቸው የሚያቃጥል ጨረር ይረጫል፡፡ ሕፃናቱ በሙሉ በአንድ ድም “ይህች ሴት ነፍሰ ገዳይ ናት ፤ ገና በእናታችን ማጸን እያለን ሳንወለድ እንድንሞትደማችን በየሜዳው እንዲፈስ አድርጋለች፤ እኛን መና እንዳስቀረችን እኛም እርሷን እንበቀላታለን ” እያሉ ይጮሀሉ ፡፡ መልአከ ሞትም “እባካችሁ አሳልፉን ፍርድ የእግዚአብሔር ነው” ኣላቸውና ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከሕናቱ ዐይን የሚወጣው ብርሃን የነስ አካሌን በሙሉ ሲያቃጥለኝ “ወይኔ ተቃጠልኩ እባካችሁ ጠብታ ውሃ ለምላሴ ስጡኝ ብዬ በመጮህ ተማጸንኩኝ፡፡ የሰማኝም ሆነ የደረሰልኝ ማንም አልነበረም፡፡
        ትንሽ እልፍ እንዳልኩኝ ከጨለማ ውስጥ ጐልማሳ ገበሬ ብቅ ብሎ እንዲህ አለ “ይህቺ ሴት የዘለዓለም ኩነኔ ይገባታል፤ እኔ ገደል ጨምራ ደሜን አፍስሳለች” ብሎ በብስጭት ይናገራል፡፡ በጨረፍታ አየሁ ይህ የማውቀው ድም ይመስላል ማነው ? እያልኩ ሳለ በድንገት ከፊት ለፊቴ መጥቶ ድንቅር በማለት መንገዱን ዘጋው፡፡ ቀና ብዬ ሳየው ለካስ ባለቤ የነበረው ገበሬ ነው፡፡ የምገባበትም ጠፋኝ፤ ደነገጥኩ፡፡ መልአከ ሞትም በከሳሾቼ ና በኃጢአቴ መብዛት ግራ ተጋባ ፡፡ በብስጭት እስቲ እናንተ ዝም በሉ! ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ እባካችሁ መንገዱን ክፈቱት ብሎ እኔን አስከትሎ ጉዞውን ወደ ፊት ቀጠለ ፡፡
        መልአከ ሞትን ተከትዬ ወደፊት ሄድ“ ያዟት! ያዟት! የሚል ጫጫታ” ሰማሁ፡፡  በጣም ብዙ የውሻ ቡችላ፣ የድመት ሙጭሊት ከበቡኝ፤ ነፍሴ የለበሰችውን ቀሚስ መሳይ ጨርቅ በሹል ጥርሳቸው ቦጫጨቁት፡፡ በከፍተኛ ድምም “ገና የእናታችን ጡት ጠብተን ሳጨርስ ገደል ወርውራ ፈጥፍጣ ገላናለች ጨካኝ ሴት ናት” እያሉ ሊናጠቁኝ ሞከሩ፡፡ “አረ ተሰቃየሁው ነከሱኝ” ብዬ ጮኩኝ ፡፡ መልአከ ሞትም በከሳሾቼ መብዛት በጣም ተደነቀ፡፡ ከልብም አዝኖ “አይ ሰው ! ምን አይነት ጨካኝ እና ከንቱ ነው? ለወገኑም ለእንስሳትም ጭምር የማይራራ ”በማለት አዘነ ፡፡ የዚህችን ሴት ነፍስ በብርሃን ፍጥነት ወደ ንጉሡ ዙፋን ይዤ መሄድ አለብኝ አንዱ ጐትቶ ወደ መቀመቁ ሲኦል ውስጥ ቢጥላት ጦሱ ለእኔ ይተርፋል፡፡ መንገዴን ልቀር” ብሎ  በሌላ አቅጣጫ መብረር ጀመረ፡፡
         ነፍሴን ይዞ በመካከለኝው የሲኦል እስር ቤት አቋርጦ አለፈ፡፡ በዚያም እኔ መምጣት የተደሰቱ ነበሩ፡፡ ግማሾቹ ያፎጫሉ፣ ካንቺ ብዙ ተምረናል! ለክፉ ሥራችን ዋና አርዓያችን አንቺ ነሽ እያሉ ያጨበጭባሉ፣ ይስቃሉ፡፡ አንዱ ቀጠን ያለ ድም ከወደ ኋላዬ ሰማሁ “በየማዳበሪያው ሰፍተሽ ባጠራቀምሽው ገንዘብ ፤ጠበቃ ገዝተሽ ነፍስሽን ከሲኦል ታድኛት እንደሆነ እስቲ እናያለን?” ብሎ ተሳለብኝ፡፡ ብዙ የማውቃቸው የመንደራችን ሰዎች በጨለማ እስር ቤት በብረት ሰንሰለት ታስረው ተመለከትኩኝ፡፡ የሚያውቁኝ ሁሉ ስሜን ይጣራሉ፤ የተወሰኑት ሙሉ ሰውነታቸው ጨለማ ውስጥ የተዋጠ ሲሆን፤ ፊታቸው ብቻ ይታያል ፡፡ በግንባራቸው ላይ የክርስትና ስማቸው ተጽፎል፤ አንገታቸውን ብቅ በማድረግ ታይተው ተመልሰው ይጠፋሉ ፡፡ ከብዙዎች መካከል በቅርብ ጊዜ የሞተው ጎረቤቴን ስመለከት በጣም ደነገጥኩ ፤ የዚህ ሰው ቦታ እዚህ ይሆናል ብዬ አስቤ አልሜም አላውቅም ፡፡  “ድምን ከፍ አድርጎ ስሜን እየተጣራ ውሳኔውን ሰምተሽ ስትመለሺ  እኛ ክፍል እንዲመድብሽ አለቃችንን ለምኝ” አለኝ፡፡ በሆነው ነገር በጣም ተጨንቄ መልስ ስላጣው ብቻ “እሺ እነግረዋለሁ” አልኩት፡፡
ከዚያ ቦታ ትንሽ እልፍ እንዳልን መልአከ ሞትን ፈራ ተባ እያልኩኝ ጥያቄ ጠየኩት ፡፡ “ይሄ ጐረቤቴ የነበረው ሰው ቤተ ክርስቲያን ይሄድ አልነበረም እንዴ ? እኔ ፍጹም ጻድቅ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ይገርማል እንዴት ተኮነነ ? ” አልኩት፡፡ መልአከ ሞትም በአግራሞት ቁልቁል እየተመለከተኝ ፤ የተናገርኩትን ቃል በመድገም “እንዴት ተኮነነ አልሽ ? ”ብሎ መልሶ ጠየቀኝ፡፡ ደንግ በሀፍረት ወደታች አቀረቀርኩ፡፡ መልአከ ሞት መልሱን ቀጠል አደረገና  “ለመሆኑ አንቺ ማን ሆነሽ ስለሌላው ሰው መኮነን ትጠይቃለሽ” አለ፡፡ በልቤም ሥራዬን እና ከሳሾቼን አስቤ በፍረት ሽምቅቅ አልኩኝ፡፡
        መልአከ ሞት እንዲህ አለ “ይህ ሰው የሞተ ቀን ነፍሱን ይዤ የመጣሁት እኔ ነኝ፤ የሚገርመው ከቤተ ክርስቲያን አይለይም ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል ግን በተግባር አይፈጽምም፤ በምግባር በሃይማኖት አይጸናም፤ በእግሩ ይመላለሳል እንጂ ፤ የንሥ ሕይወት የለውም፡፡ ላዩ ሲያዩት አነጋገሩን እና አለባበሱን አሳምሮ እዉነተኛ ይመስላል፡፡ ክርስቲያን መሳይ በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ መሸታ ቤትም ዳንኪራ ሲረግጥ፣ በጫት ቤት ሲመሽግ ፣ ድሀ ሲበድል፣ ሲያመነዝር፤ ሲጣላ ፣ ሲጨቃጨቅ፣ ሲከስ ሲካሰስ፣ ራሱን ንጹህ አድርጎ በሰው ላይ ሲፈርድ ወዘተ … በአጠቃላይ ክርስቲያናዊ ሕይወቱን ሲያሳድፍ የኖረ ሁሉም አይቅርብኝ ባይ የተሰጠውን ጊዜ በከንቱ ባከ ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ መልካም ሥራው ሲመዘን ጥቂት ሆነ፤ ክ ሥራው ደግሞ በዛ፣ ተትረፈረፈ ፤የሲኦል ቅጣትም ተፈረደበት ”ብሎ መለሰልኝ፡፡ 
        ከጨለማው ሥፍራ እወጣን በብርሃን የተከበበ ዙፋን ወዳለበት ስፍራ ደረስን፡፡ ቦታውን በነፍስ ዐይኔ ማየት አልተቻለኝም፤ መቁጠር በማይቻሉ ቅዱሳን መላእክት ተከቦአል ልዩ ደስታ የሚሰጥ መልካም መዓዛ አለው፡፡ መልአከ ሞት በእጁ መዳፍ ጭብጥ አድርጎ ይዞኛል ነፍሴ ተጨነቀች፤ ፍርስርስ፣ ብትንትን የምትል መሰለኝ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ነፍ ምንም ነገር የማትፈራ ጨካኝ ደንዳና ደፋር ነበረች፡፡ በፈጣሪዬ ፊት ለመቅረብ እየተጠጋው እየተጠጋው በመጣሁ ቁጥር ራሴን ወቀስኩት፤ በደለኛነቴም አወኩ እንባዬ መጣ ከጥልቅ ሀዘን የመነጨ ጥፋተኝነት፣ ከንቱነት ተሰማኝ በደለኛነቴንም በፊቴ ባለ ነጭ ሰሌዳ ላይ ከኃጢአቴ ዝርዝር ጋር በጥቁር ቀለም ተጽፎ ታየኝ፡፡ ነፍሴን በኃጢአት መቆሸሿን እና መከርፋቷን፣ ማደፏንም ጭምር ፤በጥቁር ርቅ መጠቅለሌን ሳስተውል ሀፍረት ተሰማኝ፡፡ የመቅደሱ መጋረጃ ፊት ቆመን ሳለ ሳናስበው መጋረጃው ካላይ ወደታች ተከፈተ፡፡ ከሚያስፈራው ግርማው የተነሳ መቆም ስላልቻልን በግንባራችን ተደፋን፡፡ መልአከ ሞትም ኃይሉን አጥቶ በፊቱ እንደሰም ቀለጠ ፡፡ እኔም በኃጢአቴ አፍሬ ከነጥብ እጅግ አንሼ በፊቱ ተደፋሁ፡፡ ተደፍቼ ድም ብቻ፤ የሚያስፈራ የሰማያዊ ንጉሥ ድምፅ ይሰማኛል፡፡
        መልአከ ሞት ይሄው ጌታዬ “በታዘዝኩት መሰረት “አመተ ማርያም” የተባለችውን ነፍስ ይዤ መጥቼአለሁ” አለ፡፡ ሰማያዊው ንጉሥ ተቆጣ “በደንብ አትሰማም! እኔ ይህችን ኃጢአተኛ ነፍስ መቼ አምጣልኝ አልኩህ ፤ እኔ ያልኩህ  “አጸደ ማርያምን” እንጂ፤ በል አሁኑኑ ይህችን ነስ ወደ ማደሪያዎ ሥጋ መልስ” አለው፡፡ መልአከ ሞትም ደንግጦ ሰውነቱ ተንዘፈዘፈ፤ ኃይሉ ቀነሰ ጉልበቱ ራደ ፤ እየተንቀጠቀጠ እና እያቃሰተ፣ እንዲህ አለ “አቤቱ ማረኝ ይቅር በለኝ ጌታዬ አምላኬ፤ የስም ስህተት ነው ምህረትህ ይደረግልኝ ” ብሎ ሰገደ ፡፡ ሰማያዊውም ንጉሥ “ምሬሀለሁ ዳግመኛ ግን አትበድል፤ ተነስ የታዘዝከውን ብቻ ፈጽም”  አለው፡፡
        እኔን አንጠልጠሎ ዘወር ሲል መጋረጃው ተዘጋ፡፡ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በመላእክት መቋሚያ፣ በብርሃን ጸናጽል፣ አዲስ ምስጋና ከእጣኑ ሽታ ጋር ወደ ኋላዬ ስሰማ ደስ እያለኝ ምነው ባልተመለስኩ እዚሁ በቀረው እያልኩኝ ጉዞዬ ከሰማይ ወደ ምድር ሆነ ፡፡ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ መልአከ ሞት “አንቺ ዕድለኛ ነፍስ በይ ደህና ሁኝ ፤ የተሰጠን ጊዜ ተጠቀሚበት” አለ፡፡ ጭብጥ አድርጎ ከያዘበት መዳፉ ፍልቅ አድርጐ ወደ ታች ሲለቀኝ  ከትልቅ ተራራ ላይ እንደተወረወረ ድንጋይ ጭው እያልኩኝ  ወደታች ቀናት እና ሌሊት ተጉዤ  ወደ ማደሪያዬ ሥጋ መጣሁ፡፡
        እመት አይጠግቤ በቤተ ክርስቲያን ውሎአቸውንም አዳራቸውንም አድርገዋል፡፡ እኔ ዘንድ መጥተው “እሁድ የዳግማይ ተንሳይ ዕለት ለምዕመናን ምስክርነት መስጠት ስለምፈልግ ላስፈቅዶት” አሉኝ፡፡ እኔም “መልካም ከቅዳሴ በኋላ ይመሰክራሉ” አልኩአቸው፡፡ በትህትናም ሆነው “ይህ ብቻ አይደለም እኮ አባ ተመልከቱ” እያሉ ጸጉራቸው ላይ ያለውን ሻሽ እየገለጡ የተላጨውን ጸጉራቸውን አሳዩኝ፡፡ በረጅሙ ተንፍሰውም “ የዚህ ዓለም ኑሮ ከእንግዲህ ወዲህ ይበቃኛል፤ ንብረቴን ገሚሱን ለድሆች፤ የቀረውን ደግሞ ለእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይሰጥልኝ፤ በቸርነቱ ለነፍሴ ቤዛ ይሆናት ዘንድ” በማለት አሳሰቡኝ፡፡ ለእሁድ ሰንበት ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ እሁድ ሥርዓተ ቅዳሴ አልቆ ተአምረ ማርያም ከተነበበ በኋላ፤ በመጀመሪያ እኔ አጠር ያለ ትምህርት ሰጠሁ፡፡ ቀጥለውም እመት አይጠግቤ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጋበዝኳቸው፡፡ ለተሰበሰበው ሕዝ ክርስቲያንም ሞተው በአካለ ነፍስ ሆነው ያዩትን ሁሉ መሰከሩ ፡፡ እንዲህም አሉ “እሳቱ የማይጠፋበት፣ ትሉ የማያንቀላፋበትን ሲኦልን ጥልቅ ጨለማ አይቻለሁ፡፡ ብዙ ነፍሳትም በዘለዓለማዊ ቅጣት ውስጥ ወድቀው በማየቴ እስከ አሁን እንባዬ አላቆመም፤ በሕይወተ ሥጋ ያለን ሁሉ ይህ ዓለም ከንቱና እና ጠፊ መሆኑን አውቀን እንኑር፡፡ እርስ በእርሳችን እንዋደድ፣ እንተዛዘን፤ የንሥሐ ሕይወት ይኑረን፡፡ ለሞቱትም ወገኖቻችን ለነፍሳቸው ምህረት ማግኘት ይረዳቸው ዘንድ ለድሆች በመመጽወት፣ ቁርባን በማስቆረብ፣ ፍትሀት በማስፈታት እረፍተ ነፍስ እናሰጣቸው፡፡” በማለት ተናገሩ፡፡ በመቀጠልም ምእመናን አሉ “የሚፈርድብን የሠራነው ኃጢአት እንጂ፤ እግዚአብሔር አይደለም፤ እርሱ ሰውን ለማዳን ምክንያት የሚፈልግ መሀሪ ይቅርባይ ነው፡፡ ለፍርድ በዙፋኑ ፊት ስንቀርብ በሠራነው ሥራ እንጸጸታለን፡፡” በማለት ንግራቸውን እየቋጩ ምዕመናን “ዘወትር ጸልዩ ሳንዘጋጅ በሞት እንዳንጠራ፤ ለንስሓ ሞት እንዲያበቃን፡፡” ብለው ከመድረክ ወረዱ፡፡ ብዙ ሰዎች ተከትለዋችው የሞተውን ዘመዳቸውን ነፍስ እንዴት ነው? አይተውታል ወይ ? የት ይሆን ያለው? እያሉ ይጠይቁ ጀመር፡፡ ያዩዋቸውን እና ያሉበትን ቦታ ሲነግሩአቸው ብዙዎቸ ስለወገናቸው እና ስለራሳቸው መሪር እንባ አለቀሱ፡፡ለተከተሎአቸውም ሰዎች ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው “ከእንግዲ ወዲህ ስሜ እመት አይጠግቤ ሳይሆን ዓመተ ማርያም፤ የማርያም አገልጋይ ሆኖአል በቸር ያገናኘን መልካም ሥራ ሥሩ ንሥሐ ግቡ ....” እያሉ የቤተ ክርስቲያኑን ግቢ ለቀው ወጡ ፡፡ የውሃ መቅጃ ቅል ፣መቋሚያ ፣የጸሎት መጻሕፍት እና መናንያን የሚለብሱት ልብስ ወይባ ይዘው ቁልቁል ወደ ማርያም ገዳም ተጓዙ፡፡

ያዕቆብ ሰንደቁ  
ሚያዚያ 8 2008ዓ.ም
አዲስ አበባ