ሰኞ 16 ፌብሩዋሪ 2026

ስብከት ሂድ! አንተ ሰይጣን! (ማቴ.4፥10)

  

+++ ሂድ! አንተ ሰይጣን! +++   (ማቴ.410)

በመጋቤ ሰናይ በፍቃዱ ደስአለኝ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን።

 

እንኳን ለጾመ እግዚእ (ዐቢይ ጾም) በሰላም አደረሳችሁ።

 

ሐዋርያና ወንጌላዊ የሆነ ቅዱስ ማቴዎስ በምዕራፍ 4 ላይ ስለ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾም ታሪክ ይነግረናል።

 

ከእኔ ተማሩ (ማቴ.1129) ያለን ጌታ ጾም ለርሱ የሚረባው ነገር ሳይኖር፣ በመብል ምክንያት ፈቃዱን ፈጽመን ከገነት እንድንወጣ ያደረገንን ጠላት፣ የቀደመውን እባብ ዘንዶ ዲያብሎስን ባለመብላት ሃሰተኛ ፈቃዱን ድል የምናደርግበትን መንገድ ሊያስተምረንና የጦር እቃውንም ሊያስታጥቀን ሲወድ አብነት ሆኖ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ጾመ።

 

ለጾም የመረጠው ቦታ ደግሞ ምድረ በዳን ነው። ምድረ በዳ ምንም ምን የሌለበት ጭው ያለ በረሃ ነው። እንዲህ ላለ መንፈሳዊ  ተግባር  ትኩረት ከሚሰርቅ ነገር የጸዳና በተመስጦ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ለመገናኘት የተመቸ ቦታ።

 

ስለዚህ ጌታ፣ በጾም ጊዜ ወደ ምድረ በዳ እንድንወርድ ብቻ ሳይሆን ባለንበት ቦታ ዙሪያችንን በፈቃዳችን ምድረ በዳ እንድናደርገው፣ የከበበንን ቁሳዊና ምድራዊ የሆነውን ነገር ሁሉ እንድንረሳው፣ የአምሥቱን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን በር በመዝጋት(ማቴ.66) አካባቢያችንን ለጾምና ለጸሎት ዝግጁ ማድረግ እንዳለብን (በተለይ ቤታችንን) በዚህም በአርምሞ፥ በጽሞና፥ በተመስጦና በሰቂለ ኅሊና ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ ያስተምረናል።

 

ወንጌላዊው ማቴዎስ፣ ጌታ ከጾመ በኋላ በሰይጣን እንደተፈተነ ይነግረናል። ብዙዎቻችን ክርስቲያኖች፣  መጽሐፍ ቅዱስ ሰፊ ትምህርት እያስተማረን ስለ ሰይጣን ያለን እውቀት አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ያለን ግንዛቤ አጠያያቂ ነው። በዚህም ምክንያት ተዘልለን ስለምንኖር በቀላሉ የጥፋት ሰለባዎቹ ነን። ማቴዎስ እንደሚነግረን ግን አባታችን አዳምን በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ያሳተው ጠላታችን ሰይጣን የአዳምን ሥጋ ለብሶ የመጣውን አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳን እንደ ፈተነው ነው። እኛንማ እንዴት?

 

ዛሬ ብዙዎች ከጠላታችን ሰይጣን የተነሳ በቃሉ እንደሚስቱ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ የፈተነውን ፈተና ጌታም ከቃሉ እየጠቀሰ መልስ አሳጥቶ ድል ነስቶታል (እናንተም እንዲሁ አድርጉ ሲለን) አሳች የተባለው ሰይጣን ለሕይወት የተሰጠውን ቅዱስ ቃል በተሳሳተ አረዳድና ግንዛቤ እንዴት ለጥፋትና ለሞት እንደሚያደርገው ከዚህ እንማራለን። በጠላት ተታለው በቃሉ የሳቱትን ወገኖች የሰው ልጅ ሁሉ ይድን ዘንድ በቀራንዮ የተሰቀለው አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊውን የቃሉን ብርሐን ያብራላቸው። ከእሥራታቸውም ይፍታቸው። (2ጴጥ.316) አሜን!

 

ከሁሉ ይልቅ የመጨረሻው ፈተና የሚደንቅ ነው።ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው" ይለናል እጅግ የላቀ የክብርን ከፍታ ለመግለጽ ነው ለአንተ የምሰጥህ ከታች ካሉት የምድር ነገሥታት ሁሉ የበለጠ ነው ሲል። "የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ" ይላል ይህንን በደንብ ማስተዋል ያስፈልጋል። (ማቴ.48)

 

ሰይጣን የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው ማሳየት ለምን አስፈለገው? እስኪ እነዚህን ጥቅሶች በማስተዋል ተመልከቷቸው፡-

 

አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤”(ዮሐ.1231)

 

ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤” (ዮሐ.1430)

 

ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።” (ዮሐ.1611)

 

ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።”(2 ቆሮ 44)

 

ጠላታችን ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክ፣ የዚህ ዓለም ገዥ እንደተባለ አስተዋላችሁን? በእውነት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በሚያምኑት ላይ ሥልጣን ባይኖረውም ይህን ዓለም እንደሚገዛ ተረዳችሁን? እንዴት ባለ ዓለም ውስጥ እንደምትኖሩስ? ስለዚህ ሰይጣን ደግሞ ኃላፊ ሥልጣንን ከነክብሩ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ለምድር ነገሥታት አክፋፍሏቸዋል።

 

ነገር ግን በዚህ አትደንግጡ፤ ጌታችን "እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።" (ዮሐ. 1714-16) እንዳለ፣ በዓለምም ብንኖር በፍቅሩ ከዓለም ስለለየን  የዚህ ዓለም ገዥ ጠላታችን ሰይጣን በኛ ላይ ሥልጣን የለውም። (ዮሐ.1519) ክብርና ምስጋና በቀራንዮ ለተሰቀለው አምላካችንና ጌታችን ይሁን። አሜን!

 

የዚህ ዓለም ገዥ የተባለው ዲያብሎስ የዓለም መንግሥታትን በሥልጣንና በክብር እያሳተ እንዴት በራሱ መንገድ እንደሚያሰልፋቸው ደግሞ እንመልከት። በጌታም ላይ ሊሞክር የፈለገው ይሄንኑ መንገድ ነው።

 

"ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ" (ራእ.1613-14) በተጨማሪም ራዕይ 17 ያንብቡ።

 

እንዲሁም ነቢዩ ዳንኤል በፆም ላይ በነበረበት ወቅት በተገለጠለት ራዕይ፡- "እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።

 

የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት።" ይላል።

(ዳን.1012-13)

 

ከዚህ አንፃር ዛሬ በዓለማችን ላይ ከሚፈጸሙት አስጨናቂ ነገሮች እና ልክ ከሌለው ግፍ አንፃር መንግሥታት የሚያገለግሉት ማንን ነው? የሚለውን በጥንቃቄ ለመመለስ መሞከር ይኖርብናል። ታዲያ፣ ድብቁ ማኅበረሰብ፥ የአዲሱ ዘመን ንቅናቄ፥ ኢሉሚናቲ፥ 666 የሚባሉትስ እነማን ይመስሏችኋል? ከአገዛዛቸውስ ለማምለጥ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 

የዓለምን መንግሥታት በቁጥጥሩ ሥር ባደረገበት በዚሁ መንገድ ጌታንም ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ ክብርና ሥልጣን እሰጥሃለሁ በማለት ፈትኖታል። (ማቴ.49) በጣም የሚደንቀው ግን፣ ሰይጣን የራሱ የሆነ ምንም ነገር የሌለው ለራሱም ፍጡር ሲሆን የራሱ ያልሆነውን እሰጥሃለሁ የሚለው ለፈጣሬ ዓለማት፥ ለነገሥታት ንጉሥና ለጌቶች ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ነው። ስንቶቻችንን ነው በዚህ አይነት የራሱ ያልሆነውን እሰጥሃለሁ እያለ የተጫወተብንና የሚጫወትብን? ስንቶቹስ መንግሥታት ናቸው ይህንን ፈተና ተቋቁመው የእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚያገለግሉት

 

በዚህ ጊዜ ግን ጌታ ሁለቱን ፈተናዎች በትዕግስትና በትኅትና ቢያስተናግድም የአምልኮ ጉዳይ በትዕግስት የሚታለፍ ባለመሆኑ "ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።" (ማቴ.410) ሰይጣንም ሂድ! የሚለውን አምላካዊ ተግሳጽ ሰምቶ በፊቱ መቆም አልተቻለውም ምን መጣብኝ ብሎ ከአጠገቡ በኖ ጠፍቷል።

 

በዚህ መንገድ ጠላታችንን በጾም ኃይል ሂድ! አንተ ሰይጣን ብለን ድል የምናደርግበትን አቅም በተግባር ፈጽሞ አሳይቶናል። ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው? (ማቴ.1721) ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ የተባለው ሰይጣን ፈቃዱን የሚያስፈጽምበት የብሉይ ዘመን ጣዖታትን በመጠበቅ እንዳትዘናጋ። ያለነው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ ዛሬ ጠላታችን በገንዘብና በብዙ ዓይነት ዲጂታል ጣዖታት አማልክት ዙሪያችንን ከቦ ነው የሚያስጨንቀን። ታዲያ "ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።" (ማቴ.410) የሚለው ሕያው አምላክዊ ቃል በልባችን ከታተመና ከተጠቀምንበት አሸናፊዎች ነን።

 

ስለዚህ ጾም ሰይጣንን ድል ማድረጊያ ዐቢይ መንፈሳዊ የጦር እቃ መሆኑን አምነን በሥጋ ፈቃዳችን ላይ ለመሠልጠን፣ ዓለምን ለመካድና ከዓለማዊነት ለመውጣት፣ ይልቁንም የሰይጣንን ሽንገላ ለመቃወምና ድል ለማድረግ እንችል ዘንድ ከኔ ተማሩ ካለን ከጌታ ተምረን በፈተና ሁሉ በጾም ኃይል  ሂድ! አንተ ሰይጣን! የምንልበትን አቅም ለማሳደግ እንትጋ።

 

አርእስተ ኃጣውዕ የተባሉ ስስት፣ ፍቅረ ንዋይና ትዕቢትን በጾም ኃይል ድል አድርገን እንሻገራቸው።

 

እንዲሁም የዚህ ዓለም ገዥን አሠራር በመቃወም ለሠይጣን ሀሳብ ተገዥ እንዳይሆኑ "የነገሥታቱንና የኃያላኑን ልቦና መልስ" እያለች ያለማቋረጥ ከምትፀልይ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ጋር በመተባበርና ፆምን መሣሪያ በማድረግ ስለ መሪዎቻችንና ስለቅድስት ሀገራችን በመንፈስ እንዋጋ።

 

የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችንና ቅዱሳት እናቶቻችን የዚህ ዓለም ገዥ ዲያብሎስ በምድራችን ላይ እንዳይሠለጥንና ሀገራችን በውጭ ጠላት እንዳትገዛ በሥጋም በመንፈስም በርትተው እየተዋጉ ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት አድርገው አቆይተውልን ያለፉት በጾምና በጸሎት ኃይል ነው። ለዚህም ሊቀ ሠማዕታት ወፍጡነ ረድዔት ቅዱስ ጊዮርጊስ ምስክራችን ነው።

 

ሂድ! አንተ ሰይጣን የምንልበትን ኃይል ለማግኘትና ወርሃ ጾሙን በድል ለማጠናቀቅ ጾማችን በምድረ በዳ ይሁን።

መልካም ሱባዔ።

ይቆየን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ