ዓርብ 27 ፌብሩዋሪ 2026

ክንፍ አልባ ወፍ

 

ክንፍ አልባ ወፍ

ያዕቆብ ሰንደቁ

ወዳጆቼ! አሁን ያለንበት የተቀደሰው የአቢይ ጾም ወቅት ከምግብ መከልከል ባለፈ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት እውነተኛ መንፈሳዊ ጉዞ ነው። ነገር ግን ጸሎት ከሌለው ጾማችን መሬት ላይ እንደሚንፈራገጥ፣ መብረር እንደማይችል ወፍ ይሆንብናል።

ጸሎት እንደ "መንፈሳዊ ክንፍ"

ታላቁ አባት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ጸሎትን "መንፈሳዊ ክንፍ" ይለዋል። "ሰው ሳይጸልይ መዋል ማለት ክንፍ የሌለው ወፍ ለመብረር እንደሚሞክር ነው" ይላል። ጸሎት ከዚህ ዓለም የመሬት ስበት (ከጭንቀትና ከምኞት) አውጥቶ ወደ መለኮታዊው ዓለም ያደርሰናል።

ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎትን "ከከንፈር" ይልቅ "ከአንጀት" እንዲሆን ያደረገ ታላቅ አባት ነው። "የሕይወቴ ጌታና ሹም ሆይ! የሥራ ፈትነትን፣ የልብ መሰላቸትን፣ የሥልጣን መውደድንና የከንቱ ንግግርን መንፈስ አትስጠኝ። ይልቁንም የንጽሕናን፣ የትሕትናን፣ የትዕግሥትንና የፍቅርን መንፈስ ለእኔ ለባሪያህ ስጠኝ።" በማለት ይጸልያል፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚነግረን፣ መዝሙረ ዳዊት መፀለ የነፍሳችን መስታወት ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ "ወደ ማርሴሊኖስ በተላከ መልእክት" ላይ እንደሚነግረን፣ መዝሙረ ዳዊት ከሌሎች መጽሐፍት ልዩ የሚያደርገው የሰውን ልጅ ውስጣዊ ማንነት የሚገልጥ በመሆኑ ነው። ሌሎች መጽሐፍት የታሪክ ክስተቶችን ሲነግሩን፣ መዝሙረ ዳዊት ግን የራሳችንን ስሜትና ሕይወት በቃለ እግዚአብሔር ውስጥ እንድናገኝ ያደርገናል።

መዝሙራትን ስናነብና ስንጸልይ የዳዊትን ቃላት ብቻ አንደግምም፤ ይልቁንም ቃላቱን እንደ ራሳችን ቃላት አድርገን እንድንጸልይ ይረዱናል። ለምሳሌም በጠላቶች ስንከበብ (መዝ. 3) በኃጢአት ተጸጽተን ይቅርታ ስንሻ (መዝ. 50/51) ወይም እግዚአብሔርን ማመስገን ስንፈልግ (መዝ. 102) እንደ መድኃኒት እንጠቀምባቸዋለን ይላል።

ጸሎት በየትኛውም ቦታና ሰዓት

ብዙዎቻችን ጸሎት የሚቻለው ቤተ ክርስቲያን ተንበርክከን ብቻ ወይም ጸጥ ባለ መንፈሳዊ ሥፍራ ብቻ ይመስለናል። ነገር ግን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት፣ ጸሎት ቦታና ጊዜ አይገድበውም። በሥራ ገበታህ፣ በመንገድ ላይ ወይም በቤት ውስጥ ሆነህ ልብህን ወደ ሰማይ በማንሳት ከፈጣሪህ ጋር መነጋገር ትችላለህ በማለት ያስተምራል። ጸሎት በአንደበት የሚደገም ቃል ብቻ ሳይሆን፣ በልብ የሚደረግ ምስጢራዊ ንግግር ነው ሲል ይገልጻል፡፡

ንባብና ጸሎት፦ ቅዱስ ጀሩም እንደገለጸው "ስትጸልይ አንተ እግዚአብሔርን ታናግረዋለህ፤ መጽሐፍ ስታነብ ደግሞ እርሱ ያናግርሃል" ጸሎታችን የአእምሮ ሰላም እንዲሰጠን መጽሐፍትን በማንበብ ልባችንን ማነቃቃት ይኖርብናል። መጽሐፍትን ማንበብ ለጸሎታችን እንደ ነዳጅ ነው፤ ጸሎታችን እንዲያርግና ወደ እግዚአብሔር ዙፋን እንዲደርስ ያደርገዋል።

 ጸሎት እንደ "መንፈሳዊ መድኃኒት ቤት ነው" በዚህ በጭንቀትና ሩጫ በሞላበት ዓለም ውስጥ አእምሯችን ሰላም የሚያገኘው በጸሎት ነው። ቅዱስ አትናቴዎስ መዝሙራትን እንደ "መንፈሳዊ መድኃኒት ቤት " ይቆጥራቸዋል። ለማንኛውም የአእምሮ ጭንቀትና የነፍስ መታወክ የሚሆን ፈውስ በመዝሙራትና በጸሎት ውስጥ ይገኛል። ጸሎት ነፍሳችንን የሚያረጋጋ ወደብ፣ አእምሯችንንም ከዓለማዊ ማዕበል የሚጠብቅ መልሕቅ ነው።

አንባቢያን ሆይ! በዚህ በተቀደሰ የዓቢይ ጾም ወቅት ጸሎትን የዕለት ተዕለት እስትንፋሳችን እናድርገው። እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ ምክር መዝሙረ ዳዊትን እንደ መስታወት እንጠቀምበት። በአንደበት ብቻ ሳይሆን በልብ፣ በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ቦታ ሆነን ወደ ፈጣሪያችን እንጮህ። እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ጸሎትን "መንፈሳዊ ክንፍ"  አድርገን በጸሎት ኃይል ወደ ሰማያዊ ሕይወት እንክነፍ።

መጽሐፍትን በማንበብና በመጸለይ የምናገኘው ሰላም ከማንኛውም ምድራዊ ደስታ በላይ መሆኑን በተግባር የምናይበት ጾም ይሁንልን።

"መዝሙረ ዳዊት እንደ ገነት ነው፤ በውስጡም የሌሎቹ መጽሐፍት ፍሬዎች ሁሉ ይገኙበታል።" — ቅዱስ አትናቴዎስ

 

ያዕቆብ ሰንደቁ

እሁድ ዘወረደ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ/ም

 አዲስ አበባ

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ