ወግ ነነዌ፡ ከንስሐ ዕንባ ወደ ደም ዕንባ !

በስም ስህተት ነው

ክፍል አንድ

አባ ዘመደ ብርሃን

     ሰዓቱ መሽቷል የቦታው አቀማመጥ ቁልቁለት ስለሆነ ወደታች ይገፋተራል፤ አዘቅዝቀው ሲመለከቱት ጨለማው አምሳለ ሲኦል ነው ነፋሱ ደግሞ አርጩሜ ይዞ ይጋረፋል፤ የተከናነብነውን ነጠላ  ጋቢ ሊናጠቅ ይውተረተራል ጭል ጭል በምትለው ባትሪ ብርሃን ጨለማውን እየተጋፋን አባ ዘመደ ብርሃን ተከትለን ጉዞችንን የቁልቁሊት ቀጠልን፡፡

ከአባ ዘመደ ብርሃን ጋር የምንተዋወቀው ከዓመታት በፊት ነው ጠይም ረጅም ቁመት፣ ቀጭን ሰውነት፣ በነጭ ሪዝ የተሞላ ፊት፣ አርቆ ማሰብ የሚችል ብሩህ አእምሮ የተሰጣቸው  የሚያስቡትን  እግዚአብሔር የሚያሳካላቸው፤ ለመንፈሳዊ ዓላማ የመነኮሱ አባት ናቸው፡፡

 ወደ እኛ እየተመለከቱ “አይዞችሁ ልንደርስ ጥቂት ይቀረናል በርቱ አሉ ቁልቁለቱን እንደጨረስን ወደ ሜዳው ዘልቀን ጉቡታው ላይ ስንደርስ ነጋ፡ የቀዘቀዘው ሰውነታችን በጠዋቷ ፀሐይ ተፍታታ፡፡አቀበቱን መውጣት ስንጀምር አባ ዘመደ ብርሃን “ልጆቼ እዚያ ማዶም ሜዳው ላይ ያለው ጢሻው ጋር ስንደርስ የእመት አይጠግቤ ኃይለኛ ውሻ ስላለ እንዳያስደነግጣችሁ” አሉን፡፡ ቀጠል አድርገው “ውሻው እንደ አሳዳጊው ኃይለኛ እና ክፉ ነው፡፡ አሳዳጊው እመት አይጠግቤ ክፉ ሴት ነበረች ፡፡ ታዲያ ሆን ብላ ሻንቆን ፈትታ የለቀቀችው እንደሆነ፤ በላዩ ላይ ያደረው ርኩስ መንፈስ ጉልበቱ እና ፍጥነቱን ጨምሮለት ያገኘውን ሰውም ይሁን ከብት በጥርሶቹ ቦጫጭቆ ይነክሳል፡፡ ” ብለው በረጅሙ ተነፈሱ፡፡


የእመት አይጠግቤ ታሪክ ስነግራችሁ በእግዚአብሔር ሥራ ትደነቃላችሁ፡፡ የእርሻ ቦታቸውን ፣የጎተራውን እህል፣የደበቁትን ገንዘብ፤ ከፊሉን ለድሆች የተቀረውን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም በስጦታ ሰጥተዋል፡፡ ኃይለኛውን ሻንቆ እንኳን ንብረት ጠባቂ እንዲሆን ትተውት ሄደዋል፡፡ ለማንኝውም ነገ ቦታው ድረስ ሄደን እንጎበኘዋለን፡፡ በቦታው ላይ ልሠራው ያቀድኩትን የልማት ሥራ ገዳማችን በገንዘብ አቅም ለመደገፍ ያቀድኩትን ሁሉ አስረዳችኋለሁ” ብለው ንግግራቸውን ቋጩት፡፡


 አባ ታሪኩን እንዲነግሩን ብንጓጓም፤ ቦታውን ስንጎበኝ ይደርሳል ብለንን በመጽናናት ጉዞአችንን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ቤተ ክርስቲያ አቀናን ዕድሜ ጠገቡ በሆኑ የዝግባ ዛፎች የተከበበችው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን፤ ሥሪቷ ክብ ሆና ዙሪያዋን በአረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ቀለም አጊጦል  በጉልላቱ ላይ ያለው መሶበ ወርቅ ከነ መስቀሉ የቤተ ክርስቲያኑ ሞገስ ሆኖ ከሩቅ ይታያል በመሶበ ወርቁ ዙሪያው ያለው ወርቃማው ዘርፍ ድምፅ አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ምስጋና ይመስላል ቤተ ክርስቲያኑን ተሳልመን ስንጨርስ ከቤተ ክርስቲያኑ እልፍ ብሎ በሚገኘው ሰንበቴ ቤት ገብተን፤ በተዘጋጀልን ጠባብ ክፍል ውስጥ በተነጠፈልን ጅባ ላይ ተኛን ጎናችን ከምንጣፉ ጋር እንደተገናኘ ሁላችንም እንቅልፍ ጣለን፡፡

     “ተነሱ ልጆቼ ሰዓት ደርሷል” የሚል ድምፅ ስሰማ፡፡ ውይ ከመቼው ነጋ ? ብዬ እንቅልፍ ያልጠገበውን ዐይኔን እያሻሸሁ ተነሳሁ፡፡ ቡራኬ  ተቀብለን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አቀናን፤ ከጸሎተ ኪዳን በኋላ ጉዞችን ወደ እመት አይጠግቤ ቤት አደረግን፡፡

በአጋም፣ በቀጋ ፣በሰንሰል ችምችም ተደርጎ የታጠረ ሰፊ ግቢ ከመንደሩ ንጥል ብሎ ብቻውን ተቀምጦ ይታያል፡፡ ግዙፉ ዋርካ እና የኮሶ ዛፍ ለጊቢው ሞገስ ሆነውት በኩራት ዝም እንዲል አድርገውታል፡፡ በጥግ በኩል ሰው ገብቶበት የማያውቅበት የምትመስል አጭር ቆርቆሮ በር አለች፡፡ አባ ከፊት ቀድመው በሩ የታሰረበትን ገመድ ፈትተው ወደ ግቢው ዘለቁ፡፡ ገና ወደ ግቢው ስንጠጋ ጀምሮ ሁሉ ነገሩ ጥቁር የሆነ ውሻ መጮህ ጀመረ  ፈርተን ወደ ኋላ ስንል፡፡ አባ ዘወር ብለው “ አይዞችሁ አትፍሩት አይነካችሁም” አሉን፡፡ ኪዚያም “ሻንቆ ብለው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተጣሩ” ውሻ በፊታቸው መጥቶ የጫማቸውን ትቢያ መላስ ጀመረ፡፡ አባም “ምነው ሻንቆ እንግዳም አታውቅም እንዴ የምትጮኸባቸውበል እዚያ ጥግ ድንጋዩ ላይ ተቀመጥ፡፡ እንዳትንቀሳቀስ ! ” አሉት፡፡ ድምፁን አጥፍቶ ጭራውን ሸጉጦ ተቀመጠ፡፡

  ወደ ትልቁ ቤት በረንዳ ላይ ወጣን አባ ዘመደብርሃን በመስቀላቸው እየጠቆሙ “ይህ ሁሉ ግቢ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጦታ የተሠጠ ነው የእርሻውን መሬት ማሳረስ ጀምሬአለሁ  ከጅረቱ ጠልፌ ወፍጮ ቤት ለማቋቋም  እዚህ ሜዳዉ ላይ ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤት መክፈት የወደፊት እቅዴ ነው፡፡ ከዚህ ቦታ ገቢ ብቻ የገዳማችንን መናንያን የዓመት ቀለብ እና የመምህራን ደመወዝ ለማስቻል ምኞት አለኝ ፡፡ እናንተም በእውቀታችሁ እና በገንዘባችሁ  እንደተለመደው ከጎኔ  ከሆናችሁ  ብዙ  መልካም  ሥራ  እንሠራለን፡፡ ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን” አሉ፡፡ መንፈሳዊ ቁጭት በተሞላበት ስሜት፡፡

 ልጆቼ ይህን ቦታ የሰጠን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ብዙ ኃጢአት  ባለችበት  የእግዚአብሔር  ጸጋ  ትበዛለች” እንዲል  ሊቁ  ኃጢአቷ  እጅግ  በዝቶ  የነበረችው ሴት በእግዚአብሔር ችርነት  ድና  መላ  ሕይወቷን   እግዚአብሔር  ሰጥታለቸ፡፡ ወደ ውስጥ  ዘልቃችሁ  መደብ  ላይ  ተቀመጡና  ታሪኩን  ልንገራችሁ፡፡”  ብለው  ትረካቸውን  ለመጀመር  ተዘጋጁ ፡፡

**********************

እመት አይጠግቤ

  የአካባቢው ሰው “እመት አይጠግቤ” እያለ ይጠራቸዋል  የሚኖሩት ብቻቸውን ሻንቆ ከተባለው ውሻቸው ጋር    ነው ከመንደሩ ሰው  ከጎረቤቱ  ከቀዬዉ፣ ካሳሩ ከቅጠሉ ጋር አይስማሙም፤ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱ ፣ያዘነ አያጽናኑ  የታመመ አይጠይቁ፤ ማኅበር ፣ጽዋ አይጠጡ ብቻቸውን ይውላሉ ያድራሉ  ጭካኔያቸው ወሰን ዳር ድንበር    የሌለው፤ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ነው ፡፡

      የሀገሬው ሰው እንደሚያወራው አንዱን ጐበዝ ገበሬ ከሚስቱ ቀምተው በመድኃኒት አፍዝዘው ጉልበቱን እየበዘበዙ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ከዚያም ንብረቱን እና ከብቶቹን ሁሉ ሸጦ የቀደመ ትዳሩን እንዲበትን አስገደዱት፡፡ ንብረቱንም ለመዝረፍ ቤትህንም እናቃጥለው እያሉ ያስጨንቁት ጀመር አሳባቸውን በመቃወሙ ሊገድሉት ጊዜ ይጠብቁ ጀመር፡፡

     እመት አይጠግቤ ከገበሬው ጋር ተያይዘው ገበያ ሲሄዱ፤ ቀኑ ጭጋጋማ ነበር ጉም ጋርዶት አዳልጦት ወደቀ እገደል ጫፍ ተንጠልጥሎ “እጅሽን ዘርግተሽ አድኝኝ” ቢላቸው ወደ ገደል ገፍትረው ወረወሩት ሰባራ ሳንቲም የወደቀባቸው ሳይመስላቸው ባላቸውን ገደል ጨምረው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ፀሐይ ወጥቶ ደመናው ገፈፈ  ከገበያ የተመለሱ ሰዎች የደሙን እንጥብጣቢ ተመለከቱ፡፡ ቁልቁል ወርደው ገደል የገባውን ገበሬ አግኝተው ከገደሉ አውጡት፡፡ በበቅሎ ጭነው ወደ ጤና ኬላ አመጡ ብዙ ደም ስለፈሰሰው ሕይወቱ አለፈ  ቤተሰቦቹም በሀዘን ልባቸው ተሰብሮ ሬሳውን ወስደው ቀበሩ፡፡

 ወዲያውኑ ለፖሊስ በማመልከታቸው ሁኔታውን ለማጣራት እና ለምርመራ ለሦስት ወራት እመት አይጠግቤ ታሰሩ፤ “ገበሬው የሞተው መንገድ ስቶ ገደል ገብቶ እንጂ፤ በእርሳቸው ተገፍትሮ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ አልተገኘም፡፡” ብለው በነጻ ለቀቋቸው የመንደሩ ሰው “የሰው ሚስት መቀማቷ ሳያንስ አፍዝዛ ገደለችው” እያለ ከበፊቱ አብልጦ ጠላቸው፣ አራቃቸው፡፡

     ከወሕይኒ ቤት ከተለቀቁ በኋላ ከቀድሞው የበለጠ ከሰው ተገለሉ፤ የሚጎዙት በሌሊት ሲሆን በዱሩ፣ በጫካው ፣በበረሀው ሁሉ ይውላሉ ያድራሉ የሚወርሳቸው ልጅ ወይም ዘመድ የላቸውም  ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ አይጠግቡም፤ በሌሊት ተነስተው የጎረቤት ክምር ይዘርፋሉ፤ የሰው ጎተራ ሰብረው ይሰርቃሉ  ይህንንም ተግባር የሚፈጽሙት ሆን ብለው በተንኰል ከተሞላው ልባቸው አመንጭተው ነው የሚጠሉት ሰውን ብቻ አይደለም እንስሳትንም በጣም ይጠላሉ፤ በመንገድ ላይ የበግም ይሁን የፍየል ግልገል ካገኙ ከእናቲቱ ነጥለው ይወስዳሉ  በመንደሩ ዙሪያ ገባ አዲስ የተወለደ የድመት ብጭሊት  የውሻ ቡችላ ካገኙ ወደ ገደል ፈጥፍጠው ይገላሉ፡፡

     ከአባቴ ተምሬዋለሁ የሚሉት የባህል ሕክምና እውቀት አላቸው የአካባቢው “ሰው የዛር መንፈስ አለባቸው  ጋኔን ሰፍሮባቸዋል  ጠንቋይ ናቸው” ይላቸዋል ከማንኝውም ሰው ጋር ተግባቦት ባይኖራቸውም ሕፃናት እና ሴትን ግን ማየትን አይወዱም፡፡ ሲያሰኛቸው ተማተው ካልሆነላቸውም ደግሞ አስፈራርተው ከአጠገባቸው ያባርራሉ፡፡ ከመኖሩያቸው ርቆ በሚገኘው ገበያ አካባቢ ባለች አንዲት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ከሳምንቱ የተወሰነ ቀናት ያሳልፋሉ፡፡ ለልዩ ልዩ በሽታዎች የሚሆን ባሕላዊ መድኃኒቶች  እጽዋት እና ከአራዊት ስለሚቀምሙ ከሩቅ ሀገር ድረስ እየመጡ መድኃኒቱን በውድ ዋጋ ስድብ እና ግልምጫ ታክሎበት ይገዛሉ፡፡ 

     ከልዩ ልዩ ቦታ ለሚመጡ ሴቶች ብዙ ገንዘብ አስከፍለው ፅንስ ያስወርዳሉ በዚህ በኃጢአት ሥራ በየጊዜው ብዙ ገንዘብ ይሰበስባሉ ሴቶቹ ሊከፍሉት ይዘውት ከመጡት ገንዘብ በተጨማሪ፤ የአንገታቸውን ሀብል፣ የጣታቸውን ቀለበት፣ የዕጃቸውን አንባር ይዘርፋሉ የዘረፉትን ጌጣጌጥ እና ያገኙትን ገንዘብ በማዳበሪያ እየሰፉ ፍራሽ እና ትራስ አድርገው ይተኙበታል፡፡ 

     ከአካባቢው ነዋሪዎች እመት አይጠግቤን የሚቀርቦቸውም ሆነ ቤታቸው የሚገባ ማንም ሰው የለም፡፡ መኖሪያቸውን የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ መንገድ ላይ እንኳን ሳገኛቸው “ሰው ወዳጁ አባ ይጠይቁኝ እንጂ እቤት አይመጡም እንዴ ! ኃጢአቴ እኮ በዛ፤ ይፍቱኝ ጠበልም ይርጩኝ” ብለው መስቀል ተሳልመው ይሄዳሉ፡፡

     ዐብይ ጾም ሊገባ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ መሀል መንገድ ላይ ብቻቸውን ቆመው አየኋቸው፡፡ ሰውነታቸው በጣም ከስቶ ሥጋቸው አልቆአል፡፡ የለበሱት ቀሚስ እላያቸው ብጭቅጭቅ ብሎአል ፡፡ ጠጉራቸው ተንጨባሯል፤ በፍጥነት ወደ እኔ መጡ፤ ነገሩን በትኩረት እየተከታተልኩ “እንደምን አደሩ እሜቴ” አልኳቸው፤ እሳቸውም ድክም ባለ ቃል አዝነው “አሞኝ ሰንበተ እኮበጣም አመመኝ ! ” አሉ ወዲያው በፍጥነት ከየት መጣ ሳይባል በቁጣ ቃል “አባ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ታማለች ልትሞት ደርሳለች እያለ ከበሮ ይደልቃል፤ እኔ ግን አልሞትም !  እናተን ሁላችሁን ቀብሬ ሳልጨርስ አልሞትም በሏችው” እያሉ በመጮኸ ጥለውኝ በሩጫ ሄዱ፡፡

     አባ ዘመደ ብርሃን በዐብይ ጾምን የሚያሳልፉት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሰለሆነ ለሁለት ወር አልነበሩም ፡፡ እመት አይጠግቤ አቅማቸው ደክሞ፣ ጉልበታቸው ዝሎ፣ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዘው ይሰቃያሉ  በአጠገባቸው ውሀ ቀድቶ የሚሰጣቸው፣ ምግብ አብስሎ የሚያቀምሳቸው ማንም የለም በዚያ ሰፊ ግቢ ውስጥ ሻንቆ ብቻውን ያላዝናል የሰፈሩ ሰው የእመት አይጠግቤን መጥፋት ቢያውቅም “ይህች ጉድ እንደ ልማዷ መድኃኒት ስትቀምም ተደብቃ ይሆናል” ብሎ ያወራል በኋላ ግን ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት አለፉ  እመት አይጠገቤ ግን ከቤታቸው ብቅ ማለት አልቻሉም፡፡

**********************  

ወዳጅ ዘመድ እርምህን አውጣ

ልጅ በጠና የታመመባቸው ሁለት ሰዎች ከሩቅ ሀገር ድረስ የባሕል መድኃኒት አዋቂዋን እመት አይጠግቤን ቤት አጠያይቀው መጡ፡፡ የመንደሩ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ደፍሮ የሚገባ ሰው ስለሌለ እኛም ካየናቸው ቆየን አሉ ለሰዎቹ፡፡ ለዕድሩ ዳኛ  ለቀጠናው ፖሊስ ሁኔታውን እናሳውቅ ብለው ወደ ጣቢያ ወረዱ፡፡

     የዕድሩ ዳኛ  የአካባቢው ሽማግሌዎች እና የታጠቁ ፖሊሶች ግቢውን ከፍተው ገብ፡ውሻው ሻንቆ ወፍራም ሰውነቱ ሟሾ መራመድ አቅቶታል፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ ጸጥታ ሰፍኖአል፡፡ ሞተዋል እንዳይሉ የግቢው ጠረን በመጥፎ ሽታ አልታወደም፡፡ ወደ መኝታ ክፍላቸው ዘልቀው ሲገቡ መደቡ ላይ እመት አይጠግቤ ራቁታቸውን ተዘርረዋል፡፡ ተጠግተው ሲያዳምጧቸው ትንፋሻቸው ተቋርጧል፤ ሰውነታቸውን ሲዳብሱት ቀዝቅዞአል፡፡ “አይ ይህች ጉድ ሞታለች” ሲል አንዱ ጐበዝ ተናገረ፡፡ ሌላኛው ጐበዝ ቀበል አድርጐ እደጅ ለተሰበሰበው ሰው “ወዳጅ ዘመድ እርምህን አውጣ” ብሎ ሲናገር የሰፈነው ጸጥታ በአንዴ በለቅሶ ተደበላለቀ፡፡

      የአካባቢው ሽማግሌዎች የመግነዝ ጨርቅ አምጥተው አጥበው ገነዙአቸው፡፡ አስከሬኑን በሰሌን ውስጥ ጠቅልለው ለመክተት ሲዘጋጁ፤ ትንሽ ትንፋሽ ሲጥ፣ ሲር፣ሲጢጥ ሲል ሰሙ፡፡ ሁሉም ተደናገጡ “ገሚሶቹ አረ ጉድነፍሳቸው አልወጣችም፤ አየር ያግኙ ፊታቸውን ፍቱላቸው” አሉ፡፡ ሁሉም ተረባርበው በፍጥነት የመግነዙን ጨርቅ ፈቱላቸው፤ አየር እንዲገባም መስኮቱ ተከፈተ፡፡ ከቆይታ በኋላም ሰውነታቸው በዝግታ ተንቀሳቀሰ፣ ተወራጨ፡፡ ምን እንደሆነ የማይገባ ቋንቋ መናገር ጀመሩ፡፡ 

ነገሩን ያስተዋሉ ሽማግሌዎች እደጅ የሚለቀሰውን ለቅሶ እና ሙሾ አስቁመውጸልዩ እግዚኦ መሐረነበሉ ብለው ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ካህናት ይጠሩ ዘንድ፤ መልእክተኞች በፍጥነት ተላኩ ፡፡

      ሱባኤውን ጨርሼ ከገዳም የማዕዶት ማግስት ማክሰኞ ወደ ሰፈር ደረስኩ፡፡ መንገድ ላይ ሁለት ሰዎች ወደ እኔ እየሮጡ መጡና ተደናግጠው “እመት አይጠግቤ ሞተው ተገንዘው ሊቀበሩ ሲሉ እንደገና ከሞት ተነስተዋል፤ ሽማግሌዎቹ ካህናት ጠርታችሁ  ብለውን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄድን ሳለ እነሆ እርሶን አገኘኖት” ብለው አረዱኝ፡፡ ከዚያም አብረን ወደ እመት አይጠግቤ ቤት ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡

    እመት አይጠግቤ ቤት ስንደርስ ግቢው በሰው ተሞልቷል፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ አሮጊቷ መደቡ ላይ ተዘርረዋል፡፡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች አስወጥተን ውዳሴ ማርያም  መዝሙረ ዳዊት፣ ፍትሀ ዘወልድ  ደግመን ጸሎቱን ጨረስን፡፡ ከዚያም በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ብለን መስቀል ስናሳልማቸው ከእንቅልፍ እንደተቀሰቀሰ ሰው አፈፍ ብለው ብድግ አሉ፡፡

         እመት አይጠግቤ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ይንዘፈዘፋል ያለቅሳሉ፡፡ወይኔ ! ወይኔ ጉዴወየው ጉድ! ጉድ ! ጉድ ” ይላሉ ደጋግመው፡፡ ከእራስ ጸጉራቸው አንስቶ እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ይርገበገባል፡፡ ከንፈራቸው እየተንቀጠቀጠ “አየሁ በዐይኔ፣ በዐይኔ አየሁእያሉ ይንዘፈዘፋሉ፡፡ በፍርሀት ተውጠው በጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ ልብስ ደራርበው ወንበር ላይ አስቀመጧቸው ፡፡ ከዚያም እንደምንም እህል ቀምሰው ትንሽ በረቱ፡፡ እህል ውሃ ለማለት፤ እንዲሁም ለሌላም ሥራ መኝታ ቤት የነበረውን ሰው ወደ ውጭ እንዲወጡ አዘዝኩኝ፡፡ እመት አይጠግቤን ስላዩት ነገር እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው፡፡ ያዩትንም ነገር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ በሚገርም ሁኔታ ተረኩልኝ፡፡

        በደከመ ድምፅ እንዲህ ሲሉ “መልአከ ሞት መጣና አንቺ ኃጢአትሽ ከሰው ሁሉ የከፋ ነፍስ ፈጣሪሽ ይፈልግሻል” በማለት ጠራኝ፡፡ ወዲያው ነፍስ እና ሥጋዬ ተለያዩ፡፡ ነፍሴን በጥቁር ጨርቅ ሸፍኖ በመዳፉ ጭብጥ ውስጥ አስገባት፡፡ በሚያስፈራ ፍጥነትም በጨለማ መንገድ ወደ ሰማይ ወሰደኝ፡፡ በመንገዳችን ላይ በግምት ብዛታቸውም አምስት መቶ ሕፃናት ተሰልፈው ጠበቁኝ፡፡ ዐይናቸው የሚያቃጥል ጨረር ይረጫል፡፡ ሕፃናቱ በሙሉ በአንድ ድምፅ “ይህች ሴት ነፍሰ ገዳይ ናት ገና በእናታችን ማህጸን እያለን ሳንወለድ እንድንሞት፤ ደማችን በየሜዳው እንዲፈስ አድርጋለች፤ እኛን መና እንዳስቀረችን እኛም እርሷን እንበቀላታለን ” እያሉ ይጮሀሉ ፡፡ መልአከ ሞትምእባካችሁ አሳልፉን ፍርድ የእግዚአብሔር ነውኣላቸውና ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከሕፃናቱ ዐይን የሚወጣው ብርሃን የነፍስ አካሌን በሙሉ ሲያቃጥለኝወይኔ ተቃጠልኩ፤ እባካችሁ ጠብታ ውሃ ለምላሴ ስጡኝ” ብዬ በመጮህ ተማጸንኩኝ፡፡ የሰማኝም ሆነ የደረሰልኝ ማንም አልነበረም፡፡

        ትንሽ እልፍ እንዳልኩኝ ከጨለማ ውስጥ ጐልማሳ ገበሬ ብቅ ብሎ እንዲህ አለይህቺ ሴት የዘለዓለም ኩነኔ ይገባታል፤ እኔን ገደል ጨምራ ደሜን አፍስሳለችብሎ በብስጭት ይናገራል፡፡ በጨረፍታ አየሁ ይህ የማውቀው ድምፅ ይመስላል ማነውእያልኩ ሳለ በድንገት ከፊት ለፊቴ መጥቶ ድንቅር በማለት መንገዱን ዘጋው፡፡ ቀና ብዬ ሳየው ለካስ ባለቤቴ የነበረው ገበሬ ነው፡፡ የምገባበትም ጠፋኝ፤ ደነገጥኩ፡፡ መልአከ ሞትም በከሳሾቼ እና በኃጢአቴ መብዛት ግራ ተጋባ ፡፡ በብስጭት “እስቲ እናንተ ዝም በሉ! ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ እባካችሁ መንገዱን ክፈቱት ብሎ ” እኔን አስከትሎ ጉዞውን ወደ ፊት ቀጠለ ፡፡

        መልአከ ሞትን ተከትዬ ወደፊት ስሄድያዟት! ያዟት! የሚል ጫጫታሰማሁ፡፡  በጣም ብዙ የውሻ ቡችላ፣ የድመት ሙጭሊት ከበቡኝ፤ ነፍሴ የለበሰችውን ቀሚስ መሳይ ጨርቅ በሹል ጥርሳቸው ቦጫጨቁት፡፡ በከፍተኛ ድምፅምገና የእናታችንን ጡት ጠብተን ሳንጨርስ ገደል ወርውራ ፈጥፍጣ ገላናለች  ጨካኝ ሴት ናትእያሉ ሊናጠቁኝ ሞከሩ፡፡አረ ተሰቃየሁው ነከሱኝብዬ ጮኩኝ ፡፡ መልአከ ሞትም በከሳሾቼ መብዛት በጣም ተደነቀ፡፡ ከልብም አዝኖ “አይ ሰው ! ምን አይነት ጨካኝ እና ከንቱ ነውለወገኑም ለእንስሳትም ጭምር የማይራራ ”በማለት አዘነ ፡፡ የዚህችን ሴት ነፍስ በብርሃን ፍጥነት ወደ ንጉሡ ዙፋን ይዤ መሄድ አለብኝ አንዱ ጐትቶ ወደ መቀመቁ ሲኦል ውስጥ ቢጥላት ጦሱ ለእኔም ይተርፋል፡፡ መንገዴን ልቀይርብሎ  በሌላ አቅጣጫ መብረር ጀመረ፡፡

         ነፍሴን ይዞ በመካከለኝው የሲኦል እስር ቤት አቋርጦ አለፈ፡፡ በዚያም በእኔ መምጣት የተደሰቱ ነበሩ፡፡ ግማሾቹ ያፎጫሉ፣ ካንቺ ብዙ ተምረናል! ለክፉ ሥራችን ዋና አርዓያችን አንቺ ነሽ እያሉ ያጨበጭባሉ፣ ይስቃሉ፡፡ አንዱ ቀጠን ያለ ድምፅ ከወደ ኋላዬ ሰማሁ “በየማዳበሪያው ሰፍተሽ ባጠራቀምሽው ገንዘብ ፤ጠበቃ ገዝተሽ ነፍስሽን ከሲኦል ታድኛት እንደሆነ እስቲ እናያለን?” ብሎ ተሳለቀብኝ፡፡ ብዙ የማውቃቸው የመንደራችን ሰዎች በጨለማ እስር ቤት በብረት ሰንሰለት ታስረው ተመለከትኩኝ፡፡ የሚያውቁኝ ሁሉ ስሜን ይጣራሉ፤ የተወሰኑት ሙሉ ሰውነታቸው ጨለማ ውስጥ የተዋጠ ሲሆን፤ ፊታቸው ብቻ ይታያል ፡፡ በግንባራቸው ላይ የክርስትና ስማቸው ተጽፎአል፤ አንገታቸውን ብቅ በማድረግ ታይተው ተመልሰው ይጠፋሉ ፡፡ ከብዙዎች መካከል በቅርብ ጊዜ የሞተው ጎረቤቴን ስመለከት በጣም ደነገጥኩ የዚህ ሰው ቦታ እዚህ ይሆናል ብዬ አስቤ አልሜም አላውቅም ፡፡  “ድምፁን ከፍ አድርጎ ስሜን እየተጣራ ውሳኔውን ሰምተሽ ስትመለሺ  እኛ ክፍል እንዲመድብሽ አለቃችንን ለምኝውአለኝ፡፡ በሆነው ነገር በጣም ተጨንቄ መልስ ስላጣው ብቻእሺ እነግረዋለሁአልኩት፡፡

ከዚያ ቦታ ትንሽ እልፍ እንዳልን መልአከ ሞትን ፈራ ተባ እያልኩኝ ጥያቄ ጠየኩት ፡፡ይሄ ጐረቤቴ የነበረው ሰው ቤተ ክርስቲያን ይሄድ አልነበረም እንዴ ? እኔ ፍጹም ጻድቅ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ይገርማል እንዴት ተኮነነ ? ” አልኩት፡፡ መልአከ ሞትም በአግራሞት ቁልቁል እየተመለከተኝ  የተናገርኩትን ቃል በመድገምእንዴት ተኮነነ አልሽ ? ”ብሎ መልሶ ጠየቀኝ፡፡ ደንግጬ በሀፍረት ወደታች አቀረቀርኩ፡፡ መልአከ ሞት መልሱን ቀጠል አደረገና  “ለመሆኑ አንቺ ማን ሆነሽና ስለሌላው ሰው መኮነን ትጠይቃለሽአለ፡፡ በልቤም ሥራዬን እና ከሳሾቼን አስቤ በሀፍረት ሽምቅቅ አልኩኝ፡፡

        መልአከ ሞት እንዲህ አለይህ ሰው የሞተ ቀን ነፍሱን ይዤ የመጣሁት እኔ ነኝ፤ የሚገርመው ከቤተ ክርስቲያን አይለይም የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል  ግን በተግባር አይፈጽምም፤ በምግባር በሃይማኖት አይጸናም፤ በእግሩ ይመላለሳል እንጂ  የንሥሓ ሕይወት የለውም፡፡ ላዩ ሲያዩት አነጋገሩን እና አለባበሱን አሳምሮ እዉነተኛ ይመስላል፡፡ ክርስቲያን መሳይ በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በየመሸታ ቤትም ዳንኪራ ሲረግጥ፣ በጫት ቤት ሲመሽግ ድሀ ሲበድል፣ ሲያመነዝር፤ ሲጣላ ሲጨቃጨቅ፣ ሲከስ ሲካሰስ፣ ራሱን ንጹህ አድርጎ በሰው ላይ ሲፈርድ ወዘተበአጠቃላይ ክርስቲያናዊ ሕይወቱን ሲያሳድፍ የኖረ  ሁሉም አይቅርብኝ ባይ የተሰጠውን ጊዜ በከንቱ ያባከ ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ መልካም ሥራው ሲመዘን ጥቂት ሆነ፤ ክፉ ሥራው ደግሞ በዛ፣ ተትረፈረፈ ፤የሲኦል ቅጣትም ተፈረደበትብሎ መለሰልኝ፡፡ 

        ከጨለማው ሥፍራ እየወጣን በብርሃን የተከበበ ዙፋን ወዳለበት ስፍራ ደረስን፡፡ ቦታውን በነፍስ ዐይኔ ማየት አልተቻለኝም፤ መቁጠር በማይቻሉ ቅዱሳን መላእክት ተከቦአል ልዩ ደስታ የሚሰጥ መልካም መዓዛ አለው፡፡ መልአከ ሞት በእጁ መዳፍ ጭብጥ አድርጎ ይዞኛል፤ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ፍርስርስ፣ ብትንትን የምትል መሰለኝ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ነፍሴ ምንም ነገር የማትፈራ ጨካኝ ደንዳና፣ ደፋር ነበረች፡፡ በፈጣሪዬ ፊት ለመቅረብ እየተጠጋው እየተጠጋው በመጣሁ ቁጥር ራሴን ወቀስኩት፤ በደለኛነቴም አወኩ እንባዬ መጣ ከጥልቅ ሀዘን የመነጨ ጥፋተኝነት፣ ከንቱነት ተሰማኝ በደለኛነቴንም በፊቴ ባለ ነጭ ሰሌዳ ላይ ከኃጢአቴ ዝርዝር ጋር በጥቁር ቀለም ተጽፎ ታየኝ፡፡ ነፍሴን በኃጢአት መቆሸሿን እና መከርፋቷን፣ ማደፏንም ጭምር ፤በጥቁር ጨርቅ መጠቅለሌን ሳስተውል ሀፍረት ተሰማኝ፡፡ የመቅደሱ መጋረጃ ፊት ቆመን ሳለ ሳናስበው መጋረጃው ካላይ ወደታች ተከፈተ፡፡ ከሚያስፈራው ግርማው የተነሳ መቆም ስላልቻልን በግንባራችን ተደፋን፡፡ መልአከ ሞትም ኃይሉን አጥቶ በፊቱ እንደሰም ቀለጠ ፡፡ እኔም በኃጢአቴ አፍሬ ከነጥብ እጅግ አንሼ በፊቱ ተደፋሁ፡፡ ተደፍቼ ድምፅ ብቻ፤ የሚያስፈራ የሰማያዊ ንጉሥ ድምፅ ይሰማኛል፡፡

        መልአከ ሞት ይሄው ጌታዬበታዘዝኩት መሰረት “አመተ ማርያም” የተባለችውን ነፍስ ይዤ መጥቼአለሁአለ፡፡ ሰማያዊው ንጉሥ ተቆጣበደንብ አትሰማም! እኔ ይህችን ኃጢአተኛ ነፍስ መቼ አምጣልኝ አልኩህ እኔ ያልኩህ  “አጸደ ማርያምን” እንጂ፤ በል አሁኑኑ ይህችን ነፍስ ወደ ማደሪያዎ ሥጋ መልስአለው፡፡ መልአከ ሞትም ደንግጦ ሰውነቱ ተንዘፈዘፈ፤ ኃይሉ ቀነሰ  ጉልበቱ ራደ  እየተንቀጠቀጠ እና እያቃሰተ፣ እንዲህ አለአቤቱ ማረኝ ይቅር በለኝ ጌታዬ አምላኬ፤ የስም ስህተት ነው ምህረትህ ይደረግልኝብሎ ሰገደ ፡፡ ሰማያዊውም ንጉሥምሬሀለሁ ዳግመኛ ግን አትበድል፤ ተነስ የታዘዝከውን ብቻ ፈጽም”  አለው፡፡

        እኔን አንጠልጠሎ ዘወር ሲል መጋረጃው ተዘጋ፡፡ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በመላእክት መቋሚያ፣ በብርሃን ጸናጽል፣ አዲስ ምስጋና ከእጣኑ ሽታ ጋር ወደ ኋላዬ ስሰማ ደስ እያለኝ፤ ምነው ባልተመለስኩ እዚሁ በቀረው እያልኩኝ፤ ጉዞዬ ከሰማይ ወደ ምድር ሆነ ፡፡ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ መልአከ ሞትአንቺ ዕድለኛ ነፍስ በይ ደህና ሁኝ  የተሰጠሽን ጊዜ ተጠቀሚበት” አለኝ፡፡ ጭብጥ አድርጎ ከያዘበት መዳፉ ፍልቅቅ አድርጐ ወደ ታች ሲለቀኝ  ከትልቅ ተራራ ላይ እንደተወረወረ ድንጋይ ጭው እያልኩኝ  ወደታች ቀናት እና ሌሊት ተጉዤ  ወደ ማደሪያዬ ሥጋ መጣሁ፡፡

        እመት አይጠግቤ በቤተ ክርስቲያን ውሎአቸውንም አዳራቸውንም አድርገዋል፡፡ እኔ ዘንድ መጥተውእሁድ የዳግማይ ተንሳይ ዕለት ለምዕመናን ምስክርነት መስጠት ስለምፈልግ ላስፈቅዶትአሉኝ፡፡ እኔምመልካም ከቅዳሴ በኋላ ይመሰክራሉአልኩአቸው፡፡ በትህትናም ሆነውይህ ብቻ አይደለም እኮ አባ ተመልከቱእያሉ ጸጉራቸው ላይ ያለውን ሻሽ እየገለጡ የተላጨውን ጸጉራቸውን አሳዩኝ፡፡ በረጅሙ ተንፍሰውም “ የዚህ ዓለም ኑሮ ከእንግዲህ ወዲህ ይበቃኛል፤ ንብረቴን ገሚሱን ለድሆች፤ የቀረውን ደግሞ ለእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይሰጥልኝ፤ በቸርነቱ ለነፍሴ ቤዛ ይሆናት ዘንድበማለት አሳሰቡኝ፡፡ ለእሁድ ሰንበት ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ እሁድ ሥርዓተ ቅዳሴ አልቆ ተአምረ ማርያም ከተነበበ በኋላ፤ በመጀመሪያ እኔ አጠር ያለ ትምህርት ሰጠሁ፡፡ ቀጥለውም እመት አይጠግቤ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጋበዝኳቸው፡፡ ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያንም ሞተው በአካለ ነፍስ ሆነው ያዩትን ሁሉ መሰከሩ ፡፡ እንዲህም አሉእሳቱ የማይጠፋበት፣ ትሉ የማያንቀላፋበትን የሲኦልን ጥልቅ ጨለማ አይቻለሁ፡፡ ብዙ ነፍሳትም በዘለዓለማዊ ቅጣት ውስጥ ወድቀው በማየቴ እስከ አሁን እንባዬ አላቆመም፤ በሕይወተ ሥጋ ያለን ሁሉ ይህ ዓለም ከንቱና እና ጠፊ መሆኑን አውቀን እንኑር፡፡ እርስ በእርሳችን እንዋደድ፣ እንተዛዘን፤ የንሥሐ ሕይወት ይኑረን፡፡ ለሞቱትም ወገኖቻችን ለነፍሳቸው ምህረት ማግኘት ይረዳቸው ዘንድ ለድሆች በመመጽወት፣ ቁርባን በማስቆረብ፣ ፍትሀት በማስፈታት እረፍተ ነፍስ እናሰጣቸው፡፡በማለት ተናገሩ፡፡ በመቀጠልም ምእመናን አሉየሚፈርድብን የሠራነው ኃጢአት እንጂ፤ እግዚአብሔር አይደለም፤ እርሱ ሰውን ለማዳን ምክንያት የሚፈልግ መሀሪ ይቅርባይ ነው፡፡ ለፍርድ በዙፋኑ ፊት ስንቀርብ በሠራነው ሥራ እንጸጸታለን፡፡በማለት ንግራቸውን እየቋጩ ምዕመናንዘወትር ጸልዩ ሳንዘጋጅ በሞት እንዳንጠራ፤ ለንስሓ ሞት እንዲያበቃን፡፡ብለው ከመድረክ ወረዱ፡፡ ብዙ ሰዎች ተከትለዋችው የሞተውን ዘመዳቸውን ነፍስ እንዴት ነውአይተውታል ወይየት ይሆን ያለው? እያሉ ይጠይቁ ጀመር፡፡ ያዩዋቸውን እና ያሉበትን ቦታ ሲነግሩአቸው ብዙዎቸ ስለወገናቸው እና ስለራሳቸው መሪር እንባ አለቀሱ፡፡ለተከተሎአቸውም ሰዎች ድምጻቸውንም ከፍ አድርገውከእንግዲ ወዲህ ስሜ እመት አይጠግቤ ሳይሆን ዓመተ ማርያም፤ የማርያም አገልጋይ ሆኖአል በቸር ያገናኘን መልካም ሥራ ሥሩ፣ ንሥሐ ግቡ ....” እያሉ የቤተ ክርስቲያኑን ግቢ ለቀው ወጡ ፡፡ የውሃ መቅጃ ቅል ፣መቋሚያ ፣የጸሎት መጻሕፍት እና መናንያን የሚለብሱት ልብስ ወይባ ይዘው ቁልቁል ወደ ማርያም ገዳም ተጓዙ፡፡

 

ያዕቆብ ሰንደቁ  

ሚያዚያ 8 2008.

አዲስ አበባ 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ