ጸረ ሰላም ኃይሎች።
በመገናኛ ብዙኃን መስኮቶች፣ በጋዜጦች አምዶችና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ዘወትር የሚንቦገቦግ አንድ ርዕስ አለ—"ጸረ-ሰላም ኃይሎች"። እነዚህ ኃይሎች ሽብርን ከመንዛት ጀምሮ በረቀቀ ቴክኖሎጂ መረጃ በመዝረፍ የሰው ልጅን ሰላም እንደሚነሱ፣ አንዱን ከሌላው እንደሚያጋድሉና የክፋታቸው ጥግ አጥፍቶ ጠፊ በመሆን የሰውን ልብ በሐዘን እንደሚሰብሩ ጠዋት ማታ ይነገረናል። ዓለም በጭንቀት ተወጥራ ሰላም በጠፋበት በዚህ ዘመን፣ ሰው ለብሶ አምሮበት "ሰላም ነኝ" ብሎ ሰላምታ ቢሰጥህም፣ በልቡ ውስጥ ግን ለዘመናት የቆየ የሰላም ማጣት ጥማት እንዳለ ስትረዳ ትገረማለህ።
ዛሬ በሀገር፣ በከተማ፣ አልፎም በሥራ ቦታና በቤተሰብ መካከል ሰላም ጠፍቶ "ምን ይደረግ?" ብለው የሚጨነቁ ጥቂቶች አይደሉም። የሚያሳዝነው ግን፣ የሰላም ማጣት በድህነት ውስጥ ብቻ አለመሆኑ ነው። ባማረ መኪና እየተንሸራሸሩ፣ በተንጣለለ ቪላ ውስጥ እየኖሩና ሰው ሲያያቸው ሁሉ ነገር የተሟላላቸውና ሰላም የሰፈነባቸው የሚመስሉ ሰዎች፣ በውስጣቸው ግን ከፍተኛ የሰላም ረሃብ አለባቸው። ብዙዎች "ሰላም ነው?" ተብለው ሲጠየቁ የውስጣቸውን ባዶነት ደብቀው "ሰላም ነው" ይባባላሉ። ይህ ግን የልብ ሳይሆን የከንፈር ሰላም ነው፤ ሰላም ሞልቶ የተረፈ ለማስመሰል የሚደረግ የሽፋን ኑሮ ነው።
የዚህን ጥያቄ ምሥጢራዊ ምላሽ ለማግኘት ወደ ቀደመው የሰው ልጅ አፈጣጠርና ታሪክ መለስ ብሎ ማየት የግድ ይላል። በታሪካዊው ዳራ፣ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች አዳምና ሔዋን በገነት የነበራቸውን ሰላማዊ ኑሮ ያጡት "በአሸባሪው ዲያብሎስ" ክፉ ምክር ነበረ። ያን ጊዜ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ጥል ሆነ፤ ሰላምም ከምድር ተሰደደች።
በሐዲስ ኪዳን በመስቀሉ መሥዋዕትነት ያ የጥል ግድግዳ ፈረሰ፤ ጸረ-ሰላም ኃይሉ ዲያብሎስና ሠራዊቱም ድል ተመቱ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ተከትሎ፣ በሰላም ማጣት ምክንያት በራቸውን ዘግተው ለተቀመጡት ሐዋርያት በተዘጋ በር ገብቶ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" በማለት ያደላቸው ስጦታ፣ ዛሬም በጸጋው ግምጃ ቤት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታደል ድንቅ ጸጋ ሆነ።
የክርስትና ሰላም በተዘጋ በር ሳይከፍት የሚገባ፣ በወረቀት ፊርማ ሳይሆን በልብ አንድነት የሚረጋገጥ ውሳጣዊና ረቂቅ ስጦታ ነው። ሆኖም ግን፣ "ብዙ ክርስቲያኖች ባሉበት ቦታ እንዴት ራሳችን ሰላም ልናጣ ቻልን?" የሚለው ጥያቄ የዛሬው ትውልድ ትልቁ እንቆቅልሽ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 ላይ "በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከፍትወቶቻችሁ አይደሉምን?" በማለት እንደገለጸው፣ ትልቁ ጸረ-ሰላም ኃይል በውጭ ያለ ሳይሆን በገዛ ውስጣችን የሚገኘው ያልተገራ ፍላጎታችንና ስሜታችን ነው። ራሳችን ለራሳችን ጸረ-ሰላም ሆነን፣ በቁሳዊ ምኞትና በውድድር መንፈስ ተተብትበን የእግዚአብሔርን ሰላም በገዛ እጃችን እናርቃለን።
የቅዱሳን አባቶች ተሞክሮ እንደሚያስተምሩን፣ ዲያብሎስና ሠራዊቱ ልምድ ያካበቱበት ዋናው የጥፋት ሙያ የሰው ልጆችን ከፈጣሪያቸው ጋር ማጋጨትና የልብ ሰላምን መስረቅ ነው። በገዳመ ቆሮንጦስ ጌታችንን "ወድቀህ ብትሰግድልኝ ዓለምን ሁሉ እሰጥሃለሁ" በማለት በድፍረት እንደፈተነው ሁሉ፣ ዛሬም ሰላም በወርቅና በብር፣ በቪላና በመኪና የሚገኝ በማስመሰል ወጣቱን ትውልድ ያስታል።
ሐዋርያው "ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል" (ያዕቆብ 4:7) በማለት መፍትሔውን ይጠቁመናል። ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ከልብ መቃወምና ለፈጣሪ በፍርሃት መገዛት፣ የጠፋውን ሰላም ዳግም ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ነው።
በመጨረሻም፣ ለዚህ ዓለም ሰላም ብቸኛው መፍትሔ ከዓለም የማይገኝና ዓለም ሊሰጠን የማይችለው "የእግዚአብሔር ሰላም" ነው። ዮሐንስ ወንጌል 14:27 ላይ ጌታችን "ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም" እንዳለ፣ ይህ ሰላም የሚገኘው በመንፈሳዊ ሕይወት ስንስተካከልና በቅዳሴ ጊዜ የሚታደለውን ሰማያዊ ጸጋ በልባችን ስንቀበል ብቻ ነው።
ሰላም የታጣው የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሐሳብ በልባችን ስላስተናገድን ነውና፣ እነዚያን ክፉ ሐሳቦች "ዞር በል ከፊቴ" በማለት የእግዚአብሔርን ሰላም አጥብቀን ልንፈልግ ይገባል። የሰው ልጅ በመንፈሳዊ ሕይወት ሲስተካከል፣ ራሱንም ሆነ አካባቢውን የሚፈውስ እውነተኛ ሰላምን ይጎናጸፋል። እርሶስ ለሰላም መገኘት መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?
ይቆየን
#እውነተኛ_ሰላም #መንፈሳዊ_ሕይወት #የልብ_እረፍት #ጸረ_ሰላም_ኃይሎች #ኦርቶዶክስ_ተዋሕዶ #ሰላም_ለኩልክሙ
ያዕቆብ ሰንደቁ
ህዳር 13 ቀን 2018 ዓ/ም
ዕለተ ሰንበት
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ