ሰኞ 5 ጃንዋሪ 2026

ቤተልሔም፡ የትንቢት መፈጸሚያ

 

ቤተልሔም፡ የትንቢት መፈጸሚያ

በይሁዳ ምድር ካሉ ኮረብታዎች መካከል አንዷ በሆነችው ቤተልሔም ላይ ቆመን ወደ ኋላ ዘመናትን ብንቃኝ፣ ዓለምን የቀየሩ ታላላቅ ክስተቶች ይነ ህሊናችን ይታያሉ። ቤተልሔም ዝምተኛ ከተማ ብትመስልም፣ አፈርዋ ግን የነገሥታትን ደም፣ የአርበኞችን ላብና የቅዱሳንን ጸሎት አቅፋ የያዘች የታሪክ ሙዚየም ናት።

ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኘው ቤተልሔም፣ ስሟ ሲተረጎም "የእንጀራ ቤት" ማለት ነው። ይህች ከተማ በቆዳ ስፋቷ አነስተኛ ብትሆንም፣ በውስጧ የያዘችው የታሪክ ክምችት ግን ዓለምን የለወጠ  እና ያዳነው ነው። እስኪ የዚችን ከተማ አውራ ጎዳናዎች እና ዋሻ በታሪክ መነጽር እንቃኛቸው።

1.      የራሔል መቃብርና የቤተልሔም ጥንታዊነት

የቤተልሔም ከተማ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጎልቶ የሚወጣው በሐዘን ታሪክ ነው። አባታችን ያዕቆብ ወደ ኬብሮን በሚጓዝበት ወቅት፣ የምትወደው ሚስቱ ራሔል በምጥ ተይዛ በቤተልሔም (ኤፍራታ) አቅራቢያ አረፈች።ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በሚወስደውም መንገድ ተቀበረች እርስዋም ቤተ ልሔም ናት።” (ዘፍጥረት 35:19) ያዕቆብም በመቃብሯ ላይ የሐውልት ድንጋይ አቆመ። ይህ ክስተት ቤተልሔም ከክርስቶስ ልደት በብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የታወቀች ስፍራ መሆኑዋን ያሳየናል። እስከ ዛሬ ድረስ ይህ መቃብር የአይሁድ፣ የክርስቲያንና የሙስሊም ተጓዦች የሚጎበኙት የታሪክ ምልክት ነው።

2. የሩትና የቦዔዝ የፍቅር ታሪክ፡

ወደ መሳፍንት ዘመን ስንመለስ፣ ቤተልሔም የአንዲት ሞአባዊት ሴት የጽናት ታሪክ መድረክ ሆና እናገኛታለን። ቤተልሔም "የእንጀራ ቤት" የተባለችው በከንቱ አይደለም። በሩት መጽሐፍ ውስጥ እንደምናየው፣ በምድሪቱ ላይ ረሃብ በነበረበት ወቅት ቤተልሔም የተስፋ ምድር ነበረች። ሞአባዊቷ ሩት አማቷን ናኦሚን ተከትላ ወደዚች ከተማ በመጣች ጊዜ፣ በቦዔዝ የእርሻ ማሳ ውስጥ ቃርሚያ ስትሰበስብ ያገኘችው በረከት ለታላቁ የዳዊት የትውልድ ግንድ መገኛ ሆነ። ይህ ታሪክ ቤተልሔም የሰው ልጅ ዘርና ጎሳ ሳይለይ እግዚአብሔር ለሁሉ ጸጋውን የሚሰጥባት ስፍራ መሆኗን ያበስራል።

3. የዳዊት ከተማና የቅብዐት ምስጢር

ቤተልሔም በታሪክ መዝገብ ላይ በደመቀ ቀለም የተጻፈችው ግን በንጉሥ ዳዊት ምክንያት ነው። እረኛው ዳዊት በቤተልሔም ሜዳዎች ላይ በጎቹን እየጠበቀ በበገናው እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። ነቢዩ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ እሴይ ቤት በመጣ ጊዜ፣ ከታላላቆቹና ቁመና ካላቸው ወንድሞቹ ይልቅ፣ በቤተልሔም ሜዳ ላይ በግ የሚጠብቀው ታናሹ ዳዊት ለእስራኤል ንጉሥነት ተቀባ።“ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ።” (1 ሳሙኤል 16:13)

ቤተልሔም "የዳዊት ከተማ" የተባለችውም ዳዊት የተወለደባት፣ ያደገባትና የተቀባባት በመሆኗ ነው። የዳዊት ወታደሮች ሳይቀሩ "ከቤተልሔም በበር አጠገብ ካለው ጉድጓድ ውሃ ማን በሰጠኝ!" ብለው የሚናፍቋት የተባረከች ስፍራ ነበረች።

4. የትንቢቱ ፍጻሜ፡ የዓለም መድኃኒት ልደት

ይህች ትንሿ ከተማ የዓለም ትኩረት የሆነችው ግን የነቢያት ትንቢት ሲፈጸምባት ነው። ነቢዩ ሚክያስ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት "አንቺ ቤተልሔም... ከአንቺ እስራኤልን የሚገዛ ይወጣል" (ሚክያስ 5:2) ብሎ የተነበየው ትንቢት በግርግም ውስጥ ተፈጸመ።

የሮማው ንጉሥ አውግስጦስ ቄሳር ባወጣው የሕዝብ ቆጠራ ትዕዛዝ ምክንያት፣ ዮሴፍና ማርያም ከናዝሬት ተነስተው ወደ ትውልድ ከተማቸው ቤተልሔም መጡ። በዚያም የእንግዳ ማረፊያ ቦታ በመጥፋቱ፣ በቤተልሔም ዋሻ ውስጥ የዓለም ብርሃን ተወለደ። ያን ዕለት የቤተልሔም እረኞች የመላእክትን የምስራች የሰሙባት፣ ሰብአ ሰገልም ከሩቅ ምስራቅ በኮከብ ተመርተው ወርቅ፣ እጣንና ከርቤ ያቀረቡባት ድንቅ ከተማ ሆነች።

5. ዮሴፍና ማርያም፡ ወደ ትውልድ ስፍራ ጉዞ

ምንም እንኳን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ያደገው በናዝሬት ቢሆንም፣ የዮሴፍና የማርያም የትውልድ ሥር ከቤተልሔም (ከዳዊት ቤት) ጋር የተሳሰረ ነው። ሉቃስ 2:4 ላይ እንደሚነግረን፣ ዮሴፍ ከዳዊት ወገንና ቤት ስለነበረ "የዳዊት ከተማ ወደምትሆን ወደ ቤተልሔም" ወጣ ይላል። ይህ ጉዞ ቤተልሔም የቤተሰብ ሥርና የቃል ኪዳን መገኛ መሆኗን ያረጋግጣል።

ዛሬ ቤተልሔም ምን ትመስላለች?

በአሁኑ ወቅት ቤተልሔም በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የሆነውን የልደት ቤተክርስቲያንን (Church of the Nativity) በጉያዋ ይዛለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞች በየዓመቱ የክርስቶስን የልደት ስፍራ ለመሳለምና የታሪኩ ተካፋይ ለመሆን ወደዚህች ከተማ ይተማሉ።  ቤተልሔም ዛሬም እንደ ጥንቱ የዓለም መንፈሳዊ መካነ ህብስት ሆኖም ግን የዛሬዋ ቤተልሔም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ብቻ ሳትሆን፣ የፖለቲካ፣ የቱሪዝም እና የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት መገናኛ ነጥብ ናት።




1. የጌታ ልደት አከባበር በቤተልሔም

በቤተልሔም የጌታ ልደት (ገና) አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሦስት ጊዜ ነው የሚከበረው። ይህም በከተማዋ ባሉ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የዘመን አቆጣጠር ምክንያት ነው፡-

·         ታኅሣሥ 25 (December 25): በካቶሊክ እና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት።

·          ታህሳስ 29 (January 7): በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ በግብፅ ኮፕቲክ፣ በግሪክ እና በሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት።

·         ጥር 19 (January 19): በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን።

በእነዚህ ቀናት የከተማዋ ማዕከል የሆነው የማንገር አደባባይ (Manger Square) በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ይሞላል። የልደት ዋሻ በሚገኝበት "የልደት ቤተክርስቲያን" ውስጥ ታላላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ይከናወናሉ። በተለይም በታኅሣሥ 24 ምሽት የሚደረገው የቅዳሴ ጸሎት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቴሌቪዥን በቀጥታ ይከታተሉታል።

2. በቤተልሔም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት

ቤተልሔም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሚታይባት ስፍራ ናት። ዋና ዋናዎቹም፡-

·         የልደት ቤተክርስቲያን (Church of the Nativity): በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ሲሆን፣ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህ ቤተክርስቲያን በጋራ በግሪክ ኦርቶዶክስ፣ በአርመን ኦርቶዶክስና በሮማ ካቶሊክ ቁጥጥር ስር ነው።

 ·         የቅድስት ካትሪን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን: ከልደት ቤተክርስቲያን ጋር ተያይዞ የሚገኝ ሲሆን የገና ሌሊት ቅዳሴ የሚካሄድበት ስፍራ ነው።

 ·         የወተት ዋሻ : እመቤታችን ቅድስት ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስን ስታጠባ የወተት ጠብታ የፈሰሰበትና ድንጋዩ ወደ ነጭነት የተቀየረበት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስፍራ ነው።

 ·         የእረኞች ሜዳ: መላእክት ለእረኞች የምስራች የነገሩበት ስፍራ ሲሆን፣ እዚያም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት (ካቶሊክና ግሪክ ኦርቶዶክስ) የየራሳቸው ይዞታ አላቸው።

 ·         የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን: በቤተልሔም ውስጥ የራሷ የሆነ ገዳም እና ይዞታ ያላት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንገደኞች በዚያ ያርፋሉ፣ ይጸልያሉ።

3. አይሁድ ቤተልሔም ከተማዋን እንዴት ያዩታል?

ለአይሁድ ቤተልሔም ታሪካዊቷ የንጉሥ ዳዊት ከተማ ናት። ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት ቤተልሔም ፍልስጤም አስተዳደር ስር የምትገኝ በመሆኗ፣ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው አይሁድ ወደ ከተማዋ በነፃነት መግባት በሕግ ተከልክለዋል።

አይሁድ ከከተማዋ መግቢያ ላይ የሚገኘውን የራሔልን መቃብር በከፍተኛ ሁኔታ ያከብራሉ። ይህ ስፍራ በእስራኤል ወታደራዊ ጥበቃ ስር ስለሆነ አይሁድ በብዛት መጥተው ይጸልዩበታል። ነገር ግን ወደ ከተማዋ መሃል መግባት ለደህንነታቸው አስጊ እንደሆነ ስለሚታሰብና በፖለቲካዊ ውጥረቱ ምክንያት ግንኙነቱ ውስብስብ ነው።

4. የቱሪስቶች ብዛት

ቤተልሔም ኢኮኖሚ በቱሪዝም ላይ የተመሰረተች ከተማ ናት።

·    የቱሪስት ብዛት: በየዓመቱ በአማካይ 1.5 ሚሊዮን እስከ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ቱሪስቶች ቤተልሔምን ይጎበኛሉ። በተለይ በገና ወቅት ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ ይያዛሉ።

 

·   የእደ ጥበብ ውጤቶች: ከተማዋ በወይራ እንጨት በሚሠሩ ቅርጻ ቅርጾች (መስቀል፣ በረት፣ ቅዱሳን ሥዕላት) ትታወቃለች። ይህ የከተማዋ ነዋሪዎች ዋና የገቢ ምንጭ ነው።

5. የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ

ቤተልሔም ዛሬ ከእስራኤል ከተሞች በግዙፍ የኮንክሪት ግድግዳ ተለይታ ትገኛለች። ወደ ከተማዋ ለመግባትና ለመውጣት በእስራኤል ወታደሮች የሚጠበቁ ኬላዎችን ማለፍ ግድ ይላል። ይህ ሁኔታ በነዋሪዎች እንቅስቃሴና በቱሪዝሙ ላይ አንዳንድ ጊዜ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ሆኖም ቱሪስቶች በሰላም ገብተው እንዲወጡ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረጋል።

6 .ጌታ የተወለደበት ዋሻ

"ጌታ የተወለደው እዚህ ነው" ተብሎ ለሚታመነው ስፍራ (የልደት ዋሻ) እንደ ማረጋገጫ የሚጠቀሱ የታሪክ እና የመንፈሳዊ ተአምራት ማስረጃዎች አሉ።

 የታሪክና የትውፊት ማረጋገጫ

ጌታ በተወለደ በአጭር ጊዜ ውስጥ (100 ዓመታት ባነሰ ጊዜ) ስፍራ በክርስቲያኖች ዘንድ ይታወቅ ነበር።

·    ቅዱስ ዩስጢኖስ: 150 . አካባቢ (ኢየሱስ በተወለደ 150 ዓመቱ) ጌታ የተወለደው በቤተልሔም አቅራቢያ ባለ ዋሻ ውስጥ እንደሆነ ጽፏል።

· ኦሪገን: 248 . ቤተልሔምን በጎበኘበት ወቅት፣ በከተማዋ ያሉ ሰዎች ሁሉ ጌታ የተወለደበትን ዋሻ እንደሚያውቁና አህዛብ (ሮማውያን) እንኳ ሳይቀሩ ስፍራውን ለይተው እንደሚያውቁት መስክሯል።

የአፄ ቆስጠንጢኖስና የእናቱ የንግሥት ዕሌኒ ምስክርነት

4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣች ጊዜ፣ የአካባቢው ሰዎች ጥንት ጀምሮ ሲጠብቁት የነበረውን የልደት ዋሻ አሳዩዋት። 326 . በዚህ ዋሻ ላይ የመጀመሪያው የልደት ቤተክርስቲያን (Church of the Nativity) ተሠራ።  የሚገርመው ነገር፣ ከዚያ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቤተክርስቲያኑ በተለያዩ ጦርነቶች ቢፈርስም፣ ዋናው መሠረትና ዋሻው ግን ሳይነካ ጸንቶ ቆይቷል።

የሚታይ ድንቅ ምልክት፡ የብር ኮከቡ

በዋሻው ውስጥ ጌታ ተወለደ ተብሎ በሚታመነው ትክክለኛ ስፍራ ላይ የብር ኮከብ ተቀምጧል። ይህ ኮከብ 14 ጨረሮች አሉት።

· ምልክቱ፡ 14 ጨረሮች ያሉት መሆኑ ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ላይ ያለውን የጌታን የትውልድ ግንድ (ከአብርሃም እስከ ዳዊት 14 ከዳዊት እስከ ባቢሎን 14 ከባቢሎን እስከ ክርስቶስ 14 ትውልድ) ለመወከል ነው።

·    ጽሑፉ፡ በኮከቡ ላይ በላቲን ቋንቋ "Hic de Virgine Maria Jesus Christus Natus Est" (እዚህ ከድንግል ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ) የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል።

7 ተአምራዊው "የወተት ዋሻ"

ከዋሻው ጥቂት ሜትሮች ርቆ የሚገኝ ሌላው ድንቅ ምልክት "የወተት ዋሻ" ነው። ትውፊቱ እንደሚነግረን እመቤታችን ሕፃኑን ስታጠባ የወተት ጠብታ በድንጋዩ ላይ በመፍሰሱ፣ ቀይ የነበረው የዋሻው ድንጋይ ወደ ነጭነት ተቀይሯል።

·   ተአምራቱ፡ ዛሬም ድረስ መካን የሆኑ ሴቶች (ክርስቲያኖችም ሙስሊሞችም) ከዚህ ነጭ ድንጋይ ላይ የተፈጨውን ዱቄት በእምነት በመውሰድ ልጅ እንደሚወልዱ ይነገራል፤ ለዚህም ምስክር የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የልጆች ፎቶዎች በቤተክርስቲያኑ ግድግዳ ላይ ተለጥፈው ይታያሉ።

 ድንቅ የታሪክ ክስተት (የፋርስ ወራሪዎች)

614 . ፋርሶች (ፐርሺያ) ፍልስጤምን በወረሩ ጊዜ በየቦታው ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥለው ነበር። ሆኖም የቤተልሔምን የልደት ቤተክርስቲያን ለማጥፋት ሲገቡ፣ በግድግዳው ላይ የተሣለውን የሰብአ ሰገልን ሥዕል ተመለከቱ። ሰብአ ሰገል የፋርስ ልብስ (የራሳቸውን ሀገር ልብስ) ለብሰው ስለነበር፣ ፋርሶቹ ሥፍራውን አክብረው ሳይነኩት ወጥተዋል። ይህ ለቤተክርስቲያኑ መትረፍ እንደ ትልቅ ተአምር ይታያል።

ወደ ዋሻው ውስጥ የገባ ማንኛውም ሰው የሚሰማው ልዩ ሰላምና መንፈሳዊ ኃይል አለ። ዋሻው ጠባብና ዝቅ ያለ በመሆኑ፣ ወደ ስፍራው የሚገባ ሁሉ ጎንበስ ብሎ (በትሕትና) መግባት አለበት። ይህም የጌታን ትሕትና የሚያስታውስ ድንቅ ምልክት ነው።

በበረት ተኛ በጨርቅ ተጠቀለለ የዓለም መድኃኒት በቤተልሔም ተወለደ።

ሰኞ 29 ዲሴምበር 2025

የናብከደነጾር ሁለተኛው ሕልም

 

የናብከደነጾር ሁለተኛው ሕልም

ክፍል ሦስት ከባለፈው የቀጠለ

 የታላቁ ዛፍ ሕልም ( (ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 4 )

ይህ ሕልም ግን በቀጥታ በናቡከደነጾር ትዕቢት ላይ ያተኮረ ነበር።

እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር።  ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ።

በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት።  የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረⴾ

 እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ።  ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።

በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ።  በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ።  ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን።  ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት።

እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፤ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።

 የዛፉ ሕልም ዝርዝር

ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየው የሚከተለውን ነበር፦

   ታላቅ ዛፍ፦ በምድር መካከል በጣም ረጅም፣ ሰማይን የነካ፣ ቅጠሉ ያማረና ፍሬው የበዛ ዛፍ አየ። በታችዋ የምድር አራዊት ይጠለላሉ፣ በቅርንጫፎቿም የሰማይ ወፎች ይሰፍራሉ፤ ፍጡርም ሁሉ ከእርሷ ይበላ ነበር።

   ቅዱሱ መልአክ፦ አንድ "ቅዱስ ጠባቂ" ከሰማይ ወርዶ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ "ዛፉን ቍረጡት፣ ቅርንጫፎቹንም ቍረጡ፤ ቅጠሉን አርግፉ፣ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊቱም ከሥሩ ይውጡ... ነገር ግን የሥሩን ጉቶ በብረትና በናስ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል በምድር ውስጥ ተውት።"

   ፍርዱ፦ በሰማይ ጠል ይርሰስ፣ ዕድሉም ከምድር አራዊት ጋር ይሁን፤ የሰው ልብ ከእርሱ ይወሰድ፣ የእንስሳም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም (ሰባት ዓመታት) በላዩ ይለፉ አለው።

2. የነቢዩ ዳንኤል ትርጓሜ

ነቢዩ ዳንኤል ሕልሙን ሲሰማ በጣም ደነገጠ። ትርጉሙም እንዲህ ነበር፦

   ዛፉ አንተ ነህ፦ ዛፉ የንጉሡን ታላቅነትና ግዛቱን ይወክላል።

   መቆረጡ፦ ንጉሡ ከሰው ተለይቶ እንደሚባረርና ከሜዳ አራዊት ጋር እንደሚኖር ያሳያል።

   ሰባቱ ዘመናት፦ ንጉሡ "ልዑሉ እግዚአብሔር በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሰለጥን፣ ለወደደውም እንደሚሰጠው" እስኪያምን ድረስ ለሰባት ዓመታት አእምሮውን እንደሚስት ተነገረው።

  ጉቶው፦ የዛፉ ጉቶ መተው ግን እግዚአብሔርን ካወቀ በኋላ መንግሥቱ እንደሚመለስለት ተስፋ የሚሰጥ ነበር።

3. ፍጻሜው (የንጉሡ መውደቅና መነሣት)

ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ፣ ናቡከደነጾር በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ እንዲህ አለ፦

"ይህች እኔ ለክብሬ ግርማ በጉልበቴ ብርታት የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?" ይህንን የትዕቢት ቃል ተናግሮ ሳይጨርስ ከሰማይ ድምፅ መጣ። ወዲያውም፦

1.   ቅጣቱ፦ አእምሮውን ሳተ፤ ከሰው ተለይቶ ተባረረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰሰ።

2.     ለውጡ፦ ጠጉሩ እንደ አንበሳ ጠጉር ረዘመ፣ ጥፍሩም እንደ ወፍ ጥፍር ሆነ።

3.   ፈውሱ፦ ሰባቱ ዓመታት ሲያበቁ ናቡከደነጾር ዓይኑን ወደ ሰማይ አነሣ፤ አእምሮውም ተመለሰለት። በዚያን ጊዜ ትዕቢቱን ትቶ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነ።

4. የታሪኩ ትምህርት

ይህ ታሪክ የሚያስተምረን "እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚያዋርድና ትሑታንን ከፍ እንደሚያደርግ" ነው። ናቡከደነጾር ከዚህ ክስተት በኋላ እግዚአብሔርን "የሰማይ ንጉሥ" ብሎ በማመስገን ታሪኩን አጠናቋል።

 

 የታላቋቋ ባቢሎን መውደቅ

የባቢሎን ግዛት በታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ አስደናቂና በሀብት የበለጸጉ ስልጣኔዎች አንዱ ነበር። በተለይ በናቡከደነጾር ዘመን (ከ605-539 ዓ.ዓ.) የነበራት ገጽታ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው እንደ ተረት የሚመስል ውበት የነበራት ታላቅ በወርቅ የተንቆጠቆጠች ከተማ ነበረች።

1. የምድር ጌጥ የሆነችው ከተማ

ባቢሎን በዚያ ዘመን የዓለም የንግድ፣ የጥበብና የሀብት ማዕከል ነበረች። ሄሮዶተስ (Herodotus)፦ "የታሪክ አባት" በመባል የሚታወቀው የግሪክ ታሪክ ጸሐፊ ስለ ባቢሎን ግንቦች ግርማና ስለ ከተማዋ ስፋት በዝርዝር ጽፏል። ከተማዋ በታላላቅ ግንቦች የታጠረች ሲሆን፣ ግንቦቹ ላይ ሁለት ሰረገላዎች ጎን ለጎን ካለምንም ችግር መሮጥ ያስችሉ ነበር ይባላል። የከተማዋ መግቢያ የነበረው "የኢሽታር በር" (Ishtar Gate) መስተዋት በሚመስሉ ሰማያዊ ጡቦች የተሠራና በፈረሶችና በዘንዶዎች ምስል ያጌጠ በመሆኑ፣ ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶች በሙሉ በከተማዋ ግርማ ይገረሙ ነበር።




ለባቢሎን ከተማ ስምንተኛውና ዋናው መግቢያ በር የነበረው "የኢሽታር በር" በወቅቱ በባቢሎን ብትመለከው ለፍቅርና ለጦርነት አምላክ ለ"ኢሽታር" የተሰጠ በመሆኑ በሷ ስም ተሰይሟል። በነገራችን ላይ የኢሽታር በር (Ishtar Gate)፦ በጀርመን አርኪኦሎጂስቶች ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን አገር፣ በርሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፐርጋሞን ሙዚየም (Pergamon Museum) ውስጥ ነው። የፐርጋሞን ሙዚየም ለትልቅ እድሳት (Renovation) ሲባል ለተወሰኑ ዓመታት ለጎብኚዎች ተዘግቷል። እድሳቱ እስከ 2027 ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ስለሚችል፣ በአካል ሄዶ ለማየት የሚፈልግ ሰው አስቀድሞ የሙዚየሙን ድረ-ገጽ ማረጋገጥ ይኖርበታል። መጎብኘት የቻለ ሰው ፎቶ ተነስቶ ይህን ታሪክ ያጋራን  ይሆናል ?

2. የለም ድንቅ፦ የባቢሎን ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ

ቤሮሰስ (Berossus)፦ በ3ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የነበረ የባቢሎን ካህን ሲሆን፣ ስለ ናቡከደነጾር የግንባታ ሥራዎችና ስለ "ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራዎች" መረጃ ጥሏል። ናቡከደነጾር ከሜዶን ላገባት ሚስቱ (አሚቲስ) የትውልድ አገሯን ተራራማና አረንጓዴ ገጽታ ትናፍቅ ስለነበር ለዚያ ብሎ በባቢሎን ሜዳ ላይ ሰው ሠራሽ ተራራ አስገነባላት። ይህ "የተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ" ተብሎ የሚታወቀውና ከዓለም ሰባት ድንቆች አንዱ የሆነው ስፍራ ሲሆን፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ በረቂቅ ጥበብ ውኃ እየተቀዳ የሚጠጣ ደረጃ በደረጃ የተገነባና አረንጓዴ ገነት የሚመስል ውብ የአትክልት ሥፍራ ነበር።

3. የወርቅና የንግድ ማዕከል

በባቢሎን ውስጥ የሚገኙት ቤተ መቅደሶች፣ በተለይም የባዕድ አምላኩ የ"ማርዱክ" መቅደስ፣ በወርቅ የተለበጡ ነበሩ። ከተማዋ ከሕንድ እስከ ግብፅ ባለው የንግድ መስመር መካከል ስለምትገኝ፦

   ከየአቅጣጫው የሚመጡ ውድ ጨርቆች፣ ቅመማ ቅመሞችና ዕንቁዎች ይፈሱባት ነበር።

   ሕንጻዎቿ በደማቅ ቀለማት ያሸበረቁና በሥነ-ሕንጻ ጥበብ የመጠቁ ነበሩ።

   ከተማዋን በሁለት በኩል የሚከፍላት የኤፍራጥስ ወንዝ ለከተማዋ ግርማና ለንግድ ሥራዋ ትልቅ አንቀሳቃሽ ነበር።

4. የታሪክና የጥበብ መፍለቂያ

ናቡከደነጾር ከተማዋን ሲገነባት "ለዘላለም እንድትኖር" አስቦ ከተማዋ በታሪክ ስትታወስ እንድትኖር በእያንዳንዱ ጡብ ላይም ስሙን ያሳርፍ እንደነበር ይነገራል። ባቢሎን በሀብት እና በታሪካዊነት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትም የመጠቀች ነበረች። የከዋክብት ምርምር እና የሒሳብ ጥበብ እጅግ የዳበረባት ስፍራ ሆና ነበር።

የባቢሎን ውድቀት (በ539 ዓ.ዓ.)

ባቢሎን በዚያ ዘመን የነበራት ውበትና ሀብት "የወርቁ ራስ" መባሏ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ሆኖም ግን፣ ነቢዩ ዳንኤል አስቀድሞ እንደተነበየው፣ ይህ ሁሉ ግርማና ሞገስ በ539 ዓ.ዓ. በፋርሳውያን እጅ ወድቆ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ዘንድ ታዋቂውን የታሪክ መጽሐፍ "ዜና አይሁድ" የጻፈው ዮሴፍ ወልደኮርዮን በኋላ ወደ ሮም ከሄደ በኋላ "ፍላቪየስ" የሚለውን የሮማውያን ስም ወስዷ ፍላቪየስ ጆሴፈስ (Flavius Josephus ) ተብሎ የሚታወቀው በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ፣ በ20 ጥራዞች ተከፋፍሎ የቀረበ ታላቅ ድርሳን አዘጋጅቷል።  የታሪካዊ ጽሁፉ ዋና ዓላማው ለአረማውያን (ለሮማውያንና ለግሪካውያን) የአይሁድን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት ጥንታዊነትና ክብር ለማስረዳት ነው። ከጻፋቸው ታሪክ ውስጥም የናቡከደነጾርንና የዳንኤልን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ምንጮች አቀናጅቶ መከተቡ ነው።

የባቢሎን ውድቀት በታሪክ ውስጥ በጣም ከሚታወቁትና በብልሃት ከተመሩ ድሎች አንዱ ነው። ባቢሎን በታላላቅ ግንቦች የታጠረችና በጣም የሰለጠነ የጦር ሠራዊት የነበራት ለዓመታት የሚበቃ ምግብ ያከማቸች ስለነበረች፣ በጦርነት ሰብሮ ለመግባት የማይቻል ይመስል ነበር። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የቆረጠው ቀን ሲመጣ አወዳደቋ የእንቦይ ካብ ሆነ እንዲህም ሆነ፦

  የቂሮስ ብልሃት፦ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ (Cyrus the Great) የከተማዋን ቅጥሮች ሰብሮ መግባት እንደማይችል ሲረዳ፣ እንዲህ ብልሀት አሰበ በከተማዋ መካከል የሚያልፈውን የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫ አስቀይሮ በወንዙ በኩል ወደ ከተማዋ ለግባት አቀደ።

  የወንዙ መድረቅ፦  የወንዙን አቅጣጫ በመቀየሩ የወንዙ ውሃ ዝቅ ሲል፣ የፋርስ ወታደሮች በወንዙ የታችኛው ስር ተሹለክልከው ወደ ከተማዋ ገቡ።

  የበልጣሶር ድግስ፦ በዚያው ምሽት የናቡከደነጾር የልጅ ልጅ የሆነው ንጉሥ በልጣሶር በቤተ መንግሥቱ ለሺህ መኳንንት ታላቅ ግብዣ እያደረገ ነበር። በዚያ ድግስ ላይ ከኢየሩሳሌም መቅደስ የተማረኩትን የወርቅ ዕቃዎች ለወይን መጠጫነት ተጠቀሙ።

  በግድግዳው ላይ የተጻፈው ጽሕፈት፦ በድንገት የሰው እጅ ጣቶች መጥተው በግድግዳው ላይ "ሜኔ፥ ሜኔ፥ ቴቄል፥ ፋሬስ" የሚል ጽሕፈት ጻፉ። ትርጉሙም "መንግሥትህ ተቆጠረ፣ በሚዛን ተመዘንህ ቀልለህም ተገኘህ፣ መንግሥትህም ለሜዶንና ለፋርስ ተሰጠች" የሚል ነበር።

  የመጨረሻው ውጤት፦ በዚያው ሌሊት በልጣሶር ተገደለ፤ ያለ ምንም ትልቅ ውጊያ ታላቂቱ ባቢሎን በፋርስ ቁጥጥር ስር ወደቀች።

ነሀስ የሆነው የግሪክ መንግስት

ክፍል አራት ይቀጥላል