የነሐሱ የግሪክ መንግስት እና ዝነኛውን ታላቁን እስክንድር ክፍል አራት ከባለፈው የቀጠለ
በዓለም የታሪክ ምዕራፍ
እጅግ አስደቂ
ከሆኑት የዓለም
መንግስታት ሽግግሮች
አንዱ ነው።
ባቢሎን በፋርስ
እጅ ከወደቀች
በኋላ፣ ዓለምን
ለረጅም ጊዜ
የገዛው የሜዶንና
የፋርስ መንግስት
ነበር። ነገር
ግን፣ የነሐስ
መንግስት ተብሎ
የተመሰለው የግሪክ
(የመቄዶንያ) መንግስት
ወደ ስልጣን
የመጣው በራሱ
ለየት ባለ ሂደት ነው።
በክፍል አራት ታሪካችን አስደናቂውን የግሪክ መንግስት እና ዝነኛውን ታላቁን እስክንድር ፣የነሐሱን
መንግስትም እንመለከታለን ጥሩ የንባብ ጊዜን ተመኘሁላችሁ።
የግሪክ መንግሥት መነሳትና መውደቅ በትንቢት መነጽር
የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ዓለምን በኃያልነት የገዛው ለ208 ዓመታት ያህል ነው። ይህ ዘመን የሚሰላው ታላቁ ቂሮስ ባቢሎንን ድል ካደረገበት ከ539 ዓ.ዓ. ጀምሮ ነው። ይህም የመጨረሻው የፋርስ ንጉሥ እስከ ወደቀበት እስከ 331 ዓ.ዓ. ድረስ ነው። በንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ዘመነ መንግስት የፋርስን መንግሥት በግሪክ መንግስት ተሸንፎ ፍጻሜውን
አገኘ።
የነብር ፍጥነት
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ንጉሥ እስክንድር መቅዶንዮስ
(Alexander the Great) ዓለምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንቀጠቀጠ መሪ ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ዛሬ የምናየው ይህ ታሪክ ግን እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፣ ገና ዓለም ሳይሰማውና ሳይገነዘበው በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት በምስልና በምሳሌ ተቀምጦ የነበረ ታላቅ መለኮታዊ "ትዕይንት" ነው።
1. የናሱ መንግሥትና ባለ ክንፉ ነብር
ትንቢቱ የሚጀምረው ከታላቁ እስክንድር መወለድ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነው። ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ያየው ያ ግዙፍ ምስል አራት ታላላቅ መንግሥታትን ይወክላል። የመጀመሪያው ወርቅ (ባቢሎን)፣ ሁለተኛው ብር (ሜዶ ፋርስ) ሲሆኑ፣ ሦስተኛውና ሆዱና ጭኑ ናስ የሆነው ክፍል ግን የግሪክን መንግሥት ይወክላል (ዳን. 2:39 )።
ነቢዩ ዳንኤል ይህንኑ የግሪክ መንግሥት በሌላ ራዕይው እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ "ነብር የሚመስል
ሌላ ነበረ፤ በጀርባውም ላይ አራት የወፍ ክንፎች ነበሩት፤ ለአውሬውም አራት ራሶች ነበሩት" (ዳን. 7:6)።
ለምን በነብር ተመሰለ? ነብር በተፈጥሮው ፈጣን ነው፤ አራት ክንፍ ሲጨመርበት ደግሞ ፍጥነቱ ከተፈጥሮ በላይ ይሆናል። የግሪክ ንጉሥ ታላቁ እስክንድር በፈጣን ክንፍ ባለው ነብር የተመሰለው
ገና በ20 ዓመቱ ንጉሥ ሆኖ፣ በ10 ዓመት ውስጥ ብቻ በፍጥነት እስከ ሕንድ ዳርቻ ዝናው ናኝቶ ዓለም የተቆጣጠረ ፤በጦር ጉልበቱ እና ኃይሉ በትንቢቱ መሰረት ፈጣን ነበር መሆኑን በተግባር ያስሰከረ ፈጣን ንጉሥ በሆኑ ነው።
ለምን በነሐስ ተመሰለ? የግሪክ ወታደሮች የነሐስ (ናስ) ጥሩር፣ ጋሻና ቆብ ያደርጉ ስለነበር የታላቁ እስክንድር ጦርን "ነሐስ የለበሱ የግሪክ ልጆች" በመባል በታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ይጠራሉ ።
ወጣቱ እስክንድር ገና በ20 ዓመቱ የንጉሥነት ዘውድ ሲደፋ፣ በዓይኖቹ ውስጥ የሚታየው ረሃብ ግዛትን የማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የመጠቅለል ብሎም ማንነታቸውን
በማጥፋት ፍጹም ግሪካዊ እንዲሆኑ ባሕላቸውን ማስለወጥ ነበር።
ታላቁ እስክንድር
የግሪክ ወታደሮች የነሐስ ጋሻዎቻቸውን እያጋጩ፣ ረዣዥም የጦር መሣሪያዎቻቸውን ወደ ሰማይ ሰቅለው የሄልስፖንትን ባሕር ሲሻገሩ ታላቁ ሽግግር ያንጊዜ ተጀመረ። ሄልስፖንት (Hellespont) ባሕር፣ ዛሬ ዳርዳኔልስ (Dardanelles) ተብሎ የሚጠራው ጠባብ የባሕር ስርጥ ነው። ይህ ስፍራ በአውሮፓና በእስያ መካከል ያለ ድልድይ በመሆኑ በታሪክ ውስጥ እጅግ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው።
ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግስት ለመውረር ጉዞውን ሲጀምር ሄልስፖንት ባሕር ወደ 160 የሚጠጉ መርከቦችን አሰልፎ ሰራዊቱን ማሻገር ነው። በዚያን ወቅት መርከቦቹ ባሕሩን ሲሞሉት፣ የአውሮፓና የእስያ ምድር የተገናኙ ይመስል ነበር።
ታሪክ እንደመዘገበው፣ ታላቁ እስክንድር መርከቧ ወደ እስያ ምድር ከመጠጋቷ በፊት፣ ከመርከቧ ላይ ሆኖ ጦሩን ወደ እስያ አፈር ወረወረ። ጦሩ መሬቱ ላይ ተሰክቶ ሲቆም፣ "እስያ በአማልክት የተሰጠችኝ የጦር ምርኮዬ ናት!" ብሎ አወጀ። ይህ ድርጊት ለወታደሮቹ ዓለምን ለመቆጣጠር ትልቅ ወታደራዊ ወኔ ሰጥቷቸዋል። ከዚያ ጦሩን
አነቃቅቶ በከፍተኛ ጀብዱ
ወደ እስያ ዘመተ።
ፋርሳውያን ታላቁ እስክንድር መሻገሩን
ሲሰሙ፣ በወንዙ ማዶ ባለው ዳገታማ ቦታ ላይ መሸጉ። የፋርስ ጦር መሪዎች "ታላቁ እስክንድር
ወንዙን ሲሻገር ዳገቱን እስኪወጣ ድረስ ጠብቀን ከላይ ሆነን እንጨርሰዋለን" ብለው አሰቡ። የፋርስ ፈረሰኞች በወንዙ ዳርቻ ላይ እንደ ግድግዳ ተደርድረው ይጠብቁት ነበር።
አንጋፋው የጦር አዛዥ ፓርሜንዮ ታላቁ እስክንድር እንዲህ አለው፦ "ንጉሥ ሆይ፣ ወንዙ ጥልቅ ነው፣ ዳርቻውም ጭቃማና ዳገት ነው፤ ዛሬን አርፈን ነገ ማለዳ ድንገት እናጥቃቸው።" ብሎ አስተያየት ሰጠ ። ታላቁ እስክንድር እንዲህ ብሎ መለሰ፦ "የሄልስፖንትን ባሕር የተሻገረ ሰራዊት ይህን ትንሽ ወንዝ መሻገር ካቃተው አሳፋሪ ነው።" በማለት መልሶለታል። ታላቁ እስክንድር ፋርሳውያን
ተደራጅተው እንዲቆዩ ጊዜ መስጠት አልፈለገም፤ ወዲያውኑ ጥቃት በመጀመር ጦርነቱ ተፋጸመ። ይህ ውጊያ ታላቁ እስክንድር "ሞት የማይፈራ ጀግና" ያስባለበትና የፋርስን ጦር ክፉኛ ያስደነገጠበት ክስተት ሆነ።
ታላቁ እስክንድር የሚያብረቀርቅ የነሐስ ጥሩሩንና በሁለት በኩል ነጭ ላባ ያለው የራስ ቁር (Helmet) ለብሶ በጦርነቱ መካከል ጎልቶ እንዲታይና ወታደሮቹ እንዲከተሉት አደረገ። በፈረሱ ላይ ሆኖ ወደ ወንዙ ዘለለና ተሻገረ ሰራዊቱም ተከትለውት ገቡ ። ከወንዙ በላይ የፋርስ ጦር ቀስትና ጦር ያዘንብባቸው ነበር። ወንዙን ተሻግረው ዳገቱን ሲወጡ፣ በእጅ በእጅ የሚደረግ ውጊያ ተጀመረ። እስክንድር በፋርስ
መኮንኖች ተከበበ። አንድ ፋርስ መስፍን የራስ ቁሩን በሰይፍ ሰነጠቀው። ሌላኛው ፋርሳዊ ደግሞ ከጀርባው ሊቀላው ሰይፉን ሲያነሳ፣
የቅርብ ጓደኛው የፋርሳዊውን እጅ ቆርጦ እስክንድር ከሞት አተረፈው።
በመጨረሻም የግሪክ ወታደሮች የፋርስን መስመር ሰብረው ወጡ። የፋርስ ፈረሰኞች ተበታተኑ። እስክንድር በዚህ ውጊያ ራሱን ለዓለም አስተዋወቀ። የፋርስ መንግስት "ይህ ልጅ ተራ ወራሪ ሳይሆን፣ ሊያጠፋን የመጣ መቅሰፍት ነው" ብሎ እንዲያምን አደረገ። ይህ ድል ለእስክንድር ወደ ትንሿ እስያ (የዛሬዋ ቱርክ) ከተሞች በቀላሉ ለግባት በሩን ከፈተለት።
የኢሱስ (Issus) ሜዳ ውጊያ፣ የፋርስ መንግሥት ውድቀት
በ333 ዓ.ዓ. የተካሄደው የኢሱስ (Issus) ውጊያ፣ የፋርስ መንግሥት ውድቀት የማይቀር መሆኑን ለዓለም ያሳየበት የታሪክ ምዕራፍ ነው። የእስክንድርን መስፋፋት የሰማው የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ ራሱን ለጦርነት ዝግጁ አድርጎ መውጣቱ ተሰማ። ታላቁ እስክንድር ወደ ደቡብ እየገሰገሰ ሳለ፣ ንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ግዙፍ ሠራዊቱን አስከትሎ ከፋርስ ተነቃነቀ። ዳርዮስ "ይህን ወጣት እዚሁ መጨረስ አለብኝ" ብሎ ስለቆረጠ፣ የግሪኩን ጦር ከኋላው ዞሮ በመምጣት መንገድ ዘጋበት። ሁለቱ ጦሮች በባሕርና በተራራ መካከል ባለው ጠባብ የኢሱስ ሜዳ ላይ ተገናኙ።
ዳርዮስ ቢያንስ 600,000 የሚጠጋ (አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት) ሠራዊት ነበረው። እስክንድር ግን የነበረው ወደ 40,000 አካባቢ ብቻ ነበር። ነገር ግን ቦታው ጠባብ በመሆኑ፣ ዳርዮስ ግዙፉን ሠራዊቱን በሙሉ ሊጠቀምበት አልቻለም። ወታደሮቹ አንዱ በሌላው ላይ እየተረጋገጡ መጨናነቅ ጀመሩ።
ታላቁ እስክንድር የጠላቱን
ድክመት አየ። የፋርስ ጦር መሃል ላይ ንጉሥ ዳርዮስ በከፍተኛ ክብር በሰረገላው ላይ ሆኖ ይታያል። በጥንት ዘመን፣ ሰራዊቱ የሚዋጋው ለንጉሡ ካለው ታማኝነትና ንጉሡ በሜዳው ላይ ካለው መገኘት የተነሳ ነበር። "ንጉሡ ከወደቀ ወይም ከሸሸ፣ ሰራዊቱ ተስፋ ይቆርጣል፣ ትዕዛዝ የሚሰጠው ይጠፋል፣ ከዚያም መላው አካል (ሰራዊቱ) ይበታተናል" ።
በኢሱስ ጦርነት ወቅት፣ የፋርስ ሰራዊት ከግሪኩ ሰራዊት በአሥር እጥፍ ይበልጥ ነበር። እስክንድር ግን ጊዜውን በጎንና በጎን ባለው ውጊያ አላጠፋም። በጦርነቱ መካከል ቀዳዳ አግኝቶ በቀጥታ ፈረሱን ወደ ዳርዮስ ሰረገላ አቀና። ዳርዮስ ታላቁ እስክንድር ሊገድለው
ሲመጣ ሲያይ፣ በፍርሃት ሸሸ። ልክ ታላቁ እስክንድር እንዳቀደው፣ ንጉሡ መሸሹን ያየው የፋርስ ሰራዊት ወዲያውኑ የውጊያ መንፈሱ ሞተና መሸሽ ጀመረ። "ራሱ" (ዳርዮስ) ሲሸሽ "አካሉ" (ሰራዊቱ) ወደቀ።
ኢራቅ ግዛት በጋውጋሜላ ሜዳ
በ331 ዓ.ዓ. በዛሬው ኢራቅ ግዛት በጋውጋሜላ ሜዳ ላይ፣ የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ግዙፍ ሠራዊቱን አሰልፏል። የፋርስ ሠራዊት ብዛት ልክ እንደ ባሕር አሸዋ ነበር፤ ከርቀት ሲታዩ ሜዳውን የሸፈኑ አንበጣዎች ይመስላሉ። በሌላ በኩል፣ እስክንድር ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ግን በቆረጡ ወታደሮቹ ታጅቦ ቆሟል። ሌሊቱን ሙሉ የፋርስ ወታደሮች ድንገተኛ ጥቃት በመፍራት ሳይተኙ ሲጠበቁ አደሩ፤ እስክንድር ግን ወታደሮቹን አሳርፎ እርሱም በሰላም ተኝቶ አደረ።
ጎህ ሲቀድ፣ የግሪኩ ጦር እንደ ቀስት ተወረወረ። እስክንድር የፋርስን ጦር ወደ ጎን እንዲሳቡ በማድረግ መሃል ላይ ቀዳዳ ፈጠረ። ያንን ቀዳዳ ሲያይ፣ እስክንድር ከፈረሰኞቹ ጋር በመሆን ልክ እንደ ሹል ጦር ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ በቀጥታ አመራ።
በፋርስ ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ሽብር ተፈጠረ። የነሐስ ጋሻዎቻቸው በፀሐይ ብርሃን ስር እየተንፀባረቁ ጠላትን ያሳውሩ ነበር። ዳርዮስ፣ እስክንድር በአቅራቢያው ሲመለከትና የጦር ሰረገላዎቹ ሲሰባበሩ ባየ ጊዜ፣ በፍርሃት ተውጦ ፈረሱን አዙሮ ሸሸ። ዳርዮስ ከሸሸ በኋላ፣ የፋርስ ግርማ ሞገስ አበቃለት።
በዚህ ጦርነት ዳርዮስ የራሱን ሕይወት ለማዳን ሲል እጅግ ውድ የሆኑትን ነገሮች ጥሎ ሄደ አንዱ የንጉሣዊ ድንኳኑን ነበር እስክንድር ወደ ድንኳኑ ሲገባ በወርቅና በብር የተለበጡ ዕቃዎችን፣ ውድ ሽቶዎችንና ምግቦችን አገኘ። "ንጉሥ መሆን ማለት ይህ ነው ለካ!" ብሎ በግርምት ተናገረ ይባላል።
የዳርዮስ እናት፣ ሚስቱና ሁለት ሴት ልጆቹ ተማረኩ። እስክንድር ግን እንደ ሌሎቹ ድል አድራጊዎች አልበደላቸውም። ይልቁንም፣ "እኔ የምዋጋው ከዳርዮስ ጋር እንጂ ከእናንተ ጋር አይደለም" በማለት ልክ እንደ ንጉሥ ቤተሰብ በታላቅ ክብር እንዲጠበቁ አዘዘ።
እስክንድር ዳርዮስን በሕይወት ለመያዝ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ዳርዮስ ወደ ባክጥሪያ (የዛሬዋ አፍጋኒስታን አካባቢ) እየሸሸ ሳለ፣ በገዛ መኮንኖቹ ተከዳና ተወጋ። እስክንድር ዳርዮስ ወዳለበት ሲደርስ ንጉሡ ሕይወቱ አልፎ ነበር። በጠላቱ አሟሟት አዝኖ የራሱን ካባ ደረበለትና ወደ ፐርሴፖሊስ ልኮ በንጉሣዊ ሥነ-ሥርዓት እንዲቀበር አደረገ።
እስክንድር ወደ ታላቂቱ ባቢሎን ሲቃረብ፣ ከተማዋ በጦርነት ሳይሆን በዝማሬና በክብር ተቀበለችው። መንገዶቹ ሁሉ በአበቦች ተነጠፉ። የብር መንግስት የተባለችው ፋርስ አበቃላት፤ የነሐስ መንግስት የተባለችው ግሪክ ደግሞ ዓለምን ተቆጣጠረች።
የሱሳ (Susa) ከተማ
ታላቁ እስክንድር በጋውጋሜላ ጦርነት ዳርዮስን ድል ካደረገ በኋላ፣ ቀጥታ ፊቱን ያዞረው ሱሳን ከተማ ነበር። የሱሳ (Susa) ከተማ በጥንቱ ዓለም የሥልጣኔ፣ የሀብትና የውበት ተምሳሌት ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ሱሳ ግንብ" ተብላ የምትጠራው ይህች ከተማ፣ የፋርስ ነገሥታት የክረምት መኖሪያና የንጉሣዊ ግርማ ሞገሳቸው ማሳያ ነበረች።
ሱሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙባት መድረክ ናት፦ የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው በዚሁ በሱሳ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነው። ንጉሥ አርጤክስስ ያንን ታላቅ የ180 ቀናት ግብዣ ያደረገው፣ አስቴር ንግሥት የሆነችውና አይሁዳውያን ከጥፋት የዳኑት እዚህ ከተማ ውስጥ ነበር።
ነቢዩ ዳንኤል በባቢሎንና በፋርስ መንግሥት ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሰው ሲሆን፣ ስለ መንግሥታት መተካካት (ስለ ግሪክ መነሳት ጭምር) የታዩት ታላላቅ ራእዮች የታዩት በሱሳ ግንብ አጠገብ ነበር (ዳንኤል 8:2)።
ነህምያ ለፋርሱ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊ ሆኖ ያገለግል የነበረውና የኢየሩሳሌም ቅጥር እንዲታደስ ትእዛዝ የተቀበለው በሱሳ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር (ነህምያ 1:1)።
እስክንድር ወደ ከተማዋ ሲገባ ያየው ነገር እጅግ የሚያስደምም ነበር። የታሪክ ጸሐፍት የከተማዋን ግርማ እንዲህ ይገልጹታል "አፓዳና" (ታላቁ አዳራሽ)፦ የሱሳ ቤተ መንግሥት እጅግ ረዣዥም በሆኑና በጥበብ በተጠረቡ የድንጋይ አምዶች የተደገፈ ነበር። የቤተ መንግሥቱ ግድግዳዎች በሰማያዊ፣ በቢጫና በነጭ ቀለማት በሚያብረቀርቁ ጡቦች የተሰሩ ነበሩ።
በአስቴር መጽሐፍ ላይ እንደሚገለጸው፣ ቤተ መንግሥቱ በነጭ፣ በሰማያዊና በሐምራዊ በፍታ የተሰሩ መጋረጃዎች፣ በብር ቀለበቶችና በዕብነ በረድ አምዶች ላይ የተንጠለጠሉ ነበሩ። መሬቱም በበዝበዛ፣ በዕብነ በረድና በሉል ድንጋዮች የተነጠፈ ነበር።
እስክንድር በሱሳ ያገኘው ወርቅና ብር በሺዎች የሚቆጠሩ ግመሎችና በቅሎዎች እንኳ ሊጭኑት የማይችሉት ነበር። 50,000 ታላንት (በዛሬው ስሌት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር) ወርቅ በግምጃ ቤቷ ውስጥ ተከምሮ ተገኝቷል።
የፋርስ ነገሥታት ሱሳን "የዓለም ማእከል" አድርገው ይቆጥሯት ነበር። በከተማዋ ውስጥ የሚፈሰው የኮአስፔስ ወንዝ ውሃ እጅግ ንጹህ ከመሆኑ የተነሳ፣ ንጉሡ ከዚህ ወንዝ ውጭ ሌላ ውሃ አይጠጣም ነበር። ንጉሡ ወደ የትኛውም አገር ቢሄድ፣ የዚህ ወንዝ ውሃ በብር ዕቃዎች ተቀድቶ በበቅሎ ተጭኖ ይከተለው ነበር።
እስክንድርም ወደ ሱሳ ሲቃረብ፣ ከተማዋ እንደ ባቢሎን ሁሉ በሰላም እጇን ሰጠች። የከተማዋ ገዥ የነበረው አቡሊተስ፣ የእስክንድርም ኃይል መቋቋም እንደማይችል ስለተረዳ፣ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን እጅግ ግዙፍ ሀብት ይዞ ወጥቶ ተቀበለው። እስክንድርም በድል አድራጊነት ወደ ቅጥሯ ገባ።እስክንድር ይህን ሁሉ ሀብትና ውበት ሲቆጣጠር፣ ያ "የብር ደረት" የተባለው የፋርስ መንግሥት
ክብር ወደ "ነሐሱ መንግሥት" (ግሪክ) መዛወሩን በተግባር አረጋገጠ።
የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት፦ እስክንድር በሱሳ ያደረገው አንድ ትልቅና የታወቀ ክስተት አለ። የግሪክንና የፋርስን ባህል ለማዋሃድ በማሰብ፣ 80 የሚሆኑ የግሪክ መኮንኖቹን የፋርስ መኳንንት ሴት ልጆችን እንዲያገቡ አደረገ። ራሱ እስክንድርም የዳርዮስን ልጅ ስታቲራን (Stateira)
በዚሁ ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ አገባ። ይህ ድርጊት "የነሐሱ መንግስት" (ግሪክ) የፋርስን ግዛት በጉልበት ብቻ ሳይሆን በደምም ለመውረስ ያደረገው ሙከራ ነበር።
የፐርሴፖሊስ
(Persepolis) ቤተ መንግስት
እስክንድርም ሱሳን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ጉዞው አላበቃም፤ ይበልጥ ወደ ምስራቅ፣ ወደ ፋርስ ልብ ወደሆነችውና ወደ ሚቃጠለው የፐርሴፖሊስ
(Persepolis) ቤተ መንግስት አመራ።
ፐርሴፖሊስ የፋርስ ነገሥታት የክብርና የግርማ ሞገስ መገለጫ ነበረች። እስክንድርም ከተማዋን እንደተቆጣጠረ፣ በታሪክ ውስጥ እስካሁን አከራካሪ የሆነው ክስተት ተፈጠረ። ከተማዋ በእሳት ጋየች። ለምን ነደደች? አንዳንዶች እስክንድርም ይህን ያደረገው ከ150 ዓመታት በፊት ፋርሳውያን አቴንስን ስላቃጠሉባት "የበቀል እርምጃ ነው" ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በአንድ ትልቅ ግብዣ ላይ ሰክረው በነበሩበት ወቅት በስህተት የተለኮሰ እሳት ነው ይላሉ። ያ ሁሉ ጥበብ የተሞላበት ቤተ መንግስት ወደ አመድነት ተቀየረ። ይህ ክስተት የፋርስ ግዛትን ታሪክ በይፋ የመዝጋት ምልክት ሆኖ ቀረ።
2. እስክንድር በኢየሩሳሌም፦
ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ዮሴፍ ወልደኮርዮን እንደዘገበው፣ እስክንድር ፋርስን ድል እያደረገ ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ አይሁዳውያን በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ነበሩ። ሊቀ ካህናቱ ኢያዱዋ ሕዝቡን ሰብስቦ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠየቀ። በሕልሙም "ከተማዋን አስውባችሁ በነጭ ልብስ ተቀበሉት" የሚል መለኮታዊ መልእክት ደረሰው።
እስክንድር ከተማዋ ሲደርስ፣ ሊቀ ካህናቱን በክብርና በነጭ ልብስ አይቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወርዶ ለሊቀ ካህኑ ሰገደለት። የጦር አዛዦቹ "ይህ ዓለም የሰገደለት ንጉሥ እንዴት ለካህን ይሰግዳል?" ብለው ሲገረሙ፣ እስክንድር እንዲህ አለ፦ "እኔ የሰገድኩት ለካህኑ ሳይሆን ለለበሰው ልብስና ለሚቀድሰው አምላክ ነው፤ ይህንኑ ሰውዬ በመቅዶንያ ሳለሁ በሕልሜ አይቼዋለሁ፣ በፋርስ ላይ ድል እንደማገኝም አብስሮኝ ነበር።" በማለት ተናገረ።
ከዚያም ታላቁ እስክንድር ከሊቀ ካህኑጋር በመሆን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መስዋዕት አቀረቡ። ካህናቱም የዳንኤልን መጽሐፍ አውጥተው "የግሪክ ንጉሥ የፋርስን መንግሥት እንደሚያጠፋ እንዲሁም ዓለምን
እንዲቆጣጠር" የሚናገረውን ትንቢት (ዳን. 8:5-21) አነበቡለት። እስክንድር ትንቢቱ ስለ እሱ መሆኑን ሲረዳ እጅግ ተደስቶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአይሁድ ክብር እና ልዩ ነፃነት ሰጠ።
3. "ታላቁ ቀንድ" ሲሰበር፦ ክፍል አምስት ይቀጥላል

%20%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9B.jpg)

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ