ማክሰኞ 2 ሴፕቴምበር 2025

እንቅልፍ ከበደባቸው

 

እንቅልፍ ከበደባቸው፤  የሉቃስ ወንጌል 932 

 ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።  እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።  ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።  ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም። ሉቃ 9÷28-37 

 የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበ ዕለት ነው፡፡ 

 ለደብረ ታቦር ኩነት እንደ ዐበይት ምክንያት አድርገን የምንወስደው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከተሉትን ደቀመዛሙርቱን በቄሳርያ አካባቢ ሲደርሱ የጠየቃቸው ጥያቄ ነው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ እንዲህ ጽፎታል፡፡  

 ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።  እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። 

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። ብሎታል፡፡ (ማቴ 1613-20) 

 ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የመሰከረውን ምስክርነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ይሰሙ ዘንድ፣ ከነቢያት (ሙሴና ኤልያስ) አንደበት ይረዱ ዘንድ፣ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን  ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ይዞቸው ወጣ፡፡ (ማቴ 171-10) 

 ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ማርቆስ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር ቅዱስ ጰጥሮስ የተናገረበትን ቀን እና  የደብረ ታቦር ተራራ ድርጊት የተፈጸመበትን ቀን ቆጥረው ስድስት ቀን በኃላ ብለው ሲጽፉ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ በፊልጶስ ቂሣርያ ድርጊቱ ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ደብረ ታቦር መገለጥ ያሉትን ቀኖች በሙሉ በመቁጠር ስምንት እንዳደረሰው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡ 

 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙን ሐዋርያት በተራራው ሥር ትቶ ለምን ቅዱስ ጴጥሮስን ቅዱስ ያዕቆብን እና ቅዱስ ዮሐንስን ለምን መርጦ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ላይ አውጥቶ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይመልስልናል፡፡ 

   ‹‹ቅዱስ ጴጥሮስ ፍቅሩን በተደጋጋሚ በመናገር ገልጿል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም  ለመድኃኒታችን የተለየ ፍቅር  እንዳለው በወንጌል ሳይቀር ጌታን የሚወደው ተብሎ ተነግሮለታል ፡፡ቅዱስ ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር በመሆን በለመነው ልመና አንተ የምትጠጣውን ጽዋ እንጠጣለን እስከማለት የጠየቀ በመሆኑ  በማቴ 2022  በዚህ ምክንያት መርጦቸዋል ›› በሏል፡፡ 

 በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር አብ ለመጀመሪያ ጊዜ መድኃኒታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ "እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ። " ማቴ 317  በደብረታቦር ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ "ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።"ሉቃ 935  

 የደብረ ታቦር ተራራን ወጥተው የተገኙት ሦስቱ ደቀመዛሙርት ምስጢረ መለኮት ተካፋይ ሲሆኑ ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።  

 ታላቁን ምሥጢረ ሥጋዌ እግዚአብሔር ዓለምን የሚያድንበትን ጥበብ በሚነገርበት በብርሃን በተከበበ ተራራ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው በተለይም ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎቹን ሐዋርያት ዘንግቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በደብረታቦር ተራራ ላይ ዳስ ሠርቶ /ድንኳን ጥሎ / መኖር ይሻለናል ብሎ ጠየቀው ፡፡ 

 ወንጌላዊያኑ ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ደካማ ጎን ገልጸውታል ቅዱስ ማርቆስ "እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር።" ሲል  (ማርቆስ 96 )  ቅዱስ ሉቃሰ  ደግሞ  "የሚለውንም አያውቅም ነበር።"   ሉቃ 933 በማለት ነቅፈውታል፡፡ 

 ቅዱዱ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ስለ ከበደባቸው ድምጹን መስማት አልቻሉም። ጌታችን የከበደባቸውን እንቅልፍ በችርነቱ አርቆላቸው ሙሴን እና ኤልያስን እንዲሁ መለኮታዊ ክብሩን ተመለከቱ።  

ከከበደበት እንቅልፍ በደንብ ያልነቃው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች ከእርሱም ሲለዩ  ምድራዊ ጥያቄ አቀረበ። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ።      

 ቅዱስ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ የከበደባቸው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ብቻ አልነበር። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉ በጌቴ ሴኒ የሆነውን እንዲህ ጽፎታል በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፦ እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና፦ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ።  ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ቅዱስ  ማርቆስም  ደግሞም "መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።" በማለት ይህንኑ ታሪክ ነግሮናል ማር 1440    

በጌቴ ሴማኒም ሆነ ደብረ ታቦር ምስጢረ መለኮት የተገለጠባቸው የብርሃን ድንኳን የሚተከልበት ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝባቸው ድምፁን የምንሰማበት የክብር ቦታ የቤተ ክርስቲያን  ምሳሌዎች ናቸው። 

በዚህ ስፍራ ተገኝተው ከመንፈሳዊ ይልቅ ሥጋዊ ከሰማያዊ ይልቅ ምድራዊ ሀሳብ የሚቀባጥሩ ሰዎች እንቅልፍ የከበደባቸው ሰነፎች ናቸው።በሠርግ ቤት ተገኝተው ሙሽራው አይመጣም ብለው እንደተኙት ሰነፍችን ይመስላል  "ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። " የማቴዎስ ወንጌል 255  እንቅልፍ የከብድባቸው ሰዎች ሰነፎች ናቸው ጠቢብ ሰሎሞንም  "አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?  ይላል ምሳ 69  ቅዱስ ጳውሎስም "ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና።"ወደ ሮሜ ሰዎች 1311  ይለናል። 

 በቅዱሱ ተራራ ከፍ ብለን ከተገኘን ከእንቅልፍ ነቅተን ለጽድቅ ለመንግስተ ሰማያት ለሚያበቃ ሥራ እንትጋ።      

 

            ይቆየን 

             ያዕቆብ ሰንደቁ 

     ነሐሴ 13 ቀን 2017 /

              አዲስ አበባ።

 

ረቡዕ 28 ፌብሩዋሪ 2024

ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቷል፡፡

 

ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 4 1

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ከዓመታት በፊት በሚሊንየም አዳራሽ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ትምህርቱን ስትሰሙት ለዛሬ ጊዜ የቤተክርስቲያን ፈተና ሁሉ ምላሽ የሚሰጥ ፤የሐዲስ ኪዳን ጥላ በሆነው በቡሉይ ኪዳን ዘመን በተፈጸመ ታሪክ ውስጥ፤ የአሁን ዘመን የቤተክርስቲያ ፈተና የሚያሳይ፤  ዲያቢሎስ ልጆቿን ባለዕዳ አድርጎ ሊወስድ ቢሞክርም እንደማይችል፤ ጊዜው ሲያልፍ ፈተናውም እንደሚያልፍ፤ ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃቤት ሆና እንደምትኖር የሚያስረዳ የሚያጽናና ትምህርት ነው፡፡

ከታች ያለውን ማስፈንጠሪያ ተጭነው ይህን ስብከት ያዳምጡ

https://youtu.be/ahg57DS5UP4

3፡28᎓-  መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው እርሱም ሄደሽ ዘይትሽን ሽጪ ለባለዕዳውም ክፈይ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተገመገቡ አለ

5፡56᎓-  መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ የእሥራኤል መንግስት የሚለው የአሥሩን ነገድ መንግስት ነው፡፡

6፡45᎓- በብሉይ ኪዳን ጊዜ መቅደሱ አንድ ብቻ ነው እርሱም ኢየሩሳሌም ነው በየአውራጃው በየወረዳው የነበረው ሙክራብ ይባላል::

8፡36᎓- አክአብ በጣም ጨካኝ ሚስቱ ኤልዛቤል በትውልዷ ሶርያዊት  ስለነበረች  እግዚአብሔርን ስለማምለክ ከፍተኛ ጥላቻ ነበራት::

10፡02᎓- በዚያን ዘመን ነቢዩ ኤልያስ ነበረ የእግዚአብሔር አምላክነት እንዲታወቅ ሰማይን እና ምድርን ገዘተ::

10፡42᎓- አቡዲዩ የአክአብ ባለሥልጣን ሆኖ በአክአብ ቤተመንግስት እየኖረ መቶ ነቢይነት ትምህርት የሚማሩ ደቀመዛሙርትን ሃምሳውን በአንድ ዋሻ  ሃምሳውን በአንድ ዋሻ  ብቻውን ደብቆ  ማስተማር መመገብ ጀመረ::

17፡36᎓- ባሌ ባርያህ ሞቷል እግዚአብሔርን ይፈራ እንደነበረ አንተ ታውቃለህ::

26፡26᎓- ወደ ኤልሳ የሄደቸው ሴት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት ኤልሳ ደግሞ የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው ልጆቿ ደግሞ የምእመናን ምሳሌዎች ናቸው ባለ ዕዳ የተባለው ደግሞ ዲያብሎስ ነው

28፡23᎓- ቤተክርስቲያን ልጆቿን ለመሥጠት ፈቃደኛ አይደለችም ምንም ያህል ባለእዳዎች ብንሆንም ምንም ያህል ኃጢአተኞች ብንሆን::