ረቡዕ 15 ማርች 2023

ወግ “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.19፥12

 

 “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.1912

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ትምህርት በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለማየት ገና ልዑል አልጋወራሽ ሆነው እያለ በገንዘባቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን አሠርተው ሚያዚያ 17 ቀን 1917 ዓ/ም አስመርቀዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን ይኖሩበት የነበረውን ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስትን ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን በመስጠት እና  የግል ገንዘባቸውን ማቋቋሚያ እንዲሆን በማርክት ሚያዚያ 27 ቀን 1952 ዓ/ም ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት፤ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን ፤ከቤተ መንግስት ቀለብ እየተሰፈረ በልዩ እንክብካቤ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ጎበዝ ተማሪዎች ይማሩበታል፡፡ ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ከአውሮፓ እና አሜሪካን የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ፡፡ አስተማሪዎቹ የቀለም ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ የካቶሊክ ዕምነትን ለማስፋፋት የሚሲኦናዊ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተማሪዎች ባደረጉት ክትትል ደረሱባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ይህ መረጃ ሲደረሳቸው የኢየሱሳዊያኑን እንቅስቃሴ የሚያጠና ሕቡ ማኅበር በማቋቋም ክትትል ጀመሩ፡፡ ማኅበሩ ጉዳዩን በማጥናት ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ፤ ለጠቅላይ ቤተ-ክህነት አሳውቀው፤ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ሊቃውንትን ሰብስበው ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተጋረጠውን ፈተና በማስረዳት ጉባኤውን በዕንባ አራጩት፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት ተመሳሳይ ውይይት እንዲደረግ ጉባኤው ወስኖ ተበተነ፡፡

ከጉባኤው በኋላ ወዲያውኑ የማኅበሩ ምሥጢር እየሾለከ በመውጣቱ ዋና ዋናዎቹ የማኅበሩ መሪዎች ታሰሩ፡፡ ተማሪዎች ከተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ታገዱ፤ ገሚሶቹም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ፡፡ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ማስፈራሪያና ቅጣት ለሃይማኖታቸው ጠበቃ ከመሆን ሳያግዳቸው፤ በተዘዋወሩበት ትምህርት ቤትም ቅርንጫፍ ማኅበር በማቋቋም ማህበሩን ከበፊቱ የበለጠ አጠናከሩ፡፡

በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የቀሩት ተማሪዎች ግን ስለብዙ ምክንያት የተማሪዎች አድማ እንዲቀሰቀስ አደረጉ፡፡ በተማሪዎቹም አመጽ ትምህርት ተቋረጠ ንብረት ወደመ፡፡ ብጥብጡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ከቤተ መንግስት አባ ሐና ጂማና ተልከው ተማሪዎቹን አነጋገሩ፤አድማው ግን ሊበርድ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም አድማው ሊረግብ የቻለው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በመገኘት ተግሳጽ እና ምክር በመስጠታቸው ነበር፡፡

ንጉሡ በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ራሳቸውን የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ከራሳቸው ገንዘብ እና ንብረት ወጪ በማውጣት ለሌት ተቀን ይጥሩ ነበር፡፡ ይህን ምኞታቸውን እና ተስፋቸውን የሚያሰናክል ተግባር ተማሪዎች በመፈጸማቸው አዘኑ እጅግም ተቆጡ፡፡ ተማሪዎቹም በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው የአድማቸውን ምክንያት ማስረዳት ጀመሩ፡፡ የተማሪዎቹ የተወረጠ ተወካይ በንጉሡ ፊት የአድማውን ምክንያት በዝርዝር ያስረዳ ጀመር፡፡ ንጉሡ በሆነው ነገር ተበሳጭተው የሚናገረውን ተማሪ በጥፊ መቱት፡፡ የንጉሡን ጥፊ የቀመሰው ተማሪ ሌላውን ያልተመታው ሁለተኛ ጉንጩን አመቻችቶ ሰጣቸው፡፡ ንጉሡም በሁኔታው ተደናግጠው በድጋሚ ለመማታት የሰነዘሩት እጃቸውን ለመሰብሰብ ተገደዱ፡፡

ተማሪው ከሁሉም ነገር በላይ ሃይማኖቴ ይበልጣል በማለቱ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ “እኔ ግን እላችኋለው ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩግን ቀኝ ጉጭህን በጥፊ ለሚመታ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙሩለት፡፡”ማቴ.5፥39 “ጉንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ሥጠው፤መጎናጸፊያውንም ለሚወስድብህ እጀጠባብህን ደግሞ አትከልክለው” ሉቃ.6፥29 የሚለውን የወንጌል ቃል በንጉሡ ፊት ፈጸመው፡፡

በዚያን ወቅት የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ለማንቃት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች መፈጠር እና መስፋፋት፣ ምስካዬ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር እንዲመሰረቱ ምክንያት መሆኑን ጀጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ ሕይወቴ በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈውልናል፡፡

ወዳጄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተማሪው በፈጸመው መንፈሳዊ ተግባር ደንግጠው ትምህርት ወስደው እጃቸውን በድጋሚ ሊፈጽሙት ከነበረው የኃይል ተግባር እንዲቆጠብ አድርገዋል፡፡ ሁለተኛውን ጉንጩን ሰጥቶኛል ምን ያመጣል ብለው ጥፊያቸውን ሳይደግሙት ፤ በዙሪያቸው ባሉት  የሃይማኖት አባቶች መኮንንቱ እና መሳፍንቱ ፊት የንጉሡን ክብር የሚቀንስ ስህት ከመሥራት ተቆጥበዋል፡፡ የዚያን ሰሞን ይህ ክስተት በተማሪዎቹ እና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ሲወራ ሰነበተ፤ ንጉሡም በጥቁር መዝገብ ጥቁር ታሪክ ሳይጽፍ በጣም ካበሳጫቸው ተማሪ ትምህርት ወሰዱ፡፡

በየትኛውም ከፍታ ቦታ ብንሆን፣ ሥልጣን እና ጉልበት ቢኖረንም ፣በአጠገባችን በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ትምህርት የምንወስድ ከሆነ ፤ ከዳግማዊ ስህተት እንጠበቃለን፡፡ ከ እኛ ዙፋን በታች የሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ እኛን ከስህተት የመጠበቅ አቅም የማስተማርም ዕድል አላቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሜት በስህተት እጃችንን ሰንዝረን ከሆነ ጥፋታችንን እንዳንደግመው አስተማሪ ካገኘን ፣ካደመጥንም ከ ከባዱ ሁለተኛው ሥህተት እንተርፋለን፡፡ ታስቦሙ ይሁን በድንገት ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ቶሎ ትምህርት መውሰድ እና ራስን ማስተካከል ብልህነት ነው፡፡

በዓለማችን ላይ እንደምንመለከተው ብዙ ነገሥታት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ ብዙ አስተማሪ ክስተቶች በተደጋጋሚ ቢፈጠሩም፤ልባቸው ደንድኖ ትምህርት መውሰድ ሲያቅታቸው እንመለከታለን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ የጻፈው ቃልም ይህን ያሳያል “ ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፍ ነገር አለ፤ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፡፡” መክብብ.10፥5  ወዳጄ ስህተቱን አውቆ የሚያርም ሰው አስተዋይ ነው!

ያዕቆብ ሰንደቁ  

መጋቢት 2 ቀን  2015ዓ/ም

አዲስ አበባ

ቴሌግራም https://t.me/MaedotYakobSendekupage

የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርስ  ፔጁን Like Share Comment ያድርጉ::

ዓርብ 10 ማርች 2023

ወግ

 

 “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ”

በቅርቡ ናጄሪያ ውስጥ አንድ የሃይማኖት ተቋም ለአምልኮ ሥፍራ ግንባታ እያካሄደ እያለ የተሾመው አገልጋይ ሲሚንቶውን፣ ብረቱን እየወሰደ ገንዘቡን እመዘበረ የራሱን ቤት ይሠራል፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች አዝነው ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ያደርጉታል፡፡

 ይህን መጥፎ ምግባር አምርሮ ይጠላ የነበረ ሌላ አገልጋይ ይሾማል፡፡ የተሾመው አዲስ አገልጋይ የአምልኮ ቦታውን ግንባታ መጎተቱን አይቶ ሥራውን ያፋጥናል፤ ሙስናንም ይጠየፋል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ አገልጋዩም ሥራውን ከተቀበለ ወራት አለፈ፡፡ የአምልኮ ቦታው ግንባታ ግን ጭራሹኑ ቆመ፡፡

አዲሱ ተሾሚ አገልጋይ ለግንባታ በተመደበው በጀት በውድ ዋጋ መሀል ከተማ መሬት ገዝቶ ባለ አራት ፎቅ ቤት ለራሱ መሥራት ጀመረ፡፡ በፍጥነት ብቅል ያለው ሕንጻ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ አገልጋዩም ሲሚንቶውን፣ ብረቱንም ቁሳቁሱንም እየወሰደ የራሱን ቤት መገንባቱን አፋጠነው፡፡

ሁኔታውን ያዩት አማኞች “ገንዘባችን ተዘረፈ የባሰው መጣብን” ብለው ጮሁ፡፡ ከዚያም ስብሰባ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ አገልጋዩንም ጠርተው “የአምልኮ ቤታችንን ግንባታ አቁመህ የራስህን ቤት ሠራህ ኃላፊነትህ አስረክቡ” ብለው ጮሁበት፡፡ አገልጋዩም ሰውን ሳያፍር ፈጣሪን ሳይፈራ በኩራት “የመጣው ይመጣል እንጂ በፍጹም አገልግሎቴን አልተውም ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ሕዝቡም አጥብቆ “ገንዘባችን ዘርፈሀል በፍጥነት ልቀቅ ” ብለ ተቆጡ፡፡

አገልጋዩም የነገሩን መጋጋል አይቶ “እባካችሁ በፈጣሪ ስም እለምናችኋለው የጀመርኩትን ፎቅ ቤት እስክጨርስ ድረስ ታገሱኝ፤ ከዚያ አገልግሎቴን አቆማለው” ብሎ አረፈው፡፡ ሕዝቡም “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ሠራህ” ብለው ጉዳዩን ወደ ሕግ ወሰዱት፡፡

“ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት”

በአንድ አፍሪካ ሀገር የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት የሚሠራ የእቃ ግዥ ባለሙያ ነበር፡፡ ግብረሰናይ ድርጅቱ ዋና መሥሪያቤቱን ሲገነባ፤ የግንባታ ቁሳቁስ እንዲገዛ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ግንባታው ቶሎ እንዲጠናቀቅ በጀት ተመደበለት፡፡ ነገርግን ሥራው ሊፋጠን አልቻለም፡፡

የግዥ ባለሙያ የሚከፈለው መጠነኛ ደመወዝ ቢሆንም በሥራው ግን ትጉህ ነው፡፡ መቼም ወሬ አይደበቅም አይደል “ቤት እየሰራ ነው” ተብሎ ይወራል፤ እናም አጅሬው ከመሥሪያቤቱ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የጀመረውን የራሱን ቤት ግንባታ፤ አጣድፎ ይሠራ ጀመር፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በሙሉ መብራት፣ ሶኬት፣ መዝጊያ፣የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች፣ታይልስ፣ ሴራሚክ፣ የግድግዳ ቀለም፣ ምንጣፍ ፣ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ጌጣጌጥ ብቻ የቀረ ነገር የለም “ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት” በሚል መርህ ቤቱን በአጭር ጊዜ አሳምሮ ሠራው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ሰውዬው ይግረማችሁ ብሎ አዲሱን ቤት ለማስመረቅ ተዘጋጀ፡፡

የቤቱን ምርቃት አስመልክቶ ድግስ ደግሶ ሰው አላበዛም በማለት የመሥሪያቤቱ ባልደረቦቹን እና የሥራ ኃላፊዎችን ብቻ የድግሱ ታዳሚ አደረጋቸው፡፡ እንግዶቹን ጠርቶ ሳይፈራ ሳያፍር በሙሉ ልብ የሠራውን አዲስ ቤት እየዞረ አስጎኛቸው፡፡ ሠራተኞቹ እና የሥራ ኃላፊዎቹ በነገሩ ተገርመው ፊታቸው ቀላ፣ናላቸው ተበጠበጠ፡፡

 ከመካከላቸው አንዱ የሥራ ኃላፊ በቁጣ “ለካ የዋናው መሥሪያቤት ግንባታ የዘገየው ቅርንጫፉ እየተሠራ ነው” አለ፡፡ ቀጠለ በቁጣ ንግግር “የተጠራነው ለቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን ምርቃት ነው ማለት ነው ብሎ ጠየቀ ? የግዥ ባለሙያ ትንሽ እፍረት እንኳን ሳይሰማው ፈገግ እያለ ማስጎብኘቱን ቀጠለ፡፡ ሌላው ሠራተኛ ደግሞ “ይህ እኮ የአንተ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ሁሉ ነገሩ የግብረሰናይ ድርጅቱ ነው፤ የግድግዳው ቀለም እንኳን የመስሪያቤታችን ጋር ተመሳሳይ ነው ”አለ በንዴት፡፡ ሌሎቹም ሰዎች “በፍጥነት እና በጥራት ተገንብቶ ያለቀውን ቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን በመመረቃችን ተደስተናል ብለው በምጸት ቀልደው እርፍ አሉ፡፡

የግዥ ባለሙያው በማግስቱ ጠዋት ሥራ ሲገባ የስንብት ደብዳቤ እና የፖሊስ ምርመራ መጥሪያ ተሰጠው፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት የተቀበለውን ደብዳቤ ይዞ ራሱ ወደ ገነባው ቅርንጫፍ መሥሪያቤት  ወደ ሆነው አዲሱ መኖሪያ ቤቱ ሄደ፡፡

ወዳጄ ! እንዚህን ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ቦታቸው የተለያየ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ፤ ሥራቸው ደግሞ አገልጋይ እና ደሞዝተኛ፤ ምን ትላቸዋለህ ?

 

 

 

 

ይህን ሐሳብ እንወያይበት

 

ከመጣብን ፈተና ምን አተረፍን ?

ጥር 14 ቀን ጠዋት የሰማነው ዜና የቤተክርስቲያን ፈተና ነበር፡፡ አይምጣብን አይባል ነገር ለብዙዎች ያልተጠበቀ የቤተክርስቲያን ሕልውና ላይ የተጋረጠ ፈተና፡፡ “ሳይደግስ አይጣልም ” እንዲሉ የነነዌ ሰዎች ጾም በመካከል በመኖሩ የመጣውን ፈተና ለማሽነፍ ማቅ ለብሰን እንባችን እንደ ጎርፍ እያወረድን የሐዘናችን ጥግ ለመግለጽ ጸጉራችንን ተላጭተን፣ ጥቁር ለብሰን “ አቤቱ አድነን ልንጠፋነው” ብለን ጮህን፡፡

ፈተናው ጠንክሮ ብዙዎች በአደባባይ አንድ ሲኖዶስ ብለው መሰከሩ፡፡ ቤተመቅደስ ተደፈረ ሰዎች ሞተው ሰማዕትነትን ተቋናጁ ደማቸውን አፈሰሱ ቆሰሉ፣ ታሰሩ ከቤተ-ክርስቲያን ጎን ቆሙ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም የምስራች ሰማን፤ የሐዘናችን ደመና ተገፎ ፀሐይ ወጣ ችግሩ በሰላም ተፈታ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሳትከፋፈል በአንድነቷ ፀናች፡፡

ይህ ፈተና የመጣው ለምን ይሆን ? አንድም ለቅጣት፣ አንድም ለትምህርት ብቻ ስለ ብዙ ምክንያት ነው ብለን እንለፈው፡፡ በመጣብን ታላቅ ፈተና ምን ትምህርት ወስደን ? ምንስ ትርፍ አግኝተን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነው፡፡

አዎ በቤተክርስቲያን ላይ በመጣው ፈተና ምን አተረፍን ? ምን ፀጋና በረከት አገኘን ?  እንወያይበት፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ፈተና ምን አተረፈች?

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ-ክርስቲያን ምን አተረፈች?

ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቋሚ ሲኖዶስ ምን አተረፉ?

ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ምን አተረፈ?

እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምን አተረፈ?

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምን አተረፉ?

በሀገር ውስጥም በውጭውም ሀገር ያሉ አገልጋዮች ምን አተረፉ?

እያንዳንዱ ክርስቲያንስ በግል መንፈሳዊ ሕይወቱ ምን አትርፎበት ይሆን?

ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያልሆኑ ሰዎችስ ይህን ፈተና አይተው ሰምተው ምን አትርፈውበት ይሆን ?  እንወያይበት!

 

16 ቁጥር ወግ


16 ቁጥር

በያዕቆብ ሰንደቁ

የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ እኛ ክፍል በተመሳሳይ ስም የምንጠራ ሁለት ሴት ተማሪዎች ነበርን፡፡ የሁለታችንም ስም እስከ አያት ድረስ ተመሳሳይ በመሆኑ ማንነታችንን በስማችን ለመለየት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ታዲያ ክፍል ውስጥ ስም በተጠራ ቁጥር ሁለታችንም “አቤት መምህር ” ስለምንል ተማሪዎች ይስቃሉ፡፡

በጣም የምፈራው የክፍል ኃላፊ አስተማሪያችን በነጎድጎድ ድምጹ “ከእንግዲህ ወዲህ እናንተን ለይቶ ለማወቅ እንዲቻል እናንተን ጋር ስደርስ በቁጥር እጠራለሁ” ብሎ መመሪያ ሰጠ፡፡ ከዚያም ስም በተጠራ ቁጥር እኛ አካባቢ ሲደርስ 14 ‚15 ‚16 እያለ ይጠራል፡፡ እየዋል እያደረ ግን ከ እኔ በፊት ያለችው ተማሪ በስሟ ተጠራች፡፡ እኔን ግን በጣም በመረበሽ በመደባደብ ታዋቂ ስለነበርኩኝ በ16 ቁጥር መጠሪያዮ መታወቂያዬ ሆነ፡፡ በዚያው ጸድቆልኝ ከመደበኛ ስሜ ውጪ 16  ቁጥር ቅጽል ስሜ ሆኖ ተማሪው፣ መምህሩ ሁሉ ይጠሩኝ ጀመር፡፡

*   *   *

አዲስ አበባ ሽሮሜዳ እንጦጦ ኪዳነ-ምህረት አቅራቢያ ባለው ሰፈር የካቲት 16 ቀን ተወለድኩኝ፡፡ 16 ቁጥር ቅጽል ስሜም ብቻ ሳይሆን የልደቴም ቀን በመሆኑ እወደዋለሁ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተል የቅጽል ስሜ የሆነው 16 ቁጥር ተከትሎኛ መጣ፡፡ ብዙውን ጌዜ በ አጋጣሚ ይሁን በተአምራት ባይገባኝም የክፍል መጠሪያ ተራ ቁጥሬም 16 ቁጥር ይሆን ነበር፡፡

አሥራ ሁለተኛ ክፍል  ብሔራዊ ፈተና ተፈትኜ ማለፊያ ውጤት ስላላመጣሁ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት አልቻልኩም፡፡ በጊዜው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስላልነበረ የመንግስት ዩኒቨርስቲ መግባት ያልቻለ ተማሪ ቀጣይ የትምህርት ዕድል የለውም፡፡ ያለው አማራጭ አሥራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቆ ሥራ መፈለግ ፣ሥራ ካልቀናው እቤት መቀመጥ አለበለዛም ዕድለኛ ከሆነ ደግሞ በስደት ከሀገር መውጣት ነው፡፡

ትምህርት ካለቀ በኋላ ለ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያሕል ብዙም ሳይታወቀኝ ዕቤት ተቀመጥኩኝ፡፡ ከቆይታ በኋላ በብዙ ምልልስ ከሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት መሥሪያቤት የሥራ አጥነት መታወቂያ አገኘሁ፡፡ እቤት በመቀመጤ በጣም ስለተማረርኩኝ ሥራ መፈለግ አለብኝ ብዬ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት የሥራ አጥ ማስታወቂያ፣ የአሥራሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት፣ የሥራ ማመልከቻ አዘጋጅቼ ሥራ ፍለጋ ከቤት ወጣሁ፡፡

ሥራ ፍለጋው ከቤት እንደጣሁ በዚያው ቀረው ማለት ይቻላል፡፡ ሥራ መፈለግ ቀላል አልነበረም ብዙ ትዕግስት ይጠይቅ ያንገላታልም ነበር፡፡ በአንበሳ የከተማ አውቶብስ ለመሳፈር ከ አንድ ሰዓት በላይ መጠበቅ፤ የሥራ ማስታወቂያ ይለጠፍባቸዋል በሚባል ቦታ ሁሉ መንከራተትን ይጠይቅ ነበር፡፡

 በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስት መሥሪያቤቶች በሙሉ በጽናት አንድ በአንድ በራቸው ላይ ተገኝቼ ማስታወቂያ ተለጠፈ ወይ ብዬ ጠየኩኝ፡፡ አንዳንዴም ደግሞ በድፍረት ጽህፈት ቤት ድረስ ገብቼ ማመልከቻዬን ሰጥቼ ሥራ ካላችሁ በጎረቤት ስልክ ደውሉ ብዮ እመለሳለሁ፡፡

ሥራ ማግኘት ግን እንደሰማይ ራቀኝ ፤ በመጨረሻም ሥራ ለማግኘት ብዙ ብደክምም ቅንጣት የምታህል ተስፋ በማጣቴ ተስፋ ቆረጥኩኝ፡፡ ጠዋትም ቀንም ማታም እቤት ተቀምጦ ከቤተሰቦቼ ጋር መፋጠጥ የሕይወቴ አቅጣጫ ሆነ፡፡  

*   *   *

ሥራፈት መሆኔ ሰልችቶኝ ስበሳጭ በምሬት “ድሮም የስዕለት ልጅ ሆኜ እኳ ነው ጣጣዬ የበዛው” እላለሁ፡፡ እናቴ ለረጅም ጊዜ ልጅ መውለድ እንቢ ብሏት ለእንጦጦ ኪዳነ ምህረት “ኪዳነምህረት በአማላጅነትሽ ልጅ የሰጠሽኝ እንደሆነ ልጄን ክርስትና የማስነሳው አንቺ ጋር ነው” ብላ ተሳለች፡፡ ቆይታ ፀነሰች የካቲት ኪዳነ-ምህት ዕለት በዓሉ አክብራ ስትመለስ ከሰዓት በኋላ እኔን ወለደች፡፡

የመንግስት ሠራተኛ በሆነው አባቴ ደሞዝ ቤተሰባችንን ይተዳደራል፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ለዛውም የስዕለት በመሆኔ ቤተሰቦቼ ከአቅማቸው በላይ አንቀባረው ነው ያሳደጉኝ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ሞልቃቃ ከአቅሜ በላይ ለመኖር የምንጠራ፣ ድህነትን የምጠየፍ ፣ሁሌም የምኖረውን ኑሮ የማማርር የተሻለ የምመኝ የሆንኩት፡፡

እኔም ሆንኩኝ ቤተሰቦቼ ከአቅማችን በላይ ጥሩ ነገር እንዲኖረን አብዝቼ እመኛለሁ፤ ጥሩ መልበስ፣ ጥሩ መብላት ያምረኛል፡፡ ይህን ጠባዬን የምታውቀው እናቴ የተለመደ ምክር ነበራት የእኔ ልጅ “ሰው እንደቤቱ ነው እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም፤ ባለሽ ነገር ተመስገን ብዬ የባስ አታምጣ ነው ” ትላለች፡፡

የእኛቤት ኑሮ ሁሌም አንድ አይነት ነው ለውጥ የለውም፡፡ እኔ ደግሞ በተፈጥሮዬ ለውጥ ፈላጊ ነኝ አዲስ ነገር እወዳለው፡፡ እናቴን ምግብ ስታቀርብ “ዛሬም ሽሮ ወጥነው አሁንስ ሰለቸኝ” እላታለው፡፡ እሷም የእኔ ልጅ “እርሱም አይጥፋ እርሱም እኮ ተወዷል” ትላለች፡፡ እኔ ደግሞ መልሼ “አረ ድራሹን ያጥፋው” ስል እናቴ ተቆጥታ “አንቺ ልጅ ሥርዓት ያዢ ” ትላለች፡፡ በሀሳቤ የሚመላለሰው የጠዋትም ሆነ የማታ ጥያቄዬ፤ የእኔንም ሆነ የቤተሰቦቼ ተመሳሳይይ የድህነት ኑሮ እንዴት ከላያችን እንላቀው የሚል ነው፡፡

*   *   *

በአቅራቢያችን እንጦጦ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አለች፡፡  በዕለተ ሰንበት ቤተሰቡ ሁሉ ሊያስቀድስ ቤተክርስቲያን ሲሄድ እኔ ግን እተኛለሁ፡፡ አንዳንድ ቀን ደግሞ አርፍጄም ቢሆን ኪዳነምህረት ሄጄ ከበር ላይ ተሳልሜ እመለሳለሁ፡፡

በሆነ ጊዜ ወቅት በሐመረ ኖህ ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን ጠበል የሚደረግ ድንቅ ተአምር በጣም ዝናው ገነነ፡፡ ከመላው ዓለም ብዙ ሰው እየመጣ ተጠምቆ ይድን ጀመር፡፡ በየወሩም በኪዳነ ምህረት በዓል ዕለት በፀበሉ የዳኑ ሰዎች የተደረገላቸውን ድንቅ ተአምራት ዓውደ ምህረት ላይ ወጥተው ይመሰክራሉ፡፡

አንድ ቀን የኪዳነ ምህረት ዕለት ነው በማታ የትምህርት ጉባኤ ላይ ተገኘሁ፡፡ የልቦናቸው ሀሳብ  የተፈጸመላቸው፣ ታመው የዳኑ፣ የኑሮአቸው እንቆቅልሽ የተፈታላቸው  ምዕመናን ሁሉ ምስክርነት ሲሰጡ በኪዳነምህረት አማላጅነት የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራቶችን ሰማሁ፡፡ በስተመጨረሻ  “እኔን የሰማች ኪዳነምህረት የእናንተንም ትስማ የልቦናችሁን ሀሳብ ትፈጽምላችሁ” የሚል ምርቃት ሲመርቁ ስሰማ ውስጤ የተለየ ስሜት ቀረ፡፡ ጉባኤው ተጠናቆ ሰው ሁሉ ወደ ቤቱ ሄዶ ግቢው ርጭ ብሏል፡፡ ጥቂት አምሽተው ለመሳለም ከመጡ ሰዎች በቀር ብዙ ሰው የለም፡፡ ፊትለፊት ያለውን የኪዳነምህረት ስዕል ትኩር ብዬ እያየሁ “እኔንስ የምትሰሚኝ መቼነው? እኔስ መቼነው እንደ ምእመናን ቆሜ ምስክርነት የምሰጠው ? እያልኩኝ በተመስጦ መጸለይ ጀመርኩኝ፡፡

በሌላው ጊዜ ከበራፍ ተሳልሜ ደቂቃ እንኳን ለመቆም ትዕግስት የሌለኝ ራሴን ረጅም ሰዓት በቤተክርስቲያን ውስጥ አገኘሁት፡፡ ልቤ ተሰብሮ የብሶት እንባዬ ነጠላዬን አርሶት ኪዳነምህረት ፊት ቆመወኩኝ፡፡ ወደ ራሴ መለስ ብዬ ሳስብ በራሴ ሁኔታ ተገርሜ በፍጥነት ወጥቼ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ፡፡

እቤት እንደገባሁ ሰውነቴ ዝሎ እሳት የሞቀ ሰው ያህል አተኩሷል ማንንም ሳላናግር ደክሞኛል   ብዬ ጥቅልል ብዬ ተኛሁ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ “ኪዳነምህት የእኔን የልብ መሻት ሁሉ እንድትሰማኝ ምን ላድርግ? ” እያልኩ ሳሰላስል የወፎች ዜማ ተሰምቶ መንጋቱ ታወቀ፡፡

*   *   *

የተለመደው የአዲስ አበባ ኑሮ አሰልችቶኛል፡፡ አሁን ግን ውስጤ አንድ አዲስ ሀሳብ ወልዷል፡፡ በስደት ወደ ሰው ሀገር በመሄድ መስራት እና መለወጥ፡፡ የሰው ሸክም ሆኜ ከመኖር ሠርቼ ማደር የቤተሰቦቼን ሕይወት መለወጥ ይገባኛል የሚል ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ፡፡

ቤተሰቦቼ እንደሆነ እንኳን ስደት መሄድ አይደለም ከቤት ወጥቼ እስክገባ ድረስ እንኳን አያምኑም፡፡ ስለዚህ ይህን ጉዳይ ለማንም ሳልናገር በልቦናዬ ያዝኩት፡፡ ወቅቱ ዐቢይ ጾም ሊገባ አንድ ሳምንት ቀርቶታል ይህ የልቦናዬ ምኞት እንዲሰምር ቤተክርስቲያን ሄጄ መጸለይ አለብኝ አሰቡኩኝ፡፡

* * *

ዐቢይ ጾም ሲገባ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ተጀመረ፡፡ ጠዋት ጸበል መጠመቅ፣ ከሰዓት ቅዳሴ ማስቀደስ፣ ማታ ስብከተ ወንጌል መማር ሆነ፡፡ ቤተሰቦቼ በመጀመሪያዎቹ ቀናት የወረት መስሏቸው “እንደለመድሽው ደግሞ ጀምረሽ እንዳታቆሚው እኪ ዘንደሮን እንኳን ዝለቂበት ” እያሉ ይወቅሱኛል፡፡  

እኔ ግን በዓላማዬ ጸናሁ፡፡ በስብከተ ወንጌል የሚሰጠውን ትምህርት ስከታተል በዘልማድ የነበረው ኦርቶዶክሳዊ ሕይወቴን መንፈሳዊ መልኬን በመስታወት እንደማየት ያሕል ተመለከትኩት፡፡ በጣም ተርቦ እንደከረመ ሰው የሕይወት እንጀራ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል በጉጉት መመገብ ጀመርኩኝ፡፡ ነፍሴ ከያዛት የእግዚአብሔር ቃል ጠኔ ተላቀቀች፡፡ መንፈሳዊ ሕይወቴ እጠነከረ በቃለ እግዚአብሔር እየታነፀ መጣ፡፡ መንፈሳዊ ትምህርቱ ኃይል ጉልበት ጽንአት ሆነኝ በረታሁ፡፡

እግዚአበሔርን በማወቅም ባለማወቅ እንደበደልኩት ተሰማኝ ከዚህ ቀደም በነበረኝ ሕይወት የኑሮ ዘይቤን ሳስበው በራሴ አፈርኩኝ፡፡ ልቤ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅ ፈለገ ፤ መንገዱ ደግሞ ንስሓ መግባት መሆኑን ስማር የንሥሓ አባት በመያዝም ኃጢአቴን ተናዘዝኩኘ ቀኖናዬን ተቀበልኩኝ፡፡ 

በኪዳ-ነምህረት ቃልኪዳን፤ ጸበል ተጠምቆ የሚፈወሰው ሰው በጣም ብዙ ነው፤እኔ የማላውቀው በቅርቤ ያለ ቦታ የምህረት እና የፈውስ ቦታ መሆኑን ቀርቤ ሳይ ተገረምኩ፡፡ ለማመን የሚከብዱ ድንቅ የእግዚአብሔር ቸርነት በየዕለቱ ይፈጸማል፡፡ በዚያው መጠን ፈውስ ፈልገው ከሩቅ መጥተው በመጠለያ ሆነው ደጅ የሚጠኑ የአልጋ ቁራኛ ሆነው በአስታማሚ የሚረዱ በአጋንት እስራት ውስጥ ሆነው እጅና እግራቸው በሰንሰለት የታሰሩ ስመለከት የሰውልጆች ያለባቸውን የዚህ ዓለም ፈተና ብዙ መሆኑ ተረዳሁ  እጅግም አዘንኩኝ ልቤም ተሰበረ፡፡

አዲሱ መንፈሳዊ ሕይወት ቀጠለ ጠዋት ለኪዳን፣ ቀን ለቅዳሴ ፣ማታ ለስብከ ወንጌል ብቻ በየቀኑ ወደ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን መገስገስ የዕለት ተዕለት ሥራዬ ሆነ፡፡ ትኩረቴ በኪዳነምህረት ጸበል አካባቢ አደረኩኝ፡፡ ነገረዓለሙን ረስቼ የሚያስጨንቀኝ እና የሚያሳስበኝ ለጸበል መጥተው ስንቅ ያለቀባቸው እናቶች ፣አስታማሚ የሌላቸው ሕመምተኞች፣በርኩሳን መናፍስት ተይዘው የሚጨነቁ ሰዎችን ሆኑ፡፡ የተቸገሩ ሰዎችን ለማገዝ በአካባቢው ያለውን ሰው በሙሉ የማስተባብርበትን መንገድ አስብ ጀመር፡፡ ዓለምን ናኩት ከንቱነቱንም ተረዳሁ ልቤ ለዚህ ጊዜያዊ ዓለም የነበረው ጉጉት ሁሉ ከሰመ እንደ ጉም ተኖ ከአጠገቤ ጠፋ፡፡

*   *   *

ጸበል ለመጠመቅ ከሚመጡ ሰዎች መካከል ከአንዲት ልጇ በጠና የታመመባት ሴት ጋር በአጋጣሚ ተግባባን፡፡ የታማሚው ልጁ ቤተሰቦች የስም ኦርቶዶክሶች ናቸው እንጂ ሃይማኖታቸውንም ሆነ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ በልተው ጠጥተው አጊጠው መኖር ብቻ ነው ሕይወት የሚመስላቸው፡፡ በድንገት ልጃቸው ታመመ፤ በፍጥነትም መላ ሰውነቱ የማይንቀሳቀስ ሆነ ቆይቶም መናገር መስማት አቆመ፡፡ በታዋቂ ሆስፒታሎች ሕክምና ቢደረግለት በህክምና ፈውስ ማግኘት አልቻለም፤ ይባስኑ በሕይወት የሚቆየው ለጥቂት ጊዜያት ብቻ መሆኑ ተነገራቸው፡፡

አንድ ቀን የታመመውን ልጅ ጠበል ለማስጠመቅ እንጦጦ ኪዳነ-ምህረት ይዘውት መጡ፡፡ በአጋጣሚ ቤተክርስቲያኑ በር ላይ አንዲት ሴት "የኔ እህት እባክሽ የሚከራይ ቤት ካለ ብታሳይኝ፤ ልጄ ታሞ ላስጠምቀው መጥቼ ማረፊያ ቦታ ፈልገን ነው ብታሳይኝ" አለችኝ፡፡ እኔም ፈጠን ብዬ "ወደ ታች ሰፈር እኮ አይጠፋም የታለ ልጁ አልኳት፡፡ እርሷ አንገቷን ሰበር አድራ በሀዘን ስሜት ልጄ እኮ እንደልቡ መራመድ መንቀሳቀስ አይችልም አልጋ ላይ ነው በሰው ሸክም የሚወጣው የሚገባው " ስትለኝ ሰውነቴ በድንጋጤ ቀዝቅዞ ቀረ፡፡ ሴትዮዋ ንግግሯን ቀጥለች "በትህትና እባክሽ ለጸበሉ ቅርብ የሆነ ቦታ ፈልጌጊልኝ እና ልከራይ" አለች፡፡ የምትከራየው ቤት ፈልጌ አከራይቻት የጸበል አካባቢውን እና የቤተክርስቲያኑን ዙሪያ ገባውን ሁሉ አሳየኋት፡፡ በዚያን ቀን ትውውቅ ተግባባን በጣም ወዳጅ ሆንን፡፡

በሰው ሸክም ወደ ጸበል ይወርድ የነበረው ልጄ ሦስት ቀን እንደተጠመቀ ራሱንችሎ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ልጁ ተሽሎት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እስኪሆን ድረስ ከስድስት ወራት በላይ ከእናቱ ጋር በመሆን ጸበል እናስጠምቀዋለን፣ ቅዳሴ እንዲያስ ቀድስ፣ ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበል እናደርገው ነበር፡፡  ልጁ ድኖ ከኪዳነ-ምህረት ወጥቶ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ ከልጁ ቤተሰብ ጋር ዝምድናችን ጠነከረ፡፡

*   *   *

እኔም ጠዋትም፣ ማታም ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን እገኛለሁ፡፡ ስለ ዓለማዊ ሕይወት ማሰብ ስለ ሥራ ስለ ኑሮ መጨነቅ እርግፍ አድርጌ ትቼዋለው፡፡ ትኩረቴ መንፈሳዊ አገልግሎት በተለይም በጸበል ቦታ ያሉ ችግረኞችን መርዳት ነበር፡፡

በአንድ ቀን የኪዳነ-ምህረት ዕለት ልጇ የዳነላት እናት ስዕለቷን ይዛ ከልጆ ጋር ሆና ዕንባዋን እየረጨች በደስታ እየፈነጠዘች እልታዋን አሰማች፡፡ በዓውደ ምህረት ቆማ የተደረገላትን ታላቅ ተአምራት የኪዳነ ምህረትን አማጅነት መሰከረች፡፡ እግዚአብሔር በኪዳነ-ምህረት አማላጅነት ልጆ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሸጋገረላት ድንቅ ተአምራት ሁሉ መሰከረች፡፡

የማታው ጉባዔው ተጠናቆ ወደ ቤታችን ስንሄድ ከመለያየታችን በፊት “አንድ ደስ የሚል ዜና ልንገርሽ ዝርዝር ጉዳዮች ነገ እቤት መጥተሽ በደንብ እናወራለን” አለችኝ፡፡ ነገሩን ስትነግረኝ “ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ አዲስ ነገር ምንድ ነው ” ብዬ ልቤ ደስታም ፍርሀትም ሳይሰማው እሽ ብዬ ብቻ ተሰናበትኳት፡፡

በማግስቱ ጠዋት እቤቷ ሄጄ የመጣሁበትን ጉዳይ በዝርዝር አስረዳችኝ፡፡ አዲስ ሥራ እንደተገኘልኝ ሥራው ከሀገር ውጭ ምስራቅ አፍሪካ ኬንያ እንደሆነ ለጉዞው የሚያስፈልገኝን ሰነዶች እና ፓስፖርት ማዘጋጀት እንዳለብኝ አበሰረችኝ፡፡ ውስጤ ግራ ተጋብቶ ለቤተሰቦቼ ሁኔታውን አስረዳዋቸው እነርሱ ነገሩን ያዩት እኔ ባላሰብኩበት መንገድ ነበር “ እግዚአብሔር የሚወደውን ሥራ ስትሰሪ የተቸገሩትን ስትረጂ ስለቆየሽ በረከቱን ሊያድልሽ ይሆናል” የሚል ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ ፓስፖርት ማውጣት ልክ ውጭ ሀገር እንደሚሄድ ያህል አታካች አስቸጋሪ ነበር፡፡ በኪዳነ-ምህረት በአማላጅነት ያላለፍኩት መከራ ያልተሻገርኩት ገደል የለምና በሁለተኛው ወር ፓስፖርት ተሰጠኝ፡፡

*   *   *

ጊዜው ሲደርስ እና መሄዴ ቁርጥ ሲሆን ከቤተሰቦቼ ከምወዳት ከእንጦጣ ሐመረ ኖህ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ተለይቼ መሄድ በጣም ጭንቅ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ሀዘኔን ውጬ እንባዬን እየጠራረኩኝ በአውሮፕላን ተሳፍሬ ወደ ኬኒያ ሄድኩኝ፡፡

ናይኖቢ ከተማ ውስጥ በአንድ የአየር መንገድ ትኬት መሸጫ ቢሮ ረዳት የሽያጭ ሠራተኛ ሆኜ በመቀጠር የስደት ኑሮዬ አንድ ብሎ ተጀመረ፡፡ የቤተክርስቲያን፣ የቤተሰብ ናፍቆት ብቸኝነት ድብርት ጭንቀት የኑሮ ጫና ተጫጫነኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በናይሮቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ስተዋወቅ የመጀመሪያው ጥያቄዬ “በዚህ ሀገር ለመሆኑ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አለ? የት ነው የሚገኘው ? ”የሚል ነበር፡፡

ከቀናት በኋላ ከምኖርበት መንደር ራቅ ብሎ በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኬንያም ሐመረ ኖህ ንጽይተ ንጹሀን ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያንን መኖሯን ስሰማ ወደር የሌለው ደስታ ተሰማኝ ፡፡ እሁድ ደርሶ አካባቢውን ጠይቄ እስክሄድ ድረስ በጣም ተጨነኩኝ፡፡ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም የከበደኝ የድብርት የጭንቀት የብቸኝነት ሸክም ከላዩ ላይ ሲራገፍ ታወቀኝ፤ ሕይወቴ ሁሉ በሀሴት ተሞላ፡፡

 ዕለተ እሁድ የተመረጠች ቀን ዕለተ ሰንበት፡፡ በጠዋት ተነስቼ ታክሲ ጠራሁ፡፡ ሰው ለመኖር ምግብ እና መጠለያ ያስፈልገዋል ይባላል፡፡ እኔ ግን ያ ብቻ በቂ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እኔ ባለፉት ወራት በሰው ሀገር ከእግዚአብሔር ቤት ርቆ ዕጣኑን ሳያሸቱ፣ ቅዳሴ ሳያስቀድሱ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሰሙ መኖር እጅግ አስጨናቂ እና ከባድ እንደሆነ ምስክር ነኝ፡፡ ለመኖር የእግዚአብሔር ቤት መሄድ፣ ቃሉን መስማስ ፣ማስቀደስ፣ ጸበል መጠጣትም ያስፈልጋል እያልኩ ከራሴ ጋር እያወራሁ ታክሲው ቤተክርስቲያኑ በር ላይ አደረሰኝ፡፡

 የኬንያም ሐመረ ኖህ ንጽይተ ንጹሀን ኪዳነምህረት ሕንፃ ቤተክርስቲያን በሸክላ የተገነባ ጥቁር እና ነጭ ቀለም የተቀባ ነው፡፡ በደስታ ወደ ቤተመቅረሱ ውስጥ ገብቼ ተሳለምኩኝ ምንጣፉ ላይም ተንደባለልኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእለተ ሰንበት በጠዋት ተነስቼ በመሄድ አስቀድሼ በዓል ሲኖርም አክብሬ ዘምሬ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ፡፡ ኪዳነ-ምህረትን መጽናኛዬ ለስደት ኑሮዬ ዋስትናዬ አድርጌ ደጅ እጠናት ጀመር፡፡

* * *

በኬንያ የኑሮው ውድነቱ ኃያል ነው፡፡ ተርፎኝ እንኳን ቤተሰቦቼን ልረዳ ቀርቶ ራሴንም ችዬ ወር ለመድረስም በግድ ሆነ፡፡ ቀናት እና ሳምንታት ወራት ዓመታት ቢቀያየሩ የእኔ ኑሮ ሳይለወጥ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ ችግሬ እየጸና መጣ፡፡ ጊዜ አግኝቼ ኬንያ ሐመረ ኖህ ንጽይተ ንጹሀን ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያንን በመሄድ በቻልኩበት ቁጥር እቤቴ ሆኜ የዘማሪ ፍቃዱ ኪዳነምህረት ነሽ እናቴ የሚለውን መዝሙር እና ሌሎችም ኪዳነምህረት የሚጠሩ መዝሙሮችን ከፍቼ እየሰማሁ እጽናናለሁ፡፡

በአንድ ሰንበት ቀን ከሌላው ቀን በበለጠ ተከፍቼ ስለነበረ እንደተለመደው ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቼ እንባዬን አፍስሼ ጸሎቴን አደረስኩኝ፡፡ ጸሎቴን ጨርሼ ወደ ቤቴ ለመሄድ ከቤተክርስቲያን ጊቢ እየወጣሁ እያለ ኪዳን የምትባል ጎደኛዬ በቤተመቅደስ ውስጥ ለጸሎት የማሳየውን ሁኔታዬን ተመልክታ ነበር እና እስክወጣ ድረስ ጠብቃ አገኘችኝ፡፡

ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ጨዋታ ጀመርን፡፡ “ምነው ጠፋሽ አግኝቼሽ አላውቅም” ስላት “ጉዳይ ስለነበረኝ አልተመቸኝም ለዛ ነው፤ብላ ለአፍታ ዝም አለች ፡፡ እንደገና ንግሯን ቀጥላ "ቢገርምሽ ረጅም ዓመት የኖርኩበት ኬንያን ተሰናብቼ ነገ ወደ እንግሊዝ ሀገር ልሄድ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ በዚህች  በኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ስማጸን ቆየሁ፤ ከዓመታት በኋላ በእግዚአብሔር ቸርነት በኪዳነምህረት አማላጅነት ሕልሜ ተሳካ” አለችኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ረጅም ሰዓት የተለያዩ ጉዳዮችን ሥናወራ ቆይተን ልንሰናበት ስንል ለማንኛውም አድራሻዬ ስልኬንም መዝግበሽ ያዥ ከኬንያ ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ መሟላት ስላለባቸው መስፈርቶች ደግሞ ከተማ ሰንደርስ አቀብልሻለሁ አለችኝ እና ተሳስመን በፍቅር ተለያየን፡፡

* * *

በኬንያ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን የአጭር ጊዜ ትውውቅ ያላት ኪዳን ለእኔ የኪዳነምህረት ሥጦታዬ ነበረች፡፡ እንደሌሎች ሰዎች ዝምድናን ብሔርን ተገን አድርጋ ሳይሆን እንዲሁ እርሷ ያገኘቸውን መልካም ነገር ሌላው ሰውም እንዲያገኝ በመመኘት ብቻ ምኗም ላልሆንኩኝ ደሀ ስደተኛ ትጨነቃለች፡፡ ኪዳን እንግሊዝ ሀገር ከገባችበት ቀን ጀምሮ እኔጋ ያልደወለችበት ቀን አልነበረም፡፡ እንደ እናት፣ እንደ አባት፣ እንደ እህት ሆና ለእኔ ትጨነቃለች፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በራሷ ገንዘብ ወደ እንግሊዝ ሀገር መሄድ የሚያስችል የሥራ ፈቃድ ገዝታ ላከችልኝ፡፡ ኬንያ በሚገኘው እንግሊዝ ሀገር ኤምባሲ መረጃዎቼን ይዥ ገባሁ፡፡ አንዱ ሁለት ጊዜ አመላለሱኝ፡፡ እኔ ደግሞ ተስፋ ሳልቆርጥ ኪዳነምህረትን መልሼ መላልሼ በጸሎት ደጅ ጠናሁ፡፡ ብቻ ደስታ የመከራን ያህል ረጅም አይደለም ረጀም ጊዜ የተጨነኩበት ጉዳይ ተሳካሀ፡፡ ሀሳቤ ሞላ ቪዛ አግኝቼ ወደ እንግሊዝ ሀገር መሄድ ቻልኩኝ ረጅሙ መከራ አለፈ አጭሩ ደስታ ደግሞ መጣ፡፡

*   *   *

ለንደን ከተማ ስደርስ ኪዳን ከጎደኞቿ ጋር ሆና ተቀበለችኝ፡፡ ወደ መኖሪያ ቤቷም ይዛኝ ሄደች፡፡ በለንደን ከተማ ባሉት ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች በባልንጀራዬ ቤት ተጠልዬ መኖር ከጀመርኩኝ እነሆ ስድስት ወር ሆነኝ፡፡ የመኖሪያ ፈቃድ ከሌለኝ እንደልብ መንቀሳቀስም ሆነ ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ከሀገሬ የወጣሁበትን ቤተሰቦቼን የመርዳት ዓለማ ማሳካት አያስችለኝም፡፡ በዚህ ሁኔታ በጎደኛዬ ቤት ተጠልዬ ሥራ ሳልሰራ ቤተሰቦቼንም ሳልረዳ ጊዜው ነጐደ፡፡ ይህ ደግሞ ከኬንያ ወደ እንግሊዝ ስመጣ የነበረኝን የደስታ ጊዜ አሳጠረው በሁኔታው መከፋት እና በድብርት ውስጥ መውደቅን ተያያዝኩት፡፡

 ለእንግሊዝ የስደተኞች ባለስልጣን ማመልከቻዩን በማስገባት የመኖሪያ ፈቃዴን የማገኝበትን ቀን መጠባበቅ ጀመርኩኝ፡፡ አንድ ቀን ስደተኞች መሥራቤት ቆሜ ወረፋ ስጠብቅ አጠገቤ ያለ ጎልማሳ  ሀበሻ መጨዋወት ጀመርን ቀጠል አደረገ እና እንዲህ አለኝ "ይገርምሻል እኳ እንግሊዝ ሀገር 10 እስከ 15ዓመት ድረስ በለንደን ኖረው የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ሰዎች አሉ ታውቂያለሽ በዚህ ሀገር በቀላሉ የመኖሪያ ፈቃድ አይገኝም፡፡ ይህን ሲለኝ እኔ ውስጤን ላብ እያሳጠመው ነበር፡፡ ሰውዬው መርዶውን አይጨርስም እንዴ ለምን ተስፋ ያስቆርጠኛል እያለኩኝ እያለ የእጅ ስልኩ ጠራና ይቅርታ አንዴ ላናግር ብሎ ከአጠገቤ ዞር ሲሊ ቦታ ቀይሬ ወደሌላኛው ጥግ ሄድኩኝ፡፡ የዛን ቀን ሌላ ቀጠሮ ቀን ተቀብዬ ተሰፋ በቆረጠ ስሜት ወደ ቤቴ በባብር ተሳፍሬ መጣሁ፡፡

ለእንግሊዝ የስደተኞች ባለስልጣን ያስገባሁትን ማመልከቻ ደብዳቤዬን ተመልክተው መልስ ይሰጠኛል ብዬ ለወራት ብጠብቅም ምንም መልስ ጠፋ፡፡ በሰው ቤት በእንግድነት ተቀምጦ ምንም ሥራ ሣይሰሩ መኖር ለእኔ የህሊና ቁስል ሆነብኝ፡፡ ስበላ ስጠጠና ስወጣ ስገባ በጣም እሳቀቃለሁ፡፡ መፍትሄው ግራ ቢገባኝም ከነገ ዛሬ ይሳካል ብሎ ተስፋ በማድረግ መጠበቅ ብቻ ሆነ ኑሮዬ፡፡ ነገር ግን ኪዳነ-ምረትን ስዕሏን በቦርሳዬ ይዤ በቤቴ ለጥፌ ስወጣም ሰገባ በስልኬም መዝሙሯን እየሰማው እማጸናታለሁ ፡፡

አንድ ቀን የኪዳነ-ምህረት ቀን ዋዜማ ነው፡፡ ከኪዳን ጋር ነገ ኪዳነ-ምህረት ናት ብለን ስናወራ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እዚህ ሀገር ለመሆኑ የኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን የለም እንዴ? ብዬ ጠየኳት፡፡ እርሶም “እኔ እንጃ እኔ እንኳን አላውቅም እስኪ የሚያውቁ ሰዎች ካሉ እጠይቃለን ”አለችኝ፡፡ ብዙም ሳትቆይ ወደምታውቃቸው አንድ ሁለት ሰዎች ጋር ደወለች፡፡ ባደረገቸው ፍለጋም በለንዶን ከተማ የኤርትራ ደብረ መድኃኒት ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን መኖሩን አረጋገጠች፡፡

በለንደን ከተማ የሚገኘው የደብረ-መድኃኒት ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን በማግስቱ ሄድኩኝ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ትልቅ ካቴድራል እና ሰፊ ነው፡፡ ዕለቱ ኪዳነምህረት በመሆኑ ጊቢው በምዕመናን ተሞልቷል፡፡ ወደ ቤተመቅደሱ ስጠጋ “እነቺውነሽ ተስፋው ለአዳም ኪዳነምህረት በተሰደደ ጊዜ ከገነት” እያሉ የሚዘምሩ መዘምራን ተመለከትኩኝ፡፡ አብሬ በእልታ ስዘምር ቆይቼ ወደ ጥግ ባየሁት የኪዳነ ምህረት ስዕል ፊት በመሄድ ተደፍቼ በእንባ ጸሎት ማድረጉን ተያያዝኩት፡፡ መቼም አሁን ላይ ሆኜ ያንን ንዝዛዬን ጭቅጨቃዬን ሳስበው እገረማለሁ ብቻ ዋናው ጸሎቴ የመኖሪያ ፈቃዴን ጉዳይ ኪዳነምህረት እባክሽ ጨርሺልኝ የሚል ነበር፡፡

 ከሰዓታት በኋላ በደስታ እና በእምነት ከቤተክርስቲያኑ ወጥቼ ወደ መኖሪያ ቤቴ ሄድኩኝ፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ተመልሼ ቤቴ ስገባ ለጎደኛዮ ኪዳንን "ይገርምሻል የኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አገኘሁት ሄድኩኝ እኮ እያልኩ በደስታ በፈካ ፊት ሆኜ ነገርኳት፡፡

"ኪዳነምህረትን ካገኘሁ እንደተለመደው ሁሉም ነገር ይሳካል" እያልኩ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያመለከትኩበትን ወረቀት ካስቀመጥኩበት አውጥቼ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ገጽ በገጽ እየገላለጽኩኝ ስመለከት አጋጣሚ ዐይኔ የማመልከቻ ቁጥሩ ላይ ትኩረት አደረገ፡፡ ትኩር ብዬ ሳየው ደግሞ የቁጥሩ መጨረሻ 16 ሆኖ አገኘሁት፡፡ በሁኔታው ተገርሜ "ለካ ጉዳዩን የያዘቸው ኪዳነምህረት ነሽ" ብዬ ተመሰተጦ ውስጥ ገባሁ፡፡ እቤቴ ባለው በኪዳነ-ምህረት ስዕል ፊት ተደፍቼ ስቅስቅ ብዩ አለቀስኩኝ፡፡

*   *   *

ከ አንድ ወር በኋላ በደረሰኝ የፖስታ መልዕክት በመጪው ሰኞ በእንግሊዝ የስደተኞች መስሪያ ቤት በአካል በመገኘትና ቃለመጠይቅ ማድረግ እንዳለብኝ የሚያስታውስ ደብዳቤ ነበር፡፡ ረጅሙ የስቃይ ጊዜ ያጠረው፤የቀጠሮው ቀንም እንዲህ የተፋጠነው ኪዳነ-ምህረት በአንቺ አማላጅነት በልጅሽ ቸርነት ነው ብዬ ሰፈር ጉድ እስኪል እልልታውን አቀለጠኩት፡፡ 

በእንግሊዝ የስደተኞች መስሪያ ቤት በአካል የምገኝበት ቀን በአውሮጳውያን የቀን አቆጣጠር  ፌብርዋሪ 24 ነው፡፡ በ ፌብርዋሪ 23 ቀን ጠዋት እኔ ብዙ የማልቀርባቸው የኪዳን የኪዳነምህረት ማህበርተኞች ስልክ ደወሉልኝ፡፡ አንዷ እህት "ዛሬ ማታ በዋዜማው አዳራችን ሄደን በዓሉን ለማክበር መንፈሳዊ ጉዞ አዘጋጅተናል አጋጣሚ ትርፍ ቦታ ስላለን መሄድ የምትፈልጊ ከሆነ አብረሽን እንድትሄጂ ነው ? "አችኝ፡፡ እኔ ግን እንዴት አስታወሱኝ እያልኩ ቆይ ነገ የምን በዓል ነው ያለው አላወኩም አልኳት፡፡ ልጅቷ በመገረም "ነገ እኮ የካቲት 16 ቀን የኪዳነምህረት ዓመታዊ በዓል ነው ስትለኝ በድንጋጤ ፈዝዥ ቀረሁ፡፡ እንደምንም ብዬ ዝግ ባለና በተቆራረጠ ድምጽ አይ አልችልም አልሄድም ብዬ ስልኩን ዘጋሁት፡፡ ሰውነቴ ግን ረጅም ሰዓት ተንቀጠቀጠ በሆነው ነገር ሁሉ ተደንቄ ዝም አልኩኝ፡፡ የዛን ቀን ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ እንቅልፍ ሳይወስደኝ አደረ፡፡ ለሌቱን  ደግሜ ደጋግሜ የሰኔ ጎልጎታን መጽሐፍን ስጸልይ አደርኩኝ፡፡ ጠዋት ሲነጋ ቃለመጠይቅ ወደ ማደርግበት የእንግሊዝ መንግስት ስደተኞች ቢሮ ሄድኩኝ፡፡

ስደርስ ከ እኔ በፊት የተወሰኑ ሰዎች ተሰልፈው ይጠብቃሉ፡፡ በየተራቸው ቃለመጠይቅ ወደ ሚደረግበት አዳራሽ ውስጥ ገብተው ቆይተው ይወጣሉ፡፡ አብዛኞቹ ሲመለሱ ያገኙት ምላሽ ጥሩ ስላልሆነ ተከፍተው እና አኩሩፈው ሲመለሱ ይታያሉ፡፡ ይህን ሳይ በውስጤ ፍርሀት ተሞላ ተጨነኩኝ በቃ እኔም ዋጋ የለኝም ብዬ ፈራሁ፡፡

 የእኔ ተራ ደርሶ ስገባ በልቤ ኪዳነ-ምህረት ተከተይኝ ብዬ ወደ አዳራሱ ውስጥ ገባሁ፡፡ ስሜን ተናግሬ ጉዳዬን እያስረዳሁ እያለ ከበፊት ለፊቴ ደመና የሚያስፋራ ደማቅ ብርሃን ይታየኝ ጀመር፡፡ ከዚያም ወዲያውኑ ኪዳነምህረት ከደመና ውስጥ ወጥታ ቆማ ታየችኝ፡፡ በዝግታ ከአንደኛው ጥግ ወደ ሌላኛው ጥግ ትመላለስ ጀመር፡፡ በጣም ደነገጥኩ ሰውነቴ ዛለ አንደበቴ ተሳሰረ መላ አከላቴ በላብ ተጠመቀ ከዚያም ኪዳነ ምህረት እናቴ እያልኩ መሬት ላይ ተደፍቼ ማልቀስ ጀመርኩኝ፡፡

ቤቱ በብርሃን ደምቋል ሀምራዊ ምንጣፍ ተነጥፎል አስደናቂ ልብን ደስ የሚያሰኝ ሽቱ ይሸታል፡፡ ይህ ነገር ለእኔ ብቻ ይታኝ ለሌላው ሰውም ይገለጥለት አላውቅም፡፡ ደማቅ ብርሃን ልብስ ለብሳ ሰማያዊ ቀሚስ አርጋ ከላይዋ ላይ 12 ከዋክብት ከበዋት ቀረብ ብላ ተገለጠችልኝ ፡፡ በደመና ተጭና እጆቿን ወደ ኤኔ ዘርግታ አይዞሽ ልጄ አታልቀሺ ጸሎትሽ ልመናሽ ተሰምቷል ልጄ መድኃኔ ዓለም ብዙ ጸጋና በረከት ያድልሻል፡፡ አይዞሽ ተነሺ በእምነት ጸንተሸ ቁሚ ካገኘሽው ገቢ አሥራት በኩራትሽን አውጪ በጠበል ቦታ የወደቁትን ችግረኞች እርጂ ሥላሴን ዘክሪ ብላኝ በደመና ከአይኔ እየራቀች ተሰወረችብኝ ፡፡

በሁኔታው የእንግሊዝ የስደተኞች ባለስልጣን ሠራተኞች ግራ አጋባቸው፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ አባብለው አንስተውኝ  ወንበር ላይ አስቀመጡኝ፡፡ ስለሆነው ነገር ለመናገር ቃላት አጠረኝ፡፡ የስደተኞች ጉዳይ ሐላፊም ካለበት ክፍል ወጥቶ አጠገቤ መጥቶ ደግፍ አድርጎ ያባብለኝ ጀመር፡፡ አይዞሽ ብዙ አትጨነቂ ብሎ ምክር ሰጠኝ፡፡ ሌላው ባለሙያ ደግሞ ፓስፖርቴን እና የመኖሪያ ፈቃድ ምስክር ወረቀቴን እየሰጠኝ እንኳን ደስ አለሽ በእንግሊዝ ሀገር መኖር ትችያለሽ መልካም ጊዜ ይሁልሽ አለኝ፡፡

ኪዳነ-ምህረት በአማላጅነቷ ለሚያምኗት ሁሉ ትደርሳለች፡፡ በቃልኪዳኗም ታስምራለች፡፡

የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ/ም

አዲስ አበባ