ሰኞ 8 ጃንዋሪ 2024

ካነበቡኩት

 


 ልጃቸውን በስለት ለቤተ ክርስቲያን የሰጡት ፊሊፒንሳዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካህን

   የፎቶው ባለመብት, Dante Alonzo/ Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ,  ቀሲስ ዳንቴና ዲያቆን ዮሐንስ 6 ጥር 2024

ዳንቴ አሎንዞ ካህን ናቸው።  አገልግሎታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው።  በቤተ ክርስቲያኒቱ ለጥቂቶች ብቻ የተፈቀደውንም ምስጢር ያውቃሉ። ሁለተኛ ቄስ ሆነው ቅዳሴ ይመራሉ። ከቅዳሴ በኋላ ምዕመናንን ያቆርባሉ። ታቦት ይይዛሉ። ሌላም ሌላም አገልግሎት ይሰጣሉ። ተወልደው ያደጉት በሩቅ ምሥራቋ አገር ፊሊፒንስ ነው።

ፓኒኪ ታርላ በተሰኘችው ከተማ ልጅነታቸውን አሳልፈዋል። በዚያች ከተማ ጎዳናዎች ላይ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ዳቦ ይሸጡ ነበር። የዳቦ ንግዳቸውን ጠዋት ጨርሰው ከሰዓት ማርሻል አርት ይማራሉ። አብዛኛው የልጅነት ጊዜያቸው እንዲህ ነበር ያለፈው።

ያኔ ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚባል ሃይማኖት ስለመኖሩ አያውቁም።  ለነገሩ በፊሊፒንስ የኦርቶዶክስ ክርስትና ብዙም አይታወቅም። በአገራቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን፣ እስልምና ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል።

ፊሊፒንስ እያለሁ ስለ ኦርቶዶክስ ክርስትና ፍጹም ሰምቼ አላውቅምይላሉ። ታዲያ ዳንቴ የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶን ከማወቅ አልፈው አገልጋይ ለመሆን እንዴት በቁ? እሳቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታይ የሆንኩበት አጋጣሚእጅግ የሚገርመኝ እና ተዓምር ነውሲሉ ይገልጹታል።

አንድ ቀን፣የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማወቅመጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው ማንበብ ጀመሩ።  መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ የመጀመሪያቸው ነበር። በመጀመሪያዎቹ ገጾች ልባቸውን የያዘ ቃል አገኙ።  ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ ያለው ጥቅስቀልቤን ገዛውይላሉ። ያ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልምየሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባልይላል። ይህ አጋጣሚ ስለኢትዮጵያ ለማወቅ ጉጉትን ፈጠረባቸው። ይህ ሲሆን ወደ ካናዳ ተሰደዋል።

በምኖርበት ቶርንቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ማፈላለግ ጀመርኩሲሉ ይገልጻሉ። ከብዙ ፍለጋ በኋላ፣ በካናዳ ጃማይካውያን በአውሮፓውያኑ 1977 ያቋቋሙት መድኃኒዓለም የተሰኘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስርስቲያንን አገኙ። ከቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ቆመው አንኳኩ።  ምላሽ ግን አልነበረም። ስልክ ደወሉ። በቀጣዩ ሳምንት እንዲመጡ ተነገራቸው። ጥሩ አጋጣሚሆኖ ቀን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ትንሳኤ የሚከበርበት ምሽት ነበር።  በዚያን ጊዜ ካቶሊክ ነበርኩ። አንድ ሳምንት ቀደም ብዬ በካቶሊካውያን የሚከበረውን ትንሳኤ አክብሪያለሁሲሉ ያስታውሳሉ።

የሆነው ሆኖ በዚያች የፋሲካ ምሸት በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደረሱ።  ልክ ስደርስ ሥርዓተ አምልኮቱ ተጀምሮ ነበር። በሕይወቴ በጣም ስሜቴ የተነካው ያኔ ነው። ምንም የማውቀው ነገር ባይኖርም፣ ይህ ትክክለኛ ቦታ ነው አልኩ። በመጀመሪያ ቅጽበት የነበረኝ ስሜት በጣም ጠንካራ ነበርይላሉ።

ያዩት ሥርዓተ አምልኮ ለእሳቸው ፍጹም አዲስ ቢሆንም፣ ቋንቋው ባይገባቸውም ነገሩ በሕይወታቸው ትልቅ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ ግን ተገንዘበውታል። ይህ የእኔ ቤተክርስቲያን ነው አልኩ። ሥርዓተ አምልኮቱ ሲጀምሩ፣ ማልቀስ ጀመርኩ። ልክ ሕጻናት እንደሚያለቅሱት ነው ያለቀስኩት። በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር። እግዚአብሔርን አላውቅም ነበር አልኩኝ።

በዚያው ቀን አንድ ምዕመን ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያትት መጽሐፍ እንደሰጣቸው ያስታውሳሉ።   መጽሐፍ ብዙ ረድቷቸዋል። ከጊዜ በኋላም የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ እምነትን ተቀብለው ተጠመቁ። ገብረ መድኅን የሚል የክርስትና ስምም ተሰጣቸው።

 

የቤተክርስቲያን አገልግሎትን የጀመርኩት ከጽዳት ነው

ዳንቴ የኦርቶዶክስ ክርስትናን ተቀብለው ብቻ አላቆሙም። የቤተክርስቲያኒቱን የአምልኮ ሥርዓት መማር ጀመሩ።   በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ መጻህፍትን ያነባሉ።   አባ ደስታ ከተባሉ አባት የኦርቶዶክስ አስተምህሮቶችን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ታሪክን እና ሌሎች መጽሐፍትን ለሁለት ዓመታት ተማሩ።  አባ ደስታ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን በካናዳ ለሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታይ ጃማይካውያን ትህምርትን ይሰጡ ነበር።

እሳቸው 1993 .. ከካናዳ ሲወጡ፣ ቀሲስ ዳንቴ እስካሁን ድረስ እያገለገሉ ወደሚገኙበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቶሮንቶ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አመሩ።  ወደዚህ ቤተክርስቲያንየማይመጣ የውጪ ዜጋ የለም።ስለኢትዮጵያ የሰሙ ወይም ያነበቡ የውጭ አገራት ዜጎች ይመጣሉ፤ ይጠይቃሉ። ማገልገል እንፈልጋለን ይላሉ። ይህ የተለመደ ነው።  ችግሩ የሚዘልቁትእጅግ በጣምጥቂቶቹ ናቸው።  ብዙዎች ይመጣሉ። ቋንቋው እና ባህሉ አዲስ ሲሆንባቸው ተመልሰው ይሄዳሉይላሉ አቶ ዓለማየሁ።

አቶ ዓለማየሁ ዘነበ በቤተክርስትያኑ 32 ዓመታት አገልግለዋል።  በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በሥነ መለኮት የተመረቁ ሲሆን፣ አሁን ላይ የመንበረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። ዳንቴ አሎንዞንም በደንብ ያውቋቸዋል።  ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ዳንቴ መጥተው እንደሚመለሱት ሌሎች የውጭ አገራት ዜጎች እንዳልሆኑ ተረዱ። የሚመላለሱበት ድግግሞሽ፣ ትህትናቸው እና ትጋታቸው የተለየ ሆኖ አገኙት።  እኛ ይህን ሁሉ ስናይይሄ ሰውዬ ለካ የምሩን ነውአልን. . . ለቤተክርስቲያን ልዩ ፍቅር እና ታማኝነት አለው። ከሰው ጋር ተግባቢ ነው። ቤተሰቡንም ይዞ ይመጣ ነበር። ልጆቹም እዚህ ካሉት ልጆች ጋር ወዲያው ነበር የተግባቡት። እኛም በትልቅ ደስታ ነበር የተቀበልነውሲሉ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ, ቀሲስ ዳንቴ በዲቁና በሚያገለግሉበት ወቅት

የቤተክርስቲያኒቱ አግልግሎት በግዕዝ እና በአማርኛ መሆኑ የቀሲሱ ዳንቴን የአገልግሎት ጉዞ ፈታኝ አድርጎታል።

ቢሆንም አገልግሎታቸው ቀጥሏል።  እውነትን እንዳገኘሁ ሲገባኝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምችለውን አገልግሎት ለመስጠት ወሰንኩኝ። በእኔ አቅም ሊሠራ የሚችል ሥራን መሥራት ጀመርኩ። ጽዳት እና ምግብ የሚያበስሉትን ማገዝ ጀመርኩ። ስፈልገው የነበረውን እውነት ስላገኘሁ ቤተ ክርስቲያንን የሕይወቴ አንድ አካል አደረኳትሲሉ ይገልጻሉ።

ከዓመታት የትምህርት እና የቤተክርስቲያን አገልግሎት በኋላ ድቁናን እንዲቀበሉ መወሰኑ ተነገራቸው። አላመኑም።በወቅቱ የተፈጠረብኝን ስሜት ቃላት አይገልጸውምይላሉ። በዚህ መካከል የተወለዱት ሁለት ልጆቻቸውን ወደ ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ይዘዋቸው ይመጡ ነበር።  ልጆቹ መዘምራን ክፍል ውስጥም ገብተዋል። ዮሐንስ [ወንዱ ልጃቸው] የሦስት ዓመት ልጅ እያለ [አባቱ] ትንሽ ከበሮ ሰርቶለት ሁልጊዜ ከፊት ቆሞ ይዘምር ነበርሲሉ አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ።

የዳንቴ ክህነት እና አገልግሎት

ዳንቴ ግንቦት 3/ 2008 .. ድቁናን ከአቡነ መቃሪዮስ ተቀበሉ።

ይኼኔ ዕድሜያቸው 39 ዓመት ነበር።

ድቁናን ሲቀበሉ እጅግ ደስ ብሏቸዋል። ደስ ቢላቸውምይህ ለእኔ አይገባም፣ ብቁ አይደለሁምብለውም ነበር።

እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ እና ከሌሎች መምህራን ለዓመታት ለድቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት በእንግሊዝኛ ተምረዋል።  ለአገልግሎት ብቁ እንደሆኑ ሊቀ ካህናት እንግዳ ምስሌ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደላቸው ይናገራሉ።

ለዚህ ሥርዓት አዲስ ስለሆንኩ ብዙ ነገር አላወቅም ነበር የሚሉት ዳንቴበእያንዳንዱ ነገርቀጥሎ ምን ላድርግ?’ እያልኩ እጠይቅ ነበርሲሉ ይገልጻሉ።   አቶ ዓለማየሁ ደግሞበጣም ትሁት ሰው ስለሆነ የሚያወቀውን ለመናገር አይደፍርም። ለዚያ ብቁ መሆኑ ከታመነ በኋላ ነው ወደ ድቁና እንዲሄድ የተደረገው. . . ለቤተክርስቲያን ትጉህ እና ታማኝ ነውሲሉ ይመሰክሩላቸዋል።

በግዕዝ እና በአማርኛ የተጻፉ ግን በላቲን ፊደል የተቀረጹ መጻህፍትን አጥንተዋል።  ቋንቋውን ለመናገር ይቸገሩ እንጂ አንዳንድ መጽሐፍትን በቃላቸው ይዘዋል።  በዚህ ሁኔታ፣ በተለይ በእንግሊዝኛ የቤተ ክርስቲያንን አግልግሎት መስጠት ጀመሩ።  በዚህ ጊዜ የዳንቴ አራተኛ ልጅ በዚያው ቤተክርስቲያን የድቁና ትምህርትን ከሌሎች ሕጻናት ጋር እየተከታተለ ነበር።  ይህ ከሆነ ልክ 10 ዓመታት በኋላ የዳንቴ የዲያቆንነት አገልግሎት አበቃ።  ቅስናን ለመቀበል እና ቀሲስ ለመባል ተመረጡ።  የጠበቁት ግን አልነበረም።

የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መጥተው ቄስ ልትሆን ነው ሲሉኝ። ደነገጥኩዝግጁ አይደለሁም እኮስላቸውልጅህ ዲያቆን ሊሆን ነው። አንተም እሱም ዲያቆን መሆን አትችሉም፣ ይህ የቤተክርስቲያንን ሕግ ይጻረራል አሉኝእንኳን ለቅስና ለድቁናው እኮ በደንብ አልበቃሁም አልኳቸው’ ” ይላሉ።  የሆነው ሆኖ፣ ሚያዚያ 28/ 2010 .. ቅስናን ተቀበሉ። ቀሲስ ዳንቴ (ቀሲስ ገብረ መድኅን) ተባሉ።  

እውነት ለመናገር ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።በዚህ ባህል ውስጥ አላደግኩም። ዕድገቴ በምዕራባውያኑ ባህል ውስጥ ነውየሚሉት ቀሲሱለዚህ አልገባምቢሉም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተቀበሉ።  ቀሲስ ዳንቴ በቅዳሴ ወቅት ረዳት ወይም ሁለተኛ ቄስ በመሆን ሥርዓቱን ይመራሉ። ከቅዳሴ በኋላ ምዕመናንን ያቆርባሉ።

በክብረ በዓላት ወቅት ደግሞ ታቦት ይይዛሉ።  ለመጀመሪያ ጊዜ ታቦት እንዲይዙ ሲነገራቸውይህንን ለማድረግ ብቁ አይደለሁምብለው ተከራክረዋል።  ግድ መሆኑን ስረዳ፣ ፈጣሪ ይቅር በለኝ። እኔ ይህንን ለማድረግ አልበቃሁም አልኩኝይላሉ።  በተጨማሪም በቅዳሴ ወቅት የወንጌል ንባቦችን በእንግሊዝኛ ያነባሉ። በግዕዝ እና በአማርኛ ቋንቋ ክርስትና ለማንሳት እና ለማጥመቅ እየተማሩም ነው።  ለአንዳንድ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ምዕመናን መንፈሳዊ አባታቸውእንደሆኑ አቶ ዓለማየሁ ጠቅሰዋል። ከዚህም ውጪ በእጅ ሙያቸው ቤተ ክርስቲያንን ያግዛሉ።  ካህናት፣ ዲያቆናት እና ምዕመናን በፍቅር ነው የሚያዩዋቸው እንጂ መጠራጠር እና አይችሉም ብሎ ማሰብ የለምበማለትም አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ።

ዲያቆን ዮሐንስ አሎንዞ፡ በስለት የተሰጠው ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ, ዲያቆን ዮሐንስ አሎንዞ (ከመሐል)

ዳንቴ 1971 .. ልክ 16 ዓመት ሲሞላቸው የተወለዱበትን፣ ያደጉበትን ዳቦ የሸጡበትን የፊሊፒንስ መንደሮች ጥለው ወደ ካናዳ ተሰደዱ።  ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኑሯቸው ካናዳ ሆነ።  ቤተሰባቸው ትልቅ ነው - 13 ወንድም እና እህት አላቸው።  ወደ ካናዳ የተሰደዱት ግን እሳቸውን ጨምሮ ሰባት የቤተሰቦቻቸው አባላት ናቸው። ከ28 ዓመታት በፊት 1988 .. ትዳር መሠረቱ።  ጋብቻቸው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ካናዳ ውስጥ ነበር የተፈጸመው።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ከመተዋወቃቸው በፊት የተወለዱት ሦስት ልጆቻቸውም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠምቀዋል።  ከዚያ በኋላ የተወለዱት 2 ልጆች ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሥርዓት የክርስትና ጥምቀት ተደርጎላቸዋል። ዮሐንስ እና ማክዳ የሚል ስምም ተሰጥቷቸዋል። ቀሲስ ዳንቴ ወደዚህ ሕይወት ከመጡ በኋላ ወንድ ልጃቸው ዮሐንስ ከቤተክርስቲያን ጋር የተለየ ቁርኝት እንዲኖረው ወሰኑ።

20 ዓመታት በፊት የሆነውን ልክ ዛሬ እንደሆነ ያስታውሱታል። ኦርቶዶክስን በተቀልኩበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ዮሐንስ የጸሎቴ ሁሉ አካል ነበር።ፈጣሪ ወንድ ልጅ ስጠኝ። ስሙን ዮሐንስ ብዬ አንተን እንዲያገለግል እሰጠዋለሁስል ለመንኩ። ይህ ከሆነልኝ ወደ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ [ብዬ ተሳልኩ] አልኩ። ይገርማል፣ ፈጣሪ አደረገው። ዮሐንስ 1996 .. ተወለደ። እኔ ደግሞ 2001 ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሄድኩይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ,  ዮሐንስ ክራርን ጨምሮ ሌሎች የዜማ መሳሪያዎችን ይጫወታል

በኢትዮጵያ የአንድ ወር ቆይታቸው በርካታ አካባቢዎችን ረግጠዋል። በርካታ ገዳማትን እና አብያተ ክርስቲያናትን ተሳልመዋል።  ወደ ጣና፣ አክሱም፣ ጎንደር ላሊበላ፣ ደብረዳሞ እና ሌሎች ቦታዎች ተጉዘው በገዳማቱለጸሎታቸው ምላሽ የሰጣቸውንፈጣሪ አመሰግነዋል።  የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መነሻቸው ጃማይካውያን የመሠረቱት ቤተ ክርስቲያን መሆኑን አስበው ወደ ሻሽመኔ አቅንተው ጃማይካዎችን ጎብኝተዋል።

ወደ ዮሐንስ እንመለስ።

ቀሲስ ቃላቸውን ጠበቀው ልጃቸው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግል ሰጥተውታል።  ልጄ ይህንን ያደርግልኛል ብለው ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላል ብለው ነው የተሳሉት። እግዚያብሔር የለመኑትን ነው ያደረገላቸው. . .የገቡትን ስለት ሰጥተዋል። የሚጠየቁት ነገር የለምይላሉ አቶ ዓለማየሁ።

ልጃቸውበቤተክርስቲያኑ ካሉት ዲያቆናት የሚመረጠው ነውሲሉም ጨምረዋል። ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንን ከልጅነቱ ጀምሮ ያውቃል።   ብሎ ፊደል ቆጥሮ የጀመረው ትምህርት እስከ ዜማ ደርሷል።

ዲያቆን ሆኖ መቀደስ የጀመረው ግን 13 ዓመቱ ነበር። በቤተ ክርስቲያኑ በወር አንድ ጊዜ በሚሰጠው የእንግሊዝኛ ቅዳሴ ላይ መሪ ዲያቆን ሆኖ ማገልገል የጀመረው ያኔ ነው።  ዮሐንስ ትርጉሙን ባይረዳውም በአማርኛ መጻፍ እና ማንበብ ይችላል።  ሆኖም ለድቁና የበቁትን መጽሐፍት ትርጉም በእንግሊዝኛ ይነገረዋል።

ዮሐንስ ዲያቆን ብቻ አይደለም ዘማሪም ነው።  ዘማሪ ብቻ አይደለም፣ ክራር ይገርፋል፣ ማሲንቆም ይጫወታል፣ ከበሮ ይመታል።  ከዚያም አልፎ፣ እንጨት ቆርጦ፣ ክሮችን ወጥሮ ክራር እና ማሲንቆን ይሠራል።  የእሱ ታናናሾችንም ያስተምራል። በዩቲዩብ እና ቲክ ቶክ ላይ የሙዝር እና የዜማ መሳሪያ አጨዋወትን የሚያሳይ ቪዲዮም ይጭናል።

የዮሐንስ ሥራ ብዙ ነው።  ከድምጽ ማጉያው ፊት ቆሞ ምዕመናኑን የሚመስጥ ዜማ ያሰማል። ያ ድምጽ ማጉያ እክል ቢገጥመው ዮሐንስ ይጠግነዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥየቴክኒክ ችግርካጋጠመ ዮሐንስ አለ። ለዚያ ነው አቶ ዓለማየሁ የዲያቆን የሐንስ ተግባርከሚጠበቀው በላይ ነውየሚሉት።

በጣም ትሁት ነው። ሲታዘዝእሺ፣ ወዴት እንጂ ማን ያዘኛል?’ የሚል ነገር የለውምየሚሉት አቶ ዓለማየሁዮሐንስ [በግዕዝ እና በአማርኛ] ዳዊት፣ ወንጌልና መልዕክቶችን ሲያነብ ብዙ ኢትዮጵያውያን በጣም ይጸጸታሉ።ልጆቻችንን እኛ ሳናስተምር። እሱ ከሌላ ቋንቋ መጥቶ እንዲህ አይነት አገልግሎት ሲሰጥ በራሳችን እናፍራለንይሉናልይላሉ።

በአውሮፕላን ቴክኒሺያንነት የተመረቀ ሲሆን ካልጋሪ በሚገኝ አንድ የአውሮፕላን ኩባንያ እየሠራ ይገኛል። በትምህርቱም የተመሰገነ ነው።  ዮሐንስ ስለ ቤተክርስቲያኑ ሲናገርየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ካልኖርክበት አትረዳውም. . . እኔ እዚያ ነው ያደግኩት። ሁልጊዜ በየሳምንቱ እሄዳለሁ። የሳምንቱን ጉልበት የማገኘው ከቤተ ክርስቲያን ነውይላል።

“ዮሐንስ  የሶስት ዓመት ልጅ እያለ [አባቱ] ትንሽ ከበሮ ሰርቶለት ሁልጊዜ ከፊት ቆሞ ይዘምር ነበር”

 

 

 

 

 

 

 

የፎቶው ባለመብት, Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ,  ዮሐንስ የሦስት ዓመት ልጅ እያለ [አባቱ] ትንሽ ከበሮ ሰርቶለት ሁልጊዜ ከፊት ቆሞ ይዘምር ነበርአሁን በሥራ ምክንያት ካደገበት ቤተ ክርስቲያን ቢርቅም አገልግሎቱ ግን እንደሚቀጥል ይጠቅሳል።

በምችለው መጠን ቤተ ክርስቲያንን አገለግላለሁ። እርግጠኛ ነኝ ፈጣሪ ለእኔ ያለው ነገር አለ። ማን ያውቃል? ካህን ወይም መነኩሴ እንድሆን ይፈልግ ይሆናል። ዲያቆን የሆንኩት ራሱ በእኔ ዕቅድ አይደለም። በእሱ ዕቅድ እና ባዘጋጀልኝ ነገር እምነት አለኝብሏል።  የንግሥተ ሳባን ታሪክ እጅግ እንደሚወዱት የሚናገሩት ቀሲሱ፣ በንግሥቲቱ ሌላኛው ስም የመጨረሻዋን ልጃቸውንማክዳብለዋታል።  በጥርስ ሕክምና የተመረቀችው ማክዳ በዘማሪነት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታገለግላለች።  በግዕዝ እና አማርኛ ቋንቋዎችም ትዘምራለች።

የፎቶው ባለመብት, Alemayhu Zenebe

የምስሉ መግለጫ,  ዲያቆን ዮሐንስ አሎንዞ

ቤተሰቦቼ አእምሮዬ የታመመ መስሏቸው ነበር

ቀሲስ ዳንቴ ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ቤተሰቦቻቸውን ለማሳመንእጅግ አስቸጋሪጊዜያትን አሳልፈዋል። እኔ እውነቱ ሲገለጥልኝ እነሱ በተሳሳተ መንገድ ነበር የተረዱኝ። ያበድኩ መስሏቸው ነበር። ጤነኛ እንደሆንኩ ለማረጋገጥ ከመካከላቸው አስቀምጠው ያዋሩኝ ነበር። እንዴት እንደምመልስ፣ እንዴት እንደማወራ ይከታተሉኝ ነበር። በሁለተኛው ጊዜ ደግሞ እኔን ለመርዳት የአእምሮ ጤና ባለሙያ ጋር ደወሉይላሉ።

ቀጥለውቤተሰቦቼ ጃማይካውያኑ ጓደኞቼ የምበላው ምግብ ውስጥ የሆነ ነገር ያደረጉብኝ ነበር የመሰላቸውብለዋል። ነገሩ ካለፈ በኋላ እናታቸው ለቤተሰቦቻቸው የነገሩትን ለዳንቴ ነግረዋቸዋል። እናቴ ለቤተሰቡወንድማችሁ አላበደም። በራሱ ለሕይወቱ እጅግ አስፈላጊ የሆነውና የሚያስደሰተውን ነገር አግኝቷል። ከዚህ ነገር ልታላቅቁት አትቸሉምብላቸዋለችሲሉ ይገልጻሉ።

ቢሆንም እህት እና ወንድሞች አልተስማሙም። በተለይ ከታላቅ ወንድማቸው ከባድ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ብዙ ውይይት እና ክርክር ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። የተቀየረ ነገር አልነበረም። ሃይማኖት የግል ነውበሚል ቤተሳባዊነቱ ቀጠለ።

እኔ የእነሱን ምርጫ አክበራለሁ፤ እነሱም የእኔን ያከብራሉሲሉ ጠቅሰዋል። የፊሊፒንስ እና የካናዳ ጥምር ዜግነት ያላቸው ቀሲስ ዳንቴ የተከበሩ የእጅ ባለሙያ ናቸው። በኢንዱስትሪ ውስጥ ብረቶችን ቅርጽ እያወጡ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ያውላሉ።

አባቴ በቤተ ክርስቲያን ካለው አገልግሎት ባሻገር እጅግ ጎበዝ የእጅ ባለሙያ ነው። ሥራውን ጠንቅቆ ያውቃል። ጥሩ የፈጠራ ችሎታ አለውይላል ዲያቆን ዮሐንስ። በትውልድ አገራቸው ፊሊፒንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማስገንባት ዕቅድም አላቸው።

ዕቅድ ብቻ ሳይሆን ሥራ ጀምረዋል። 10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ቤተክርስቲያን ለማስገንባት የሚሆን መሬት በግላቸው ገዝተዋል።  በአገሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ማስተዋወቅ እፈልጋለሁ። ሰዎች በዚያ እንዲያመልኩ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲመጡ እፈልጋለሁይላሉ።

ልጃቸው ዮሐንስአባቴ ለሐይማኖታችን እጅግ ታማኝ እና ትጉህ ነውሲል አቶ ዓለማየሁ የዳንቴ ቤተሰብየክርስቶስን መንገድ የተከተሉ ናቸውሲሉ መስክረውላቸዋል። 

ወደ ኢትዮጵያ ዳግም የመመለስ ሀሳብ እንዳላቸው እና አማርኛ መማር እንደሚፈልጉ የሚገልጹት ቀሲስ ዳንቴ ደግሞበኢትዮጵያም ይሁን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ፈተና እንዳለ አውቃለሁ። ምንም ቢሆን ኢትዮጵያ የእኔ ዕጣ ፈንታ ነች። ለኢትዮጵያ ያለኝ ፍቅር መቼም አይቀየርምብለዋል።

 

ረቡዕ 15 ማርች 2023

ወግ “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.19፥12

 

 “ ስህተትን ማን ያስተውላታል” መዝ.1912

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ትምህርት በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለማየት ገና ልዑል አልጋወራሽ ሆነው እያለ በገንዘባቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን አሠርተው ሚያዚያ 17 ቀን 1917 ዓ/ም አስመርቀዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን ይኖሩበት የነበረውን ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስትን ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን በመስጠት እና  የግል ገንዘባቸውን ማቋቋሚያ እንዲሆን በማርክት ሚያዚያ 27 ቀን 1952 ዓ/ም ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት፤ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን ፤ከቤተ መንግስት ቀለብ እየተሰፈረ በልዩ እንክብካቤ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ጎበዝ ተማሪዎች ይማሩበታል፡፡ ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ከአውሮፓ እና አሜሪካን የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ፡፡ አስተማሪዎቹ የቀለም ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ የካቶሊክ ዕምነትን ለማስፋፋት የሚሲኦናዊ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተማሪዎች ባደረጉት ክትትል ደረሱባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ይህ መረጃ ሲደረሳቸው የኢየሱሳዊያኑን እንቅስቃሴ የሚያጠና ሕቡ ማኅበር በማቋቋም ክትትል ጀመሩ፡፡ ማኅበሩ ጉዳዩን በማጥናት ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ፤ ለጠቅላይ ቤተ-ክህነት አሳውቀው፤ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ሊቃውንትን ሰብስበው ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተጋረጠውን ፈተና በማስረዳት ጉባኤውን በዕንባ አራጩት፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት ተመሳሳይ ውይይት እንዲደረግ ጉባኤው ወስኖ ተበተነ፡፡

ከጉባኤው በኋላ ወዲያውኑ የማኅበሩ ምሥጢር እየሾለከ በመውጣቱ ዋና ዋናዎቹ የማኅበሩ መሪዎች ታሰሩ፡፡ ተማሪዎች ከተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ታገዱ፤ ገሚሶቹም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ፡፡ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ማስፈራሪያና ቅጣት ለሃይማኖታቸው ጠበቃ ከመሆን ሳያግዳቸው፤ በተዘዋወሩበት ትምህርት ቤትም ቅርንጫፍ ማኅበር በማቋቋም ማህበሩን ከበፊቱ የበለጠ አጠናከሩ፡፡

በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የቀሩት ተማሪዎች ግን ስለብዙ ምክንያት የተማሪዎች አድማ እንዲቀሰቀስ አደረጉ፡፡ በተማሪዎቹም አመጽ ትምህርት ተቋረጠ ንብረት ወደመ፡፡ ብጥብጡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ከቤተ መንግስት አባ ሐና ጂማና ተልከው ተማሪዎቹን አነጋገሩ፤አድማው ግን ሊበርድ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም አድማው ሊረግብ የቻለው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በመገኘት ተግሳጽ እና ምክር በመስጠታቸው ነበር፡፡

ንጉሡ በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ራሳቸውን የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ከራሳቸው ገንዘብ እና ንብረት ወጪ በማውጣት ለሌት ተቀን ይጥሩ ነበር፡፡ ይህን ምኞታቸውን እና ተስፋቸውን የሚያሰናክል ተግባር ተማሪዎች በመፈጸማቸው አዘኑ እጅግም ተቆጡ፡፡ ተማሪዎቹም በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው የአድማቸውን ምክንያት ማስረዳት ጀመሩ፡፡ የተማሪዎቹ የተወረጠ ተወካይ በንጉሡ ፊት የአድማውን ምክንያት በዝርዝር ያስረዳ ጀመር፡፡ ንጉሡ በሆነው ነገር ተበሳጭተው የሚናገረውን ተማሪ በጥፊ መቱት፡፡ የንጉሡን ጥፊ የቀመሰው ተማሪ ሌላውን ያልተመታው ሁለተኛ ጉንጩን አመቻችቶ ሰጣቸው፡፡ ንጉሡም በሁኔታው ተደናግጠው በድጋሚ ለመማታት የሰነዘሩት እጃቸውን ለመሰብሰብ ተገደዱ፡፡

ተማሪው ከሁሉም ነገር በላይ ሃይማኖቴ ይበልጣል በማለቱ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ “እኔ ግን እላችኋለው ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩግን ቀኝ ጉጭህን በጥፊ ለሚመታ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙሩለት፡፡”ማቴ.5፥39 “ጉንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ሥጠው፤መጎናጸፊያውንም ለሚወስድብህ እጀጠባብህን ደግሞ አትከልክለው” ሉቃ.6፥29 የሚለውን የወንጌል ቃል በንጉሡ ፊት ፈጸመው፡፡

በዚያን ወቅት የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ለማንቃት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች መፈጠር እና መስፋፋት፣ ምስካዬ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር እንዲመሰረቱ ምክንያት መሆኑን ጀጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ ሕይወቴ በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈውልናል፡፡

ወዳጄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተማሪው በፈጸመው መንፈሳዊ ተግባር ደንግጠው ትምህርት ወስደው እጃቸውን በድጋሚ ሊፈጽሙት ከነበረው የኃይል ተግባር እንዲቆጠብ አድርገዋል፡፡ ሁለተኛውን ጉንጩን ሰጥቶኛል ምን ያመጣል ብለው ጥፊያቸውን ሳይደግሙት ፤ በዙሪያቸው ባሉት  የሃይማኖት አባቶች መኮንንቱ እና መሳፍንቱ ፊት የንጉሡን ክብር የሚቀንስ ስህት ከመሥራት ተቆጥበዋል፡፡ የዚያን ሰሞን ይህ ክስተት በተማሪዎቹ እና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ሲወራ ሰነበተ፤ ንጉሡም በጥቁር መዝገብ ጥቁር ታሪክ ሳይጽፍ በጣም ካበሳጫቸው ተማሪ ትምህርት ወሰዱ፡፡

በየትኛውም ከፍታ ቦታ ብንሆን፣ ሥልጣን እና ጉልበት ቢኖረንም ፣በአጠገባችን በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ትምህርት የምንወስድ ከሆነ ፤ ከዳግማዊ ስህተት እንጠበቃለን፡፡ ከ እኛ ዙፋን በታች የሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ እኛን ከስህተት የመጠበቅ አቅም የማስተማርም ዕድል አላቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሜት በስህተት እጃችንን ሰንዝረን ከሆነ ጥፋታችንን እንዳንደግመው አስተማሪ ካገኘን ፣ካደመጥንም ከ ከባዱ ሁለተኛው ሥህተት እንተርፋለን፡፡ ታስቦሙ ይሁን በድንገት ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ቶሎ ትምህርት መውሰድ እና ራስን ማስተካከል ብልህነት ነው፡፡

በዓለማችን ላይ እንደምንመለከተው ብዙ ነገሥታት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ ብዙ አስተማሪ ክስተቶች በተደጋጋሚ ቢፈጠሩም፤ልባቸው ደንድኖ ትምህርት መውሰድ ሲያቅታቸው እንመለከታለን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ የጻፈው ቃልም ይህን ያሳያል “ ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፍ ነገር አለ፤ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፡፡” መክብብ.10፥5  ወዳጄ ስህተቱን አውቆ የሚያርም ሰው አስተዋይ ነው!

ያዕቆብ ሰንደቁ  

መጋቢት 2 ቀን  2015ዓ/ም

አዲስ አበባ

ቴሌግራም https://t.me/MaedotYakobSendekupage

የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርስ  ፔጁን Like Share Comment ያድርጉ::

ዓርብ 10 ማርች 2023

ወግ “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ”

 

 “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ”

በቅርቡ ናጄሪያ ውስጥ አንድ የሃይማኖት ተቋም ለአምልኮ ሥፍራ ግንባታ እያካሄደ እያለ የተሾመው አገልጋይ ሲሚንቶውን፣ ብረቱን እየወሰደ ገንዘቡን እመዘበረ የራሱን ቤት ይሠራል፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች አዝነው ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ያደርጉታል፡፡

 ይህን መጥፎ ምግባር አምርሮ ይጠላ የነበረ ሌላ አገልጋይ ይሾማል፡፡ የተሾመው አዲስ አገልጋይ የአምልኮ ቦታውን ግንባታ መጎተቱን አይቶ ሥራውን ያፋጥናል፤ ሙስናንም ይጠየፋል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ አገልጋዩም ሥራውን ከተቀበለ ወራት አለፈ፡፡ የአምልኮ ቦታው ግንባታ ግን ጭራሹኑ ቆመ፡፡

አዲሱ ተሾሚ አገልጋይ ለግንባታ በተመደበው በጀት በውድ ዋጋ መሀል ከተማ መሬት ገዝቶ ባለ አራት ፎቅ ቤት ለራሱ መሥራት ጀመረ፡፡ በፍጥነት ብቅል ያለው ሕንጻ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ አገልጋዩም ሲሚንቶውን፣ ብረቱንም ቁሳቁሱንም እየወሰደ የራሱን ቤት መገንባቱን አፋጠነው፡፡

ሁኔታውን ያዩት አማኞች “ገንዘባችን ተዘረፈ የባሰው መጣብን” ብለው ጮሁ፡፡ ከዚያም ስብሰባ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ አገልጋዩንም ጠርተው “የአምልኮ ቤታችንን ግንባታ አቁመህ የራስህን ቤት ሠራህ ኃላፊነትህ አስረክቡ” ብለው ጮሁበት፡፡ አገልጋዩም ሰውን ሳያፍር ፈጣሪን ሳይፈራ በኩራት “የመጣው ይመጣል እንጂ በፍጹም አገልግሎቴን አልተውም ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ሕዝቡም አጥብቆ “ገንዘባችን ዘርፈሀል በፍጥነት ልቀቅ ” ብለ ተቆጡ፡፡

አገልጋዩም የነገሩን መጋጋል አይቶ “እባካችሁ በፈጣሪ ስም እለምናችኋለው የጀመርኩትን ፎቅ ቤት እስክጨርስ ድረስ ታገሱኝ፤ ከዚያ አገልግሎቴን አቆማለው” ብሎ አረፈው፡፡ ሕዝቡም “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ሠራህ” ብለው ጉዳዩን ወደ ሕግ ወሰዱት፡፡

“ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት”

በአንድ አፍሪካ ሀገር የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት የሚሠራ የእቃ ግዥ ባለሙያ ነበር፡፡ ግብረሰናይ ድርጅቱ ዋና መሥሪያቤቱን ሲገነባ፤ የግንባታ ቁሳቁስ እንዲገዛ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ግንባታው ቶሎ እንዲጠናቀቅ በጀት ተመደበለት፡፡ ነገርግን ሥራው ሊፋጠን አልቻለም፡፡

የግዥ ባለሙያ የሚከፈለው መጠነኛ ደመወዝ ቢሆንም በሥራው ግን ትጉህ ነው፡፡ መቼም ወሬ አይደበቅም አይደል “ቤት እየሰራ ነው” ተብሎ ይወራል፤ እናም አጅሬው ከመሥሪያቤቱ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የጀመረውን የራሱን ቤት ግንባታ፤ አጣድፎ ይሠራ ጀመር፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በሙሉ መብራት፣ ሶኬት፣ መዝጊያ፣የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች፣ታይልስ፣ ሴራሚክ፣ የግድግዳ ቀለም፣ ምንጣፍ ፣ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ጌጣጌጥ ብቻ የቀረ ነገር የለም “ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት” በሚል መርህ ቤቱን በአጭር ጊዜ አሳምሮ ሠራው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ሰውዬው ይግረማችሁ ብሎ አዲሱን ቤት ለማስመረቅ ተዘጋጀ፡፡

የቤቱን ምርቃት አስመልክቶ ድግስ ደግሶ ሰው አላበዛም በማለት የመሥሪያቤቱ ባልደረቦቹን እና የሥራ ኃላፊዎችን ብቻ የድግሱ ታዳሚ አደረጋቸው፡፡ እንግዶቹን ጠርቶ ሳይፈራ ሳያፍር በሙሉ ልብ የሠራውን አዲስ ቤት እየዞረ አስጎኛቸው፡፡ ሠራተኞቹ እና የሥራ ኃላፊዎቹ በነገሩ ተገርመው ፊታቸው ቀላ፣ናላቸው ተበጠበጠ፡፡

 ከመካከላቸው አንዱ የሥራ ኃላፊ በቁጣ “ለካ የዋናው መሥሪያቤት ግንባታ የዘገየው ቅርንጫፉ እየተሠራ ነው” አለ፡፡ ቀጠለ በቁጣ ንግግር “የተጠራነው ለቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን ምርቃት ነው ማለት ነው ብሎ ጠየቀ ? የግዥ ባለሙያ ትንሽ እፍረት እንኳን ሳይሰማው ፈገግ እያለ ማስጎብኘቱን ቀጠለ፡፡ ሌላው ሠራተኛ ደግሞ “ይህ እኮ የአንተ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ሁሉ ነገሩ የግብረሰናይ ድርጅቱ ነው፤ የግድግዳው ቀለም እንኳን የመስሪያቤታችን ጋር ተመሳሳይ ነው ”አለ በንዴት፡፡ ሌሎቹም ሰዎች “በፍጥነት እና በጥራት ተገንብቶ ያለቀውን ቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን በመመረቃችን ተደስተናል ብለው በምጸት ቀልደው እርፍ አሉ፡፡

የግዥ ባለሙያው በማግስቱ ጠዋት ሥራ ሲገባ የስንብት ደብዳቤ እና የፖሊስ ምርመራ መጥሪያ ተሰጠው፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት የተቀበለውን ደብዳቤ ይዞ ራሱ ወደ ገነባው ቅርንጫፍ መሥሪያቤት  ወደ ሆነው አዲሱ መኖሪያ ቤቱ ሄደ፡፡

ወዳጄ ! እንዚህን ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ቦታቸው የተለያየ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ፤ ሥራቸው ደግሞ አገልጋይ እና ደሞዝተኛ፤ ምን ትላቸዋለህ ?

 

 

 

 

ይህን ሐሳብ እንወያይበት

 

ከመጣብን ፈተና ምን አተረፍን ?

ጥር 14 ቀን ጠዋት የሰማነው ዜና የቤተክርስቲያን ፈተና ነበር፡፡ አይምጣብን አይባል ነገር ለብዙዎች ያልተጠበቀ የቤተክርስቲያን ሕልውና ላይ የተጋረጠ ፈተና፡፡ “ሳይደግስ አይጣልም ” እንዲሉ የነነዌ ሰዎች ጾም በመካከል በመኖሩ የመጣውን ፈተና ለማሽነፍ ማቅ ለብሰን እንባችን እንደ ጎርፍ እያወረድን የሐዘናችን ጥግ ለመግለጽ ጸጉራችንን ተላጭተን፣ ጥቁር ለብሰን “ አቤቱ አድነን ልንጠፋነው” ብለን ጮህን፡፡

ፈተናው ጠንክሮ ብዙዎች በአደባባይ አንድ ሲኖዶስ ብለው መሰከሩ፡፡ ቤተመቅደስ ተደፈረ ሰዎች ሞተው ሰማዕትነትን ተቋናጁ ደማቸውን አፈሰሱ ቆሰሉ፣ ታሰሩ ከቤተ-ክርስቲያን ጎን ቆሙ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም የምስራች ሰማን፤ የሐዘናችን ደመና ተገፎ ፀሐይ ወጣ ችግሩ በሰላም ተፈታ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሳትከፋፈል በአንድነቷ ፀናች፡፡

ይህ ፈተና የመጣው ለምን ይሆን ? አንድም ለቅጣት፣ አንድም ለትምህርት ብቻ ስለ ብዙ ምክንያት ነው ብለን እንለፈው፡፡ በመጣብን ታላቅ ፈተና ምን ትምህርት ወስደን ? ምንስ ትርፍ አግኝተን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነው፡፡

አዎ በቤተክርስቲያን ላይ በመጣው ፈተና ምን አተረፍን ? ምን ፀጋና በረከት አገኘን ?  እንወያይበት፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ፈተና ምን አተረፈች?

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ-ክርስቲያን ምን አተረፈች?

ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቋሚ ሲኖዶስ ምን አተረፉ?

ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ምን አተረፈ?

እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምን አተረፈ?

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምን አተረፉ?

በሀገር ውስጥም በውጭውም ሀገር ያሉ አገልጋዮች ምን አተረፉ?

እያንዳንዱ ክርስቲያንስ በግል መንፈሳዊ ሕይወቱ ምን አትርፎበት ይሆን?

ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያልሆኑ ሰዎችስ ይህን ፈተና አይተው ሰምተው ምን አትርፈውበት ይሆን ?  እንወያይበት!