ረቡዕ 15 ማርች 2023

ስህተትን ማን ያስተውላታል፡፡

 

ስህተትን ማን ያስተውላታልመዝ.1912

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ትምህርት በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለማየት ገና ልዑል አልጋወራሽ ሆነው እያለ በገንዘባቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን አሠርተው ሚያዚያ 17 ቀን 1917 / አስመርቀዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን ይኖሩበት የነበረውን ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስትን ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን በመስጠት እና  የግል ገንዘባቸውን ማቋቋሚያ እንዲሆን በማርክት ሚያዚያ 27 ቀን 1952 / ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት፤ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን ፤ከቤተ መንግስት ቀለብ እየተሰፈረ በልዩ እንክብካቤ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ጎበዝ ተማሪዎች ይማሩበታል፡፡ ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ከአውሮፓ እና አሜሪካን የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ፡፡ አስተማሪዎቹ የቀለም ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ የካቶሊክ ዕምነትን ለማስፋፋት የሚሲኦናዊ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተማሪዎች ባደረጉት ክትትል ደረሱባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ይህ መረጃ ሲደረሳቸው የኢየሱሳዊያኑን እንቅስቃሴ የሚያጠና ሕቡ ማኅበር በማቋቋም ክትትል ጀመሩ፡፡ ማኅበሩ ጉዳዩን በማጥናት ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ፤ ለጠቅላይ ቤተ-ክህነት አሳውቀው፤ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ሊቃውንትን ሰብስበው ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተጋረጠውን ፈተና በማስረዳት ጉባኤውን በዕንባ አራጩት፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት ተመሳሳይ ውይይት እንዲደረግ ጉባኤው ወስኖ ተበተነ፡፡

ከጉባኤው በኋላ ወዲያውኑ የማኅበሩ ምሥጢር እየሾለከ በመውጣቱ ዋና ዋናዎቹ የማኅበሩ መሪዎች ታሰሩ፡፡ ተማሪዎች ከተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ታገዱ፤ ገሚሶቹም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ፡፡ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ማስፈራሪያና ቅጣት ለሃይማኖታቸው ጠበቃ ከመሆን ሳያግዳቸው፤ በተዘዋወሩበት ትምህርት ቤትም ቅርንጫፍ ማኅበር በማቋቋም ማህበሩን ከበፊቱ የበለጠ አጠናከሩ፡፡

በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የቀሩት ተማሪዎች ግን ስለብዙ ምክንያት የተማሪዎች አድማ እንዲቀሰቀስ አደረጉ፡፡ በተማሪዎቹም አመጽ ትምህርት ተቋረጠ ንብረት ወደመ፡፡ ብጥብጡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ከቤተ መንግስት አባ ሐና ጂማና ተልከው ተማሪዎቹን አነጋገሩ፤አድማው ግን ሊበርድ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም አድማው ሊረግብ የቻለው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በመገኘት ተግሳጽ እና ምክር በመስጠታቸው ነበር፡፡

ንጉሡ በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ራሳቸውን የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ከራሳቸው ገንዘብ እና ንብረት ወጪ በማውጣት ለሌት ተቀን ይጥሩ ነበር፡፡ ይህን ምኞታቸውን እና ተስፋቸውን የሚያሰናክል ተግባር ተማሪዎች በመፈጸማቸው አዘኑ እጅግም ተቆጡ፡፡ ተማሪዎቹም በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው የአድማቸውን ምክንያት ማስረዳት ጀመሩ፡፡ የተማሪዎቹ የተወረጠ ተወካይ በንጉሡ ፊት የአድማውን ምክንያት በዝርዝር ያስረዳ ጀመር፡፡ ንጉሡ በሆነው ነገር ተበሳጭተው የሚናገረውን ተማሪ በጥፊ መቱት፡፡ የንጉሡን ጥፊ የቀመሰው ተማሪ ሌላውን ያልተመታው ሁለተኛ ጉንጩን አመቻችቶ ሰጣቸው፡፡ ንጉሡም በሁኔታው ተደናግጠው በድጋሚ ለመማታት የሰነዘሩት እጃቸውን ለመሰብሰብ ተገደዱ፡፡

ተማሪው ከሁሉም ነገር በላይ ሃይማኖቴ ይበልጣል በማለቱ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ እኔ ግን እላችኋለው ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩግን ቀኝ ጉጭህን በጥፊ ለሚመታ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙሩለት፡፡ማቴ.539 ጉንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ሥጠው፤መጎናጸፊያውንም ለሚወስድብህ እጀጠባብህን ደግሞ አትከልክለው ሉቃ.629 የሚለውን የወንጌል ቃል በንጉሡ ፊት ፈጸመው፡፡

በዚያን ወቅት የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ለማንቃት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች መፈጠር እና መስፋፋት፣ ምስካዬ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር እንዲመሰረቱ ምክንያት መሆኑን ጀጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ ሕይወቴ በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈውልናል፡፡

ወዳጄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተማሪው በፈጸመው መንፈሳዊ ተግባር ደንግጠው ትምህርት ወስደው እጃቸውን በድጋሚ ሊፈጽሙት ከነበረው የኃይል ተግባር እንዲቆጠብ አድርገዋል፡፡ ሁለተኛውን ጉንጩን ሰጥቶኛል ምን ያመጣል ብለው ጥፊያቸውን ሳይደግሙት በዙሪያቸው ባሉት  የሃይማኖት አባቶች መኮንንቱ እና መሳፍንቱ ፊት የንጉሡን ክብር የሚቀንስ ስህት ከመሥራት ተቆጥበዋል፡፡ የዚያን ሰሞን ይህ ክስተት በተማሪዎቹ እና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ሲወራ ሰነበተ፤ ንጉሡም በጥቁር መዝገብ ጥቁር ታሪክ ሳይጽፍ በጣም ካበሳጫቸው ተማሪ ትምህርት ወሰዱ፡፡

በየትኛውም ከፍታ ቦታ ብንሆን፣ ሥልጣን እና ጉልበት ቢኖረንም ፣በአጠገባችን በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ትምህርት የምንወስድ ከሆነ ከዳግማዊ ስህተት እንጠበቃለን፡፡ እኛ ዙፋን በታች የሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ እኛን ከስህተት የመጠበቅ አቅም የማስተማርም ዕድል አላቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሜት በስህተት እጃችንን ሰንዝረን ከሆነ ጥፋታችንን እንዳንደግመው አስተማሪ ካገኘን ፣ካደመጥንም ከባዱ ሁለተኛው ሥህተት እንተርፋለን፡፡ ታስቦሙ ይሁን በድንገት ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ቶሎ ትምህርት መውሰድ እና ራስን ማስተካከል ብልህነት ነው፡፡

በዓለማችን ላይ እንደምንመለከተው ብዙ ነገሥታት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ ብዙ አስተማሪ ክስተቶች በተደጋጋሚ ቢፈጠሩም፤ልባቸው ደንድኖ ትምህርት መውሰድ ሲያቅታቸው እንመለከታለን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ የጻፈው ቃልም ይህን ያሳያል ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፍ ነገር አለ፤ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፡፡ መክብብ.105  ወዳጄ ስህተቱን አውቆ የሚያርም ሰው አስተዋይ ነው!

ያዕቆብ ሰንደቁ  

መጋቢት 2 ቀን  2015/

አዲስ አበባ

ቴሌግራም https://t.me/MaedotYakobSendekupage

የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርስ  ፔጁን Like Share Comment ያድርጉ::

 

ዓርብ 10 ማርች 2023

እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል

 

 “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ”

በቅርቡ ናጄሪያ ውስጥ አንድ የሃይማኖት ተቋም ለአምልኮ ሥፍራ ግንባታ እያካሄደ እያለ የተሾመው አገልጋይ ሲሚንቶውን፣ ብረቱን እየወሰደ ገንዘቡን እመዘበረ የራሱን ቤት ይሠራል፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች አዝነው ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ያደርጉታል፡፡

 ይህን መጥፎ ምግባር አምርሮ ይጠላ የነበረ ሌላ አገልጋይ ይሾማል፡፡ የተሾመው አዲስ አገልጋይ የአምልኮ ቦታውን ግንባታ መጎተቱን አይቶ ሥራውን ያፋጥናል፤ ሙስናንም ይጠየፋል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ አገልጋዩም ሥራውን ከተቀበለ ወራት አለፈ፡፡ የአምልኮ ቦታው ግንባታ ግን ጭራሹኑ ቆመ፡፡

አዲሱ ተሾሚ አገልጋይ ለግንባታ በተመደበው በጀት በውድ ዋጋ መሀል ከተማ መሬት ገዝቶ ባለ አራት ፎቅ ቤት ለራሱ መሥራት ጀመረ፡፡ በፍጥነት ብቅል ያለው ሕንጻ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ አገልጋዩም ሲሚንቶውን፣ ብረቱንም ቁሳቁሱንም እየወሰደ የራሱን ቤት መገንባቱን አፋጠነው፡፡

ሁኔታውን ያዩት አማኞች “ገንዘባችን ተዘረፈ የባሰው መጣብን” ብለው ጮሁ፡፡ ከዚያም ስብሰባ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ አገልጋዩንም ጠርተው “የአምልኮ ቤታችንን ግንባታ አቁመህ የራስህን ቤት ሠራህ ኃላፊነትህ አስረክቡ” ብለው ጮሁበት፡፡ አገልጋዩም ሰውን ሳያፍር ፈጣሪን ሳይፈራ በኩራት “የመጣው ይመጣል እንጂ በፍጹም አገልግሎቴን አልተውም ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ሕዝቡም አጥብቆ “ገንዘባችን ዘርፈሀል በፍጥነት ልቀቅ ” ብለ ተቆጡ፡፡

አገልጋዩም የነገሩን መጋጋል አይቶ “እባካችሁ በፈጣሪ ስም እለምናችኋለው የጀመርኩትን ፎቅ ቤት እስክጨርስ ድረስ ታገሱኝ፤ ከዚያ አገልግሎቴን አቆማለው” ብሎ አረፈው፡፡ ሕዝቡም “እኛ የሰማይ ቤታችንን ትሠራልናለህ ስንል፤ አንተ ግን ኃላፊውን ቤት ሠራህ” ብለው ጉዳዩን ወደ ሕግ ወሰዱት፡፡

“ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት”

በአንድ አፍሪካ ሀገር የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት የሚሠራ የእቃ ግዥ ባለሙያ ነበር፡፡ ግብረሰናይ ድርጅቱ ዋና መሥሪያቤቱን ሲገነባ፤ የግንባታ ቁሳቁስ እንዲገዛ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ግንባታው ቶሎ እንዲጠናቀቅ በጀት ተመደበለት፡፡ ነገርግን ሥራው ሊፋጠን አልቻለም፡፡

የግዥ ባለሙያ የሚከፈለው መጠነኛ ደመወዝ ቢሆንም በሥራው ግን ትጉህ ነው፡፡ መቼም ወሬ አይደበቅም አይደል “ቤት እየሰራ ነው” ተብሎ ይወራል፤ እናም አጅሬው ከመሥሪያቤቱ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የጀመረውን የራሱን ቤት ግንባታ፤ አጣድፎ ይሠራ ጀመር፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በሙሉ መብራት፣ ሶኬት፣ መዝጊያ፣የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች፣ታይልስ፣ ሴራሚክ፣ የግድግዳ ቀለም፣ ምንጣፍ ፣ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ጌጣጌጥ ብቻ የቀረ ነገር የለም “ሁሉንም ነገር ከመሥሪያ ቤት” በሚል መርህ ቤቱን በአጭር ጊዜ አሳምሮ ሠራው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ሰውዬው ይግረማችሁ ብሎ አዲሱን ቤት ለማስመረቅ ተዘጋጀ፡፡

የቤቱን ምርቃት አስመልክቶ ድግስ ደግሶ ሰው አላበዛም በማለት የመሥሪያቤቱ ባልደረቦቹን እና የሥራ ኃላፊዎችን ብቻ የድግሱ ታዳሚ አደረጋቸው፡፡ እንግዶቹን ጠርቶ ሳይፈራ ሳያፍር በሙሉ ልብ የሠራውን አዲስ ቤት እየዞረ አስጎኛቸው፡፡ ሠራተኞቹ እና የሥራ ኃላፊዎቹ በነገሩ ተገርመው ፊታቸው ቀላ፣ናላቸው ተበጠበጠ፡፡

 ከመካከላቸው አንዱ የሥራ ኃላፊ በቁጣ “ለካ የዋናው መሥሪያቤት ግንባታ የዘገየው ቅርንጫፉ እየተሠራ ነው” አለ፡፡ ቀጠለ በቁጣ ንግግር “የተጠራነው ለቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን ምርቃት ነው ማለት ነው ብሎ ጠየቀ ? የግዥ ባለሙያ ትንሽ እፍረት እንኳን ሳይሰማው ፈገግ እያለ ማስጎብኘቱን ቀጠለ፡፡ ሌላው ሠራተኛ ደግሞ “ይህ እኮ የአንተ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ሁሉ ነገሩ የግብረሰናይ ድርጅቱ ነው፤ የግድግዳው ቀለም እንኳን የመስሪያቤታችን ጋር ተመሳሳይ ነው ”አለ በንዴት፡፡ ሌሎቹም ሰዎች “በፍጥነት እና በጥራት ተገንብቶ ያለቀውን ቅርንጫፍ መሥሪያቤታችን በመመረቃችን ተደስተናል ብለው በምጸት ቀልደው እርፍ አሉ፡፡

የግዥ ባለሙያው በማግስቱ ጠዋት ሥራ ሲገባ የስንብት ደብዳቤ እና የፖሊስ ምርመራ መጥሪያ ተሰጠው፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት የተቀበለውን ደብዳቤ ይዞ ራሱ ወደ ገነባው ቅርንጫፍ መሥሪያቤት  ወደ ሆነው አዲሱ መኖሪያ ቤቱ ሄደ፡፡

ወዳጄ ! እንዚህን ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ቦታቸው የተለያየ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ፤ ሥራቸው ደግሞ አገልጋይ እና ደሞዝተኛ፤ ምን ትላቸዋለህ ?

 

 

 

 

ከመጣብን ፈተና ምን አተረፍን ?

 

ከመጣብን ፈተና ምን አተረፍን ?

ጥር 14 ቀን ጠዋት የሰማነው ዜና የቤተክርስቲያን ፈተና ነበር፡፡ አይምጣብን አይባል ነገር ለብዙዎች ያልተጠበቀ የቤተክርስቲያን ሕልውና ላይ የተጋረጠ ፈተና፡፡ “ሳይደግስ አይጣልም ” እንዲሉ የነነዌ ሰዎች ጾም በመካከል በመኖሩ የመጣውን ፈተና ለማሽነፍ ማቅ ለብሰን እንባችን እንደ ጎርፍ እያወረድን የሐዘናችን ጥግ ለመግለጽ ጸጉራችንን ተላጭተን፣ ጥቁር ለብሰን “ አቤቱ አድነን ልንጠፋነው” ብለን ጮህን፡፡

ፈተናው ጠንክሮ ብዙዎች በአደባባይ አንድ ሲኖዶስ ብለው መሰከሩ፡፡ ቤተመቅደስ ተደፈረ ሰዎች ሞተው ሰማዕትነትን ተቋናጁ ደማቸውን አፈሰሱ ቆሰሉ፣ ታሰሩ ከቤተ-ክርስቲያን ጎን ቆሙ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም የምስራች ሰማን፤ የሐዘናችን ደመና ተገፎ ፀሐይ ወጣ ችግሩ በሰላም ተፈታ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሳትከፋፈል በአንድነቷ ፀናች፡፡

ይህ ፈተና የመጣው ለምን ይሆን ? አንድም ለቅጣት፣ አንድም ለትምህርት ብቻ ስለ ብዙ ምክንያት ነው ብለን እንለፈው፡፡ በመጣብን ታላቅ ፈተና ምን ትምህርት ወስደን ? ምንስ ትርፍ አግኝተን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነው፡፡

አዎ በቤተክርስቲያን ላይ በመጣው ፈተና ምን አተረፍን ? ምን ፀጋና በረከት አገኘን ?  እንወያይበት፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ፈተና ምን አተረፈች?

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ-ክርስቲያን ምን አተረፈች?

ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቋሚ ሲኖዶስ ምን አተረፉ?

ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ምን አተረፈ?

እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምን አተረፈ?

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምን አተረፉ?

በሀገር ውስጥም በውጭውም ሀገር ያሉ አገልጋዮች ምን አተረፉ?

እያንዳንዱ ክርስቲያንስ በግል መንፈሳዊ ሕይወቱ ምን አትርፎበት ይሆን?

ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያልሆኑ ሰዎችስ ይህን ፈተና አይተው ሰምተው ምን አትርፈውበት ይሆን ?  እንወያይበት!