ረቡዕ 21 ጃንዋሪ 2026

ስብከት የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ ዮሐ. 2፣3

 የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ  ዮሐ. 23

 በ ያዕቆብ ሰንደቁ

የቃና ዘገሊላው ሠርግን

 የቃና ዘገሊላው ሠርግን የደገሰው ዶኪማስ ብዙ እንግዶች የተገኙበት ትልቅ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር።  በሰርጉም ላይ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉሥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከእናቱ ከቤዛዊተ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ߹ ከሐዋርያት ጋር  ጋበዞቸው፡፡

 ዶኪማስ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሠርጉ የጠራው በአክብሮት߹ በፍቅር እንጂ ይቸግረኛል ተአምራት ያደርግልኛል ብሎ አልነበረም፡፡ ጌታችን ከዚያ በፊት ሕዝብ ፊት ያደረገው ተአምር አልነበረም፤ የተአምራት ሁሉ መጀመሪያውን ያደረገውም በዚሁ ሰርግ ቤት ነው።

  በእስራኤል ሀገር እንኳን በሰርግቤት በአዘቦትም የወይንጠጅ መጠጣት የተለመደ ነው፡፡ በዶኪማስ ቤት ገና በሰርጉ መካከል እንግዶቹ በሚገባ ሳይስተናገዱ የወይንጠጅ ማለቁ አስደንጋጭ ሆነበት

 ዶኪማስ ሆይ እስቲ ልጠይቅህ ሰርግ ደግሰህ በተከበርክበት ሰፈር እንግዳ ጠርተህ የተወደደው ወይንጠጅ ገና በግብዣው መካከል ሲያልቅ ምን ተሰማህ? ተስፋ መቁረጥ ? ብስጨት? ድንጋጤ?

 ይህ ሀፍረት የሚያከናንብ አስደንጋጭ ክስተት አሳላፊዎችሁ አውቀውት ነገሩን ለሙሽራውም ነግረው ሳያሳቅቁት፤ በእንግድነት ለመጣችው እና ለገሊላዋ ሀገር የቃና መንደር ሰው ለሆነችው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምሥጢር ነገሯት፡፡ ይህን በደስታ መካከል የተፈጠረ ሀዘን ልጅሽ መለወጥ ይችላል ብለው አስረዷት፡፡

 የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም የሚለውን የእመቤታችንን ጥያቄ ጌታችን ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለት እውነተኛውን ዘላለማዊ ሕይወት የሚያሰጠውን የወይን ጠጅ የሚሰጥበት ሰዓት ገና መሆኑን አስረድቷታል፤ ነገርግን ለቃና ሠርግቤት ግብዣ የሚሆነውን የወይን ጠጅ እንድሰጣቸው ለአገልጋዮቹ ንገሪያቸው በማለት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ልመናዋን እንደሰማት ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ እመቤታችንም አገልጋዮቹን የሚላችሁን አድርጉ በማለት አዛቸዋለች፡፡

 አገልጋዮቹ በአይሁድ ልማድ የተዘጋጁትን የድንጋይ ጋኖች እስከ አፋቸው ውኃ እንደሞሏቸው ተደርጎ ጌታችንም  ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየር የመጀመሪያው ተአምር አደረገ፡፡ አዲሱ የወይን ጠጅ በጋኖቹ መሞላታቸውን ያወቁት አገልጋዮች ብቻ ሲሆኑ፤ አሳዳሪው ከወዴት እንደመጣ ሳያውቅ ጠዓሙን ብቻ እያደነቀ ለተጋባዦቹ እንዲቀዳ አዘዘ፡፡ ተባርኮ በተሰጣቸው ወይንጠጅ የተነሳ ዶኪማስ ሳያፍር ሙሽሮቹም ሰርጋቸው ሳይበላሽ በተድላ የጋብቻን ሥነ-ሥርዓታቸውን ፈጽመዋል፡፡

 የሠርጉ የቃና የወይንጠጁ ቃና

 ወይንጠጁ ባለቀ ጊዜ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በተአምራቱ ቀየረው፡፡ ከነበረው ጥቂት ወይንጠጅ አስቀርቶ ጌታችንን ያንን የወይንጠጅ ቢያበረክት ኖሮ ያለውን ነው ያበረከተው ተአምራት አላደረገም በተባለ ነበር፡፡

 የቃና ዘገሊላ ሰርግ ደጋሽ ዶኪማስ ብልህ ሰው ስለነበረ በሰርግ መካከል ማንን መጥራት እንዳለበት አውቋል፡፡ አክብሮ የጠራው ጌታችን ዶኪማስ የገጠመውን ያልታሰበ ፈተና በድንቅ ተአምራት እንዲያልፈው አድርጎታል፡፡  ጌታችን በቃና ዘገሊላ ያደረገው ተአምራት እስከዓለም ፍጻሜ ድረስ በሚከወን የጋብቻ ሕይወት ተገኝቼ እባርክሀለው ተአምራቴን አደርጋለው ሲል የቃል ኪዳን ምልክት አድርጎታል

  ይህም የሰው ዘር የሚቀጥልበት የነገይቱ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ߹የዚህ ዓለም አስተዳዳሪዎች መሪዎች መገኛ የሆነው የጋብቻ ሕይወት፤ ከየት እንደመጣ በማናውቃቸው ከሩቅ ሳይሆን በቀላሉ እንደውሃ በምናገኘውን ነገር ተባርኮ፤ ችግሩን ፋታ ጉድለቱም ሞላል ሲል  ፈቃዱ ለማሳወቅ ያደረገው የመጀመሪያው ተአምር ነው፡፡

  የመጀመሪያው የጋብቻ ሕይወት ትምህርት ቤት የሆነው የዶኪማስ ድንኳን በጋብቻ ሕይወት ያልተጠበቀ ፈተና ሲገጥመን ጉዳዩን ገበናቸውን በጎዳ ሸፍነው ለሚመለከታቸው ብቻ መናገር እንደሚገባ የሚያስተምር ነው፡፡

 ይህ የሚሆነው ሰርጉን ለመረበሽ የጋብቻውን ዓላማ ለማሰናከል አይደለም፡፡ የወይንጠጁ ማለቅ ውኃ ከተሞሉት ጋኖች አዲስ እና ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ወይንጠጅ ለማግኘት እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡ በክርስትና ሕይወት በጋብቻ መካከል የሚመጣ ፈተና የእኛን ጽናት ለማረጋገጥ በፈተና አልፈን በረከት እንድናገኝ ነው፡፡

 የቃናውን ሠርግ ቤት ምሥጢር ያልገባው ሰው በጋብቻ ሕይወቱ እጅግ ይቸገራል፡፡ ጋብቻ እንደሰርጉ ሰሞን መጀመሪያ ፤ ሁሉ የተሟለት ያማረ߹ የደመቀ ብቻ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ በተለይ እግዚአብሔርን አምነው በቤቱ ተገኝተው ቅዱሳንን ጠርተው ወደዚህ የበረከት ቤት ሲገቡ መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዲሆን ነው እንጂ ማጣት߹ መጉደል እንዲደርስባቸው አይፈልጉም፡፡

  ወይንጠጁ ባለቀ ጊዜ ምን ሆነ ?

ወዳጄ ሠርጉ የቃና ከሆነ ወይን ጠጁ በመሀከል ላይ ማለቁ አይቀርም በዚህ አትደናገጥ፡፡ ብዙዎች ለቅድመ ጋብቻ በሰጡት ዝግጅት እና የሙሽሮች መጠናናት፤ በሀብትና በንብረት መደራጀታቸውን መሰረት አድርገው፤ ጋብቻ ሲጀመር የነበረው ፍቅር߹ መተሳሰብ ፤አብረው ሲኖሩም እንዲያው እንደሞቀ ምንም ሳይቀንስ እየጨመረ የሚቀጥል ብቻ ይመስላቸዋል፡፡

 ከቃናው ሰርግቤት ጀምሮ በእያንዳንዱ የሠርግቤት ድንኳን የወይንጠጀ ያልቃል ችግር ይፈጠራል፡፡ ይህም በወዳጅ ዘመድ ፊት ቢወጣ የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ ይሆናል፡፡ የቃናው ሰርገኞች ችግራቸውን ለማን መናገር እንዳለባቸው ጠንቅቀው በመረዳታቸው ችግራቸውን በቀላሉ ፈቱ፡፡ ባለትዳሮች በጋብቻ መካከል የሚፈጠር ጉድለት ለማን መናገር እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል፡፡

 የጋብቻ ምስጢር ለሚመለከተው ብቻ ይነገራል እንጂ፤ ለሚያዳክሙ አጽናኞች አደባባይ ላይ አይወራም፡፡ ከችግሩ ክብደት በላይ የሰዎች ወሬ ግልምጫ እና አሉባልታ ብዙ ተጋቢዎችን የትዳር ጉድለት ያባብሳል፡፡ የጋብቻ ጉድለት ለእግዚአብሔር߹ ለቤተክርስቲያን߹ ለንሥሐ አባት ߹ለሽማግሌ ለቤተሰቡ በየደረጃው ይነገራል እንጂ ገበናን በአደባባይ አውጥቶ ለአጉል አማካሪ ተናግሮ ጉድለቱን አብሶ ትደር ማፍረስ ደረጃ ያደርሳል፡፡

 በጋብቻ ሕይወት ከሰርግ ዕለተ ጀምሮ ባለው ጉዞ ውስጥ እንደ ዶኪማስ የወይንጠጅ ሌሎች ነገሮችም ሁሉ ሊያልቁ ይችላሉ፡፡ፍቅር፣ሰላም፣ትዕግስት፣ቀናነት፣በጎነት፣ስምምነት፣መተሳሰቡ፣ገንዘብ፣ጎደኝነት ብቻ ብዙ ነገሮች ባልተጠበቀ በሚያስደንቅ ፍጥነት ባዶ ይሆናሉ፡፡

 ጋብቻቸው በሥርዓተ ተክሊል በቅዱስ ቁርባን ከፈጸሙ፤ በሕጉ በትእዛዙ ከሄዱ፤ ችግር አይነካንም የፈተና ነፋስ ሽው አይልብንም የሚሉ ክርስቲያኖች አይጠፉም፡፡ ወዳጄ ሠርጉ የቃና ከሆነ ወይንጠጁ መቼ እንደሚያልቅ አታውቅም? ፤ በሕይወትህ ውስጥ ያልጠበከው ልዩ ልዩ ጉድለት ሊፈጠር ይችላል፤ በኑሮ ጉዞ በሕይወት መንገድ ላይ በመካከል መቼ ምን እንደሚፈጠር አታውቅም፤ እንደወይን የጣፈጠው የሙሽሮች ፍቅር እኳን ቢያልቅ መደናገጥ አይገባቸውም።  ምድራዊው ነገር ገንዘቡ እንጅራው፣ ዱቄቱ ፣ሽሮው ፣በርበሬው ሊያልቅ ይችላል ለምን አለቀ አይባልም። ሁሉን ወደ ሚሞላ ወደሚያስተካክል ልዑል እግዚአብሔር መጮህ እንጂ ፤ ብቻ በጎደለህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብህ እወቅ፡፡

 ዕለተ ሠርግን እንኳን ብንመለከት ብዙ ወጪ የወጣበት አማካሪ ባለሙያ የተቀጠረበት ሠርግ ድግሱ ቢያምር ፤ የጥንቃቄዎች ሁሉ ጥንቃቄዎች ቢደረግ ፤ጉድለት አይጠፋውም፡፡ በሰው ደካማነት የሚፈጠሩ ߹በተፈጥሮም ችግር የሚፈጠሩ ክስተቶች በየሠርጉ ቤቱ ሽብር ሲፈጥሩ አይተናል፡፡ ክፉ ልማድ ሆኖ ሙሽሮች ያረፍዳሉ ߹የሙሽራው መኪና ይዘገያል፣ ለሙሽሮች የተዘጋጀው ኬክ ይጠፋል ብቻ ገጠመኙ እንደየ ሠርግቤቱ ይለያል፤ ጉድለቱ ጫጉላ ቤት ደርሶ አልፎም ተርፎም ወደ አዲሱ ጎጆ በዘላቂነት ሊገባ ይችላል፡፡

 የቃናው ሰርግ ቤት ወይንጠጅ ማለቅ ዜና በአሁኑ ዘመን ቢሆን ኖሮ ሙሽሮቹ እና ቤተሰቦቻቸው ሳይሰሙት ወሬው በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ሠርግቤት ባሉት ታዳሚዎቹ ዘንድ ይደርስ ነበር፡፡ የቃናው ሰርገኞች የገጠመውን ፈተና ጉዳዩን በምስጢር በመያዝ ለሚመለከታቸው ብቻ በመናገር ፈተናውን አለፉት፡፡ በትዳር ውስጥ የሚፈጠር ጉድለት በምሥጢር ይዞ ሳይደናገጡ በእርጋታ መፍታት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡

 ጋብቻ ታላቅ ምሥጢር ነው የተባለበት ምክንያትም ይሄነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።" ኤፌ 5፥31-32 ብሏል፡፡ የጋብቻ ሕይወት ብዙ በአደባባይ የማይነገሩ የተጋቢዎቹ እና እግዚአብሔር የሚያውቁት እግዚአብሔር ለመረጣቸው ብቻ የሚነገር ምስጢር የተሞላ ሕይወት ነው፡፡

 በአባታችን ሆይ ጸሎት ላይ አቤቱ ወደፈተናም አታግባኝ የሚለው ጸሎት በተዘዋዋሪ ወይንጠጁን አታሳልቀው ማለት ነው፡፡ ከክፉ ሁሉ አድነኝ ማለት ደግሞ ወይንጠጅ ባለቀ ሰዓት߹ ፈተናውም በመጣ ጊዜ ߹አውጣኝ አድነኝ ማለት ነው፡፡ በትዳር ሕይወት ለሚመጣ ችግር ቅድመ መከላከያው መንገድ አድነኝ ከክፉ ሁሉ ጠብቀኝ ሰውረኝ ብሎ በጸሎት መትጋት ነው፡፡

 ጋኖቹን ውሀ ሙቸው

 ስድስቱ የድንጋይ ጋኖችን ውኃ በሙላት የታዘዙትን የመፈጸሙት አገልጋዮቹ ናቸው፡፡ በድንጋዩ ጋን የተሞላው በሁሉም ቤት የሚገኘውን ውኃ ነው፡፡

 አስቀድመን አክብረን የጠራነው አምላካችን ሁሉም ነገር ባለቀ ጊዜ ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው በማለት ያዘናል፡፡ ለምሳሌ የብዙሀን አባት አብርሃምን ከወገኖች ከዘመዶችህ ተለይተህ ውጣ ያለው እግዚአብሔር አምኖ ወጣ ፡፡ ነገርግን ያፈራውን ሀብት የሚወርስለት ልጅ አልነበረውም፡፡ የአብርሃም ጉድለት አንድ ልጅ ማግኘት ነበር፡፡ አብርሃም ያመነው እና የተከተለው አምላክ ጉድለቱን አውቆ የአብራኩ ክፋይን ይስሀቅን ሰጠው፡፡  የእኛ ሥራ የድንጋዮቹ ጋኖች ቦዶ እንዳይሆኑ እንደ ውኃ ንጹሕ የሆነ ፍቅር ߹ትህትና ߹መታዘዝን መሙላት ይሆናል፡፡ ባለ ትዳሮች ጋኖቹ ባዶ ሲሆን ወይኑ ሲያልቅ፤ ኑሮችሁ ሁሉ ባዶ ሲሆን ፈጥነን ውኃ ቀድተን ልጅሽ ውኃውን የወይንጠጅ ያደርግልን ዘንድ ቅድስት ሆይ ለምኝልን ልንል ይገባል፡፡

 ውኃውንም ወይንጠጁንም የሚያስቀምጠው የድንጋይ ጋን ያለው እዛው እቤታችን ውስጥ ነው፡፡ ከጎረቤት የምንዋሰው እንስራ߹ ማሰሮ አይኖርም፡፡ ባለትዳሮች ለትዳራቸው መፍትሄ የሚሰጣቸው እቤት ውስጥ ባለው ነገር ነው እንጂ በተውሶ እቃ አይደለም፡፡

 ጋኖቹን ውኃ መሙላት የሰው ድርሻ ሲሆን፤ ውኃን በጣዕምም በመልክም ልዩ ወደ ሆነው ወይን ጠጅ መለወጥ ደግሞ የአምላካችን ነው፡፡ ብዙ ባለትዳሮች የድንጋዩ ጋኖችን ውኃ ሳይሞሉ እንደ ወይንጠጅ የሚጣፍጥ ትዳርን ይመኛሉ፡፡ በሠራነው ባጠራቀምነው ውኃ ልክ ወይንጠጁንም እናገኛለን፡፡ አብዝቶ ጽድቅን የሰራ የበዛ በረከት ያገኛል፡፡

 በጎዳችን ውስጥ ያለ የድንጋይ ጋን ለእኛ የበረከታችን ምክንያት ነው፡፡ በምንሞላው ውሀ ነው፡፡ የትዳር ጉድለት የመጀመሪያው መፍትሄ ያለው እዛው እጎዳ ውስጥ በቅርበት ያለን እኛው ነን እንጂ ከሩቅ የሚመጣ ሌላ ሰው አይደለም፡፡

  ብዙ ሰዎች የትዳር ጉለትን ለማስተካከል አዲስ ሰው ፍለጋ ገበያ ሲወጡ ይታያሉ፡፡ በረከት ከሩቅ አይመጣም ባለን ነገር ላይ ረቂቅ የሆነው የእግዚአብሔር ሥራ ይገለጣል፡፡ ያለን ውኃ ߹ጣዕም የሌለው ኑሯችን ተለውጦ እንደወይን ይጣፍጣል እንጂ፤ አዲስ ወይን ከገበያ አይመጣም፡፡

 አዲሱ የወይን ጠጅ

 በቃናው ሰርግቤት በተአምራት የተገኘው የወይን ጠጅ ከበፊቱ የበለጠ በጠዕሙ ልዩ የሆነ ነበር፡፡ መጀመሪያ ከነበረው የወይንጠጅ የበለጠ በጣዕሙ ድንቅ የሆነ አዲስ የወይንጠጅ ሰጣቸው። ለምን ጎደለ ብለን የማናማርረው የተሻለ እንደምናገኝ እርግጠኞች ስለሆን ነው። በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ጉድለት ማማረሪያ ሳይሆን ማመስገኛ߹ ተስፋ መቁረጫ ሳይሆን ተስፋና በረከት ማግኛ ነው። ገንዘብ ቢጎድለን ቆይቶ ሲመጣ ጤናና በረከት ይዞ ይመጣል ልጅ ሳይመጣ ቢዘገይ ሲመጣ የተባረከ ፍሬ እንዲሆንልን ነው። ብቻ ባለቀ ጊዜ ማንን መጥራት እንዳለብን፤ ምን ማድረግ እንዳለብን እንወቅ እንጂ ጉድለቱ ጊዚያዊና ለበጎ ይሆናል፡፡ የሚያልቅበትን ጊዜ ስናስታውስ የተሞላበትንም ጊዜ እናስታውሳለን።

 ወይንጠጀ አንዴ ነው የሚጠመቀው እንደጠላ ቅራሪ የለውም፡፡ የጋብቻም ሕይወትም አንዴ ነው የሚመሰረተው፡፡ ሁለተኛ ሦስተኛ የለውም፡፡ ጋብቻን የሰው ሰውኛ ማስተካከያ አያዘልቀውም ጊዜያዊ መፍትሄ አያጸናውም፡፡ በጋብቻ ሕይወት እንደ እግር ኳስ ተጫዋች በዝውውር ወይም በግዥ አዲስ ተጫዋች መቀየር አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ የተመዘገበው ተጫዋች ነው እስከመጨረሻው የሚጸናው፡፡ ያው ተጫዎች ነው ቢታመም ታክሞ߹ ቢደክም በርትቶ ውጤት የሚያስመዘግበው፡፡ ሰነፈች ብሎ አዲስ ሚሰት ማግባት ከፋ ብሎ አዲስ ባል ማግባት መፍት አይሆንም፡፡

 የወይንጠጅ ያለቀበት ጊዜ መረበሽ አይገባም፤ በቃ አለቀ ቡሎ ተደናግጦ ፤ከእንግዲ ወዲህ የትዳራችን ሁኔታ አበቃለት፤ ዳቦ ተቆረሰ ጨዋታ ፈረሰ ማለት አይቻልም፡፡  ትዳር ይፍረስ ልጆች ይበተኑ ማለትም አይቻልም፡፡ በፊፈጠሩት ጥቃቅን ጉድለቶች ጠንከር ያሉ ፈተናዎች ሁሉ መደንበር የለብንም፡፡  ይህ የሆነው የእግዚአብሔር  ሥራ የሚገለጥበት ጊዜ ቀርቦ መሆኑን ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፡፡  በትዳር ውስጥ ፈተና ሲመጣ የጨለመ የሚመስል ጊዜ አለ፤ ያን ጊዜ ብዙዎቻችን ቀኑን ብንጠላውም ፤ቢያቀያይመን߹ ቢያጨቃጭቀንም፤ ክፍ ቀን አልነበረም፡፡ ጎህ ሊቀድ ሊነጋ ሲል ቡርሃን እንደሚወጣ ከፈተናም በኃላ መልካም ቀን ደግ ጊዜ እንደሚመጣ ልናውቅ ይገባል፡፡  

 የኢየሱስም እናት ማርያም በዚያ ነበረች

 የኢየሱስም እናት እመቤታችን ማርያም በዚያ የነበረችው በምክንያት ነው። የሚያልቀውን የሰርግቤት የኑሮ ጣጣ ለማሟላት ነው። በዙሪያችን እንደ ደመና የከበቡን ቅዱሳን የእግዚአብሔን ሥራ ተአምራት ይገለጥ ዘንድ በችግራችን ጊዜ ረዳትነታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እመቤታችን ጨምሮ ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲረዳችሁ በበረከትም እንዲጎበኛቸው እባካችሁ ታዘዙ ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽሙ የሚላችሁን አድርጉ ይላሉ፡፡

 ሰው ምን አይነት ደገኛ ፍጥረት ነው ሁልጊዜ የጎደለውን እግዚአብሔር የሚሞላለት፡፡ አዳም ከተፈጠረ በኋላ ጉድለት ነበረበት፡፡ ያንን ጉድለቱን የምትመቸው ረዳት በመፍጠር በከበረ ጋብቻ ሞላለት፡፡ በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ጋብቻ ጉድለትን ጌታችን በመሙላት የስራው ሁሉ መጀመሪያ አድርጎታል ባርኮታል፡፡

 የጋብቻ ሕይወት ረድኤተ እግዚአብሔር የማይለየው መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡ ቡዙ ተጋቢዎች በማሰሮ ወይን ሳይኖራቸው እግዚአብሔርን ከእመቤታችን ከቅዱሳን ጋር ይዘው ገብተው በብዙ ጋን ተቀድቶ የማያልቅ የወይንጠጅ በረከትን አግኝተዋል፡፡ እንደጎደለማ ቢቀር ትውልድ እንዴት ይቀጥል ነበር፡፡ የስንቱ ቤት ተፈቶ፤ ስንት ትዳር ተበትኖ በቀረ ብዙዎችም ተስፋ በቆረጡ ነበር፡፡ 

የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ አዲስ የወይን ጠጅ ከወዴት እንደመጣ ሳይታወቅ ተጠጣ፡፡

 ይቆየን

ያዕቆብ ሰንደቁ

ጥር 12 ቀን  2018 ዓም

እሑድ 18 ጃንዋሪ 2026

ዮርዳኖስ፡ባሕር አየችና ሸሸች - ከአል-መቅጠስ እስከ ዛሬው ተአምር

 

ዮርዳኖስ፡ባሕር አየችና ሸሸች - ከአል-መቅጠስ እስከ ዛሬው ተአምር

በ ያዕቆብ ሰንደቁ

በመካከለኛው ምስራቅ ምድር፣ በዮርዳኖስና በእስራኤል ድንበር መካከል የምትፈስ አንዲት ወንዝ አለች። በዓይን ሲያዩዋት እንደ አባይ ግርማ የላትም፣ እንደ አማዞንም ስፋት የላትም። ይሁን እንጂ ይህች ወንዝ ተራ የውሃ አካል አይደለችም፤ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ከሐዲስ ኪዳን የምስራች ጋር የተገናኘበት፣ ሰማያት የተከፈቱበት እና የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀበት የታሪክ ማህደር ናት። እሷም የዮርዳኖስ ወንዝ ናት።


የዮርዳኖስ መልክአ ምድር እናታሪካዊ ዳራ

ዮርዳኖስ ከሊባኖስ ተራሮች በመነሳት የገሊላን ባሕር አቋርጦ እስከ ሙት ባሕር (Dead Sea) ድረስ ይዘልቃል። "ዮርዳኖስ" የሚለው ስም ትርጉም በዕብራይስጥ "ወራጅ" ወይም "ከላይ የሚወርድ" ማለት ነው። ዛሬ ላይ ወንዙ በእስራኤል፣ በፍልስጤም እና በዮርዳኖስ ሀገር መካከል ድንበር ሆኖ ቢያገለግልም፣ ለመላው የክርስትና ዓለም ግን ከድንበር በላይ የሆነ መንፈሳዊ ድልድይ ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ወንዙ በልማትና በውሃ አጠቃቀም ምክንያት መጠኑ ቢቀንስም፣ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ለበረከት ይጎበኙታል።

አል-ማግታስ (Al-Maghtas) በሦስት ምዕራፎች የተከተበ ታሪክ

"የሃይማኖት ምሁራን መድኃኒታችን ኢየሱስ የተጠመቀው በዮርዳኖስ ማዶ በሚገኘውና በዩኔስኮ (UNESCO) ጥበቃ በሚደረግለት ቤተንያ (Bethany Beyond the Jordan) እንደሆነ ያምናሉ።" ዛሬ በዮርዳኖስ ሀገረ ግዛት ውስጥ "አል-መቅጠስ" (ትርጉሙም "የጥምቀት ቦታ") ተብሎ የሚጠራው ስፍራ፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ምዕራፎችን አሳልፏል፦

1.    የመጀመሪያው ዘመን (1ኛው .) በመጽሐፍ ቅዱስ "በዮርዳኖስ ማዶ ያለችው ቢታንያ" (ዮሐ. 1:28) ተብላ የምትጠራው ይህች ስፍራ ናት። መጥምቁ ዮሐንስ ይኖርባትና ያጠምቅባት የነበረችው ይህችው ቦታ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባትና ነቢዩ ኤልያስ በነበልባል ሰረገላ ወደ ሰማይ የዐረገባት ቅድስት ምድር ናት። በወቅቱ ስፍራው ለእንግዳ ተቀባይነትና ለጸሎት ምቹ የነበረ ጫካማ አካባቢ ነበር።

2.      የባይዛንታይን ዘመን (4ኛው - 7ኛው .) ክርስትና በመላው የሮም ግዛት ሲሰፋ፣ ንግሥት ዕሌኒን ጨምሮ በርካታ ነጋድያን ስፍራውን ይጎበኙት ጀመር። በዚህ ወቅት ጌታ በተጠመቀበት ቦታ ላይ የእምነበረድ ዓምድ ተተክሎ፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና የእንግዳ ማረፊያዎች ተገንብተው ነበር።

3.      የመጥፋትና የዳግም መገኘት ዘመን፦ ከእስልምና መስፋፋትና ከተለያዩ ጦርነቶች በኋላ ስፍራው ተረስቶና ፈንጂ ተቀብሮበት ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። .. 1994 በእስራኤልና በዮርዳኖስ መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው ፈንጂው ተጠርጎ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮ የተጀመረው። 2015 ደግሞ ዩኔስኮ (UNESCO) ቦታውን በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባት የእምነበረድ ዓምድ ቦታ

በአርኪኦሎጂና በጥናት የተረጋገጠው እውነት

ለብዙ ዘመናት በታሪክ ብቻ ሲጠቀሱ የነበሩ ስፍራዎች በቁፋሮ ዳግም ተገኝተዋል። አርኪኦሎጂስቶች በትክክል ጌታ በተጠመቀበት ቦታ ላይ የሚከተሉትን አስደናቂ እውነታዎች አግኝተዋል፦

·         አብያተ ክርስቲያናት፦ እርስ በእርሳቸው ተያይዘው የተገነቡ የአምስት አብያተ ክርስቲያናት ፍርስራሾች ተገኝተዋል። ይህም ወንዙ ጎርፍ አብያተ ክርስቲያናቱን በሰበረ ቁጥር፣ ቀደምት ክርስቲያኖች በዚያው ቅዱስ ስፍራ ላይ በድጋሚ ይገነቡ እንደነበር ያሳያል።

·    የጥምቀት ገንዳዎች፦ የመስቀል ቅርጽ ያለው እና ወደ ውስጥ የሚወርድባቸው አምስት ደረጃዎች ያሉት ጥንታዊ ገንዳ ተገኝቷል። እነዚህ ደረጃዎች አማኞች ወደ ውሃው ሲወርዱ ትሕትናን፣ ሲወጡ ደግሞ ትንሣኤን እንደሚያመለክቱ ይታመናል።

·       የእምነበረድ ዓምድ፦ 6ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ መንገደኞች "ጌታ በተጠመቀበት ቦታ ላይ የብረት መስቀል ያለበት የእምነበረድ ዓምድ አለ" ብለው የጻፉት መሠረት በትክክል በተባለው ቦታ ላይ ተገኝቷል።

 ·         የመጥምቁ ዮሐንስ ዋሻ፦ ዮሐንስ መጥምቅ ይኖርበትና ያስተምርበት የነበረው ዋሻ በታዋቂ የአርኪዎሎጂ ባለሙያ  ሺሞን ጊብሰን እ.ኤ.አ በ2004 ተገኝቷል። በዋሻው ግድግዳ ላይ ጥንታዊ ክርስቲያኖች የጻፏቸው ጽሁፎችና የሳሏቸው መስቀሎች ዛሬም ድረስ ይታያሉ።

 ዮሐንስ መጥምቅ ይኖርበትና ያስተምርበት የነበረው ዋሻ ፎቶግራፍ አንሺው ቶድ ቦለን

"ባሕር አየችና ሸሸች" የዮርዳኖስ ወንዝ ተአምር

የዮርዳኖስ ወንዝ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ ዛሬም በየዓመቱ በጥምቀት በዓል (ጥር 11/ጃንዋሪ 19) የሚከሰት ድንቅ ተአምር አለው። መዝሙረኛው ዳዊት "ባሕር አየችና ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ" (መዝ 113:3) ብሎ እንደተነበየው፣ ጸሎተ ጥምቀቱ ሲከናወን ወንዙ ባሕርዩን ይቀይራል።

የሃይማኖት አባቶች መስቀሉን ወደ ወንዙ ሲጥሉ፣ ወንዙ ፍሰቱን አቁሞ ወደ ኋላ መመለስ ይጀምራል። ይህን ክስተት በዓይናቸው ያዩ በርካታ ምእመናን እንዲህ ሲሉ ይመሰክራሉ፦

"መስቀሉ ሲወረወር ወንዙ ልክ እንደ ሰው ተባብሮ ቆመ፤ ከዚያም ፍሰቱ ወደ ኋላ መመለስ ጀመረ። ይህ በዓይን ካላዩት ለማመን የሚከብድ እውነት ነው!"ማሪና ፔትሮቫ (ከሩሲያ)

አንድሬስ ኒኮላስ የተባለ ግሪካዊ እማኝ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ "እኔ መሃንዲስ ነኝ፣ በሳይንስ አምናለሁ። ነገር ግን በዮርዳኖስ ወንዝ ያየሁት ነገር ሳይንሳዊ ማብራሪያ የለውም። ውሃው ወደ ታች መፍሰሱን አቁሞ ለደቂቃዎች ወደ ኋላ ሲመለስ ማየቴ ሕይወቴን ቀይሮታል።"

በሚዲያና በቪዲዮ የተደገፉ ምስክርነቶች

በዘመናዊው ዓለም ይህ ክስተት እንደ Pravmir RT እና Greek Reporter ባሉ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በቪዲዮ ተደግፎ ቀርቧል። መስቀሉ ውሃውን ሲነካው የሚፈጠረው መታወክ፣ ነጭ ርግቦች በድንገት ከሰማይ መጥተው በውሃው ላይ ሲያንዣብቡ እና በወንዙ ላይ የተጣሉ ቅርንጫፎች ወደ ኋላ (ወደ ላይ) ሲፈሱ ማየት ለሳይንሳዊው እይታ ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የሳይንሳዊ እይታ ፈተና ቢኖርም፣ ክስተቱ በዓመት አንድ ቀን፣ ያውም በጸሎቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት (ፓትርያርኩ 'በዮርዳኖስ በተጠመቅህ ጊዜ' የሚለውን ጸሎት በሚያደርሱበት ቅጽበት) ብቻ መከሰቱ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል (Supernatural Power) እንዳለ ማረጋገጫ ነው።

የዮርዳኖስ መንፈሳዊ ትርጉምና የመፈወስ ኃይል

ዮርዳኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራ ወንዝ አይደለም፤ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው፣ የእግዚአብሔር ተአምራት የሚገለጡበትና የሰው ልጅ ሕይወት የሚቀየርበት "የመሻገሪያ ድልድይ" ነው።

·         የእስራኤላውያን መሻገር (ኢያሱ 3)፦ እስራኤላውያን ከባርነት ምድር ወጥተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓን ለመግባት የዮርዳኖስ ወንዝ ግድ ሆኖባቸው ነበር። ነገር ግን ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው የወንዙን ውሃ ሲረግጡ፣ ውሃው እንደ ግድግዳ ቆመ፤ ሕዝቡም በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ይህ ታሪክ በጥምቀት ከኃጢአት ባርነት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመሻገራችን ታላቅ ምሳሌ ነው።

·         የነቢያቱ ኤልያስና ኤልሳዕ ተአምር (2 ነገሥት 2)፦ ዮርዳኖስ የሥልጣንና የኃይል መገለጫ ነው። ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰማይ ከመጥቀሱ በፊት ልብሱን አጣጥፎ ወንዙን ሲመታው ውሃው ለሁለት ተከፍሎለታል። ኤልያስ በሰረገላ ካረገ በኋላም፣ ኤልሳዕ የኤልያስን ካባ አንስቶ ወንዙን ሲመታው ውሃው በድጋሚ ተከፍሏል። ይህም መለኮታዊ ሥልጣን ከኤልያስ ወደ ኤልሳዕ መሸጋገሩን ያረጋገጠ ክስተት ነበር።

·         የንዕማን ሶርያዊው መፈወስ (2 ነገሥት 5)፦ የሶርያ ጦር አዛዥ ንዕማን በለምጽ በሽታ ተመትቶ ነበር። ነቢዩ ኤልሳዕ "ወደ ዮርዳኖስ ሂድና ሰባት ጊዜ ተጠምቅ" አለው። ንዕማን በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ሲጠመቅ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ሆኖ ድኗል። ይህ ክስተት ጥምቀት ሥጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ከኃጢአት ለምጽ እንደሚያነጻ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል።

·       የሥላሴ መገለጥ (ማቴዎስ 3)፦ ይህ የዮርዳኖስ ታሪክ ማጠቃለያና ትልቁ ክስተት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ በመጣ ጊዜ ምስጢረ ሥላሴ በግልጽ ተገልጧል፤ አብ በደመና "የምወደው ልጄ ይህ ነው" ሲል፣ ወልድ በዮርዳኖስ ቆሞ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል ወርዷል።


ተስፋ የሚሰጡ የተአምራዊ ፈውስ ምስክርነቶች

ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በእምነት የሚገቡና ጸበሉን የሚጠቀሙ ሰዎች ዛሬም ድረስ ልዩ ልዩ ፈውሶችን እንደሚያገኙ ይነገራል፦

·         የቆዳ በሽታዎች፦ እንደ ንዕማን ሶርያዊው ሁሉ፣ ዛሬም በቆዳ በሽታ፣ በለምጽና በተለያዩ ቁስሎች የሚሰቃዩ ሰዎች በወንዙ ተጠምቀውና ጸበሉን ተረጭተው እንደሚፈወሱ በደስታ ይመሰክራሉ።

·         የመካንነት ችግር፦ ብዙ ክርስቲያን እናቶች የዮርዳኖስን ውሃ በመጠጣትና በመታጠብ፣ በፈጣሪ ቸርነት የልጅ በረከትን እንዳገኙ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

·        መንፈሳዊ ሰላም፦ ከዓለም ጭንቀትና ከውስጥ መታወክ ለመፈወስ ብዙዎች ወደ ዮርዳኖስ ያመራሉ፤ በዚያም የሚሰማቸው ልዩ ሰላም "ከነፍስ ደዌ የመፈወስ" ትልቅ ተአምር ተደርጎ ይቆጠራል።

·   የውሃው መቀደስ፦ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃው ጭቃማና ለዓይን የሚታወክ ቢሆንም፣ በውስጡ የተቀዱት ጸበሎች ግን ለብዙ ዓመታት ሳይበላሹ፣ ሳይሸቱና ሳይደፈርሱ እንደሚቆዩ ምዕመናን በአድናቆት ይናገራሉ።

ማጠቃለያ

የዮርዳኖስ ወንዝ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት፣ የቤተክርስቲያንን ታሪክ እና የሳይንስን ጥያቄ በአንድ ላይ አቅፎ የያዘ ድንቅ ስፍራ ነው። በአል-መቅጠስ የሚገኙት ጥንታዊ ፍርስራሾች የታሪኩን እውነተኝነት ሲያረጋግጡ፣ በየዓመቱ የሚታየው የወንዙ ወደ ኋላ መመለስ ደግሞ ተአምራቱ ዛሬም እንደሚቀጥሉ ያሳየናል።

ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ በአካል መሄድ ባንችል እንኳ፣ በሃሳባችን ዮርዳኖስ ወርደን፣ በረከቱን ተካፍለን የነፍስ ሰላምን እንድንጎናጸፍ የጥምቀት በዓል ይጋብዘናል።

መልካም የጥምቀት በዓል ለሁላችሁም!

ያዕቆብ ሰንደቁ

ጥር 2018

አዲስ አበባ