መስከረም 1 የዓዲስ ዓመት መባቻ
በያዕቆብ ሰንደቁ
መስከረም 1 የዓመቱ መጀመሪያ ቀን ለምን ሆነ ?
መስከረም ሲጠባ ምድር አረንጓዴ ቀሚሷን አውልቃ በወርቃማው የአደይ አበባ ካባ ስታጌጥ፣ የክረምቱ ጨለማ ደመና ተገፎ የጥቢው የጠራ ውኃ ኩልል ብሎ ሲወርድ ተፈጥሮአዊ ውበት የሰውን ቀልብ ይስባል። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የሚሆን የተፈጥሮ ጸጋ መስከረምን ከወራት ሁሉ በዓዲስ መንፈስ የምትናፈቅ የዓዲስ ዓመት መዓዛን የምታውድ ብርጉድ አድርጓታል ፡፡ ባለቅኔውና ሠዓሊው ገብረክርስቶስ ደስታ፦
“…በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤
ይታደስ ያረጅው ፍጥረት ሌላ ይሁን…”
ሲል እንደተቀኘው ሁሉ፣ ደራሲ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ መስከረምን «ቀዳማይ፣ ርዕሰ ክራሞት፣ መቅድመ አውርኅ፣ ርዕሰ ዐውደ-ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ» ሲሉ ያመሰጥሩታል።
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መባቻ የሆነው መስከረም 1 ቀን፣ በወቅቶች መፈራረቅና በምድር ማጌጥ ብቻ የሚገለጽ የተፈጥሮ ክስተት አይደለም። ከጀርባው የ ብዙ ሺህ ዓመታት ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት የሥነ-ከዋክብት ስሌት፣ ጥልቅ የኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ነገረ-መለኮት፣ የብራናዎች ፣የፊሎሎጂ ምርምር እና የዓለም አቀፍ ምሁራን ሳይንሳዊ ምርምርን ትኩረት የሳበ የታሪክና የምሥጢር ማኅደር ነው።
«መስከረም» እና «ዕንቁጣጣሽ»
«መስከረም» የሚለው ቃል አመጣጥ በሊቃውንቱ ትምህርት ዘንድ ሁለት ታላላቅ ምሥጢራትን ይዟል። በአንድ በኩል «መስ» ማለት «ዐለፈ፤ ከረመ» ከሚለው ግሥ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም «ክረምቱን ማስረከቢያ፤ የጥቢ መባቻ» ማለት ነው። በሌላ በኩል ታዋቂው ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ /ነፍሰሄር/ አስተምህሮ ደግሞ፣ በግዕዝ ቋንቋ መርከብ «መስቀር» ይባላል። አባታችን ኖኅ በሐምሌና በነሐሴ ወራት በውኃ ላይ ሲንሳፈፍ ቆይቶ፣ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ በአራራት ተራራ ላይ አርፋ ምድርን አገኘች። ከዘመናት ብዛት በኋላ «ቀ» ወደ «ከ» ተለውጦ «መስከረም» ተባለ እንጂ «መስቀርም ምድር አገኘች፤ መርከብም ምድርን ነካች» ለማለት የተሰጠ የወሩ ስያሜ ነው ብለው አስተምረው ነበር፡፡
የአዲስ ዓመቱ ሌላኛው መጠሪያ «ዕንቁጣጣሽ»
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት «እንቁጣጣሽ» የሚለውን መጠሪያ እንዴት አገኘ? የሚለው ጥያቄ በባህላችን፣ በታሪካችን እና በቋንቋችን ውስጥ በርካታ ማራኪ ትርክቶችን ይዞ ይገኛል። ክረምቱ አልፎ ፀሐይ ስትወጣ፣ ምድር በአደይ አበባ ስትሸፈን የሚከበረው ይህ ዕለት የተለያየ ስያሜ ያገኘባቸውን ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ መሠረቶች በአግባቡ መረዳት ይቻላል።
የንግሥተ ሳባ (ማክዳ) እና የንጉሥ ሰሎሞን ታሪክ ከዚህ ስያሜ ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ታዋቂ ትርክቶች አንዱ ነው። ንግሥቲቱ የንጉሥ ሰሎሞንን ታላቅ ጥበብ ሰምታ ወደ ኢየሩሳሌም ካደረገችው ጉዞ ስትመለስ፣ አጅበዋት የነበሩ መኳንንት «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» በማለት በዕንቁ የተጌጡ ውድ ስጦታዎችን አበረክተውላታል። ንጉሥ ሰሎሞንም በበኩሉ በጨለማ ውስጥ የማብራት ልዩ ኃይል የነበረውን የዕንቁ ቀለበት እንደሰጣት ይነገራል። ይህ ክስተት ለበዓሉ መጠሪያ መሠረት እንደሆነ ቀደምት ታሪኮች ያወሳሉ።
ሌላው ሰፊ ተቀባይነት ያለው ታሪክ የኖኅ እና የልጆቹን ጉዞ ይመለከታል ከጥፋት ውኃ በኋላ አባታችን ኖኅ ምድርን ለሦስቱ ልጆቹ ሲያካፍል አፍሪካ ለካም ደርሳዋለች። የካም ልጆች እና ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሲገቡ ሀገሪቱን በወቅቱ በለመለመው የአደይ አበባ አሸብርቃ አገኙዋት። በዚህ ውብ ትዕይንት የተደሰቱት መጤዎቹ የኖህ ልጆች «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» በማለት መክረማቸውን በመግለጽ ለዚህች ወቅት «እንቁጣጣሽ» የሚል ስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መሰጠቱ ይነገራል።
በቋንቋ እና በተፈጥሮ ፍች ረገድም ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ የተለየ እና ጥልቅ ማብራሪያ ይሰጣሉ። በእሳቸው እምነት ቃሉ «ተንቈጠቈጠ» ወይም «አንቈጠቈጠ» ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተወሰደ ነው። ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ አምላክ ምድርንም በአበቦች አጎናጸፋት የሚለውን ሐሳብ የሚያሳይ ሲሆን፣ ትርጉሙም «ዕንቁ-ዕፅ አመጣሽ» ማለት ነው። በመሆኑም ቃሉ ስለ ሳባ መንግሥት ብቻ የተሰጠ ሳይሆን የተፈጥሮን ድንቅ መታደስ የሚያሳይ ነው።
በተጨማሪም ይህ ዕለት በታሪክ የኖኅ መርከብ በአራራት ተራራ ላይ ያረፈችበት እና እርግብ የወይራ ቅጠል ይዛ የተመለሰችበት ታላቅ ዕለት (ዘፍጥረት 8፥13) በመሆኑ የሰው ልጆች ተስፋ የታደሰበት ማሳያ ነው። ክረምቱ ኃይሉን ጨርሶ በጋ ሲተካ የሚታየው ይህ አዲስ ጊዜ፣ በሀገራችን የዕድሳት፣ የሰላም እና የተስፋ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል።
የ «ጥንተ ዮን» ስሌት
ባሕረ ሐሳብ ምንድን ነው?
«ባሕረ ሐሳብ» ማለት የቃሉ የቁም ትርጉም «የሐሳብ ባሕር» ወይም «የቁጥር ጥልቅ እውቀት» ማለት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ የዓመታትን፣ የወራትን፣ የዕለታትን፣ የዐውደ ፀሐይን፣ የዐውደ ጨረቃን እንዲሁም የንዑስና አበቅቴን ስሌት በመጠቀም በዓላትና አጽዋማትን ለማውጣት የሚያገለግል ጥንታዊና ድንቅ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ነው።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት፣ ዓለም የተፈጠረበት ቀን እሑድ ቢሆንም የዘመን አቆጣጠር መነሻው (ጥንተ ዮን) ግን ማክሰኞ ነው። ይህ ለምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩት በዕለተ ረቡዕ (በ4ኛው የፍጥረት ቀን) ነው (ዘፍጥረት 1፥14-19)። እግዚአብሔር እነዚህን ብርሃናት ለዕለት፣ ለወራት፣ ለዓመታትና ለዘመናት መቁጠሪያ እንዲሆኑ አደረጋቸው።
የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት፣ ፀሐይና ጨረቃ በረቡዕ ቀን ሲፈጠሩ ሙሉ ሆነው (በሙላተ ጨረቃ) ነው የተፈጠሩት። የፀሐይና የጨረቃን ዑደት ወደኋላ በማስላት የዘመናት መጀመሪያ የሆነውን የዓመተ ዓለም 1 (መስከረም 1) ቀን ሲያወጡት ዕለቱ ማክሰኞ ላይ ይውላል።
በተጨማሪም ማክሰኞ (3ኛው የፍጥረት ቀን) ውኃ ከየብስ የተለየበት፣ ምድር የደረቀችበትና ዕፅዋት የበቀሉበት ቀን በመሆኑ (ዘፍጥረት 1፥9-13)፣ ለቁሳዊው ዓለም ህልውናና ለሰው ልጅ መኖሪያነት መሠረት የተጣለበት በመሆኑ ለዘመን ቆጠራ መነሻ ተደርጓል ተወስዷል።
የመጽሐፈ ሄኖክ የ6ቱ ደጆች ስሌት
የዘመን አቆጣጠር በዋናነት ሁለት የተለያዩ ፍልስፍናዎችን ይከተላል፦ የሳምንታትን መዋቅራዊ እኩልነት መጠበቅ እና ከፀሐይ ተፈጥሯዊ ዑደት ጋር ፍጹም መጣጣም። በዘመናት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው የመጽሐፈ ሄኖክ ካላንደር እና የኢትዮጵያ የ365/366 ቀናት ካላንደር እነዚህን ሁለት እይታዎች በግልጽ የሚያንጸባርቁ ድንቅ የዘመን ቆጠራ ሥርዓቶች ናቸው።
የሳምንታት ምሉዕነት እና የተፈጥሮ ዑደት
መጽሐፈ ሄኖክ የሚከተለው የዘመን አቆጣጠር ዓመቱን በ364 ቀናት ይከፍላል። ይህ ቁጥር ለ7 ሙሉ በሙሉ የሚካፈል በመሆኑ፣ ዓመቱ በትክክል 52 ሳምንታትን ይይዛል። የዚህ ሥርዓት ዋነኛ ማራኪነት በዓላት እና ቀናት በየዓመቱ ከሰኞ እስከ እሑድ ባሉት ዕለታት ላይ በፍጹም አለመቀያየራቸው ነው፤ ይህም በዓላት ሁልጊዜ በሚታወቅ ቋሚ የሳምንቱ ቀን ላይ እንዲውሉ ያደርጋል።
እውነተኛው የፀሐይ ዑደት በግምት 365.24 ቀናት በመሆኑ፣ የሄኖክ ካላንደር በየዓመቱ በ1.24 ቀናት ያህል ከፀሐይ ይዘገያል። በዚህም ምክንያት ልዩ ማስተካከያ ካልተደረገበት በስተቀር፣ ከጊዜ ብዛት ወቅቶች ከነበሩበት ወር በመዛባት ይቀያየራሉ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ አቆጣጠር የ365/366 ቀናት ካላንደር
በኢትዮጵያ የሚሠራበት የ365 (በዘመነ ዮሐንስ፣ ማቴዎስ እና ማርቆስ) እና 366 (በዘመነ ሉቃስ) ቀናት አቆጣጠር፣ ትኩረቱን በዋናነት የፀሐይን ተፈጥሯዊ ዑደት በትክክል መከተል ላይ ያደርጋል። ዓመቱ 365 ቀናት በሚሆንበት ጊዜ ለ7 ሲካፈል 52 ሳምንታትና 1 ተረፈ ቀን ይኖረዋል። ይህች አንድ ተረፈ ቀን በየዓመቱ መስከረም 1 (የአዲስ ዓመት መባቻ) የሚውልበትን የሳምንት ዕለት በ1 ቀን ወደፊት እንድትሸጋገር ታደርጋለች። ለምሳሌ መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም. ዓርብ የሚውል ከሆነ፣ 2019 ዓ.ም. ዘመነ ሉቃስ (ጳጉሜ 6) በመሆኑ መስከረም 1 ቀን 2020 ዓ.ም. ደግሞ እሁድ ይውላል ማለት ነው።
ካላንደሩ የፀሐይን ፍጥነት በትክክል ለመከተል በየ4 ዓመቱ 1 ተጨማሪ ቀን (ጳጉሜ 6) በመጨመር የካላንደሩ እና የሥነ-ፍጥረቱ ወቅቶች ሳይዛቡ ሁልጊዜ ተጣጥመው እንዲቀጥሉ ያደርጋል።
በአጠቃላይ፣ የመጽሐፈ ሄኖክ ካላንደር ለቀናትና ለሳምንታት ቋሚ መዋቅር ቅድሚያ ሲሰጥ፣ የኢትዮጵያ የ365/366 ቀናት አቆጣጠር ደግሞ ከተፈጥሮና ከወቅቶች መደጋገም ጋር ለሚደረግ ፍጹም መጣጣም ቅድሚያ የሚሰጥ ጥበብ ነው።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት ዓመታት በ4 አውደ-ወንጌላውያን (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ) ስም ተከታታይ በሆነ ዑደት ይሽከረከራሉ። የየዓመቱ ወንጌላዊ የሚወጣው ዓመተ ዓለምን ለ4 በማካፈልና የሚቀረውን ተረፍ በማየት ነው።
የስሌቱ ደረጃዎች፦
1. ዓመተ ዓለምን መፈለግ፦ አሁን ያለንበትን ዓመተ ምሕረት ከዓመተ ኩነኔ (5500 ዓመታት) ጋር መደመር።
ዓመተ ዓለም=ዓመተ ምሕረት+5500
2. ለ4 ማካፈል፦ የተገኘውን ዓመተ ዓለም ለአራቱ ወንጌላውያን (ለ4) ማካፈል፦
ዓመተ ዓለም÷4
3. ቀሪውን (ተረፉን) መመልከት፦ አካፍለን ከደረሰን በኋላ የሚቀረውን ቁጥር መሠረት በማድረግ የወንጌላዊው ስም ይለያል፦
o ቀሪው 1 ከሆነ፦ ዘመነ ማቴዎስ
o ቀሪው 2 ከሆነ፦ ዘመነ ማርቆስ
o ቀሪው 3 ከሆነ፦ ዘመነ ሉቃስ (ይህ ዓመት ጳጉሜ 6 የምትሆንበት የመጠቅለያ ወይም የሠግር ዓመት ነው)
o ቀሪው 0 ከሆነ፦ ዘመነ ዮሐንስ
(ማስታወሻ፦ 5500 ለ4 ሲካፈል ቀሪ ስለሌለው፣ ዓመተ ምሕረቱንም በቀጥታ ለ4 በማካፈል ተረፉን ማወቅ ይቻላል።)
ተግባራዊ ምሳሌዎች፦
- ምሳሌ 1 (ለ2018 ዓ.ም.)፦
- ዓመተ ዓለም = 2017+5500=7517
- 7517÷4=1879 ደርሶ 1 ይቀረናል።
- ቀሪው 1 ስለሆነ፣ 2017 ዓ.ም. ዘመነ ማቴዎስ ነው።
- ምሳሌ 2 (ለ2019 ዓ.ም.)፦
- ዓመተ ዓለም = 2019+5500=7519
- 7519÷4=1879 ደርሶ 3 ይቀርናል።
- ቀሪው 3 ስለሆነ፣ 2019 ዓ.ም. ዘመነ ሉቃስ ይሆናል (ጳጉሜ 6 የምትሆንበት ዓመት)።
በ መስከረም 1 እና በጃንዋሪ 1 አዲስ ዓመትን መጀመር
በባሕረ ሐሳብ አቆጣጠር መስከረም 1 ሲጀምር ሌሎች በጃንዋሪ 1 ለምን ይጀምራሉ ? የሚለውን ጥያቄ በአንባቢያን ዘንድ መነሳቱ አይቀሬ ነው ምክንያቱግን የሚከተለው ይሆናል፡፡
ፀሐይ በምሥራቅ አድማስ ብቅ ብላ የጨለማውን መጋረጃ ስትገፍ፣ ለአዲሱ ቀን መወለድ የመጀመሪያው የብርሃን እስትንፋስ ይነፍሳል። በኢትዮጵያ ባህልና ዘመን አቆጣጠር የዕለት ቆጠራ የሚጀምረው ከዚሁ ከተፈጥሮ የመጀመሪያ የብርሃን መገለጥ—ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ነው። የምዕራባውያን አቆጣጠር ሕጋዊ ቀኑን በጨለማ እኩለ ሌሊት (00:00) ከነበረው ጥንታዊ የሮማውያን የሲቪል ካላንደር ሥርዓት ወርሶ ሲጀምር፣ በኢትዮጵያ ግን የሰዓታት ቆጠራ ከተፈጥሮ ሕያው እንቅስቃሴ ጋር ቀጥታ የተሳሰረ ነው።
ብርሃኑን «መዓልት»፣ ጨለማውን ደግሞ «ሌሊት» ብሎ ከሰየመው የሥነ-ፍጥረት ሕግ (ዘፍጥረት 1፥3-5) እና መድኃኒታችን «ኢየሱስም መልሶ፦ ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤» (ዮሐንስ 11፥9) ብሎ ካስተማረው መለኮታዊ ትምህርት ጋር ፍጹም ይስማማል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለምድር ወገብ ቅርብ በመሆኗ፣ ዓመቱን ሙሉ ፀሐይ በ12:00 ሰዓት ወጥታ በ12:00 ሰዓት የምትገባበት ተፈጥሮአዊ ድንቅ መጣጣም አላት
ከሰዓታት አቆጣጠሩ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ እና በጎርጎሮሳውያን ካላንደር መካከል ያለው የ7 እና የ8 ዓመታት ልዩነትም የራሱ የሆነ ጥልቅ ታሪካዊና ሥነ-ቁጥራዊ ምሥጢር አለው። በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የእስክንድርያው መነኩሴና ሊቅ አንያኖስ (Annianus) ከዓለም ፍጥረት (5500 ዓ.ዓ) ተነሥቶ በሠራው ስሌት፣ ክርስቶስ የተጸነሰው በመጋቢት 29 ቀን፣ የተወለደው ደግሞ በታኅሣሥ 29 ቀን እንደሆነ አወጣ። በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ዲዮናስዮስ ኤክሲጉኦስ የተባለው ሮማዊ መነኩሴ የክርስቶስን ልደት ከሮም ከተማ መቆርቆር (753 AUC) ጋር አያይዞ ሲያሰላ የስሌት ስህተት በመሥራቱ ከእስክንድርያው መነሻ በ7 እና በ8 ዓመታት ዘገየ።
ይህ የዓመታት ልዩነት ቋሚ ሳይሆን በየዓመቱ በ7 እና በ8 መካከል የሚቀያየርበት ምክንያት ከሁለቱ ካላንደሮች የአዲስ ዓመት መባቻ መፋለስ ጋር ይያያዛል። ምዕራባውያን አዲስ ዓመታቸውን በጃንዋሪ 1 ሲቀበሉ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ አዲስ ዓመት (መስከረም 1) እስከ ገባች ድረስ ባሉት ስምንት ወራት ተኩል ውስጥ በሁለቱ አቆጣጠሮች መካከል ያለው ልዩነት 8 ዓመት ሆኖ ይቆያል። መስከረም 1 ቀን (ሴፕቴምበር 11) ሲጠባና ኢትዮጵያ አዲሱን ዓመት ስታበስር ግን እስከ ዲሴምበር 31 ባሉት ሦስት ወራት ተኩል ገደማ ውስጥ ልዩነቱ ወደ 7 ዓመት ዝቅ ይላል።
የኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ አቆጣጠር መስከረም 1 ሲጀምር ሌሎች በጃንዋሪ 1 በሚቀበሉበት ሂደት ውስጥ ትልቅ የተፈጥሮና የፍልስፍና ልዩነት ይታያል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም ሲጠባ ክረምቱ አልፎ፣ አደይ አበባ ፈክቶና ምድር አዲስ አልባስ ለብሳ ተፈጥሮ በራሷ ውበት አዲስ ዓመትን ስታበስር፣ ሌሎች በጃንዋሪ 1 በበረዶና በቁር ወራት አዲስ ዓመታቸውን ይቀበላሉ። ይህም የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀናትንና ሰዓታትን በወረቀት ላይ የተጻፉ ቁጥሮች ብቻ ሳያደርጋቸው፣ ከሰማይ ብርሃናትና ከምድር ወቅታዊ ህልውና ጋር ተጋብተው የሚኖሩ የሕይወት እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ያሳያል።
መስከረም 1 ሲጠባ አደይ አበባ አብቦና ምድር አዲስ አልባስ ለብሳ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ድንቅ የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት ዘንድ የጽንፈ ዓለም ሰዓትና የዘመናት ዑደት እንደገና መቁጠር የሚጀምርበት ታላቅ የጥበብ የምስራች ይበሰራል። በባሕረ ሐሳብ ስሌት፣ ዘመን መለወጥ ማለት እንዲሁ በቀናት መፈራረቅ የሚተካ ተራ ክስተት ሳይሆን፣ የጊዜ ክፍፍልንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ ያለምንም የቁጥር መዛባት በሁለት መሠረታዊ መመሪያዎች በሰባቱ መስፈርታት እና በሰባቱ አዕዋዳት ሚዛን በመስፈር የሚታወጅ ጥልቅ ሥነ-ቁጥራዊ ኩነት ነው።
ሊቃውንቱ የፀሐይና የጨረቃን የፍጥነት ልዩነት በስሌት ትክክለኛነት ለመለካት «ሰባቱ መስፈርታት» የሚባሉትን የጊዜ ስፍሮች ይጠቀማሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሙሉ ቀን ዕለት (24 ሰዓት) ሲሆን፣ ይህ ዕለት በ60 ተከፍሎ ኬክሮስ (1 ኬክሮስ = 24 ደቂቃ) ይገኛል፤ ኬክሮስም በ60 ተከፍሎ ካልዒት (1 ካልዒት = 24 ሰከንድ) ይሆናል። ስሌቱ በዚህ ብቻ ሳይቆም ካልዒትን በ60 በማካፈል ሣልሲት፣ ሣልሲትን በ60 በመክፈል ራብዒት፣ ራብዒትን በ60 በመክፈል ኃምሲት፣ እና ኃምሲትን በ60 በመክፈል እስከ ሳድሲት ድረስ ይወርዳል። ይህ በ60 ቁጥር መሠረትነት ላይ የተገነባው ክፍፍላዊ ረቂቅ ክፍፍል የከዋክብትን ረቂቅ ጉዞ ሳይቀር ሳይታወክ በትክክል ለመለካት የሚያስችል የሊቃውንቱ የዘመን መለኪያ ሚዛን ነው።
እነዚህ ረቂቅ የጊዜ ስፍሮች ተደማምረው ደግሞ የታላላቅ ዘመናትን ዑደት «ሰባቱን አዕዋዳት» ይፈጥራሉ። ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉትን ቀናት የሚይዘው ዐውደ ዕለት (7 ቀናት)፣ በፀሐይ 30 ቀናትን በጨረቃ ደግሞ 29 ወይም 30 ቀናትን የሚይዘው ዐውደ ወርኅ፣ እንዲሁም ዓመቱን በ365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ (6 ሰዓት) የሚለካው ዐውደ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ናቸው። እነዚህ ተከማችተው ወደ 28 ዓመታት ሲያድጉ ዐውደ ፀሐይ ይፈጠራል፤ በዚህም ዑደት አራቱ ወንጌላውያን እና 7ቱ የሳምንቱ ዕለታት (4 ሲባዛ 7 = 28 ) ተገናኝተው ከ28 ዓመት በኋላ መስከረም 1 በዚያው ተመሳሳይ ዕለትና በዚያው ወንጌላዊ ላይ እንደገና ይውላል።
ከዚህም በላይ የጨረቃንና የፀሐይን ዑደት የሚያስተሳስረው የ19 ዓመቱ ዐውደ አበቅቴ (ዐውደ ጨረቃ) ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሜቶኒክ ዑደት የሚባለው ይከተላል። ይህ ዑደት በ4 ተባዝቶ ዐውደ ማኅተም (76 ዓመታት) የሚፈጥር ሲሆን፣ የባሕረ ሐሳብ ሁሉ ማጠቃለያና ታላቁ የዘመን ዑደት የሆነው ዐውደ ቀመር (ማኅተም ዓቢይ) ደግሞ የዐውደ ፀሐይንና የዐውደ አበቅቴን ብዛቶች በማጣመር (28 ሲባዛ 19 = 532) በየ532 ዓመቱ ይፈጸማል። ከ532 ዓመታት በኋላ የሳምንቱ ዕለት፣ ወንጌላዊው፣ አበቅቴው እና መጥቁ ሙሉ በሙሉ መጀመሪያ በነበሩበት ቦታ ላይ ተገናኝተው የዘመን ካላንደሩ አዲስ ሆኖ ይጀምራል።
በመስከረም 1 አዲስ ዓመት ሲታወጅ፣ እነዚህ ሰባቱ መስፈርታትና ሰባቱ አዕዋዳት ተጣጥመው የፈጠሩት የከዋክብትና የዘመን ድንቅ ዜማ አብሮ ይበሰራል። የኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መስከረም 1 ቀን ሲያወጅ የቁጥሮችና የዑደቶች ፍጹም ህብረት የታየበትን፣ የሰው ልጅ ከጽንፈ ዓለም ጋር ያለውን የጊዜ ትስስር የሚያድስበትን ታላቅ የጥበብ አዋጅ ለዓለም ያበስራል።
በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ትምህርት ውስጥ «ዐውደ ቀመር» ወይም «ማኅተም ዓቢይ» የሚባለው የ532 ዓመታት ታላቅ ዑደት፣ የጊዜ መቁጠሪያ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ-ከዋክብታዊ ጥበብ አጣጥሞ የያዘ ማዕከል ነው። ይህ ታላቅ ዑደት የሚፈጠረው አራቱ ወንጌላውያንና ሰባቱ የሳምንቱ ዕለታት የሚገናኙበት «ዐውደ ፀሐይ» (28 ዓመታት)፣ የፀሐይና የጨረቃ ዑደት ተመልሶ የሚገጥምበት «ዐውደ ጨረቃ» ወይም «ዐውደ አበቅቴ» (19 ዓመታት) ጋር ተባዝተው (28 ሲባዛ 19 = 532) በሚፈጥሩት ፍጹም የሂሳብ ቀመር ነው። ከእነዚህ 532 ዓመታት ፍጻሜ በኋላ የሳምንቱ ዕለት፣ ወንጌላዊው፣ አበቅቴው እና መጥቁ ሙሉ በሙሉ ወደነበሩበት የመነሻ ቦታ ተመልሰው አዲስ ዑደት ይጀምራሉ።
የ532 ዓመታት ዑደት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ጥልቅ መንፈሳዊና ምሥጢራዊ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ዐውደ ቀመር በፈጸመ ቁጥር ዓለም ተመልሳ እንደ አዲስ እንደተፈጠረች ይቆጠራል፤ ይህም እግዚአብሔር ለሥነ-ፍጥረት የሰጠውን መለኮታዊ ሥርዓት፣ ምሉዕነትና የተፈጥሮን መታደስ የሚያበስር ነው። ከዚህም ባሻገር የክርስቶስ የድህነት ታሪክ፣ የትንሣኤው ምስጢር እና የዓመታቱ አጽዋማትና በዓላት ቅደም ተከተል በስሌቱ ውስጥ ያለምንም የቀናት መዛባት እንዲጠበቁ ያደርጋል።
በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ብርሃናት (ፀሐይና ጨረቃ) ከዕለታትና ከወንጌላውያን ጋር ተጣጥመው ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት የብርሃናት ፍጹም ህብረት የሚገለጥበት ድንቅ ቀመር ነው።
ኢትዮጵያ በሌሎች የውጭ አቆጣጠሮች ላይ ሳትጠጋጋ በራሷ ሊቃውንት ጥበብ ተመርታ እንድትቀጥል ያደረጋትና የካላንደር ነፃነቷን ያረጋገጠላት ዋነኛው መሠረት የዚሁ የ532 ዓመት የዐውደ ቀመር ስሌት ትክክለኛነት ነው። የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሐፍትና ሊቃውንት የነገሥታቱን ዘመነ መንግሥት፣ ታላላቅ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ክስተቶችን እንዲሁም የትውልድ ሐረጎችን ያለ ስህተት ለመመዝገብ የተጠቀሙበት ዋና የታሪክ መመዝገቢያቸው ዐውደ ቀመር ነበር።
የዓለም አቀፍ ምሁራን ምስክርነት
ታዋቂው የብራና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ «ባሕረ ሐሳብ፦ የዘመን ቆጠራ ቅርሳችን» (1993 ዓ.ም) በታተመው መጽሐፋቸውና በAethiopica ጆርናል ላይ እንደጻፉት፣ የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት የመጽሐፈ ሄኖክን የብርሃን ደጃፎች ከመዓልትና ሌሊት እኩልነት (Equinox) ጋር አያይዘውታል። እግዚአብሔር ብርሃንን ከጨለማ ሲለይ ሁለቱንም በ12 ሰዓት እኩል ሚዛን ማድረጉ መስከረም 1 ቀን ስለሚጠበቅ የቀን መቁጠሪያው መነሻ ሆኗል በማለት በጥናታቸው እና በመጽሐፋቸው አስረድተዋል።
በተጨማሪም ኦቶ ኑገባወር (Otto Neugebauer)፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ እና ጄምስ ቫንደርካም (James C. VanderKam) በታወቁ አህጉራዊ ሳይንሳዊ ጆርናሎች (Sitzungsberichte der Österreichischen Akademie der Wissenschaften, Journal for the Study of Judaism) ባወጧቸው ጥናቶች፣ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከአይሁድ-ክርስቲያን የፀሐይ ዑደት ጋር የተሳሰረና የተፈጥሮን ሚዛን የጠበቀ ጥንታዊ ቅርስ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መስከረም 1 ቀን ለኢትዮጵያውያን የወቅቶች መለወጫ ብቻ አይደለም። ከተፈጥሮ ዑደት፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ፣ ከጥልቅ የባሕረ ሐሳብ ስሌትና ከሃይማኖታዊ ተስፋ ጋር የተያያዘ የለውጥ መባቻ ነው። አዲስ ዓመት ሲመጣ ወሩና ወቅቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወታችንም በመልካም ምግባር፣ በንስሐና በአዲስ ተስፋ ሊታደስ እንደሚገባ የሊቃውንቱ አስተምህሮ ያሳስበናል።
ዋቢ መረጃዎች (References)
1. የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና አጠቃቀሙ – በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ – ማኅበረ ቅዱሳን
2. መጽሐፈ ባሕረ ሐሳብ (የአባ ድሜጥሮስ ቀመር)፦ በ3ኛው ክፍለ ዘመን በ12ኛው የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ድሜጥሮስ የተዘጋጀና በቤተክርስቲያን ሊቃውንት የተተረጎመ ጥንታዊ የስሌት መጽሐፍ።
3. አቡሻኽር (Abushahir)፦ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈና በኢትዮጵያ ሊቃውንት የተብራራ የታሪካዊና የስነ-ኮከብ ስሌቶች ጥሁፍ።
4. መጽሐፈ ሄኖክ (ምዕራፍ 72–82)፦ ስለ ብርሃናት አካሄድ፣ ስለ መስኮቶች/ደጆችና ስለ ሰዓታት ክፍፍል የሚናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንጭ።
5. የባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ (በሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕረ ሐሳብና የስነ-ኮከብ ትምህርት ማብራሪያ።
6. https://eotcmk.org/e/biblical-literalist-chronology
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ