የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ - የታላቋቋ ባቢሎን መውደቅ /ክፍል አራት /

 የታላቋቋ ባቢሎን መውደቅ


የባቢሎን ግዛት በታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ አስደናቂና በሀብት የበለጸጉ ስልጣኔዎች አንዱ ነበር። በተለይ በናቡከደነጾር ዘመን (605-539 ..) የነበራት ገጽታ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው እንደ ተረት የሚመስል ውበት የነበራት ታላቅ በወርቅ የተንቆጠቆጠች ከተማ ነበረች።


1. የምድር ጌጥ የሆነችው ከተማ


ባቢሎን በዚያ ዘመን የዓለም የንግድ፣ የጥበብና የሀብት ማዕከል ነበረች። ሄሮዶተስ (Herodotus) "የታሪክ አባት" በመባል የሚታወቀው የግሪክ ታሪክ ጸሐፊ ስለ ባቢሎን ግንቦች ግርማና ስለ ከተማዋ ስፋት በዝርዝር ጽፏል። ከተማዋ በታላላቅ ግንቦች የታጠረች ሲሆን፣ ግንቦቹ ላይ ሁለት ሰረገላዎች ጎን ለጎን ካለምንም ችግር መሮጥ ያስችሉ ነበር ይባላል። የከተማዋ መግቢያ የነበረው "የኢሽታር በር" (Ishtar Gate) መስተዋት በሚመስሉ ሰማያዊ ጡቦች የተሠራና በፈረሶችና በዘንዶዎች ምስል ያጌጠ በመሆኑ፣ ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶች በሙሉ በከተማዋ ግርማ ይገረሙ ነበር።

 

ለባቢሎን ከተማ ስምንተኛውና ዋናው መግቢያ በር የነበረው "የኢሽታር በር" በወቅቱ በባቢሎን ብትመለከው ለፍቅርና ለጦርነት አምላክ "ኢሽታር" የተሰጠ በመሆኑ በሷ ስም ተሰይሟል። በነገራችን ላይ የኢሽታር በር (Ishtar Gate) በጀርመን አርኪኦሎጂስቶች ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን አገር፣ በርሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፐርጋሞን ሙዚየም (Pergamon Museum) ውስጥ ነው። የፐርጋሞን ሙዚየም ለትልቅ እድሳት (Renovation) ሲባል ለተወሰኑ ዓመታት ለጎብኚዎች ተዘግቷል። እድሳቱ እስከ 2027 ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ስለሚችል፣ በአካል ሄዶ ለማየት የሚፈልግ ሰው አስቀድሞ የሙዚየሙን ድረ-ገጽ ማረጋገጥ ይኖርበታል። መጎብኘት የቻለ ሰው ፎቶ ተነስቶ ይህን ታሪክ ያጋራን  ይሆናል ?

 

2. የዓለም ድንቅ፦ የባቢሎን ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ


ቤሮሰስ (Berossus) 3ኛው ክፍለ ዘመን .. የነበረ የባቢሎን ካህን ሲሆን፣ ስለ ናቡከደነጾር የግንባታ ሥራዎችና ስለ "ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራዎች" መረጃ ጥሏል። ናቡከደነጾር ከሜዶን ላገባት ሚስቱ (አሚቲስ) የትውልድ አገሯን ተራራማና አረንጓዴ ገጽታ ትናፍቅ ስለነበር ለዚያ ብሎ በባቢሎን ሜዳ ላይ ሰው ሠራሽ ተራራ አስገነባላት። ይህ "የተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ" ተብሎ የሚታወቀውና ከዓለም ሰባት ድንቆች አንዱ የሆነው ስፍራ ሲሆን፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ በረቂቅ ጥበብ ውኃ እየተቀዳ የሚጠጣ ደረጃ በደረጃ የተገነባና አረንጓዴ ገነት የሚመስል ውብ የአትክልት ሥፍራ ነበር።


3. የወርቅና የንግድ ማዕከል


በባቢሎን ውስጥ የሚገኙት ቤተ መቅደሶች፣ በተለይም የባዕድ አምላኩ "ማርዱክ" መቅደስ፣ በወርቅ የተለበጡ ነበሩ። ከተማዋ ከሕንድ እስከ ግብፅ ባለው የንግድ መስመር መካከል ስለምትገኝ፦


   ከየአቅጣጫው የሚመጡ ውድ ጨርቆች፣ ቅመማ ቅመሞችና ዕንቁዎች ይፈሱባት ነበር።


   ሕንጻዎቿ በደማቅ ቀለማት ያሸበረቁና በሥነ-ሕንጻ ጥበብ የመጠቁ ነበሩ።


   ከተማዋን በሁለት በኩል የሚከፍላት የኤፍራጥስ ወንዝ ለከተማዋ ግርማና ለንግድ ሥራዋ ትልቅ አንቀሳቃሽ ነበር።


4. የታሪክና የጥበብ መፍለቂያ


ናቡከደነጾር ከተማዋን ሲገነባት "ለዘላለም እንድትኖር" አስቦ ከተማዋ በታሪክ ስትታወስ እንድትኖር በእያንዳንዱ ጡብ ላይም ስሙን ያሳርፍ እንደነበር ይነገራል። ባቢሎን በሀብት እና በታሪካዊነት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትም የመጠቀች ነበረች። የከዋክብት ምርምር እና የሒሳብ ጥበብ እጅግ የዳበረባት ስፍራ ሆና ነበር።


የባቢሎን ውድቀት (በ539 ዓ.ዓ.)


ባቢሎን በዚያ ዘመን የነበራት ውበትና ሀብት "የወርቁ ራስ" መባሏ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ሆኖም ግን፣ ነቢዩ ዳንኤል አስቀድሞ እንደተነበየው፣ ይህ ሁሉ ግርማና ሞገስ 539 .. በፋርሳውያን እጅ ወድቆ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።


 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ዘንድ ታዋቂውን የታሪክ መጽሐፍ "ዜና አይሁድ" የጻፈው ዮሴፍ ወልደኮርዮን በኋላ ወደ ሮም ከሄደ በኋላ "ፍላቪየስ" የሚለውን የሮማውያን ስም ወስዷ ፍላቪየስ ጆሴፈስ (Flavius Josephus ) ተብሎ የሚታወቀው በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው 20 ጥራዞች ተከፋፍሎ የቀረበ ታላቅ ድርሳን አዘጋጅቷል። የታሪካዊ ጽሁፉ የታሪካ ዋና ዓላማው ለአረማውያን (ለሮማውያንና ለግሪካውያን) የአይሁድን ታሪክ፣  ባህልና ሃይማኖት ጥንታዊነትና ክብር ለማስረዳት ነው። ከጻፋቸው ታሪክ ውስጥም የናቡከደነጾርንና የዳንኤልን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ምንጮች አቀናጅቶ መከተቡ ነው።


የባቢሎን ውድቀት በታሪክ ውስጥ በጣም ከሚታወቁትና በብልሃት ከተመሩ ድሎች አንዱ ነው። ባቢሎን በታላላቅ ግንቦች የታጠረችና በጣም የሰለጠነ የጦር ሠራዊት የነበራት ለዓመታት የሚበቃ ምግብ ያከማቸች ስለነበረች፣ በጦርነት ሰብሮ ለመግባት የማይቻል ይመስል ነበር። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የቆረጠው ቀን ሲመጣ አወዳደቋ የእንቦይ ካብ ሆነ እንዲህም ሆነ፦


  የቂሮስ ብልሃት፦ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ (Cyrus the Great) የከተማዋን ቅጥሮች ሰብሮ መግባት እንደማይችል ሲረዳ፣ እንዲህ ብልሀት አሰበ በከተማዋ መካከል የሚያልፈውን የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫ አስቀይሮ በወንዙ በኩል ወደ ከተማዋ ለግባት አቀደ።


  የወንዙ መድረቅ፦  የወንዙን አቅጣጫ በመቀየሩ የወንዙ ውሃ ዝቅ ሲል፣ የፋርስ ወታደሮች በወንዙ የታችኛው ስር ተሹለክልከው ወደ ከተማዋ ገቡ።


  የበልጣሶር ድግስ፦ በዚያው ምሽት የናቡከደነጾር የልጅ ልጅ የሆነው ንጉሥ በልጣሶር በቤተ መንግሥቱ ለሺህ መኳንንት ታላቅ ግብዣ እያደረገ ነበር። በዚያ ድግስ ላይ ከኢየሩሳሌም መቅደስ የተማረኩትን የወርቅ ዕቃዎች ለወይን መጠጫነት ተጠቀሙ።


  በግድግዳው ላይ የተጻፈው ጽሕፈት፦ በድንገት የሰው እጅ ጣቶች መጥተው በግድግዳው ላይ "ሜኔ፥ ሜኔ፥ ቴቄል፥ ፋሬስ" የሚል ጽሕፈት ጻፉ። ትርጉሙም "መንግሥትህ ተቆጠረ፣ በሚዛን ተመዘንህ ቀልለህም ተገኘህ፣ መንግሥትህም ለሜዶንና ለፋርስ ተሰጠች" የሚል ነበር።


  የመጨረሻው ውጤት፦ በዚያው ሌሊት በልጣሶር ተገደለ፤ ያለ ምንም ትልቅ ውጊያ ታላቂቱ ባቢሎን በፋርስ ቁጥጥር ስር ወደቀች።


ክፍል አምስት  ይቀጥላል፡፡   


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...