-->

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጣዊ ክፍል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ የፀሐይ መውጫ የተረጋጋ መንፈሳዊ መንገድ
አዲስ ገጽ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

ገጹን ይመልከቱ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

 

በያዕቆብ ሰንደቁ

መስከረም 8 ቀን 2019ዓ.ም


 

"የቢራ ጎርፍ"

ጥቅምት 17 ቀን 1814 እ.ኤ.አ. ለንደን ከተማ ያልተለመደ እና አስገራሚ ማዕበል አስተናገደች። ሙክስ ኤንድ ካምፓኒ በተባለው የቢራ ፋብሪካ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ቢራ የያዘ ግዙፍ የእንጨት በርሜል በድንገት ፈነዳ። የዚህ በርሜል መፈንዳት በአቅራቢያው የነበሩ ሌሎች በርሜሎችም ተከታትለው እንዲፈነዱ አደረገ። በቅጽበት ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ የሚሆን ጠቆር ያለ ቢራ የፋብሪካውን የጡብ ግድግዳ በኃይል አፍርሶ በመውጣት፣ እስከ 4.5 ሜትር ከፍታ ባለው ማዕበል የለንደንን ጎዳናዎች አጥለቀለቀው። ይህ እንደ ሱናሚ የተንከባለለው የቢራ ጎርፍ ቤቶችን አፈረሰ፤ በጎዳና እና በቤታቸው የነበሩ ስምንት ሰዎችን ጠርጎ በመውሰድ ለህልፈት ዳረጋቸው። አደጋውን የተመለከተው ፍርድ ቤት ክስተቱን "በእግዚአብሔር ፈቃድ የተከሰተ" በማለት ፋብሪካውን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ አደረገው።

 

ይህ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የተከሰተ ታሪክ፣ ዛሬ ለኛ ምን ትርጉም አለው? ብልህ ሰው ከታሪክ ይማራልና፣ የዚያን ቀን የለንደን ነዋሪዎችን በድንገት ጠርጎ የወሰደው የቢራ ጎርፍ፣ ዛሬም በተለየ መልክ እና በማይታይ ማዕበል በየከተሞቻችን ይፈሳል።

 

የዘመናችን የቢራ ጎርፍ ድምፅ የለውም፤ ግድግዳ አያፈርስም። ይልቁንም፣ በመዝናኛ ስፍራዎች በሳቅ፣ በጫጫታ እና በሙዚቃ ታጅቦ፣ ሰዎችን እያሳሳቀ ይወስዳል። አብዛኛው ወጣት የመጀመሪያውን እርምጃ የሚያደርገው በነፃነት ስም አንዲት ጠርሙስ ወይም ብርጭቆ በማንሳት ነው። ሆኖም፣ ይህች ትንሽ ጅረት እያደገች ስትመጣ፣ ወጣቱን ከአንዱ መጠጥ ቤት ወደ ሌላው የሚያንገላታ፣ ደሞዙን፣ ኑሮውን እና ራዕዩን ጠርጎ የሚወስድ አደገኛ ሱናሚ ትሆናለች።

 

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) መረጃዎች ይህንኑ ስጋት ያረጋግጣሉ። ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ፋብሪካ ውጤቶች ድረስ ያለው የአልኮል መጠጥ ፍጆታ በወጣቶችና በአዋቂዎች ዘንድ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው። ይህ እያደገ የመጣው የፍጆታ መጠን በግለሰቦች ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር፣ የአገሪቱን የወደፊት አምራች ኃይል እና ማህበራዊ መረጋጋት በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል።

 

ለዚህ ጎርፍ መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት «መጠጣት የዘመናዊነት እና የነጻነት መገለጫ ነው» የሚለው የተዛባ እና ጎጂ አስተሳሰብ ነው። ብዙ ወጣቶች አልኮልን መግዛት እና መጠጣት ከማህበራዊ ደረጃ መሻሻል ጋር ሲያያይዙት፣ መንፈሳዊ እና ባህላዊ እሴቶችን በተለይ መጠጥ ጠጥቶ አለመስከርን ግን እንደ ኋላቀርነት መቁጠር ጀምረዋል።

 

በዚህ እያሳሳቀ በሚወስድ አጥፊ ማዕበል ከሚወሰዱት መካከል የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ወጣቶች በብዛት ይገኙበታል። ጎርፍ ሲወስድ እያሳሳቀ እንደሆነ ሁሉ፣ ብርቱ መጠጥም ጊዚያዊ ደስታን እየሰጠ ውስጣዊውን ማንነት በዝምታ ያፈርሳል። የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ የሆነው የሰውነት መቅደስ በስካር ማዕበል ሲናድ፣ የበርካቶች ትዳር ይፈርሳል፣ ራዕይም ይጨልማል።

 

መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን አታላይ የህይወት ጎርፍ አስቀድሞ አስጠንቅቋል። ጠቢቡ ሰሎሞን "የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።" (ምሳሌ 20፡1) በማለት የመጠጥን አሳሳችነት በግልጽ አስቀምጦታል። በየመጠጥ ቤቱ በሕይወታቸው ላይ የሚያፌዙ እና በስካር ማዕበል የሚንገላቱ ወጣቶች የዚህ ቃል ህያው ማሳያዎች ናቸው።

 

ክርስትና ስካርን አጥብቆ ይቃወማል። የፈጠረንን አምላክ ረስተን በማይታየው የመጠጥ ማዕበል መወሰድ መጨረሻው ጥፋት መሆኑን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መንግሥተ ሰማያትን ከማይወርሱት ዝርዝር ውስጥ ሰካሮች በግንባር ቀደምትነት በመጥቀስ አስተምሮናል (1ኛ ቆሮ. 6፡10፣ ገላትያ 5፡21)።

 

የ1814ቱ የለንደን የቢራ ጎርፍ ሰዎች ሳያስቡት የደረሰ ድንገተኛ አደጋ ነበር፤ የዘመናችን የመጠጥ ማዕበል ግን እያየነው በገዛ እጃችን የምንገባበት፣ ስሜታችንን አደንዝዞ ህይወታችንን የሚሰርቅ አጥፊ ኃይል ነው። ከዚህ ማዕበል ለመትረፍ መፍትሔው ሐዋርያው እንዳዘዘን ወደ እውነተኛው እና ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ቤት መመለስ ብቻ  ላለፈው ንሥሐ ለቀጣዩ እንዲጠብቀን ጸሎት ብቻ ነው፦

 

"መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤።"

 (ኤፌሶን 5፥18)

ይቆየን!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

Image 1
Image 2
Image 3
Image 4

የሳምንቱ የመፅሐፍ ቂዱስ ጥቅስ

"በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም መንገድህን ያቀናልሃል።" ምሳሌ 3፡5-6

Video