ዓርብ 23 ጃንዋሪ 2026
ናቡከደነጾር (Nebuchadnezzar II) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
ናቡከደነጾር (Nebuchadnezzar II) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የባቢሎን ንጉሥ ሲሆን፣ ታሪኩ በሰፊው የሚገኘው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነው። በተለይም በትንቢተ ዳንኤል እና በሁለተኛ ነገሥት ላይ በዝርዝር ተጽፏል። ናቡከደነጾር ዋናው የታሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚገኙባቸው ምዕራፎችና ቁጥሮች የሚከተሉት ናቸው፦
በትንቢተ ዳንኤል
ናቡከደነጾር ከነቢዩ ዳንኤል ጋር የነበረው ግንኙነትና ያያቸው ሕልሞች እዚህ ይገኛሉ፦
· ዳንኤል ምዕራፍ 1፦ ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ማርኮ ወደ ባቢሎን እንደወሰዳቸው ይናገራል።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ወደ ሰናዖር ምድር ወደ አምላኩ ቤት ወሰደው፥ ዕቃውንም ወደ አምላኩ ግምጃ ቤት አገባው።
ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም ሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ለጃንደረቦች አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ።
· ዳንኤል ምዕራፍ 2፦ ንጉሡ ያየው የታላቁ ምስል ሕልም እና ዳንኤል ሕልሙን የፈታበት ክፍል
ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።
ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፤ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ። ስለዚህም ንጉሡ ተበሳጨ እጅግም ተቈጣ፥ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ። ትእዛዝም ወጣ፥ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፤ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉ ዘንድ ፈለጉአቸው።
የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘበኞቹ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረው፤ ለንጉሡም አለቃ ለአርዮክ መልሶ፦ የንጉሡ ትእዛዝ ስለ ምን ቸኰለ? አለው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል አስታወቀው።
ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ። የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው። የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ።
· ዳንኤል ምዕራፍ 3፦ ንጉሡ የወርቅ ምስል አቁሞ እንዲሰገድ ማዘዙ፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን ወደ እቶን እሳት ማስጣሉና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸው።
ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ።
አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።
· ዳንኤል ምዕራፍ 4፦ ንጉሡ በትዕቢቱ ምክንያት አእምሮውን ስቶ እንደ አራዊት ለሰባት ዓመታት በጫካ መኖሩና በኋላም ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገኑ።
ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር። ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ።
ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና፦ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፦ መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው።
በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና።
በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።
#ናቡከደነጾር #Nebuchadnezzar #ዳንኤል #ባቢሎን #ወርቅ
ንጉሥ ናቡከደነጾርን በጣም ያስጨነቁት ሕልሞች ይቀጥላል
ናቡከደነጾርን ያስጨነቀው ሕልም እና የነቢዩ ዳንኤል ፍቺ፡፡
የታላቁ ምስል ሕልም (ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 2)
አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፤ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፤ መልኩም ግሩም ነበረ። የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ፡፡
ናቡከደነጾርን ያስጨነቀው ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን ብሎ ነቢዩ ዳንኤል ከ እግዚአብሔር በተሰጠው ጥበብ ተረጎመለት። ይህ ሕልም ስለ ወደፊቱ የዓለም መንግሥታት ታሪክ የሚያሳይ ነበር። ንጉሡ በሕልሙ አንድ ግዙፍና የሚያስፈራ ምስል አየ፤ የምስሉ አካላት ከተለያዩ ማዕድናት የተሠሩ ነበሩ፦
1. ራሱ፦ ከጥሩ ወርቅ (ይህም የናቡከደነጾር የባቢሎን መንግሥት ነው)።
· ትርጉሙ፦ ነቢዩ ዳንኤል ለናቡከደነጾር "ንጉሥ ሆይ፥ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ... የወርቁ ራስ አንተ ነህ" ባለው መሰረት የታላቁ ምስል ራስ ትርጉሙ የባቢሎን መንግሥት ነው፡፡
አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል፤ አንተ የወርቁ ራስ ነህ።
· ታሪካዊ ፍጻሜ፦ ከ605-539 ዓ.ዓ. የቆየው የባቢሎን ግዛት በሀብትና በውበት በጣም የከበረ ስለነበር በወርቅ ተመሰለ። የባቢሎን ግዛት በታሪክም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ እጅግ ባለጸጋ፣ ውብ እና ኃያል እንደነበረች ይነገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ባቢሎንን "የመንግሥታት ጌጥ" እና "የከለዳውያን ኩራት" በማለት ይጠራታል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ 13:19 "እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች" በማለት ይገልጻታል።
ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ለንግድ በጣም አመቺ ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢዩ ሕዝቅኤል የእስራኤልን ወደ ባቢሎን መውድ በጻፈበት እንቆቅልሽ ውስጥ እንዲህ ብሎ ነበር
ለዓመፀኛ ቤት፦ ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው፦ እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። በዚሁ ባቢሎንን "የነጋዴዎች ምድር" (ሕዝቅኤል 17:4) ብሎ ይጠራት ነበር፡፡
ከአራቱም ማዕዘናት የሚመጡ ነጋዴዎች ወርቅ፣ ብር፣ የከበሩ ድንጋዮችንና ጥሩ ጨርቆችን ወደ ከተማዋ ያመጡ ነበር። በጦርነትና በምርኮ የተገኘ ሀብት ባቢሎን በተለይ በንጉሥ ናቡከደነፆር ዘመን ኃያል መንግሥት ነበረች። በወቅቱ የነበሩትን መንግሥታት (ኢየሩሳሌምን ጨምሮ) ድል በማድረግ ከፍተኛ ሀብትና ወርቅ ዘርፋለች።
በ2ኛ ዜና መዋዕል 36:18 ላይ የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ተብሎ ተጽፎአል፡፡
ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎችና የመንግሥቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን እንደወሰደ ይገልጻል። ይህም ባቢሎንን የወርቅና የብር ክምችት ማዕከል አድርጓታል።
ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተማዋን በማስዋብ ረገድ ትልቅ ስም ነበረው ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ላይ የምትገኝ ድንቅ የግንባታ ጥበብ (ውበት) የተላበሰች ከተማ ነበረች ። መጽሐፍ ቅዱስ በዳንኤል 4:30 ላይ ንጉሡ እንዲህ ብሎ ሲመካ ጽፎልናል ፡- "ንጉሡም ተናገረ እንዲህም አለ፦ ‘ይህች እኔ ለክብሬ ግርማ በኃይሌ ብርታት ለንጉሥ መኖሪያ ይሆን ዘንድ የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?’" የባቢሎን ግንቦች፡ ከተማዋ በማንም የማይደፈሩና እጅግ ውብ በሆኑ ባለቀለም ጡቦች የታጠረች ነበረች።
የአንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ (Hanging Gardens)፦ ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በስም ባይጠቅሰውም፣ የታሪክ መዛግብት ናቡከደነፆር ለሚስቱ ሲል የገነባውና ከአስደናቂ የዓለም ድንቆች ሥፍራ አንዱ እንደሆነ ይነግሩናል። ይህ ድንቅ ስፍራ በአሁኑ ሰዓት በአካል የሚታይ ቅርስ የለውም። የታሪክ ተመራማሪዎች ቦታው ይህ ሊሆን ይችላል ብለው የሚገምቱት ፍርስራሽ ቢኖርም፣ ልክ እንደ ጥንቱ ውበቱ የሚታይ ነገር ግን የለም።
ባቢሎን በአሁኑ ሰዓት የምትገኘው በኢራቅ (Iraq) ሀገር ውስጥ ነው። ከዋና ከተማዋ ባግዳድ በስተደቡብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሂላ (Hillah) ግዛት ውስጥ ትገኛለች።
ምንም እንኳን ከተማዋ በጥንታዊነቷና በጦርነት ምክንያት ጉዳት ቢደርስባትም፣ አሁንም ድረስ የሚቆሙና የሚታዩ አስደናቂ ቅርሶች አሏት፦ የኢሽታር በር (Ishtar Gate Replica)፦ በባቢሎን ከተማ መግቢያ ላይ ሰማያዊውና ውቡ የኢሽታር በር አምሳያ (Replica) ተገንብቶ ይገኛል።
የባቢሎን ዋናው ጥንታዊው በር ግን በጀርመን፣ በርሊን ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ ይጎበኛል። ከጥቁር ድንጋይ የተሰራ የአንበሳ ሀውልት ምስል አሁንም በባቢሎን ፍርስራሽ ውስጥ በክብር ቆሞ ይገኛል። እስከ አሁንም ድረስ የኢራቅ ብሔራዊ ምልክትም ነው።
የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ፦ የቤተ መንግሥቱ ግንቦችና ሰፋፊ አዳራሾች በከፊል ታድሰው ለጎብኝዎች ክፍት ናቸው። የዩኔስኮ ጥበቃ፦ በ2019 እ.ኤ.አ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበች በኋላ፣ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ተቋማት (እንደ World Monuments Fund) ትልቅ እድሳትና የጥበቃ ሥራ እየተደረገላት ነው።
ባቢሎን መንፈሳዊና ጥበባዊ ዝና የነበራት የጥበብ፣ የኮከብ ቆጠራና የትምህርት ማዕከል ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የባቢሎን ጠቢባን ትልቅ ግምት ይሰጣቸው እንደነበረ ለነቢዩ ዳንኤል በሰጠው ክብር በትንቢተ ዳንኤል 2 ላይ ጽፎልናል። ይህ የጥበብና የዕውቀት ክምችት ከተማዋን በዓለም ፊት የተከበረችና ግርማ ሞገስ የተላበሰች አድርጓታል ለዘመናት አቆይቷታል።
2. ደረቱና ክንዶቹም ብር ፦ የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር ነበሩ ይህም ከባቢሎን በኋላ የሚነሳው የሜዶንና የፋርስ መንግሥት መሆኑን የሚያሳይ ነበር፡፡
ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል።
• ትርጉሙ፦ ከባቢሎን በኋላ የሚነሳ፣ ነገር ግን በክብር ከእርሱ ያነሰ መንግሥት እንደሚመጣ ለማስረዳት ነው።
• ታሪካዊ ፍጻሜ፦ ፋርሳውያን ባቢሎንን ድል አድርገው ከ539-331 ዓ.ዓ. ድረስ መንግስቱን ወረሱ አገዛዙን ተኩ። ብር ከወርቅ እንደሚያንስ ሁሉ፣ ይህ መንግሥትም ከባቢሎን ያነሰ ሀብትና ዝና የቅንጦት ደረጃ ነበረው ነበር ።
ንጉሥ ናቡከደነፆር የተካው የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ማነው ?
የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ከባቢሎን መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፣ ግንኙነታቸው በዋናነት በወረራና በሥልጣን ሽግግር ላይ ያተኮረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ታሪክ በትንቢትም ሆነ በታሪክ መልክ በስፋት ይዘግበዋል። በትንቢቱም መሰረትም የባቢሎን መንግሥት በመውደቅ የሜዶ ፋርስ ገናና መሆን ችሏል፡፡
ባቢሎን ለረጅም ዓመታት ዓለምን ከገዛች በኋላ፣ በሜዶንና በፋርስ ጥምረት እንደምትሸነፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ብሎ ተተንብዮ ነበር። በትንቢተ ዳንኤል አምስተኛው ምዕራፍ ላይ የተጻፈውም ታሪክ ይህን የሚያሳይ ነው፡፡
ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ፦ አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ። የዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁን ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው። የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ። በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፤ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ።
ይህን የሕልሙን ትርጎሜ ነቢዩ ዳንኤል ለ ንጉሡ ብልጣሶር ገልጾለታል ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው። ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር። ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው።
ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም። የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም። ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል።
የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ።
ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ግብዣ ባደረገባት በዚያች ለሌት የከለዳዊያን ንጉሥ ገደለው ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረው ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደበት የባቢሎን ኃያልነት የናቡከደነጾር ሥርወ መንግስት አበቃ "መንግሥትህ ተከፈለች ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠች" (ዳንኤል 5:28)፡፡
ነቢዩ ዳንኤል እና የሜዶንና የፋርስ መንግሥት
የባቢሎን መንግስት የኢየሩሳሌምን ቤተመቅደስ ነዋያተ ቅድሳት ከመዝረፋቸው በተጨማሪ የመረጡትን ማርከው የተቀሩትን አይሁድ አጥፍተዋቸው ነበር፡፡ የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ከባቢሎን የተለዩበት ትልቁ ሥራ ለአይሁድ ምርኮኞች የነበራቸው አመለካከት ነው፡፡ በባቢሎን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበረው ነቢዩ ዳንኤል ፤ ባቢሎን ወድቃ ሜዶ ፋርስ ስትተካም ከሦስቱ አለቆች መካከል በመሆን በሥልጣኑ ቀጥሏል። ነገር ግን በስልጣኑ እና በጥበቡ የቀኑበት በቤተመንግስቱ ዙሪያ የነበሩ አለቆችና መሳፍንቱ ተንኮል እና ሴራ ጠነሰሱ፡፡ ዳንኤልን ለማስገደል ያመቻቸው ዘንድ ንጉሥ ሳይፈቅድ ማንም ሰው ጸሎት ማድረግ አይችልም የሚል አዋጅ እንዲነገር አደረጉ፡፡
የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም። እነዚያም ሰዎች፦ ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ። ዳንኤልም ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።
የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት። ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ።
የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው። በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ።
ወደ ጕድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው። ዳንኤልም ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው። ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ኑሮው ተቃናለት።
የአይሁድ ምርኮኞች ዕጣ ፈንታ
የአይሁድ ምርኮኞች ዕጣ ፈንታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን የእግዚአብሔር መንፈስ አነሳስቶት ወደ ኢየሩሳሌም በክብር እና በደስታ መመለስ ሆነ፡፡ የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ እግዚአብሔር ቂሮስን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞ ሕዝቡን ነፃ አወጣቸው፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ 1
በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ፦
የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ አለ፡፡
ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ።
የሜዶንና የፋርስ መንግሥት መውደቅ
በትንቢቱም መሰረትም የባቢሎን መንግሥት በመውደቅ የሜዶ ፋርስ ገናና መሆን ቢችልም እርሱ ደግሞ በተራው ተንኮታክቶ በመውደቅ የደረቱና ክንዶቹም ላይ ያለው ብር በግሪክ ወታደሮች ጣርና ቀስት ተቀጥቅጦ ለባለተራው እና በናስ ለተመሰለው የግሪክ መንግስት ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ይቀጥላል
የናብከደነጾር ሁለተኛው ሕልም
ክፍል ሦስት ከባለፈው የቀጠለ
የታላቁ ዛፍ ሕልም ( (ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 4 )
ይህ ሕልም ግን በቀጥታ በናቡከደነጾር ትዕቢት ላይ ያተኮረ ነበር።
እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ።
በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት። የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረⴾ
እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ። ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።
በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ። ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን። ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት።
እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፤ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።
የዛፉ ሕልም ዝርዝር
ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየው የሚከተለውን ነበር፦
• ታላቅ ዛፍ፦ በምድር መካከል በጣም ረጅም፣ ሰማይን የነካ፣ ቅጠሉ ያማረና ፍሬው የበዛ ዛፍ አየ። በታችዋ የምድር አራዊት ይጠለላሉ፣ በቅርንጫፎቿም የሰማይ ወፎች ይሰፍራሉ፤ ፍጡርም ሁሉ ከእርሷ ይበላ ነበር።
• ቅዱሱ መልአክ፦ አንድ "ቅዱስ ጠባቂ" ከሰማይ ወርዶ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ "ዛፉን ቍረጡት፣ ቅርንጫፎቹንም ቍረጡ፤ ቅጠሉን አርግፉ፣ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊቱም ከሥሩ ይውጡ... ነገር ግን የሥሩን ጉቶ በብረትና በናስ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል በምድር ውስጥ ተውት።"
• ፍርዱ፦ በሰማይ ጠል ይርሰስ፣ ዕድሉም ከምድር አራዊት ጋር ይሁን፤ የሰው ልብ ከእርሱ ይወሰድ፣ የእንስሳም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም (ሰባት ዓመታት) በላዩ ይለፉ አለው።
2. የነቢዩ ዳንኤል ትርጓሜ
ነቢዩ ዳንኤል ሕልሙን ሲሰማ በጣም ደነገጠ። ትርጉሙም እንዲህ ነበር፦
• ዛፉ አንተ ነህ፦ ዛፉ የንጉሡን ታላቅነትና ግዛቱን ይወክላል።
• መቆረጡ፦ ንጉሡ ከሰው ተለይቶ እንደሚባረርና ከሜዳ አራዊት ጋር እንደሚኖር ያሳያል።
• ሰባቱ ዘመናት፦ ንጉሡ "ልዑሉ እግዚአብሔር በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሰለጥን፣ ለወደደውም እንደሚሰጠው" እስኪያምን ድረስ ለሰባት ዓመታት አእምሮውን እንደሚስት ተነገረው።
• ጉቶው፦ የዛፉ ጉቶ መተው ግን እግዚአብሔርን ካወቀ በኋላ መንግሥቱ እንደሚመለስለት ተስፋ የሚሰጥ ነበር።
3. ፍጻሜው (የንጉሡ መውደቅና መነሣት)
ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ፣ ናቡከደነጾር በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ እንዲህ አለ፦
"ይህች እኔ ለክብሬ ግርማ በጉልበቴ ብርታት የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?" ይህንን የትዕቢት ቃል ተናግሮ ሳይጨርስ ከሰማይ ድምፅ መጣ። ወዲያውም፦
1. ቅጣቱ፦ አእምሮውን ሳተ፤ ከሰው ተለይቶ ተባረረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰሰ።
2. ለውጡ፦ ጠጉሩ እንደ አንበሳ ጠጉር ረዘመ፣ ጥፍሩም እንደ ወፍ ጥፍር ሆነ።
3. ፈውሱ፦ ሰባቱ ዓመታት ሲያበቁ ናቡከደነጾር ዓይኑን ወደ ሰማይ አነሣ፤ አእምሮውም ተመለሰለት። በዚያን ጊዜ ትዕቢቱን ትቶ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነ።
4. የታሪኩ ትምህርት
ይህ ታሪክ የሚያስተምረን "እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚያዋርድና ትሑታንን ከፍ እንደሚያደርግ" ነው። ናቡከደነጾር ከዚህ ክስተት በኋላ እግዚአብሔርን "የሰማይ ንጉሥ" ብሎ በማመስገን ታሪኩን አጠናቋል።
የታላቋቋ ባቢሎን መውደቅ
የባቢሎን ግዛት በታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ አስደናቂና በሀብት የበለጸጉ ስልጣኔዎች አንዱ ነበር። በተለይ በናቡከደነጾር ዘመን (ከ605-539 ዓ.ዓ.) የነበራት ገጽታ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው እንደ ተረት የሚመስል ውበት የነበራት ታላቅ በወርቅ የተንቆጠቆጠች ከተማ ነበረች።
1. የምድር ጌጥ የሆነችው ከተማ
ባቢሎን በዚያ ዘመን የዓለም የንግድ፣ የጥበብና የሀብት ማዕከል ነበረች። ሄሮዶተስ (Herodotus)፦ "የታሪክ አባት" በመባል የሚታወቀው የግሪክ ታሪክ ጸሐፊ ስለ ባቢሎን ግንቦች ግርማና ስለ ከተማዋ ስፋት በዝርዝር ጽፏል። ከተማዋ በታላላቅ ግንቦች የታጠረች ሲሆን፣ ግንቦቹ ላይ ሁለት ሰረገላዎች ጎን ለጎን ካለምንም ችግር መሮጥ ያስችሉ ነበር ይባላል። የከተማዋ መግቢያ የነበረው "የኢሽታር በር" (Ishtar Gate) መስተዋት በሚመስሉ ሰማያዊ ጡቦች የተሠራና በፈረሶችና በዘንዶዎች ምስል ያጌጠ በመሆኑ፣ ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶች በሙሉ በከተማዋ ግርማ ይገረሙ ነበር።
ለባቢሎን ከተማ ስምንተኛውና ዋናው መግቢያ በር የነበረው "የኢሽታር በር" በወቅቱ በባቢሎን ብትመለከው ለፍቅርና ለጦርነት አምላክ ለ"ኢሽታር" የተሰጠ በመሆኑ በሷ ስም ተሰይሟል። በነገራችን ላይ የኢሽታር በር (Ishtar Gate)፦ በጀርመን አርኪኦሎጂስቶች ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን አገር፣ በርሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፐርጋሞን ሙዚየም (Pergamon Museum) ውስጥ ነው። የፐርጋሞን ሙዚየም ለትልቅ እድሳት (Renovation) ሲባል ለተወሰኑ ዓመታት ለጎብኚዎች ተዘግቷል። እድሳቱ እስከ 2027 ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ስለሚችል፣ በአካል ሄዶ ለማየት የሚፈልግ ሰው አስቀድሞ የሙዚየሙን ድረ-ገጽ ማረጋገጥ ይኖርበታል። መጎብኘት የቻለ ሰው ፎቶ ተነስቶ ይህን ታሪክ ያጋራን ይሆናል ?
2. የዓለም ድንቅ፦ የባቢሎን ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ
ቤሮሰስ (Berossus)፦ በ3ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የነበረ የባቢሎን ካህን ሲሆን፣ ስለ ናቡከደነጾር የግንባታ ሥራዎችና ስለ "ተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራዎች" መረጃ ጥሏል። ናቡከደነጾር ከሜዶን ላገባት ሚስቱ (አሚቲስ) የትውልድ አገሯን ተራራማና አረንጓዴ ገጽታ ትናፍቅ ስለነበር ለዚያ ብሎ በባቢሎን ሜዳ ላይ ሰው ሠራሽ ተራራ አስገነባላት። ይህ "የተንጠልጣይ የአትክልት ስፍራ" ተብሎ የሚታወቀውና ከዓለም ሰባት ድንቆች አንዱ የሆነው ስፍራ ሲሆን፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ በረቂቅ ጥበብ ውኃ እየተቀዳ የሚጠጣ ደረጃ በደረጃ የተገነባና አረንጓዴ ገነት የሚመስል ውብ የአትክልት ሥፍራ ነበር።
3. የወርቅና የንግድ ማዕከል
በባቢሎን ውስጥ የሚገኙት ቤተ መቅደሶች፣ በተለይም የባዕድ አምላኩ የ"ማርዱክ" መቅደስ፣ በወርቅ የተለበጡ ነበሩ። ከተማዋ ከሕንድ እስከ ግብፅ ባለው የንግድ መስመር መካከል ስለምትገኝ፦
• ከየአቅጣጫው የሚመጡ ውድ ጨርቆች፣ ቅመማ ቅመሞችና ዕንቁዎች ይፈሱባት ነበር።
• ሕንጻዎቿ በደማቅ ቀለማት ያሸበረቁና በሥነ-ሕንጻ ጥበብ የመጠቁ ነበሩ።
• ከተማዋን በሁለት በኩል የሚከፍላት የኤፍራጥስ ወንዝ ለከተማዋ ግርማና ለንግድ ሥራዋ ትልቅ አንቀሳቃሽ ነበር።
4. የታሪክና የጥበብ መፍለቂያ
ናቡከደነጾር ከተማዋን ሲገነባት "ለዘላለም እንድትኖር" አስቦ ከተማዋ በታሪክ ስትታወስ እንድትኖር በእያንዳንዱ ጡብ ላይም ስሙን ያሳርፍ እንደነበር ይነገራል። ባቢሎን በሀብት እና በታሪካዊነት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትም የመጠቀች ነበረች። የከዋክብት ምርምር እና የሒሳብ ጥበብ እጅግ የዳበረባት ስፍራ ሆና ነበር።
የባቢሎን ውድቀት (በ539 ዓ.ዓ.)
ባቢሎን በዚያ ዘመን የነበራት ውበትና ሀብት "የወርቁ ራስ" መባሏ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ሆኖም ግን፣ ነቢዩ ዳንኤል አስቀድሞ እንደተነበየው፣ ይህ ሁሉ ግርማና ሞገስ በ539 ዓ.ዓ. በፋርሳውያን እጅ ወድቆ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ዘንድ ታዋቂውን የታሪክ መጽሐፍ "ዜና አይሁድ" የጻፈው ዮሴፍ ወልደኮርዮን በኋላ ወደ ሮም ከሄደ በኋላ "ፍላቪየስ" የሚለውን የሮማውያን ስም ወስዷ ፍላቪየስ ጆሴፈስ (Flavius Josephus ) ተብሎ የሚታወቀው በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ፣ በ20 ጥራዞች ተከፋፍሎ የቀረበ ታላቅ ድርሳን አዘጋጅቷል። የታሪካዊ ጽሁፉ ዋና ዓላማው ለአረማውያን (ለሮማውያንና ለግሪካውያን) የአይሁድን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት ጥንታዊነትና ክብር ለማስረዳት ነው። ከጻፋቸው ታሪክ ውስጥም የናቡከደነጾርንና የዳንኤልን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ምንጮች አቀናጅቶ መከተቡ ነው።
የባቢሎን ውድቀት በታሪክ ውስጥ በጣም ከሚታወቁትና በብልሃት ከተመሩ ድሎች አንዱ ነው። ባቢሎን በታላላቅ ግንቦች የታጠረችና በጣም የሰለጠነ የጦር ሠራዊት የነበራት ለዓመታት የሚበቃ ምግብ ያከማቸች ስለነበረች፣ በጦርነት ሰብሮ ለመግባት የማይቻል ይመስል ነበር። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የቆረጠው ቀን ሲመጣ አወዳደቋ የእንቦይ ካብ ሆነ እንዲህም ሆነ፦
• የቂሮስ ብልሃት፦ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ (Cyrus the Great) የከተማዋን ቅጥሮች ሰብሮ መግባት እንደማይችል ሲረዳ፣ እንዲህ ብልሀት አሰበ በከተማዋ መካከል የሚያልፈውን የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫ አስቀይሮ በወንዙ በኩል ወደ ከተማዋ ለግባት አቀደ።
• የወንዙ መድረቅ፦ የወንዙን አቅጣጫ በመቀየሩ የወንዙ ውሃ ዝቅ ሲል፣ የፋርስ ወታደሮች በወንዙ የታችኛው ስር ተሹለክልከው ወደ ከተማዋ ገቡ።
• የበልጣሶር ድግስ፦ በዚያው ምሽት የናቡከደነጾር የልጅ ልጅ የሆነው ንጉሥ በልጣሶር በቤተ መንግሥቱ ለሺህ መኳንንት ታላቅ ግብዣ እያደረገ ነበር። በዚያ ድግስ ላይ ከኢየሩሳሌም መቅደስ የተማረኩትን የወርቅ ዕቃዎች ለወይን መጠጫነት ተጠቀሙ።
• በግድግዳው ላይ የተጻፈው ጽሕፈት፦ በድንገት የሰው እጅ ጣቶች መጥተው በግድግዳው ላይ "ሜኔ፥ ሜኔ፥ ቴቄል፥ ፋሬስ" የሚል ጽሕፈት ጻፉ። ትርጉሙም "መንግሥትህ ተቆጠረ፣ በሚዛን ተመዘንህ ቀልለህም ተገኘህ፣ መንግሥትህም ለሜዶንና ለፋርስ ተሰጠች" የሚል ነበር።
• የመጨረሻው ውጤት፦ በዚያው ሌሊት በልጣሶር ተገደለ፤ ያለ ምንም ትልቅ ውጊያ ታላቂቱ ባቢሎን በፋርስ ቁጥጥር ስር ወደቀች።
የነሐሱ የግሪክ መንግስት እና ዝነኛውን ታላቁን እስክንድር ክፍል አራት
የነሐሱ የግሪክ መንግስት እና ዝነኛውን ታላቁን እስክንድር ክፍል አራት ከባለፈው የቀጠለ
በዓለም የታሪክ ምዕራፍ እጅግ አስደቂ ከሆኑት የዓለም መንግስታት ሽግግሮች አንዱ ነው። ባቢሎን በፋርስ እጅ ከወደቀች በኋላ፣ ዓለምን ለረጅም ጊዜ የገዛው የሜዶንና የፋርስ መንግስት ነበር። ነገር ግን፣ የነሐስ መንግስት ተብሎ የተመሰለው የግሪክ (የመቄዶንያ) መንግስት ወደ ስልጣን የመጣው በራሱ ለየት ባለ ሂደት ነው። በክፍል አራት ታሪካችን አስደናቂውን የግሪክ መንግስት እና ዝነኛውን ታላቁን እስክንድር ፣የነሐሱን መንግስትም እንመለከታለን ጥሩ የንባብ ጊዜን ተመኘሁላችሁ።
የግሪክ መንግሥት መነሳትና መውደቅ በትንቢት መነጽር
የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ዓለምን በኃያልነት የገዛው ለ208 ዓመታት ያህል ነው። ይህ ዘመን የሚሰላው ታላቁ ቂሮስ ባቢሎንን ድል ካደረገበት ከ539 ዓ.ዓ. ጀምሮ ነው። ይህም የመጨረሻው የፋርስ ንጉሥ እስከ ወደቀበት እስከ 331 ዓ.ዓ. ድረስ ነው። በንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ዘመነ መንግስት የፋርስን መንግሥት በግሪክ መንግስት ተሸንፎ ፍጻሜውን አገኘ።
የነብር ፍጥነት
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ንጉሥ እስክንድር መቅዶንዮስ (Alexander the Great) ዓለምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንቀጠቀጠ መሪ ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ዛሬ የምናየው ይህ ታሪክ ግን እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፣ ገና ዓለም ሳይሰማውና ሳይገነዘበው በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት በምስልና በምሳሌ ተቀምጦ የነበረ ታላቅ መለኮታዊ "ትዕይንት" ነው።
1. የናሱ መንግሥትና ባለ ክንፉ ነብር
ትንቢቱ የሚጀምረው ከታላቁ እስክንድር መወለድ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነው። ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ያየው ያ ግዙፍ ምስል አራት ታላላቅ መንግሥታትን ይወክላል። የመጀመሪያው ወርቅ (ባቢሎን)፣ ሁለተኛው ብር (ሜዶ ፋርስ) ሲሆኑ፣ ሦስተኛውና ሆዱና ጭኑ ናስ የሆነው ክፍል ግን የግሪክን መንግሥት ይወክላል (ዳን. 2:39 )።
ነቢዩ ዳንኤል ይህንኑ የግሪክ መንግሥት በሌላ ራዕይው እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ "ነብር የሚመስል ሌላ ነበረ፤ በጀርባውም ላይ አራት የወፍ ክንፎች ነበሩት፤ ለአውሬውም አራት ራሶች ነበሩት" (ዳን. 7:6)።
ለምን በነብር ተመሰለ? ነብር በተፈጥሮው ፈጣን ነው፤ አራት ክንፍ ሲጨመርበት ደግሞ ፍጥነቱ ከተፈጥሮ በላይ ይሆናል። የግሪክ ንጉሥ ታላቁ እስክንድር በፈጣን ክንፍ ባለው ነብር የተመሰለው ገና በ20 ዓመቱ ንጉሥ ሆኖ፣ በ10 ዓመት ውስጥ ብቻ በፍጥነት እስከ ሕንድ ዳርቻ ዝናው ናኝቶ ዓለም የተቆጣጠረ ፤በጦር ጉልበቱ እና ኃይሉ በትንቢቱ መሰረት ፈጣን ነበር መሆኑን በተግባር ያስሰከረ ፈጣን ንጉሥ በሆኑ ነው።
ለምን በነሐስ ተመሰለ? የግሪክ ወታደሮች የነሐስ (ናስ) ጥሩር፣ ጋሻና ቆብ ያደርጉ ስለነበር የታላቁ እስክንድር ጦርን "ነሐስ የለበሱ የግሪክ ልጆች" በመባል በታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ይጠራሉ ።
ወጣቱ እስክንድር ገና በ20 ዓመቱ የንጉሥነት ዘውድ ሲደፋ፣ በዓይኖቹ ውስጥ የሚታየው ረሃብ ግዛትን የማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የመጠቅለል ብሎም ማንነታቸውን በማጥፋት ፍጹም ግሪካዊ እንዲሆኑ ባሕላቸውን ማስለወጥ ነበር።
ታላቁ እስክንድር
የግሪክ ወታደሮች የነሐስ ጋሻዎቻቸውን እያጋጩ፣ ረዣዥም የጦር መሣሪያዎቻቸውን ወደ ሰማይ ሰቅለው የሄልስፖንትን ባሕር ሲሻገሩ ታላቁ ሽግግር ያንጊዜ ተጀመረ። ሄልስፖንት (Hellespont) ባሕር፣ ዛሬ ዳርዳኔልስ (Dardanelles) ተብሎ የሚጠራው ጠባብ የባሕር ስርጥ ነው። ይህ ስፍራ በአውሮፓና በእስያ መካከል ያለ ድልድይ በመሆኑ በታሪክ ውስጥ እጅግ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው።
ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግስት ለመውረር ጉዞውን ሲጀምር ሄልስፖንት ባሕር ወደ 160 የሚጠጉ መርከቦችን አሰልፎ ሰራዊቱን ማሻገር ነው። በዚያን ወቅት መርከቦቹ ባሕሩን ሲሞሉት፣ የአውሮፓና የእስያ ምድር የተገናኙ ይመስል ነበር።
ታሪክ እንደመዘገበው፣ ታላቁ እስክንድር መርከቧ ወደ እስያ ምድር ከመጠጋቷ በፊት፣ ከመርከቧ ላይ ሆኖ ጦሩን ወደ እስያ አፈር ወረወረ። ጦሩ መሬቱ ላይ ተሰክቶ ሲቆም፣ "እስያ በአማልክት የተሰጠችኝ የጦር ምርኮዬ ናት!" ብሎ አወጀ። ይህ ድርጊት ለወታደሮቹ ዓለምን ለመቆጣጠር ትልቅ ወታደራዊ ወኔ ሰጥቷቸዋል። ከዚያ ጦሩን አነቃቅቶ በከፍተኛ ጀብዱ ወደ እስያ ዘመተ።
ፋርሳውያን ታላቁ እስክንድር መሻገሩን ሲሰሙ፣ በወንዙ ማዶ ባለው ዳገታማ ቦታ ላይ መሸጉ። የፋርስ ጦር መሪዎች "ታላቁ እስክንድር ወንዙን ሲሻገር ዳገቱን እስኪወጣ ድረስ ጠብቀን ከላይ ሆነን እንጨርሰዋለን" ብለው አሰቡ። የፋርስ ፈረሰኞች በወንዙ ዳርቻ ላይ እንደ ግድግዳ ተደርድረው ይጠብቁት ነበር።
አንጋፋው የጦር አዛዥ ፓርሜንዮ ታላቁ እስክንድር እንዲህ አለው፦ "ንጉሥ ሆይ፣ ወንዙ ጥልቅ ነው፣ ዳርቻውም ጭቃማና ዳገት ነው፤ ዛሬን አርፈን ነገ ማለዳ ድንገት እናጥቃቸው።" ብሎ አስተያየት ሰጠ ። ታላቁ እስክንድር እንዲህ ብሎ መለሰ፦ "የሄልስፖንትን ባሕር የተሻገረ ሰራዊት ይህን ትንሽ ወንዝ መሻገር ካቃተው አሳፋሪ ነው።" በማለት መልሶለታል። ታላቁ እስክንድር ፋርሳውያን ተደራጅተው እንዲቆዩ ጊዜ መስጠት አልፈለገም፤ ወዲያውኑ ጥቃት በመጀመር ጦርነቱ ተፋጸመ። ይህ ውጊያ ታላቁ እስክንድር "ሞት የማይፈራ ጀግና" ያስባለበትና የፋርስን ጦር ክፉኛ ያስደነገጠበት ክስተት ሆነ።
ታላቁ እስክንድር የሚያብረቀርቅ የነሐስ ጥሩሩንና በሁለት በኩል ነጭ ላባ ያለው የራስ ቁር (Helmet) ለብሶ በጦርነቱ መካከል ጎልቶ እንዲታይና ወታደሮቹ እንዲከተሉት አደረገ። በፈረሱ ላይ ሆኖ ወደ ወንዙ ዘለለና ተሻገረ ሰራዊቱም ተከትለውት ገቡ ። ከወንዙ በላይ የፋርስ ጦር ቀስትና ጦር ያዘንብባቸው ነበር። ወንዙን ተሻግረው ዳገቱን ሲወጡ፣ በእጅ በእጅ የሚደረግ ውጊያ ተጀመረ። እስክንድር በፋርስ መኮንኖች ተከበበ። አንድ ፋርስ መስፍን የራስ ቁሩን በሰይፍ ሰነጠቀው። ሌላኛው ፋርሳዊ ደግሞ ከጀርባው ሊቀላው ሰይፉን ሲያነሳ፣ የቅርብ ጓደኛው የፋርሳዊውን እጅ ቆርጦ እስክንድር ከሞት አተረፈው።
በመጨረሻም የግሪክ ወታደሮች የፋርስን መስመር ሰብረው ወጡ። የፋርስ ፈረሰኞች ተበታተኑ። እስክንድር በዚህ ውጊያ ራሱን ለዓለም አስተዋወቀ። የፋርስ መንግስት "ይህ ልጅ ተራ ወራሪ ሳይሆን፣ ሊያጠፋን የመጣ መቅሰፍት ነው" ብሎ እንዲያምን አደረገ። ይህ ድል ለእስክንድር ወደ ትንሿ እስያ (የዛሬዋ ቱርክ) ከተሞች በቀላሉ ለግባት በሩን ከፈተለት።
የኢሱስ (Issus) ሜዳ ውጊያ፣ የፋርስ መንግሥት ውድቀት
በ333 ዓ.ዓ. የተካሄደው የኢሱስ (Issus) ውጊያ፣ የፋርስ መንግሥት ውድቀት የማይቀር መሆኑን ለዓለም ያሳየበት የታሪክ ምዕራፍ ነው። የእስክንድርን መስፋፋት የሰማው የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ ራሱን ለጦርነት ዝግጁ አድርጎ መውጣቱ ተሰማ። ታላቁ እስክንድር ወደ ደቡብ እየገሰገሰ ሳለ፣ ንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ግዙፍ ሠራዊቱን አስከትሎ ከፋርስ ተነቃነቀ። ዳርዮስ "ይህን ወጣት እዚሁ መጨረስ አለብኝ" ብሎ ስለቆረጠ፣ የግሪኩን ጦር ከኋላው ዞሮ በመምጣት መንገድ ዘጋበት። ሁለቱ ጦሮች በባሕርና በተራራ መካከል ባለው ጠባብ የኢሱስ ሜዳ ላይ ተገናኙ።
ዳርዮስ ቢያንስ 600,000 የሚጠጋ (አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት) ሠራዊት ነበረው። እስክንድር ግን የነበረው ወደ 40,000 አካባቢ ብቻ ነበር። ነገር ግን ቦታው ጠባብ በመሆኑ፣ ዳርዮስ ግዙፉን ሠራዊቱን በሙሉ ሊጠቀምበት አልቻለም። ወታደሮቹ አንዱ በሌላው ላይ እየተረጋገጡ መጨናነቅ ጀመሩ።
ታላቁ እስክንድር የጠላቱን ድክመት አየ። የፋርስ ጦር መሃል ላይ ንጉሥ ዳርዮስ በከፍተኛ ክብር በሰረገላው ላይ ሆኖ ይታያል። በጥንት ዘመን፣ ሰራዊቱ የሚዋጋው ለንጉሡ ካለው ታማኝነትና ንጉሡ በሜዳው ላይ ካለው መገኘት የተነሳ ነበር። "ንጉሡ ከወደቀ ወይም ከሸሸ፣ ሰራዊቱ ተስፋ ይቆርጣል፣ ትዕዛዝ የሚሰጠው ይጠፋል፣ ከዚያም መላው አካል (ሰራዊቱ) ይበታተናል" ።
በኢሱስ ጦርነት ወቅት፣ የፋርስ ሰራዊት ከግሪኩ ሰራዊት በአሥር እጥፍ ይበልጥ ነበር። እስክንድር ግን ጊዜውን በጎንና በጎን ባለው ውጊያ አላጠፋም። በጦርነቱ መካከል ቀዳዳ አግኝቶ በቀጥታ ፈረሱን ወደ ዳርዮስ ሰረገላ አቀና። ዳርዮስ ታላቁ እስክንድር ሊገድለው ሲመጣ ሲያይ፣ በፍርሃት ሸሸ። ልክ ታላቁ እስክንድር እንዳቀደው፣ ንጉሡ መሸሹን ያየው የፋርስ ሰራዊት ወዲያውኑ የውጊያ መንፈሱ ሞተና መሸሽ ጀመረ። "ራሱ" (ዳርዮስ) ሲሸሽ "አካሉ" (ሰራዊቱ) ወደቀ።
ኢራቅ ግዛት በጋውጋሜላ ሜዳ
በ331 ዓ.ዓ. በዛሬው ኢራቅ ግዛት በጋውጋሜላ ሜዳ ላይ፣ የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ ሣልሳዊ ግዙፍ ሠራዊቱን አሰልፏል። የፋርስ ሠራዊት ብዛት ልክ እንደ ባሕር አሸዋ ነበር፤ ከርቀት ሲታዩ ሜዳውን የሸፈኑ አንበጣዎች ይመስላሉ። በሌላ በኩል፣ እስክንድር ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ግን በቆረጡ ወታደሮቹ ታጅቦ ቆሟል። ሌሊቱን ሙሉ የፋርስ ወታደሮች ድንገተኛ ጥቃት በመፍራት ሳይተኙ ሲጠበቁ አደሩ፤ እስክንድር ግን ወታደሮቹን አሳርፎ እርሱም በሰላም ተኝቶ አደረ።
ጎህ ሲቀድ፣ የግሪኩ ጦር እንደ ቀስት ተወረወረ። እስክንድር የፋርስን ጦር ወደ ጎን እንዲሳቡ በማድረግ መሃል ላይ ቀዳዳ ፈጠረ። ያንን ቀዳዳ ሲያይ፣ እስክንድር ከፈረሰኞቹ ጋር በመሆን ልክ እንደ ሹል ጦር ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ በቀጥታ አመራ።
በፋርስ ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ሽብር ተፈጠረ። የነሐስ ጋሻዎቻቸው በፀሐይ ብርሃን ስር እየተንፀባረቁ ጠላትን ያሳውሩ ነበር። ዳርዮስ፣ እስክንድር በአቅራቢያው ሲመለከትና የጦር ሰረገላዎቹ ሲሰባበሩ ባየ ጊዜ፣ በፍርሃት ተውጦ ፈረሱን አዙሮ ሸሸ። ዳርዮስ ከሸሸ በኋላ፣ የፋርስ ግርማ ሞገስ አበቃለት።
በዚህ ጦርነት ዳርዮስ የራሱን ሕይወት ለማዳን ሲል እጅግ ውድ የሆኑትን ነገሮች ጥሎ ሄደ አንዱ የንጉሣዊ ድንኳኑን ነበር እስክንድር ወደ ድንኳኑ ሲገባ በወርቅና በብር የተለበጡ ዕቃዎችን፣ ውድ ሽቶዎችንና ምግቦችን አገኘ። "ንጉሥ መሆን ማለት ይህ ነው ለካ!" ብሎ በግርምት ተናገረ ይባላል።
የዳርዮስ እናት፣ ሚስቱና ሁለት ሴት ልጆቹ ተማረኩ። እስክንድር ግን እንደ ሌሎቹ ድል አድራጊዎች አልበደላቸውም። ይልቁንም፣ "እኔ የምዋጋው ከዳርዮስ ጋር እንጂ ከእናንተ ጋር አይደለም" በማለት ልክ እንደ ንጉሥ ቤተሰብ በታላቅ ክብር እንዲጠበቁ አዘዘ።
እስክንድር ዳርዮስን በሕይወት ለመያዝ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ዳርዮስ ወደ ባክጥሪያ (የዛሬዋ አፍጋኒስታን አካባቢ) እየሸሸ ሳለ፣ በገዛ መኮንኖቹ ተከዳና ተወጋ። እስክንድር ዳርዮስ ወዳለበት ሲደርስ ንጉሡ ሕይወቱ አልፎ ነበር። በጠላቱ አሟሟት አዝኖ የራሱን ካባ ደረበለትና ወደ ፐርሴፖሊስ ልኮ በንጉሣዊ ሥነ-ሥርዓት እንዲቀበር አደረገ።
እስክንድር ወደ ታላቂቱ ባቢሎን ሲቃረብ፣ ከተማዋ በጦርነት ሳይሆን በዝማሬና በክብር ተቀበለችው። መንገዶቹ ሁሉ በአበቦች ተነጠፉ። የብር መንግስት የተባለችው ፋርስ አበቃላት፤ የነሐስ መንግስት የተባለችው ግሪክ ደግሞ ዓለምን ተቆጣጠረች።
የሱሳ (Susa) ከተማ
ታላቁ እስክንድር በጋውጋሜላ ጦርነት ዳርዮስን ድል ካደረገ በኋላ፣ ቀጥታ ፊቱን ያዞረው ሱሳን ከተማ ነበር። የሱሳ (Susa) ከተማ በጥንቱ ዓለም የሥልጣኔ፣ የሀብትና የውበት ተምሳሌት ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ሱሳ ግንብ" ተብላ የምትጠራው ይህች ከተማ፣ የፋርስ ነገሥታት የክረምት መኖሪያና የንጉሣዊ ግርማ ሞገሳቸው ማሳያ ነበረች።
ሱሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙባት መድረክ ናት፦ የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው በዚሁ በሱሳ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነው። ንጉሥ አርጤክስስ ያንን ታላቅ የ180 ቀናት ግብዣ ያደረገው፣ አስቴር ንግሥት የሆነችውና አይሁዳውያን ከጥፋት የዳኑት እዚህ ከተማ ውስጥ ነበር።
ነቢዩ ዳንኤል በባቢሎንና በፋርስ መንግሥት ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሰው ሲሆን፣ ስለ መንግሥታት መተካካት (ስለ ግሪክ መነሳት ጭምር) የታዩት ታላላቅ ራእዮች የታዩት በሱሳ ግንብ አጠገብ ነበር (ዳንኤል 8:2)።
ነህምያ ለፋርሱ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊ ሆኖ ያገለግል የነበረውና የኢየሩሳሌም ቅጥር እንዲታደስ ትእዛዝ የተቀበለው በሱሳ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር (ነህምያ 1:1)።
እስክንድር ወደ ከተማዋ ሲገባ ያየው ነገር እጅግ የሚያስደምም ነበር። የታሪክ ጸሐፍት የከተማዋን ግርማ እንዲህ ይገልጹታል "አፓዳና" (ታላቁ አዳራሽ)፦ የሱሳ ቤተ መንግሥት እጅግ ረዣዥም በሆኑና በጥበብ በተጠረቡ የድንጋይ አምዶች የተደገፈ ነበር። የቤተ መንግሥቱ ግድግዳዎች በሰማያዊ፣ በቢጫና በነጭ ቀለማት በሚያብረቀርቁ ጡቦች የተሰሩ ነበሩ።
በአስቴር መጽሐፍ ላይ እንደሚገለጸው፣ ቤተ መንግሥቱ በነጭ፣ በሰማያዊና በሐምራዊ በፍታ የተሰሩ መጋረጃዎች፣ በብር ቀለበቶችና በዕብነ በረድ አምዶች ላይ የተንጠለጠሉ ነበሩ። መሬቱም በበዝበዛ፣ በዕብነ በረድና በሉል ድንጋዮች የተነጠፈ ነበር።
እስክንድር በሱሳ ያገኘው ወርቅና ብር በሺዎች የሚቆጠሩ ግመሎችና በቅሎዎች እንኳ ሊጭኑት የማይችሉት ነበር። 50,000 ታላንት (በዛሬው ስሌት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር) ወርቅ በግምጃ ቤቷ ውስጥ ተከምሮ ተገኝቷል።
የፋርስ ነገሥታት ሱሳን "የዓለም ማእከል" አድርገው ይቆጥሯት ነበር። በከተማዋ ውስጥ የሚፈሰው የኮአስፔስ ወንዝ ውሃ እጅግ ንጹህ ከመሆኑ የተነሳ፣ ንጉሡ ከዚህ ወንዝ ውጭ ሌላ ውሃ አይጠጣም ነበር። ንጉሡ ወደ የትኛውም አገር ቢሄድ፣ የዚህ ወንዝ ውሃ በብር ዕቃዎች ተቀድቶ በበቅሎ ተጭኖ ይከተለው ነበር።
እስክንድርም ወደ ሱሳ ሲቃረብ፣ ከተማዋ እንደ ባቢሎን ሁሉ በሰላም እጇን ሰጠች። የከተማዋ ገዥ የነበረው አቡሊተስ፣ የእስክንድርም ኃይል መቋቋም እንደማይችል ስለተረዳ፣ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን እጅግ ግዙፍ ሀብት ይዞ ወጥቶ ተቀበለው። እስክንድርም በድል አድራጊነት ወደ ቅጥሯ ገባ።እስክንድር ይህን ሁሉ ሀብትና ውበት ሲቆጣጠር፣ ያ "የብር ደረት" የተባለው የፋርስ መንግሥት ክብር ወደ "ነሐሱ መንግሥት" (ግሪክ) መዛወሩን በተግባር አረጋገጠ።
የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት፦ እስክንድር በሱሳ ያደረገው አንድ ትልቅና የታወቀ ክስተት አለ። የግሪክንና የፋርስን ባህል ለማዋሃድ በማሰብ፣ 80 የሚሆኑ የግሪክ መኮንኖቹን የፋርስ መኳንንት ሴት ልጆችን እንዲያገቡ አደረገ። ራሱ እስክንድርም የዳርዮስን ልጅ ስታቲራን (Stateira) በዚሁ ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ አገባ። ይህ ድርጊት "የነሐሱ መንግስት" (ግሪክ) የፋርስን ግዛት በጉልበት ብቻ ሳይሆን በደምም ለመውረስ ያደረገው ሙከራ ነበር።
የፐርሴፖሊስ (Persepolis) ቤተ መንግስት
እስክንድርም ሱሳን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ጉዞው አላበቃም፤ ይበልጥ ወደ ምስራቅ፣ ወደ ፋርስ ልብ ወደሆነችውና ወደ ሚቃጠለው የፐርሴፖሊስ (Persepolis) ቤተ መንግስት አመራ።
ፐርሴፖሊስ የፋርስ ነገሥታት የክብርና የግርማ ሞገስ መገለጫ ነበረች። እስክንድርም ከተማዋን እንደተቆጣጠረ፣ በታሪክ ውስጥ እስካሁን አከራካሪ የሆነው ክስተት ተፈጠረ። ከተማዋ በእሳት ጋየች። ለምን ነደደች? አንዳንዶች እስክንድርም ይህን ያደረገው ከ150 ዓመታት በፊት ፋርሳውያን አቴንስን ስላቃጠሉባት "የበቀል እርምጃ ነው" ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በአንድ ትልቅ ግብዣ ላይ ሰክረው በነበሩበት ወቅት በስህተት የተለኮሰ እሳት ነው ይላሉ። ያ ሁሉ ጥበብ የተሞላበት ቤተ መንግስት ወደ አመድነት ተቀየረ። ይህ ክስተት የፋርስ ግዛትን ታሪክ በይፋ የመዝጋት ምልክት ሆኖ ቀረ።
2. እስክንድር በኢየሩሳሌም፦
ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ዮሴፍ ወልደኮርዮን እንደዘገበው፣ እስክንድር ፋርስን ድል እያደረገ ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ አይሁዳውያን በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ነበሩ። ሊቀ ካህናቱ ኢያዱዋ ሕዝቡን ሰብስቦ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠየቀ። በሕልሙም "ከተማዋን አስውባችሁ በነጭ ልብስ ተቀበሉት" የሚል መለኮታዊ መልእክት ደረሰው።
እስክንድር ከተማዋ ሲደርስ፣ ሊቀ ካህናቱን በክብርና በነጭ ልብስ አይቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወርዶ ለሊቀ ካህኑ ሰገደለት። የጦር አዛዦቹ "ይህ ዓለም የሰገደለት ንጉሥ እንዴት ለካህን ይሰግዳል?" ብለው ሲገረሙ፣ እስክንድር እንዲህ አለ፦ "እኔ የሰገድኩት ለካህኑ ሳይሆን ለለበሰው ልብስና ለሚቀድሰው አምላክ ነው፤ ይህንኑ ሰውዬ በመቅዶንያ ሳለሁ በሕልሜ አይቼዋለሁ፣ በፋርስ ላይ ድል እንደማገኝም አብስሮኝ ነበር።" በማለት ተናገረ።
ከዚያም ታላቁ እስክንድር ከሊቀ ካህኑጋር በመሆን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መስዋዕት አቀረቡ። ካህናቱም የዳንኤልን መጽሐፍ አውጥተው "የግሪክ ንጉሥ የፋርስን መንግሥት እንደሚያጠፋ እንዲሁም ዓለምን እንዲቆጣጠር" የሚናገረውን ትንቢት (ዳን. 8:5-21) አነበቡለት። እስክንድር ትንቢቱ ስለ እሱ መሆኑን ሲረዳ እጅግ ተደስቶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአይሁድ ክብር እና ልዩ ነፃነት ሰጠ።
3. "ታላቁ ቀንድ" ሲሰበር፦ ክፍል አምስት ይቀጥላል




%20%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9B.jpg)

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ