-->

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጣዊ ክፍል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ የፀሐይ መውጫ የተረጋጋ መንፈሳዊ መንገድ
አዲስ ገጽ

ወግ - መስከረም 1 የዓዲስ ዓመት መባቻ

ገጹን ይመልከቱ

ወግ - በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን


በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ቀን

 @ከ ያዕቆብ ሰንደቁ

ከዓመታት በፊት በዕለተ ስቅለት አዲስ አበባ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታሪኳን የነገረችኝ አንድ ምዕመን የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ከሚነበበው የወንጌል ንባቡ ክፍል ጋር የሚገጥም ነበር ፡፡ ታሪኩን ከመተረኬ በፊት የማቴዎስ ወንጌል 6÷1-7 የተጻፋን ኃይለቃል ላንብብላችሁ 

 

 ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። …”

 

ይህ ምንባብ የተራራው ስብከት ከሚባለው መካከልሆኖወርቃማውቃልበመባል ይታወቃል፡፡ የሚያስተላልፈው ትምህርትም መንፈሳዊ ተግባር ለሰው ታይታ ተብሎ የሚከናወን አለመሆኑን ነው፡፡ ብዙ ሰዎችጸሎታቸውን፣በጎሥራቸውን ሁሉ በአደባባይ በሰውፊት ማድረግይፈልጋሉ፡፡ምዕመናንም ለቤተክርስቲያን መባ በአይነትም ሆነ በገንዘብም በምንሰጥበት ወቅት እዩልኝ ፣አሳውቁልኝ ፣አስነግሩልኝ ሳንል በስውር ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ሰዎች እንዲያውቁልን ብለን ማንኛውንም መንፈሳዊ ተግባር የምንሠራ ከሆነግብዞችእንባላለን ዋጋችንንም ከሰማይ ሳይሆን ከሰው ዘንድ እንቀበላለን፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክስቶስምይህንን እንዳታደርጉ ተጠንቀቁነው ያለው ፡፡

 

ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም፤ ብዙ ስውራን አባቶች ወዳሉበት ጥንታዊ ቦታ ይህች ሴት ልታጋራኝ ወደ ወደደችው ታሪክ እንሂድ

 

+++++

 

ሐረር እስላም ክርስቲያኑ በአንድ ላይ ተቀላቅሎ የሚኖርበት ከተማ ነው፡፡ ተወልጄ ያደኩት እዚያው ቢሆንም እናቴ ክርስቲያን ነበረች በልጅነቴ ሞታለች፡፡ በቡቸኝነት በማደጌም ይሁን በጤና እክል ብቻ በማላውቀው ምክንያት ሁሌ ሕመምተኛ ነኝ፡፡ ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲመጣ ግን መንፈሳዊ ዝንባሌ ውስጤ አደረና በገዳም በምንኩስና ሕይወት ጸንቼ መኖር ተመኘው ፡፡

 

የሐረር ከተማ

ወንድም እና እህቴም የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ብዙ አብረን ባለመኖራችንም ያንያህል ቀረቤታም ፍቅርም የለንም፡፡ በአጠገቤ ምስጢሬን የማካፍለው ሰው የለም፤ ሁሌም ብቸኛ ጭምት ነኝ፡፡ ከገዳም ስመለስ ወይም ከሆነ የጸበል ቦታ ስመጣ አንዳንዴ ደግሞ የምበላው ሳጣ ፤የተወሰኑ ቀናት ከአባቴ እና ከወንድም እህቴ ጋር እቆያለሁ፡፡ የተቀረውን ጊዜ በገዳማት፣በጸበል ቦታ ፣የንግስ በዓል ባለበት ቦታ ሁሉ በመዞር ጤና ስፈልግ ከራረምኩኝ፡፡

 

ቤተሰቦቼ የሕልም እናት እያሉ ይጠሩኛል፡፡ እንቅልፍ ከወሰደኝ በአብዛኛው ሕልም አያለሁ፡፡ እኔ ደግሞክፉው ሕልሜነው የምለው፡፡ አንዳንዴ አስጨናቂ እና ከባድ ሕልም ስለማይ እፈራዋለው፡፡ በሕልሜ ከማየው ደስ ከሚለኝ ነገር አንዱ የማላውቀው ገዳም ስሄድ አስቀድሜ ግቢውን፣ አጸዱን፣ የቤተክርስቲያኑን ሁኔታ የማገኛቸውን አባቶች ማየቴ ነው፡፡ በተቀረው እንኳን ብዙ አስፈሪና ክፉ ሀገራዊም ፣ግለሰባዊም ሕልም ስለማይ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ሕልም እንደማይ ከቤተሰቦቼ በቀር ሌላ ሰው አያውቅም እኔም አላወራም ፡፡ ምናልባት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ካላገኘሁት በስተቀር በፍጹም ሕልሜን ለማንም ሰው አልናገርም፡፡ ሕልሜን መናገሬ ያመጣብኝ ጣጣ ብዙ ስለሆነ ትምህርት ወስጃለሁ፡፡

 

የሕመሜ ምክንያት ቤተሰቦቼ የሚያመልኩት ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዛር መንፈስ ነው፡፡  በአንድ ታላቅ ገዳም በድንገት አንዴ ብቻ ያየዋቸው ታላቅ አባትየዛር መንፈስ እንዳለብኝ ቅዱስ ገብርኤል እንደሚራዳኝ ተግቼም እንድጸልይነግረውኛል፡፡ አንድ ቀን ደግሞ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አሞኝ ወድቄ ጸበል ስጠመቅ መንፈሱ ለፍልፎ ራሱን አጋለጠ፡፡

 

ከጀመርኩት የክርስትና መንገድ ለማሰናከል የሚፈታተነኝ ዲያብሎስ የሚያደርገውን ጥረት፤ቆጥሬ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ በአንድ ገዳም የማውቃቸው አባት ያለብኝን ፈተና አይተውየዲያብሎስ ውጊያዎችየግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ፫ኛ የጻፉትን አያሌው ዘኢየሱስ የተረጎመውን መጽሐፍ አንብቢው ብለው በመከሩኝ ጊዜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ማንበብ የጀመርኩ ሰሞን እንቅልፍ እያዳፋኝ ቢያስቸግረኝም ሳላቋርጥ ጭራሽ ማስታወሻ እየያዝኩ አጠናሁት፡፡

 

 ተፈታታኜ ዲያብሎስየካበተ የሥራ ልምድ ያለው መንቻካ ፣ማንንም የማይንቅ ፣ሴሬኛ መሆኑን ከመጽሐፉተረዳሁ ፡፡ ዲያብሎስን ድል የምነሳበትን መሳሪያ ጸሎት፣ ስግደት፣ ጾም መሆኑን በመማሬ ውጊያውን አፋፍሜ፤ በሰውነቴ ውስጥ እንዳይቀመጥ አስጨነኩት፡፡ አንዳንዴ ውጊያው በጣም ሲበረታብኝቆይ ግን ለምንድን ነው? እኔን የሚፈታተነኝ ? አንዲት ትንሽ ሴት ለመጉዳት ይህ ሁሉ ድካሙ ለምን ይሆን?” እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ብዙ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት የሚችሉ ቅድስና ያላቸው አባቶች እያሉ! እኔ ላይ ለምን ጌዜውን እና ጉልበቱን ይጨርሳልእላለሁ በግርምት ፡፡

 

ለጥያቄዬ መልስ ለማግኘትየዲያብሎስ ውጊያዎችመጽሐፍን ሳገላብጥ ከዚህ በፊት ያላስተዋልኩትን ቃል አነበብኩኝውጊያውን አቋርጦ ደክሞት እረፍት ወደስዶ አያውቅም ፣ማንንም ሰው አይንቅምየሚለውን፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን በሙሉ ከእግዚአብሔር መንግስት ለማስወጣት ካለድካም የሚሠራ ጠላት መሆኑን ተረዳው፡፡ ከዚያምጠላትን ማወቅ የማሸነፊያ ቁልፍ ነውብዮ በየገዳሙ በጸሎት፣ በስግደት በየፀበሉ በመጠመቅ ውጊያውን ድል ለማድረግ ተጋሁ ፡፡

 

 በምሔድበት ገዳም ሁሉ ከአበው የማገኘው እንክብካቤ እና ፍቅር ተስፋ እንዳልቆርጥ አድርጎኛል፡፡ ጸበል ተጠምቄ፣ ሰግጄ ፣መስቀል ተሳልሜ ከላዬ አልላቀቅ ያለ ክፉ መንፈስ፤እንዴት እና መቼ ከእኔ እንደሚለይ ለማወቅ ብዙ እጸልያለሁ፡፡ አባቶችን በጸሎት ጠይቁልኝእስከመቼ እንዲህ በሰይጣን ታውኬ እኖራለሁ?” እያልኩኝ እጠይቃለሁ፡፡ መልሱ ግንቆይ ገናነው ጌዜው አልደረሰም ጠብቂ ሕመም ብቻ ሳይሆን በረከትም አለበትና ደጅ ጥኝየሚል ብቻ ነበር፡፡

 

ሐረር ብኖርም ስለ ደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ብዙም ሰምቼ አላውቅም፡፡ ምሥጢሩ ባይገባኝም የጻድቁ አባ ሳሙኤል ስም ሲጠራ፣አሰቦት ገዳም ሲነሳ ሰውነቴ ይግላል፣ ልቤ ይረበሻል፡፡ ብዙ ኪሎሜትር አቋርጬ በሰሜን፣ በደቡብም ወዳሉ ገዳማት ስሄድ ከርሜ ሐረር ስመጣ ፤በቅርብ እዚሁ በአሰበተፈሪ በኩል ወዳለው ገዳም መርቶኝ አያውቅም፡፡

 

አስታውሳለሁ ቀኑ ህዳር የቅዱስ ገብርኤል ዋዜማ ነው፡፡ ተኝቼ በሕልሜ የማየው ጠይም ሰውእኔ ቅዱስ ገብርኤል ነኝብሎ አነጋገረኝ፡፡ የተላኩበትን መልእክት በጥንቃቄ አድምጪሥሉስ ቅዱስን በአሰቦት ገዳም ተገኝተሽ አመስግኝ፤ በዚያም ጸንተሽ ተቀመጪ፤በቅርቡ የሥላሴ አገልጋይ ወደ አንቺ ይመጣሉ ብዙ በረከት ያላቸው አባት ምልክታቸውም በአንበሳ ላይ ተቀምጠው የሚሄዱ ናቸው ከእግራቸው ሥር ወድቀሽ በረከታቸውን ውሰጂብሎ አዘዘኝ፡፡ ጠዋት መኝታዮ ሥነሳ ሰውነቴ ዝሎ መቆም አቅቶች ተዝለፈለፈ፡፡ እንደምንም የተለመደውን ጸሎቴን አድርሼ ሥጋዬን ለማበርታት ምግብ ፍለጋ ከመኝታ ቤቴ ወጣሁ፡፡

 

+++++

ደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም 
 

 በታህሳስ 1 ሌሊት የለመደው ሕልሜ ከአሰበተፈሪ መገንጠያ ጀምሮ ወደ የአሰቦት ገዳም የሚወስደውን ዳገት ከዚያ አልፎም የአባ ሳሙኤልን ገዳም የሴቶች ገዳም መሆኑን ጭምር ነግሮ አሳየኝ፡፡ ጻድቁ አባ ሳሙኤልን ፊታቸው እንደ ፀሐይ እያበራ፤በአንበሳ ላይ ተቀምጠው ረጅም የብረት መቋሚያ መስቀል በዕጃቸው ይዘው አየሁ፡፡ ከእሳቸው በስተኋላ ሆኖ ራቅ ብሎ የሚከተላቸው ደግሞ አለባበሱ የከተማ ሰው አይነት የሆነ አንድ ሰው ይታየኛል፡፡ በአንገቱ ላይ የአባ ሳሙኤል ምስል ያለበት የነሀስ መስቀል አድርጎል፡፡ በአነስተኛ ሻንጣ ከያዘው ገንዘብ እያወጣይሄ ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ይሆናል፣ይሄ ደግሞ ለገዳሙ መናንያን ቀለብ መግዥያ ነው፣ ይህ ደግሞ ለእርሶ የእረፍት በዓል ዝክር ይሆናልእያለ ላጻድቁ ያስረዳል፡፡

 

አባታችን አባ ሳሙኤል ፍታቸውን ወደ እኔ አዙረው ለዚያ ሰውይህችን ልጄን ለበዓለ ዕረፍቴ ይዘሀት እንድትመጣብለው አዘዙት፡፡ ሰውዬውን ትኩር ብዬ አየሁት ፊቱ በብርሀን ተሞልቷል ትህትና የተመላ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሌላ ዳገት ወጥተን ምዕራፈ ቅዱሳን በሚባል ቦታ ደርሰን ከሰውዬው ጋር አረፍ አልን ምንም ንግግር የለም፡፡ ከተቀመጥንበት ተነስተን ረጅሙን ተራራ ወጥተን ወደ ሜዳው ስንደርስ ዙሪያውን በብርሃን የተከበበ ቤተክርስቲያን ከውሥጡ ብዙ ነጫጭ የለበሱ ሰዎች የሚያስቀድሱበት ልዩ የእጣን መዓዛ ያለው አየሁ፡፡ እየፈራሁይህ የማን ቤተ ክርስቲያን ነው?” በዬ ጠየኩ፡፡ የገዳሙ አበምኔት መሆናቸውን በኋለ ያወኳቸው ሰውየደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነውሲሉኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡

 

የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ስውራን በሞት ሳይነጠቁ የሚኖሩበት ነው፡፡ ብዙ ቅዱሳንም በሕይወተ ሥጋቸው ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉበት ቦታ ነው፡፡ ስውራን አበው ባሉበት ቦታ የከበሮ ድምጽ ይሰማል፣የዕጣኑ መአዛ ያውዳል፡፡ በገዳሙ ውስጥ መናንያን በጾም፣ በጸሎት፣ በገድል፣ በቱርፉት ተወስነው ይኖራሉ፡፡

 

ታህሳስ 12 ቀን በሚከበረው የአባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል እና በቅድስት ሥላሴ በዓል ከሩቅም ከቅርብም አበው መነኮሳት ምእመናን ከየቦታው ተሰቡስበው ይመጣሉ፡፡ የእንግዶችን እግር አጥቦ የሚበሉትን ዳቤ ፣ንፍሮ የሚጠጡት ጠላ አዘጋጅቶ መቀበል የገዳሙ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የገዳሙ የተግባር ቤት ለብዙ ሰዎች ምግብ በማሰናዳት በከባድ አገልግሎት ውስጥ ያልፋል፡፡የሚጠጣ ጠላ መጥመቅ ፣ዳቤ መጋገር፣ ንፍሮ መቀቀል፣ ወጥ መሥራት፣እንጨት መልቀም ፣ዳገቱን ወጥቶ ወርዶ ውሀ መቅዳት የመናንያኑ የአገልግሎት ድርሻ ነው፡፡

 

ገዳሙን በሚያስፈልገው ሁሉ የሚረዱ ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም፤ የሚያስፈልገው ነገር ሲሟላ ነው እንጂ እገሌ እንዲህ አደረገ ተብሎ አይነገርም፡፡ በዐቢይ ጻም፣ በፍልሰታ ገዳምያኑ በጸሎት ብዙ ስለሚጠመዱ የእነርሱን ፈንታ ድርጎውን የሚያሰናዳ ፣እንጨት የሚሰብር፣ ዱቄት የሚፈጭ ፣ጭስቤት ገብቶ ወጥ በትልቅ ጎላ የሚያበስል አንድ አገልጋይ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለታላላቅ መናንያንም ሆነ ለወጣኒ (ለጀማሪ) መነኮሳት የፈለጉበት ቦታ የሚላክ ማገልገል ብቻ ሥራው የሆነ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ታዲያ ሲመጣ እንጂ ሲሄድ አይታወቅም፡፡ ሰው እንዲያውቀው አይፈልግም፤ ብዙ አያወራም ብቻሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት ነውየሚለው፡፡

 

አሮጌ ያደፈ ልብስ የሚለብስ ሥራውን እንጂ እርሱነቱ የማይታወቅ ሰው ነበር፡፡ አንዳንዴ በዓመት ሦስት አራቴ መጥቶ ለወራት የሚሆን እህል ፈጭቶ ፣ማገዶ ለቅሞ ሌላም ሥራ ሰርቶ ሰው ሳያየው ሹልክ ብሎ ይሄዳል፡፡ስምህ ማነው? ከየትነው የመጣህው?” ብሎ የሚጠይቀውን ሰው አይወድም፡፡ እንደዚህ ሲጠይቁኝሕመሜ ይነሳብኛል ፣ግዝት አለብኝብሎ ይቆጣል፡፡እሺ ማን ብለን ስምህን እንጥራውሲሉትረድ ብላችሁ ጥሩኝ የአባ ሳሙኤል አገልጋይ እያለ ይናገራል፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት የማኅበር ጸሎት ላይ በገዳሙ ሥራዎች ቃለምዕዳን ሲሰጡ ለገዳሙ የሚያስፈልገወን ነገር ይናገራሉ፡፡ ከከተማ መምጣት ያለበት ነገር ካለ በቅጽል ስሙረድተብሎ ለሚጠራው ለአባ ሳሙኤል አገልጋይከተማ ስትሄድ ለጻድቁ ወዳጆች ንገርልንይሉታል፡፡ እርሱምአደርሳለሁ ብሎ እጅ ነስቶ ይቀመጣል፡፡ እናም የገዳሙ መናንያን የአባ ሳሙኤል አገልጋይ የሆነው ይህ ሰው ለመናንያኑ ከባድ የሆነውን የገዳሙን ማብሰያቤት ሥራ ጨፈቃ እንጨት ጨምሮ እሳቱን አንድዶ፣ውሀ ቀድቶ፣ ሊጥ አቡኩቶ ፣እንጀራ ሲጋግር ያድራል፤ወጥ በትልቅ በርሜል ሲያበስል ወላፈኑ አይፈጀውም፣እንቅልፍ አያሸንፈውም ድካም አይሰማውም ፡፡ አምስት መናኝ የሚሠራውን ሥራ ብቻውን ስለሚያከናውን መናንያኑ በሙሉ በመገረምየጻድቁ ረድኤት እየጠበቀው ነው እንጂ እንዴት እሳቱን ቻለውይላሉ፡፡

 

 የገዳሙ አበምኔትም አገልግሎቱን በማየት አረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ቀጭን ጥለት ያለው በአራቱም አቅጣጫ የአቡነ ሳሙኤል ሥዕል የተጠለፈበት ነጭ ነጠላ ሸልመውታል፡፡ ረድ በከተማ የሚያውቃቸው ብዙ ባለጠጎችን ለምኖ ለገዳሙ የሚያስፈልገውን እጣን፣ ጧፍ፣ መገበሪያ ስንዴ፣ የመናንያን ልብስ አቡጀዴ፣ ጨው፣ ዘይት ሌሎቸንም ነገር በአይሱዙ መኪና አስጭኖ ሰዎች ይዘው እንዲመጡ ይደረጋል፡፡

 

ገዳሙን ለረጅም ዘመን የሚረዱ አንድ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰው እየሰጡት ነው ረድ ይዞ የሚመጣው ይባላል፡፡ይህ በየጊዜው ለገዳሙ የሚደረገው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍነገር ምንድ ነው?” እያሉ መናንያኑ መወያያ በማድረጋቸው የተለያዩ ወሬዎች ተወሩ፡፡ የገዳሙ አበምኔት በሰርክ ጉባኤ መናንያኑ ሁሉ በተሰበሰቡበት ተቆጥተውከእንግዲህ ወዲህ በገዳም እንዲህ አይነት ወሬ ማውራት አይቻልም፤ የገደማችን በረከት ያስቀርብናልብለው ነገሩን አዳፍነው በማውገዛቸው ስዚህ ነገር ማውራት ውግዝ ሆኖ ወሬው ቆመ፡፡

 

+++++

 

  13ኛው ክፍለዘመን የተነሱ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዘመዶቼ የጤናዮን ችግር ተመልክተው እነርሱ በሚኖሩበት ሀገር ሕክምና እንዳገኝ አመቻቹልኝ፡፡ ይህን ጉዳይ ለመከታተል ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ የማርፍባቸው ዘመዶቼ ብዙ ለሃይማኖት ግድ ስለሌላቸው መንፈሳዊ ደስታ አይሰማኝም፡፡ አንድ ቅዳሜ ቀን ወደ ሐረር እቃ እንድልክ ተልኬ አይሱዙ መኪና እቃ የሚጭንበት መርካቶ ሄድኩኝ፡፡

 

በአነስተኛ ካርቶን የታሰረውን መልእክት ለማድረስ አይሱዙ መኪኖቹ የሚጭኑበት ቦታ ደርሼሐረር የሚጭነው የትነው ስልአንድ ትንሽልጅ ጠየኩኝ  እዛጋር ነውብሎ ወደ ማዶ አሳየኝ፡፡ መኪኖቹ ወደ ቆሙበት መጠጋት ጀመርኩኝ፡፡ ገና በደንብ ሳልጠጋ አንድ ሰው በርካታ ቁሳቁ በጆንያ እና በማዳበሪያ ወደ መኪና ያስጭናል፡፡ የማውቀው መስሎኝ ትኩር ብዬ አየሁት፡፡ እርሱ ግን አላየኝም፡፡

 

ሰውዮው መልከ መልካም ሙሉ ልብስ የለበሰ ባለጸጋ ኑሮ የተመቸው ሰው ይመስላል፡፡ ይህም ይጫንላቸው እያለ ካለስስት ከማከፋፈያው ብዙ ገንዘብ የሚያወጡ እቃዎችን ያስጭናል፡፡ እንዴይሄ ሰው በህልሜ ያየሁትን ሰው ይመስላል ብዮ ሳልጨርስ ሰውዬው እቃ ወደቀበት እና ወደ መሬት ጎንበስ አለ ፡፡ ከሸሚዙ ውስጥ ብቅ ያለው ማህተም ላይ ያንጠለጠለውን ሳይ ደነገጥኩኝ በሕልሜ ያየሁትን የአባ ሳሙኤል ምስል ያለበት መስቀል ነው ያንጠለጠለው ፡፡

 

እኔ በቆሙኩበት ቀረሁ እርሱ በፍጥነት ገንዘቡን ከፋፍሎአደራ አሰቦት ስትደርሱ ታጥፋችሁ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም አድርሱብሎ ሲናገር ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ከቆምኩበት ሳልንቀሳቀስ ሰማያዊ ዘመናዊ መኪናውን አስነስቶ ከአካባቢው ተሰወረ፡፡ በዐይኔ ብከተለው ተሰውሮ ቀረ ፡፡ ወዲያው ወደ አይሱዙ ሹፌር ሄድኩናይህ እቃ ሐረር ታደርስልኝ ብዬ ጠየኩትብዙ ሳያቅማማእሺ ብሎተቀበለኝ፡፡ ቀጠልኩናይህን እቃ ለማነው የጫናችሁት? ” አልኩት፡፡ በጥያቄዬ ግራ የተጋባው ሹፌርለገዳም ነዋ! ለአባ ሳሙኤልሲለኝ ልቤ ማረጋገጫ እንዳገኘ ቆጥሮ እርፍ አለ! በድንጋጤ አንደበቴ ተሳሰረና ወደ ኋላ ዞሬጉዞ ወደ ቤት ሆነ፡፡

 

+++++

 

እቤት ስገባ አመሻሽ ላይ ስለነበር ዘመዶቼ እስኪሰበባሰቡ ድረስ ጠበኩኝ፡፡ ውጭ ሀገር መሄድ እንደማልፈልግ ነገ ወደ ሐረር ለዛውም ወደ ገዳም እንደምሄድ ተናገርኩኝ፡፡ አነጋገሬ ቁጣ ቁጣ የሚል ስለነበር ዘመዶቼ ግራ ተጋብተዋልምነው? ምነካሽ? ለምን መጣሽ ለምንስ ተመልሰሽ ትሄጃለሽ?”ሲሉኝ ቡሶቴ ሁሉ ተጠራቅሞ እንባዬ በቁሜ ተዘረገፈ፤መናገር አቅቶኝ በተንተባተበ አንደበትበጠዋት መኪና አሳፍሩኝብዬ ወደ መኛታ ክፈሌ ገባሁ፡፡

 

 አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ 13ኛው ክፍለዘመን የተነሱ ከቡልጋ አውራጃ በኢቲሳ አካባቢ ከታወቁ ደጋግ ሰዎች ከአባታቸው ከእንድርያስ እና ከእናታቸው ከአርሶንያ የተወለዱ ጻድቅ ናቸው፡፡ ከአሥራ ሁለቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት ደቀመዛሙርት መካከለ አንዱ ናቸው፡፡ በዚህ ታላቅ ገዳም አጽማቸው አርፎ የቃልኪዳናቸውን በረከት ምእመናን ድኅነት ያገኙበታል፡፡

 

 ከመናሐሪያ የተነሳው አውቶብስ ሐረር ደርሰን ወደ አሰበ ተፈሪ ከተማ እስክንደርስ ድረስ ሹፌሩ መዝሙር ያዘምር ነበር፡፡ በተለይ የዘማሪ እንግዳወርቅ ለአባ ሳሙኤል መዝሙር ማን እንዳዘዘው ባለውቅም ደግሞ ደግሞ ያሰማዋል፡፡ በጣም ተመስጬ እንባዬ እየወረደ አብሬ እዘምራለሁ

 

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ መነኮስ ኃያል ቤቴ ግባ

ታስባርካለህ ሰውን ምድር ቅርብነህ አንተ ለእግዚአብሔር

 የበረሀው መናኝ ግሩምነው ገድልህ

ምድርህን አስባርከሀል ከፍ አድርገህ በእጅህ

 ታምርነው ገዳምን ላየ

ረድኤት በረከት ገበየ

 ልጆችህ በገዳም ውስጥ ያሉት

ሳሙኤል ሳሙኤል ይላሉ

አዝማች

አይሻገርብሽ  እህልም ኃጢአት

ጌታችን ብሎታል ዋልድባን መሬት

 ህርመት ይዘው ልጆቹ በሙሉ

ቋርፍ ነው ዘውትር የሚበሉ

አዝማች

የጣመ ያለመ አጥተን

ዮርዳኖስ ጠበል ምግብ ሆነልን

አዝማች

አስኬማውን ለብሶ በገዳም ሲኖር

የትህትና አባት ነው የሕግ መምህር

 ሃሌሉያን ሄደን

አይተን አብረን ካንተ እንኑር አልን

 እያለ ይቀጥላል ፡፡

 

 

አሰበ ተፈሪ ስደርስ በስተግራ የሚወስደውን መንገድ ይዥ 12 ኪሎሜትር ተጉዥ ከአውቶቡሱ ወረድኩኝ፡፡ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም በየት አቅጣጫ እንደሆነ እየጠየኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ከፊት ለፊቴ የሚታየውን ተራራ ጢሻውን መንገድ ሁሉ በሕልሜ ስላየሁት የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

« ለ አፍታ ዝም ካልኩ በኋላ መጠየቅ እንኳ አለብኝ ብዬ በፍርሀትወንድሜ አንተ ማነህ? በህልሜስ ያየሁትናንት መርካቶ ያየሁ አንተነህ?” አልኩት፡፡ አንገቱን ወደመሬት አቀርቅሮእኔ ረድ እባላለሁ የአባ ሳሙኤል ገዳም አገልጋይ ነኝአለኝ፡፡»

 

አውቶብስ ውሰጥ የሰማሁት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የሚለው መዝሙር ያቃጭልብኛል፡፡ ፍርሀት የተቀላቀለበት ደስታ እየተሰማኝ ነጠላዩን ሰብሰብ አድርጌ ዳገቱን መውጣት ጀመርኩኝ፡፡ በዚያ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ብቻዬን ዳገቱን መውጣት ተያያዝኩት፡፡ ዛፉን ንፋስ ባወዛወዘው ቁጥር ድምፅ ስሰማ እደነግጥ እና አማትባለሁ፡፡ ትንሽ አለፍ እንዳልኩኝ ደስ የሚል ወረብ ይሰማል፤ እጣን ይሸታል፣ ጸናፅል ይንሿሿል፣ ከበሮ ይመታል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኑ የቀረብኩኝ መስሎኝእንዴ እንዲህ ቅርብ ነው እንዴ?” እላለሁ ነገርግን የሚታየኝ ጫካ ብቻ ነበር፡፡ የወረቡ ድምፅ ግን ወደ እኔ እየቀረበ መጣ የሚመስጥ ልብ የሚማርክ ነበር እስከ አሁን አልረሳሁትም በልቤ ሰሌዳ ተጸፏል እንዲህ የሚል የግዕዝ ወረብ 

 

ደምፀ ወተሰብከ ውስተ ዓለም

ዓለም ውስተ ዓለም፣

ለሳሙኤል ኮከበ ገዳም ትሩፍ ዜና ምግባር፡፡

 

ተመስጬ ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ዳገት እየወጣሁ ከኋላዬ ኮቴ ተሰማኝ ደንግጬ መዞር አቃተኝ፡፡ አይዞሽ በርቼ አትፍሪየሚል ድምፅ ስሰማ ልቤ ተሰነጠቀ፡፡ እንደምንም ብዬ ወደ ኋላ ዞር ስል አንድ ሰውዬወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ነው የምትሄጂውቡሎ በትህትና ጠየቀኝ፡፡ ድንጋጤ ይሁን አላውቅም መልኩን አላየሁትም ነበር፡፡ ዝግ ባለ ድምፅ አዋ አልኩት፡፡ ላግዝሽ አለና በጀርባዮ ያያዝኩትን አነስተኛ ሻንጣ ከላዩ ላይ አወረደና ያዘው፡፡

 

በሁኔታው ግራ ገባኝ የምናገረው ጠፋኝ አሁን ሰውዩውን አስተዋልኩት ቀጭን አረንጎዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ያላት ነጭ ነጠላ ካለይ አድርጎል፡፡ ከውስጥ ያረጀ እና የነተበ በእሳት የተበላ ልብስ ለብሷል፡፡ ፊቱን ትኩር ብዬ ለማየት ፈራሁ፡፡ በጨረፍታ ሳየው በሕልሜ ወደ አባ ሳሙል ዘንድ ይዞሽ ይሄዳል የተባለው ሰውዬ መሆኑን አወኩኝ፡፡ በነጠላው ውስጥ ያየሁት የአባ ሳሙኤል ስዕል ያለበት መስቀል ያንጸባርቃል፡፡

 

የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነኩኝ ከትናንት በስትያ መሀል መርካቶ ሳየው ባማረ የከተማ ልብስ፣በጥሩ ዘመናዊ መኪና፤ዛሬ ደግሞ በገዳም አሮጌ እራፊ ጨርቅ በባዶ እግር ብዬ ተገረምኩ፡፡ አፍታ ዝም ካልኩ በኋላ መጠየቅ እንኳ አለብኝ ብዬ በፍርሀትወንድሜ አንተ ማነህ? በህልሜስ ያየሁትናንት መርካቶ ያየሁ አንተነህ?” አልኩት፡፡ አንገቱን ወደመሬት አቀርቅሮእኔ ረድ እባላለሁ የአባ ሳሙኤል ገዳም አገልጋይ ነኝአለኝ፡፡

 

ዳገቱን እየወጣን በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ እያለፍን ስለገዳሙ አመሰራረት ስለ አባ ሳሙኤል ገድል እና በረከት ይተርክልኝ ጀመር፡፡ ታሪኩን ሲተርክልኝ የተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ ደስ እያለኝ እሰማ ጀመር፡፡ ትረካውን ቀጠለበዚህ ገዳም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቸሩ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ስውር ቤተመቅደሶች አሉ፤ይህ ብቻም አይደለም በገዳሙ የከበሮ፣ የጸናጽል፣ የቅዳሴ ድምጽ ይሰማል፤ የተለየ የእጣን መዓዛም ይሸታል፡፡ በጽሞና ለሰማው ልብን ወደሰማየ ሰማያት ይዞ የሚሄድ ሕብረ ዝማሬ ይደመጣል፡፡ በአባታችን በአቡነ ሳሙኤል ገድልም እንደተጻፋ እንደ ሔኖክና ኤልያስ ሞትን ሳይቀምሱ የተሰወሩ በርካታ ቅዱሳን መኖሪያ ታላቅና ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡ በቦታው ላይ የተሰወሩ ቅዱሳን ለገዳማውያኑም ሆነ በዓለም ለሚኖሩ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው ለያዙ ሰዎች እየተገለጡ ይታዮቸዋል፤ መልእክት ይነግሯቸዋልአለኝ፡፡

 

“ በዛሬው ዕለት ይህን ቅዱስ ገዳም በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ ለዘመናት ሲያገለግለኝ የኖረውን ወዳጄን ወደ ቅዱሳን ስፍራ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ልጄ “በስውር የሠራውን መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ከሥላሴ ዘንድ በይፋ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀበልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡

 

ትረካውን ቀጠለ «በዚህ በአሰቦት ገዳም የተሰወሩ ቅዱሳን አባቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 1934 . ከዋልድባ ወደዚህ መጥተው የተሰወሩ 500 ቅዱሳን ከማኅበረ ሥላሴ ገዳም 1000 መናንያን መጥተው በዚህ ቦታ ተሰውረዋል፡፡ አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ባሕታዊ 10 ዓመት ያህል በዋሻ ዘግተው ከኖሩ በኋላ 1945 . ከሰው በመሠወር ከቅዱሳን ሕብረት ተቀላቅለዋል ፡፡ የገዳሙ ላሞችን ለብዙ ዘመናት ሲጠብቁ የኖሩ ባሕታዊ ክፍሌ የተባሉ 1964 . ተሰውረዋል፡፡ ባሕታዊ አባ በላይ /ሚካኤል የተባሉ መነኩሴ ሐምሌ 7 ቀን 1972 / ከቅዳሴ በኋላ በመነኮሳት ፊት በይፋ በቅዱሳን ተጠርተው እንደተሰወሩ በወቅቱ በቦታው የነበሩ አበው ምስክር ናቸው» አለኝ እና ለአፍታ ዝም አለ፡፡

 

ይገርምሻል ብሎ ትረካውን ቀጠለይህ ቦታ መካነ ስዋሬ የዕርገት የርቀት ቦታ ነው እያለ እየነገረኝ በተለየ ተመስጦ ውስጥ ገባሁ፡፡በፊቴ ደመና ግጥም አለ የብርሃን ምንጣፍ ተነጥፎ ይታየኛል፤ ሰማያዊ ጸናጽል ድምጽ ሰምቼው የማላውቀውን ዜማ ሰማሁ፡፡ ከፊት ለፊታችን ወደ እኛ የሚመጡ አንድ ታላቅ አባት ታዩኝ ገና ወደ እኛ እየቀረቡ ሲመጡ መቆም አቅቶኝ ወደ ምንጣፉ ተደፋው፤ ማየትም ሆነ ቀና ማለት አልቻልኩም፡፡ ድምጽ ይሰማኛል የሚያረጋጋ የታላቅ ቅዱስ አባት ብራኬአቤቱ ሕዝብህን አድን ርስትህን ባርክየሚል፡፡ ወዲያው የኪዳን ጸሎት ደረሰ፤ ቀጠለና ቅዳሴ ይቀደስ ጀመረ ፤ልዩ የእጣን መአዛ ልብን የሚያስደስት ሽቱ ይሸታል፡፡

 

አብሮኝ የመጣው ሰውእሺ ጻድቁ አባታችንእያለ ሲናገር አባ ሳሙኤል እንደተገለጹ ገባኝ፡፡ ለእኔ አይታዬኝም ድምፃቸው ነው የሚሰማኝ እንዲህ አሉበዛሬው ዕለት ይህን ቅዱስ ገዳም በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ ለዘመናት ሲያገለግለኝ የኖረውን ወዳጄን ወደ ቅዱሳን ስፍራ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ልጄበስውር የሠራውን መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ከሥላሴ ዘንድ በይፋ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀበልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሰው ያላወቀውን የጽቅ ሥራህን፣ በሥውር ያደረከውን ተጋድሎህን ሁሉ ሥላሴ አይተውቷል፤ ሰማያዊ ዋጋም ተሰጥቶሀልእያሉ ይመርቁታል፡፡ እርሱም በትህትንይህ ለእኔ አይገባም ቅዱስ አባታች ገና መቼ አገለገልኩ ምኞት ፍላጎት ፍቅር ነው እንጂ ብዙ ሥራ ይቀረኛልእያለ በፍርሀት በትህትና ሲናገር ሰማሁ፡፡

 

እኔ በሰመመን ውስጥ ሆኜ መስማቴን ቀጠልኩ እንዲህ አሉትይህችን አጠገብህ ያለችውን ትንሽ ልጄን እንኳን ይዘሀት መጣህ፡፡ ዲያብሎስ ሊያጠፋት ይፈታተናታል፤ ነገርግን በጸሎቷ ታሸንፈዋለች ዋጋዋ ትልቅ ስለሆነ በዚሁ በአባ ሳሙኤል ገዳም ጸንተሽ ተቀመጪ ከቅዱሳን ጋር አብረሽ ዲያብሎስን ተዋጊው፤ በገዳም ጸንተሽ ደጅ ጥኚ፤ ጊዜው ሲደርስና ጠላት ሲወገድልሽ ብዙ በረከት ታገኚያለሽበላት አሉት፡፡ በመስቀላቸው ሲባርኩኝ አይኔ በርቶ ማየት ጀመርኩኝ ይሕን የዛሬውን ሰማያዊ ምሥጢር ማየትሽን ለማንም ሰው እንዳትናገሪ አደራ የረድን ነጠላ እንቺ በቦርሳ ይዘሽ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ሂጂ ነጠላው የእኔ በረከት ነው ወገብሽን ታጠቂበትብለው ባረኩኝ፡፡

 

የቅድሙ ደመና ወደ አጠገቤ መጣና በድጋሚ ከበበኝ በድጋሚ ዐይኔ ተከፈተና ማየት ጀመርኩ፡፡ ሁሉት ቅዱሳን መላእክት አብሮኝ ከመጣው ከረድ አጠገብ በቀኝ እና በግራ ቆመው ታዩኝ፡፡ ልክ መላእክቱ አጠገቡ ሲቆሙ ነጠላውን ወደኔ ወርውሮ ወደ ሰማይ ከፍ ሲል ታየኝ በግዘፈ ሥጋ ከፍ ከፍ እያለ ሲወጣ ተመለከትኩኝ ዐይኔን ተክዬ እየተመለከትኩኝ ደመናው ጭኖ ቀጥ አርጎ ወደ ሰማይ ወሰደው፡፡ ከነበርኩበት መንፈሳዊ ተመስጦ ነቃሁ የረድን ነጭ ነጠላ በእጄ ይዤለሁ፡፡ በሥርዓቱ እጥፍጥፍ አድርጌ ሻጣዬ ውስጥ ከትቼ ዳገቱን ጫካውን አቋርጬ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ጉዞዩን ቀጠልኩ፡፡

 

+++++

 

            የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም

 ገዳም ስደርስ አስቀድሜ በሕልሜ ያየሁት ቤተክርስቲያን ሕንፃ አገኘሁት፡፡እግዚአብሔር ሆይ ሥራህ ድንቅ ነውበዬ አመስግኜ ዘወር እንዳልኩየገዳሙ መናንያን እግሬን ለማጠብ፣ እቃዬን ለመቀበል  የሚበላ ዳቤ ለማዘጋጀት ተሯሯጡ፡፡ ጸሎት አድርሼ ቤተ ክርስቲያኑን ዞሬ ተሳልሜ ስጨርስ ተቀብለው የማርፍበት ቦታ ሰጡኝ፡፡

 

የገዳሙ መናንያን ትናንት ቀን ብዙ እንጀራ ሲጋግር እና ወጥ ሲሠራ የነበረው ረድ የጀመረውን ሥራ አቋርጦ መጥፋቱ አሳስቧቸው ለገዳሙ አበምኔት ተነገሯቸው፡፡ አበምኔቱ ደንግጠው ትልቁን የገዳሙን ደወል አስደወሉ፡፡ መናንያኑን ሲሰበሰቡወንድማችን ረድ የጀመረው ሥራ አቋርጦ ስለጠፋ የተጀመረው የገዳሙ ሥራ እንዳይቋረጥ ተባብራችሁ በረድ ፋንታ ሆናችሁ ሥሩ፡፡ የተፈጨው እህል ትንሽ ስለሆነ ቡዙ ኩንታል መፈጨት አለበትና አደራ በየተራ ፍጩ፡፡ የተቀራችሁ ደግሞ ረድ ጾም እና ተጋድሎ አብዝቶ በገድል ብዛት አሞት አንድ ቦታ ወድቆ እንዳይሆን በየቦታው በየሥርቻው ፈልጉትብለው አዘዙ፡፡

 

ረድ ከጠፋ ቀናት ተቆጠሩ የገዳሙ አበምኔት የረድ መጥፈት በጣም አስጨነቃቸው፡፡ በሰርክ ጉባኤ ላይ ከጸሎት በኋላልጄን የበላ አውሬ አልጮህ አለ፣ ገዳማችን ተጎዳ ረድኤቱን በረከቱን አጣእያሉ ያዝናሉ ፡፡ ሀዘናቸውን ሳይ ይህንን ጭንቀት ስሰማ በጣም አዝኜበቃ ለምን እውነታውን አልነግራቸውምብዬ አሰቡኩኝ፡፡ ግን ደግሞ መልሼ አሰብ ሳደርግለማንም እንዳትናገሪየሚለውን ማስጠንቀቂያ ሳስታውስ ፈራሁ፡፡ ደግሞስየወደፊቱም ኑሮዩ በዚሁ ገዳም አይደል እንዴ የሚቀጥለው እንዴት ብዬ ይህን መናገር እችላለሁ? ”ብዩ በትምህርተ መስቀል አማትቤ ዝም አለኩኝ፡፡

 

በአባ ሳሙኤል ገዳም ሰባተኛ ቀን ሞላኝ፡፡ ከሌሎች ገዳም የበለጠ መንፈሳዊ በረከት ያገኘሁበት ስለሆነ መንፈሳዊ ደስታ ተሰሞቶኛል፡፡ ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል አጽማቸው ያረፈበት ቦታ ማታ ማታ ሄጄ እጸልያለሁ፡፡አባቴ በበረኮቶት ይባርኩኝ ወደ ፈተና እንዳልገባ ጠብቁኝ፣ ዲያብሎስን ድል የማደርግበትን ኃይል ስጡኝእያልኩኝ እማፀናለሁ፡፡ የረድ መጥፋት የገዳሙ መናንያን መነጋረሪያ ነቱን ቀጥሏል፡፡ ከማንም ሰው ጋር በዚህ ጉዳይ ፈጽሞ አላወራም ሁሉንም ነገር በልቤ ይዥዋለው፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት ብራኬ ለመቀበል መስቀል ለመሳለም ሲሄድ እንግዳ በመሆኔ ይሁን በሌላ ምክንያት በትኩረት ያዩኛል፡፡ እኔምያየሁትን ምስጢር ያውቁ ይሆን?” እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ እስከመቼ ይሆን ? ይህ ምሥጢራዊ መንፈሳዊ ትዕይንት ለማንም ሳልናገር የምኖረውእያልኩኝ ከራሴ ጋር አወራለሁ፡፡ ለካ ምሥጢር መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

 

በአባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ሱባኤ (ሰባት ቀን) ማለቴ ነው በሰላም በማጠናቀቄ መንፈሳዊ ደስታ ተሰማኝ፡፡ የዲያቢሎስ ውጊያ እንደማያቋርጥ ባውቅም ለዛሬ የተለመደውን ያህል ጸሎት ለማድረግ ድካም ተሰማኝ፡፡ ሰው ደካማ ፍጥረት ነው ለዛሬ የተለመደው ጸሎቴ ስግደቴን ልተወው ብዬ ተኛሁ፡፡ ጠዋት ስነሳ ሰውነቴ ተሳሰረ አእምሮዬ ደነዘዘ፡፡ ቀኑን ሙሉ እንዲሁ በራስምታት፣ በቁርጥማት አሳልፌ ማታ የሰርክ ጸሎት ለማድረግ ወደ ቤተክርስቲያን ገባሁ፡፡ ገዳማውያኑ በተመስጦ ደስ በሚል ዜማ ጸሎት እያደረሱ እያለ ጸሎቱን የሚያውክ ነጎድጎዳዊ ድምጽ ተሰማ፡፡ ገዳሙን ማወክ የፈለገው ዲያብሎስ እያጎራ በጠበጠው፡፡ ደግነቱ የገዳሙ አበምኔት ስለገዘቱት ሌላ ምስጢር ሳይቀባጥር ዝም እንዲል ተደረገ ፡፡ ስነቃ ጸሎቱ አልቆ ስለነበር ሰዎች ደግፈውኝ ወደ ማደሪያዬ ሄድኩኝ፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት እላዬ ላይ ያደረውን ጸላየ ሰናይ ኃይል ተመለክተውበምን ቻለችው ይህን ክፉ ጠላትብለው አዘኑ፡፡ ማምሻውንዮርዳኖስ በሚባለው ጸበል ጠዋት እንዳጠምቅሽ ነይብለው መልእክተኛ ላኩብኝ፡፡ የመጀመሪያው ቀን በሰላም ተጠመኩ፡፡ በሁለተኛው ቀን በጣም አመመኝ፡፡ ለሥስተኛ ቀን እንዳልጠመቅ ብዙ ጥረት ቢያደርግም በግድ በትግል ተጠመቅሁ፡፡ መቼም የሀሰት አባት ነው ተሰናብቻለሁ እለቃለው ብሎ ማለ ተገዘተ፡፡ ወደ ህሊናዬ ስመለስ ጠበል ጠጥቼ ገብቼ ተኛሁ፡፡

 

 ከምሽት ጸሎት ሰዓት ጀምሮ ዲያብሎስ ገዳሙን እጀግ በሚያሳዝን ሁኔታ አወከው፡፡ መናንያኑን መደብደብ ጸሎታቸውን ማቋረጥ መዝለፍ ለሊቱን ሁሉ ሲረብሽ አድሮ በነጋታው ጸበል እንዳልጠመቅ የሴቶች ልማድ (የወር አበባ) መጣብኝ እናም ጸበሉን መጠመቅ አቋረጥኩኝ፡፡

 

ከዚያች ቀን ጀምሮ አእምሮዩን አሳተኝ መናንያኑን መረበሽ፣ በመሳደብ፣ በመደብደብ ብዙ በጠበጥኩኝ፡፡ የሚመለከተኝ ሁሉለገዳሙ ፈተና ሆኜ እንደመጣሁ ቆጠረኝ፡፡ ጥቂት ወደ ራሴ ስመለስ ወደ ገዳሙ አበምኔት ቀርቤመዳኛዬ ይህ ገዳም እንደሆነ እና ከዚህ መውጣት እንደማልፈልግነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም “የሴቶች ልማዱ ከቆመ እኔ ራሴ አጠምቅሻለሁ አይዞሽ ብለው በፍቅር እና በትህት ተስፋ ሰጡኝ!” ከቀን ወደ ቀን አይምሮዬን እያሳተኝ እየባሰቡኝ ገዳሙን በሙሉ አወኩኝ፡፡ የገዳሙን አንድነት እና ጸሎት የሚፈትን ችግር በመከሰቱ ምክንያት ገዳሙን የሚያስተዳድሩ አባቶች በጉዳዩ ላይ ሰፉ ውይይት አደረጉ፡፡ በጉባኤው ቡዙ ክርክር ከተደረገ በኋላለገዳሙ ሰላም እና አንድነት ሲባል ከገዳሙ ውጭ ባለ ሌላ ጸበል ቦታ ተጠምቃ ሲሻላት ትምጣየሚል ውሳኔ ተወሰነ፡፡

 

የመጨረሻውን ውሳኔ የነገሩኝ የገዳሙ አበምኔት ነበሩልጄ የገዳሙ አስተዳደር ከገዳሙ ለቀሽ እንድትወጪ ስለወሰነ ሌላ ቦታ ሄደሽ ጸበል ተጠመቂአሉኝ፡፡ እንባዬ ዱብ፣ ዱብ እያለ ሲቃ ያዘኝ፡፡ እዚህ ለመቆየትበቃ አትናገሪ የተባልኩትን ነገር መናገር አለብኝ በዬ አሰብኩነገርግን አፌ ላይ አድርሼ እንደገና ይህ ታላቅ ምስጢር ነው ቡዬ ዋጥኩት፡፡ እየተንተባተብኩኝእኔ መሆን የምፈልገው እዚሁ ገዳም ነውአልኩኝ፡፡ አበምኔቱምአይሆንም የሚሸኙሽ መናንያን መጥተዋል እኔም በር ድረስ እሸኝሻለሁአሉ፡፡

 

ጎዜን ሰብስቤበውስጤ የያዝኩትን ምስጢር ልናገር ወይስ ይዤው ሊሂድእያልኩ እያመነታው ወደ ገዳሙ በር ተጠጋው እኔን ከገዳም ማስወጣት አላማው የነበረው ዲያብሎስ መውጣቴን ለማፋጠን ብሎ እኔን ቀየረኝ እና የተለመደውን ስድቡን ረብሻውን ቀጠለ፡፡ የሚሸኙን መናንያን በመማታት፣ በመገፈታተር በመሳደቡ ጉልበቱን አሰባስቦ ይወራጭ ጀመረ፡፡ የለበስኩት ልብስ ከላዬ ላይ ተበጫጨቀ ሻንጣዬ ልብሴ ሁሉ ተበታተነ፤ በአካባቢው ግርግር በመፈጠሩ ለመተጋገዝ ብዙ መናንያን ተሰበሰቡ፡፡ አንድ አባትእቃዋን ሰብስቡላት ተሸክማችሁ ከገዳሙ ውጭ ወዳለው ዋርካ ሥር አድርጎትአሉ፡፡ ወዲያው በፍጥነት ተሸክመው ከገዳሙ አስወጡኝ፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት ግን በድንጋጤ ዐይናቸውን በተበታተነው ልብስ ላይ አሳረፉ፤የሚያዩትን ነገር ማመን አቃታቸው፡፡ ነጭ ነጠላ ቀጨን አረንጎዴ፣ ቢጫ ፣ቀይ ጥለት ያለው በላዩ ላይ አባ ሳሙኤል ዘወገግ ተብሎ ሥዕል የተጠለፈበት ነጠላ አዩ፡፡

 

 ይህ ነጠላ ለምወደው ልጄ ለረድ የሰጠሁት ነበር፤ እንዴት እርሷ ዘንድ መጣ? ምሥጢሩ ምንድ ነው፡፡ መናንያኑ ነጠላውን አንስተው ለገዳሙ አበምኔት ሰጧቸው፡፡ ነጠላው በክብር አጣጥፈው ምሥጢሩ ምንድነው? የሚለውን ለመጠየቅ ከገዳሙ ግቢ ውጭ ወዳለሁት ወደ እኔ ዘንድ መጡ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከገዳሙ ሳልወጣ በፊት ቢሆን ምንኛ ድንቅ ነበር፡፡

 

+++++

   
 አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ቤተክርስቲያን

ይህ ሁሉ ታሪክ ከሆነ እነሆ ሰባት ዓመት ሆነው፡፡ ከዲያቢሎስ ውጊያ ነፃ ባልወጣም፤ በእግዚአብሔር ቸርነት በመላኩ በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት በመንፈሳዊ ሕይወት እየተጋሁኝ ነው፡፡ ይህን የተረዳው ዲያቢሎስ እኔን ከሃይማኖት ለማሳት በምግባር ለማቆሸሽ አሕዛብ ለማድረግ ብዙ ሮጧል፡፡ ወደ ገዳሙ መንገድ ስጀምር፣ የአባ ሳሙኤል ስም ስጠራ በሕመም ይመታኛል፤ ወደ ቦታውም እንዳልደርስ ይፈትነኛል፡፡


ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ተመልሼ ለመግባት እና እግዚአብሔር በፈቀደልኝ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ገና ደጅ እየጠናሁ ነው፡፡ በዚህ በብሥራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ዕምነቱን ተቀብቼ፣ መስቀሉን ተሳልሜ ሕመሜ ሲቀልልኝ ፊቴን ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት አዞራለሁ፡፡ በምሄድበት ቦታ ሁሉ በምስጢር በጥንቃቄስለ አሰቦት ገዳም ስለ ጻድቁ አባታችን አቡነ ሳሙኤልብዬ ስለምን እጁን የማይዘረጋልኝ፤ ምን ላድርግ የማይለኝ ሰው የለም፡፡ እንደዋዛ ከየሰዉ የሰበሰቡኩትን ገንዘብም ሆነ ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ በማጠራቀም ከረድ እንደተማርኩትም በማይታወቅ ሰው ለገዳሙ በሥውር እልካለሁ፡፡ 

 

በዐይኔ የተመለከትኩት በብርሃን የተከበበ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል አስደናቂ ክብር ተፈታታኜን ዲያብሎስን እንደ ጉም ተኖ እንዲጠፋ ማድረግ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም ያገለግል የነበረውን ረድን ተክቼ በስውር ገዳሙን አገልግዬ በረከት እንዳገኝ በሥጋዬ ላይ የመጣብኝ ሕመም፣ መከራ ሁሉ ለበጎ ሆነ፡፡ በህመሜ ምክንያት ገዳም ተመልሼ መግባት ስለማልችል፤ ሁሉም ለበጎ ሆኖ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ የኃጢአት መደምሰሻ ሥራ እንድሠራ ሌሎችም ምዕመናንን ከበረከቱ እንዳሳትፍ አደረገኝ፡፡ 

 

ከገዳም ከወጣሁበት ከዚያች ቀን በኋላ ከገዳሙ መናንያን አንድም ሰው አግኝቼ አላውቅም፡፡ የበለጠውን ክብር ለማግኘት ጊዜያዊውን ፈተና መከራ ሁሉ ለመቋቋም ጠዋት ማታ በጸሎት እማጸናለሁ፡፡ ምኞቴ በአባ ሳሙኤል ገዳም በድንግልና ሕይወት ተወስኖ እያገለገሉ መኖር ነው፡፡ በእውነት አምናለው ይህ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ ውብ ሆኖ ይከናወናል፡፡ አሁን ረድን ተክቼ የገዳሙ አገልጋይ ሆኜ ወደ ቅዱሳን ስፍራ እኔም እንዲሄድ ተሰወሩት ቅዱሳን ጋር በቅዱሳን ሀገር አብሬ መኖር እየናፈኩኝ በዚህ ከንቱ ዓለም እየኖርኩኝ ነው፡፡ 

 

ተፈጸመ


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

Image 1
Image 2
Image 3
Image 4

የሳምንቱ የመፅሐፍ ቂዱስ ጥቅስ

"በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም መንገድህን ያቀናልሃል።" ምሳሌ 3፡5-6

Video