የጥር ምሥጢር
የጥር ወር መጨረሻ ነው። የአዲስ አበባ ፀሐይ በኃይል ደምቃ ጭንቅላት ላይ ታቃጥላለች። ሙሽራው ረጅሙን የታክሲ ሰልፍ ተጋፍጦ፣ በላብ ተጠምቆና ራሰ በረሀው አናቱ በፀሐይ ግሏል፤ የባሰ የሚለበልበው ግን በውስጡ የያዘው ምስጢር ነው። ዛሬ ለባለቤቱ ሳያሳውቅ ወደ አንድ ብድር ተቋም በመሄድ የጋብቻቸውን አምስተኛ ዓመት ለማክበር ብድር ጠይቋል፡፡ ያሰበውን ያህል የብድር መጠን አለማግኘቱ ሳያንስ የሚሠጡት ገንዘብ አነስተኛ መሆኑ አበሳጭቶታል፡፡ ላለፉት ሦስት ወራት አከራዩን አዛውንት ለማምለጥ ሲል፣ እንደ ሌባ በመሽሎክለክ ማታ በጨለማ ነበር ወደ ቤት የሚገባው። ዛሬ ግን አልቀናውም፤ ብረት መዝጊያውን ሲያንኳኳ ከአዛውንቱ ጋር ፊትለፊት ተፋጠጡ።
"አጅሬ! ስትደበቅ ስትደበቅ አገኘሁህ አይደል? ሦስተኛ ወርህእኮ መጣ!" አሉት አዛውንቱ በደከመ ድምፃቸው። እርሱ ግን "አስተካክላለሁ" ብሎ በድንጋጤ አልፏቸው ወደ ጠባቡ ባለ አንድ መኝታ ክፍል ገባ።
ባለቤቱ የለበሰችው ያረጀ የቤት ልብስና የተዝረከረከው ጸጉሯ የኑሮውን ጫና ይናገራሉ። በእጇ የጨበጠችው ወረቀት ግን መብረቅ ሆነበት። ገና ጋብቻውን ከመመስረቱ አምስት ዓመት በፊት፣ ለሠርጉን ድል አድርጎ ለመደገስ እና ለማድመቂያ ብሎ ደብቆ የተበደረው 300 ሺህ ብር፣ ዛሬ ከነወለዱ
500 ሺህ ብር ሆኖ የክስ መጥሪያ መጣ።
ሚስት ይህን ዕዳ ፈጽሞ አታውቅም ነበር! ለልጃቸው ወተት
የሚገዛበት አጥተው፣ ሚስት ያላትን የወርቅ ሀብልና የጆሮ ጌጥ ሸጣ የዕለት ጉርስ ስትሸፍን፣ እርሱ ግን ከዕዳው ይልቅ ለ"ድንገቴ
ፈንጠዝያ" የሚሆን ብድር ፍለጋ ይባክናል። በአምስተኛው ዓመት የጋብቻ በዓላቸው ቀን፣ ለፍቅራቸው መታሰቢያ የሚሆን ስጦታ
ሳይሆን፣ ልብሳቸውን የያዙ ሻንጣዎች በሩ ላይ ተደርድረዋል።
አምስተኛው ዓመት በደስታ ሊከበር ሲገባው፣ በአንድ በኩል የአከራዩ ጩኸት፣ በሌላ በኩል የባንክ ክስ፣ መሀል ላይ ደግሞ የወተት ጥያቄ ይዞ የሚያለቅስ ሕፃን። ዛሬ በራቸው የተከፈተው ለመውጫ እንጂ ለደስታ አይመስልም። ገንዘብ እና ጋብቻ ምን እና ምን ናቸው:: ገንዘብን የማስተዳደር ብልሀት ለባለትዳሮች ወሳኝ ይሆን?
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ