ከ ምዕራፍ ሁለት የቀጠለ
ማራናታ - ጌታችን ሆይ ******* ምዕራፍ ሦስት
በኢትዮጵያ የነበራት የሁለት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን ቆይታ እንዳሰበችው መንፈሳዊ እርካታ ያገኘችበት አልነበረም። ጥንታውያኑንና ታሪካውያኑን የአክሱም ጽዮንን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የፋሲል ግንብን፣ የጣና ቂርቆስ ገዳምን እንዲሁም በቅርብ የሚገኘውን የደብረ ሊባኖስ ገዳም የመሳለም ጥልቅ ፍላጎት ቢኖራትም፣ በሀገሪቱ ባለው አስተማማኝ ያልሆነ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ልትሄድ አልቻለችም። ሁሉም ሰው እንዲህ ባለው ወቅት ረጅም መንገድ እንዳትጓዝ ስለመከራት፣ ፍላጎቷን ውጣ በቅርብ የሚገኙትን ብስራተ ገብርኤልን፣ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታን፣ ደብረ ምህረት ሚካኤልንና የእንጦጦ ኪዳነ ምህረትን ብቻ ተሳልማ ለመመለስ ተገደደች።
የሥራ ፈቃዷ የቀረው ሁለት ሳምንት ብቻ በመሆኑ፣ የቀሩትን ጥቂት ቀናት በዋሺንግተን ዲሲ ሆና ነገሮችን ለማስተካከል በማሰብ የአየር መንገድ ትኬቷን ቆረጠች፤ ሻንጣዋንም ሸክፋ ለጉዞ ተዘጋጀች። ሆኖም የሀገር ቤት ናፍቆቷ ባይወጣላትም፣ በአንጻሩ ደግሞ በዲሲ ያሉትን ባለቤቷንና ሁለቱን ልጆቿን በጽኑ ትናፍቅ ጀመር።
ከመሄዷ በፊት ፀጉሯን ለመሰራት በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ አንድ የሴቶች ፀጉር ቤት አመራች። የፀጉር ቤቱ ስትገባ በካስክ ውስጥ ገብተው መጽሔት ከሚገልጡ፣ ከስልካቸው ላይ ዓይናቸውን ሳይነቅሉ እርስ በእርስ ከሚያወሩ ሴቶች ወሬ ጋር ተቀላቀለች። በዚህ መሃል ሜሪ በሰፈሯ የምታውቃትን ልጅ ከአንዲት ጓደኛዋ ጋር ስታወራ አገኘቻት። የሀገር ቤት ቆይታዋ የሚያበቃበት ቀን በማብቃቱ ልትሰናበታት እያሰበች በውጭ ሳለች ያሰበችውን መንፈሳዊ ትርፍ ሳታገኝ እንደከሰረች ሰው ተሰምቷት ፣ በውስጥ ጭንቀት ተውጣ ሰላምታ ሰጥታ አጠገባቸው ቆመች። ሆኖም በሰፈሯ የምታውቃትን ልጅ ጋር አብራ ከነበረችው ሴት አፍ የሚወጣው ወሬ ድንገት የሜሪን ቀልብ በኃይል ሳበው።
ሴትዮዋ፣ "ለመጀመሪያ ጊዜ ሱባኤ የገባሁት ዓለማዊ ነገር ፍለጋ ነበር፤ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ዝግጅት አልነበረኝም። እንዲያውም ተመርቄ ሥራ ስላላገኘሁ ሥራ እንዳገኝ ብቻ ብዬ ነበር የገባሁት። ነገር ግን በሁለተኛው ሳምንት ያልጠበቅኩት ነገር ሆነ፤ እጅግ በርካታ ተአምራትን አየሁ..." እያለች ስታወራ፣ በሐሳብ ተውጣ የነበረችው ሜሪ ሳታስበው፣ "እሺ ከዛስ?" ብላ ወደ ጨዋታቸው ተቀላቀለች። የሰፈሯ ልጅም፣ "ይኸውልሽ፣ ከትናንትና ወዲያ ነው ከሩቅ ገዳም የመጣችው፤ የከረመችበትን እያወራችኝ ነው" በማለት ወሬውን እንድትቀጥል መንገድ አመቻቸችላት።
ተራኪያዋም በመቀጠል፣ "በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሱባኤ መግባት የፈለግኩት ሥጋዊ ነገር ለመጠየቅ ሳይሆን፣ መንፈሳዊ ሕይወቴን ለመገንባት ነበር። እግዚአብሔር አምላክ ኃጢአተኛ ሆኜ ሳለሁ በምሕረቱ ወደ እኔ ስለመጣ፣ ከዚያች ዕለት ጀምሮ ፍቅሩ እንደ ውሃ ይጠማኛል፣ እንደ እንጀራም ይርበኛል። 'ጌታዬ ሆይ! አገኝህ ይሆን?' ብዬ ስለምነው፣ እርሱም 'ልጄ' ብሎ ተገለጠልኝ" እያለች ያገኘችውን መንፈሳዊ በረከት ገለጸችላት። ሜሪ በልጅቷ መንፈሳዊ ልምድ በበጎ ቅናት ተሞላች። "ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣል?" እንዲሉ፣ ባልጠበቀችበትና ባልገመተችበት የፀጉር ቤት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወቷን የሚያነቃቃ ታላቅ ስንቅ አገኘች። "ፍቅሩ ዘወትር የሚያስደንቀኝ ችሩ አምላኬ የነፍሴ ጠባቂ የልቤን ናፍቆት፣ ጌታዬንና አምላኬን የት አገኘው ይሆን? በሱባኤ አገኘው ይሆን?" የሚለው አዲስ መንፈሳዊ ጥያቄ በልቧ ውስጥ ይነድድ ጀመር።
ምዕራፍ አራት ******
ከረጅም የጉዞ ሰዓታትና አታካች የአየር በረራ በኋላ በዋሽንግተን ዳላስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አየር ውስጥ ያለው ቅዝቃዜ ሜሪን መድረሷን በደስታ አበሰራት። የመውጫውን በር አልፋ ገና ብቅ ስትል፣ በጉጉት ሲጠብቋት የነበሩት ባለቤቷ ዶክተር ታዴዎስ፣ ሴት ልጇ ማራናታ እና ወንድ ልጇ ማርቆስ በፍቅርና ስሜት ተሞልተው እጆቻቸውን ዘርግተው ተቀበሏት። የሁለት ወራት ናፍቆት በዚያው አየር ማረፊያ ውስጥ በመተቃቀፍ በመሳሳም በደስታ ተሻረ።
ወደ ቤታቸው እንደገቡ ግን የጠበቃቸው ሌላ ትልቅ ደስታ ነበር፤ የአቀባበሉን ዜና የሰሙ ጎረቤቶቿና የሥራ ባልደረቦቿ በህብረት ተሰብስበው እቤቷ በቅድመ ዝግጅት ይጠብቋት ነበር። የደስታው ድባብ፣ የምሳ ግብዣው፣ የሚቆረሰው ኬክ፣ የእንግዶቹ ብዛትና ከየአቅጣጫው የሚጎርፈው "እንኳን ደህና መጣሽ!" የሚለው ሞቅ ያለ ሰላምታ እስከ ምሽት ድረስ ቤቱን በደስታ ሲያናውጠው አመሸ። ከሀገር ቤት ይዛው የመጣችው እጅ የሚያቆረጥም የዶሮ ወጥ በትኩስ እንጀራ ማዕድ ላይ ቀርቦ፣ ጨዋታውና ግብዣው ይበልጥ ደመቀ፤ የቤቱን መንፈስም ሙሉ በሙሉ በሀገር ቤት ጠረን ታወደ።
ምሽቱ ገፍቶ እንግዶች ሁሉ በየፊናቸው ሲሸኙና የሜሪ ቤተሰብ ብቻውን ሲቀር፣ በቤቱ ውስጥ ሌላ ዓይነት የረጋ ናፍቆት ሰፈነ። ባለቤቷና ልጆቿ ለሁለት ወራት ያህል ከጎናቸው ያልነበረችውን እመቤት ዓይን ዓይኗን እያዩ የቆይታዋን ወግ ይጠብቁ ጀመር። ዶክተር ታዴዎስ "ቆይታሽ እንዴት ነበር ሜሪ?" ሲል ላቀረበላት ጥያቄ፣ ሜሪ "ጥሩ ነበር" የሚል አጭርና የደከመ መልስ ብቻ ሰጠች። እናታቸው ዘርዘር አድርጋ እንድታወራላቸው የፈለገችው ማራናታ ግን "በስልክ ካወራነው ውጭ በአጠቃላይ ስታይው ምን ይመስል ነበር እማ?" እያለች ትወተውታት ጀመር። ሜሪ ግን ውይይቱን ወደ እነርሱ በመመለስ "እናንተስ እኔ በሌለሁበት ጊዜ እንዴት አሳለፋችሁት?" ስትል ጠየቀቻቸው።
ወዲያው ማርቆስ ጨዋታውን ተቀብሎ "እኛማ ከባድ ጊዜ አሳለፍን የከበደን ደግሞ ጠዋት በቁርስ ሰዓት እና ማታ በራት ሰዓት ነው" አለ። ሜሪ ከአፉ ተቀብላ "አሃ! ምግብ መስራትና እቃ ማጠብን ማለትህ ነው?" ስትለው፣ የቤቱ ሳሎን በደስታና በሳቅ ተሞላ። ማርቆስ እየሳቀ "እርሱን ማለቴ አይደለም እማማ! እርሱንማ እንደ ምንም ሁላችንም ተወጥተነዋል፤ ባይሆን የጎዳን እቃውን የት እንዳደረግሽው ስለማይታወቅ እቃ በመፈለግ ጊዜያችንን ማቃጠላችን ነበር" ሲል የነበረውን የቤት ውስጥ ውጣ ውረድ ገለጸላት።
በመቀጠል ማራናታ የልቧን ገጠመኝ ማውራት ጀመረች፤ "እማማ እውነት ነው፣ አንቺ የሌለሽ ጊዜ አባባ በጊዜ ይመጣል፣ ሁላችንም በጊዜ እንገባለን፤ ነገር ግን ቤቱ ጭር የሚል የሚደብር ነበር። ከዚያ አንድ ቀን አባባ ከሁላችንም ቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ጠበቀን። የሚያነበው ደግሞ ስለ እኔ ስም ስለ ማራናታ ነው፤ እርግጥ በእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ ነው ቃል በቃል የሚገኘው " አለች። ማራናታ ንግግሯን ቀጥላ ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16፥22 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ የጻፈውን እያነበበ አሳየኝ እንዲህ ይላል ፤ "The salutation of me Paul with mine own hand. If any man love not the Lord Jesus Christ, let him be Anathema Maranatha" በማለት መጽሐፍ ቅዱሱን ገልጣ አነበበችው።
ማራናታ በደስታ እየተሞላች፣ "ይህ በአራማይክ (Aramaic) ቋንቋ የተጻፈ ቃል ነው። የእኔ ስም ትርጉም ምን እንደሆነ እስከዛሬ ሳላውቀው፣ ለካ 'የጌታችን መገለጥ መናፈቅ' ወይም 'ጌታችን ሆይ ቶሎ ና' ማለት ነው!" አለች። ከዚህ ረጅም ማብራሪያዋ በኋላም "ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁላችንም በጋራ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብና የህብረት ጸሎት ማድረግ ጀመርን" ስትል ገለጸችላት።
ማርቆስም "እኔ በበኩሌ ማታ እስኪደርስ ይናፍቀኛል፤ በጉጉት ነው የምንጠብቀው፤ የሕብረት ጸሎት ልብን ይፈውሳል፣ ያሳርፋልም" ሲል ነገሩን አጸናው።
ዶክተር ታዴዎስ፣ " ስለ ልጃችን ማራናታ ስም ትርጉም ሳላስበው ብዙ ጥናት አደረኩኝ ይገርምሻል ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቱን በግሪክ ቋንቋ እየጻፈ ሳለ፣ ይህንን ቃል ግን ሳይተረጉም በነበረበት የአረማይክ ድምፅ ያስቀመጠበት ምክንያት በዚያ ዘመን በነበሩ ክርስቲያኖች ዘንድ ይህ ስም በጣም የታወቀ እና የተለመደ የእምነት መፈክር ስለነበረ ነው።
ደግሞም በአንደኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች የሚናገሩት ቋንቋ አረማይክ ነበር ። ክርስቲያኖቹ በሮም መንግሥት እና በወቅቱ በነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከባድ ስደትና መከራ ሲደርስባቸው በዚያ የተነሳ ቃሉን እርስ በርስ ለመበረታታትና ተስፋ ለመስጠት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ቃል ይጠቀሙበት ነበር። በአጠቃ ላይ “ማራናታ” የጥንት ክርስቲያኖች መከራን የሚያሸንፉበት፣ ተስፋቸውን በሰማያዊው መንግሥት ላይ የሚያደርጉበት እና የክርስቶስን መመለስ የሚናፍቁበት የጸሎትና የፍቅር መግለጫ ቃል ነበር" በማለት ንግግሩን ደመደመ፡፡
ሜሪ በልቧ 'ማራናታ' የሚለውን የልጇን ስም ትርጉም እንደ አዲስ እየመረመረችው፣ የጸሎቱ ህብረት በቤቷ ውስጥ በመፈጠሩ ጥልቅ እረፍት መንፈሳዊ ሀሴት ተሰማት። ምላሿን በጉጉት ለሚጠባበቁት ባለቤቷና ልጆቿ ቀና ብላ፣ "በአብዛኛው ያየሁት ለሥጋዊ ምቾት የሚሆን ነው፤ ይሄው በፊት ከነበረኝ ክብደት 5 ኪሎ ጨምሬ ወፍሬ ነው የመጣሁት እኔ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት ለነፍሴ እረፍት ነበር። ብቻ በመጨረሻው ሰዓት በፀጉር ቤት ያገኘኋት ልጅ የሱባኤን ጥቅም አስረዳችኝ፤ ያንን መንፈሳዊ ተስፋ ይዤ መጣሁ። አሁን ግን እጅግ ደክሞኛል፣ ሁላችንም እንተኛ" አለች። ሁላቸውም ወደ የክፍላቸው ሲያመሩ፣ የሜሪ ልብ በኢትዮጵያ ካጣችው መንፈሳዊ እርካታ ይልቅ፣ በራሷ ቤት ውስጥ በበቀለው የጸሎትና የመንፈሳዊ ትምህርት ፍሬ ተበረታታ።
ምዕራፍ አምስት ይቀጥላል *****************
ለሜሪ በሳምንቱ ቀናት መካከል ዕለተ ዓርብ ልዩ ቦታና ትርጉም አላት። ይህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አዳም ልጆች የኃጢአት መሠረዝ በቀራንዮ አደባባይ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ