ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

በእጅ የተያዘ የወርቅ መስቀል በብርሃን ያጌጡ መስቀሎች እና ምእመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የክብር መስቀሎች የቤተክርስቲያን በዓል አከባበር
አዲስ ገጽ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

ገጹን ይመልከቱ →

ወግ ፡-የቴሌቪዥን ወንጌላዊው ጂም ባከ

 

የቴሌቪዥን ወንጌላዊው ጂም ባከር (Jim Bakker)


 የገበያ መር ክርስትናና የስግብግብነት መጨረሻው ምን እንደሆነ ለማየት፣ በ1980ዎቹ አሜሪካን ያናወጠውን የቴሌቪዥን ወንጌላውያኑን የጂም ባከር (Jim Bakker) እና የባለቤቱ ታሚ ታሪክ ማየት በቂ ነው።

 በ1980ዎቹ ጂም ባከርና ባለቤቱ ታሚ PTL (Praise the Lord) የተባለ ግዙፍ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም ክርስትናን መስበክ ጀመሩ። በስብከታቸውና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞቻቸው የዓለምን ዘመናዊ ምቾት ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ለማዋሃድ አልመው ስለነበር፣ የብዙ ሚሊዮን አሜሪካውያንን ቀልብ ሳቡ፣ ብዙ ተከታዮችንም አፈሩ። ባከር በተሰጠው የመስበክ ጸጋ ተጠቅሞ የሳተላይት ቴሌቪዥኑን በማገልገል በቀን 24 ሰዓት ወደ ሚሊዮኖች አእምሮ መግባት ቻለ።

 የ PTL (Praise the Lord) ጣቢያ ባለቤቶች ባከርና ባለቤቱ «ወንጌልን ለዓለም ሁሉ እናስፋፋለን፣ የቀጥታ የወንጌል ሥርጭትም ለሁሉም ሰው መድረስ አለበት» ብለው ዘወትር የፕሮግራም ተከታዮቻቸውን ያሳምኑ ነበር።

 አንድ ቀን በካሜራ ፊት በመቅረብ «የቴሌቪዥን ጣቢያው በከፍተኛ የባጀት ዕጥረት ምክንያት የወንጌል ስርጭቱን ሊያቋርጥ ነው፤ ይህ ለብዙዎች ብርሃን የሚሆን የወንጌል አገልግሎት ሊጨልም ነው» በማለት በከፍተኛ ሐዘን እንባቸውን እያፈሰሱ ድምፃቸውን አሰሙ። በደራሲዎቹ የተዘጋጀ አሳዛኝ ተውኔት መሆኑን ግን ማንም አላወቀም ነበር።

 ድራማው ልብን የሚነካ ስለነበር፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው የተሰራውን ድራማ አምነው የወንጌል ሥርጭቱ እንዳይቋረጥ ወደ ኪሳቸው ዘልቀው የቻሉትን ዶላር አዘነቡላቸው። ባከር በፈጠረው የድራማ ድርሰት ጥሩ ገንዘብ ማግኘት በመቻሉ የልመና ዘዴውን ወደደው፤ እንደ ማር ጣፈጠው። ከጊዜያት በኋላ የልመና ስልቱን ረቂቅ ማድረግ ሰፊ የሥርጭት ጊዜ ሰጠው። 

የቴሌቪዥን ጣቢያው የወንጌል መድረክነቱ ተቀይሮ ወደ ንግድ ዓውድማነት ተለወጠ። የማሳመን ችሎታውና የተከታዮቹንም የልብ ትርታ ማወቁ ሥራውን ውጤታማ አደረገለት። ጥቂት የሚያስተውሉ ሰዎች ካልሆኑ በቀር፣ አብዛኛው ተከታይ ቀሳጢና ምንደኛ አገልጋይ መሆኑን አላወቀም። እንዲያውም በማር የተለወሰ መርዝ አድርጎ በወንጌል አገልግሎት ውስጥ በረቀቀ መንገድ ምድራዊውንና የሥጋ ሥራ የሆነውን ነገር ያቀርብ ነበር።

 መድረኩ ወደ ወንጌል የሚመራ መሆኑ ቀርቶ ወደ ገበያ የሚመራ ሆነ። ተከታዮቹም ተሰባኪያን መሆናቸው ቀርቶ ምርትና አገልግሎት የሚገዙ ሸማቾች ሆኑ። ሰባኪው ምድራዊ ምቾትና ሀብት ዋነኛ የክርስትና ሃይማኖት መገለጫ መሆኑን አበክሮ ያስተምራል። «በመካከላችን ችግረኛና ድሀ ሊኖር አይገባም፤ ሀብት ዋናው የመንፈሳዊነት ማረጋገጫ ነው» ብሎ ያምናል። «ክርስቲያኖች በሥጋዊ ሕይወታቸው በምቾትና በመዝናናት መኖር አለባቸው» ይላል። ለአማኞቹ «የክርስትና ሕይወት ተስፋንና ምቾትን እውን የምናደርግበት ልዩ ስጦታ ይዤላችሁ መጥቻለሁ» እርሱም «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ» (Heritage USA) ፕሮጀክት ነው ብሎ በቴሌቪዥን ጣቢያው አማካኝነት የምሥራቹን አወጀ።


 የቅንጦቱ ጥግ እና «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ»

 «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ» ፕሮጀክት በደቡብ ካሮላይና ግዛት፣ ፎርት ሚል (Fort Mill) በተባለ ስፍራ ከ2,300 ኤከር በላይ መሬት ላይ የክርስቲያናዊ የመዝናኛ ፓርክና ሆቴል ሆኖ መገንባት ተጀመረ። ግንባታው በጣም ዘመናዊና ልዩ በመሆኑ ሚሊዮናት ዶላሮችን ጠየቀ።

 ዘመናዊውን የክርስቲያኖች መዝናኛ ሥፍራ መገንቢያ ገንዘብ ለማግኘት በተሌቪዥን ጣቢያው ካሜራ ፊት በመቅረብ፦ «በዚህ ዘመናዊ ሆቴልና መዝናኛ ሥፍራ የሚገነባው ለእናንተ ለአማኞች ስለሆነ፣ የሕይወት ዘመን አጋር እንድትሆኑ በ1 ሺህ ዶላር ብቻ በመክፈል ተመዝገቡ። ለከፈላችሁበትም በዓመት ለ3 ቀናት በሆቴሉ ውስጥ በነፃ ማደርና መዝናናት ትችላላችሁ» ብሎ ቃል ገባላቸው።

 «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ» ፕሮጀክት በአማኞች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ግንባታው ተፋጠነ። ባለ 22 ፎቅ ሲሆን ሆቴሉ 500 የመኝታ ክፍሎች ነበሩት። በቴሌቪዥን ጣቢያው የሚተላለፈው ቅስቀሳ በጣም ብዙ ሰው የሕይወት ዘመን አጋር ለመሆን እንዲሻማ አደረገ። የሕይወት ዘመን አባል ለመሆን የተመዘገቡት አማኞች ቁጥር ሆቴሉ ሊያስተናግደው ከሚችለው የሰው መጠን በላይ ሆነ።

 በከፊል ግንባታው የተጠናቀቀው «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ» ዘመናዊ የሰው ሰራሽ የውኃ መዝናኛ ፓርክ፣ በኮረብታ ላይ በኢየሩሳሌም የመጨረሻው እራት የተዘጋጀበት አምሳል የሆነ «ዘ አፐር ሩም» ተብሎ የተሰየመ የጸሎት ሕንፃ፣ ቅንጡ መኝታ ቤት ያለው ሆቴል፣ እንዲሁም በቀን 24 ሰዓት በቀጥታ ስርጭት የሚሰራጨው የወቅቱ ድንቅ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ብዙ ሀብት የፈሰሰበት የ PTL (Praise the Lord) ቴሌቪዥን ስቱዲዮን ያካተተ ነበር።

 ጎብኚዎች በሕንፃው ውስጥ ሆነው ከቤት ውጭ በከተማ መንገድ ላይ እየተዟዟሩ እንደሆነ እንዲሰማቸው ኮርኒሱ ላይ አርቴፊሻል ሰማይና ደመና ተስሎበት፣ ተሳቢ አየር ማቀዝቀዣ ተገጠመለት። «ሄሪቴጅ ዩኤስኤ» ለመጎብኘት የሚፈለግ ውብና ድንቅ መናፈሻ ሆነ። በወቅቱም የባለቤቶቹና የመዝናኛ ስፍራው ስም በዓለም ሁሉ ናኘ። በአሜሪካ በየዓመቱ ብዙ ሰው ከሚጎበኛቸው የመዝናኛ ሥፍራዎች መካከል ሦስተኛው ለመሆንም ቻለ።

 ቅዱስ ወንጌልን ለማስፋፋት በሰበሰበው ገንዘብ «የክርስትና ኑሮ የቅንጡነትና የዘመናዊነት ሕይወት ነው» በማለት ተከታዮቹም ሆኑ ራሱ በቅንጡ ሕይወት ዋኙ። የዕለት ተዕለት ኑሮውን በግል ጀት አውሮፕላን በመመላለስ ያሳልፋል። የሚኖርበት ዘመናዊ ቪላ መጸዳጃ ቤቱ ሳይቀር ከወርቅ የተሰራ ነበር። የቤት ውስጥ ቁሳቁሱና መመገቢያ ሳህኑ የወርቅ ሆነ። «እንዲህ ዓይነት የቅንጡ ሕይወት ለእኔ የሚገባኝ ነው፤ የሰማያዊው ንጉሥ ልጅ በመሆኔ ይገባኛል» ይላል። በተለይ የእርሱ ከሌሎች ሁሉ የተለየ፣ ለእግዚአብሔር የቀረበ አገልጋይ ስለሆነ የተሰጠው የበረከት ሕይወት እንደሆነ ያሳምናል በዙሪያው የሚሰበሰቡት ሁሉ እርሱ ከሚሰጣቸው ትርፍራፊ የሚቋደሱ ስለነበሩ፣ አንዳቸውም ለመቃወምም ሆነ ለመገሰጽ ድፍረት አልነበራቸውም። ተከታዮቹ በእግዚአብሔር በማመኑና በጽድቅ ሥራው ያገኘው በረከት አድርገው ስለቆጠሩት፣ እርሱን ከመጠራጠርና ከመንቀፍ ተቆጠቡ።




 ፎርብስ (Forbes) መጽሔት እንደዘገበው፣ ባከርና ባለቤቱ አማኞች ለወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ብለው የሰጡትን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው፣ ለዛውም እጅግ አላስፈላጊ ቅንጦት ለሆነ ነገር አውለውት ነበር። ከወርቅ የተሰሩ የሽንት ቤት ዕቃዎች፣ የቅንጦት መኪኖች፣ በርካታ ቪላዎች እና የራሱ አየር ማቀዝቀዣ ያለው የውሻ ቤት ሳይቀር አሰርተው እንደነበር በምርመራ ዘገባው ገልጿል።

 PTL ሚኒስትሪ እና የቲቪ ስርጭቱ በሚሰጠው ስብከትና መንፈሳዊ አገልግሎት፣ እራሱን መስበኪያና ማስተዋወቂያ ሰብዕናውን መገንቢያ አደረገው። «እዩኝ እዩኝ» የሚል የትዕቢትና የቁሳቁስ ፍላጎት በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የጨመረው ባከር፣ በብዙ ግራና ቀኛቸውን ለማይመለከቱ፣ በቴሌቪዥን መስኮት የሚታየው ነገር እውነት እንደሆነ በሚያምኑ ተከታዮቹ ዘንድ ማንም የማይነቀንቀው ጽኑ አለት አድርጎ ራሱን ቆጠረ።

 አማኞች የ PTL ሚኒስትሪና የቲቪ ስርጭቱ እንዲስፋፋና እንዲጠነክር ገንዘባቸውን ይሰጣሉ። ከአማኞች በሚሰበሰበው ገንዘብ ግን ለወንጌል አገልግሎት ሳይሆን፣ ለባለቤቱ ያልተገባ የቅንጡ ሕይወት፣ ለቴሌቪዥን ጣቢያው እና ስለ እርሱ መልካም ዜናን አብዝተው ለሚያወሩ ድጋፍ ለሚያደርጉ ረዳቶቹ አበል መክፈያ ያውለው ነበር።

 አንድ ጀንበር ግን ለጂም ባከር ጠለቀችበት። በምቾትና በቅንጦት የሚኖረው የወንጌል አገልጋይ ጂም ባከር፣ የ21 ዓመቷ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረችው ጄሲካ ሃን (Jessica Hahn) ጋር የዘመናት ትዳር አጋሩን በቤት አስቀምጦ በፍሎሪዳ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ የፆታ ግንኙነት ፈጸመ።

 ጄሲካ ሃን «አደንዛዥ ዕፅ ተሰጥቶኝ ነው የተደፈርኩት» ስትል፣ ባከር ደግሞ «ግንኙነታችን በስምምነት የተደረገ ነበር» በማለት መከራከር ጀመሩ። ክስተቱ ለሕዝብ ይፋ ከወጣ የ PTL ሚኒስትሪ እና የቲቪ ስርጭቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጋ፣ የገንዘብ ምንጫቸውም እንደሚደርቅ ያወቁት ረዳቶቹ፣ ምስጢሩን ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

 በ1985 እ.ኤ.አ. የጄሲካ ሃንን አፍ ለማዘጋት በሚል፣ በጠበቃዋ በኩል በተደረገ እልህ አስጨራሽ ድርድር በሕግ እንዳትከሳቸው «የዝምታ ክፍያ» የሚሆን 279,000 ዶላር ለመክፈል ተስማሙ። ክፍያውም ለወንጌል አገልግሎት ተብሎ በቴሌቪዥን ጣቢያው ከተሰበሰበው የአስራት ገንዘብ ከቤተ ክርስቲያኑ ካዝና ተወስዶ እንዲፈጸም ተደረገ።


ምስጢሩ ለጥቂት ዓመታት ተሸፍኖ ቢቆይም፣ በ1987 እ.ኤ.አ. ዘ ሻርሎት ኦብዘርቨር (The Charlotte Observer) የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ በሰራው የምርመራ ዘገባ የዝምታ ክፍያው መፈጸሙን አጋለጠ። ጋዜጣው የቤተ ክርስቲያኑ ገንዘብ የፆታ ቅሌትን ለመሸፈን መዋሉን ይፋ ሲያደርግ፣ በመላው አሜሪካ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ታላቅ ድንጋጤና ቁጣ ተፈጠረ።

"የሥነ-ምግባር ቅሌቱ ይፋ መሆንን ተከተሎ፣ የድርጅቱ የገንዘብ ምንጭ በአንድ ጀንበር ተዘጋ። የመጀመሪያው ስህተት ሌሎቹን ወልዶ ከአማኞች የሚሰበሰበው ገንዘብ ወዴት እንደሚገባ የመመርመር ጥያቄን አነሳ።"

 ይህ የሞራል ቅሌት የፍርሃት በር በመክፈቱ፣ የፌደራል መርማሪዎች (FBI) የ PTLን የፋይናንስ መዝገቦች በጥልቀት መመርመር ጀመሩ። ባከር «ለሕይወት ዘመን አባልነት» በሚል ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከደጋፊዎቹ ሰብስቦ ለግል ጥቅሙ ማዋሉን የሚያጋልጥ የፋይናንስ ሪፖርት ሲወጣ፣ ግለሰቡም ሆነ ተቋሙ ከላይ እስከ ታች በፍርሃት ተናወጡ።

 ቢቢሲ (BBC) የጂም ባከርን የፍርድ ቤት ውሎ እና የቴሌቪዥን ወንጌላውያንን ስውር የንግድ ሴራ በዝርዝር የዘገበ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1989 የፌደራል ፍርድ ቤት በ24 የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ ብሎ በ45 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ወሰነበት (በኋላ በይግባኝ ወደ 8 ዓመት ዝቅ ተደርጓል)። ጂም ባከር በአማኞች ዘንድ የነበረው ግርማ ሞገስ በቅጽበት ወደ አቧራነት ተቀየረ። ገንዘብን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን «የት አደረስከው?» ብሎ የሚጠይቅ፣ የሚያከብር ብቻ ሳይሆን የሚያዋርድ አማኝ መኖሩን ካለፈ በኋላ ተረዳ።

 አንድ ወቅት አርቴፊሻል ሰማይ ተስሎበት በጎብኚዎች የተጨናነቀው የንግድ ማዕከል ባዶውን ቀረ። ጣሪያው ተሰነጣጥቆ ውኃ ያፈስ ጀመር፤ የቅንጦት ምንጣፎቹ በመሻገት ተበላሹ፤ የውኃ መዝናኛ ገንዳዎቹ በበሰበሰ አረንጓዴ ውኃ ተሞልተው የእንቁራሪት መራቢያ ሆኑ። ተፈጥሮ እንኳን ሳይቀር በመተባበር የቀረውን ፍርስራሽ አካባቢውን በሙሉ «ሃሪኬን ሁጎ» (Hurricane Hugo) በተባለው አውሎ ነፋስ ሙሉ በሙሉ አወደመው። ቦታው ጥበቃ በማጣቱ፣ ለሌቦችና የመጥፎ መንፈስ መሸሸጊያ ሆኖ ቆየ። በወቅቱ አካባቢውን የጎበኘ ሰው በዓለም ታሪክ ከታዩ አስፈሪ «የመንፈስ ከተሞች» (Ghost Towns) አንዱ እንደሆነ ይናገራል።

 ጂም ባከር ከአማኞች በሰበሰበው ገንዘብ ሊገነባው አስቦ ሳይጠናቀቅ የቀረው ባለ 21 ፎቅ ሕንፃ የብረት አፅም፣ የስግብግብነትና የውድቀት ታላቅ ማስታወሻ ሆኖ ለብዙ ማይሎች ይታያል። የጂም ባከር ታሪክ በክርስትናና በሃይማኖት ታሪክ ውስጥ «እዩኝ እዩኝ» የሚል የትዕቢትና የቁሳቁስ ፍላጎት በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ሲገባ የሚያስከትለውን ውድቀት ያሳየ ታላቅ የታሪክ ማስታወሻ ሆኖ ይኖራል።



 የቴሌቪዥን ወንጌላውያን (Televangelists) በሚዲያና በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተአማኒነት በከፍተኛ ሁኔታ ወደቀ። ዘ ኢኮኖሚስት (The Economist) እንደተነተነው፣ የጂም ባከር ታሪክ «ያልተገደበ የገንዘብ ፍላጎት ከሃይማኖታዊ ስልጣንና ከሕግ ቁጥጥር እጦት ጋር ሲደመር የሚፈጠረውን አደገኛ ውድቀት» የሚያሳይ የታሪክ ምሳሌ ነው።

ለአንባቢያን የቀረበ የውይይት ጥያቄ፦

 "የጂም ባከር ታሪክ እንደሚያሳየው፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ከምድራዊ ንግድና ከሀብት ማሳደድ ጋር ሲቀላቀል የሚከተለው ውድቀት የጎላ ነው። በእርስዎ እይታ—ዛሬ ባለንበት ዘመን አገልጋዮች አገልግሎታቸውን ወደ ንግድ ዓውድማነት ከመለወጥ እንዴት መጠበቅ ይችላሉ? ምዕመናንስ በስሜታዊ ድራማ ሳይነዱ በመንፈሳዊ ማስተዋል እና በተጠያቂነት የመጠየቅ ኃላፊነታቸውን እንዴት ሊወጡ ይገባል? እርሶዎስ ምን ያስባሉ? አስተያየትዎን በአስተያየት መስጫ ሳጥን ውስጥ ይጻፉልን።"

 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 1
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 2
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 3
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 4

የሳምንቱ የመፅሐፍ ቂዱስ ጥቅስ

"በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም መንገድህን ያቀናልሃል።" ምሳሌ 3፡5-6

Video