ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

በእጅ የተያዘ የወርቅ መስቀል በብርሃን ያጌጡ መስቀሎች እና ምእመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የክብር መስቀሎች የቤተክርስቲያን በዓል አከባበር
አዲስ ገጽ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

ገጹን ይመልከቱ →

ወግ ፡- ገበያ መር ክርስትና

 ገበያ መር ክርስትና

ምዕራፍ 1

በ ያዕቆብ ሰንደቁ

በዕለታዊ ውሎአችን ውስጥ «ገበያ መር ኢኮኖሚ» የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ለጆሮአችን እንግዳ አይደለም። በገበያ ሕግጋት የሚመራ የገንዘብና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ይህ ቃል፣ ዛሬ በሌላ ገጽታው አደባባይ ወጥቷል። ይኸውም «ገበያ መር ክርስቲያናዊ ሕይወት» ወይም የወንጌል አገልግሎት ወደ ሸቀጥነት የመለወጡ አደገኛ አዝማሚያ ነው። 

 

ገበያ መር ሥርዓት በሚታወቁም ሆነ ባልታወቁ የኃይል አዝማቾች የሚዘወር፣ ማስታወቂያዎችና የተጠቃሚዎች ፍላጎት በሚወስኑት መርህ የሚመራ፣ ተጠቃሚው ሊደሰትበት ወይም ሊጎዳበት የሚችልበት አሠራር ነው። ታዲያ ይህ የምድራዊ ገበያ ሕግ ወደ ቅዱሱ የወንጌል መድረክ ሰርጎ ሲገባ ምን ዓይነት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ውድቀትን ያስከትላል?


ወንጌል በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሲሰበክ ዓልጫው ዓለም ጣፈጠ፤ ጨለማውም በክርስቶስ ብርሃን ተዋጠ። በዘመነ ሰማዕታት የሮም ገዢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የከፈቱት መከራና ፈተና የሻማውን ብርሃን ማጥፋት አልቻለም፤ ይልቁንም ይበልጥ እንዲደመቅ አደረገው እንጂ።

 

ክርስትና በዓለም ላይ ታላቅ ተፅዕኖ በፈጠረበት በዚያ ዘመን፣ ነገሥታትና ልዑላን የሞቀ ቤተ መንግሥታቸውን ትተው፣ ፈላስፎችም ዓለምን ንቀው የመነኮሱበት የቅድስና ዘመን ነበር። በ6ኛው ክፍለ ዘመን ዓለምን ንቀው የመነኮሱ አባቶች በመብዛታቸው የመነኮሳት ከተማ እስከ መመሥረት ደርሰው እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። በኋላም መነኮሳቱ ወደ በረሃ በመሄድ በጽሞናና በተጋድሎ መኖር ጀመሩ።


"ክርስትና በተጓዘበት ዘመን ሁሉ ዓለምን እያሸነፈና ወደ መልካም መንገድ እየመራ እንጂ፣ በዓለም ተሸንፎና በገበያ ሕግ ተስቦ ሲጎተት አልነበረም።"

 

በዚያ ዘመን የነበሩ አገልጋዮች እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበረ። ጸልየው ጸሎታቸው ይሰማል፤ ጽፈው፣ ደጉሰውና ሰብከው ሰዎችን ወደ ንሥሐ ያደርሳሉ። ቅድስናቸው የተሰወረ ታላቅ  ቢሆንም፣ ትሕትናቸው ግን የሰማይ ጥግ የደረሰ ነበር። አገልግሎታቸው ራሳቸውን ሳይሆን፣ በቀራንዮ አደባባይ ለሰው ልጅ ቤዛ ሆኖ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማሳየት ብቻ ነበር።

 

ከሐዋርያት አባቶቻችን ቃሉን ሰምተው፣ የእጁን ተአምራት ተመልክተው፣ በቃል አንብበውና በመጽሐፍ ጽፈው ወደ ትውልድ አስተላለፉ። ከሐዋርያት በኋላ የተነሱት ሐዋርያነ አበውም የአባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው፣ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ የተለኮሰውን የወንጌል ችቦ ለቀጣዩ ትውልድ አስረከቡ።


በዚህ ባለንበት ዘመን ግን የወንጌል ገበያ በሐዋርያት ቀኖና መመራቱን ትቶ በገበያ ሕግ መዘወር ጀምሯል። «ሂዱና ዓለምን ሁሉ ወንጌልን ስበኩ» የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ ተረስቶ፣ መንፈሳዊ ሕይወት በአቅርቦትና ፍላጎት፣ በትርፍና ኪሳራ እንዲሁም በግል ምቾት ስሌት እንዲመራ ተደረገ። ለዚህ ነው ርዕሳችንን «ገበያ መር ክርስትና» ያልነው።

 

ይህ አስተሳሰብ ወደ ክርስቲያናዊው ዓለም ሰርጎ በመግባት የጀመረው በተለይ እንደ አውሮፓና አሜሪካ ባሉ በሰለጠኑና በገበያ መር ኢኮኖሚ በሚዘወሩ አገራት ነው። አስተሳሰቡም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአማኞች አኗኗርና በመንፈሳዊ ሕይወት እሴቶች ላይ ጥልቅና ስውር ተፅዕኖዎችን አሳድሯል።

 

የችግሩ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው የአገልጋዮቿ መንፈሳዊ ተልዕኳቸውን መሳት ነው። አገልጋዮች በአገልግሎት በረከት ማገልገል ቀርቶ፣ ዋና ጭንቀታቸው ራሳቸውን ለገበያው ማቅረብና በተከታዮቻቸው ዘንድ የሚኖራቸውን ቦታ ማጠናከር ሆኗል። ወንጌልን ለመስበክ የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ዘንድ እንዲያድር ከመጨነቅ ይልቅ፣ የሚያሳስባቸው በተሰባኪው ዘንድ የሚኖራቸው ዝናና ጥቅማጥቅም ነው።

 

 የብሉይ ኪዳን መጨረሻና የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የሆነውን፣ የጽድቅና የወንጌል መንገድ ጠራጊ የነበረውን የዘካሪያስና የኤልሳቤጥ ልጅ የመጥምቁ ዮሐንስን ሕይወት እንመልከት።

 

በይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው አገር ሁሉ በስብከቱ ታዋቂ፣ በአጥማቂነቱም ፈዋሽ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፤ ወገቡ በጠፍር የሚታጠቅ፣ የግመል ጠጉር የሚለብስ፣ ምግቡም አንበጣና የበረሃ ማር የነበረ ባሕታዊ ነው። ህዝቡም ሁሉ በልባቸው «ይህ ክርስቶስ ይሆንን?» ብለው ሲያስቡ፣ ዮሐንስ መልሶ እንዲህ አለ፦

 

"እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።" (ሉቃስ 3:16)

 

ርዕሰ ሰባኪያን መጥምቁ ዮሐንስ የመጀመሪያው የሐዲስ ኪዳን ሰባኪ በመሆን የስብከት ዘዴን ያሳየ የአገልግሎት ፋና ወጊ ነው። የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ራሱን በትሕትና ያሳነሰ፣ ከእርሱ በኋላ የሚመጣውን ክርስቶስን ግን አጉልቶ ያሳየ ነው። አበክሮ የተናገረው ከእርሱ የሚበረታውን ጌታ ለማስተዋወቅ ሲሆን፣ የተሰባኪያኑንም ልብ የሚያውቅ መንፈሳዊ ሰው ከቅርብም ከሩቅም መጥተው ለተጠመቁት ተከታዮቹ ገና ሲመጣ የሚያዩትን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና አስተዋወቀ፡፡ የዓመት ጉርስ፣ የሚለበስ ጨርቅ፣ የሚበላ፣ የሚጠጣ ወይም የሚያስክርና የማያሰክር ነገር የማይፈልግ ባሕታዊ ቅዱስ ዮሐንስ ተጠማዊዎቹን ከጌታው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አስተዋወቀ።

 

በመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን የተሰበከው ወንጌል ዛሬም ይሰበካል። ዛሬም የሚመጣውን ክርስቶስ የሚያስተዋውቁ ሰባኪያን አሉ። ጥያቄው «አገልጋዮች የመጥምቁ ዮሐንስን አሰረ ፍኖት ተከትለዋል ወይ?» የሚለው ነው። አሁን አሁን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን የተሰቀለውን መድኃኒታችንን ማሳየት ቀርቶ፣ ራሳቸውን በምዕመናን ልብ ሰሌዳ ላይ መጻፍ እንደ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ማሳየት የሚፈልጉ አገልጋዮችን የምናይበት ዘመን ሆኗል።

 

የስብከቱ ዓውደ ምህረት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በትሕትና «የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም» የሚል አገልግሎት በብዛት የሚታዩበት መሆኑ ቀርቶ፣ ቤተ ክርስቲያንን ማዕከል ከማድረግ የወጣ፣ ግለሰብን ከፍ ያደረገ ራስን ማስተዋወቂያ መድረክ ሆኗል።


"ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።" (1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ቢመክርም፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ባሕታዊ መሆን ባይሳካላቸው እንኳ አገልጋዮች ሆዳቸው አምላካቸው፣ ክብራቸውም በነውራቸው መሆን የለበትም። አንዱ አገልጋይ ከአንዱ የሚበልጥበትንና ተለይቶ የሚታወቅበትን መንገድ በመጨነቃቸው ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ አስተውለናል። በዚያው መጠን የአገልግሎት የገበያውን ፉክክር ለማሸነፍ በሚደረግ ጥረት፣ እጅግ የከፋና ከሃይማኖተኛ ሰው ወደማይጠበቅ ዝቅተኛ ተግባር ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ።

 

የትሕትናና ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስን ትተው አገልጋዮች ለምንድነው ከፍተኛ የታዋቂነት ጥማት የሚሰማቸው ? የሚለውን ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። በተለይ ደግሞ «መጽሐፍት ያውቃሉ፣ ወንጌል ይሰብካሉ» ተብለው የቤተ ክርስቲያን ቱርጁማን (ተረጓሚ) ሆነው በዓውደ ምሕረት ላይ የሚቆሙ ሰዎች በዚህ ያህል መጠን ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ለምን ደከሙ ? የግላቸውን ጎዳና ጎድጎዳ በየመንገዱ ለማሳየት ለምን አብዝተው ተጋደሉ ? የሚለውን መረዳታችን፣ በጭፍን «ሆ» ብሎ ከማድነቅ ወይም ክፉኛ ከመተቸት ይታደገናል።

 

ምዕራፍ 2

የሸማችነት (ኮንሲዩመሪዝም) ሥነ-ልቦና እና ወንጌል

 

በአሁኑ ዘመን የሃይማኖት አገልግሎት እንደ ጥሩ የሥጋዊ መጠቀሚያ መንገድ ተቆጥሯል። ሰዎች ሃይማኖትንና እምነትን በገበያ እንደሚለወጥ፣ እንደሚገዛና እንደሚሸጥ ሸቀጥ መቁጠራቸውም ተጨማሪው ምክንያት ሊሆን ይችላል። ዛሬ መንፈሳዊ አገልግሎት ዋናው የሥጋዊ ጥቅም ማግኛ ብሎም ሀብት ማጋበሻና መበልጸጊያ መንገድ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።

 

ጥቂት የማይባሉ አገልጋዮች ወደ አገልግሎት የሚሠማሩት «እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለመስዋዕትነት» ሳይሆን፣ «የእኔን ፍላጎት፣ ስሜትና ምቾት የትኛው ያሟላልኛል?» በሚል የሸማችነት ሥነ-ልቦና ሆኗል። የሚያጓጓችው እና የሚያተጋቸው ከአገልግሎቱ ጀርባ ያለው ሥጋዊ ክብርና ጥቅም ነው፡፡

 

ሌላው ቢቀር በዓለም የገበያ ሕግ «ደንበኛ ሁልጊዜ ትክክል ነው» እንደሚባለው ሁሉ፣ ለአገልጋዮች በገንዘብ የሚደግፉ፣ የትራንስፖርት አበላቸውንና የዓመት ቀለባቸውን የሚሰፍሩላቸውን ባለሀብቶች በከባድ ኃጢአት ውስጥ እንኳን ቢገቡ ለመገሰጽ ድፍረት የላቸውም።


"ኮንሲዩመሪዝም «ሰው ማንነቱ የሚለካው ባለውና በሚበላው/በሚለብሰው ቁሳቁስ መጠን ነው» የሚል እምነት አለው። ይህ አስተሳሰብ ከክርስትና ጋር ሲደባለቅ  በወንጌል መበልጸግ  ይወልዳል።"

ክርስቲያናዊ ሕይወት በዓለማዊ ቁስን በማግኘትና በማጣት እንዲወሰን ያደርጋል። ሰው ባለሀብት ከሆነ «ኃጢአት የለበትም» ወደሚል ስህተት እስከ መድረስ ያደርሳል።

 

ክርስትና በገበያ መር ሲመራ፣ በወንጌል የተጻፈው «ዓለሙም ንብረቱም ሁሉም ያልፋል» የሚለው ተዘንግቶ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር የሰውን የቁሳቁስና የፍጆታ ፍላጎቶች የሚያሟላ «የፍላጎት ማሽን» ተደርጎ ይወሰዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማዕከል የሆኑት መስቀል፣ ራስን መካድ፣ ትሕትና እና የዘላለም ሕይወት፤ ቦታቸውን ለቁሳዊ ስኬት፣ ለሀብት ማከማቸትና ለዚህ ዓለም ምቾት አሳልፈው እንዲሰጡ ያደርጋል።

 

ክርስትና የፍላጎት ማሟያ ሳይሆን ክርስቶስን የመከተልና ራስን የማቅረብ ሕይወት መሆኑን በመዘንጋታቸው ነው በዚህ መርህ የሚመሩ አገልጋዮች ከትሕትናቸው ይልቅ ራሳቸውን ሲኮፍሱ የምንመለከተው። ለሰው ከማዘንና ለችግረኞች ከመድረስ ይልቅ አባካኝነትንና ዓለማዊነትን በአደባባይ ተግባራቸው ያሳያሉ፡፡ ምዕመናንን «ዓለምን ናቁ፣ ዓለሙም ንብረቱም ያልፋል» ብለው ቢሰብኩም፣ እነርሱ ግን ለዚህ ዓለም ዓይን አምሮትና ለሥጋ ፍላጎት ሲጨነቁና ሲብከነከኑ ይስተዋላሉ።

 

ገበያ መር ስንል በእውነትና በጽድቅ የሚመራ ክርስትና ሳይሆን፣ በአስተውሎትና «እንዴት? ለምን?» በሚል ሳይሆን በብዙ ሕዝብ ጩኸትና ሆሆይታ የሚመራ ክርስቲያን፣ እንዲሁም በድጋፍ ሰጪ የሚመራ አገልጋይ ይፈጥራል ማለታችን ነው። አገልጋዮች እግዚአብሔር የሰጠንን ሀብት ለድሆች ማካፈልና ለወንጌል ማስፋፊያ መጠቀም ሲገባን፣ ለግል ያልተገደበ ፍጆታና ለቁሳቁስ ውድድር እንድናውለው ያደርገናል።

 

ምዕራፍ 3

የሥነ-ልቦና እይታ፡ «መንፈሳዊ ናርሲሲዝም» እና የገጽታ ግንባታ

 

ለዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ዝግጅት ያናገርኩት የሥነ-ልቦና ባለሙያ እንደገለጸልኝ፤ መንፈሳዊ አገልጋዮች ወይም የሃይማኖት መሪዎች በሰው ዘንድ ለመደነቅ፣ ለመከበር ወይም «ልዩ መንፈሳዊነት አለኝ» ለማለት ሲሉ የግል ሕይወታቸውን አጋኖ ወይም በሐሰት አድምቆ ማቅረብ እና ለዚህም ትልቅ መሥዋዕትነት ሲከፍሉ መታየት በሥነ-ልቦና (Psychology) እና በማኅበራዊ ሥነ-ልቦና (Social Psychology) ዘንድ በሰፊው የተጠናና የታወቀ ባህሪ ነው።

 

"በመንፈሳዊነት ሽፋን ውስጥ የሚታየው «የአድናቆትና የሐሰት ገጽታ ጥማት» መንፈሳዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በጥልቅ የውስጥ ስነ-ልቦናዊ ቁስል፣ በባዶነት ስሜትና በናርሲሲዝም የሚመራ ችግር ነው።"

 

እውነተኛ መንፈሳዊነትና የበሰለ ሥነ-ልቦና የሚጀምረው ከትሕትና፣ ከእውነተኛነት እና ራሱን እንዳለ አምኖ ከመቀበል ነው፤ ምክንያቱም በሐሰትና በአጋኖ የተገነባ አድናቆት መጨረሻው ውድቀትና የውስጥ ሰላም ማጣት ነው።

 

አንድ አገልጋይ የሰዎችን አድናቆት ለማግኘት ሲል ራሱን በሐሰት ወይም በአጋኖ የሚያቀርብበት የችግሩ ሥነ-ልቦናዊ መንስኤዎች በርካታ እንደሆኑ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ያብራራል።

 

1.    ናርሲሲዝም እና የተጋነነ የራስ ግምት (Narcissism & Spiritual Narcissism)

 ናርሲሲዝም ማለት ሰዎች ከልክ ያለፈ የሰው አድናቆት፣ ትኩረትና ሙገሳ የመፈለግ ባህሪ ነው። ይበልጥኑ «መንፈሳዊ ናርሲሲዝም» (Spiritual Narcissism) ደግሞ፣ ግለሰቡ «ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት አለኝ»፣ «ከሌሎች የተለየሁ ቅዱስ ነኝ» ወይም «ትልቅ ዋጋ የከፈልኩ አገልጋይ ነኝ» በማለት ራሱን ከፍ አድርጎ በማቅረብ የሰዎችን አምልኮትና አድናቆት የመጠማት ባህሪ ነው።


2. የውስጥ የታችኝነት ስሜት እና ዝቅተኛ የራስ ግምት (Low Self-Esteem & Insecurity)

 በውጫዊ ማንነታቸው በራስ መተማመን የሌላቸው ወይም የውስጥ ባዶነት (Emptiness) የሚሰማቸው ሰዎች፣ ያንን ባዶነት በሰዎች አድናቆት ለመሙላት ይሞክራሉ። ዘወትር በሕይወታቸው ውስጥ ያለውን ጉድለት እያሰቡ ይጨነቃሉ። ያንን ባዶነታቸውን እየሞሉት እንኳን «እውነተኛ ማንነቴን ቢያውቁት አይወዱኝም» የሚል ስጋት ስላላቸው፣ ሰው እንዲያደንቃቸውና እንዲቀበላቸው ሲሉ የፈጠራ ወይም የተጋነነ የሕይወት ታሪክ ይፈጥራሉ።

 

ከዚህ በፊት ሌሎች ሰዎች የፈጸሟቸውንና እነርሱ የመጀመሪያ ያልሆኑበትን ነገር ልዩ ድንቅ አድርገው ያወራሉ የተማሩ እንደሆነ የእነርሱ ትምህርት የተለየ፣ ያጩ እንደሆነ የእነርሱ እጮኛ የተለየች፣ ያገቡ እንደሆነ የእነርሱ ሠርግ የተለየ አድርገው ይቆጥራሉ። የውስጥ ባዶነታቸውን የሞሉ እንደሆነም በጣም እንዲታወቅላቸው ይጨነቃሉ ይጣጣራሉ፡፡

 

2.  የገጽታ ግንባታ እና የማስመሰል ሥነ-ልቦና (Impression Management)

 በማኅበራዊ ሥነ-ልቦና Impression Management የሚባል ጽንሰ-ሐሳብ አለ። ሰዎች በሌሎች ዘንድ የሚኖራቸውን ስም እና ገጽታ ለመቅረጽ የሚያደርጉት ጥረት ማለት ነው። ይህም በአገልጋዮች ዘንድ የሚታይ የገጽታ ግንባታና የማስመሰል ሥነ-ልቦና ነው። በተለይ የሚያገለግሉና በሰው ዘንድ የሚታወቁ ሰዎች «ደካማ ወይም ተራ ሰው ሆኜ ከተገኘሁ ተሰሚነቴና ተፅዕኖዬ ይቀንሳል» የሚል ፍርሃት ስለሚያድርባቸው፣ ከተራው ሕዝብ በላይ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ።


4. የማኅበራዊ ጥቅም እና ዝና

 በዛሬ ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎት በብዙ ጉርሻና ጥቅማጥቅም የተሞላ በመሆኑ፣ የሰው አድናቆት ብቻ ሳይሆን አድናቆቱ የሚያስከትለው ዝና እና ቁሳዊ ጥቅም ይፈለጋል። ግለሰቡ «በጸሎቴ በተጋድሎዬ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ» ብሎ ሲናገር ተከታዮች ይታዘዙታል፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጉለታል፣ በፍርሃትና በአክብሮት ይመለከቱታል።


5. የጋራ ማህበረሰባዊ ጫና

 ምዕመናንም ወይም ተከታዮችም ቢሆኑ አገልጋዮቻቸውን እንደ ልዩ ፍጡር የመመልከት አዝማሚያ አላቸው። አገልጋዩ ይህንን የሕዝብ ፍላጎትና መስፈርት ለማሟላት ሲል በሌለው ማንነቱ ለመታየት ይገደዳል። ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦች ለሐሰተኛው አድናቆት ሲሉ የሚያወጡት መሥዋዕትነት እጅግ ከፍተኛ ነው፦


·        የሥነ-ልቦና ውጥረት፦ እውነተኛ ማንነታቸውና በሰው ፊት የሚያሳዩት «ሐሰተኛ ማንነት» ሲጋጭ በውስጣቸው ከፍተኛ ጭንቀት፣ ፍርሃትና የሕሊና ወቀሳ ይፈጠራል። ወቃሽ ተገኝቶ «እንዴት እንደዚህ ይደረጋል?» ከተባሉ ደግሞ ወጥተው ይቅርታ እስከ መጠየቅ ይደርሳሉ።

 

·        የማያቋርጥ ስጋት፦ «ሐሰቴ ተንኮሌ ታውቆብኝ ውርደት እንዳይደርስብኝ» በሚል የማያቋርጥ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ይኖራሉ።

 

ይህንን መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግር ለመቅረፍ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ደረጃዎችና መፍትሔዎች ይመክራሉ፦

 

1.   እውነተኛ የራስ ግንዛቤን ማሳደግ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ሌሎችን የሚያስተምር አገልጋይ ራሱንም እንዲያስተምር እውነተኛውን የራስ ግንዛቤ ማሳደግ ይኖርበታል። ግለሰቡ ምንም እንኳን አገልጋይ ቢሆንም ሰው መሆኑን፣ ድክመትና ጉድለት እንዳለው፣ ፍጹም አለመሆኑን አምኖ መቀበል አለበት። እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በሰዎች አድናቆት ሳይሆን በራስ እውነተኛ ማንነት መኖር ሲቻል ነው።

 

2.     የሙያ ሕክምና ማግኘት፦ በተለይም የናርሲሲዝም፣ የውስጥ ባዶነት ወይም የታችኝነት ስሜት ያሉባቸው ከሆነ ከሙያተኛ ጋር በመነጋገር የችግሩን ሥር መፍታት አለባቸው። የሥነ-ልቦና ምክር አገልግሎት (Psychotherapy & Counseling) ሊያገኙ ይገባል።

 

3.   የምዕመናን ማስተዋል፦ ምዕመናንም አገልጋዮች እንደ እኛ ሰዎች መሆናቸውን መርሳት የለባቸውም። አገልጋዮችን እንደ ማኅበረሰብ አባላትና እንደ ተራ ሰዎች እንጂ እንደ ፍጹም ወይም እንከን-የለሽ አድርጎ አለመመልከት ያስፈልጋል። «በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ» የሚለውን መመሪያ መሠረት በማድረግ፣ ሰዎች በሚደሰኩሩት ወሬ፣ በቃላት አጋኖ፣ በተጋነነ ታሪክና «ዋጋ ከፈልኩ» በሚል ጉራ ሳይሆን፣ የሚኖሩትን እውነተኛና ትሁት ሕይወት ማስተዋል ያስፈልጋል።

 

4.     ዋናውን ማንነት ማወቅ፦ የሰው ልጅ ዋና ማንነቱና ዋጋው በሚገዛቸውና በሚጠቀማቸው ነገሮች ሳይሆን፣ በክርስቶስ የተሰጠው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሆነ በጥብቅ መረዳት ይገባል።

 

ይህንን መንፈሳዊ ውድቀት ለመግታት ዋናው መፍትሄ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስቀመጠው ግልጽና የማያወላውል መለኮታዊ መስፈርት ነው። ጌታችን «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ»  ( ማቴ. !6፡Ý@4) በማለት እንደደነገገው፣ እውነተኛ ወንጌላዊነት የሚጀምረው ራስን ከመካድ እና ስለ እውነት ብሎ የሚመጣውን መከራ ታግሦ የመስቀሉን መንገድ ከመከተል ነው።


 ምርጡ የክርስቶስ ዕቃ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ምዕመናን ሲጽፍ «ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና» (2ኛ ቆሮ. 4፡5) እንዳለው፣ የሐዋርያት አሰረ-ፍኖት ራስን፣ ዝናንና ገጽታን ማስተዋወቅ ሳይሆን ተሰቅሎ ያዳነውን ክርስቶስን ብቻ ማሳየት ነበር። አገልጋይ ራሱን በምዕመናን ልብ ሰሌዳ ላይ እንደ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ለማሳየት ሲታገል፣ የወንጌሉ እውነት ይሸፈናል፤ የአገልግሎቱም መንፈሳዊ ኃይል ይመክናል።


በመሆኑም፣ ጌታችን «ከሰው ክብርን አልቀበልም» (ዮሐ. 5:$1) በማለት ያስተማረውን መለኮታዊ መመሪያ አጽንቶ መያዝ የዚህ ዘመን ትልቅ የቤት ሥራ ነው። በገንዘብና በቁሳዊ ድጋፍ ሰጪዎች ፍላጎት የሚዘወር፣ እውነትን ደብቆ ባለሀብቶችን ደስ ለማሰኘት የሚሮጥና በሥነ-ልቦናዊ ናርሲሲዝም (Spiritual Narcissistic) በትዕቢት በታይታ የተወጠረ አገልግሎት ከክርስትና እውነተኛ ባሕሪ ጋር ይጋጫል። ስለሆነም አገልጋዮችም ሆኑ ምዕመናን ከዚህ የሸማችነትና የከንቱ ዝና ማሳደድ አዙሪት ወጥተው፣ ወደ ጥንታዊው የሐዋርያት፣ የሰማዕታትና የባሕታውያን ቅን፣ ትሁት እና መስቀሉን የሚሸከም እውነተኛ የወንጌል አገልግሎት ሊመለሱ ይገባል።

ይቆየን

ያዕቆብ ሰንደቁ ተጻፈ መስከረም 21 2019 ዓ/ም 

አዲስ አበባ

 ✍️ የእርስዎስ ምልከታ ምንድን ነው? በዘመናችን የአገልግሎት አቀራረብ እና በ«ገበያ መር ክርስትና» ዙሪያ ያለዎትን ሀሳብ ወይም አስተያየት ከታች በኮመንት (Comment) ሳጥን ውስጥ ያካፍሉን።

የቴሌቪዥን ወንጌላዊው ጂም ባከር (Jim Bakker)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 1
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 2
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 3
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 4

የሳምንቱ የመፅሐፍ ቂዱስ ጥቅስ

"በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም መንገድህን ያቀናልሃል።" ምሳሌ 3፡5-6

Video