የቀራንዮው ጥሪና የማራናታ ፍፃሜ
ምዕራፍ አምስት
የቀራንዮ ውሎ እና የዐቢይ ጾም ትጋት
ለሜሪ በሳምንቱ ቀናት መካከል ዕለተ ዓርብ ልዩ ቦታና ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አላት። ይህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አዳም ልጆች የኃጢአት መሠረዝ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተበት ማሕያዊት ቀን ናት። በመሆኑም ከዓመት እስከ ዓመት ባለችበት ቦታ ሁሉ ሆና ይህችን ልዩ ቀን በጾምና በጸሎት ታስባታለች። በዕለቱ በቀን አንዴ ቁራሽ ዳቦ ብቻ በመቅመስና ውሃ በመጠጣት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ በጎ ነገር በማድረግ እንዲሁም "ድርሳነ ማሕያውያዊ" የተባለውን የጸሎት መጽሐፍ በማንበብ ታሳልፈዋለች። በየሳምንቱ ዓርብ የክርስቶስን ጥልቅ ፍቅር አብዝታ የምታስተውለው ሜሪ፣ በተለይ ዕለቱ ከመድኃኔዓለም ወርሃዊ በዓል ጋር ሲገጣጠም አከባበሯ ይበልጥ የተለየና መንፈሳዊ ድምቀት ያለው ይሆናል።
ከኢትዮጵያ እረፍቷ ተመልሳ ሁለት ወራት ከተቆጠሩ በኋላ፣ ታላቁ የዐቢይ ጾም መቃረብ ለሜሪ ታላቅ ደስታንና መንፈሳዊ ጉጉትን ፈጠረላት። በሙያዋ ከፍርድ ቤት ጋር የተያያዘ የሕግ ሥራ
ስለምትሠራ፣ በሁለቱ የጾም ወራት የሥራ ጫና እንዳይኖርባትና ትኩረቷ እንዳይበታተን
በማሰብ በእጇ ያሉትን መዛግብትና ጉዳዮች በቅድሚያ ቶሎ ቶሎ በመጨረስ በትጋት ተሰናዳች። አላማዋ ታላቁን የዐቢይ ጾም በግሏም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ በታላቅ የመንፈስ ዝግጅት የተቀደሰ አድርጋ መቀበል ነበር።
ጾሙ ከመግባቱ ከሁለት ቀን በፊት፣ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ተሰብስበው ጾሙን እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው ከወትሮው የተለየ ጠንከር ያለ ውይይት አደረጉ። ሜሪ ለቤተሰቧ በሰጠችው ማብራሪያ፣ ዐቢይ ጾምን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደምታደርገው
ቁራሽ ዳቦና ውሃ ብቻ እየተመገበች
በስግደትና በጸሎት ለማሳለፍ ማሰቧን ነገረቻቸው። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ቆይታዋ የሰማችውን የሱባኤ አያያዝ፣ በተለይም ከተቻላት የጸጥታና የእረፍት ሰዓት የሚሰጠውን "የአርምሞ ሱባኤ" ለመግባት፣ ካልሆነ ደግሞ መላውን የጾም ወቅት እጅግ በተረጋጋ መንፈስና በጸሎት ለማሳለፍ መወሰኗን አሳወቀች።
ባለቤቷ ዶክተር ታዴዎስ ግን ነገሩን ሲሰማ ጥቂት ቆጣ ብሎ፣ "አንቺ መቼም አንዳንዴ በራስሽ ወስነሽ መጥተሽ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበሽ 'አጽድቁልኝ' ትያለሽ!" ሲል ተናገረ። በመቀጠልም በሞቀ ስሜት፣ "ዐቢይ ጾምን ሙሉ በሙሉ በዳቦና በውሃ ብቻ እጾማለሁ ማለት አይቻልም፤ ተቀባይነትም
የለውም። አንድ ሰው በቂ ምግብ ሳያገኝ እንዴት በዓለም ያለውን ውጣ
ውረድና የሥራ ጫና ተቋቁሞ ይውላል? ይህን እንድታደርጊ እኔ
ፈጽሞ አልፈቅድም። እንዲያውም እስከ ስድስት ሰዓት ጾመሽ ቢሮ
ከጓደኞችሽ ጋር
ምሳሽን መብላት አለብሽ። በሳምንት በሳምንቱ የምትጾሚውን
የዓርብ ጾም
እንኳን መተው አለብሽ፤ በዓመት አንዴ በስቅለት ዕለት ብትጾሚ ይበቃሻል። ጌታ እኮ የተሰቀለው አንዴ ነው!" በማለት የራሱን ማሳመኛ አቀረበ።
ሜሪ ግን
በረጋና በአክብሮት በተሞላ አንደበት፣ "አባቶቻችን የረቡዕ እና የዓርብን ጾም
የሠሩልን ሕማማቱን እንድናስብበት
ነው፤ እኛ
በዘልማድ ስለምንጾመው እንጂ ረቡዕ የታሰረበት፣ ዓርብ ደግሞ የተሰቀለበት ቀን መሆኑን ለማስታወስ ነው። እኔ በዚህ ዐቢይ ጾም
ሱባኤ መግባት የፈለግኩት ከምወደው አምላኬ ጋር በግል የምነጋገረው ጥልቅ ነገር ስላለኝ ነው" በማለት የልቧን መንፈሳዊ ጥማት ገለጸችለት።
በዐቢይ ጾም
መግቢያ ዕለት—በዘወረደ—ቤተሰቡ በሙሉ ከቅዳሴ መልስ ተሰብስቦ ሳለ፣ ማርቆስ የበገናውን አውታሮች እያጠባበቀ የእናቱን ፈቃድ ለመጠየቅ በማሰብ፣ "እኔ ማታ ማታ ከጓደኞቼ ጋር
በገና የመደርደርና የመለማመድ ፕሮግራም አለኝ" አለ። ማራናታ በበኩሏ፣ "እኔ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ስለምጾም ከትምህርት ቤት ስመለስ በ10
ሰዓት አካባቢ ነው ምግብ የምበላው፤ ስለዚህ እንድታውቁት ነው"
አለች። ሜሪም፣ "እኔም ያው ከዚህ ቀደም እንደነገርኳችሁ አምላኬ ካበረታኝ ዳቦና ውሃ ብቻ በመመገብ ለመጾም ነው
ያሰብኩት" ስትል ገለጸች። ዶክተር ታዴዎስም የቤተሰቡን መንፈሳዊ ቁርጠኝነት አይቶ በተሸናፊነት
ስሜት፣ "እንግዲህ እንደ እናንተ ባይሆንም እኔም እጾማለሁ፤ በምችለው ሁሉ
ደግሞ አግዛችኋለሁ" ሲል አሳቡን ለወጠ።
የዘንድሮው ዐቢይ ጾም ከዘወረደ ወደ
ቅድስት፣ ከቅድስት ወደ ምኩራብ እያለ ቀናቱ ወደ ሳምንታት ተቀይረው ጊዜው ነጎደ። ሜሪ ሁለተኛውን ሳምንት አጠናቅቃ ሦስተኛውን ሳምንት ጀምራለች። የምትጾመው በታላቅ ዓላማ ነበር፤ እርሱም ስለ
ሰው ልጅ
ፍቅር ሲል
በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለው እውነተኛው የበጎች እረኛ መድኃኔዓለምን ለማግኘት ነው። ማታ ማታ ቁራሽ ዳቦ
እየቀመሰች፣ ላቧ
ጠብ እስኪል ድረስ በትጋት ትሰግዳለች። መዝሙረ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምንና ድርሳነ መድኃኔዓለምን ታነባለች። ጸሎቷን ስታጠናቅቅም እንደ ማሳረጊያ፡ "ማራናታ! ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ወደ እኔ ና! ቶሎ ና! የተወጋው ጎንህ፣ የቆሰሉት እጆችህ፣ የእሾህ አክሊል የጎነጎነው ራስህ አሳየኝ፤ እግዚአብሔር
ሆይ እወድሃለሁ ክብርህን ግለጥልኝ!" እያለች እያነባች ትጸልያለች።
ከደብረ ዘይት እኩለ ጾም በኋላ ያለው ጊዜ
ግን ለሜሪ እጅግ ከባድ ፈተና ሆነባት። በጠንካራው ጾም
ምክንያት ሰውነቷ እጅግ ከሳ፤ በሥራ ቦታዋ የምትወጣውና የምትወርደው ውጣ ውረድ አቅሟን አሳጣት፣ ጉልበቷም መንቀጥቀጥ ጀመረ። የሚያገኛት ሀበሻ ሁሉ "ምነው እንዲህ ከሳሽ? ምነው ገረጣሽ?" እያለ ለሚያቀርብላት ጥያቄ ማብራሪያ መስጠት ሰለቻት። ቅዳሜና እሁድ የሥራ ውጥረት ባይኖርባትም፣ በሰንበት ቀናት ዳቦና ውሃ
ብቻ መመገብ ሌላው ትልቅ ፈተና ሆነባት። የቀረው የቤተሰቧ ክፍል እንጀራ በሽሮና በየዓይነቱ ሲመገብ እርሷ ግን ጨው እንኳን የሌለው ውኃ
ውኃ የሚል ዳቦ በውኃ ተነክሮ ነበር የምትበላው። ይህ
ሁሉ የሚሆነው ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ነበር፤ ግን ሥጋዊ ፍላጎቷን መቋቋም ታጋፍታ የማታልፈው ጽኑ
አለት ሆኖባት ፊቷ ላይ ተጋረጠባት።
ይህን ፈተና ለማለፍ አቅም የሚሆናት ደግማ ደጋግማ የምትሰማው የዘማሪ ይልማ ኃይሉ መዝሙር ነበር፡
እግዚአብሔር ሆይ እወድሃለሁ፣ ስለስምህ እቃጠላለሁ፤
ዲያብሎስ የሜሪን ትጋትና ሱባኤ ለማሰናከል ብዙ ዓይነት የፈተና እጆቹን ይዘረጋል። አንዳንዴ በዘመድና በጓደኛ አድሮ፣ "ሰውነትሽ ተጎዳ እኮ!
ትታመሚያለሽ፣ በሕይወት አትቆይም ትሞቻለሽ፤ ጾሙን አቋርጠሽ ብትበይ ይሻልሻል" ይላታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ የሐሳብ ማዕበል እያመጣ፣ "ምን ያደክምሻል? እግዚአብሔር እንደሆነ አይመለከትሽም፤
ለምን ብለሽ ነው እንደዚህ የምትራቢው? መብላትና መጠጣት እኮ
ኃጢአት አይደለም!" እያለ ተስፋ ለማስቆረጥ ይሞክራል።
በሆሳዕና ዕለት ሜሪ ከፍተኛ በሌሊት ቤተ ክርስቲያን ብትሄድም ጉልበቷ መቆም አቅቶት ብርክ ብርክ አላት፤ እንደምንም ቅዳሴውን አጠናቃ በቀጥታ ወደ ቤቷ በመሄድ ተኛች። በዚህ በዓቢይ ጾም
በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የነበራት መንፈሳዊ ጥንካሬ እየላላ መጣ። በጾሙ አገኘዋለሁ ብላ የምታስበው ፀጋና በረከት በሙሉ የማታገኘው ከንቱ ድካም ሆኖ ተሰማት። "በመለኮታዊ ክብሩ የሚገለጠውን
የቀራንዮውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን በክብረ መንግሥቱ አየዋለሁ" የሚለው ተስፋዋ እየተሟጠጠ መጣ። "ማራናታ! ጌታ
ሆይ ቶሎ
ና!" የሚለው ቃል
ትርጉም ያጣበት መሰላት። "ጌታ ሆይ ተገለጥልኝ፣ ቶሎ
ና" ብላ ብትማጸንም፣
እንኳን ሰማያዊው በረከት፣ ሕልም እንኳን ሳታይ ቀረች፤ እንዲሁ እንደተራበችና
እንደጸለየች የሚመጣባትን የዲያብሎስ ውጊያ በመንፈስ እየመከተች ቆየች። የዘገየው የጸሎቷ መልስ ባለመገኘቱ ልቧ በሐዘን ተከፋ።
በሰሙነ ሕማማት ሳምንት በልጇ በማርቆስ የበገና ዝማሬ እየተጽናናች ዕለተ ዓርብ ደረሰች። ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ እንኳን ጉልበት አጥታ የዛለ ሰውነት የነበራት ሜሪ፣ በዕለተ ስቅለት ወደ
ቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ስትገባ የሚያበረታታና የሚያነቃቃ መንፈስ ቅዱስ በላይዋ ላይ ሲያርፍ ተሰማት። ተርቦና ጎስቁሎ የነበረው ሰውነቷ ድንቅ ጥካሴና ኃይልን አገኘ። ከንጋቱ ጀምሮ በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት እና በዘጠኝ ሰዓት ያሉትን የስግደት ሰዓታት በታላቅና በሚያስገርም
ኃይል ትሰግዳለች፤ ወዟም ወደ ምድር ጠብ ጠብ ይላል።
ጌታችን ሲታሰር፣ ለፍርድ ሲቀርብ፣ ሲንገላታ፣ ምራቅ ሲተፋበት፣ ሲቸነከርና በመስቀል ላይ
ሲሰቀል የሚሰማውን ሕማም እያሰበች ማሕያዊ የሆነ ሕማም በነፍሷ ተሰማት፤ የቅርብ ዘመድ እንደሞተበት
ሰው ከልብ የሆነ ጥልቅ ሐዘን አንጀቷን ያላውሰዋል። የዓርብን የስቅለት በዓል በዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ተመስጦ አክብራ፣ ቅዳሜን በከፍተኛ የድካም እረፍት አሳልፋ፣ እሁድ ታላቁን የትንሣኤ በዓል በታላቅ ደስታና ድል አድራጊነት ለማክበር በቃች።
ምዕራፍ ስድስት
የተሰማው ድምፅ እና የሱባኤው ተስፋ
ከ አንድ
ዓመት በኃላ የነነዌ ጾምን ለሦስት ቀናት የጾመችውን ጾምና ጸሎት እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ በማቆየት በቅዳሜ ለመፈሰክ አቅዳ ነበር። ዓርብ በለመደችው የጾም ሥርዓት ቁራሽ ዳቦና ውሃ በመብላት ጾመች። ቤተ ክርስቲያን ገብታ ጸሎት እያደረገች በሐሳቧ ባለፈው ዓመት በዐቢይ ጾም ካላት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ የጌታችንና የመድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበለውን
መከራ ማየት ፈልጋ፣ በዘመነ ሰማዕታት እንደነበሩ ክርስቲያኖች "ማራናታ - ጌታችን ሆይ፣ ና" እያለች የእርሱን መገለጥ አጥብቃ ትመኛለች። በሥጋ ከሳች፣ ገረጣች፣ ከቤተሰቧና ከዘመድ አዝማድ ሸሸች። የሰውን ጥያቄ፣ ሐሜትና ነቀፌታ ችላ ብላ ይህን ሁሉ
ዋጋ የከፈለችበት ሱባኤ ዕርባናቢስ፣ ፍሬ
የሌለው ዛፍ
መሰላት።
ለራሷ እንዲህ ትለው ጀመር፡ "እግዚአብሔር ቢረሳኝ ባያስታውሰኝ ነው እንጂ ይህ ሁሉ ተማፅኖና ጩኸት ከንቱ ቀረ። ከእንግዲህ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ዋጋ አልከፍልም፤ እንደ ማንኛውም ክርስቲያን እስከ 9 ሰዓት ከጾምኩ ይበቃኛል። በምግብ እጦት የደረሰብኝ ፈተና ገና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው። ከደመና በታች ለሚቀረው ጸሎቴ የቅዱሳንን ያህል ካለ አቅሜ ለምን እጋደላለሁ?" ብላ
ታማርራለች።
በዚያ ቅጽበት ግን ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ፍቅርና ርኅራኄ የተሞላበት ድምፅ ይሰማት ጀመር።
"የእኔ ልጅ፣ አይዞሽ አትፍሪ፤ ተስፋ አትቁረጪ!"
"ለእኔ ብለሽ ያቀረብሽውን የፍቅር መሥዋዕት አይቼዋለሁ፤ ጸሎትሽን ሰምቻለሁ። በዐቢይ ጾም የደከምሽውን ድካም በከንቱ የምያስቀርብሽ አይደለም፤ የኃጢአት መደምሰሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መወረሻ አደርግልሻለሁ። የዘንድሮውን የዓቢይ ጾም ከባለፈው ዓመት አስበልጠሽ ጹሚ፤ አብዝተሽ ለጽድቅ ተጋደዪ፤ የልብሽን መሻት እፈጽምልሻለሁ። ክብሬን፣ ማሕያዊ የምትሆን ሕማሜን፣ የቆሰሉትን እጆቼን፣ የተወጋውን ጎኔን፣ የተገረፈውን ጀርባዬን አሳይሻለሁ። በሕማሜ ለመታመም፣ በፍቅሬም የአዳምን ልጆች ለመውደዴ የፈጸምኩትን ሁሉ አይተሽ ትገረሚያለሽ" የሚል ድምፅ። ከዚያም ሌላ ድምፅ፡ "ንዜኑ ሞተከ ወትንሣኤከ ቅድስት..." የሚል የቅዳሴ ድምፅ ተሰማ።
ምዕራፍ ሰባት
የቀራንዮው ራዕይ እና የቅዳሴው ምሥጢር
ዘወረደ—የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት። የጾሙን የመጀመሪያ ቅዳሴ ለማስቀደስ ሜሪ በቤተ መቅደስ ተገኝታለች። ኪዳን መድረስ ሲጀምር እና "ቅዱስ እግዚአብሔር..." ብለው ካህናቱ ሲያመሰግኑ፣ ሜሪ ልዩ ደስ የሚያሰኝ የእጣን መዓዛ ይሸታታል። "ዕጣን በዚህ ሰዓት አልታጠነም፤ ከየት የመጣ ነው?" እያለች እያሰበች ሳለ፣ ከቤተ ክርስቲያኑ ጥግ በወንዶች በኩል ያለውን የመድኃኔዓለም ሥዕል መልካቸው እንደ ፀሐይ የሚያበራ አረጋዊ ካህን ሲያጥኑት ተመለከተች። ባየችው ነገር ተገርማ እግዚአብሔርን እያመሰገነች ቅዳሴዋን አስቀድሳ፣ "በሰላም ወደ ቤታችሁ ግቡ" ሲባል ወደ ቤቷ ሄደች።
"የዘንድሮው የዐቢይ ጾም የበረከት ጾም ነው። ወደ እኛ ቤተሰብ፣ ወደ
እኛ ሕይወት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በረድኤት ይመጣል። የጌታችን ወደ እኛ መምጣት ቶሎ
እንዲሆን 'ማራናታ' እንበለው!" በጥንት በዘመነ ሰማዕታት ወደ ጌታ ክብር ሰማዕትነትን ተቀብለው ለመሄድ እንደሚናፍቁ፣ እንዲሁ እነርሱም በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሊተጉ ተስማምተው በቤተሰብ ደረጃ የጸሎትና የመንፈሳዊ ትጋት ፕሮግራም ጀመሩ።
ሜሪ በመጀመሪያዎቹ የዐቢይ ጾም ሳምንታት—ዘወረደና ቅድስት—ስትጾም ሰውነቷ ብርቱ ነበር። የምትመገበው ዳቦና ውኃ ብቻ፣ እርሱም በቀን አንድ ጊዜ
በመሆኑ ከባድ ነበር። "ሥጋ ደካማ ነው፣ መንፈስ ግን ተዘጋጅቷል" እንደሚባለው ነፍሷ መንፈሳዊነትን
ብትፈልግም፣ ደካማ ሥጋዋ ግን የላመና የጣመ መብላትን ይ ይመኛል። ከደብረ ዘይት በኋላ ባለው አንድ ዓርብ ቀን
ገና ከቀን ጀምሮ ሰውነቷ ዛለ። "በቃ! ሰውነቴ ደከመ፤ በዘንድሮው የዐቢይ ጾም
ብዙ በረከት ታገኛለሽ ተብሎ ቃል
ቢገባልኝም እስከ አሁን ያገኘሁት ነገር የለም" እያለች ታማርራለች።
ራቡ
ጸናባት፤ በተለይ አንደበቷ ደርቆ ውኃ
እያለች ተቸገረች፤ ጨው ወይም በርበሬ ያለው ነገር መብላት አሰበች። ሰዓቱ ማታ
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሆነ። የተለመደውን ዳቦ በውኃ ለመብላት ብላ ተነሳች፤ እንደገና አመነታች። "መራብ አይበቃኝም? ያገኘሁትን ብበላስ?" እያለች ተወዛገበች። ወደ መኛታዋ ለመሄድ ተነሳች ግን ወደ እግሯ ወደ ጸሎት ቤት አመራት ። የሚያበረታታና የሚያጠነክር መለኮታዊ ድምፅ ይሰማታል፡ "ጌታችን በገዳመ
ቆሮንጦስ ከጾመና ከጸለየ በኋላ ተራበ ይል የለምን? እንዴት አንቺ ግን 'ለምን ተራብኩ'
ብለሽ ታማርሪያለሽ?" አላት።
ሜሪ ከዚህ የሚያበረታቻ
መልእክት ከደረሳት በኋላ፣ ከደብረ ዘይት ሰንበት በኋላ ያለውን የጾም ወቅት በተለየ ሁኔታ መጾም ጀመረች። ያ የተልፈሰፈሰው ሥጋዋ ኃይል እንዳገኘ ሆኖ
ጠነከረ። በላብ እስክትዘፈቅ
ድረስ ትሰግዳለች፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ታነባለች፤ በእንባና በንሥሐ ፈጣሪዋን ይቅርታ ትጠይቃለች። አብዛኛውን ሰዓት በጽሞና ሆና
ቤተ ክርስቲያን ታሳልፋለች።
"የለመኑትን የማይነሳ ጌታ የውስጤን መንፈሳዊ ራብ ያሞላልኛል፤ የናፈቅኩትንና የምፈልገውን
አምላኬን አገኘዋለሁ" ብላ ትናፍቃለች። "ማራናታ! ጌታ
ሆይ ና!"
እያለች የዘወትር ጸሎቷን ታቀርባለች።
በዕለተ ሰንበት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ እያስቀደሰች፣
የቁርባኑ ምስጋና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ነበር። በዚያች ቀን ቅዳሴው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሰማይ የተከፈተ ያህል ሆነ። የሚቀድሱት ካህን ንባቡን ሲያነቡ፣ ሜሪ እኔም ከእነርሱ ጋር
በራዕይ ተሰጥቼ ወደ ዕለተ ዓርብ ቀራንዮ ወጣሁ።
ሕማሙን፣ ቁስሉን፣ ከለሜዳ መልበሱን፤ አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቸንካር ሲቸነከሩ፣ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቸንካር ሲቸነከሩ፣ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መጣጣን ሲጠጣ በግልጽ ተመለከትኩ።
የፍቅር የጌታ ሕማማት ባየሁ ጊዜ
ልቤ ደነገጠ፣ ሕሊናዬም ተመታ፣ ነፍሴም ተንቀጠቀጠች፣
ሥጋዬም ደከመ። ምን አንደበት ይገልጸዋል? ምን ከንፈር ይናገረዋል? መከራውን መናገር የሚችል ምንም አፍ የለም!
እርሱም እንደተማፀንኩት፡ "እነሆ ልጄ፣
ተመልከቺ! ስለ ሰው ልጅ የተቀበልኩት መከራ ይህ ነው" ብሎ
የመስቀሉን መከራና ሕማሙን አሳየኝ። የሚያይ ዓይን፣ የሚቆም ጉልበት አልነበረኝም።
ይ.ካ. የተሰበሰብን እኛም የማይታመመው የእርሱን ሕማሙን እንናገራለን፤ የማይሞተው የእርሱን ሞቱን እንናገራለን፤ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተቀመጠበት በዚያች ሌሊት በአባቱ ፈቃድ በራሱም ፈቃድ ሰውነቱን ለሞት ሰጠ፤
ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሰሩት፤ የሕያው የአምላክን ልጅ አሰሩት፤ በቁጣ ጐተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው፤ በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር
እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤
ሊቃነ መላእክት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በፊቱ የሚቆሙለትን
በአደባባይ አቆሙት፤ ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጣእ አሉት፤ መኳንንትን በሚፈርደው በእርሱ ፈረዱበት፤
ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጁአቸውን
የእሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የግርማ ልብስ የሚያለብሱአቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤


.jpeg)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ