ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

በእጅ የተያዘ የወርቅ መስቀል በብርሃን ያጌጡ መስቀሎች እና ምእመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የክብር መስቀሎች የቤተክርስቲያን በዓል አከባበር
አዲስ ገጽ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

ገጹን ይመልከቱ →

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ክፍል 8

 

የሚያደቅ ብረት አራተኛው የሮም መንግስት

 

 

"የኪቲም መርከቦች ይመጡበታል"  ዳንኤል 11:30

«የኪቲም መርከቦች ይመጡበታል» (ዳንኤል 11:30) የሚለው ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ የሮምን ኃይል ብቅ ማለት እና የዓለምን ታሪክ አቅጣጫ መቀየር በግልጽ ከሚያሳዩን ትንቢቶች አንዱ ነው። በነቢዩ ዳንኤል ትንቢት «ብረቱ መንግሥት» ተብሎ የተገለጸው የሮም ኃይል መነሳት፣ በወቅቱ በነበሩት ታላላቅ ግዛቶች መካከል በተደረገ አስከፊ የደም መፋሰስና የሥልጣን ትግል የታጀበ ነው።

ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት የሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ የነበረው ዓለም በአንድ ግዙፍ የማዕበል ለውጥ ውስጥ ሲያልፍ፣ የሮም ሪፐብሊክ የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካና የሕግ ሥርዓት ከምሥራቁ የግሪክ ባህል ጋር አዋህዶ ዓለምን የሚጨፈልቅና የሚያደቅ ግዙፍ የብረት መንግስት ሆኖ ብቅ አለ።

በመጽሐፍ ቅዱስ (በተለይም በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 11) «የሰሜኑ ንጉሥ» እና «የደቡቡ ንጉሥ» ተብሎ የተጠቀሰው ከታላቁ እስክንድር ሞት በኋላ ግዛቱ በተከፋፈለበት ወቅት የተነሱትን ተቀናቃኞች ናቸው፡፡ የደቡቡ ንጉሥ ማለትም የግብፅ ላይ ተቀምጦ የነበረውንና በቶለሚ (Ptolemy) የተመሠረተውን ሥርወ-መንግሥት ሲሆን የሰሜኑ ንጉሥ ደግሞ በሶርያና በሜሶጴታሚያ አካባቢ ተቀምጦ የነበረውንና በሰሉከስ (Seleucus) የተመሠረተውን ታላቁን የሰሉከስ መንግሥት ይወክላል።

መቅዶንዮስና ትሬስ በጥንታዊቷ ግሪክ በባልካን ደሴት ይገኙ የነበሩ ኃያላን ግዛቶች ናቸው፡፡ መቅዶንዮስ በታላቁ እስክንድር አባት በንጉሥ ፊሊፕ ሁለተኛ የተገነባችና መላውን ግሪክ አስተባብራ የነበረች መንግሥት ናት፡፡ ትሬስ ደግሞ ከመቅዶንዮስ በስተምስራቅ (በአሁኗ ቡልጋሪያ፣ ሰሜን ግሪክና ቱርክ አካባቢ) ይኖሩ የነበሩ የጦረኛ ጎሳዎች ሀገር ነበረች።

መቅዶንዮስ ከሮም ጋር ባደረገችው ተከታታይ የ"መቅዶንዮስ ጦርነቶች" (Macedonian Wars) ተሸንፋ በ168 ዓ.ዓ. በፒድና ጦርነት (Battle of Pydna) ድል በመመታቷና በ148 ዓ.ዓ. ሙሉ በሙሉ የሮም ግዛት  በመሆኗ  እነዚህ ግዛቶች በሮም እጅ ሊወድቁ ቻሉት፡፡

ጎረቤቷ ትሬስ ደግሞ በመቅዶንዮስ መውደቅ ምክንያት መከላከያ በማጣቷና በሮም የውስጥ ፖለቲካዊ ሴራና ወታደራዊ ግፊት እየተዳከመች ቆይታ በመጨረሻ በ46 እ.ኤ.አ. በንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ (Claudius) ዘመን ሙሉ በሙሉ ተጠቅልላ በሮም ቁጥጥር ሥር ውላለች።

ታሪኩ ሲጀምር በመርከብ የተመሰሉት ሮማውያን ከምዕራብ ብቅ ብለው መቅዶንዮስንና ትሬስን አንድ በአንድ ወደ ግዛታቸው ወደ መጠቅለል ይገቡ ጀመር። በመቀጠልም፣ ለብዙ ዘመናት እርስ በርሳቸው ሲፋለሙ የነበሩት «የሰሜኑ እና የደቡቡ ነገሥታት» የሮማን ኃይል መቋቋም አቅቷቸው ተረኛ ተጠቅላይ እንዲሆነ አደረጋቸው፡፡

 የሰሜኑ የሰሉከስ መንግሥት በታላቁ አንቲኦከስ (Antiochus III) ዘመን በሮማውያን እጅ በታላቁ የማግኔስያ ጦርነት (Battle of Magnesia) ክፉኛ ስለተሸነፈና በድል አድራጊዎቹ ሮማውያን በተጣለበት የአፓሜዳ የሰላም ስምምነት (Treaty of Apamea) መሠረት ግዛቱን ከቶሮስ ተራሮች ምዕራብ እንዲለቅ በመገደዱ እንዲሁም ግዙፍ የጦር ማካካሻ እንዲከፍል በመወሰኑ ምክንያት መንግስቱ በቀውስ ውስጥ ወደቀ።

በዕዳ ክፍያ ምክንያት በ63 ዓ.ዓ. በሮማው ጄነራል ፖምፒ እጅ ሙሉ በሙሉ ወደቀ። ይህ ክስተት ትንቢተ ዳንኤል 11:30 ላይ «የኪቲም መርከቦች ይመጡበታል» እንደሚለው፣ የሮማውያን የኪቲም ኃይል በግሪክ ነገሥታት ላይ የነበረውን የበላይነትና አጽንቶ የግሪክ መንግሥት በመክሰም ደብዛው መጥፋቱን የሚያሳይ ግልጽ የታሪክ ምዕራፍ ሆነ።

በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ “ኪቲም” የሚለው ቃል በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክተው ቆጵሮስ ደሴት ላይ የሚገኘውን ጥንታዊውን የከተማ መንግሥት ቢሆንም፣ በዘመናት ሂደት ውስጥ ትርጉሙ እየሰፋ ሄዶ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ሥልጣናቸውን እያሰፉ የመጡትን የምዕራብ ኃያላን ለመግለጽ ውሏል።

የካቲት 15 (ማርች 15) ቀን 44 ዓ.ዓ. የሮም ሪፐብሊክ ዋና ገዥና ጄኔራል የነበረው ጁሊየስ ቄሳር፣ ፍጹማዊ ሥልጣን በመያዙና የሪፐብሊኩን ሥርዓት አደጋ ላይ ጥሏል በሚል ስጋት በብሩተስ እና ካሲየስ በሚመሩት የሴኔት አባላት ሴራ በፖምፔ ቲያትር አቅራቢያ በሚገኘው የሴኔት መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተከቦ በካራ ተወግቶ በግፍ የተገደለ፡፡ ይህንን ክስተት የሮምን ፖለቲካዊ መልክ ቀየረ፣ የሪፐብሊኩን ማብቂያ እና የርስበርስ ጦርነት መባቻ አበሰረ፡፡

የሮም ዋና ገዥ ጁሊየስ ቄሳር በሴኔት አባላት እጅ በግፍ መገደሉ በሮም ታላቅ መንቀጥቀጥንና የሥልጣን ክፍተትን ፈጠረ። ቄሳር መገደሉ ሮምን ነፃ ያወጣታል ተብሎ ቢታሰብም፣ ሕዝቡ ግን ቄሳርን እንደ አባት ይወደው ስለነበር በሴራው ላይ በከፍተኛ ቁጣ ተነሣ።

የቄሳር የቅርብ ጓደኛ ማርክ አንቶኒ እና የ19 ዓመቱ ወጣት ኦክታቪያን የቄሳርን ገዳዮች (ብሩቱስ እና ካሲየስን) ለመበቀል አብረው ተሠለፉ። ከሌላ ጄኔራል ከሌፒዱስ ጋር በመሆን «ሁለተኛው ሦስትዮሽ ሥልጣን» የሚባል ጣምራ ገዥ አካል አቋቋሙ፤ በግሪክ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው የፊሊፒ ሜዳ ላይ ባደረጉት ኃይለኛ ወታደራዊ ዘመቻ ገዳዮቹን ድል አደረጉ።

ከድሉ በኋላ የሮም ግዛት በሦስቱ ሰዎች መካከል ተከፋፈለች፤ ሌፒዱስ አፍሪካን፣ አንቶኒ ሀብታሟን ምሥራቅ ግዛት ግብፅን ጨምሮ፣ እና ኦክታቪያን ምዕራቡን ግዛት ተረከቡ። ጊዜው ሲረዝም ሌፒዱስ ከሥልጣን ተገለለ፤ ኃይሉም በማርክ አንቶኒ እና በኦክታቪያን እጅ ብቻ ተወሰነ። ነገር ግን ሮም ለአንድ ሰው ብቻ የምትመጥን ግዙፍ ግዛት ነበረችና ሁለቱ በፍጹም ሊስማሙ አልቻሉም።

ኦክታቪያን በሮም ሆኖ ሕግንና ሥርዓትን የሚያስከብር ቀዝቃዛ ፖለቲከኛ ሲሆን፣ ማርክ አንቶኒ ግን በምሥራቅ ከግብፅ ንግሥት ከክሊዎፓትራ ጋር በፍቅር ወድቆ የሮምን ባሕርይ እየተወ የግብፅን ንጉሣዊ ሥርዓት ማዘውተር ጀመረ።

ክፍል ዘጠኝ ይቀጥላል፡፡

 ህዳር 2019 ዓ/ም

አዲስ አበባ  

 

«ከታላቁ እስክንድር ሞት በኋላ ሲፋለሙ የነበሩት የቀድሞ ኃያላን መንግሥታት (የሰሜኑና የደቡቡ ንጉሥ) በመጨረሻ በሮም ብረት ኃይል እንደተበጣጠሱ ሁሉ፤ ታሪክ ሁልጊዜም አንዱን አውርዶ ሌላውን በሰገነት ላይ ያወጣዋል። ከዚህ ታሪክ አንፃር የሰው ልጆች የሥልጣን ትግል መጨረሻው ምን ይመስላችኋል? ሐሳባችሁን አጋሩን!»

"አንባቢያን፦ ከዚህ ታሪክ ምን ተማራችሁ? በሐሳባችሁ  በአስተያየት መስጫው ላይ አጋሩ !"

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ክፍል 9

የክሊዎፓትራ እና የማርክ አንቶኒ ፍቅር

 የግብፅ የቶለሚ ሥርወ-መንግሥት የመጨረሻዋ ንግሥት ክሊዎፓትራ (7ኛ)፣ ኃያላንን በፊቷ የማንበርከክ ምስጢር የነበራት ጥበበኛ መሪ ነበረች። የክሊዎፓትራ እና የሮም መሪዎች ግንኙነት የተጀመረው ግብፅን ከሮም የጦር ወረራና ፍጹማዊ የበላይነት ለመታደግ በተደረገ ስልታዊ የፖለቲካ ትግል ሲሆን፤ -----

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 1
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 2
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 3
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 4

Video

>