ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ

ማዕዶት የያዕቆብ ሰንደቁ የጡመራ ገጽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና የአንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰባኪ እና መምህር የሆነው የያዕቆብ ሰንደቁ መንፈሳዊ ትምህርቶች እና ወጎች የሚፃፉበት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የጡመራ ገጽ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ወደ መልካም ሥነምግባር እንዲመለሱ ማስተማር ነው፡፡ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ፡፡” ትንቢተ ዳንኤል 12÷3

በእጅ የተያዘ የወርቅ መስቀል በብርሃን ያጌጡ መስቀሎች እና ምእመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የክብር መስቀሎች የቤተክርስቲያን በዓል አከባበር
አዲስ ገጽ

አንቀጸ ወራዙት/ወጣቶች/-"የቢራ ጎርፍ"

ገጹን ይመልከቱ →

ስብከት፡- የሥውራን ደቀመዛሙርት አዲስ መቃብር ::


የሥውራን ደቀመዛሙርት አዲስ መቃብር::

 ዮሐ.19:41

@ በ ያዕቆብ ሰንደቁ 



ፀሐይ ፈርታ በጨለመችበት፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተሰንጥቆ መሠረቱ በተናወጠበት፣ ደቀ መዛሙርቱ  በፈራ መንፈስ በየጓዳው ተበትነው ቀራንዮን ጭር ባደረጉበት ያቺ ዕለተ ዓርብ ማምሻ፤ የሰው ልጅ ታሪክን የለወጠ አንድ ታላቅና አስደናቂ ገድል ተፈጸመ።

በአራቱም ወንጌላውያን ማለትም በማቴዎስ 27፥57-61፣ በማርቆስ 15፥42-47፣ በሉቃስ 23፥50-56 እና በዮሐንስ 19፥38-42 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው፤ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ከመስቀል ወርዶ በአዲስ መቃብር መቀበሩ የቤተ ክርስቲያናችን የድል አክሊል ነው። ወንጌላውያኑ የአርማትያስ ዮሴፍን በግንባር ቀደምትነት ሲጠቅሱ፤ የጲላጦስን ፈቃድ መጠየቁን፣ ሥጋው በጥሩ የተልባ እግር ጨርቅ መገነዙን፣ ሰንበት ከመግባቱ በፊት በፍጥነት በአዲስ መቃብር ማረፉን እና ሴቶች በቦታው መገኘታቸውን በአንድ ልብ ጽፈውታል።

ወንጌላዊያኑ የጻፈላቸውን ማኅበረሰብ እና አውድ ታሳቢ በማድረግ የየራሳቸው መለያ ጭብጥ አስቀምጠዋል። ቅዱስ ማቴዎስ፦ ዮሴፍ «ሀብታም» እንደነበረና መቃብሩም «የራሱ አዲስ መቃብር» መሆኑን በማጉላት፣ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር።» (ኢሳይያስ 53፥9) ብሎ የተናገረው የብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጹም መፈጸሙን ለአይሁድ አንባቢዎቹ አሳይቷል።

ቅዱስ ማርቆስ በበኩሉ፦ ዮሴፍ «የከበረ አማካሪ» እንደነበረና ጲላጦስም ከመቶ አለቃው የሞቱን እውነተኛነት በጦር መወጋቱንና ደም ከጎኑ መፍሰሱን አረጋግጦ ፈቃድ መስጠቱን በመግለጽ፣ ለሮማውያን አንባቢዎች ታሪካዊና ሕጋዊ ማረጋገጫ ይሰጣል።

ቅዱስ ሉቃስ፦ ዮሴፍ «ደግና ጻድቅ» ሰው መሆኑን፣ በጌታ ላይ በተደረገው የክፉዎች ምክር ፈጽሞ ያልተባበረና በሐሳባቸው የልብ ስምምነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ የክርስቶስን ፍጹም ንጹሕነትና የደጋግ ሰዎችን ጽኑ ምላሽ ያጎላል።

ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ፦ «ኒቆዲሞስ» መቶ ንጥር ውድ ሽቱ ይዞ መምጣቱንና ቀብሩ «በአትክልት ስፍራ» መፈጸሙን በማካተት፣ ለክርስቶስ የተሰጠውን ታላቅ ንጉሣዊ አክብሮትና ጥልቅ ምስጢር በሰፊው ያቀርባል። የአራቱ ወንጌላውያን ልዩነቶች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ሳይሆኑ፣ ይልቅስ አንዱ የሌላውን ክፍተት እየሞላ የጌታችንን ቀብር በስዕላዊ ትዕይንት ሙሉ በሙሉ እንድናየው የሚያደርጉ ድንቅ ምስክሮች ናቸው።

በወቅቱ ይሁዳን ያስተዳድር የነበረው ጴንጤናዊው ጲላጦስ፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት ፍርድ የሚገባው ጥፋት እንዳላገኘበት ያውቃል። የሕዝብን ሁከትና የካህናትን ጫና በመፍራት ብቻ አሳልፎ በመስጠቱ ተጸጽቶ «ከዚህ ደም ንጹህ ነኝ» በማለት እጁን የታጠበ መስፍን ነው። በመስቀል ላይ የሚሰቀሉ ሰዎች ለመሞት ቀናት ስለሚፈጅባቸው፣ የጌታችን መሞት ሲነገረው በቀላሉ ማመን አቅቶት፤ የሮሙን መቶ አለቃውን ጠርቶ አረጋገጠ። በመቶ አለቃውም ጐኑ በጦር ተወግቶ ደምና ውሃ መፍሰሱን ሲሰማ ለአርማትያሱ ዮሴፍ ሥጋውን እንዲሰጥ ፈቀደለት፡፡

  

 የአርማትያስ ዮሴፍ ጽኑ ፍቅርና ድፍረት

የአርማትያስ ሰው የተባለው ዮሴፍ በይሁዳ ግዛት ውስጥ ከኢየሩሳሌም ውጭ በምትገኝ በትንቯ አርማትያ ከተማ በመኖሩ «የአርማትያስ ዮሴፍ» ተባለ። እርሱ ባለጸጋና የአይሁድ ከፍተኛ ምክር ቤት የሳንሄድሪን አባል ነው። በጌታችን ትምህርትና ኃይል በልቡ ያመነ፣ ትምህርቱንም በስውር የተከታተለ «የስውር ደቀ መዝሙር» ነው።

የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን በጌታ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ቢያውቅም፣ ከማኅበራዊ ደረጃውና ከምክር ቤት አባልነቱ ይሰርዙኛል በሚል ፍርሃት፤ እምነቱን በግልጽ መናገር ሳይችል፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት በጸጥታ ሲጠባበቅ ኖረ። ነገር ግን የሸንጎው አባላት ጌታን ለመስቀል በወሰኑበት ክፉ ውሳኔ ፈጽሞ አልተባበረም፤ ሐሳባቸውንም አልተቀበለም።

የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን የሚያውቅ፣ የመሲሑን መምጣት ያመነ ደግና ጻድቅ ሰው ዮሴፍ የሚመጣበትን ሁሉ ፈተና ለመቀበል ራሱን አዘጋጅቶ በድፍረት ቆመ። ወንጌላዊው ማርቆስ ሁኔታውን በማድነቅ «ደፍሮ ወደ ጲላጦስ ገባ እና የጌታን ሥጋ ለመነ »ይለናል፡፡ የክርስቶስን ትምህርትና ተአምራት ሲመለከት «የእግዚአብሔር መንግሥት» በክርስቶስ በኩል እንደመጣች ስላመነ፣ በልቡ የጌታ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ የእምነቱን ፍሬ ፍቅሩን በዕለተ ዓርብ በአደባባይ ሳይፈራ መሰከረ።

በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ አደባባይ የሆነው ክስተት ነፍስን ከሥጋ የሚለይ አስጨናቂ መከራ ነበር። ከንጋት እስከ አሥራ አንድ ሰዓት፤ መስቀል ከመሸከም እስከ ልብስ መገፈፍ ፤ የደረሰ የሚያስፈራ የመከራ ቀን። የመድኃኔ ዓለም የጀርባው ግርፋት፣ የእጆቹን መቸንከር ያየው ሕዝብ ሁሉ ፈርቶ ቀራንዮን ሰው አልባ አደረገው። ከእመቤታችንና ከዮሐንስ ወዳጁ በቀር ከመስቀሉ ሥር ማንም አልነበረም።

ከወንበዴዎች ጋር የተሰቀለውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓምስት ገበያ ሕዝብ የእጁን ተዓምራት አይቷል፡፡ በሆሳዕና ዕለት አሁን አድነን ብለው ከተማውን በጩኽት ያንቀጠቀጡ ተከታዮች ነበሩት፡፡ በ ዕለተ ዓርብ ሕዝቡ ሁሉ ፈርቶ ቀራንዮን ሰው አልባ ከተማ አድርገው ጭር አደረጉት፡፡ የዳነው የመቶ አለቃው ልጅ ፣ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የነበረው እና የተፈወሰው ሰው በዚች ዕለት “አድኖኛል ውለታው አለብኝ ” ብለው አጠገቡ አልተገኙም፡፡

 ዕለተ ዓርብ ለአዳም የመዳን ቀን ብትሆንም ለብዙዎች የፍርሀት ቆፈን አጨማዳ የያዘቻት አስጨናቂ ቀን ሆናባቸው ነበር። በመጨረሻው ሰዓት ሥጋውን በርቀት ከሚመለከቱ ከአይሁድ ጭፍሮች በቀር ማንም አልነበረም፡፡ ከመስቀል ላይ የእጆቹን ችንካር የሚያነሳ ፤የተወጋ ጐኑን የሚሸፍን ማንም ወዳጅ አልተገኘም፡፡ የእሾ አክሊሉን ከራሱ ላይ የሚነቅል ፤ የብርሃን እግሮቹን ከችንካር የሚያላቅቅ ሰው አልነበረም፡፡ ሁሉም በፈራባት ድንግዝግዝ ጨለማ የእግዚአብሔር መንግስት እንደተገለጠች፤ ብርሃን እንደመጣ የተረዳ አንድ ጻድቅ ሰው የአርማትያሱ ዮሴፍ ብቻ ነው፡፡ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ የለመነ። ነገር ግን በዚያ ድንግዝግዝ ጨለማና ፍርሃት ውስጥ ዮሴፍ «ክብሬ፣ ማዕረጌ ይቅርብኝ!» ብሎ እንደ ችቦ አበራ።

በሮማውያን ሕግ መሠረት በመስቀል ላይ የተሰቀለ ሰው ከሞተ በኋላ ሥጋው መስቀል ላይ ማደር አልነበረበትም፤ ማመልከቻ በማስገባት ሥጋውን ለመውሰድ ፈቃድ የማግኘት ልማድ አለ። በዚህም ልማድ ዮሴፍ «ደፍሮ ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነ። » (ማር. 15፥43)  ከወንበዴዎች ጋር ተሰቅሎ የሞተውን ጌታ ሥጋ መለመን «የወንጀለኛ ደጋፊ» ያስብል ነበር፤ ነገር ግን ጻድቁ ዮሴፍ ይህንን ሁሉ ፈተና ለመቀበል ራሱን አዘጋጅቶ በድፍረት ቆመ።

 "የአርማትያሱ ሰው ዮሴፍ በስውር የነበረውን ደቀመዝሙርነት ወደ አደባባይ በማውጣት በመንፈሳዊ ሕይወት ማደጉን አስመሰከረ፡፡ በፍርሀት እና በይሉንታ የተያዘውን እምነቱን በጭንቅ ቀን ራሱን አሳልፎ በመሰጠት ፍጽምናውን አሳየ ጸድቅና በጎ ሰው ተባለ፡፡"

 በማግስቱ ቅዳሜ ታላቁ የፋሲካ ሰንበት ስለሚገባ፣ በሙሴ ሕግ መሠረት አስክሬን በዕለቱ መሬት ውስጥ መግባት አለበት እንጂ በሰንበት ተሰቅሎ ማደር የለበትም። (ዘዳግም 21፥22-23) እውነተኛው የፋሲካ በግ ክርስቶስ ዓርብ ተሰቅሎና ተገንዞ በመቃብር በማደሩ፣ የብሉይ ኪዳን ሰንበትን በሥጋው አሳረፋት፤ እሁድ ጠዋት ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ትንሣኤን አበሰረ። ዓለም በኃጢአት ጨልማ «በመሸችበት» እና የብሉይ ኪዳን ዘመን በሚያበቃበት ፍጻሜ ላይ፣ እውነተኛው የፋሲካ በግ በመስቀል ላይ ተሰውቶ የዓለምን በብርሃን መላ መዳንንም አበሰረ።

የአርማትያሱ ሰው ዮሴፍ በስውር የነበረውን ደቀመዝሙርነት ወደ አደባባይ በማውጣት ፤በመንፈሳዊ ሕይወት ማደጉን አስመሰከረ፡፡ በፍርሀት እና በይሉንታ የተያዘውን እምነቱን በጭንቅ ቀን ራሱን አሳልፎ በመስጠት ፍጽምናውን አሳየ፡፡ “ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት አይደለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።” 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡2፡18 ብሎ ወንጌላዊው በመልዕክቱ እንጸጻፈው የመድኃኒታችን ፍቅር ፍርሀቱን አስወገደለት፡፡

በወቅቱ በነበረው ሥርዓት ወንጀለኞች ወይም በጣም ድሆች ሲሞቱ የክብር መቃብር አያገኙም። በጅምላ መቃብር ወይም የውርደት ቦታዎች ይጣላሉ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ወንጀለኛ ቢቆጠርም፣ ሲሞት ግን በአርማንቴው ዮሴፍ «አዲስ እና የራሱ በሆነ ውድ መቃብር» ማረፉ በሀብታም መቃብር ተቀበረ፡፡ አስቀድሞ “ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር።”ኢሳይያስ 53፥9 በዚህም ምክንያት «ከሀብታሞች ጋር» ተቀበረ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡

ዮሴፍ የጌታን ሥጋ አክብሮ ለመቅበር እንደ ትልቅ ስጦታና ዕድል ቆጥሮት በትህትና አገለገለ። በባለጸግነቱ ወቅት ለራሱ የገዛውን አዲሱንና ውዱን መቃብር «ክስ ይመጣብኛል፣ ለራሴ ያዘጋጀሁት ነው» የሚል ምክንያት ሳይደረድር፣ የክርስቶስን ሥጋ ለማሳረፍ በስጦታ ሰጠ። የጌታችን ውለታና ፍቅር ስለገባው ከዚህ የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ ተገለጸለት፡፡ ለጌታዬ ለአምላኬ የምሰጠው ሥጦታ ካለማ ብሎ በጭንቅ ቀን በደስታ አዲሱን መቃብር ሰጠ፡፡

 

ዮሴፍ ሆይ! እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ 

በዓርብ ምሽት በቀራንዮ አደባባይ የእጆቹን ችንካር እንዴት አላቀከው? የእግሮቹን ሚስማር በምን እጅ አነሳህው? በጦር የተወጋውን ደምና ውሃ ያፈለቀውን ቅዱስ ጎን እንዴት በጨርቅ ሸፈንከው? ለ እኛ ሲል የተገረፈውን የጀርባውን ሰንበር በምን ዐይንህ አየኸው?  ሥጋውን አውርደህ በጥሩ የተልባ እግር ጨርቅ ስትጠቀልለው የ ሕማሙ  መጠን እንዴት ቻልከው ? በምን ክንድ ተሸከምከው? ደግነትና ጽድቅ ይህን ሁሉ አስችሎህ ይሆን?

 

 ዮሴፍ ሆይ!

ዓለምን በእጁ የያዘውን አምላክ ያን ጊዜ በበፍታ ጨርቅ ስትጠቀልለው ምን ዓይነት ታላቅ ርኅራኄና ጥልቅ ፍቅር ነበረህ?


ዮሴፍ ሆይ !

ጌታህን እንዴት ብትወደው ነው በአካለ ሥጋ የለም ተሰቅሎ ሞቷል ሳትል የራስህን የዕረፍት ቦታ፣ ያዘጋጀኸውን አዲስ መቃብር አሳልፈህ የሰጠኸው? ይህ ምን ዓይነት ጽኑ ፍቅር ነው? ዓለም ሲሸሽ አንተ በድፍረት የቆምክበት ፤ ለባለጸግነት ያልሰሰተ ቆራጥነትና መንፈሳዊነት ከየት መጣ? እስኪ ለእኛ ለደካሞቹ ንገረን፤ ጸልይልንም፡ ከምትወደው ጌታ ለምንልን፡፡ ዛሬ ለእርሱ የሚሆን አዲስ መቃብር እንዴት ማዘጋጀት ይቻለን ይሆን? የዚህን ዓለም ጩኸትና ኃጢአት አስወግደን ንጹሕና አዲስ ማደሪያ ለጌታ ጠብቆ ማቆየት የሚቻለውስ እንዴት ይሆን ?  እንዴት እንደ አንተ በጎና ጻድቅ መሆን እንችል ይሆን ? የአንተን ያህል ፍቅር እና የቆራጥነት እንድናገኝ ሥጋችንን በሚያስፈራ ክፉ ቀን በእውነት መቆም እንድንችል ጸልይልን ፡፡

 የኒቆዲሞስ መንፈሳዊ ዕድገትና የከርቤ ስጦታ

 ከአርማትያስ ዮሴፍ ጎን ደግሞ የሌሊቱ ተማሪ የኒቆዲሞስ ታሪክ በደማቅ ሁኔታ ይፃፋል። የኒቆዲሞስ ሕይወት የእምነት ዕድገትና የጽናት ፍጹም ማሳያ ነው። ቅዱስ ወንጌል የእርሱን መንፈሳዊ ጉዞ በሦስት የተያያዙ ምዕራፎች ከፍሎ ያቀርበዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በዮሐንስ ምዕራፍ 3 ላይ እንደምንመለከተው፣ ኒቆዲሞስ የነበረበትን ማኅበራዊ ክብርና ሥልጣን በመፍራት ከጌታችንን ለመማር የሚሄደው በሌሊት ነበር። ጥያቄ እያቀረበ፣ በዚያን ጊዜ ጌታን በልቡ ሙሉ በሙሉ ባለማመኑ በስውር ይከተለው ነበር።

የእምነቱ አድማስ እያሰፋ ሲመጣ ግን ሁለተኛው ምዕራፍ ተከፈተ። በዮሐንስ ምዕራፍ 7 ላይ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላትና ፈሪሳውያን በኢየሱስ ላይ መከራ ለማድረስና ለማስያዝ ሎሌዎችን በላኩ ጊዜ ኒቆዲሞስ በድፍረት ተነሣ። «በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሳይሰማ፣ ጥፋቱ በምስክሮች ሳይረጋገጥና የራስ መከላከያ ሳይሰጠው በጅምላ አይፈረድበትም» በማለት ሕጋዊና ፍትሐዊ ጥያቄ አቀረበ። ፈሪሳውያንን በራሳቸው ሕግ ገሠጻቸው፤ መምህሩንም ከፍትሕ አልባ ፍርድ ታደገ። በወቅቱ ሎሌዎቹም፦ «እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም» ብለው መመለሳቸው ይታወሰል።

በሦስተኛው ምዕራፍ ኒቆዲሞስ ወደ ፍጹማን ደረጃ ተሸጋገረ። በዮሐንስ ምዕራፍ 19 እንደተመዘገበው፣ በዕለተ ዓርብ ፍጹም ድፍረትን ተጎናጸፈ። «ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? » ዮሐ.7፡48 የሚለውን የፈሪሳውያን ኩራተኛ አባባል በድርጊቱ አፈረሰው። ቀደም ሲል በስውር ይከተለው ከነበረው ፍርሃት ወጥቶ፣ በሞቱ ሰዓት ላለበት ጥልቅ ፍቅር፣ አክብሮትና ንሥሓ መግለጫ ይሆን ዘንድ ሀብቱን ሳይሰስት እጅግ ውድ የሆነ ቅመም አቀረበ።

 በጌታችን ስቅለት ዕለት ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። «መቶ ንጥር» በሚዛን ሲሰላ ወደ 33 ኪሎ ግራም የሚጠጋ ሲሆን፣ እጅግ በጣም ውድና ከፍተኛ መጠን ያለው የሽቱ ዓይነት ነው። በአይሁድ ባህል እንዲህ ያለው ከፍተኛ መጠን ውድ ቅመም ጥቅም ላይ የሚውለው ለታላላቅ ነገሥታት አስከሬን አገናነዝ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ አሳ በእንዲህ መልኩ መገነዙ ተጽፎልናል። “ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላ አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።” (2ኛ ዜና 16:14)  ኒቆዲሞስ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከወንበዴዎች ጋር ተሰቅሎ ቢሞትም፣ እርሱ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን አምኖ እንደ ንጉሥ አከበረው።

 ኒቆዲሞስ ሆይ ! እስኪ እንጠይቅህ ?

በሌሊት በጥያቄና በፍርሃት የጀመርከውን ጉዞ፣ እንዴት ከጥርጣሬ ወደ ጽኑ እምነት አሸጋገረከው? በሊቃነ ካህናቱና በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመህ "ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማው... ይፈርዳልን?" በማለት እንዴት በድፍረት ተከራከርካቸው?

ኒቆዲሞስ ሆይ!

በሌሊት በስውር የጀመርከውን ክርስትና፣ በቀራንዮ አመሻሽ ላይ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ መቶ ንጥር የሚመዝን ከርቤና ሬት ይዘህ በግልጽ እስከመቆም እንዴት አደረሰኸው? ለእኛ ለደካሞቹ ንገረን፤ ለሥልጣን፣ ለዝና፣ ለክብር ለሀብት ሳይሳቀቁ በጲላጦስና በጠላቶች ፊት በድፍረት መቆም እንዴት ይቻላል?

 

ኒቆዲሞስ ሆይ፣ እስኪ እንጠይቅህ!

ከባልንጀራህ ከዮሴፍ ጋር ሆናችሁ ያን የከበረ ሥጋ ከመስቀል ላይ ስታወርዱት፣ የቆሰለውን አካሉን፤ በውድ ከርቤና በሬት ስትገንዙት፤ በውስጣችሁ ምን ተሰማችሁ? ዓለምን ሁሉ በእጁ የያዘው አምላክ ፤እንደ ልደቱ በጨርቅ መጠቅለሉን አስበህ ፤ዛሬ ደግሞ በበፍታ ጨርቅ ሲጠቀለል፣ በዚያ በአዲስ መቃብር ውስጥ ሲቀበር ምን አላችሁ? ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሳ፣ በመቃብርም እንደማይቀር ያን ጊዜ በምን ዐይነት መንፈሳዊ ዐይን አያችሁት?

 

ኒቆዲሞስ ሆይ!

ጸልይልን እስኪ እንደ አንተ ፍቅሩ እንዲገባን እርሱ ለእኛ እንደታመመ እኛ ደግም እንዳንተ ውድ ዋጋ ሳይሆን ጥቂት ንጥር መልካም ሥራ ይዘን እንድንቀርብ፡፡ እስኪ ለእኛ እምነታችን ላነሰብን፣ በጥርጣሬ ለተዋጥንና በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ለተሳነን ኒቆዲሞስ ሆይ ንገረን፤ ከፍርሃት ወጥተን ወደ ፍጹም ፍቅርና ወደ ጽናት ማደግ የሚቻለው እንዴት ይሆን ? ያንተን ያህል ድፍረት ፍጹም ፍቅር ተላብሶ በብርሃን መመላለስ  እስኪ አስተምረን።

 

የመቃብሩ ምስጢር፣ የትንሣኤው ብርሃን

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሆይ የጌታን ቅዱስ ሥጋ በከርቤና በእሬት አሽታችሁ በንጹህ የበፍታ ጨርቅ ጠቀለላችሁ። ይህ ድርጊታቸው ጥልቅ መንፈሳዊ ምስጢር ነበረው። ከርቤ የመራራ ሞትና የዕፎይታ ምሳሌ ሲሆን፣ አስክሬን እንዳይበሰብስ ይጠብቃል። «ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወው» (መዝ. 16፥10) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል። ይህም የጌታ ሥጋ በመቃብር አድሮ ሳለ መበስበስን እንደማያይ ያመለክታል።

ሬት ደግሞ ከበፍታው ጨርቅ ጋር ተጣብቆ አካሉን የሚጠብቅ፣ የመፈወስ ባሕርይ ያለውና መልካም መዓዛ የሚሰጥ ነው። ጌታችን የተጠቀለለበት የበፍታ ጨርቅም ሌላ ታላቅ ምስጢር አለው።  በብሉይ ኪዳን የበፍታ ጨርቅ የሊቃነ ካህናት ልብስ እንደመሆኑ መጠን፣ ክርስቶስ እውነተኛው ሊቀ ካህናት መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

የቀብሩ ስፍራም የአዳምን መታደስ ያበስራል። የመጀመሪያው አዳም ኃጢአት የሠራውና ሞት ወደ ዓለም የገባው በገነት ወይም በአትክልት ስፍራ ውስጥ ነበር። ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ ደግሞ ሞትን ሽሮ ፤የትንሣኤን ሕይወት የሰጠን ፤በአትክልት ስፍራ ባለው አዲስ መቃብር ውስጥ ነው።

ዮሴፍ አርማማታዊው በአትክልቱ ቦታ ያዘጋጀው አዲስ መቃብር ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለማሳረፍ ተዘጋጅቶ ነበር፤ አስቀድሞ ይህን አዲስ መቃብር ማዘጋጀቱ ጌታውን በክብር ገንዞ ለማስቀመጥ አብቅቶታል። ይህ መቃብር «ማንም ፈጽሞ ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር መሆኑ» ሁለት ታላላቅ መንፈሳዊ ምስጢራትን ይይዛል፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ነቢዩ ኤልሳዕ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ፣ እስራኤላውያን በሞዓብ ወራሪዎች አደጋ ተደናግጠው ፤ አንድን የሞተ ሰው በችኮላ በኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ የሞተውም ሰው የኤልሳዕን አጥንት ሲነካ ሕያው ሆኖ ተነሥቶ ነበር (2ኛ ነገሥት 13:20-21)። ታዲያ ይህን ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች “ኢየሱስ ክርስቶስም ከሙታን የተነሣው እንደ ኤልሳዕ አጥንት ነክቶ ነው” ብለው የተሳሳተ ትርጉም እንዳይሰጡ (የትንሣኤውን መለኮታዊ ኃይል ከሌላ አካል ጋር እንዳያያይዙ) ጌታችን ያረፈው ማንም ባልተቀበረበት፣ ንጹሕ በሆነ አዲስ መቃብር ውስጥ ነው። ይህ የሚያሳየው ክርስቶስ በራሱ መለኮታዊ ኃይል ከሙታን መነሣቱን ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን፤ ያለ ወንድ ዘር እንደተወለደ ሁሉ፣ ከሞት ሲነሣም ማንም ባላረከሰው፣ ማንም ባልተቀበረበት በድንግል መቃብር ተቀብሮ ተነሥቷል። ይህም የልደቱን ንጽህና ከመቃብሩ ጋር የሚያስተሳስር ድንቅ ምሥጢር ነው።

 ምድራዊ ሕይወቱን በፍጹም ትህትና የጀመረው የፍጥረት ሁሉ ባለቤት፤ ወደዚህች ዓለም ሲመጣ የዓለምን ግርማና ጌጥ አልመረጠም። በቤተልሔም በእንግዳ ዋሻና በግርግም መወለዱ ለሰው ልጅ ያደረገውን የፍቅር  ጉዞ ያሳያል። የነገረ-መለኮት ሊቃውንት እንደሚተነትኑት፣ ጻድቁ ዮሴፍ ንጽሕት እናቱን እንደጠበቀ ሁሉ፣ ዮሴፍ አርማማታዊውም የጌታን ሥጋ ማንም ፈጽሞ ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር መርጦ ማረፊያ አድርጎለታል። ይህ ድንቅ መጣጣም ክርስቶስ በእንግዳ ዋሻ ተወልዶ በእንግዳ መቃብር መቀበሩን፣ በግልጽ ያሳያል።

የክርስቶስ አካል በክብር መገነዙና በመቃብር ውስጥ ማረፉ የእርሱን እውነተኛ ሰው መሆን እና እውነተኛ ሞት የሚያረጋግጥ ሐቅ ነው። እርሱ በእውነት ሞተ፣ በእውነት ተገነዘ፣ በእውነትም ተቀበረ፤ በመጨረሻም፣ ምንም እንኳ በሥጋ ተገንዞ በመቃብር ቢቀበርም፣ ሞትና መቃብር አሸንፈው ሊይዙት አልቻሉም። የሰው ልጅ የድኅነት ተስፋ የሆነው አምላክ በመቃብር ውስጥ ሳይቀር በራሱ መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ከድንግል ማኅጸን እስከ ድንግል መቃብር ድረስ የዘለቀው ይህ መለኮታዊ ታሪክ፣ የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት፣ ፍጹም ሰውነት እና የትንሣኤውን የማይናወጥ እውነት በደማቅ ሁኔታ ለዓለም ይመሰክራል።

ደቀ መዛሙርቱ በሰቀቀንና በፍርሃት ተበታትነው በነበሩበት የጨለማ ሰዓት፣ እስከዚያው ድረስ በስውር ይከተሉት የነበሩት ጀግኖች ፊት ለፊት ወጡ። ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚመሰክረው፤ በችግርና በመከራ ሰዓት የተደበቁት እነዚህ ሰዎች፣ የጌታን ሥጋ ለመለመን ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ ጲላጦስ በድፍረት ቀረቡ። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የጌታን ሥጋ በልመና አግኝተው በክብር እንዳሳረፉት ሁሉ፣ እኛም ዛሬ በጸሎት ተለምነንና ተጸጽተን የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ልንቀበል ይገባናል። 

 እነርሱ የተቀበሉትን የጌታን ሥጋ ያኖሩት ማንም ባልተቀበረበት አዲስ መቃብር ውስጥ እንደነበረ ሁሉ፣ እኛም የክርስቶስን ሥጋና ደም ስንቀበል በሕይወታችን በአዲስ ማንነት፣ በዕንባ ንሥሓ እና በይቅር ባይነት ሊሆን ይገባል።

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ በቤተልሔም የሚያድርበት የእንግዶች ማደሪያ ሥፍራ አላገኘም ነበር፤ በዕለተ ዓርብም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ሥጋውን የሚያወርድ፣ የሚገንዝና የሚቀብር የቅርብ ዘመድ አልነበረውም። ነገር ግን በዚያች የበደልና የፍርሃት ሰዓት ኒቆዲሞስና ዮሴፍ በድፍረት ቀርበው፤ የጌታን እርቃን በክብር ሸፈኑ፤ በባለጸጋው የአትክልት ሥፍራ በሚገኘው አዲስ መቃብርም አሳረፉት። ዛሬም ቢሆን እንደ ኒቆዲሞስና ዮሴፍ የጌታን እርቃን ሸፍነን ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ማግኘት ለምንፈልግ አማኞች፣ በየመንገዱና በየጎዳናው ለወደቁት የተቸገሩ ወገኖች ማልበስና መመገብ ቀጥታ ለራሱ ለክርስቶስ እንደ ማድረግ ይቆጠራል።

 ታላቁ የቤተክርስቲያን አባትና የዜማ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በስበከቶቹና በድርሳናቱ (በተለይም በጾም ድርሳኑ / Homily on the Fast እና በመዝሙራቱ / Hymns on Faith and Charity ላይ) እንደሚያስተምረው፡ ክርስቶስን ከተቸገሩትና ዕርቃናቸውን ከደቁ ሰዎች ጋር አንድ አድርጓል። ቅዱስ ኤፍሬም እንደሚያስረዳው፤ «በየመንገዱ ዕርቃኑን የቀረውንና የቆረፈደውን ወንድምህን /እህትህን ስታለብሰው፣ የቀራንዮውን ክርስቶስ አልብሰሃል፤ ለተራበው ስትመግብም ራሱን ክርስቶስን መግበሃል» በማለት የመጽሐፍ ቅዱሱን የትምህርት መሠረት (ማቴዎስ 25:35-40) በማብራራት ይናገራል።

 ስለሆነም ኒቆዲሞስና ዮሴፍ በዕለተ ዓርብ ያደረጉት የበጎ አድራጎት ሥራ፤ ታሪክ ብቻ ሆኖ ሊቀር አይገባውም። ዛሬም ቢሆን በዙሪያችን የሚገኙ የተቸገሩ፣ የሚለብሱት ያጡና የተራቡ ወገኖቻችንን ስንረዳ፣ የክርስቶስን እርቃን የመሸፈን ያህል ታላቅ መንፈሳዊ በረከትንና ዋጋን እናገኛለን።

ጌታችን፦ «እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ» (ዮሐ. 13፥34) በማለት የፍቅርን ሰንሰለት ለአማኞች አበርክቷል። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን መሰረት አድርጎ፦ «እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው» (ሮሜ 12፥1) በማለት ለአማኞች ሁሉ ጥሪ አቅርቧል። የዮሴፍና የኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ የተከናወነው መስዋዕትነት እና አገልግሎት ታዲያ ለዚህ መለኮታዊ ቃል ፍጹም ሕያው ምሳሌና ለአእምሮ የሚመች እውነተኛ መንፈሳዊ አገልግሎት ነበረ።

 

የዕለተ ዓርብ ምሽት በሰቀቀን፣ በድንጋጤና በከፍተኛ ፍርሃት የታጀበ የጨለማ ሰዓት ነው፤ የመምህራቸው መያዝ ያስደነገጣቸው ደቀ መዛሙርት ሁሉ ተበትነውና ሸሽተው ተደብቀው ነበር። ነገር ግን በዚህ በሚያስፈራና ሁሉም በሰጋበት ቅጽበት፣ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከፍርሃት እስር ነፃ የወጣ ጽኑ አቋም አሳዩ። እነርሱን ያስቀራቸውና ፊት ለፊት እንዲቆሙ ያስቻላቸው የገዛቸው፣ ዋጋ ያስከፈላቸው እና የሕይወታቸውን አቅጣጫ የወሰነው ፤ የሕሊና ዳኝነት እና የአእምሮ ነፃነት ነበር። ዓለም በጥርጣሬና በፍርሀት በተዋጠችበት ሰዓት፣ እነርሱ ግን ፍቅር ፍርሃትን እንደሚያስወግድ በተግባር አሳይተዋል።

 

ዛሬም ክርስቶስን መከተል ማለት ፈተና በጠነከረት ሁሉም ወደ ኋላ ባለበት ሰዓት፤ ከእውነት ጎን መቆም ማለት ነው። ከዮሴፍና ኒቆዲሞስ ገድል ትልቁ ትምህር፦ እውነተኛ ክርስትና በምቾት ጊዜ የሚገለጥ ሳይሆን፣ ዋጋ በሚያስከፍልበት፣ መስቀል በሚበዛበትና ሕይወት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ሰዓት የሕሊናን ድምፅ አሰምቶ መገኘት መሆኑን ይመሰክርልናል።

ዛሬም ቢሆን ያ የዕለተ ዓርብ ጽኑ አገልግሎትና መስዋዕትነት ከእርሱ ከሚያመኑት እና ከሚከተሉት ክርስቲያኖች ሁሉ ይጠበቃል፤ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል ላይ የጌታን ሥጋ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ተቀብለው፤ በአዲስ መቃብር እንዳስቀመጡት ፤ እኛም የክርስቶስን ሕያው ቃል፤ በንሥሓ በጸዳ ሕይወት ውስጥ ማሳረፍ ይገባናል።

ዮሴፍ በብዙ ዋጋ የገዛውን ያንን ውድ አዲስ መቃብር ሲያበረክት፦ «ለራሴ ያዘጋጀሁት ነው፤ ብዙ ገንዘብ አውጥቼበታለሁ፤ ነገ የይሁዳ መሪዎች ክስ ያመጡብኛል፣ ሥልጣኔንና ንብረቴን አጣለሁ» የሚል የስስትና የዓለምን ምክንያት መደርደር አልፈለገም፤ ማንም እንዳይጠቀምበትም ለራሱ አላስቀረውም። ይልቅስ በአዲስ የመንፈሳዊ ሕይወት ምዕራፍ ላይ ስለነበር፣ ለራሱ ያዘጋጀውን አዲሱን መቃብር በታላቅ ውድ ፍቅር ለጌታ አበረከተ። ነገር ግን ከዚያ ከመቃብሩ ውብ ስጦታ በፊት፣ በጲላጦስ ግቢ ፊት ለፊት በድፍረት በመቆም፤ የጌታን ሥጋ በመለመን ራሱን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሳልፎ ሰጥቶ ነበር።

 «ሕይወቱን የሚያድን ይጠብቃታል፤ ሕይወቱን በእኔ ምክንያት የሚያጣ ግን ያገኛታል» (ማቴ. 10፥39) እንዳለ፣ ራሱን ለእግዚአብሔር ፍቅር አሳልፎ የሰጠ ሰው ሁሉ፤ ሕይወቱም ሁሉምነገሩም የባለቤቱ የእግዚአብሔር ይሆናል። ክርስቲያን ሰውም፤ አካሉንና ሰውነቱን፤ በዕንባ በንሥሓ አዲስ በማድረግ ፤ ለቀራንዮው አምላክ የክብር ማደሪያነት በደስታ አሳልፎ ይሰጣል።

የዚህ ዓለም ክብር፣ የጊዜያዊ ዝናና የሹመት ሽኩቻ ለእግዚአብሔር አዲስ ነገርና ፍጹም መስዋዕትን ከማዘጋጀት ፈጽሞ ሊያቆሙን እንደማይገቡ፤ የዮሴፍና የኒቆዲሞስ ታሪክ በሰፊው ያስተምረናል። አምላካችን እግዚአብሔር ዛሬም ከሚያምኑትና ከሚከተሉት የሚሻው አዲስ ነገርን፣ ንጹሕ መሥዋዕትን እና እርሱ ብቻ ሙሉ በሙሉ የሚከብርበትን ፤ ልዩ የሕይወት ሥፍራ ነው። ንጹሐ ባሕርይ ለሆነው ለክቡር አምላካችን ማደሪያ የሚሆነው የልብ መቃብር ሥፍራ ማንም ኃጢአት ያልገባበት፣ በ ንሥሓ የታጠበ ንጹሕ መሆን አለበት፤ ንጹሕ አምላክ ክብሩን የሚመጥን የቅድስና ማደሪያን ያሻዋልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ እንደ መሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ እንዲኖር አታውቁምን?» (1ቆሮ. 3፥16) በማለት በገለጠው መሠረት፣ የክርስቲያኖች አካልና ሕይወት ዛሬም የእግዚአብሔር ሕያው ቤተ መቅደስ ነው።

 ዛሬም በአትክልቱ ሥፍራ እንደተፈጸመው፣ በምድር ላይ የጌታ ሥጋ ማደሪያ የሚሆን በማንም የዓለም ኃጢአት ያልተነካ ፤ ንጹሕ ሥፍራ ይፈለጋል። የክርስቲያኖች ሰውነት ወጪ ወራጅ የሚኖርበት፣ መጪ ሂያጁ የሚመላለስበት የርኩሰት መጫወቻ ቤት አይደለም፤ ይልቁንስ ብቸኛ አምላክ እግዚአብሔር በክብር የሚያድርበት ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነው።


 ነገር ግን ዛሬ የሰው ልጅ አካልና ሕይወት፤ በኃጢአት ርኩሰት በመቆሸሹ የተነሳ አዳፋ ሆኗል፤ ለክርስቶስ ግርማ የሚመች ማደሪያም ሳይሆን ቀርቷል። ብዙ ኃጢአት የገባበትና የወጣበት፣ በበደል የደነዘና የጨለመ ሆኗል። «እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» (1ጴጥ. 1፥16) እንዳለ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ሰውነታችን በንጽህና ሊጠበቅ ሊቀደስ ይገባል።

ዛሬ ለእግዚአብሔር የሚሆን አዲስና ንጹሕ ሥፍራ በዕንባ ንሥሓ ማዘጋጀት የግድ ይለናል። ልክ ዮሴፍ ንጽሁን አዲሱን መቃብር ለጌታ እንዳበረከተው ሁሉ፣ እኛም በታደሰና በነጻ አእምሮ፤ ጌታችንን በሕይወታችን መቃብር ውስጥ እናሳርፈው። ነቢዩ ዳዊት በጸሎቱ፦ « አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።  ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። » (መዝ. 51፥10) ብሎ እንደለመነው፣ ዛሬም የቆሰለውንና የረከሰውን ሕይወታችንን በ ንሥሓ ለማንጻት እግዚአብሔርን የምንለምንበት ሰዓት ነው።

ዛሬ የሰው ልጅ በዘመናዊ ሕይወት ውስጥ  በቴክኖሎጂ ፣ በዓለማዊ ሩጫ የተወጠረ በቁሳቁስ ግርማ የታወረው ሆኗል ። ሆኖም በዚህ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ የሰው ልብ ከውጭ ሲያብብ፤ ከውስጥ ግን በኃጢአት ርኩሰት፣ በጥርጣሬና በግዴለሽነት ቆሽቯል። ዛሬም ቢሆን አምላካችን እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ሕዝቡን ሲጠራ፡ «የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ» (ሕዝ. 18፥31) በማለት የፍቅር ጥሪውን ያቀርብልናል። ዛሬ በየዕለቱ በምናደርገው ሩጫ በበደል እየሞተ ያለውን ሕይወታችንን የሚጠራን ያው የሚወደን አምላክ ነው።

ነገር ግን የሰው ልጅ በራሱ ጉልበትና ጥረት ይህንን የደነዘዘ ሕሊናውን ማደስ አይችልም፤ ለዚህም ነው ጌታ ራሱ በገባው ቃል፡ «አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ» (ሕዝ. 36፥26-28) ብሎ ተስፋ የሰጠን። በዘመናችን በሀብትና በክፋት የደነደነውን የድንጋይ ልባችንን በጸጋው ሰብሮ፣ የሚሰማ፣ የሚራራና የሚወድ የሥጋ ልብ የሚሰጠን እርሱ ብቻ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን ሲያድር፤ በዘመኑ የጥልና የጥላቻ ሩጫ ውስጥ ሰላምን እናገኛለን፤ የሕይወታችንም መዳረሻ ወደሆነችው ሰማያዊቷ ምድር እንተላለፋለን።

እንግዲህ ዛሬ፣ በችግርና በፈተና ለተወጠረው፤ የዘመኑ ሰውነታችን እውነተኛው ዕረፍቱ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ሕይወታችንን በአዲስ ንሥሓ፣ በዕንባ ጸሎት፣ በይቅር ባይነት እና ያለፉትን ቁስሎች በሚያጠፋ እውነተኛ ፍቅር ጠራርገን የጌታ ማደሪያና የትንሣኤው ሕያው መገለጫ እናድርገው።

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ውዱን አዲሱን መቃብር ለጌታ እንዳበረከቱት ሁሉ፣ እኛም ዛሬ አዲሱን ልባችንን ለቀራንዮው አምላክ በስጦታ እናቅርብ፤ አምላካችንም በታደሰችውና በተቀደሰችው ልባችን ውስጥ ለዘላለም በሰላም ይንገሥ።

የዮሴፍን እና የኒቆዲሞስን ጸጋና በረከት የተረዳው አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ “በዚህ ምሥጢር እየተራዳኝ ከኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደ ገነዙት እንደ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ አድርገን ።” በማለት ረድኤታቸውን እና ታላቅ ማዕረጋቸውን ተመኝቷል፡፡ እኛንም ከዮሴፍ እና ኒቆዲሞ ጥቂት ረድኤታቸው ድል የማትነሳ ሃይማኖታቸውን መድኃኔ ዓለም ያድለን አሜን ።

                                                                  የመድኃኔ ዓለም ቸርነት አይለየን አሜን!

ይቆየን!

ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ/ም

አዲስ አበባ

 

 ተጨማሪ  ማንበብ ከፈለጉ ማስፈንጠሪያው ይጫኑ  ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ

  

💡 የሐሳብ ማዕድ

ውድ የብሎግ አንባቢያን! የዮሴፍና ኒቆዲሞስን ከስውርነት ወደ ድፍረት የተሸጋገረ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሁም ዛሬ በሕይወታችን ውስጥ አዲስ መቃብር (ንጹሕ ማደሪያ) ማዘጋጀት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ እንዴት ተረዱት? በእናንተ ሕይወት ውስጥ እንደ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ፍርሃትንና ይሉንታን አሸንፎ በድፍረት መቆም ያስፈለጋችሁበት ወቅት ነበረ?

 ሐሳባችሁን፣ ጥያቄዎችዎን እና አስተያየታችሁን ከታች ባለው የኮሜንት መስጫ ላይ በማስቀመጥ የበኩላችሁን መንፈሳዊ ተሳትፎ አድርጉ!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕዶት አንቀጸ ወራዙት እና የወጣቶች ተግባራዊ ክርስቲያናዊ ሕይወት

ማዕዶት፡- ወደ መንፈሳዊነት አብረን እንሻገር! "ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት  ለዘላለም ይደምቃሉ"  (ትንቢተ ዳንኤል 12÷3) በቤተክርስቲያናችን...

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መፃሕፍት

በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 1
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 2
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 3
በመምህር ያዕቆብ ሰንደቁ የተዘጋጀ መንፈሳዊ መጽሐፍ 4

Video

>